PHPWord

 

 

التَّحْذِيرُ مِنَ البِدَعِ

 

 

ከቢድዓ ማስጠንቀቂያ

 

 

 

 

 

 

لِسَمَاحَةِ الشَّيْخِ العَلَّامَةِ

عَبْدِ العَزِيزِ بْنِ عَبْدِ اللهِ بْنِ بَازٍ

رَحِمَهُ اللهُ

 

ዝግጅት፦ የተከበሩ ሸይኽ

ዐብዱልዐዚዝ ቢን ዐብደላህ ቢን ባዝ

 

 

 


بِسْمِ اللهِ الرَّحمَنِ الرَّحِيمِ

አምስተኛው መልዕክት፡

የነብዩን ﷺ መውሊድና ሌሎች መውሊዶችን የማክበር ብይን

ምስጋና ሁሉ ለአላህ የተገባ ነው። የአላህ ሰላትና ሰላም በአላህ መልእክተኛ፣ በቤተሰቦቻቸውና በባልደረቦቻቸው እንዲሁም የእርሳቸውን ቅን ጎዳና በተከተለም ላይ ሁሉ ይስፈን።

ከዚህ በመቀጠል፡- የነብዩን ﷺ ልደት (መውሊድ) ስለማክበር፣ በዝግጅቱ ላይ ለርሳቸው መቆም፣ በርሳቸው ላይ ሰላምታ ማቅረብ እና በመውሊዶች ላይ የሚፈፀሙ ሌሎች መሰል ድርጊቶች ብይንን በተመለከተ ከብዙዎች ዘንድ ጥያቄ ተደጋግሞ ቀርቧል።

መልሱም እንዲህ የሚል ነው፡ የመልክተኛውን ﷺ ልደት (መውሊድ) ማክበርም ሆነ የሌላን ማክበር አይፈቀድም፤ ምክንያቱም ይህ በዲን ውስጥ አዲስ መጤ (ቢድዓ) ነውና፤ መልክተኛው ﷺ እና ቅን የሆኑ ኸሊፋዎቻቸው፣ ሌሎችም ሶሓቦች (አላህ ስራቸውን ይውደድላቸውና) እንዲሁም በበላጭ ክፍለ ዘመናት ውስጥ በመልካም የተከተሏቸው ታቢዒዮችም አልሰሩትም። እነርሱም ከነሱ በኋላ ከመጡት ሰዎች ይልቅ ሱናን በበለጠ የሚያውቁ፣ ለመልክተኛው (ሶለሏሁ ዐለይሂ ወሰለም) ያላቸው ፍቅርም የተሟላ እንዲሁም ሸሪዓውን በመከተል የላቁ ነበሩ። ጥራት ይገባውና የላቀው አላህ ግልፅ በሆነው ቁርኣን ውስጥ እንዲህ ብሏል፦

﴿...وَمَآ ءَاتَىٰكُمُ ٱلرَّسُولُ فَخُذُوهُ وَمَا نَهَىٰكُمۡ عَنۡهُ فَٱنتَهُواْ...﴾

{…መልዕክተኛው የሰጣችሁን ማንኛዉንም ነገር ያዙት፤ ከእርሱም የከለከላችሁን ነገር ሁሉም ተከልከሉ።…}

[አል-ሐሽር፡ 7] ግርማው የላቀው አላህ እንዲህ ብሏል፦

﴿...فَلۡيَحۡذَرِ ٱلَّذِينَ يُخَالِفُونَ عَنۡ أَمۡرِهِۦٓ أَن تُصِيبَهُمۡ فِتۡنَةٌ أَوۡ يُصِيبَهُمۡ عَذَابٌ أَلِيمٌ﴾

{…እነዚያም ትእዛዙን የሚጥሱ መከራ እንዳትደርስባቸው ወይም አሳማሚ ቅጣት እንዳያገኛቸው ይጠንቀቁ::} [አን-ኑር፡ 63] ጥራት የተገባው አላህ እንዲህም ብሏል፡

﴿لَّقَدۡ كَانَ لَكُمۡ فِي رَسُولِ ٱللَّهِ أُسۡوَةٌ حَسَنَةٞ لِّمَن كَانَ يَرۡجُواْ ٱللَّهَ وَٱلۡيَوۡمَ ٱلۡأٓخِرَ وَذَكَرَ ٱللَّهَ كَثِيرٗا21﴾

{ለእናንተ አላህንና የመጨረሻውን ቀን የሚከጅል ለሆነ ሰው፣ አላህንም በብዙ ለሚያወሳ በአላህ መልዕክተኛ መልካም መከተል አልላችሁ::} [አልአሕዛብ፡ 21] ጥራት የተገባው አላህ እንዲህም ብሏል፡

﴿وَٱلسَّٰبِقُونَ ٱلۡأَوَّلُونَ مِنَ ٱلۡمُهَٰجِرِينَ وَٱلۡأَنصَارِ وَٱلَّذِينَ ٱتَّبَعُوهُم بِإِحۡسَٰنٖ رَّضِيَ ٱللَّهُ عَنۡهُمۡ وَرَضُواْ عَنۡهُ وَأَعَدَّ لَهُمۡ جَنَّٰتٖ تَجۡرِي تَحۡتَهَا ٱلۡأَنۡهَٰرُ خَٰلِدِينَ فِيهَآ أَبَدٗاۚ ذَٰلِكَ ٱلۡفَوۡزُ ٱلۡعَظِيمُ100﴾

{ከስደተኞቹና ከረዳቶቹም ሲሆኑ የመጀመሪያዎቹ ቀዳሚዎች እነዚያም በበጎ ሥራ የተከተሏቸው አላህ ከእነሱ ወዷል:: ከእርሱም ወደዋል:: በሥሮቻቸውም ወንዞች የሚፈሱባቸውን ገነቶች በውስጣቸዉም ዘለዓለም ነዋሪዎች ሲሆኑ ለእነርሱ አዘጋጅቶላቸዋል:: ይህ ታላቅ እድል ነው::} [አት-ተውባህ: 100] የላቀው አላህ እንዲህም ብሏል፡

﴿...ٱلۡيَوۡمَ أَكۡمَلۡتُ لَكُمۡ دِينَكُمۡ وَأَتۡمَمۡتُ عَلَيۡكُمۡ نِعۡمَتِي وَرَضِيتُ لَكُمُ ٱلۡإِسۡلَٰمَ دِينٗا...﴾

{…ዛሬ ሃይማኖታችሁን ሞላሁላችሁ:: ጸጋየንም በእናንተ ላይ ፈጸምኩ:: ለእናንተም በሃይማኖትነት ኢስላምን ወደድኩላችሁ::…} [አል‐ማኢዳህ: 3] በዚህ ዙሪያ የመጡ ቁርአናዊ ማስረጃዎች በርካታ ናቸው። ነቢዩም ﷺ እንዲህ ማለታቸው ተረጋግጧል፦

«مَنْ أَحْدَثَ فِي أَمْرِنَا هَذَا مَا لَيْسَ مِنهُ فَهُوَ رَدٌّ».

"በዚህ ሃይማኖታችን ውስጥ ከእርሱ ያልሆነን አዲስ ነገር ያመጣ ሰው እርሱ ውድቅ ነው።" ማለትም፦ በእርሱ ላይ ተመላሽ ነው። በሌላ ሐዲሥ እንዲህ ብለዋል:

«عَلَيكُم بِسُنَّتِي وَسُنَّةِ الخُلَفَاءِ الرَّاشِدِينَ المَهْدِيَّينَ مِنْ بَعدِي، تَمَسَّكُوا بِهَا، وَعَضُّوا عَلَيهَا بِالنَّوَاجِذِ، وَإِيَّاكُمْ وَمُحْدَثَاتِ الأُمُورِ، فَإِنَّ كُلَّ مُحْدَثَةٍ بِدْعَةٌ وَكُلَّ بِدْعَةٍ ضَلَالةٌ».

«በኔ እና ከኔ በኋላ ባሉት የተመሩ ቅን በሆኑት ምትኮቼ ሱና አደራችሁን! እርሷን አጥብቃችሁ ያዟት፤ በመንጋጋ ጥርሳችሁም ነክሳችሁ ያዟት። አደራችሁን አዳዲስ መጤ ነገሮችን ተጠንቀቁ! አዲስ መጤ ነገር ሁሉ ቢድዓ ነውና፤ ሁሉም ቢድዓ ደግሞ ጥመት ነው።» እናም በነዚህ ሁለት ሐዲሦች ውስጥ ቢድዓዎችን ከመፈብረክና ቢድዓን በመስራት ላይ ብርቱ ማስጠንቀቂያ አለ።

እንዲህ አይነት መውሊዶችን መፈብረካቸው "ኋላ ላይ ዘግይተው የመጡ ሰዎች ይህንን አላህ ያልፈቀደውን የአላህ ድንጋጌ ወደ አላህ ያቃርበናል በሚል ሙግት እስኪፈበርኩ ድረስ አላህ ለዚህ ህዝብ ሃይማኖቱን ሙሉ አላደረገም፣ መልክተኛውም (ዐለይሂ ሶላቱ ወሰላም) ኡመታቸው ሊሰራበት የሚገባውን ነገር አላደረሱም" ማለታቸውን ያስይዛል። ይህም ያለጥርጥር ታላቅ አደጋና በላቀው አላህ እንዲሁም በመልዕክተኛው ﷺ ላይ መቃወም ነው። የላቀው አላህ ለባሮቹ ሃይማኖቱን አሟልቶላቸዋል፤ ፀጋውንም በእነርሱ ላይ ሙሉ አድርጓል። መልዕክተኛውም ﷺ ግልፅ የሆነውን መልእክት አድርሰዋል። ወደ ጀነት የሚያደርስና ከእሳት የሚያርቅ የትኛውንም መንገድ ለህዝባቸው ግልፅ አድርገው እንጂ አልተዉም። ከዐብደላህ ኢብኑ ዐምር (አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና) በተዘገበ ሶሒሕ ሐዲስ ላይ እንደተረጋገጠው እንዲህ ብለዋል፦ የአላህ መልዕክተኛ ﷺ እንዲህ ብለዋል፦

«مَا بَعَثَ اللهُ مِن نَبِيٍ إِلَّا كَانَ حَقًّا عَلَيهِ أَن يَدُلَّ أُمَّتَهُ عَلَى خَيرِ مَا يَعْلَمُهُ لَهُم، وَيُنْذِرَهُمْ شَرَّ مَا يَعْلَمُهُ لَهُمْ».

«አላህ አንድንም ነቢይ ሕዝቡን ወደሚያውቅላቸው መልካም ነገር እንዲመራቸውና ከሚያውቅላቸው ክፉ ነገር እንዲያስጠነቅቃቸው ግዴታው ተደርጎ እንጂ አልላከም፡፡» ሙስሊም በሰሒሓቸው ዘግበውታል።

እንደሚታወቀው ነቢያችን ﷺ ከነቢያት ሁሉ በላጭና መደምደሚያቸውም ናቸው፤ መልእክትን በማድረስና ህዝባቸውን በመምከርም ከማንም በላይ የተሟሉ ናቸው። መውሊድን ማክበር አላህ ከሚወደው ዲን ቢሆን ኖሮ፤ መልእክተኛው (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ለህዝባቸው በገለፁት ነበር፤ ወይም እርሳቸው በህይወታቸው በሰሩት ነበር፤ ወይም ሰሓቦቻቸው (ረዲየላሁ ዐንሁም) በሰሩት ነበር። ከዚህ መካከል አንዳቸውም ነገር ስላልተከሰተ ይህ ከእስልምና ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለው ይታወቃል። ይልቁንም መልእክተኛው (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ህዝባቸውን ካስጠነቀቁባቸው መጤ ነገሮች (ቢድዓ) ውስጥ የሚካተት ነው። ይህም ቀደም ብሎ በሐዲሶች ላይ እንደተገለፀው ነው። በዚህ ዙሪያ የመጡ የቁርኣን አንቀጾችና ሐዲሶች በርካታ ናቸው።

በርካታ ዑለማዎች የተጠቀሱትንና ሌሎችንም ማስረጃዎች መሰረት በማድረግ መውሊድን አውግዘዋል፤ ከእርሱም አስጠንቅቀዋል። ኋላ ላይ የመጡት ከፊሎች ግን በተቃራኒ የአላህ መልዕክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ላይ ድንበር ማለፍ፣ የሴቶችና የወንዶች መቀላቀል፣ የመዝናኛ መሳርያዎችን መጠቀም እና የመሳሰሉ ንጹሑ ሸሪዓ የሚያወግዛቸውን መጥፎ ነገሮች እስካላካተተ ድረስ ይፈቀዳል ብለዋል። ከመልካም ቢድዓዎች መካከል እንደሆነም አስበዋል።

ሸሪዓዊው መርህ ሰዎች የሚከራከሩበትን ነገር ወደ አላህ ኪታብና ወደ መልዕክተኛው ሙሐመድ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ሱና መመለስ ነው፤ ታላቅና ከፍ ያለው አላህም እንዲህ ብሏል፦

﴿يَٰٓأَيُّهَا ٱلَّذِينَ ءَامَنُوٓاْ أَطِيعُواْ ٱللَّهَ وَأَطِيعُواْ ٱلرَّسُولَ وَأُوْلِي ٱلۡأَمۡرِ مِنكُمۡۖ فَإِن تَنَٰزَعۡتُمۡ فِي شَيۡءٖ فَرُدُّوهُ إِلَى ٱللَّهِ وَٱلرَّسُولِ إِن كُنتُمۡ تُؤۡمِنُونَ بِٱللَّهِ وَٱلۡيَوۡمِ ٱلۡأٓخِرِۚ ذَٰلِكَ خَيۡرٞ وَأَحۡسَنُ تَأۡوِيلًا59﴾

{እናንተ ያመናችሁ ሆይ! አላህን ታዘዙ:: መልዕክተኛውን እና ከመካከላችሁም የስልጣን ባለቤቶችን ታዘዙ:: በማንኛዉም ነገር ብትከራከሩም በአላህና በመጨረሻው ቀን የምታምኑ ከሆናችሁ የተከራከራችሁበትን ነገር ወደ አላህና ወደ መልዕክተኛው መልሱት:: ይህ የተሻለ እና መጨረሻዉም ያማረ ነው::} [አን-ኒሳእ፡ 59] ጥራት ይገባውና እንዲህም ብሏል፡

﴿وَمَا ٱخۡتَلَفۡتُمۡ فِيهِ مِن شَيۡءٖ فَحُكۡمُهُۥٓ إِلَى ٱللَّهِ ...﴾

{«ያ የተለያያችሁበት ነገር ሁሉ ፍርዱ ወደ አላህ ብቻ ነው...»} [አሽ ሹራ፡ 10]

