አሳሳቢ ትምህርቶች ለብዙሀኑ ህዝብ (አማርኛ)

አሳሳቢ ትምህርቶች ለብዙሀኑ ህዝብ

  • earth ቋንቋ
    (አማርኛ)
  • earth ዝግጅት፦:
    الشيخ عبد العزيز بن باز

ሌሎች ትርጉሞች 53

hi هندي- हिन्दी or أورومو- afaan oromoo ne نيبالي- नेपाली hu هنجاري مجري- magyar pl بولندي- polski sr صربي- Српски vi فيتنامي- Tiếng Việt mos موري- Mõõré wo ولوف- Wollof tg طاجيكي- тоҷикӣ dv ديفهي- ދިވެހި bs بوسني- bosanski mfe كريولي- créole mg ملاغاشي- Malagasy as آسامي- অসমীয়া ml مليالم- മലയാളം bn بنغالي- বাংলা ur أردو- اردو fr فرنسي- Français ru روسي- Русский ms ملايو- Melayu ha هوسا- Hausa en إنجليزي- English id إندونيسي- Indonesia zh صيني- 中文 sw سواحيلي- Kiswahili uz أوزبكي- Ўзбек ps بشتو- بشتو fa فارسي- فارسي tl فلبيني تجالوج- Tagalog gu غوجاراتية- ગુજરાતી te تلغو- తెలుగు ar عربي- العربية am أمهري- አማርኛ si سنهالي- සිංහල ka جورجي- ქართული da دنماركي- dansk cs تشيكي- čeština lo لاو- ພາສາລາວ prs دري- فارسی دری az أذري- azərbaycanca lt ليتواني- lietuvių lg لوغندي- Luganda aa عفري- Afaraf es إسباني- español ro روماني- română kd كردي كرمنجي- Bi zimanê Kurdî yo يوربا- Èdè Yorùbá de ألماني- Deutsch uk أوكراني- українська sv سويدي- svenska st سوتي- Sesotho zh صيني- 中文
PHPWord

 

 

 

الدُّرُوسُ المُهِمَّةُ لِعَامَّةِ الأُمَّةِ

 

 

አሳሳቢ ትምህርቶች ለብዙሀኑ ህዝብ

 

 

 

لِسَمَاحَةِ الشَّيْخِ العَلَّامَةِ

عَبْدِ العَزِيزِ بْنِ عَبْدِ اللهِ بْنِ بَازٍ

رَحِمَهُ اللهُ

 

በተከበሩ እውቁ ሸይኽ

ዐብዱልዐዚዝ ቢን ዐብደላህ ቢን ባዝ (አላህ ይዘንላቸውና)

 


بِسْمِ اللهِ الرَّحمَنِ الرَّحِيمِ

አሳሳቢ ትምህርቶች ለብዙሀኑ ህዝብ

በአላህ ስም እጅግ በጣም ርህሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው

የጸሐፊው መግቢያ

ምስጋና ሁሉ ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ነው። የመጨረሻውም ሀገር አላህን ለሚፈሩ ለጥንቁቆቹ ነው። የአላህ ሰላትና ሰላም የአላህ ባሪያውና መልዕክተኛው በሆኑት ነቢዩ ሙሐመድ፣ በተከታዮቻቸውና በባልደረቦቻቸውም ላይ ሁሉ ይስፈን።

በመቀጠልም፦

ይህ መልዕክት አጠር ባለ መልኩ የተዘጋጀና ሙስሊሙ ማህበረሰብ ስለ ኢስላም ሊያውቃቸው የሚገቡ አንዳንድ ቁም ነገሮችን የሚያብራራ ሲሆን ርዕሱንም፦ "አሳሳቢ ትምህርቶች ለብዙሀኑ ህዝብ" ብዬ ሰይሜዋለሁ።

በዚህ መልዕክት ሙስሊሙን ማህበረሰብ ሊጠቅምበትና ይህንን ሥራዬን ሊቀበለኝም ዘንድ አሏህን እማፀነዋለሁ። እርሱ በጣም ቸርና ለጋሽ ነውና።

ዐብዱልዐዚዝ ቢን ዐብደላህ ቢን ባዝ አሳሳቢ ትምህርቶች ለብዙሀኑ ህዝብ1

የመጀመሪያው ትምህርት ሱረቱል ፋቲሓ (የመክፈቻ ምዕራፍ) እና አጫጭር ሱራዎች

ሱረቱል ፋቲሓ እና ከሱረቱ አዝ-ዘልዘላህ እስከ ሱረቱ አን-ናስ ድረስ ያሉትን አጫጭር ምዕራፎች የተቻለውን ያህል ቃል በቃል እንዲያጠኑ ማድረግ። የአነባበብ ስህተትንም ማስተካከል፤ የሚያነቧቸውንም ምዕራፎች በቃላቸው ማሸምደድና ከምዕራፎቹ መረዳት የሚገባቸዉን መልዕክቶች ማብራራት።

ሁለተኛ ትምህርት: የእስልምና ማዕዘናት

የአምስቱ የእስልምና ማዕዘናት ማብራሪያ፡ የመጀመሪያውና ትልቁ: "ከአላህ በቀር በእውነት የሚመለክ አምላክ እንደሌለና ሙሐመድም የአላህ መልክተኛ መሆናቸውን መመስከር" ነው። ይህም ትርጉሙን ከመተንተንና የ"ላኢላሃ ኢለሏህ"ን መስፈርቶች ከማብራራት ጋር ነው። ትርጉሙም፦ (ላኢላሃ) የሚለው ቃል ከአላህ ውጪ የሚመለኩ ነገሮችን በጠቅላላ ውድቅ የሚያደርግ ሲሆን (ኢለሏህ) የሚለው ቃል ደግሞ አምልኮን አጋር ለሌለው ለአላህ ብቻ የሚያፀድቅ ነው። የ(ላኢላሃ ኢለሏህ) መስፈርቶች ደግሞ: መሃይምነትን የሚፃረር ዕውቀት፤ ጥርጣሬን የሚፃረር እርግጠኝነት፤ ሺርክን የሚፃረር ለአላህ ብቻ ማጥራት (ኢኽላስ)፤ ማስተባበልን የሚፃረር እውነት፤ ጥላቻን የሚፃረር ውዴታ፤ መተውን የሚፃረር ታዛዥነት፤ እምቢተኝነትን የሚፃረር መቀበልና ከአላህ ውጪ በሚመለኩ ነገሮች መካድ ናቸው። እነዚህ ስምንት መስፈርቶችም ከዚህ ቀጥሎ ባሉ የግጥም ስንኞች ተሰብስበው ይገኛሉ።

ማወቅ፣ እርግጠኝነት፣ ማጥራት፣ እውነተኝነት .... መውደድ፣ ታዛዥነት፣ መቀበል የርሱን ብቸኝነት መካድ የቱንም ባላንጣነት .... ጨምረው በስምንተኝነት።

በተጨማሪም "ሙሐመድ የአላህ መልክተኛ ናቸው ብሎ መመስከርን።" ማብራራትም ያስፈልጋል። እርሷም የሚከተሉትን ታስፈርዳለች። እርሳቸው የተናገሩትን እውነት ብሎ መቀበል፤ እርሳቸው ያዘዙትንም መታዘዝ፤ እርሳቸው የከለከሉትንና ያስጠነቀቁትን መራቅ፤ አላህና መልክተኛው(የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) በደነገጉት መልኩ ካልሆነ በቀርም አላህን አለማምለክ ነው። በመቀጠል የተቀሩትን የእስልምና አምስት ማዕዘናትን ለተማሪው ያብራራል። እነርሱም:- ሶላት፣ ዘካህ፣ ረመዳንን መፆምና ወደርሱ መንገድን ለቻለ ሰው የተከበረውን የአላህን ቤት ሐጅ ማድረግ ናቸው።

ሶስተኛ ትምህርት: የኢማን ማዕዘናት

የኢማን (እምነት) መሰረቶች ስድስት ናቸው። እነርሱም፡- በአላህ፣ በመላእክቶቹ፣ በመጻሕፍቱ፣ በመልዕክተኞቹ፣ በመጨረሻው ቀን ማመን፣ እንዲሁም ጥሩም ይሁን መጥፎ በአላህ ውሳኔና ፍቃድ (በቀደር) መሆኑን ማመን ናቸው።

 

አራተኛው ትምህርት: የተውሒድ እና የሺርክ ክፍሎች

የተውሒድ (አላህን በአምልኮ ብቸኛ ማድረግ) ክፍሎችን ማብራራት፤ ዓይነቶቹም ሦስት ሲሆኑ እነርሱም፦ የጌትነት አንድነት(ተውሒድ አርሩቡቢያ)፣ የአምላክነት አንድነት(ተውሒድ አልኡሉሂያ)እና የስሞና ባህሪያት አንድነት(ተውሒድ አልአስማእ ወስሲፋት) ናቸው።

1 - ተውሒድ አር-ሩቡቢያህ (የጌትነት አንድነት)፡- ማለት አላህ የሁሉም ነገር ፈጣሪና የሁሉም ነገር አስተናባሪም መሆኑን በዚህም ላይ ምንም አጋር እንደሌለው ማመን ነው።

2 - ተውሒድ አል-ኡሉሂያህ (የአምላክነት አንድነት) ማለት፡- በእውነት የሚመለከው አሏህ ብቻ እንደሆነና በአምልኮ ምንም አጋር እንደሌለው ማመን ነው። የ “ላኢላሀ ኢለላህ” ትርጓሜውም ይህ ነው። ትርጉሙም ከአላህ ውጪ በእውነት የሚመለክ አምላክ የለም ማለት ነውና። ሶላትና ፆም እንዲሁም ሌሎችም የዒባዳ (አምልኮ) አይነቶችን በአጠቃላይ ለአላህ ብቻ ጥርት አድርጎ መፈጸም የግድ ይላል። ከአላህ ውጪ ላለ ለማንኛውም አካል እነዚህን አምልኮዎች መስጠት አይፈቀድም።