ይህንን የመውሊድ ክብረ በዓልን የማክበር ጉዳይ ጥራት ወደተገባው የአላህ መጽሐፍ መልሰነዋል፤ መጽሐፉም ረሱልን (የአላህ ሶላትና ሰላም በርሳቸው ላይ ይስፈንና) ይዘውት በመጡት ነገር እንድንከተል ሲያዘንና ከከለከሉን ነገርም ሲያስጠነቅቀን፣ እንዲሁም ጥራት የተገባው አላህ ለዚህች ህዝብ ሀይማኖቷን እንዳሟላላት ሲነግረን አግኝተነዋል። ይህ ክብረ በዓል ረሱል (የአላህ ሶላትና ሰላም በርሳቸው ላይ ይስፈንና) ይዘውት ከመጡት ነገሮች አይደለም፤ ስለሆነም አላህ ለኛ ካሟላልንና መልክተኛውንም እንድንከተልበት ካዘዘን ሀይማኖት ውስጥ የሚካተት አይደለም።

ይህንን ጉዳይ ወደ መልእክተኛው (የአላህ ሶላትና ሰላም በርሳቸው ላይ ይስፈንና) ሱና ስንመልሰው፤ እርሳቸው የሰሩትም ሆነ ያዘዙበት፣ እንዲሁም ሶሓቦቻቸው የሰሩት ሆኖ አላገኘንም። በዚህም ከዲን አለመሆኑን፤ ይልቁንም አዲስ መጤ ፈጠራ እና በበዓላቶቻቸው ከየሁዶችና ከክርስቲያኖች ጋር መመሳሰል መሆኑን አውቀናል።

በዚህም አነስተኛ ግንዛቤ ላለው፣ እውነትን ለሚከጅልና በፍለጋውም ሚዛናዊ ለሆነ ማንኛውም ሰው፤ መውሊድን ማክበር ከእስልምና ዲን እንዳልሆነ፣ ይልቁንም አላህ እና መልዕክተኛው (የአላህ ሶላትና ሰላም በርሳቸው ላይ ይስፈንና) ልንተዋቸውና ልንጠነቀቃቸው ካዘዙን አዲስ መጤ ቢድዓዎች መካከል መሆኑ ግልፅ ይሆንለታል። አእምሮ ያለው ሰው በተለያዩ ሀገራት አንድን ድርጊት በሚፈፅሙ ሰዎች ብዛት ሊታለል አይገባውም። እውነት የሚታወቀው በፈፃሚዎቹ ብዛት ሳይሆን በሸሪዓዊ ማስረጃዎች ነውና። የላቀው አላህ ስለ አይሁዶችና ነሷራዎች እንዲህ ብሏል፦

﴿وَقَالُواْ لَن يَدۡخُلَ ٱلۡجَنَّةَ إِلَّا مَن كَانَ هُودًا أَوۡ نَصَٰرَىٰۗ تِلۡكَ أَمَانِيُّهُمۡۗ قُلۡ هَاتُواْ بُرۡهَٰنَكُمۡ إِن كُنتُمۡ صَٰدِقِينَ111﴾

{«ጀነትን አይሁድ ወይም ክርስቲያኖች የሆነ እንጂ ሌላ አይገባትም።» አሉ:: «ይህች ከንቱ ምኞታቸው ናት:: (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) እውነተኞች እንደሆናችሁ እስቲ ማስረጃችሁን አምጡ።» በላቸው።} [አል-በቀራህ፡ 111] ጥራት የተገባው አላህ እንዲህም ብሏል፡

﴿وَإِنْ تُطِعْ أَكْثَرَ مَنْ فِي الْأَرْضِ يُضِلُّوكَ عَنْ سَبِيلِ اللَّهِ...﴾

{(መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) በምድር ካሉት መካከል አብዛኞቹን ብትከተል የአላህን መንገድ ያሳስቱሀል::} [አል‐አንዓም: 116]

ከዚያም አብዛኛዎቹ እነዚህ የመውሊድ ክብረ በዓላት ቢድዓ ከመሆናቸውም ጋር ሌሎች ውግዝ ተግባራትን ከመያዝ የጸዱ አይደሉም፤ እንደ የሴቶችና የወንዶች መቀላቀል፣ የዘፈንና የሙዚቃ መሳሪያዎችን መጠቀም፣ አስካሪ መጠጦችንና አደንዛዥ እፆችን መጠቀም እና ሌሎችም መሰል መጥፎ ተግባሮችን አካተዋል። ከዚህም የባሰ ነገር ሊከሰት ይችላል፤ እርሱም ትልቁ ሺርክ ነው። ይህም በአላህ መልክተኛ (የአላህ ሶላትና ሰላም በርሳቸው ላይ ይስፈንና) ወይም ከእርሳቸው ውጭ ባሉ ወልዮች ላይ ድንበር በማለፍ፣ እነርሱን በመማጸን፣ በእነርሱ እገዛን በመጠየቅ፣ ረድኤትን ከእነርሱ በመፈለግ፣ የተሰወረውን ነገር ያውቃሉ ብሎ በማመን እና የመሳሰሉትን የክህደት ተግባራት መፈጸም ነው። ብዙ ሰዎች እነዚህን የክህደት ተግባራት የሚፈፅሙት የነብዩን (የአላህ ሶላትና ሰላም በርሳቸው ላይ ይስፈንና) የልደት በዓል (መውሊድ) ወይም ‘ወልዮች’ ብለው የሚጠሯቸውን ሲያከብሩ ነው። የአላህ መልክተኛም (የአላህ ሶላትና ሰላም በርሳቸው ላይ ይስፈንና) እንዲህ ማለታቸው ተረጋግጧል፦

«إِيَّاكُم وَالغُلُوُّ فِي الدِّينِ، فَإِنَّمَا أَهْلَكَ مَن كَانَ قَبْلَكُم الغُلُوَّ فِي الدِّينِ».

"በሃይማኖት ላይ ወሰን ከማለፍ ተጠንቀቁ! ከናንተ በፊት የነበሩትን ያጠፋቸው በሃይማኖት ላይ ወሰን ማለፍ ነውና።" እንዲህም ብለዋል፦

«لَا تُطْرُونِي كَمَا أَطْرَتِ النَّصَارَى ابْنَ مَرْيَمَ، إِنَّمَا أَنَا عَبدٌ، فَقُولُوا: عَبدُ اللهِ وَرَسُولُه».

“ክርስቲያኖች የመርየም ልጅን እንዳጋነኑት እኔን አታጋንኑኝ፤ እኔ ባሪያ ብቻ ነኝ። ስለዚህ ‘የአላህ ባሪያና መልክተኛው’ በሉኝ።” ቡኻሪይ በሶሒሐቸው ላይ ከዑመር ረዲየላሁ ዐንሁ ዘግበውታል።

ከሚያስደንቁና ከሚያስገርሙ ጉዳዮች መካከል ብዙ ሰዎች በእነዚህ የተፈበረኩ የቢድዓ ዝግጅቶች ላይ ለመገኘት ሲነቃቁና ሲተጉ እንዲሁም ሲከላከሉላቸው፤ በሌላ በኩል ግን አላህ ግዴታ ካደረገባቸው ከጁሙዓና ከጀመዓ ሰላቶች ይቀራሉ። ለዚህም ምንም ትኩረት አይሰጡትም፤ ታላቅ የሆነን የተወገዘ ድርጊት እንደፈፀሙም አድርገው አያዩትም። ይህ ደግሞ የኢማን ድክመት፣ የማስተዋል ማነስ እና በልቦቻቸው ላይ ከተደራረቡት የተለያዩ ወንጀሎችና ኃጢአቶች ብዛት የመነጨ መሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም። አላህን ለእኛም ሆነ ለመላው ሙስሊሞች ዐፊያ እንዲሰጠን እንለምነዋለን።

ከዚህም ውስጥ ከፊሎቹ የአላህ መልዕክተኛ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) በመውሊድ ላይ እንደሚገኙ ማሰባቸው ነው። ለዚህም ነው ሰላምታ እያቀረቡና እንኳን ደህና መጡ እያሉ ለእርሳቸው የሚቆሙት። ይህ ደግሞ ከታላላቅ ውድቅ ነገሮች እና እጅግ አስቀያሚ ድንቁርና ነው። ምክንያቱም መልዕክተኛው (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ከትንሳኤ ቀን በፊት ከቀብራቸው አይወጡም። ከየትኛውም ሰው ጋር ግንኙነት አይፈጥሩም፤ በስብሰባዎቻቸው ላይም አይገኙም። ይልቁንም እስከ ትንሳኤ ቀን ድረስ በቀብራቸው ውስጥ የጸኑ ናቸው። ነፍሳቸው ደግሞ ከጌታቸው ዘንድ በክብር አገር በአዕላ ዒልዪን ውስጥ ናት። የላቀው አላህ እንዲህ እንዳለው፦

﴿ثُمَّ إِنَّكُمْ بَعْدَ ذَلِكَ لَمَيِّتُونَ15 ثُمَّ إِنَّكُمْ يَوْمَ الْقِيَامَةِ تُبْعَثُونَ16﴾

{(ሰዎች ሆይ!) ከዚያም እናንተ ከዚህ በኋላ በእርግጥ ሟቾች ናችሁ::

ከዚያም እናንተ በትንሳኤ ዕለት ትቀሰቀሳላችሁ::} [አል-ሙእሚኑን፡ 15-16]

ነብዩም የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን እንዲህ ብለዋል፦

«أَنَا أَوَّلُ مَنْ يَنْشَقُّ عَنْهُ القَبْرُ يَومَ القِيَامَةِ، وَأَنَا أَوَّلُ شَافِعٍ، وَأَوَّلُ مُشَفَّعٍ».

«እኔ የትንሳኤ ቀን ቀብሩ የሚሰነጠቅለት የመጀመሪያው ነኝ፤ እኔም የመጀመሪያው አማላጅና የመጀመሪያውም አማላጅ ተደራጊ ነኝ።» የጌታችን በላጩ ሰላምና እዝነት በርሳቸው ላይ ይስፈን።

እነዚህ ሁለት የተከበሩ አንቀጾች፣ የተከበረው ሐዲስ፣ እንዲሁም በይዘታቸው ተመሳሳይ የሆኑ ሌሎች አንቀጾችና ሐዲሶች ሁሉም የሚያመለክቱት ነቢዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) እና ሌሎችም ሙታን ከመቃብራቸው የሚወጡት በትንሳኤው ቀን መሆኑን ነው። ይህም በሙስሊም ሊቃውንት መካከል ስምምነት የተደረሰበትና በመካከላቸውም ምንም አይነት ውዝግብ የሌለበት ጉዳይ ነው፡፡ በመሆኑም እያንዳንዱ ሙስሊም እነዚህን ጉዳዮች ሊገነዘብ፣ እንዲሁም ጃሂሎችና መሰሎቻቸው ካመጧቸውና አላህ በርሷ ላይ ምንም ማስረጃ ካላወረደባቸው ፈጠራዎችና ኹራፋቶች ሊጠነቀቅ ይገባል። አላህ እርዳታው የሚከጀል ነው። መመካትም በርሱው ላይ ነው። ከአላህ በስተቀር ብልሃትም ሀይልም የለም።

በአላህ መልእክተኛ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ላይ ሶለዋትና ሰላምን ማውረድማ በላጭ ከሆኑ መቃረቢያዎችና ከመልካም ስራዎችም ነው። አላህ እንዲህ ብሏል፦

﴿إِنَّ ٱللَّهَ وَمَلَٰٓئِكَتَهُۥ يُصَلُّونَ عَلَى ٱلنَّبِيِّۚ يَٰٓأَيُّهَا ٱلَّذِينَ ءَامَنُواْ صَلُّواْ عَلَيۡهِ وَسَلِّمُواْ تَسۡلِيمًا56﴾

{አላህና መላዕክቱ በነቢዩ (ሙሐመድ) ላይ የአክብሮት እዝነትን ያወርዳሉ:: እናንተ ያመናችሁ ሆይ! በእርሱ ላይ የአክብሮት እዝነትን አውርዱ:: የማክበርን ሰላምታንም ሰላም በሉ::} [አል-አሕዛብ: 56] ነቢዩም የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን እንዲህ ብለዋል፦

«مَنْ صَلَّى عَلَيَّ وَاحِدَةً؛ صَلَّى اللهُ عَلَيهِ بِهَا عَشْرًا».

«በኔ ላይ አንዲትን ሶላት ያወረደ፤ አላህ በርሱ ላይ አስር ሶለዋት ያወርድለታል።» እርሷም በሁሉም ወቅቶች የተደነገገች ስትሆን፣ በእያንዳንዱ ሶላት መጨረሻ ላይ ደግሞ ጠንከር ያለች ናት። ይልቁንም በከፊል ዑለማዎች ዘንድ በእያንዳንዱ ሶላት የመጨረሻው ተሸሁድ ላይ ግዴታ ትሆናለች። ሱና መሆኗ በበርካታ ቦታዎች ላይ አፅንዖት ይሰጠዋል። ከእነዚህም ውስጥ ከአዛን በኋላ፣ እርሳቸው (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) በሚወሱበት ጊዜ፣ በጁምዓ ቀንና በሌሊቷም ላይ ሲሆን፤ ይህንንም በርካታ ሐዲሶች ጠቁመዋል።

አላህ እኛንም ሆነ መላ ሙስሊሞችን ሃይማኖቱን በአግባቡ ለመገንዘብና በእርሱ ላይ ለመፅናት እንዲያድለን፣ በሁሉም ላይም ሱናን አጥብቆ መያዝንና ከቢድዐ መጠንቀቅን እንዲለግስልን እንማፀነዋለን። እርሱ ቸርና ለጋስ ነውና።

የአላህ ሰላትና ሰላም በነቢያችን ሙሐመድ ላይ እንዲሁም በቤተሰቦቻቸውና በባልደረቦቻቸው ላይ ይስፈን።

 

***

 


بِسْمِ اللهِ الرَّحمَنِ الرَّحِيمِ

ስድስተኛው መልእክት፡

የኢስራእ እና ሚዕራጅን ሌሊት የማክበር ህግ

ምስጋና ሁሉ ለአላህ የተገባ ነው። የአላህ ሰላትና ሰላም በአላህ መልእክተኛ፣ በቤተሰቦቻቸውና በባልደረቦቻቸው ላይ ይስፈን።

ከዚህ በመቀጠል፡ ኢስራእና ሚዕራጅ ያለምንም ጥርጥር የመልዕክተኛውን የሙሐመድን ﷺ እውነተኛነትና ልቅናው የላቀው አላህ ዘንድ ያላቸውን ታላቅ ደረጃ ከሚያመላክቱ የአላህ ታላላቅ ተአምራት መካከል ነው። እንዲሁም የአላህን አስደናቂ ችሎታና ከፍጡራኑ ሁሉ በላይ ያለውን ልቅና ከሚያሳዩ ማስረጃዎችም አንዱ ነው። ሁሉን ቻይ የሆነው አላህ እንዲህ ብሏል፡

﴿سُبۡحَٰنَ ٱلَّذِيٓ أَسۡرَىٰ بِعَبۡدِهِۦ لَيۡلٗا مِّنَ ٱلۡمَسۡجِدِ ٱلۡحَرَامِ إِلَى ٱلۡمَسۡجِدِ ٱلۡأَقۡصَا ٱلَّذِي بَٰرَكۡنَا حَوۡلَهُۥ لِنُرِيَهُۥ مِنۡ ءَايَٰتِنَآۚ إِنَّهُۥ هُوَ ٱلسَّمِيعُ ٱلۡبَصِيرُ1﴾

{ያ ባሪያውን (ሙሐመድን) ከተከበረው የሐረም መስጊድ ወደ እዚያ ዙሪያውን ወደ ባረክነው ሩቁ (አል አቅሷ) መስጊድ በሌሊት ውስጥ ያስኬደው (ጌታ) ጥራት ይገባው:: ከተዓምራቶቻችን ልናሳየው (አስኬድነው):: እነሆ እርሱ (አላህ) ሰሚዉና ተመልካቹ ነው::} [አል-ኢስራእ: 1]

ከአላህ መልዕክተኛ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) በተዋቱር (በሰፊና በተረጋገጠ ዘገባ) እንደተላለፈው እርሳቸው ወደ ሰማያት አርገዋል፤ በሮቿም ተከፍተውላቸው ሰባተኛውን ሰማይ አልፈዋል። ጌታቸውም (አላህ) በፈለገው መልኩ አናግሯቸዋል፤ አምስቱንም ሶላቶች ግዴታ አድርጎባቸዋል። አላህ መጀመሪያ ላይ ግዴታ ያደረገው ሀምሳ ሶላቶችን ነበር። ነብያችን ሙሐመድም (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) እንዲቀነስላቸው በተደጋጋሚ እየተመለሱ ይጠይቁት ነበርና በመጨረሻም አምስት አደረገላቸው። በመሆኑም በግዴታነት አምስት ሲሆኑ በምንዳ ግን ሀምሳ ናቸው፤ ምክንያቱም አንዲት መልካም ስራ በአስር እጥፍ ትመነዳለችና። ለአላህም በሁሉም ፀጋዎቹ ላይ ምስጋና ተገባው።

ይህች ኢስራእ እና ሚዕራጅ የተከናወነባት ሌሊት፣ በረጀብ ወርም ሆነ በሌላ ወር ውስጥ መሆኗን በትክክለኛ ሐዲሶች ላይ አልተገለጸም። ስለ እርሷ መለያም የተዘገቡ ሁሉ በሐዲስ ሊቃውንቶች ዘንድ ከነቢዩ ﷺ ያልጸደቁ ናቸው። አላህም ሰዎች እንዲረሷት በማድረግ ላይ ፍጹም ጥበብ አለው። ሌሊቷ የምትውልበት ቀን በትክክል ቢረጋገጥ ኖሮ ሙስሊሞች በተለየ የአምልኮ አይነት እንዲለዩዋትም ሆነ እንዲያከብሯት አይፈቀድላቸውም ነበር፤ ምክንያቱም ነቢዩ ﷺ እና ባልደረቦቻቸው (አላህ ሥራቸውን ይውደድላቸውና) አላከበሯትም፤ በምንም ነገርም አልለዩዋትምና። እርሷን ማክበር የተደነገገ ጉዳይ ቢሆን ኖሮ ረሱሉ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ለኡመታቸው በንግግራቸውም ሆነ በተግባራቸው ያብራሩት ነበር። ከዚህ መካከል አንዱ እንኳ ተከስቶ ቢሆን ኖሮ በታወቀና በገነነ ነበር፤ አላህ ስራቸውን ይውደድላቸውና ሶሓቦችም ለእኛ ባስተላለፉልን ነበር። ነቢያቸው (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ኡመታቸው የሚፈልገውን ነገር ሁሉ አስተላልፈዋልና፤ ከዲንም አንዱንም ነገር አላጓደሉም፤ ይልቁንም ወደ መልካም ነገር ሁሉ ቀዳሚ ናቸው። ይህችን ሌሊት ማክበር የተደነገገ ቢሆን ኖሮ ወደ እርሱ ከሰዎች ሁሉ የቀደሙ በሆኑ ነበር። ነቢዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ከሰዎች ሁሉ ለሰዎች የበለጠ መካሪ ናቸው። መልእክቱንም በሚገባ አድርሰዋል፤ አደራውንም ተወጥተዋል። ይህችን ሌሊት ማላቅና በሷ ማክበር ከአላህ ዲን ቢሆን ኖሮ ነቢዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) አይዘነጉትም እንዲሁም አይደብቁትም ነበር። ከዚህ ውስጥ አንዳቸውም አለመከሰቱ፤ በሷ ማክበርና እሷን ማላቅ ከእስልምና በምንም መልኩ አለመሆኑን ያሳያል። አላህ ለዚህ ህዝብ ዲኑን ሞልቶለታል፤ ፀጋውንም በእርሷ ላይ ሙሉ አድርጓል። አላህ ያልፈቀደውን በዲን ውስጥ የደነገገን ሰውም አውግዟል። አላህ ግልፅ በሆነው መጽሐ ላይ እንዲህ ብሏል፦

﴿...ٱلۡيَوۡمَ أَكۡمَلۡتُ لَكُمۡ دِينَكُمۡ وَأَتۡمَمۡتُ عَلَيۡكُمۡ نِعۡمَتِي وَرَضِيتُ لَكُمُ ٱلۡإِسۡلَٰمَ دِينٗا...﴾

{…ዛሬ ሃይማኖታችሁን ሞላሁላችሁ:: ጸጋየንም በእናንተ ላይ ፈጸምኩ:: ለእናንተም በሃይማኖትነት ኢስላምን ወደድኩላችሁ::…} [አል‐ማኢዳህ: 3] ክብሩ የላቀው አላህ እንዲህ ብሏል፦

﴿أَمۡ لَهُمۡ شُرَكَٰٓؤُاْ شَرَعُواْ لَهُم مِّنَ ٱلدِّينِ مَا لَمۡ يَأۡذَنۢ بِهِ ٱللَّهُۚ وَلَوۡلَا كَلِمَةُ ٱلۡفَصۡلِ لَقُضِيَ بَيۡنَهُمۡۗ وَإِنَّ ٱلظَّٰلِمِينَ لَهُمۡ عَذَابٌ أَلِيمٞ21﴾

{ከሓዲያን ከአላህ ያልተፈቀደውን ሃይማኖት የደነገጉ ተጋሪዎች ለእነርሱ አሏቸውን? የፍርዱ ቃል ባልነበረ ኖሮ በመካከላቸው ወዲያውኑ በተፈረደ ነበር:: በደለኞችም አሳማሚ ቅጣት በእርግጥ አለባቸው::} [አሽ-ሹራ: 21]

ከቢድዐዎች ማስጠንቀቅና ጥመት መሆኗንም በግልፅ መግለፅ ከአላህ መልዕክተኛ ‐የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን‐ በሰሒሕ ሐዲሶች ተረጋግጧል፤ ይህም ኡማውን ስለከፍተኛ አደገኛነቷ ለማንቃትና እንዳይፈጽሟትም ለማራቅ ነው። ከዚህም ውስጥ በሰሒሐይን ከእናታችን ዓኢሻ ‐ረዲየላሁ ዐንሃ‐ የተረጋገጠው፤ ነቢዩ ‐የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና‐ እንዲህ ማለታቸው ነው፡-

«مَنْ أَحْدَثَ فِي أَمْرِنَا هَذَا مَا لَيْسَ مِنْهُ؛ فَهُوَ رَدٌّ».

""በዚህ ሃይማኖታችን ጉዳይ ከእርሱ ያልሆነን አዲስ ነገር ያመጣ ይዞት የመጣው አዲስ ፈሊጥ ውድቅ ነው።"" በሙስሊም ዘገባም፡

«مَنْ عَمِلَ عَمَلًا لَيْسَ عَلَيهِ أَمْرَنَا؛ فَهُوَ رَدٌّ».

""በርሱ ላይ የኛ ትዕዛዝ የሌለበትን ነገር የሰራ ሰዉ ስራው ወደርሱ ተመላሽ ነዉ።"" በሶሒሕ ሙስሊም ከጃቢር ረዲየሏሁ ዐንሁ እንደተዘገበው፤ የአላህ መልዕክተኛ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) በጁሙዓ ቀን ኹጥባቸው ላይ እንዲህ ይሉ ነበር፦

«أَمَا بَعْدَ، فَإِنَّ خَيرَ الحَدِيثِ كِتَابُ اللهِ، وَخَيرَ الهَدْيِ هَدْيُ مُحَمَّدٍ ﷺ، وَشَرَّ الأُمُورِ مُحْدَثَاتُهَا، وَكُلَّ بِدْعَةٍ ضَلَالَةٌ».

«ከዚህ በመቀጠል፤ በላጩ ንግግር የአላህ ኪታብ ነው፤ በላጩ መመሪያ ደግሞ የሙሐመድ ‐ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ‐ መመሪያ ነው፤ ከጉዳዮች ሁሉ ክፉ ደግሞ አዲስ መጤ ነገሮች ናቸው፤ ፈጠራም በሙሉ ጥመት ነው።» ነሳኢይ ጥሩ በሆነ ሰነድ የሚከተለውን ጨምረዋል፡

«وَكُلَّ ضَلَالَةٍ فِي النَّارِ».

""ሁሉም ጥመት በእሳት ውስጥ ነዉ።"" በሱነን መጽሐፍት ውስጥ ከዒርባድ ቢን ሳሪየህ - አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላቸውና - እንደተላለፈው እንዲህ አሉ: «የአላህ መልክተኛ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ልቦናዎች የራዱበትና አይኖች ያነቡበትን ጥግ የደረሰ ምክር መከሩን። እኛም "የአላህ መልክተኛ ሆይ! ምክሮት ልክ የተሰናባችን ምክር ይመስላል። ምከሩን!" አልናቸው። እርሳቸውም:

«أُوصِيكُم بِتَقْوَى اللهِ وَالسَّمعِ وَالطَّاعَةِ وَإِنْ تَأَمَّرَ عَلَيكُم عَبدٌ، فَإِنَّهُ مَنْ يَعِشْ مِنْكُم فَسَيَرَى اخْتِلَافًا كَثِيرًا، فَعَلَيكُم بِسُنَّتِي وَسُنَّةِ الخلُفَاءِ الرَّاشِدِينَ المَهْدِيِّينَ مِنْ بَعْدِي، تَمَسَّكُوا بِهَا وَعَضُّوا عَلَيْهَا بِالنَّوَاجِذِ، وَإِيَّاكُم وَمُحْدَثَاتِ الأُمُورِ، فَإِنَّ كُلَّ مُحْدَثَةٍ بِدْعَةٍ وَكُلَّ بِدْعَةٍ ضَلَالَةٌ».

«አላህን በመፍራት፤ ባሪያ እንኳ ቢሾምባችሁ እንድትሰሙና እንድትታዘዙ አደራ እላችኋለሁ። እነሆ! ከናንተ መካከል የሚኖር ሰው ብዙ ልዩነትን ማየቱ አይቀርም፤ ስለሆነም በኔ ሱናና ከኔ በኋላ ባሉት የተመሩ ቅን በሆኑት ምትኮቼ ሱና አደራችሁን! እርሷን አጥብቃችሁ ያዙ፤ በማኘኪያ ጥርሳችሁም ነክሳችሁ ያዟት። አደራችሁን አዳዲስ መጤ ነገሮችን ተጠንቀቁ! አዲስ መጤ ነገር ሁሉ ቢድዓ ነው፤ ቢድዓም ሁሉ ጥመት ነውና።» ይህንን መልዕክት ይዘው የመጡ ሐዲሦች እጅግ በጣም ብዙ ናቸው።

ከአላህ መልእክተኛ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ሶሐቦች፣ እንዲሁም ከእነሱ በኋላ ከመጡት ደጋግ ሰለፎች ከቢድዓዎች (ፈጠራዎች) ማስጠንቀቅና ከእርሷም ማስፈራራት ተረጋግጧል፤ ይህም የሆነው እርሷ (ቢድዓ) በዲን ላይ ጭማሪ፣ አላህ ያልፈቀደው ድንጋጌ፣ እንዲሁም በሃይማኖታቸው ላይ በመጨመርና አላህ ያልፈቀደውንም በውስጡ በመፍጠር የአላህ ጠላቶች የሆኑትን አይሁዶችንና ክርስቲያኖችን መመሳሰል በመሆኗ ነው፡፡ በተጨማሪም አስገዳጅ ውጤቷ የእስልምናን ሃይማኖት ማጉደልና ፍፁም አይደለም ብሎ መወንጀል ነው፡፡ በዚህ ውስጥ ያለው ታላቅ ጥፋት፣ አስከፊ ክፋት እና ልዕልናው የላቀው ከሆነው ከሚከተለው የአላህ ቃል ጋር መጋጨትም የታወቀ ነው፡

﴿...ٱلۡيَوۡمَ أَكۡمَلۡتُ لَكُمۡ دِينَكُمۡ...﴾

{…ዛሬ ሃይማኖታችሁን ሞላሁላችሁ…} [አል‐ማኢዳህ: 3] ከቢድዐ የሚያስጠነቅቁና ከእርሷም የሚያርቁ የመልዕክተኛውን የአላህ ሶላትና ሰላም በርሳቸው ላይ ይስፈን ሐዲሶች በግልፅ መቃረንም ነው።

እስካሁን የጠቀስናቸው ማስረጃዎች ይህችን ቢድዓ —ማለትም የኢስራእና ሚዕራጅን ሌሊት የማክበርን ፈጠራ— ውድቅ ለማድረግና ከእርሷም ለማስጠንቀቅ፤ እንዲሁም ከኢስላም ዲን ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌላት ለመገንዘብ ለሐቅ ፈላጊ በቂና አሳማኝ እንደሚሆኑ ተስፋ አደርጋለሁ።

አላህ ለሙስሊሞች መመካከርን (መቆርቆር) እና ከዲንም የደነገለላቸውን ነገር ማብራራትን ግዴታ ከማድረጉ እንዲሁም እውቀትን መደበቅ ክልክል ከመሆኑ አንፃር፤ በብዙ ሀገራት ተሰራጭታ አንዳንድ ሰዎችም ከዲን እስከሚቆጥሯት የደረሱትን ይህችን ቢድዓ አስመልክቶ ሙስሊም ወንድሞቼን ማንቃት ወደድኩ።

አላህን የሙስሊሞችን ሁኔታ በሙሉ እንዲያስተካክልልን፣ የሃይማኖት ግንዛቤን እንዲለግሳቸው፣ እኛንም ሆነ እነርሱን እውነትን አጥብቆ መያዝንና በርሱ ላይ መፅናትን፣ የሚፃረረውንም መተው እንዲገጥመን እንጠይቀዋለን። እርሱ ለዚህ ባለቤትም ቻይም ነውና።

የአላህ ሰላትና ሰላም በረከቱም በባሪያውና በመልዕክተኛው በነብያችን ሙሐመድ፣ በቤተሰቦቻቸውና በባልደረቦቻቸው ላይ ይስፈን።

 

 

***

 


بِسْمِ اللهِ الرَّحمَنِ الرَّحِيمِ

ሰባተኛው መልእክት፡

የሸዕባን ወር አጋማሽ ሌሊትን የማክበር ህግ

ምስጋና ለዚያ ሃይማኖትን ላሟላልን፣ ፀጋውንም በእኛ ላይ ለሞላልን አላህ የተገባ ነው። የአላህ ሶላትና ሰላምም የንስሃና የእዝነት ነብይ በሆኑት በነብዩና በመልእክተኛው ሙሐመድ ላይ ይስፈን።

በመቀጠልም፦ የላቀው አሏህ እንዲህ ብሏል:

﴿...ٱلۡيَوۡمَ أَكۡمَلۡتُ لَكُمۡ دِينَكُمۡ وَأَتۡمَمۡتُ عَلَيۡكُمۡ نِعۡمَتِي وَرَضِيتُ لَكُمُ ٱلۡإِسۡلَٰمَ دِينٗا...﴾

{…ዛሬ ሃይማኖታችሁን ሞላሁላችሁ:: ጸጋየንም በእናንተ ላይ ፈጸምኩ:: ለእናንተም በሃይማኖትነት ኢስላምን ወደድኩላችሁ::…} [አል‐ማኢዳህ: 3] ጥራት የተገባው አላህ እንዲህም ብሏል፡

﴿أَمۡ لَهُمۡ شُرَكَٰٓؤُاْ شَرَعُواْ لَهُم مِّنَ ٱلدِّينِ مَا لَمۡ يَأۡذَنۢ بِهِ ٱللَّهُ...﴾

{ከሃይማኖት አላህ በእርሱ ያልፈቀደውን ለእነርሱ የደነገጉ ተጋሪዎች ለእነርሱ አሏቸውን?…} [አሽ ሹራ፡ 21] በሁለቱ ሶሒሖችም ውስጥ ከእናታችን ዓኢሻ -አላህ መልካም ስራዋን ይውደድላትና- እንደተላለፈው ነቢዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) እንዲህ ብለዋል:

«مَنْ أَحْدَثَ فِي أَمْرِنَا هَذَا مَا لَيْسَ مِنْهُ؛ فَهُوَ رَدٌّ».