3 - ተውሒድ አል አስማእ ወስሲፋት (የስሞና ባህሪያት አንድነት) ማለት፡- በቁርኣንና በትክክለኛ ሐዲሦች ስለ አላህ ስሞችና ባህርያት የተጠቀሱትን በሙሉ ማመን፤ እነዚህን ስምና ባህሪያቱን ለእርሱ በሚገባው መልኩ ለብቻው ማፅደቅ፤ ይህንንም ስናደርግ ያለ ተሕሪፍ (ትክክለኛ ትርጓሜያቸዉን ሳንቀይር)፣ ያለ ተዕጢል (ትርጉም አልባ ሳናደርግ)፣ ያለ ተክዪፍ (ዝርዝር ሁኔታቸውን ሳንገልጽ) እና ያለ ተምሢል (ከፍጡራን ጋር ሳናመሳስል) ማፅደቅ ነው። ይህንንም የምናደርገው የሚከተለውን የአላህ ቃል መሰረት በማድረግ ነው፦

﴿قُلۡ هُوَ ٱللَّهُ أَحَدٌ 1 ٱللَّهُ ٱلصَّمَدُ 2 لَمۡ يَلِدۡ وَلَمۡ يُولَدۡ 3 وَلَمۡ يَكُن لَّهُۥ كُفُوًا أَحَدُۢ 4

(በል «እርሱ አላህ አንድ ነው። (1)

አላህ (የሁሉ) መጠጊያ ነው፡፡ (2)

አልወለደም፤ አልተወለደምም። (3)

ለእርሱም አንድም ብጤ የለውም፡፡) [ሱረቱ አል'ኢኽላስ: 1-4] አሸናፊና የበላይ የሆነው አላህ እንዲህ ብሏል፦

﴿...لَيۡسَ كَمِثۡلِهِۦ شَيۡءٞۖ وَهُوَ ٱلسَّمِيعُ ٱلۡبَصِيرُ﴾

{የሚመስለው ምንም ነገር የለም። እርሱም ሰሚው ተመልካቹ ነው።} [አሽ ሹራ፡ 11] ከፊል ዑለሞች ደግሞ የተውሒድን ክፍሎች ሁለት አይነት እንደሆኑ ጠቅሰዋል። የስምና ባህሪያት አሀዳዊነቱን በጌትነት አሀዳዊነቱ ስር አጠቃለውት ማለት ነው። ይህንን ማድረጋቸውም የሚያወዛግብ አይደለም። ምክንያቱም በሁለቱም የአከፋፈል ዘዴዎች የተፈለገው ምን እንደሆነ ግልፅ ነውና።

የሺርክ ክፍሎች ሶስት አይነት ናቸው። ትልቁ ሺርክ፣ ትንሹ ሺርክና ድብቁ ሺርክ ናቸው።

ትልቁ ሺርክ: የሥራ መበላሸትንና በርሱ ላይ ሆኖ ለሞተ ሰውም እሳት ውስጥ የመዘውተርን መዘዝ ያስከትላል። አላህ እንዲህ ብሏል:-

﴿...وَلَوۡ أَشۡرَكُواْ لَحَبِطَ عَنۡهُم مَّا كَانُواْ يَعۡمَلُونَ﴾

{ባጋሩም ኖሮ ይሰሩት የነበሩት ከነሱ በታበሰ ነበር።} [አል አንዓም፡ 88] በሌላም አንቀጽ አላህ እንዲህ ብሏል፦

﴿مَا كَانَ لِلۡمُشۡرِكِينَ أَن يَعۡمُرُواْ مَسَٰجِدَ ٱللَّهِ شَٰهِدِينَ عَلَىٰٓ أَنفُسِهِم بِٱلۡكُفۡرِۚ أُوْلَٰٓئِكَ حَبِطَتۡ أَعۡمَٰلُهُمۡ وَفِي ٱلنَّارِ هُمۡ خَٰلِدُونَ 17

(ለከሓዲዎች በነፍሶቻቸው ላይ በክህደት የሚመሰክሩ ሲሆኑ የአላህን መስጂዶች ሊሠሩ አይገባቸውም፡፡ እነዚያ ሥራዎቻቸው ተበላሹ፡፡ እነሱም በእሳት ውስጥ ዘውታሪዎች ናቸው፡፡) [አት ተውባህ፡ 17] ሸርክን እየፈፀመ የሞተ ምህረትን አያገኝም ጀነትም በእርሱ ላይ እርም ናት። አላህ በተከበረ ቃሉ እንዲህ ብሏል፦

﴿إِنَّ ٱللَّهَ لَا يَغۡفِرُ أَن يُشۡرَكَ بِهِۦ وَيَغۡفِرُ مَا دُونَ ذَٰلِكَ لِمَن يَشَآءُ...

“አላህ በእርሱ ማጋራትን በፍጹም አይምርም። ከዚህ ሌላ ያለውንም (ኀጢአት) ለሚሻው ሰው ይምራል።” [ኒሳእ፡ 48] በሌላም አንቀጽ አላህ እንዲህ ብሏል፦

﴿...إِنَّهُۥ مَن يُشۡرِكۡ بِٱللَّهِ فَقَدۡ حَرَّمَ ٱللَّهُ عَلَيۡهِ ٱلۡجَنَّةَ وَمَأۡوَىٰهُ ٱلنَّارُۖ وَمَا لِلظَّٰلِمِينَ مِنۡ أَنصَارٖ﴾

{እነሆ! በአላህ የሚያጋራ ሰው አላህ በርሱ ላይ ገነትን በእርግጥ እርም አደረገ፡፡ መኖሪያውም እሳት ናት፡፡ ለበዳዮችም ምንም ረዳቶች የሏቸውም፡፡} [አል ማኢዳህ:72]

ከትልቁ ሽርክ አይነቶች መካከልም ሙታንንና ጣኦታትን መለመን፣ እርዳታ ከነርሱ መፈለግ፣ ለእነርሱም ስለት መግባት፣ እርድ ማቅረብና የመሳሰሉት ተጠቃሽ ናቸው።

ትንሹ ሽርክ (ሽርኩል-አስገር)፡- ይህ ደግሞ በቁርአንና በሐዲሥ መረጃዎች ሽርክ የሚል ስያሜ ቢሰጠውም ነገር ግን ከትልቁ ሽርክ የማይመደብ ነው። ለምሳሌ፡ አንዳንድ ስራዎችን ለይዩልኝ መስራት፣ ከአላህ ውጪ ባለ አካል መማል፣ "አላህ እና እገሌ የፈለጉት ሆነ" ብሎ ማለትና የመሳሰሉት ናቸው። ይህንንም ያልንበት ምክንያት የአላህ መልዕክተኛ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) እንዲህ ስላሉ ነው፦

«أَخْوَفُ مَا أَخَافُ عَلَيْكُمْ الشِّرْكَ الَأصْغَرَ» فَسُئِلَ عَنْهُ، فَقَالَ: «الرِّيَاءُ».

"በናንተ ላይ ከምፈራቸው ነገሮች መካከል እጅግ አስፈሪው ነገር ትንሹ ሺርክ ነው።" አሉ። ስለርሱም ተጠየቁ። እርሳቸውም "ይዩልኝ ነው።" አሉ።}2 ይህንንም ሐዲሥ ኢማሙ አሕመድ እና በይሀቂይ ከመሕሙድ ቢን ለቢድ አልአንሷሪይ - አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላቸውና - ጠንካራ በሆነ ሰነድ ዘግበውታል። ጠበራኒይም እንዲሁ ከመሕሙድ ቢን ለቢድ፣ መሕሙድ ደግሞ ከራፊዕ ኢብን ኸዲጅ ከነብዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ጠንካራ በሆነ ሰነድ ዘግበውታል።

ተከታዩም የአላህ መልዕክተኛ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ንግግር፦

«مَنْ حَلَفَ بِشَيْءٍ دُونَ اللَّهِ فَقَدْ أَشْرَكَ».

“ከአላህ ውጭ ባለ አንዳች ነገር የማለ በእርግጥም አጋርቷል።”3 ኢማሙ አሕመድ ከዑመር ቢን አልኸጧብ - አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላቸውና - ሶሒሕ በሆነ ሰነድ ዘግበውታል። እንዲሁም አቡ ዳውድ እና ቲርሚዚይም ሶሒሕ በሆነ ሰነድ ከኢብኑ ዑመር - አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላቸውና - በተላለፈ ሐዲሥ ነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) እንዲህ ማለታቸውን ዘግበዋል፦

«مَنْ حَلَفَ بِغَيْرِ اللَّهِ فَقَدْ كَفَرَ أَوْ أَشْرَكَ».

"ከአሏህ ውጭ ባለ አካል የማለ በእርግጥም ክዷል ወይም አጋርቷል።"4 ተከታዩም የአላህ መልዕክተኛ(የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ንግግር፦

«لَا تَقُولُوا: مَا شَاءَ اللَّهُ وَشَاءَ فُلانٌ، وَلَكِنْ قُولُوا: مَا شَاءَ اللَّهُ ثُمَّ شَاءَ فُلانٌ».