""በዚህ ጉዳያችን ከእርሱ ያልሆነን አዲስ ፈሊጥ ያመጣ፤ ይዞት የመጣው ፈሊጥ ውድቅ ነው።"" በሶሒሕ ሙስሊም ከጃቢር (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደተዘገበው፤ ነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) በጁሙዓ ኹጥባቸው እንዲህ ይሉ ነበር፡

«أَمَّا بَعْدُ: فَإِنَّ خَيرَ الحَدِيثِ كِتَابُ اللهِ، وَخَيرَ الهَدْيِ هَدْيُ مُحَمَّدٍ صَلَّى اللهُ عَلَيهِ وَسَلَّمَ، وَشَرَّ الأُمُورِ مُحْدَثَاتُهَا، وَكُلَّ بِدْعَةٍ ضَلَالَةٌ».

«ከዚህ በመቀጠል፥ በላጩ ንግግር የአላህ ኪታብ ነው፤ በላጩ መንገድም የሙሐመድ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) መንገድ ነው፤ ከጉዳዮች ሁሉ ክፉው አዲስ መጤዎቹ ናቸው፤ ፈጠራ በሙሉ ጥመት ነው፡፡» በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ያሉ አንቀጾችና ሐዲሶች በርካታ ሲሆኑ እነዚህም የላቀው አላህ ለዚህ ህዝብ (ኡማ) ዲኑን እንዳሟላለትና ጸጋውንም በእርሱ ላይ ሙሉ እንዳደረገ በግልጽ ያመላክታሉ። ነብዩንም (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ግልጽ የሆነውን መልዕክት ካደረሱና ለህዝቡም አላህ የደነገገላቸውን የንግግርና የተግባር ድንጋጌዎች በሙሉ ካብራሩ በኋላ ቢሆን እንጂ አላሳረፋቸውም። ነቢዩም (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ከእርሳቸው በኋላ ሰዎች የሚፈጥሩትና ወደ ኢስላም ሃይማኖት የሚያስጠጉት ማንኛውም ንግግርም ሆነ ተግባር፤ ሐሳቡ መልካም ቢሆንም እንኳ በፈጠረው ሰው ላይ ተመላሽ የሆነ ቢድዓ መሆኑን አብራርተዋል። ይህንንም ጉዳይ የአላህ መልዕክተኛ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ሶሐቦች እንዲሁም ከእነርሱ በኋላ የመጡ የኢስላም ሊቃውንት አውቀውታል። በመሆኑም ቢድዓዎችን አውግዘው ከእርሷም አስጠንቅቀዋል። ይህንንም ሱናን ስለማላቅና ቢድዓን ስለማውገዝ የጻፉ ሁሉ እንደ ኢብኑ ወዷሕ፣ አጥ-ጡርጡሺ፣ አቡ ሻማና ሌሎችም ጠቅሰውታል፡፡

አንዳንድ ሰዎች ከፈጠሯቸው ቢድዓዎች መካከል፡ የሻዕባንን ወር የአስራ አምስተኛዋን ሌሊት ማክበርና ቀኗን በጾም መነጠል ይገኝበታል። ለዚህም ሊመረኮዙበት የሚፈቀድ ምንም አይነት ማስረጃ የለም። ስለ ትሩፋቷ የተዘገቡ ደካማ ሐዲሶች ቢኖሩም፤ ሊደገፉባቸው ግን አይፈቀድም።

በእርሷ ውስጥ ስለሚሰገደው ሶላት ትሩፋት የተዘገበው ዘገባማ በርካታ ሊቃውንት እንዳስጠነቀቁበት ሁሉም የተቀጠፈ ነው። አላህ ከፈቀደ ከንግግራቸውም የተወሰነው ወደፊት ይወሳል።

እንዲሁም በዚህች ላይ ከሻም ሰዎችና ከሌሎችም ከሆኑት ከተወሰኑ ቀደምት አበዎች አሰሮች መጥተዋል።

በአብዛኞቹ ዑለሞች ዘንድ ስምምነት የተደረሰበት ጉዳይ ይህንን በዓል ማክበር ቢድዓ መሆኑ እና ስለ ትሩፋቱም የተዘገቡት ሐዲሦች በሙሉ ያልተረጋገጡ (ዶዒፎች) ሲሆኑ ከፊሎቹ ደግሞ የተቀጠፉ (መውዱዕ) መሆናቸው ነው። ይህንንም ካስጠነቀቁት መካከል ሓፊዝ ኢብኑ ረጀብ (ለጧኢፉል መዓሪፍ) በተሰኘው ኪታባቸው እና ሌሎችም ይገኙበታል። እንደሚታወቀው ደግሞ ያልተረጋገጡ (ዶዒፍ) ሐዲሦች ስራ ላይ የሚውሉት መሰረታቸው በትክክለኛ ማስረጃዎች በተረጋገጡ ዒባዳዎች ላይ ነው። የሸዕባንን ወር አስራ አምስተኛ ሌሊት ማክበርን በተመለከተ በደካማ ሐዲሶች እንኳ የሚጠናከርለት ትክክለኛ መሰረት የለውም። ይህችንም ታላቅ መመሪያ ኢማሙ አቡል ዐባስ ሸይኹል ኢስላም ኢብኑ ተይሚያህ አላህ ይዘንላቸውና ጠቅሰዋታል።

ውድ አንባቢ ሆይ፤ በዚህ ጉዳይ ላይ ግልጽ ግንዛቤ እንዲኖርህ አንዳንድ ዐሊሞች የተናገሩትን እጠቅስልሃለሁ።

ዑለማዎች (አላህ ይዘንላቸውና) ሰዎች በሚወዛገቡባቸው ጉዳዮች ላይ ወደ ታላቁ አላህ ኪታብና ወደ መልዕክተኛው (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ሱና መመለስ ግዴታ በመሆኑ ላይ በሙሉ ድምፅ ተስማምተዋል። ሁለቱም ወይም አንዳቸው የፈረዱበት ነገር ሊከተሉት የሚገባ ሸሪዓ ሲሆን ሁለቱንም የሚፃረር ነገር ደግሞ መጣል ግዴታ ነው። በሁለቱም ውስጥ ያልተጠቀሰ የዒባዳ አይነት ቢድዓ ነው፤ መስራቱ አይፈቀድም፤ ወደ እርሱ መጣራትና እንዲወደድ ማድረግ ይቅርና አላህ ሱብሓነሁ ወተዓላ እንዲህ ብሏል፦

﴿يَٰٓأَيُّهَا ٱلَّذِينَ ءَامَنُوٓاْ أَطِيعُواْ ٱللَّهَ وَأَطِيعُواْ ٱلرَّسُولَ وَأُوْلِي ٱلۡأَمۡرِ مِنكُمۡۖ فَإِن تَنَٰزَعۡتُمۡ فِي شَيۡءٖ فَرُدُّوهُ إِلَى ٱللَّهِ وَٱلرَّسُولِ إِن كُنتُمۡ تُؤۡمِنُونَ بِٱللَّهِ وَٱلۡيَوۡمِ ٱلۡأٓخِرِۚ ذَٰلِكَ خَيۡرٞ وَأَحۡسَنُ تَأۡوِيلًا59﴾

{እናንተ ያመናችሁ ሆይ! አላህን ታዘዙ:: መልዕክተኛውን እና ከመካከላችሁም የስልጣን ባለቤቶችን ታዘዙ:: በማንኛዉም ነገር ብትከራከሩም በአላህና በመጨረሻው ቀን የምታምኑ ከሆናችሁ የተከራከራችሁበትን ነገር ወደ አላህና ወደ መልዕክተኛው መልሱት:: ይህ የተሻለ እና መጨረሻዉም ያማረ ነው::} [አን-ኒሳእ፡ 59] ጥራት የተገባው አላህ እንዲህም ብሏል፡

﴿وَمَا ٱخۡتَلَفۡتُمۡ فِيهِ مِن شَيۡءٖ فَحُكۡمُهُۥٓ إِلَى ٱللَّهِ...﴾

«ያ የተለያያችሁበት ነገር ሁሉ ፍርዱ ወደ አላህ ብቻ ነው...» [አሽ ሹራ፡ 10] ጥራት የተገባው አላህ እንዲህም ብሏል፡

﴿قُلۡ إِن كُنتُمۡ تُحِبُّونَ ٱللَّهَ فَٱتَّبِعُونِي يُحۡبِبۡكُمُ ٱللَّهُ وَيَغۡفِرۡ لَكُمۡ ذُنُوبَكُمۡ...﴾

{(መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!)፡- «አላህን የምትወዱ እንደሆናችሁ እኔን ተከተሉኝ:: አላህም ይወዳችኋል፤ ኃጢአቶቻችሁንም ለእናንተ ይምራልና...» በላቸው።} [አሊ ዒምራን: 31] የላቀው አላህ እንዲህ ብሏል፦

﴿فَلَا وَرَبِّكَ لَا يُؤۡمِنُونَ حَتَّىٰ يُحَكِّمُوكَ فِيمَا شَجَرَ بَيۡنَهُمۡ ثُمَّ لَا يَجِدُواْ فِيٓ أَنفُسِهِمۡ حَرَجٗا مِّمَّا قَضَيۡتَ وَيُسَلِّمُواْ تَسۡلِيمٗا65﴾

{(መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ጉዳዩ እነርሱ እንዳሉት አይደለም:: በጌታህ እምላለሁ በመካከላቸው በተከራከሩበት ፍርድ የሚያስፈርዱህ ሆነው ከዚያ ከፈረድከው ነገር በነፍሶቻቸው ውስጥ ጭንቀትን እስከማያገኙና ፍጹም መታዘዝንም እስከሚታዘዙ ድረስ አማኝ አይሆኑም::} [አንኒሳእ፡ 65] የዚህን ዓይነት መልዕክት ያዘሉ አንቀጾች በርካታ ናቸው። እነሱም የልዩነት ጉዳዮችን ወደ ቁርኣንና ሱና መመለስ ግዴታ መሆኑን፣ ፍርዳቸውንም በውዴታ መቀበል ግዴታ መሆኑን፣ ይህም የኢማን መስፈርት እንደሆነ፣ ለባሮችም በቅርቢቱም ሆነ በኋለኛው ዓለም መልካም እንደሆነና በፍጻሜውም እጅግ የተሻለ መሆኑን በግልጽ የሚያስረዱ ናቸው።

አል-ሐፊዝ ኢብኑ ረጀብ ـ አላህ ይዘንላቸውና ـ "(ለጣኢፉ-ል-መዓሪፍ)" በተሰኘው ኪታባቸው ላይ፣ ከዚህ ቀደም ካብራሩት በመቀጠል ይህችን ነጥብ አስመልክተው እንዲህ ብለዋል፦

«የሻዕባን ወር አጋማሽ ሌሊትን፤ ከሻም ሰዎች የሆኑት ታቢዒዮች፤ እንደ ኻሊድ ኢብኑ መዕዳን፣ መክሑል፣ ሉቅማን ኢብኑ ዓሚር እና ሌሎችም፣ ያከብሯትና በዒባዳ ላይ ይጥሩባት ነበር። ሰዎችም ትሩፋቷንና ማክበሯን የወሰዱት ከእነርሱ ነው። በዚህ ጉዳይ የኢስራኢሊያህ ዘገባዎች እንደደረሷቸው ተዘግቧል። ይህ ነገራቸው በየሀገራቱ ሲታወቅም ሰዎች በጉዳዩ ላይ ያላቸው አቋም ተለያይቷል፤ አንዳንዶቹ ከእነሱ ተቀብለውት እርሷንም በማላቅ ገጥመዋቸዋል፤ ከእነዚህም መካከል የበስራ ዒባዳ አብዢዎች እና ሌሎችም ይገኙበታል። አብዛኞቹ የሒጃዝ ዑለማዎች ይህንን ተቃውመዋል፤ ከእነሱም መካከል አጧእ እና ኢብኑ አቢ ሙለይካህ ይገኙበታል። ዐብዱ'ር-ረሕማን ኢብኑ ዘይድ ኢብኑ አስለምም ከመዲና ሊቃውንት ዘግበውታል፤ ይህም የማሊክ ተከታዮችና የሌሎችም አቋም ሲሆን ይህ ሁሉ ቢድዐ ነውም ብለዋል።

የሻም ዑለማዎቸ በአፈፃፀሙ ሁኔታ ላይ በሁለት ሀሳብ ተለያይተዋል:

አንደኛው፡ "እሷን (ሌሊቷን) በመስጂዶች ውስጥ በጀመዓ በዒባዳ ማሳለፍ ይወደዳል" የሚል ነው። ኻሊድ ኢብኑ መዕዳንና ሉቅማን ኢብኑ ዓሚር እንዲሁም ሌሎችም ምርጥ ልብሳቸውን ይለብሱ፣ ይታጠኑ እንዲሁም ይኳሉ ነበር፤ ያቺንም ሌሊት በመስጂድ (በዒባዳ) ሲቆሙ ያሳልፏት ነበር። ኢስሓቅ ኢብኑ ራሀወይህም በዚህ ላይ ተስማምቶባቸዋል። በመስጂዶች ውስጥ በጀመዓ ስለመስገዷም «ይህ ቢድዐ አይደለም» ብለዋል፤ ይህንንም ሐርብ አል-ኪርማኒ በመሳኢላቸው ላይ ዘግበውታል።

ሁለተኛው፦ በመስጂዶች ውስጥ ለሶላት፣ ለቂሷና ለዱዓ መሰብሰብ የተጠላ ነው። አንድ ሰው ለብቻው ቢሰግድበት ግን አይጠላም። ይህ የሻም አገር ኢማም፣ ፈቂህና ዐሊም የሆኑት የአውዛዒይ አቋም ሲሆን፤ ኢንሻአላህ (በአላህ ፈቃድ) ይበልጥ ትክክለኛውም ይኸው ነው።» …እንዲህም ብለዋል፦ «ለኢማም አህመድ የሸዕባን ወር አጋማሽ ሌሊትን በተመለከተ የተናገሩት ነገር አይታወቅም። በዚህች ሌሊት መስገድ መወደድን በተመለከተ ከርሳቸው የተገኙት ሁለት ሪዋያዎች ከሁለቱ የኢድ ሌሊቶች መስገድን አስመልክቶ ከርሳቸው ከተዘገቡት ሁለት ሪዋያዎች የሚወሰዱ ናቸው። እርሳቸው (በአንደኛው ሪዋያ) በጀመዓ መስገድን አልወደዱትም፤ ምክንያቱም ከነብዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በርሳቸው ላይ ይስፈንና) እና ከባልደረቦቻቸው አልተዘገበምና።» ሙስተሐብ (የተወደደ) መሆኑም (በአንድ ዘገባ) ተጠቅሷል፤ ይህም ከታቢዒዮች አንዱ የሆነው ዐብዱራሕማን ኢብኑ የዚድ ኢብኑል አስወድ ይህንኑ በመፈፀሙ ነው። ልክ እንደዚሁ የ(ሻዕባን) አጋማሽ ሌሊት ስግደትን በተመለከተ ከነቢዩ ﷺ ሆነ ከባልደረቦቻቸው ምንም የተረጋገጠ ነገር የለም። ከሻም አገር ታላላቅ የፊቅህ ሊቃውንት ከሆኑት ታቢዒዮች መካከል ግን መፈፀሙ ተረጋግጧል።»

ከሐፊዝ ኢብኑ ረጀብ (አላህ ይዘንላቸው) ንግግር የተወሰደው ዋና ሀሳብ፣ በሸዕባን አጋማሽ ሌሊት ላይ ከነብዩም ﷺ ሆነ ከሶሐቦቻቸው (አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላቸው) የተረጋገጠ ምንም ነገር እንደሌለ በግልጽ የሚናገር መሆኑ ነው።

አል-አውዛዒይ -አላህ ይዘንላቸውና- በግል መስገድ የተወደደ መሆኑን መምረጣቸው እና ሓፊዝ ኢብኑ ረጀብም ይህንን አቋም መምረጣቸው እንግዳና ደካማ ነው። ምክንያቱም በሸሪዐዊ ማስረጃዎች የተደነገገ መሆኑ ያልተረጋገጠን ማንኛውንም ነገር አንድ ሙስሊም በአላህ ዲን ውስጥ ሊፈጥረው አይፈቀድለትምና፤ በግልም ሆነ በጀመዓ፣ በስውርም ሆነ በይፋ ቢፈጽመው የነቢዩ (ሶለሏሁ ዐለይሂ ወሰለም) ንግግር ይህን ሁሉ የሚያጠቃልል በመሆኑ ነው፦

«مَنْ عَمِلَ عَمَلًا لَيْسَ عَلَيهِ أَمْرُنَا؛ فَهُوَ رَدٌّ».

"በርሱ ላይ የኛ ትዕዛዝ የሌለበትን ነገር የሰራ ሰዉ ስራው ወደርሱ ተመላሽ ነዉ።" ይህ ሐዲሥ እና ሌሎችም ቢድዐን የሚያወግዙና ከእርሷ የሚያስጠነቅቁ ማስረጃዎች ይህን ይጠቁማሉ።

አልኢማም አቡ በክር አጥ-ጦርጡሺይ ـ አላህ ይዘንላቸውና ـ «አል-ሐዋዲስ ወል-ቢደዕ» በተሰኘው ኪታባቸው እንዲህ ብለዋል፡-

«ኢብኑ ወዳሕ ከዘይድ ኢብኑ አስለም እንደዘገቡት እንዲህ ብለዋል፦ ከመሻኢኾቻችንም ሆነ ከፉቀሃዎቻችን ለሸዕባን አጋማሽ ትኩረት ሲሰጡ፣ የመክሑልንም ሐዲስ ሲመለከቱ፣ እንዲሁም ከሌሎች (ሌሊቶች) የተለየ ብልጫ እንዳላት ሲያምኑ አንድንም አላገኘንም ነበር።»

ለኢብኑ አቢ ሙለይካህም ዚያድ አን-ኑመይሪ እንዲህ እንደሚል ተነገራቸው፦ «የሻዕባን አጋማሽን ሌሊት ምንዳ እንደ ለይለቱል ቀድር ምንዳ ነው» እንዲህም አሉ: «እንዲህ ሲል ስሰማው በእጄ ዱላ ቢኖር ኖሮ እመታው ነበር።» ዚያድ የተባለውም ተራኪ ነበር፣ ማስተላለፍ የተፈለገው መልዕክት እዚህ ላይ አበቃ።

አል-ዐላማህ አሽ-ሸውካኒ ـ አላህ ይዘንላቸውና ـ «አል-ፈዋኢዱ-ል-መጅሙዓህ» በተሰኘው ኪታባቸው እንዲህ ብለዋል፡-

«“አንተ ዐልይ ሆይ፥ በሸዕባን ወር አጋማሽ ሌሊት በእያንዳንዱ ረከዓ ላይ ፋቲሐቱል ኪታብን እና ‘ቁል ሁወላሁ አሐድ’ን አስር ጊዜ እየቀራ መቶ ረከዓዎችን ለሰገደ ሰው አላህ ጉዳዩን ሁሉ ይፈጽምለታል።” እስከመጨረሻው » የሚለው ሐዲሥ የተፈበረከ ነው፤ በቃላቶቹ ውስጥ ፈፃሚው ስለሚያገኘው ምንዳ በግልፅ የተጠቀሰው ነገር የማገናዘብ ችሎታ ያለው ሰው በመፈብረኩ ላይ እንዳይጠራጠር ያደርገዋል፤ ዘጋቢዎቹም የማይታወቁ ናቸው፤ እንዲሁም ሁሉም የተፈበረኩና ዘጋቢዎቻቸውም የማይታወቁ በሆኑ በሁለተኛና በሶስተኛ ሰነዶች ተዘግቧል። በ«ሙኽተሶር» ላይ እንዲህ ብለዋል፡- «የሻዕባን አጋማሽ ሶላት ሀዲስ መሰረተ-ቢስ ነው።» ኢብኑ ሒባን ከዐሊይ በዘገቡትም «የሻዕባን አጋማሽ ሌሊት ሲሆን ሌሊቱን በሶላት አሳልፉ፤ ቀኑንም ጹሙ» የሚለው ሀዲስ ደካማ ነው። በ«አል-ለኣሊእ» ላይ እንዲህ ብለዋል፦ «"በሸዕባን አጋማሽ መቶ ረከዓዎችን በኢኽላስ አስር ጊዜያት (የመስገድ)" ሐዲሥ፣ ትሩፋቱ በሰፊው ቢተረክም በደይለሚይ እና በሌሎችም የተዘገበ ቢሆንም የተቀጠፈ (መውዱዕ) ነው። በሶስቱም የዘገባ ሰንሰለቶች ውስጥ ያሉ አብዛኞቹ ዘጋቢዎቹም ተለይተው የማይታወቁ (መጅሁሎች) እና ደካሞች (ዶዒፎች) ናቸው።» እንዲህም ብለዋል: «አስራ ሁለት ረከዓ በኢኽላስ ሰላሳ ጊዜ» የሚለው ሐዲሥ የተቀጠፈ ነው፤ «አስራ አራት ረከዓ» የሚለውም የተቀጠፈ ነው።

በዚህ ሐዲስ ከፊቅህ ሊቃውንት የተወሰኑት፤ እንደ (ኢሕያ) ባለቤትና ሌሎችም እንዲሁም ከሙፈሲሮችም ጭምር ተሸውደዋል፤ የዚህች ሌሊት ሶላት — ማለቴም የሻዕባን አጋማሽ ሌሊት — በተለያዩ መንገዶች የተዘገበ ሲሆን ሁሉም ውድቅና የተቀጠፉ ናቸው። ይህም ቲርሚዚ ዓኢሻ (አላህ ስራዋን ይውደድላትና) ነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ወደ በቂዕ መሄዳቸውን፣ ጌታ በወሩ አጋማሽ ሌሊት ወደ ቅርቢቱ ሰማይ መውረዱን እና ከከልብ ነገድ በግ ፀጉር ብዛት ለሚበልጡ ሰዎች እንደሚምር ከዘገበችው ሐዲሥ ጋር አይቃረንም፤ ምክንያቱም እያወራን ያለነው በዚህች ሌሊት ላይ ስለተቀጠፈችው ሶላት ብቻ ነውና። «ይህ የዓኢሻ -አላህ መልካም ስራዋን ይውደድላትና- ሐዲሥ ድክመትና መቆራረጥ አለበት። ልክ እንደዚሁም ቀደም ብሎ የሌሊት ሶላቷን አስመልክቶ የተጠቀሰው የዓሊይ (ረዲየሏሁ ዐንሁ) -አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና- ሐዲሥ እኛ እንደጠቀስነው በራሱ ላይ ድክመት ቢኖርበትም እንኳ ይህቺ ሶላት የተቀጠፈች መሆኗን አይቃረንም።» ከንግግሩ የተፈለገው እዚህ ላይ ያበቃል።

አል-ሐፊዝ አል-ዒራቂይ እንዲህ ብለዋል: «የኒስፍ (የወሩ አጋማሽ) ሌሊት ሶላት ሐዲሥ በአላህ መልክተኛ -የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና- ላይ የተቀጠፈና ውሸት ነው።» ኢማም ነወዊይ (አልመጅሙዕ) በተሰኘው መጽሐፋቸው እንዲህ ብለዋል፦ “'ሶላተ አር-ረጋኢብ' በመባል የምትታወቀውና በረጀብ ወር የመጀመሪያ ጁሙዓ ሌሊት በመግሪብና ዒሻ መካከል የምትሰገድ አስራ ሁለት ረከዓ ሶላት እንዲሁም የሸዕባን ወር አጋማሽ ሌሊት የምትሰገደው የመቶ ረከዓ ሶላት፤ እነዚህ ሁለቱ ሶላቶች የተወገዙ ቢድዓዎች ናቸው። (ቁቱል ቁሉብ) እና (ኢሕያኡ ዑሉሚዲን) በተባሉ መጽሐፍት ውስጥ በመጠቀሳቸውና በውስጣቸውም በተወሳው ሐዲሥ ማንም አይሸወድ፤ ይህ ሁሉ ውድቅ ነውና። አንዳንድ ሊቃውንት ፍርዱ ስለተመሳሰለባቸው ተወዳጅ መሆኑን የሚገልጹ ጽሑፎችን በማዘጋጀታቸውም ማንም አይሸወድ፤ በዚህ ጉዳይ ላይ ተሳስተዋልና።”

ሸይኽ ኢማም አቡ ሙሐመድ ዐብዱረሕማን ኢብኑ ኢስማዒል አል-መቅዲሲ የሁለቱን ጉዳዮች ውድቅነት በማስመልከት እጅግ ጠቃሚ የሆነ ኪታብ አዘጋጅተዋል፤ በኪታባቸውም ላይ እጅግ አሳምረውበታል። በዚህ ርእሰ ጉዳይ ላይ የሊቃውንት ንግግር በጣም ብዙ ነው። በጉዳዩ ላይ ያገኘናቸውን ንግግሮች ሁሉ ለማስተላለፍ ብንሞክር ኖሮ ሐተታው ይረዝምብን ነበር። ምናልባት እኛ የጠቀስነው ሐቅን ለሚፈልግ ሰው በቂና አሳማኝ ይሆናል።

ከዚህ ቀደም ከቀረቡት የቁርኣን አንቀፆች፣ ሐዲሶች እና የእውቀት ባለቤቶች ንግግሮች በመነሳት እውነትን ለሚፈልግ ሰው የሸዕባንን ወር አጋማሽ ሌሊት በሶላት ወይም በሌላ ነገር መለየት፣ እንዲሁም ቀኑን ለፆም መነጠል፤ በአብዛኛዎቹ የእውቀት ባለቤቶች ዘንድ የተወገዘ ፈጠራ (ቢድዓ) መሆኑ ግልፅ ይሆንለታል። በጠራው ሸሪዓ ላይ ምንም መሰረት የለውም፤ ይልቁንም ከሰሃባዎች (አላህ ስራቸውን ይውደድላቸውና) ዘመን በኋላ በእስልምና ውስጥ የተከሰተ ነው። በዚህም ሆነ በሌሎች ጉዳዮች ላይ እውነትን ለሚፈልግ ሰው ክብሩ ከፍ ያለው የአላህ ቃል በቂው ነው፡

﴿...ٱلۡيَوۡمَ أَكۡمَلۡتُ لَكُمۡ دِينَكُمۡ...﴾

{…ዛሬ ሃይማኖታችሁን ሞላሁላችሁ…} [አል‐ማኢዳህ: 3] በተመሳሳይ ሃሳብ የመጡ የቁርአን አንቀፆችና፣ ነቢዩም ﷺ እንዲህ ማለታቸው፦

«مَنْ أَحْدَثَ فِي أَمْرِنَا هَذَا مَا لَيْسَ مِنْهُ فَهُوَ رَدٌّ».

"በዚህ ጉዳያችን ከእርሱ ያልሆነን አዲስ ነገር ያመጣ ይዞት የመጣው አዲስ ፈሊጥ ውድቅ ነው።" ይህንኑ መልዕክት ይዘው ከመጡ ሐዲሶችም መካከል።

በሶሒሕ ሙስሊምም አቡ ሁረይራ -አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና- እንዳስተላለፉት የአላህ መልዕክተኛ ﷺ እንዲህ ብለዋል፦

«لَا تَخُصُّوا لَيْلَةَ الْجُمُعَةِ بِقِيَامٍ مِنْ بَيْنِ اللَّيَالِي، وَلَا تَخُصُّوا يَوْمَهَا بِالصِّيَامِ مِنْ بَيْنِ الْأَيَّامِ، إِلَّا أَنْ يَكُونَ فِي صَوْمٍ يَصُومُهُ أَحَدُكُمْ».