"አላህ እና እከሌ ከፈለጉ ..." አትበሉ። ይልቁንም "አላህ ከፈለገ ከዚያም እከሌ ከፈለገ... " በሉ።5 አቡዳውድም ከሑዘይፋ ኢብኑል የማን - አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላቸውና - በሶሒሕ ሰነድ ዘግበውታል።

ይህ የሽርክ አይነት (ትንሹ ሽርክ) ከዲን እስከመውጣት አያደርስም፤ እንዲሁም በእሳት ዘላለም ለመዘውተርም አይዳርግም፤ ነገር ግን ማመን ግዴታ የሆነውን የተውሒድን ምሉዕነት (ከማል) ያጓድላል።

ሶስተኛው የሽርክ አይነት ደግሞ ድብቁ ሽርክ (ሽርኩል ኸፍይ ይባላል)፡- ማስረጃውም የሚከተለው የነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ንግግር ነው፡-

«أَلَا أُخْبِرُكُمْ بِمَا هُوَ أَخْوَفُ عَلَيْكُمْ عِنْدِي مِنَ المَسِيحِ الدَّجَّالِ؟» قَالُوا: بَلَى يَا رَسُولَ اللَّهِ، قَالَ: «الشِّرْكُ الخَفِيُّ، يَقُومُ الرَّجُلُ فَيُصَلِّي فَيُزَيِّنُ صَلاتَهُ لِمَا يَرَى مِنْ نَظَرِ الرَّجُلِ إِلَيْهِ».

"እኔ ዘንድ ከመሲሑ ደጃል ይበልጥ የምፈራላችሁን ነገር አልነግራችሁምን?” አሉ። ሶሓቦችም፡ “አዎን ይንገሩን የአላህ መልዕክተኛ ሆይ!” አሉ፤ እሳቸውም “ድብቁ ሽርክ ነው። (የዚህም ምሳሌው) አንድ ሰው ለሰላት ይቆምና ሰዎች እርሱን የሚመለከቱት መሆኑን ሲያውቅ ሰላቱን ይበልጥ ያሳምረዋል።”6 ኢማሙ አሕመድ በሙስነዳቸው ከአቡሰዒድ አልኹድሪይ - አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላቸውና - ዘግበውታል።

ሽርክን በሁለት ብቻ መክፈልም ይቻላል እነርሱም፦

ትልቁና ትንሹ ነው። ድብቁ ሽርክ የተባለው ሁለቱንም የሽርክ አይነቶች የሚያጠቃልል ይሆናል። (ድብቁ ሺርክ) ትልቁ ሽርክ ሆኖ ሊከሰትም ይችላል፤ የዚህም ምሳሌው የሙናፊቆች ሽርክ ነው። ምክንያቱም ለነፍሳቸው ፈርተው ለታይታ ከላይ ብቻ ኢስላምን እያንፀባረቁ ባጢል የሆነውን እምነታቸውን ስለሚደብቁ ነው።

ትንሹ ሽርክ ሆኖ ሊከሰትም ይችላል፤ የዚህም ምሳሌው ለታይታ መስራትን የመሰለው ነው። ቀደም ብሎ በተጠቀሰው ከመሕሙድ ኢብኑ ለቢድ አልአንሳሪይና ከአቡሰዒድ አልኹድሪይ በተላለፈው ሐዲሥ ላይ ተገልጿል። መልካምን የሚገጥመው አላህ ብቻ ነው።

አምስተኛው ትምህርት: ኢሕሳን (በጎ ማድረግ)

የአል-ኢሕሳን (የበጎ ማድረግ) ማዕዘን፡- አላህን ልክ እንደምታየው ሆነህ ልታመልከው ነው፤ አንተ ባታየው እንኳ እርሱ ያይሃልና።

ስድስተኛው ትምህርት: የሶላት መስፈርቶች

የሰላት ቅድመ ሁኔታዎች (መስፈርቶች) ዘጠኝ ናቸው። እነርሱም፦

ሙስሊም መሆን፣ የጤናማ አእምሮ ባለቤት መሆን፣ ነገሮችን መለየት የሚያስችል እድሜ ላይ መድረስ፣ ሐደሥን (ዉዱእን ወይም የገላ ትጥበትን ግዴታ የሚያደርጉ ነገሮችን) ማስወገድ፣ ነጃሳን (ከአካል፣ ከልብስና ከመስገጃ ሥፍራ) ማስወገድ፣ ሀፍረተ ገላን መሸፈን፣ የሰላት ወቅት መግባት፣ ወደ ቂብላ (ካዕባ) አቅጣጫ መዞር እና ኒያ ናቸው።

ሰባተኛው ትምህርት: የሶላት ማዕዘናት

የሰላት ማዕዘናት (ሩክኖች) አስራ አራት ናቸው እነርሱም፡-

የመቆም አቅሙ ላለው ሰው ቆሞ መስገድ፤ ተክቢረተል ኢሕራም (የመክፈቻ ተክቢራ)፤ የፋቲሓን ምዕራፍ ማንበብ፤ ሩኩዕ ማድረግ (ማጐንበስ)፤ ከአጎነበሱበት ቀና ብሎ መቆም፤ በሰባቱ የሰውነት አካላት ሱጁድ ማድረግ (በሁለቱ የእጅ መዳፎች፣ ሁለት ጉልበቶች፣ ሁለት የእግር ጣቶች የውስጠኛው ክፍልና በግንባር አፍንጫን ጨምሮ መሬት ላይ መደፋት)፤ ከሱጁድ መነሳት፤ በሁለቱ ሱጁዶች መካከል መቀመጥ፤ በሁሉም የስግደት ተግባራት ላይ እርጋታን መላበስ፤ በማእዘናቱ መካከል ያለውን ቅደም ተከተል መጠበቅ፤ የመጨረሻው ተሸሁድ (አተሒያቱ) ማለት፤ ለተሸሁዱ መቀመጥ፤ በነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ላይ ሶላትን ማውረድ እና ሁለቱ ተስሊሞች (በቀኝና በግራ እየዞሩ አሰላሙ ዐለይኩም) ማለት ናቸው።

ስምንተኛው ትምህርት: የሶላት ዋጂቦች (ግዴታዎች)

ስምንት ናቸው፤ እነርሱም፦

ከተክቢረተል ኢሕራም ውጪ ያሉት ተክቢራዎች በሙሉ፤ ኢማም ሆኖ ወይም ብቻውን ሆኖ ለሚሰግድ ሰው (ሰሚዐላሁ ሊመን ሐሚዳህ) ማለቱ (ትርጉሙም፡ አላህ አመስጋኙን ሰሚ ነው)፤ ለሁሉም ሰጋጅ (ረበና ወለከል ሐምድ) ማለቱ (ትርጉሙም፡ ጌታችን ሆይ ምስጋና ለአንተ የተገባ ነው።)፤ ሩኩዕ ላይ (ሱብሐነ ረቢየል ዐዚም) ማለት (ትርጉሙም፡ ታላቁ ጌታዬ ከጉድለቶች ጥራት የተገባው ነው)፤ ሱጁድ ላይ (ሱብሐነ ረቢየል አዕላ) ማለት (ትርጉሙም፡ የበላይ የሆነው ጌታ ጥራት የተገባ ነው።)፤ በሁለቱ ሱጁዶች መካከልም (ረቢግፊርሊ) ማለት (ትርጉሙም፡ ጌታዬ ማረኝ)፤ የመጀመሪያው ተሸሁድ ላይ (አትተሒያቱ) ማለት፤ ለመጀመሪያው ተሸሁድ መቀመጥ ናቸው።

ዘጠነኛው ትምህርት: የተሸሁድ ማብራሪያ

እርሱም እንዲህ የሚለው ነው፦

{አትተሒያቱ ሊላሂ ወስሰለዋቱ ወጥጦዪባቱ አስሰላሙ ዐለይከ አይዩሀ-ንነቢዩ ወረሕመቱላሂ ወበረካቱሁ አስሰላሙ ዐለይና ወዐላ ዒባዲላሂ-ስሷሊሒን አሽሀዱ አን-ላኢላሀ ኢለላህ ወአሽሀዱ አንነ ሙሐመደን ዐብዱሁ ወረሱሉህ።} (ትርጉሙም፦ ክብር ለአላህ የተገባ ነው። እዝነቶችና መልካም ነገሮች ሁሉ የአላህ ናቸው። አንተ ነብይ ሆይ! የአላህ ሰላም፣ እዝነትና በረከቱ ይስፈንብህ። በእኛና በአላህ ቅን ባሪያዎች ላይም ሰላም ይስፈን። ከአላህ ሌላ በእውነት የሚመለክ አምላክ እንደሌለ እመሰክራለሁ። ሙሐመድም ባሪያውና መልዕክተኛው መሆናቸውን እመሰክራለሁ።)

በመቀጠል በነቢዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ላይ ሰለዋትና በረካ ለማውረድ እንዲህ ይላል፦ “አልላሁመ ሰሊ ዐላ ሙሐመድ ወዐላ ኣሊ ሙሐመድ ከማ ሰለይተ ዐላ ኢብራሂም ወዐላ ኣሊ ኢብራሂም ኢንነከ ሐሚዱን መጂድ ወባሪክ ዐላ ሙሐመድ ወዐላ ኣሊ ሙሐመድ ከማ ባረክተ ዐላ ኢብራሂም ወዐላ ኣሊ ኢብራሂም ኢንነከ ሐሚዱን መጂድ።” (ትርጉሙም፡ አላህ ሆይ! በኢብራሂምና በቤተሰቦቻቸው ላይ ውዳሴህን እንዳወረድክ ሁሉ በሙሐመድና በቤተሰቦቻቸው ላይም ውዳሴህን አውርድ፤ አንተ ምስጉንና የላቅክ አምላክ ነህና። አላህ ሆይ! በኢብራሂምና በቤተሰቦቻቸው ላይ በረከትህን እንዳሰፈንክ ሁሉ በሙሐመድና በቤተሰቦቻቸው ላይም በረከትህን አዉርድ። አንተ ምስጉንና የላቅክ አምላክ ነህና።)

የመጨረሻው ተሸሁድ ላይም ከጀሀነምና ከቀብር ቅጣት፣ በህይወት ሳለም ሆነ ከሞት በኋላ ከመፈተን፣ እንዲሁም ከመሲሕ አድደጃል ፈተና የአሏህን ጥበቃ ይማፀናል። ከዚያም የሚፈልገውን ዱዓእ መርጦ ያደርጋል። በተለይም ከነብዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) የተዘገቡትን ይበል። ከነዚህም መካከል፦