"ከሌሊቶች መካከል የጁሙዓን ሌሊት በቂያም አትለዩ፤ ከቀናትም መካከል ቀኑን በጾም አትልዩት፤ አንዳችሁ ከሚፆመው ፆም ጋር የሚገጥም ቢሆን እንጂ።" ከሌሊቶች መካከል አንዷን በሆነ የዒባዳ አይነት መለየት የተፈቀደ ቢሆን ኖሮ፣ የጁሙዓ ሌሊት ከሌሎች የበለጠ ተገቢ ትሆን ነበር፤ ምክንያቱም ከአላህ መልዕክተኛ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) በተገኙ ትክክለኛ ሐዲሶች በግልፅ እንደተነገረው ቀኗ ፀሐይ ከወጣችባቸው ቀናቶች ሁሉ በላጩ ቀን ነውና። ነቢዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) አንዷን ሌሊት ከሌሎች ሌሊቶች መካከል ለይቶ በቂያም ልዩ ከማድረግ ማስጠንቀቃቸው ይህ የሚያመላክተው ከእርሷ ውጪ ያሉ ሌሎች ሌሊቶችም በበለጠ መልኩ ልዩ ስለመደረጋቸው የሚያመላክት ትክክለኛ ማስረጃ ካልተገኘ በቀር በአንዳችም የአምልኮ አይነት ልዩ ማድረግ እንደማይፈቀድ ነው።

ለይለተል ቀድርና የረመዷን ሌሊቶች በሶላት ሊቆሙባቸውና በዒባዳ ሊተጋባቸው የተደነገገ በመሆኑ ዙሪያ ነቢዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) በዚህ ላይ አሳስበዋል። ኡማውንም እንዲቆሟቸው አነሳስተዋል። ይህንንም በራሳቸው ፈፅመውታል። በሁለቱ ሶሒሕ መዛግብት ከነቢዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) እንደተዘገበው እንዲህ ብለዋል፦

«مَنْ قَامَ رَمَضَانَ إِيمَانًا وَاحْتِسَابًا، غُفِرَ لَهُ مَا تَقَدَّمَ مِنْ ذَنْبِهِ، وَمَنْ قَامَ لَيْلَةَ الْقَدْرِ إِيمَانًا وَاحْتِسَابًا، غُفِرَ لَهُ مَا تَقَدَّمَ مِنْ ذَنْبِهِ».

"ረመዷንን አምኖበትና (ምንዳ እንደሚያገኝበት) አስቦ (በሶላት) የቆመ ሰው ያለፈው ወንጀሉ ይማርለታል። ለይለቱል ቀደርንም አምኖበትና (ምንዳ እንደሚያገኝበት) አስቦ (በሶላት) የቆመ ሰው ያለፈው ወንጀሉ ይማርለታል።" የሸዕባን ወር አጋማሽ ሌሊት፣ ወይም የረጀብ ወር የመጀመሪያው ጁሙዓ ሌሊት ወይም የኢስራእ እና የሚዕራጅ ሌሊት በበዓል ወይም በሆነ የአምልኮ አይነት መለየቱ የተደነገገ ቢሆን ኖሮ ነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ህዝባቸውን ወደርሱ ባመላከቱ ወይም እራሳቸው በሰሩት ነበር። ከዚህ አይነቱ አንዱም ነገር ተከስቶ ቢሆን ኖሮ ሶሓቦች (አላህ ስራቸውን ይውደድላቸውና) ለህዝቡ ባስተላለፉት ነበር፤ ከነርሱም አይደብቁትም ነበር። እነርሱ ከነቢያት (ዐለይሂሙ ሰላም) በኋላ ከሰዎች ሁሉ በላጭና ለሰዎች ሁሉ በበለጠ መካሪዎች ናቸውና። አላህም ከአላህ መልእክተኛ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ባልደረቦች ስራቸውን ይውደድላቸው፤ እነሱንም ደስ ያሰኛቸው።

ከዚህ ቀደም ከሊቃውንት ንግግር እንደታወቀው የረጀብ ወር የመጀመሪያ ጁሙዓ ሌሊትንም ሆነ የሸዕባን ወር አጋማሽ ሌሊትን ብልጫ አስመልክቶ ከነቢዩም ﷺ ሆነ ከሶሓቦቻቸው ረዲየላሁ ዐንሁም ምንም የጸደቀ ነገር የለም። በመሆኑም በነዚህ በሁለቱ (ሌሊቶች) ማክበር በእስልምና ውስጥ አዲስ መጤ ፈጠራ መሆኑ ይታወቃል። በተመሳሳይም በሆነ አምልኮ ነጥሎ መለየት የተወገዘ ፈጠራ (ቢድዓ) ነው። እንደዚሁም አንዳንድ ሰዎች የኢስራእና የሚዕራጅ ሌሊት ናት ብለው የሚያምኗት የረጀብ ወር ሃያ ሰባተኛዋ ሌሊት ቀደም ሲል በተጠቀሱት ማስረጃዎች መሰረት በምንም አይነት አምልኮ መለየትም ሆነ እርሷን ማክበር አይፈቀድም። ይህ እኮ ሌሊቷ የምትታወቅ ናት ካልን ነው፤ ታዲያ ከዑለማዎች ንግግሮች ትክክለኛው አቋም ሌሊቷ የማትታወቅ መሆኗ ሆኖ ሳለ እንዴት ሊሆን ይችላል? እርሷ የረጀብ ወር ሃያ ሰባተኛዋ ሌሊት ናት የሚለው ንግግር በትክክለኛ ሐዲሶች መሠረት የሌለው ውድቅ የሆነ አባባል ነው። እንዲህ ያለውም ሰው መልካም ተናግሯል፦

ከጉዳዮች ሁሉ በላጩ በቅኑ መንገድ ላይ የነበሩት የቀደሙት ሲሆኑ ከጉዳዮች ሁሉ ክፉው ደግሞ አዲስ መጤ ፈጠራዎች ናቸው።

አላህን እኛንም ሆነ መላ ሙስሊሞችን ሱናን አጥብቆ መያዝንና በእርሷ ላይ መፅናትን፣ ከሚቃረናት ነገርም መጠንቀቅን እንዲገጥመን እንጠይቀዋለን። እርሱ ቸርና ለጋስ ነውና።

የአላህ ሰላትና ሰላም በባሪያውና መልዕክተኛው በነብያችን ሙሐመድ፣ በቤተሰቦቻቸውና በባልደረቦቻቸው ሁሉ ላይ ይስፈን።

 

***

بِسْمِ اللهِ الرَّحمَنِ الرَّحِيمِ

ስምንተኛው መልዕክት፡

በውሸት ስለተነገረው ኑዛዜ የተሰጠ አስፈላጊ ማሳሰቢያ

ለሐረመ ነበዊ አሸሪፍ አገልጋይ ሸይኽ አሕመድ

ከዐብዱልዐዚዝ ቢን ዐብደላህ ቢን ባዝ ይህንን መልዕክት ለሚያገኘው ሙስሊም ባጠቃላይ የተላለፈ መልዕክት፦ አላህ በእስልምና ይጠብቃቸው፤ እኛንም እነርሱንም ከመሃይማንና ከብኩኖች (ከመናኛ) የቅጥፈት ክፋት ይጠብቀን። አሚን።

የአላህ ሰላም እዝነትና በረከቱ በናንተ ላይ ይስፈን

ከዚህ በመቀጠል፡ በተከበረው የነብዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ሐረም አገልጋይ በሆኑት በሸይኽ አሕመድ ስም የተላለፈችንና «ይህች ከመዲነቱል ሙነወራ፤ ከተከበረው የነብዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ሐረም አገልጋይ ከሸይኽ አሕመድ የተላለፈች ምክር ናት» የሚል ርዕስ ያላትን አንድ መልእክት ተመልክቻለሁ፤ በውስጧም እንዲህ ብሏል፡-

«የጁሙዓን ሌሊት ሳልተኛ ክቡር ቁርኣንን እቀራ ነበር። የአላህን መልካም ስሞችም ከቀራሁ በኋላ ለመተኛት ተዘጋጀሁ። በዚያም አንፀባራቂ ገፅታ ባለቤት የሆኑትን፣ የቁርኣን አንቀፆችንና የተከበሩ ህግጋትን ይዘው የመጡትን፣ ለዓለማት እዝነት የሆኑትን መሪያችንን ሙሐመድን (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) በህልሜ አየኋቸው። እንዲህም አሉኝ፦ ‹ሸይኽ አሕመድ ሆይ!› እኔም አልኩኝ፦ ‹አቤት! የአላህ መልክተኛ ሆይ! የፍጡራን ሁሉ በላጭ ሆይ!›» እንዲህም አሉኝ፦ "በሰዎች አስቀያሚ ድርጊት አፍሬያለሁ፤ ጌታዬንም ሆነ መላኢካዎችን መገናኘት አልቻልኩም፤ ምክንያቱም ከጁምዓ እስከ ጁምዓ መቶ ስልሳ ሺህ ሰዎች በእስልምና ዲን ላይ ሳይሆኑ ሞተዋል።" ከዚያም ሰዎች ከወደቁባቸው ኃጢኣቶች መካከል ከፊሉን ጠቀሰ፤ ከዚያም «ይህች ምክር አሸናፊና ሃያል ከሆነው (ጌታ) ዘንድ ለነርሱ የተደረገች እዝነት ናት።» አሉ፡፡ ከዚያም የተወሰኑ የትንሳኤ ምልክቶችን አውስተው እንዲህ አሉ፦ «አንተ ሸይኽ አሕመድ ሆይ ይህችን ኑዛዜ ንገራቸው፤ ምክንያቱም እሷ ከለውሐል መሕፉዝ በቀደር ብዕር የተወሰደች ናትና፤ የሚጽፋትና ከሀገር ወደ ሀገር፣ እንዲሁም ከቦታ ወደ ቦታ የሚልካት ሰው በጀነት ውስጥ ቤተ-መንግስት ይገነባለታል፤ ያልጻፋትና ያልላካት ሰው ደግሞ የትንሳኤው ቀን ሸፋዓዬ በርሱ ላይ እርም ትሆንበታለች።» የጻፋትም ሰው ድሃ ቢሆን አላህ ባለፀጋ ያደርገዋል፤ እዳ ያለበትም ቢሆን አላህ እዳውን ይከፍልለታል፤ ወይም ወንጀል ያለበት ቢሆን በዚህች ኑዛዜ በረከት አላህ ለእርሱም ለወላጆቹም ይምርላቸዋል። ከአላህ ባሮችም ውስጥ ያልጻፋት፤ ፊቱ በቅርቢቱም ሆነ በመጨረሻይቱ ዓለም ይጠቁራል። እንዲህም አለ፡ «በታላቁ አላህ ሶስት ጊዜ እምላለሁ፤ ይህ እውነት ነው። እኔ ውሸታም ከሆንኩ ከእስልምና ውጪ ሆኜ ከዱንያ ልውጣ። በርሷ ያመነ ከእሳት ቅጣት ይድናል፤ በርሷ ያስተባበለ ደግሞ ከፍሯል።»

ይህ በአላህ መልክተኛ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ላይ የተቀጠፈው የኑዛዜው ማጠቃለያ ነው። ይህንኑ የተቀጠፈ ኑዛዜ ከበርካታ ዓመታት ወዲህ ብዙ ጊዜ ሰምተነዋል፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ በሰዎች መካከል እየተሰራጨና በብዙሃኑ ተራው ህዝብም ዘንድ እየተስፋፋ ይገኛል። በአገላለጾቹም ላይ ልዩነቶች አሉት። ይህም ቀጣፊ ነቢዩን (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) በህልሙ እንዳያቸውና ይህችንም አደራ እንደሰጡት ይናገራል። አንባቢ ሆይ ላንተ በጠቀስናት በዚህች የመጨረሻዋ ጽሑፍ ላይም፣ ቀጣፊው ለመተኛት በተዘጋጀ ጊዜ ነቢዩን (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) እንዳያቸው ይሞግታል፤ ይህ ማለት ደግሞ፡ በውናቸው አይቷቸዋል ማለት ነው።

ይህ ቀጣፊ በዚህ ኑዛዜው ውስጥ እጅግ ግልጽ ውሸት እና ፍጹም ከንቱ የሆኑ ብዙ ነገሮችን ሞግቷል፤ ኢንሻ አላህ በዚሁ ጽሑፍ ውስጥ በቅርቡ እጠቁምሃለሁ። በእርግጥም ባለፉት ዓመታት ይህንን ጉዳይ በተመለከተ አስጠንቅቄያለሁ፤ ለሰዎችም እጅግ ግልጽ ውሸት እና ፍጹም ከንቱ ነገር መሆኑን አብራርቻለሁ። ይህን የመጨረሻውን ህትመት ባየሁ ጊዜ፤ ከንቱነቱ ግልጽ በመሆኑና ቀጣፊው በውሸት ላይ ያለው ከፍተኛ ድፍረት የተነሳ ስለ ጉዳዩ ከመጻፍ አመንትቼ ነበር። ይህ ከንቱ ነገር ትንሽ እንኳን ማስተዋል ወይም ጤናማ ተፈጥሮ ባለው ሰው ዘንድ ተቀባይነት ያገኛል ብዬ ፈጽሞ አላሰብኩም ነበር። ነገር ግን ብዙ ወንድሞች በብዙ ሰዎች ዘንድ እንደተሰራጨች፣ በመካከላቸውም እንደሚቀባበሏትና ከፊሎቻቸውም እውነት መሆኗን እንዳመኑ ስለነገሩኝ፣ ሀሰትነቷንና በአላህ መልዕክተኛ -የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን- ላይ የተቀጠፈች መሆኗን በመግለፅ ማንም እንዳይታለልባት በእኔ አምሳያዎች ላይ መፃፍ እንደሚገባ አየሁ። ከእውቀትና ከእምነት ባለቤቶች፣ ወይም ከንጹሕ ተፈጥሮና ከትክክለኛ አእምሮ ባለቤቶች የሆነ ሰው እርሷን ቢያስተነትናት፤ በብዙ መንገዶች ውሸትና ቅጥፈት መሆኗን ያውቃል፡፡

በእርግጥም ይህች ቅጥፈት የምትጠጋባቸውን የሸኽ አሕመድን አንዳንድ ዘመዶች ስለዚች ኑዛዜ ጠይቄአቸው ነበር፤ የመለሱልኝም መልስ፦ ኑዛዜዋ በሸኽ አሕመድ ላይ የተቀጠፈች መሆኗንና እርሳቸውም በፍፁም አለማለታቸውን ነው። እናም ጽሁፉ ላይ የተጠቀሱት ሼኽ አሕመድ ከሞቱ ቆይተዋል። የተጠቀሱት ሼኽ አሕመድ ወይም ከእርሳቸው የበለጠ ትልቅ ሰው ነቢዩን (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) በህልምም ሆነ በእውን እንዳያቸውና ይህንንም አደራ እንደሰጡት ቢሞግት እንኳ በእርግጠኝነት ውሸታም መሆኑን ወይም ይህን ያለው አካል መልእክተኛው (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ሳይሆን ሰይጣን መሆኑን እናውቅ ነበር፤ ይህም ለበርካታ ምክንያቶች ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ፡

በመጀመሪያ: መልእክተኛው (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ከሞቱ በኋላ በእውን አይታዩም። ከሱፊያ ጃሂሎች ውስጥ ነቢዩን (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) በእውን እንደሚያይ፣ ወይም በመውሊድ ላይ እንደሚገኙ፣ ወይም ይህን የመሳሰለውን ነገር የሚሞግት ሰው፤ በእርግጥም እጅግ አስቀያሚ የሆነን ስህተት ተሳስቷል፤ በከፍተኛ ሁኔታም ነገሩ ተመሳስሎበታል፤ በታላቅ ስህተትም ውስጥ ወድቋል፤ ቁርአንን፣ ሱናንና የእውቀት ባለቤቶችን ስምምነትም ተፃርሯል። ምክንያቱም ሙታን ከቀብራቸው የሚወጡት በትንሳኤ ቀን እንጂ በዱንያ አይደለምና። ከዚህ በተቃራኒ የተናገረ ሰው፤ እርሱ ደጋግ ቀደምቶች ያወቁትንና የአላህ መልእክተኛ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ሶሓቦችና እነርሱን በበጎ የተከተሏቸው የተጓዙበትን እውነት ያላወቀ ግልጽ ውሸታም፣ ወይም የተሳሳተና ነገሩ የተምታታበት ነው። የላቀው አላህ እንዲህ ብሏል፦

﴿ثُمَّ إِنَّكُم بَعۡدَ ذَٰلِكَ لَمَيِّتُونَ15 ثُمَّ إِنَّكُمْ يَوْمَ الْقِيَامَةِ تُبْعَثُونَ16﴾

{ ከዚያም እናንተ ከዚህ በኋላ በእርግጥ ሟቾች ናችሁ:: ከዚያም እናንተ በትንሳኤ ዕለት ትቀሰቀሳላችሁ::}

«أَنَا أَوَّلُ مَنْ تَنْشَقُّ عَنْهُ الْأَرْضُ يَوْمَ الْقِيَامَةِ، وَأَنَا أَوَّلُ شَافِعٍ وَأَوَّلُ مُشَفَّعٍ».

«እኔ የትንሳኤ ቀን ምድር መጀመሪያ የምትሰነጠቅለት ነኝ፤ የመጀመሪያው አማላጅም የመጀመሪያውም ምልጃ ተቀባይ የሆነ ነኝ።» ይህንን መልዕክት ያዘሉ የቁርኣን አንቀጾችና ሐዲሦች በርካታ ናቸው።

ሁለተኛው: መልክተኛው (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) በህይወታቸውም ሆነ በሞታቸው ከሐቅ ውጭ የሆነን ነገር አይናገሩም፤ ይህ ኑዛዜ ሸሪዐቸውን በግልፅ ይፃረራል፤ ይህም -በኋላ ላይ እንደሚብራራው- በብዙ መልኩ ነው። እርሳቸው (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) በህልም ይታያሉ። በህልሙ በተከበረው ቁመናቸው ያያቸው ሰው በእርግጥም እርሳቸውን አይቷል፤ ምክንያቱም ሸይጧን በእርሳቸው ቁመና ሊመሰል አይችልምና፤ ትክክለኛ በሆነው በተከበረው ሐዲስ እንደመጣው። ነገር ግን ዋናው ጉዳይ ያለው ህልም ባየው ሰው ኢማን፣ እውነተኝነት፣ ፍትሐዊነት፣ ጥንቁቅነት፣ ሃይማኖተኝነትና ታማኝነት ላይ ነው፤ እናም ነቢዩን (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ያያቸው በእውነተኛ ቁመናቸው ነው ወይስ በሌላ? የሚለው ነው።

ነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) በሕይወት ዘመናቸው የተናገሩት ሐዲሥ ቢመጣ እንኳን፤ ታማኝ፣ ፍትሐዊና ጠንካራ የማስታወስ ችሎታ ባላቸው ዘጋቢዎች መንገድ ካልሆነ ተቀባይነት አይኖረውም፤ ማስረጃም አይሆንም። ወይም ታማኝና ጠንካራ የማስታወስ ችሎታ ባላቸው ዘጋቢዎች መንገድ ቢመጣ ነገር ግን ከእነርሱ የበለጠ ጠንካራ የማስታወስ ችሎታ ያላቸውንና ይበልጥ ታማኝ የሆኑትን ዘገባ ሁለቱን ማስታረቅ በማይቻልበት ሁኔታ የሚፃረር ከሆነ፤ ይህ መስፈርቶቹን ባሟላ ሁኔታ የሚቻል ከሆነ፤ አንደኛው ሥራ ላይ የማይውል ‘መንሱኽ’ (የተሻረ) ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ሥራ ላይ የሚውል ‘ናሲኽ’ (ሻሪ) ይሆናል። ማስታረቅም ሆነ መሻር የማይቻል ከሆነ ደግሞ፤ የማስታወስ ችሎታው አነስተኛና ፍትሐዊነቱም ዝቅተኛ የሆነውን ዘጋቢ ዘገባ ውድቅ ማድረግ ግዴታ ይሆናል። ዘገባውም ሥራ ላይ የማይውል “ሻዝ” (ብቸኛና ደካማ ዘገባ) ተብሎ ይፈረድበታል።

ታዲያ ከአላህ መልእክተኛ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ያስተላለፈው ባለቤቱም ሆነ ታማኝነቱና ፍትሃዊነቱ የማይታወቅ ኑዛዜ እንዴት [ተቀባይነት ይኖረዋል]! ይህ ኑዛዜ በዚህ ሁኔታው በውስጡ ሸሪዓን የሚፃረር ነገር ባይኖርበትም እንኳ ሊጣልና ትኩረት ሊነፈገው የተገባ ነው። ታዲያ ኑዛዜው ሐሰት መሆኑን የሚያመላክቱ በርካታ ጉዳዮችን ያካተተ፣ በአላህ መልእክተኛ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ላይ የተቀጠፈ እና አላህ ያልፈቀደውን ዲን የሚደነግግ ከሆነማ እንዴት ሊሆን ነው?

ነቢዩም የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን እንዲህ ብለዋል፦

«مَنْ قَالَ عَلَيَّ مَا لَمْ أَقُلْ؛ فَلْيَتَـبَوَّأْ مَقْعَدَهُ مِنَ النَّارِ».

"በኔ ላይ ያላልኩትን የተናገረ ሰው ከእሳት የሆነ መቀመጫውን ያዘጋጅ።" በእርግጥ ይህንን ኑዛዜ በአላህ መልክተኛ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ላይ የቀጠፈው ሰው እርሳቸው ያላሉትን ተናግሯል፤ ግልፅና አደገኛ የሆነ ውሸትንም በርሳቸው ላይ ዋሽቷል። ወደ ተውበት (ንሰሀ) ለመመለስ ካልተጣደፈና ይህ ኑዛዜ በአላህ መልክተኛ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ላይ የተቀጠፈ ውሸት መሆኑን ለሰዎች ይፋ ካላደረገ ለዚህ ታላቅ ዛቻ የተገባ ይሆናል። ምክንያቱም በሰዎች መካከል ባጢልን (ውድቅን) ያሰራጨና ወደ ዲንም ያስጠጋ ሰው፤ ሰዎች ከውሸቱ መመለሱንና ራሱንም ማስተባበሉን እንዲያውቁ በይፋ በማወጅና ግልፅ በማድረግ ካልሆነ በስተቀር ከዚህ ወንጀሉ ተውበቱ ተቀባይነት አይኖረውም። ክብሩና ጥራቱ የላቀው አላህ እንዲህ ብሏልና፦

﴿إِنَّ ٱلَّذِينَ يَكۡتُمُونَ مَآ أَنزَلۡنَا مِنَ ٱلۡبَيِّنَٰتِ وَٱلۡهُدَىٰ مِنۢ بَعۡدِ مَا بَيَّنَّٰهُ لِلنَّاسِ فِي ٱلۡكِتَٰبِ أُوْلَٰٓئِكَ يَلۡعَنُهُمُ ٱللَّهُ وَيَلۡعَنُهُمُ ٱللَّٰعِنُونَ159 إِلَّا ٱلَّذِينَ تَابُواْ وَأَصۡلَحُواْ وَبَيَّنُواْ فَأُوْلَٰٓئِكَ أَتُوبُ عَلَيۡهِمۡ وَأَنَا ٱلتَّوَّابُ ٱلرَّحِيمُ160﴾

{ እነዚያ ከአንቀጾችና ከቅን መምሪያ ያወረድነውን ለሰዎች በመጽሐፉ ከገለጽነው በኋላ የሚደብቁትን አላህ ይረግማቸዋል:: ረጋሚዎችም ሁሉ ይረግሟቸዋል::

እነዚያ የተጸጸቱ፤ (ያበላሹትን) ያስተካከሉና (የደበቁትንም) የገለጹ ሲቀሩ:: የእነርሱን ጸጸትንማ እቀበላለሁ:: እኔም ጸጸትን ተቀባይ አዛኝ ነኝ::} [አል-በቀራህ 159-160] የላቀው አላህ በዚህች በተከበረች አንቀጽ ላይ ከእውነት አንዳች ነገር የደበቀ ሰው፤ ካስተካከለና ግልፅ ካደረገ በኋላ ካልሆነ በቀር ንስሃው ትክክል እንደማይሆን አብራርቷል። የላቀው አላህ ለባሮቹ ሃይማኖትን አሟልቷል፤ መልዕክተኛውን ሙሐመድን (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) በመላክና ወደ እርሳቸውም ካወረደው የተሟላ ሸሪዓ ጋር ፀጋውንም በነርሱ ላይ ሙሉ አድርጓል። እርሳቸውንም ከማሟላትና ግልፅ ከማድረግ በኋላ እንጂ ወደ ራሱ አልወሰዳቸውም፤ የላቀው እንዲህ እንዳለው፦

﴿...ٱلۡيَوۡمَ أَكۡمَلۡتُ لَكُمۡ دِينَكُمۡ وَأَتۡمَمۡتُ عَلَيۡكُمۡ نِعۡمَتِي وَرَضِيتُ لَكُمُ ٱلۡإِسۡلَٰمَ دِينٗا...﴾

{…ዛሬ ሃይማኖታችሁን ሞላሁላችሁ፤ ጸጋየንም በእናንተ ላይ ፈጸምኩ፤ ለእናንተም በሃይማኖትነት ኢስላምን ወደድኩላችሁ።…} [አል‐ማኢዳህ: 3]

የዚህ ወሲያ ቀጣፊ በአስራ አራተኛው ክፍለ ዘመን የመጣ ሲሆን፣ ድንጋጌውን ለተቀበለ ጀነት እንዲገባና ላልተቀበለው ደግሞ ከጀነት ተከልክሎ እሳት እንዲገባ የሚያደርግ አዲስ ዲን በሰዎች ላይ ሊያምታታባቸው ይፈልጋል። ይህችን የቀጠፋትን ኑዛዜ ከቁርኣን የበለጠችና የላቀች ሊያደርጋት ይፈልጋል። በውስጧም እንዲህ ሲል ቀጥፏል፦ «ይህችን የጻፈና ከአገር ወደ አገር ወይም ከቦታ ወደ ቦታ የላካት ሰው፤ በጀነት ቤተ መንግስት ይገነባለታል። ያልጻፋትና ያልላካት ደግሞ የቂያማ ቀን የነቢዩን (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ምልጃ ይከለከላል።» ይህ ከውሸቶች ሁሉ እጅግ የከፋው ሲሆን የዚህንም ኑዛዜ ውሸትነት፣ የቀጣፊውንም የሐፍረት ማጣትና በውሸት ላይ ያለውን ታላቅ ድፍረት ከሚያሳዩ ግልጽ ማስረጃዎች መካከል አንዱ ነው። ምክንያቱም የተከበረውን ቁርኣን ጽፎ ከአገር ወደ አገር ወይም ከቦታ ወደ ቦታ የላከ ሰው እንኳ በተከበረው ቁርኣን ካልሠራበት ይህን ትሩፋት አያገኝም። ታዲያ ይህን ቅጥፈት ለጻፈውና ከአገር ወደ አገር ላስተላለፈው እንዴት ሊገኝለት ይችላል? ቁርኣንን ያልጻፈና ከአገር ወደ አገር ያልላከ ሰው በነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ያመነና ሸሪዓቸውን የሚከተል ከሆነ የርሳቸውን ሸፋዓ አይከለከልም። በዚህ ኑዛዜ ውስጥ ያለችው ይህቺ አንዲት ቅጥፈት ብቻዋን፣ የኑዛዜውን ውድቅነት፣ የአሰራጩን ውሸታምነት፣ ድፍረቱን፣ ጅልነቱንና መልእክተኛው ﷺ ይዘውት ከመጡት ቅን መንገድ ያለውን ርቀት ለማመላከት በቂ ናት።

በዚህ ኑዛዜ ውስጥ — ከተጠቀሰው በተጨማሪ — ውድቅና ውሸት መሆኑን የሚያመለክቱ ሌሎች ጉዳዮች ይገኙበታል። ቀጣፊው ትክክል መሆኑን ለማረጋገጥ ሺህ ጊዜ ወይም ከዚያ በላይ ቢምልም፣ እውነተኛ መሆኑን ለማሳየት በራሱ ላይ ታላቁን ቅጣትና የከፋውን መከራ ቢለምንም (ቀጣፊው) እውነተኛ ሊሆን አይችልም፤ ኑዛዜውም ትክክል አይሆንም። ይልቁንም በአላህም ከዚያም በድጋሚ በአላህም (እምላለሁ)፤ ከባጢሎች ሁሉ እጅግ የከፋና አስቀያሚ ነው። እኛም አላህን (ሱብሓነሁ) እና ከእኛ ጋር የተገኙትን መላኢኮች እናስመሰክራለን! ይህ ጽሑፍ ከደረሳቸው ሙስሊሞች ዘንድ የምንመሰክረው ምስክርነት — እርሱም ጌታችን ጀለ ጀላሉሁ ፊት የምንቀርብበት ነው — ይህ ኑዛዜ በአላህ መልክተኛ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ላይ የተፈጠረ ውሸትና ቅጥፈት መሆኑን ነው። ይህን የቀጠፈውን አላህ ያዋርደው፤ የሚገባውንም ፍርዱን ይስጠው።

ከዚህ ቀደም ከተጠቀሰው በተጨማሪ የዚህችን ኑዛዜ ውሸት መሆኗንና መበላሸቷን ከተጠቀሰው ጽሑፍ የሚጠቁሙ በርካታ ነገሮች አሉ። ከነሱም መካከል፡