“አልላሁመ አዒንኒ ዐላ ዚክሪከ ወሹክሪከ ወሑስኒ ዒባደቲክ፤ አልላሁመ ኢንኒ ዞለምቱ ነፍሲ ዙልመን ከሢራ ወላ የግፊሩ ዙኑበ ኢላ አንተ ፈግፊርሊ መግፊረተን ሚን ዒንዲክ ወርሐምኒ ኢንነከ አንተል ገፉሩ ረሒም።” (ትርጉሙም፡- አላህ ሆይ! አንተን ለማስታወስ፣ ለማመስገንና አምልኮህን ለማሳመር እርዳኝ። አላህ ሆይ! እኔ ነፍሴን በበርካታ በደል በድያለሁ ኅጢአትንም ከአንተ ውጭ የሚምር የለምና ከአንተ የሆነን ምህረት ለግሰኝ። እዘንልኝም አንተ መሀሪና አዛኝ ነህና።)

የመጀመሪያውን ተሸሁድ በተመለከተ በዙሁር፣ በዐስር፣ በመግሪብ እና በዒሻእ ሶላቶች ልክ ከሁለቱ የምስክርነት ቃላት በኋላ ለሦስተኛው ረከዓ ይቆማል፤ በነብዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ላይ ሰለዋት ካወረደ በኋላ መቆሙ ደሞ በላጭ ነው። ይህም የሐዲሦቹ አጠቃላይ መልዕክት ይህን የሚያሲዝ በመሆኑ ነው። ከዚያም ለሦስተኛው ረከዓ ይቆማል።

አስረኛ ትምህርት: የሶላት ሱናዎች

ከእነርሱም መካከል፦

1 - የመክፈቻ ዱዓእ (ዱዓኡል ኢስቲፍታሕ)

2 - ከሩኩዕ በፊትና በኋላ በሚቆም ጊዜ ቀኝን መዳፍ በግራ መዳፍ ላይ አድርጎ ደረት ላይ ማሳረፍ፤

3 - የእጆችን ጣቶች ገጣጥሞ በመዘርጋት ከትከሻ ወይም ከጆሮ ትይዩ አድርጎ ማንሳት፤ ይህም የሚደረገው በሚከተሉት ቦታዎች ይሆናል። የመጀመሪያው የመክፈቻ ተክቢራ ላይ፤ ሩኩዕ በሚደርግበት ጊዜ፤ ከሩኩዕ ቀና በሚባልበት ጊዜ፤ ከመጀመሪያው ተሸሁድ በኋላ ለሶስተኛው ረከዓ በሚነሱበት ጊዜ ናቸው።

4 - በሩኩዕና በሱጁድ ወቅት ከአንድ ጊዜ በላይ ተስቢሕ (ሱብሓነ ረቢየል ዐዚም ወይም ሱብሓነ ረቢየል አዕላ)ማለት፤

5 - ከሩኩዕ ቀና ካሉ በኋላ "ረበና ወለከል ሐምድ" ከሚለው ሌላ ዱዓዎችን መጨመር፤ በሁለቱ ሱጁዶች መካከል በሚያደርገው ዱዓእ "ረብቢግፊርሊ" በሚለው መሀርታን ሲጠይቁ ከአንድ ጊዜ በላይ መጨመር።

6 - ሩኩዕ በሚያደርጉበት ጊዜ ጭንቅላትን ከወገብ ትይዩ ማድረግ።

7 - ሱጁድ በሚያደርጉበት ጊዜ የእጅን ጡንቻዎች ከጐኖቹ ማላቀቅ እንዲሁም ሆድን ከታፋ፣ ታፋን ከባት ማራራቅ፤

8 - ሱጁድ በሚያደርጉበት ጊዜ ክንዶችን ከመሬት ከፍ ማድረግ፤

9 - በሁለቱ ሱጁዶች መካከል እና በመጀመሪያው ተሸሁድ ላይ ግራ እግርን አንጥፎ እላዩ ላይ በመቀመጥ የቀኝ እግርን ጣቶች ቀጥ ማድረግ፤

10 - አራት እና ሦስት ረከዓዎች ባላቸው ሶላቶች የመጨረሻ ተሸሁድ ላይ “ተወሩክ” በማድረግ መቀመጥ፤ “ተወሩክ” ማለት ግራ እግርን ከቀኝ እግር ስር አሳልፎ የቀኝ እግር ጣቶችን ቀጥ በማድረግ መቀመጫን መሬት ላይ አሳርፎ መቀመጥ ነው።

11 - በመጀመሪያው እና በመጨረሻው ተሸሁድ ላይ ከተቀመጡበት ሰዓት አንስቶ እስከ ተሸሁድ መጨረሻው ድረስ በአመልካች ጣት ማመላከትና ዱዓእ ላይ ጣትን ማንቀሳቀስ።

12 - በመጀመሪያው ተሸሁድ ላይ በነብዩ ሙሐመድ እና በቤተሰቦቻቸው እንዲሁም በኢብራሂምና በቤተሰቦቻቸውም ላይ የአላህ ውዳሴና በረከት እንዲሰፍን አሏህን መለመን፤

13 - በመጨረሻው ተሸሁድ ላይ ዱዓእ ማድረግ፤

14 - በፈጅር ሰላት፣ በጁምዓ ሰላት፣ በሁለቱ ዒዶች ሰላት እና በኢስቲስቃእ (በዝናብ እጦት ጊዜ የሚሰገድ ሰላት) ላይ እንዲሁም በመግሪብ እና በኢሻዕ የመጀመሪያ ሁለቱ ረከዐዎች ላይ ድምፅን ከፍ አድርጐ መቅራት፤

15 - በዙህር እና ዐስር ሰላቶች እንዲሁም የዒሻእ የመጨረሻዎቹ ሁለት ረከዓዎች እና የመግሪብ ሶስተኛው ረከዓ ላይ ድምፅን ሳያሰሙ መቅራት፤

16 - ከፋቲሓ በተጨማሪ ሌላ የቁርአን ምዕራፍ ማንበብ እንዲሁም ከላይ ከጠቅስናቸው በተጨማሪ ሌሎች የሰላት ሱናዎችንም መተግበር፤ ከነዚህም ውስጥ፡- ለብቻው የሚሰግድም ሆነ ኢማሙ ወይም ኢማሙን ተከትሎ የሚሰግድ ሰው ከሩኩዕ በሚነሳበት ወቅት (ረበና ወለከል ሐምድ) ከሚለው ውጪ ያሉ ተጨማሪ ውዳሴዎችን ማድረግ ይህም ሱና ነው፤ ሩኩዕ በሚያደርግበት ጊዜ የእጆቹን ጣቶች በመከፋፈት (በመሀከላቸው ክፍተት በማድረግ) ሁለቱን እጆች ጉልበቶቹ ላይ ማሳረፍም ተጠቃሽ ሱናዎች ናቸው።

አስራ አንደኛ ትምህርት: ሶላትን የሚያበላሹ ነገሮች

ሰላትን የሚያበላሹ ነገሮች ስምንት ናቸው፤ እነርሱም፦

1 - በማወቅና እያስታወሱ በሶላት መሀል መናገር ሰላትን ያበላሻል። የረሳ ወይም ያላወቀ ሆኖ ቢናገር ግን ሶላቱ አይበላሽበትም።

2 -መሳቅ

3 -መብላት

4 -መጠጣት

5 - የሐፍረተ ገላ መገለጥ

6 - የቂብላ አቅጣጫን እጅግ በሳተ መልኩ መዞር

7 - በሶላት ውሰጥ ከሶላቱ ጋር ግንኙነት የሌላቸውን ተደጋጋሚ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ

8 - የጦሃራ መበላሸት (መፍረስ)

አስራ ሁለተኛ ትምህርት: የዉዱእ ቅድመ መስፈርቶች (ሸርጦች)

እነርሱም፡- አስር ናቸው።

ሙስሊም መሆን፣ የአይምሮ ጤናማ መሆን፣ ነገሮችን መለየት የሚያስችል እድሜ ላይ መድረስ፣ ኒያ ማድረግ (በልብ ማሰብ)፣ የዉዱእን ብይን ማጎዳኘት ይህም ዉዱእን እስከሚያጠናቅቅ ድረስ ላለማቋረጥ መነየት (መወሰን)፣ ውዱእ ማድረግን ግዴታ ከሚያደርጉ ነገሮች መራቅ፣ አስቀድሞ በውሃ ኢስቲንጃ ማድረግ (ማጠብ) ወይም በደረቅና በሚፈቀዱ ነገሮች ማደራረቅ፣ ውሃው ንፁህና የተፈቀደ መሆን አለበት፣ ውሃ ወደ ሰውነት ቆዳ እንዳይገባ የሚከለክሉ ነገሮችን ማስወገድ፣ ሁል ጊዜ ያለማቋረጥ የዉዱእ መጥፋት ችግር ላለበት ሰው የሶላቱ ወቅት መግባቱ ናቸው።