አንደኛው ነጥብ፡ በውስጡ የተጠቀሰው «ከጁሙዓ እስከ ጁሙዓ አንድ መቶ ስልሳ ሺህ ሰዎች ከእስልምና ውጭ በሆነ ሃይማኖት ላይ ሆነው ሞተዋል» የሚለው ንግግር ነው። ምክንያቱም ይህ የሩቅ ምስጢር እውቀት ነውና። መልዕክተኛው (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ከሕልፈታቸው በኋላ ወሕይ ተቋርጦባቸዋል። እርሳቸው በህይወት እያሉ ሩቅ ምስጢርን የማያውቁ ከነበሩ ከሕልፈታቸው በኋላ እንዴት ሊያውቁ ይችላሉ? ልዕልናው የላቀው አላህ እንዲህ ብሏል፡

﴿قُل لَّآ أَقُولُ لَكُمۡ عِندِي خَزَآئِنُ ٱللَّهِ وَلَآ أَعۡلَمُ ٱلۡغَيۡبَ...﴾

{«የአላህ ግምጃ ቤቶች እኔ ዘንድ ናቸው አልላችሁም:: ሩቅ ሚስጥርንም አላውቅም...» በላቸው።} [አል'አንዓም: 50] አላህ እንዲህም ብሏል:

﴿قُل لَّا يَعۡلَمُ مَن فِي ٱلسَّمَٰوَٰتِ وَٱلۡأَرۡضِ ٱلۡغَيۡبَ إِلَّا ٱللَّهُ...﴾

{«በሰማያትና በምድር ያለው ሁሉ ሩቅን ምስጢር አያውቅም:: አላህ ግን ያውቀዋል...» በላቸው።} [አንነምል፡ 65] ሶሒሕ በሆነ ሐዲሥም ነቢዩ ﷺ እንዲህ ማለታቸው ተላልፏል፡-

«يُذَادُ رِجَالٌ عَنْ حَوْضِي يَوْمَ القِيَامَةِ، فَأَقُولُ: يَا رَبِّ! أَصْحَابِي أَصْحَابِي، فَيُقَالُ لِي: إِنَّكَ لَا تَدْرِي مَا أَحْدَثُوا بَعْدَكَ، فَأَقُولُ كَمَا قَالَ العَبْدُ الصَّالِحُ: ﴿وَكُنتُ عَلَيۡهِمۡ شَهِيدٗا مَّا دُمۡتُ فِيهِمۡۖ فَلَمَّا تَوَفَّيۡتَنِي كُنتَ أَنتَ ٱلرَّقِيبَ عَلَيۡهِمۡۚ وَأَنتَ عَلَىٰ كُلِّ شَيۡءٖ شَهِيدٌ [المائدة: 117]».

«በትንሳኤው ቀን ሰዎች ከሐውዴ ይከለከላሉ፤ እኔም፡- “ጌታዬ ሆይ! ባልደረቦቼ፤ ባልደረቦቼ” እላለሁ። ለኔም፡- “ከአንተ በኋላ ምን አዲስ ነገር እንደፈጠሩ አታውቅም” እባላለሁኝ። እኔም መልካሙ ባሪያ እንዳለው እላለሁ፡-{በውስጣቸውም እስካለሁ ድረስ በነርሱ ላይ ተጣባበቂ ነበርኩ፡፡ በተሞላኸኝም ጊዜ (ባነሳኸኝ ጊዜ) አንተ በነሱ ላይ ተጠባባቂ ነበርክ፡፡ አንተም በነገሩ ሁሉ ላይ ዐዋቂ ነህ።} [አል-ማኢዳህ፡ 117]»

ሁለተኛው ጉዳይ፦ -ይህ ኑዛዜ ውድቅና ሐሰት መሆኑን ከሚያመላክቱት መካከል-፤ በውስጡ የተጠቀሰው ቃል እንዲህ የሚል ነው፦ «ይህን የጻፈ ሰው ድሃ ቢሆን አላህ ባለጸጋ ያደርገዋል፤ ባለዕዳ ከሆነ አላህ እዳውን ይከፍልለታል፤ ወንጀል ያለበት እንደሆነም በዚሁ ኑዛዜ በረከት አላህ ለርሱም ለወላጆቹም ይምርለታል» ወዘተ። ይህ ደግሞ ከባድ ውሸትና የቀጣፊውንም ውሸታምነት እንዲሁም ከአላህና ከባሮቹ ሐያእ ማጣቱን የሚያሳይ ግልፅ ማስረጃ ነው። ምክንያቱም እነዚህ ሦስቱ ነገሮች የተከበረውን ቁርኣን በመጻፍ ብቻ አይገኙምና። ታዲያ ይህችን ውድቅ ኑዛዜ ለጻፈው ሰው እንዴት ሊገኙለት ይችላሉ? የዚህ ውዳቂ ፍላጎቱ ሰዎችን ማወናበድና በዚህ ኑዛዜ እንዲቆራኙ ማድረግ ነው፤ ይህም ኑዛዜውን እንዲፅፉትና በዚህ ሀሰተኛ ትሩፋት እንዲንጠለጠሉ፣ እንዲሁም አላህ ለባሮቹ የደነገጋቸውንና ወደ ሲሳይ፣ እዳን መክፈልና የወንጀል ምህረት የሚያደርሱ ሰበቦችን እንዲተዉ ነው። ከውርደት ሰበቦች፣ ስሜትን ከመከተልና ከሸይጧንም በአላህ እንጠበቃለን።

ሦስተኛው ጉዳይ፡ —ይህ ኑዛዜ ውድቅ መሆኑን ከሚያመላክቱ ጉዳዮች መካከል— በውስጡ “ከአላህ ባሪያዎች መካከል ይህችን ያልጻፈ፤ ፊቱ በዱንያም በአኼራም ይጠቁራል።” ማለቱ ነው። ይህ ደግሞ እጅግ አስቀያሚ ከሆኑ የውሸት አይነቶችና ይህ ኑዛዜ ፍፁም ውድቅ መሆኑን እንዲሁም ቀጣፊውም ውሸታም እንደሆነ ከሚያመላክቱ ግልፅ ማስረጃዎች መካከል ነው። ለነገሩ እንዴት ሆኖ ነው አንድ አዕምሮ ያለው ሰው በአስራ አራተኛው ክፍለ ዘመን አንድ ማንነቱ ያልታወቀ ግለሰብ በአላህ መልዕክተኛ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ላይ ቀጥፎ ይዞት መጣ የተባለውንና «ይህን ኑዛዜ ያልፃፈ ሰው ፊቱ በዱንያም በአኺራም ይጠቁራል፤ የጻፈው ደግሞ ከድህነት በኋላ ሃብታም ይሆናል፤ ከተደራረበበት እዳም ነፃ ይወጣል፤ ለሰራውም ወንጀል ሁሉ ምህረት ያገኛል!!» የሚለውን ኑዛዜ ሊቀበለው የሚችለው?

ሱብሐነሏህ፤ ይህ ታላቅ ቅጥፈት ነው!! ማስረጃዎችና ነባራዊው ሁኔታም የዚህን ቀጣፊ ውሸታምነት፣ በአላህ ላይ ያለውን የድፍረቱን ታላቅነት፣ ከአላህና ከሰዎችም ያለውን የሐፍረት ማነስ ይመሰክራሉ፡፡ እነሆ ብዙ ሕዝቦች አልጻፏትም፤ ፊቶቻቸውም አልጠቆሩም፡፡ እዚህም ጋር ቁጥራቸውን አላህ እንጂ ሌላ የማያውቃቸው እጅግ በርካታ ሕዝቦች ብዙ ጊዜ ጽፈዋታል፡፡ ዕዳቸውም አልተከፈለም፤ ድህነታቸውም አልተወገደም፡፡ ከቀልቦች ጥመትና ከወንጀሎች ዝገትም በአላህ እንጠበቃለን፡፡ እነዚህማ የተከበረው ሸሪዓ ከመጽሐፍት ሁሉ በላጩንና ታላቁን የሆነውን የተከበረውን ቁርኣን ለጻፈ ሰው እንኳን ያልደነገጋቸው ባህሪያትና ቅጣቶች ናቸው። ታዲያ የተለያዩ የባጢል (የውሸት) አይነቶችንና በርካታ የክህደት ንግግሮችን የያዘችን የሐሰት ኑዛዜ ለጻፈ ሰው እንዴት ትገኛለች? አላህ ጥራት ይገባው! በእርሱ ላይ በመዋሸት ድፍረት በፈጸሙት ላይ ምንኛ ታጋሽ ነው!

አራተኛው፦ ይህ ኑዛዜ ፍፁም ውድቅና ግልፅ ውሸት መሆኑን ከሚያመለክቱት መካከል፤ በውስጡ «በእርሷ ያመነ ከጀሀነም ቅጣት ይድናል፤ የካዳትም ከፍሯል» የሚለው ንግግሩ ነው። ይህም ደግሞ በውሸት ላይ ከሚደረግ ከባባድ ድፍረት እና ከእጅግ አስቀያሚ ውሸትም ነው። ይህ ቀጣፊ ሰዎችን ሁሉ በቅጥፈቱ እንዲያምኑ ይጣራል፤ በዚህም ከጀሀነም ቅጣት እንደሚድኑና በርሱ ያስተባበለ ደግሞ እንደሚከፍር ይሞግታል። በአላህ ይሁንብኝ! ይህ ውሸታም በአላህ ላይ ታላቅ ቅጥፈትን በእርግጥ ቀጥፏል፤ ከእውነት የራቀንም ነገር ተናግሯል። ያስተባበላት ሳይሆን በእርሷ ያመነ ሰው ነው ከሓዲ ሊሆን የሚገባው፤ ምክንያቱም እርሷ ምንም ዓይነት የእውነት መሠረት የሌላት ቅጥፈት፣ ከንቱና ውሸት ናትና። እኛም እርሷ ውሸት መሆኗንና ቀጣፊዋም ውሸታም መሆኑን አላህን እናስመሰክራለን። አላህ ያልፈቀደውን ለሰዎች ሊደነግግና ከእርሱ ያልሆነውንም በዲናቸው ውስጥ ሊያስገባ ይፈልጋል። አላህ ግን ከዚህች ቅጥፈት በአሥራ አራት ክፍለ ዘመናት በፊት ለዚህ ኡማ ዲኑን ሙሉ አድርጎና አሟልቶታል። እናንተ አንባቢያንና ወንድሞች ሆይ አስተውሉ፤ እንዲህ አይነት የተቀጠፉ ውሸቶችን ከማመንና በመካከላችሁ እንዲሰራጩ ከማድረግ ተጠንቀቁ፡፡ እውነት ብርሃን ስላለው በፈላጊው ላይ አሻሚ አይሆንምና። ስለዚህ እውነትን በማስረጃው ፈልጉ፤ አሻሚ የሆነባችሁንም ነገር የዕውቀት ባለቤቶችን ጠይቁ፡፡ በውሸታሞች መሐላም አትሸወዱ፤ የተረገመው ኢብሊስ ለወላጆቻችሁ ለአደም እና ሐዋ እርሱ ለነርሱ ከመካሪዎች እንደሆነ ምሎላቸዋልና። እርሱ ግን ከከሐዲዎች ሁሉ ታላቁና ከውሸታሞችም ሁሉ የበለጠ ውሸታም ነው፡፡ አላህ ስለ እርሱ ይህን ሲተርክ እንዲህ ብሏል፦

﴿وَقَاسَمَهُمَآ إِنِّي لَكُمَا لَمِنَ ٱلنَّٰصِحِينَ21﴾

{«እኔ ለእናንተ በእርግጥ ከሚመክሯችሁ ነኝ።» ሲልም ማለላቸው።} [አል-አዕራፍ፡ 21] እርሱንና ቀጣፊ ተከታዮቹንም ተጠንቀቁ። እርሱም ሆኑ እነርሱ፣ ለማሳሳትና ለማጥመም ስንትና ስንት የውሸት መሐላዎች፣ ቃል አፍራሽ ኪዳኖችና ያጌጡ ንግግሮች አሏቸውና! ይህ ቀጣፊ ስለ ውግዝ ተግባራት መበራከት የጠቀሰው ነገር እውን የሆነ ጉዳይ ነው። ክቡር ቁርኣንና የጠራችው ሱናም ከእርሷ በብርቱ አስጠንቅቀዋል። በሁለቱም ውስጥ መመራትና በቂነት አለ።

የሰዓቲቱን ምልክቶች በተመለከተ ለተጠቀሰው ነገርማ፤ የነቢያዊ ሐዲሦች ከሰዓቲቱ ምልክቶች መካከል የሚሆኑትን አብራርተዋል። ክቡር ቁርኣንም ከፊሉን አመላክቷል። ይህንን ማወቅ የፈለገ ሰው ከሱና መጽሐፍትና ከዕውቀትና ከእምነት ባለቤቶች ድርሳናት ውስጥ በቦታው ያገኘዋል። ሰዎች የዚህ አይነቱን ቀጣፊ ማብራሪያና ማደናገር፣ እንዲሁም እውነትን ከሐሰት ጋር መቀላቀሉን አያስፈልጋቸውም። አላህ እኔንም ሆነ እናንተን እንዲሁም መላውን ሙስሊሞች ከሰይጣኖች ክፋት፣ ከአሳሳቾች ፈተና፣ ከጠማሞች ጥመት፣ እንዲሁም የአላህን ብርሃን በአፎቻቸው ለማጥፋትና በሰዎች ላይ ሃይማኖታቸውን ለማደባለቅ ከሚፈልጉ ሀቅን በውሸት ከሚለውጡ የአላህ ጠላቶች ማታለል ይጠብቀን። አላህ ግን ጠላቶቹ የሆኑት ሰይጣናትና ተከታዮቻቸው ከሀዲያንና አምላክ የለም ባዮች ቢጠሉትም እንኳ ብርሃኑን ሙሉ አድራጊ፤ ሃይማኖቱንም አሸናፊ የሚያደርግ ነው። አላህን የሙስሊሞችን ሁኔታ እንዲያስተካክል፣ እውነትን እንዲከተሉ፣ በርሱም ላይ እንዲጸኑ እንዲሁም ከኃጢአት ሁሉ ወደ እርሱ (ጥራት የተገባው) እንዲመለሱ እንዲያድላቸው እንጠይቀዋለን። እርሱ ጸጸትን ተቀባይ፣ አዛኝና በሁሉም ነገር ላይ ቻይ ነውና። አላህም መመኪያችንና በቂያችን ነው፤ ሁሉን ቻይ ታላቅ በሆነው አምላክ በቀር ምንም ኃይል እና ዘዴ የለም።

ምስጋና የዓለማት ጌታ ለሆነው አላህ ይገባው። የአላህ ሶለዋትና ሰላም እውነተኛና ታማኝ በሆኑት በባሪያውና በመልእክተኛው ላይ፣ በቤተሰቦቻቸው ላይ፣ በባልደረቦቻቸው ላይ እና እስከ ትንሳኤ ቀን ድረስ በመልካም በተከተሏቸውም ላይ ይስፈን።

***

 

am397v4.0 - 21/04/2026