አስራ ሶስተኛ ትምህርት: የዉዱእ ግዴታዎች

ስድስት ናቸው። እነርሱም፡-

ፊትን መታጠብ፣ ይህም ሲባል መጉመጥመጥና በአፍንጫ ውሃን ስቦ መመለስን ያካትታል፤ ሁለቱ እጆችን ክርንን ጨምሮ መታጠብ፤ ራስን (የራስ ቅልን) ሙሉ በሙሉ በውሃ ማበስ፤ ይህም ሁለቱ ጆሮዎችን ማበስንም ያካትታል። ሁለቱ እግሮችን ከቁርጭምጭሚት ጋር መታጠብ፤ ቅደም ተከተልን መጠበቅ፤ ለውዱእ የሚታጠቡ አካሎችን በመሀከላቸው የጊዜ ክፍተት ሳይኖር አከታትሎ ማጠብ ናቸው። ፊትን፣ ሁለት እጆችንና እግሮችን በሚያጥቡበት ጊዜ ሶስት ጊዜ ደጋግሞ ማጠብ ይወደዳል። እንዲሁ በሚግሞጠሞጥበት እና በአፍንጫው ውሃ በሚያስገባበት ጊዜ ሶስት ሶስት ቢያደርግ ይወደዳል። ይህን ማድረግ ካልቻለ ግን ግዴታ የሚሆንበት አንድ ጊዜ ብቻ ማድረጉ ነው። የራስ ቅልን ማበስ በተመለከተ ግን ትክክለኛ ሐዲሦች እንደሚያመላክቱት ከአንድ በላይ መደጋገሙ አይወደድም።

አስራ አራተኛ ትምህርት: ዉዱእን የሚያበላሹ ነገሮች

ስድስት ናቸው። እነርሱም፡-

ከሁለቱ የቆሻሻ መውጫ ክፍሎች የወጣ ሁሉ፤ ከሰውነት ነጃሳና የሚያስጠላ የሆነ ነገር መውጣቱ ፤ በእንቅልፍና በሌሎች አእምሮን ሊያስቱ በሚችሉ ነገሮች አእምሮን መሳት፤ ከፊት ወይም ከኋላ ያለውን ሀፍረተ ገላ ያለምንም ግርዶሽ በቀጥታ በእጅ መንካት፤ የግመል ስጋ መብላት ፤ እኛንም መላውንም ሙስሊም አላህ ይጠብቀንና ‐ ከእስልምና መውጣት ናቸው።

ወሳኝ ማሳሰቢያ፦ ሬሳን ማጠብ (ውዱእ ያበላሻል ወይስ አያበላሽም የሚለውን) አስመልክቶ ትክክለኛው አስተያየት ዉዱእ አያበላሽም የሚለው ነው። ይህ አስተያየት ደግሞ የአብዛኛዎቹ ሊቃውንት አቋም ነው። ምክንያቱም ያበላሻል የሚለው ምንም ማስረጃ የለውምና። ነገር ግን የሟቹን ሀፍረተ ገላ ያለምንም ግርዶሽ የነካ ሰው ዉዱኡ ይበላሻልና ዉዱእ የማድረግ ግዴታ አለበት።

የሬሳውን ሀፍረተ ገላ ያለምንም ከለላ መንካትም ይከለከላል። እንዲሁም ትክክለኛ በሆነው የዑለማዎች አቋም መሰረት ሴትን በስሜትም ሆነ ያለ ስሜት መንካትም ከብልቱ ፈሳሽ እስካልወጣ ድረስ ውዱእ አያበላሽም የሚለው ነው። ምክንያቱም ነቢዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን)ከሚስቶቻቸው አንዷን ስመው ውዱእ ሳያደርጉ ሰግደዋልና።

በሱረቱ አን-ኒሳእ እና በሱረቱል ማኢዳህ ምዕራፍ ውስጥ የተጠቀሰው ተከታዩን የአላህን ቃል በተመለከተ፦

﴿أَوۡ لَٰمَسۡتُمُ ٱلنِّسَآءَ﴾

{ወይንም ሴቶችን ብትነካኩ።} [አንኒሳእ: 43] [አልማኢዳ: 6] በእነዚህ አንቀጾች ማስተላለፍ የተፈለገው መልዕክት በትክክለኛው የዑለማዎች አቋም መሰረት የግብረ ስጋ ግንኙነት ነው። ይህም አቋም የዐብደላህ ኢብኑ ዐባስ - ረዲየሏሁ ዐንሁማ - እና የብዙ ሰለፎች (ቀደምት ዑለማዎች) እንዲሁም የመልካም ሰለፎች ምትክ ዑለማዎች አቋማቸው ይህ ነው። ተውፊቅን የሚሰጠው አላህ ነውና (አላህ ይወፍቀን)።

አስራ አምስተኛ ትምህርት: ለሁሉም ሙስሊም የተደነገጉ መልካም ስነምግባሮችን መላበስ

ከእነዚህም ውስጥ፡- እውነተኝነት፣ ታማኝነት፣ ጥብቅነት፣ አይነአፋርነት (ሐያእ)፣ ጀግንነት፣ ለጋሽነት፣ በቃል መገኘት፣ አላህ ከከለከለው ነገር ሁሉ መራቅ፣ ጉርብትናን ማሳመር፣ በተቻለ አቅም ሁሉ የተቸገረን መርዳት እና ሌሎችም ቁርኣን እና ሐዲሥ ውስጥ የተደነገጉ እና የተወሱ ስነምግባራት ይገኙበታል።

አስራ ስድስተኛ ትምህርት: በኢስላማዊ ስነስርአቶች መታነጽ

ከነርሱም መካከል: እስላማዊ ሰላምታን መለዋወጥ (አስሰላሙ ዐለይኩም ማለት እና ምላሹን መስጠት)፤ ለሰዎች ጥሩ ፈገግታ ማሳየት፤ በቀኝ መብላትና መጠጣት፤ ሲጀምሩ ቢስሚላህ ብሎ መጀመር ሲጨርሱ ደግሞ “አልሐምዱሊላህ” ማለት፤ በምናስነጥስበት ጊዜም አልሐምዱሊላህ ማለት፤ አስነጥሶ “አልሐምዱሊላህ” ላለ ሰው “የርሐሙከላህ” ማለት፤ የታመመን መጠየቅ፤ የሙስሊም አስክሬን ላይ ለመስገድና ለመቅበር ሲባል አስክሬኑን መከተል፤ መስጂድ ወይም ቤት ሲገባ እና ሲወጣ፣ ጉዞ ላይ፣ ከወላጆች፣ ከዘመዶች፣ ከጐረቤቶች በዕድሜ ከሚበልጡን ሰዎች ከታናናሾቻችን ጋር ኢስላማዊ ስርዓቶችን መጠበቅ፤ እንዲሁም የወለደን እንኳን ደስ አለህ ማለት፤ ላገባ ሰው በረካን መለመን (ባረከላሁ ለኩማ … ማለት) ፤ ችግር የደረሰበትን ሰው ማፅናናት፤ እንዲሁም ልብስ እና ጫማ በምንለብስበትና በምናወልቅበት ጊዜ ኢስላማዊ ስርዓቶችን መጠበቅ ይገባል።

አስራ ሰባተኛ ትምህርት: ከሺርክና ከወንጀል አይነቶች ሁሉ ማስጠንቀቅ

ከእነርሱም መካከል: ሰባቱ አጥፊ ወንጀሎች ይገኙበታል። እነርሱም፦ በአላህ ማጋራት፤ ድግምት፤ በሐቅና በፍትህ ካልሆነ በቀር አላህ መግደል ክልክል ያደረገውን ነፍስ መግደል፤ ወለድ ወይም አራጣ መብላት፤ የየቲምን ንብረት መብላት፤ በጂሀድ ጦርነት ወቅት ከጠላት ፊት ለፊት ገጥሞ ጦርነቱ ከተፋፋመ በኃላ መሸሽ፤ ከወንጀል የራቁ ጥብቅ ምዕመናትን በዝሙት መወንጀል ናቸው።

ከእነርሱም መካከል፡- ወላጅን መበደል (መጨቆን)፤ ዝምድናን መቁረጥ፤ በውሸት መመስከርና መማል፤ ጐረቤትን ማስቸገር፤ ሰዎችን በደማቸው፣ በንብረታቸውና በክብራቸው ላይ በደል ማድረስ፤ አስካሪ መጠጥ መጠጣት፤ ቁማር መጫወት፤ ሀሜት፤ ነገር ማሳበቅ እና ሌሎችም አላህ ወይም መልዕክተኛው (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) የከለከሉትን በሙሉ መራቅ ናቸው።

 

 

አስራ ስምንተኛ ትምህርት: ሟችን ለቀብር ማሰናዳት፣ በርሱ ላይ መስገድና መቅበር

ዝርዝሩም እንደሚከተለው ነው፦

በመጀመሪያ፡ ተልቂን (ማስደጋገም)፡ ጣዕረ ሞት ላይ የደረሰን ሰው “ላ ኢላሃ ኢለላህ” የሚለውን አርፍተ ነገር ደጋግሞ ማስባል በሸሪዓችን ተደንግጓል። ምክንያቱም ነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) እንዲህ ብለዋል፦

«لَقِّنُوا مَوْتَاكُمْ: لَا إِلَهَ إِلَّا اللَّهُ».

“ሙታኖቻችሁን ላኢላሃ ኢለላህ አስብሏቸው።”7 ሙስሊም በሶሒሓቸው ዘግበውታል። በዚህ ሐዲሥ ውስጥ "ሙታኖችን" በሚለው ቃል የተፈለገበት የሞት ምልክት የታየባቸው በጣዕረ ሞት ላይ ያሉ ሰዎችን ለማለት ነው።

ሁለተኛ: መሞቱ በተረጋገጠ ጊዜ ሁለት ዓይኖቹ ይጨፈናሉ፤ መንጋጭሎቹም እንዲጋጠሙ ይደረጋሉ። ምክንያቱም ይህ ተግባር በሱና ስለተረጋገጠ ነው።

ሶስተኛ: በጦር ሜዳ ፍልሚያ ላይ ሰማዕት (ሸሂድ) ከሆነ ሰው በስተቀር የሙስሊምን ሬሳ ማጠብ ግዴታ ይሆናል። ሰማዕት የሆነ ሰው አይታጠብም፤ ሰላትም አይሰገድበትም፤ የሚቀበረውም ከነልብሱ ነው። ምክንያቱም ነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) የኡሑድ ዘመቻ ላይ የተገደሉትን ሰማዕታት አላጠቡምም አልሰገዱባቸውምም።

አራተኛ: የሬሳ አስተጣጠብ፡

ሀፍረተ ገላው ይሸፈንና ከእራሱ በኩል ትንሽ ቀና ተደርጎ ሆዱን በቀስታ ጫን ይደረጋል። ቀጥሎ አጣቢው እጁን በጨርቅ ወይም በመሰል ነገር ይጠቀልልና ኢስቲንጃእ ያደርግለታል። ቀጥሎ ለሶላት እንደሚያደርገው ዉዱእ ያደርግለታል። ቀጥሎ ጭንቅላቱንና ፂሙን በውሃና በቁርቁራ ቅጠል ወይም በመሰል ነገር ያጥበዋል። ቀጥሎ ቀኝ ጎኑን ከዚያም ግራ ጎኑን ያጥባል። በዚህ መልኩ ለሁለተኛና ለሶስተኛ ጊዜ ያጥበዋል። በየሁሉም ትጥበት እጁን በሆዱ ላይ ጫን እያደረገ ያሳልፋል። ከሆዱም አንዳች ነገር ከወጣ ያጥበውና ቀዳዳውን በጥጥ ወይም በመሰል ነገር ይዘጋዋል። ይህም ሳይገድበው ከቀረ በስሚንቶ ነገር ወይም ፋሻና ፕላስተርን በመሰሉ የዘመናዊ ህክምና መሳሪያ ያስቆመዋል።

ዉዱእም ድጋሚ ያደርግለታል። በሶስት ትጥበት ካልፀዳ እስከ አምስት ወይም እስከ ሰባት ትጥበት ይጨምራል። ከዚያም በልብስ ያደራርቀዋል። መተጣጠፊያ እና የሱጁድ አካላቶቹ ላይ ሽቶ ያድርግለት። ሙሉ ሰውነቱን ሽቶ ከቀባውም ጥሩ ነው። ከፈኑ ላይ ዕጣን ያጭስበት። ቀድሞ ቀመሱ ወይም ጥፍሩ ከረዘሙ ይቁረጥለት። ሳይቆርጥ ቢተወውም ግን ችግር የለውም። ምንም ማስረጃ ስላልመጣበት ፀጉሩ አይበጠርም፣ የብልት ፀጉሩም አይላጭም፣ አይገረዝምም። ሴት ልጅ ፀጉሯ ለሶስት ተጎንጉኖ ወደ ኋላዋ ይለቀቃል።

አምስተኛ: ሟችን መከፈን

ወንድ ከሆነ ልክ ለነብያችን (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) እንደተደረገው ቀሚስና ጥምጣም በሌላቸው ሶስት ነጫጭ ጨርቆች መሆኑ በላጭ ነው። ተራ በተራ ይጠቀለልበታል። በቀሚስ፣ በሽርጥና ብትን በሆነ ጨርቅ ቢጠቀለልም ችግር የለውም።

ሴት ከሆነች ደግሞ በአምስት ጨርቆች ትጠቀለላለች፤ ማለትም በቀሚስ፣ በሻሽ፣ በአንድ ሽርጥና በሁለት ብትን ጨርቆች ነው። ወንድ ህጻን ከሆነ ከአንድ እስከ ሦስት ባሉ ብትን ጨርቆች ይጠቀለላል፤ ትንሽ ሴት ህጻን ከሆነች በቀሚስ እና በሁለት ብትን ጨርቆች ትጠቀለላለች።

ወንድም ሆነ ሴት ሲገነዙ መላ ሰውነትን ሊሸፍን በሚችል አንድ ብትን ጨርቅ መጠቅለላቸው ግዴታ ነው። ነገር ግን ሟች ሙሕሪም ሆኖ የሐጅና የዑምራ ተግባራትን እያከናወነ ባለበት ወቅት የሞተ ከሆነ በውሃና በቁርቁራ ይታጠብና እርሱ በነበረው ሽርጥና ኩታ ወይም ከዛ ውጭ ባለ ጨርቅ ይከፈናል። ሆኖም ግን ራሱንና ፊቱን አይሸፈንም፤ ሸቶም አይደረግለትም። ምክንያቱም ከአላህ መልክተኛ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) በመጣው ትክክለኛ ዘገባ የቂያማ ቀን ተልቢያ (ለብበይከ-ል-ላሁምመ ለበይክ ...) እያለ ይቀሰቀሳልና። በሐጅ ስነስርአት ላይ የሞተችው ሴት ከሆነች ደግሞ እንደሌሎች ሰዎች ትከፈናለች ነገር ግን ሽቶ አትቀባም፤ ፊቷም ኒቃብ አይሸፈንም፤ እጇም ጓንት አይለብስም፤ ነገር ግን የሚሸፈነው ከላይ ባሳለፍነው የሴት አገናነዝ መሰረት ፊቷም እጇም በተመሳሳይ ከፈን ይሆናል።

ስድስተኛ: ሬሳውን ለማጠብና ለመስገድ ቅድሚያ የሚሰጣው

ሬሳውን ለማጠብ በእርሱ ላይ ለመስገድና እርሱንም ለመቅበር ቅድሚያ የሚሰጣቸው ሰዎች በመጀመርያ ሟቹ የተናዘዘለት ሰው ነው። ከዚያም አባት፣ ከዚያም አያት፣ ከዚያም ጠቅላይ ቅርብ ወራሽ (ወንድም፣ አጐት፣ የወንድም ልጅ) ለሰውዬው እንዳላቸው ቅርበት መብት ይኖራቸዋል።

ሴትን በማጠብ ላይ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ደግሞ፦ በመጀመርያ የተናዘዘችላት ሴት፤ ከዚያም እናቷ ከዚያም ሴት አያቷ ከዚያም ሴት ዘመዶቿ እንደየቅርበታቸው ደረጃ ቅድሚያ ይሰጣቸዋል። ባልና ሚስት አንዱ ሌላውን ሊያጥብ ይችላል። ምክንያቱም አቡበከር ሲዲቅንም ባለቤታቸው ነች ያጠበቻቸው፤ እንዲሁም ዐሊይም ባለቤታቸው ፋጢማን አጥበዋልና።

 

ሰባተኛ: የሰላተል ጀናዛ አሰጋገድ

አራት ጊዜ ተክቢራ ያደርጋል፡ ከመጀመሪያ ተክቢራ በኋላ አል ፋቲሓ (የመክፈቻው ምዕራፍን) ያነባል፤ ከዚህም በተጨማሪ አጠር ያለ የቁርአን ምዕራፍ ወይም አንድ ወይም ሁለት አንቀፅ ቢቀራም ጥሩ ነው። ይህንን የተመለከተ ከዐብደላህ ኢብኑ ዐባስ የተዘገበ ትክክለኛ ሐዲሥ ስላለ ነው። ከዚያም ለሁለተኛ ጊዜ ተክቢራ ያደርጋል፤ ተሸሁድ ላይ ባለው መልኩ በነብዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ሰለዋት ያወርዳል። ከዚያም ሦስተኛውን ተክቢራ ካደረገ በኃላ እንዲህ ይላል፦ ("አልላሁምመ‐ጝፊር ሊሐዪና ወመዪቲና ወሻሂዲና ወጛኢቢና ወሶጚሪና ወከቢሪና ወዘከሪና ወኡንሣና፤ አልላሁምመ መን አሕየይተሁ ሚንና ፈአሕዪሂ ዐለል ኢስላም ወመን ተወፈይተሁ ሚንና ፈተወፈሁ ዐለል ኢማን፤ አልላሁምመ‐ጝፊር ለሁ ወርሓምሁ ወዓፊሂ ወዕፉ ዓንሁ ወአክሪም ኑዙለሁ ወወሲዕ ሙድኸለሁ ወጝሲልሁ ቢልማኢ ወሠልጂ ወልበረዲ ወነቂሂ ሚነልኸጣያ ከማ ዩነቀ አሥ-ሠውቡል አብየዹ ሚነ‐ድደነሲ፤ ወአብዲልሁ ዳረን ኸይረን ሚን ዳሪህ ወአህለን ኸይረን ሚን አህሊህ ወአድኺሉሁል‐ጀነተ ወአዒዝሁ ሚን ዓዛቢል ቀብሪ ወዓዛቢ ናር ወፍሰሕ ለሁ ፊ ቀብሪሂ ወነዊር ለሁ ፊህ አልላሁምመ ላተሕሪምና አጅረሁ ወላቱዲለና በዕደሁ።") (ትርጉሙም “አላህ ሆይ! በህይወት ያለነውንም፣ የሞቱብንም፣ በቅርብ ያለነውንም ሩቅ ያሉትንም፣ ትልልቆቻችንንም፣ ትንንሾቻችንንም፣ ወንዶቻችንንም፣ ሴቶቻችንንም ማርልን። አላህ ሆይ! ከመካከላችን የምታኖረውንም ኑሮውን በኢስላም አድርግለት፤ የምትገለውንም በእምነት ላይ እንዲሞት አድርገው። አላህ ሆይ! (ለሟቹ) ምህረት አድርግለት፤ እዘንለትም፤ (ከእሳት) ጠብቀው፤ ይቅርም በለውም፤ መስተንግዶውንም አሳምርለት፤ መግቢያውንም አስፋለት፤ ሀጢአቱንም በውሃ፤ በበረዶና በቀዝቃዛ ውሃ እጠብለት፤ ነጭ ልብስ ከቆሻሻ እንደሚፀዳው የእርሱንም ወንጀል አፅዳለት፤ ከቤቱ የተሻለ ቤት ከቤተሰቡ የተሻለ ቤተሰብን ተካለት። ወደ ጀነት አስገባው፣ ከቀብር ቅጣትና ከእሳት ቅጣትም ጠብቀው፤ ቀብሩንም አስፋለት አብራለትም። አላህ ሆይ! ምንዳውን አትንፈገን ከእርሱም በኋላ እጣችንን ጥመት አታድርግብን።") ከዚያም አራተኛውን ተክቢራ ካደረገ በኋላ በቀኝ በኩል ብቻ “አስሰላሙ ዐለይኩም” በማለት ያጠናቅቃል።

ከየሁሉም ተክቢራ ጋር ሁለት እጆቹን ከፍ ማድረጉ ይወደድለታል። ሟቿ ሴት ከሆነች "አላሁመ‐ግፊር ለሃ… " (አላህ ሆይ ለርሷ ማራት ..) ይባላል። ሬሳዎቹ ሁለት ከሆኑ ደግሞ "አላሁመ‐ግፊር ለሁማ… " (አላህ ሆይ ለነርሱ ማራቸው ...) ይባላል። ከዚህም የበዙ ከሆነ ደግሞ "አላሁመ‐ግፊር ለሁም… " (አላህ ሆይ ለነርሱ ማራቸው ...) ይባላል። ሟቹ ህፃን ልጅ ከሆነ ለርሱ ዱዓ ከማድረግ ይልቅ እንዲህ ይባላል: "አልላሁምመ ኢጅዐልሁ ፈረጠን ወዙኽረን ሊዋሊደይሂ ወሸፊዓን ሙጃበን አልላሁምመ ሠቂል ቢሂ መዋዚነሁማ ወአዕዚም ቢሂ ኡጁረሁማ ወአልሒቁሁ ቢሷሊሒ ሰለፊል ሙእሚኒን ወጅዐልሁ ፊ ከፋለቲ ኢብራሂመ ዐለይሂ አስሰላቱ ወስሰላም፤ ወቂሂ ቢራሕመቲከ ዓዛበል ጀሒም።" (ትርጉሙም፦ “አላህ ሆይ (አኼራ ላይ) ቀድሞ ሄዶ ለወላጆቹ የሚያመቻች፤ ለችግር ቀን አለኝታቸው፤ ተሰሚነት ያለው አማላጅ አድርግላቸው። አላህ ሆይ! የመልካም ስራቸው ሚዛን ማክበጃና የምንዳቸው ማጎልበቻ አድርግላቸው። ከደጋግ ምእመናን ጋርም አስጠጋው፤ ከነብዩ ኢብራሂም ዓለይሂ ሰላም እንክብካቤ ስርም አድርገው፤ በችሮታህም ከጀሐነም እሳት ጠብቀው።”)

ኢማሙ ሲያሰግድ ሟች ወንድ ከሆነ በጭንቅላቱ በኩል ሴት ከሆነች ደሞ በወገቧ ትይዩ መቆሙ ሱና ነው። ጀናዛዎች የበዙ ጊዜ ደግሞ ወንዱ ሬሳ በኢማሙ በኩል ሲሆን ሴቷ ሬሳ ደግሞ በቂብላው በኩል ትሆናለች። ከሬሳዎቹ መካከል ህፃን ካለ ደግሞ የህፃኑ ልጅ ሬሳ ከሴት ሬሳ (በሰውዬውና በሴትዮዋ መካከል) ይቀደማል። ከዚያም የሴቷ ሬሳ ትቀጥላለች ከዚያም የሴት ህፃን ሬሳ ትቀጥላለች። የወንድ ህፃን ሬሳ ጭንቅላቱም በትልቁ ወንድ ሬሳ ጭንቅላት ትይዩ ይደረጋል። የሴቷ ሬሳ ወገብም በወንዱ ሬሳ ጭንቅላት ትይዩ ይደረጋል። የሴቷ ህፃን ሬሳም በትልቋ ሴት ሬሳ ትይዩ ይደረጋል። የህፃኗም ወገብ በወንዱ ጭንቅላት ትይዩ ይደረጋል። ሰጋጆች ባጠቃላይ ከኢማሙ ኋላ ይሆናሉ። ነገር ግን ከኢማሙ ኋላ ቦታ ያላገኘ ሰው ከኢማሙ በቀኝ በኩል ይቆማል።

ስምንተኛ: የአስክሬን አቀባበር

በሸሪዓ የተደነገገው ቀብሩ ሲቆፈር የአንድ ሰው ግማሽ አካል ቁመት ያህል ወደታች ስምጥ ተደርጐ መቆፈር፤ መቃብሩ ውስጥም በቂብላ አቅጣጫ ገባ ብሎ የሚቆፈር ("ለሕድ") ማድረግ፤ ጀናዛውን (አስክሬኑን) ለሕድ ውስጥ በምናስገባበት ጊዜ በቀኝ ጐኑ አስተኝቶ የከፈኑን ቋጠሮ መፍታት፤ ከፈኑን ማውለቅ አይፈቀድም ይልቁንም በዛው ይተዋል። ሬሳው ወንድም ሆነ ሴት ፊቱ አይገለፅም፤ ከዚያም በጀርባው በኩል ብሎኬት ይደረደርና በጭቃ ተመርጎ አፈሩ እንዳይደረመስበት ይደረጋል። ብሎኬት ማግኘት ካልተቻለ የአፈር መደርመስን የሚከላከልለት ከርሱ ውጪ ባሉ እንደጣውላ ወይም ድንጋይ ወይም እንጨት ይደረግበታል። ከዚያም በላዩ ላይ አፈሩ ይመለስበታል። በዚህ ጊዜም {ቢስሚላህ ወዐላ ሚለቲ ረሱሊላህ} ይባላል። ትርጉሙም (በአላህ ስም በአላህ መልክተኛ መንገድ ላይ) ማለት ነው። ቀብሩ የስንዝር ያህል ከፍ ይደረጋል። ከተቻለ ቀብሩ ላይ ጠጠሮች ይደረግበትና ውሃ ማርከፍከፍ።

ለሸኚዎች መቃብሩ ዘንድ ቆመው ለሟቹ ዱዓ ማድረጋቸው በሸሪዓ የተደነገገ ነው። ይህም ነቢዩ(የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን)ሟችን ከቀበሩ በኋላ እርሱ ዘንድ ቆመው እንዲህ ይሉ ስለነበር ነው:-

 

«اسْتَغْفِرُوا لِأَخِيكُمْ، وَاسْأَلُوا لَهُ التَّثْبِيتَ، فَإِنَّهُ الْآنَ يُسْأَلُ».

“ለወንድማችሁ ምህረትን ጠይቁለት! እርሱ አሁን ይጠየቃልና ፅናትን ለምኑለት።”8

ዘጠነኛ: ያልሰገደበት ሰው ካለ ከተቀበረም በኋላ በርሱ ላይ መስገዱ በሸሪዓ የተደነገገ ነው።

ይህም ነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ስለተገበሩት ነው። ይህ ግን ከአንድ ወር ባነሰ ጊዜ መሆን አለበት። ጊዜው ከወር በላይ ከሆነ ቀብሩ ላይ መስገድ አይፈቀድም። ምክንያቱም ከነቢዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና ሟች ከተቀበረ ከወር በኋላ ለሟች መስገዳቸው አልመጣምና።

አስረኛ፡ የሟች ቤተሰቦች ሊያፅናኗቸው ለመጡ ሰዎች ምግብ ማዘጋጀት አይፈቀድላቸውም።

ይህም ታላቁ ሶሐባ ጀሪር ቢን ዐብደላህ አልበጀሊይ ረዲየሏሁ ዐንሁ - አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላቸውና - እንዲህ ስላሉ ነው:-

«كُنَّا نَعُدُّ الِاجْتِمَاعَ إِلَى أَهْلِ الْمَيِّتِ وَصَنْعَةَ الطَّعَامِ بَعْدَ الدَّفْنِ مِنَ النِّيَاحَة».

(ከቀብር በኋላ ሟች ቤተሰብ ዘንድ መሰብሰብና ምግብ ማዘገጀትን ሙሾ እንደማውረድ አድርገን እንቆጥረው ነበር።)9 ኢማሙ አሕመድ ሐሰን በሆነ ሰነድ ዘግበውታል። ነገር ግን ሌላ ሰው ለሟች ቤተሰቦች ወይም ለእንግዶቻቸው ምግብ ማዘጋጀቱ ችግር የለውም። የሟች ቅርብ ዘመዶችና ጎረቤቶች ለሟች ቤተሰቦች ምግብ ማዘጋጀታቸው በሸሪዓ የተደነገገ ነው። ይህም ነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ጀዕፈር ቢን አቢጧሊብ - አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላቸውና - ሻም ላይ እንደሞቱ ዜናው የደረሳቸው ጊዜ ቤተሰባቸው ለጀዕፈር ቤተሰቦች ምግብ እንዲያዘጋጁ እንዲህ ብለው አዘዋል:-

«إِنَّهُ أَتَاهُمْ مَا يَشْغَلُهُمْ».

"እነርሱ ምግብ ከማዘጋጀት ጊዜያቸውን የሚያጣብብ ነገር አጋጥሟቸዋል።"10

የሟች ቤተሰቦች ከሌሎች የመጣላቸውን ምግብ ጎረቤታቸውን ወይም ሌላን ሰው ጠርተው ማብላታቸው ችግር የለውም። ለዚህም እስከምናውቀው ድረስ በሸሪዓ የተቀመጠለት የጊዜ ገደብ የለውም።

 

 

 

አስራ አንደኛ: ሴት ልጅ ባሏ የሞተ ጊዜ ካልሆነ በቀር ለሟች ከሶስት ቀን በላይ ለቅሶ መቀመጥ አይፈቀድላትም።

በባሏ ለቅሶ ላይ ግን አራት ወር ከአስር ቀን የመቀመጥ ግዴታ አለባት። እርጉዝ ከሆነች ግን ፅንሷን በመውለዷ የለቅሶ ጊዜዋ ይጠናቀቃል። ይህም ሶሒሕ ሐዲሥ ከነቢዩ(የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ስለተዘገበ ነው።

ወንዶች ግን ለቅርብ ዘመድም ይሁን ለሌላ አካል ሞት ብለው ለቅሶ መቀመጥ አይፈቀድላቸውም።

አስራ ሁለተኛ: ወንዶች በፈለጉበት ወቅት መቃብር መዘየር፣ ለነርሱ ዱዓእ ማድረግ፣ ለነርሱ እዝነትን መለመንና ቀብርን በመዘየር ሞትንና ከሞት በኋላ ያለውን ህይወት ማስታወስ በሸሪዓ ተደንግጎላቸዋል።

ይህም ነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) እንዲህ ስላሉ ነው፦

«زُورُوا الْقُبُورَ، فَإِنَّهَا تُذَكِّرُكُمُ الْآخِرَةَ».

"መቃብርን ዘይሩ! እርሷ መጪውን አለም ታስታውሳችኋለችና።"11 ሙስሊም በሶሒሐቸው ዘግበውታል። ነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ሶሐቦቻቸው ቀብርን በዘየሩ ወቅት እንዲህ እንዲሉ ያስተምሯቸው ነበር:-

«السَّلَامُ عَلَيْكُمْ أَهْلَ الدِّيَارِ مِنَ الْمُؤْمِنِينَ وَالْمُسْلِمِينَ، وَإِنَّا إِنْ شَاءَ اللَّهُ بِكُمْ لَاحِقُونَ، نَسْأَلُ اللَّهَ لَنَا وَلَكُمُ الْعَافِيَةَ، يَرْحَمُ اللَّهُ الْمُتَقَدِّمِينَ مِنَّا وَالْمُسْتَأْخِرِينَ».

“አሰላሙ ዐለይኩም ያ አህለ ዲያር ሚነል ሙእሚኒነ ወልሙስሊሚን ወኢና ኢንሻአላሁ ቢኩም ላሒቁን ነስአሉላሀ ለኩም ወለና አል ዓፊያ የርሐሙላሁ አልሙተቀዲሚነ ሚና ወልሙስተእኺሪን።” (ትርጉሙም፦ በዚህ መቃብር ውሰጥ የምትገኙ ሙእሚኖችና ሙስሊሞች ሆይ ሰላም ይስፈንባችሁ! እኛም በአላህ ፈቃድ እንከተላችኋለን፤ ለእኛም ለእናንተም ከአላህ ዘንድ ደህንነትን እንጠይቃለን፤ ከመካከላችን ለተቀደሙትም ወደ ኋላ ለቀሩትም አላህ ምህረትን ይለግሳቸው።)12 ሴቶች ግን ቀብርን ሊዘይሩ አይፈቀድላቸውም። ምክንያቱም የአላህ መልዕክተኛ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ቀብርን የሚጐበኙ ሴቶችን ረግመዋልና፤ የዚህም ሰበብ ቀብር በሚጐበኙበት ጊዜ ፈተናና ትግስት ማጣት ስለሚፈራላቸው ነው። እንደዚሁም እስከ ቀብር ድረስ ሬሳን መሸኘትም አይፈቀድላቸውም። ይህም የአላህ መልዕክተኛ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ይህንን ተግባር ስለከለከሉ ነው። መስጂድ ውስጥ ወይም በሚሰገድበት ቦታ ተገኝቶ ሟች ላይ መስገድ ግን ለወንድም ሆነ ለሴት የተፈቀደ ነው።

ይህ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ለማካተት ለተሞከረው ማጠናቀቂያ ነው። የአላህ ሰላትና ሰላም በነቢያችን ሙሐመድ በቤተሰባቸው እና በባልደረቦቹም ላይ ሁሉ ይስፈን።

 

 

***

ማውጫ

 

በአላህ ስም እጅግ በጣም ርህሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው 2

የጸሐፊው መግቢያ 2

የመጀመሪያው ትምህርት ሱረቱል ፋቲሓ (የመክፈቻ ምዕራፍ) እና አጫጭር ሱራዎች 3

ሁለተኛ ትምህርት: የእስልምና ማዕዘናት 3

ሶስተኛ ትምህርት: የኢማን ማዕዘናት 4

አራተኛው ትምህርት: የተውሒድ እና የሺርክ ክፍሎች 5

አምስተኛው ትምህርት: ኢሕሳን (በጎ ማድረግ) 11

ስድስተኛው ትምህርት: የሶላት መስፈርቶች 12

ሰባተኛው ትምህርት: የሶላት ማዕዘናት 12

ስምንተኛው ትምህርት: የሶላት ዋጂቦች (ግዴታዎች) 13

ዘጠነኛው ትምህርት: የተሸሁድ ማብራሪያ 13

አስረኛ ትምህርት: የሶላት ሱናዎች 15

አስራ አንደኛ ትምህርት: ሶላትን የሚያበላሹ ነገሮች 18

አስራ ሁለተኛ ትምህርት: የዉዱእ ቅድመ መስፈርቶች (ሸርጦች) 19

አስራ ሶስተኛ ትምህርት: የዉዱእ ግዴታዎች 19

አስራ አራተኛ ትምህርት: ዉዱእን የሚያበላሹ ነገሮች 20

አስራ አምስተኛ ትምህርት: ለሁሉም ሙስሊም የተደነገጉ መልካም ስነምግባሮችን መላበስ 22

አስራ ስድስተኛ ትምህርት: በኢስላማዊ ስነስርአቶች መታነጽ 22

አስራ ሰባተኛ ትምህርት: ከሺርክና ከወንጀል አይነቶች ሁሉ ማስጠንቀቅ 23

አስራ ስምንተኛ ትምህርት: ሟችን ለቀብር ማሰናዳት፣ በርሱ ላይ መስገድና መቅበር 24

ሁለተኛ: መሞቱ በተረጋገጠ ጊዜ ሁለት ዓይኖቹ ይጨፈናሉ፤ መንጋጭሎቹም እንዲጋጠሙ ይደረጋሉ። ምክንያቱም ይህ ተግባር በሱና ስለተረጋገጠ ነው። 24

ሶስተኛ: በጦር ሜዳ ፍልሚያ ላይ ሰማዕት (ሸሂድ) ከሆነ ሰው በስተቀር የሙስሊምን ሬሳ ማጠብ ግዴታ ይሆናል። ሰማዕት የሆነ ሰው አይታጠብም፤ ሰላትም አይሰገድበትም፤ የሚቀበረውም ከነልብሱ ነው። ምክንያቱም ነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) የኡሑድ ዘመቻ ላይ የተገደሉትን ሰማዕታት አላጠቡምም አልሰገዱባቸውምም። 24

አራተኛ: የሬሳ አስተጣጠብ፡ 25

አምስተኛ: ሟችን መከፈን 26

ስድስተኛ: ሬሳውን ለማጠብና ለመስገድ ቅድሚያ የሚሰጣው 27

ሰባተኛ: የሰላተል ጀናዛ አሰጋገድ 28

ስምንተኛ: የአስክሬን አቀባበር 31

ዘጠነኛ: ያልሰገደበት ሰው ካለ ከተቀበረም በኋላ በርሱ ላይ መስገዱ በሸሪዓ የተደነገገ ነው። 32

አስረኛ፡ የሟች ቤተሰቦች ሊያፅናኗቸው ለመጡ ሰዎች ምግብ ማዘጋጀት አይፈቀድላቸውም። 32

አስራ አንደኛ: ሴት ልጅ ባሏ የሞተ ጊዜ ካልሆነ በቀር ለሟች ከሶስት ቀን በላይ ለቅሶ መቀመጥ አይፈቀድላትም። 34

አስራ ሁለተኛ: ወንዶች በፈለጉበት ወቅት መቃብር መዘየር፣ ለነርሱ ዱዓእ ማድረግ፣ ለነርሱ እዝነትን መለመንና ቀብርን በመዘየር ሞትንና ከሞት በኋላ ያለውን ህይወት ማስታወስ በሸሪዓ ተደንግጎላቸዋል። 34

***

 

 

am62v2.0 - 24/06/2026


ኢማም አሕመድ በ(5/428) ፣ ጦበራኒ በ "አልከቢር" (4/338)፣ በይሃቂይ "አሽሺዕብ" በሚለው መፅሀፍ በ(14/355) ላይ ዘግበውታል። በመጅመዑ-ዝዘዋኢድ (1/121) ላይ አሕመድ ዘግበውታል። እርሳቸው የዘገቡት ሰነድ ላይ ያሉ ዘጋቢዎችም ታማኝ ናቸው።" ብለዋል።

ኢማም አህመድ በ(1/47) ዘግበውታል።

አቡ ዳውድ በቁጥር (3251) ላይ ቲርሚዚይም በቁጥር (1535) ላይ ዘግበውታል።

አቡ ዳውድ በቁጥር (4980) ላይና አሕመድ በ(5/384) ዘግበውታል።

ኢብኑ ማጃህ በቁጥር (4204) ላይ ኢማሙ አሕመድ በ(3/30) ላይ ዘግበውታል።

ሙስሊም በቁጥር (916 - 917) ዘግበውታል።

አቡ ዳውድ በቁጥር (3221) ላይ ሓኪም በ(3/399) ላይ ዘግበውታል።

ኢብኑ ማጃህ በቁጥር (1612) ላይ ኢማሙ አሕመድ በ(2/204) ላይ ዘግበውታል።

ሙስሊም በጀናኢዝ (976)፣ ነሳኢይ በጀናኢዝ (2034)፣ አቡዳውድ በጀናኢዝ (3234)፣ ኢብኑ ማጀህ በጀናኢዝ (1569)፣ አሕመድ በ(2/441) ዘግበውታል።

ኢብኑ ማጃህ በቁጥር (1569) ላይ ዘግበውታል። አልባኒም ሶሒሕ ብለውታል።

ሙስሊም በቁጥር (975) ዘግበውታል።

መጅሙዑ ፈታዋ ወመቃላቲን ሙተነዊዓህ (3/288 - 298)