PHPWord

 

 

حُكْمُ السِّحْرِ وَالكِهَانَةِ

وَمَا يَتَعَلَّقُ بِهَا

 

 

የድግምት እና የጥንቆላ ብይን እንዲሁም ተያያዥ ጉዳዮች

 

 

 

 

لِسَمَاحَةِ الشَّيْخِ العَلَّامَةِ

عَبْدِ العَزِيزِ بْنِ عَبْدِ اللهِ بْنِ بَازٍ

رَحِمَهُ اللهُ

 

ዝግጅት፦ የተከበሩ ሸይኽ

ዐብዱልዐዚዝ ቢን ዐብደላህ ቢን ባዝ

 

 

 


بِسْمِ اللهِ الرَّحمَنِ الرَّحِيمِ

ዘጠነኛው መልዕክት፦

የድግምት እና የጥንቆላ ብይን እንዲሁም ተያያዥ ጉዳዮች1

ምስጋና ሁሉ ለብቸኛው አላህ የተገባ ነው። የአላህ ሶላትና ሰላም ከእሳቸው በኋላ ነብይ የሌለ በሆኑት ነብይ ላይ ይስፈን። በመቀጠል:

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በህክምና ሰበብ ጥንቆላንና ድግምትን ተግባራዊ የሚያደርጉ ሟርተኞች ቁጥራቸው ከመብዛቱና በአንዳንድ ሀገሮችም ከመሰራጨታቸው እንዲሁም ከማህበረሰቡ መካከል አላዋቂነቱ የጠናበትን ተላላ መጠቀሚያ ከማድረጋቸው አንፃር ለአላህና ለባርያዎቹ በመቆርቆር ጉዳዩ ከአላህ ውጭ ባለ አካል መንጠልጠልና ለአላህና ለመልዕክተኛው ﷺ መመሪያ መጣስ በመሆኑ ለሙስሊሙም ይሁን ለኢስላም ያለውን አደገኝነት ግልፅ ማድረግን ወደድኩ።

ስለዚህም በአላህ በመታገዝ የሚከተለውን እላለሁ። መታከም የተፈቀደ ስለመሆኑ ሙሉ ስምምነት ያለበት ጉዳይ በመሆኑ ሙስሊሞች ለውስጥ ህመም፣ ለቀዶ ጥገና፣ ለነርቭም ይሁን ለመሳሰሉት ህመሞች ሁሉ ወደ ህክምና ሄዶ ሀኪሙም በህክምና ሳይንስ በሚያውቀው መሰረት በሽታውን መርምሮ ሐላል በሆኑ መድሃኒቶች በሚስማማው መሰረት መታከም ይቻላል። ምክንያቱም ይህ የተለመደውን ሰበብ ማድረስ በሚል ርዕስ ስር የሚታይ እንጂ በአላህ ላይ ያለ ተወኩል ጋር የሚቃረን አይደለም። ጥራት የተገባው የላቀው አላህ ደግሞ የሚያውቅ አውቆት ያላወቀ አላወቀውም እንጅ በሽታን እንዳወረደው ሁሉ መድኃኒቱንም አውርዷል። ጥራት ይገባውና የበሽታ መድሀኒቶችንም በሐራም ነገሮች አላደረገም።

በመሆኑም የትኛውም ህመምተኛ ህመሙን እንዲያውቁለት በሚልም ቢሆን የሩቅ ምስጢር እናውቃለን ባይ ብለው ወደሚሞግቱ ጠንቋዮች ሊሄድ አይፈቀድለትም። ልክ እንደዚሁ የሚሞግቱትንም ነገር ማመን አይፈቀድለትም። ምክንያቱም የጥንቆላ ንግግራቸውን የሚናገሩት ወይ በግምት አለበለዚያም ለፍላጎታቸው ጂኒዎች ሊያግዟቸው ዘንድ ጂኒዎችን በማሳተፍ ነውና። እነዚህም የሩቅ ምስጢር እናውቃለን ብለው የሚሞግቱ እስከሆኑ ድረስ ክህደትና ጥመት ላይ ናቸው።

ሙስሊም ነቢዩ ﷺ እንዲህ ማለታቸውን ዘግበዋል፦

«مَنْ أَتَى عَرَّافًا فَسَأَلَهُ عَنْ شَيْءٍ، لَمْ تُقْبَلْ لَهُ صَلَاةٌ أَرْبَعِينَ يَوْمًا».

«ጠንቋይ ዘንድ ሄዶ ስለ አንዳች ነገር የጠየቀ ለአርባ ቀናት ሶላቱ ተቀባይነት የለውም።»

አቡ ሁረይራ ረዲየላሁ ዐንሁ ባስተላለፉት ሐዲሥ ደግሞ ነቢዩ ﷺ እንዲህ ብለዋል፡-

«مَنْ أَتَى كَاهِنًا فَصَدَّقَهُ بِمَا يَقُولُ، فَقَدْ كَفَرَ بِمَا أُنْزِلَ عَلَى مُحَمَّدٍ ﷺ».

"ጠንቋይ ዘንድ ሄዶ ሟርተኛው የተናገረውን ያመነ ሰው ወደ ሙሐመድ ﷺ በወረደው ክዷል።" አቡ ዳውድ ዘግበውታል፤ እንዲሁም አራቱ የሱነን ባለቤቶችም መልዕክቱን የዘገቡት ሲሆን አል-ሐኪም በተከታዩ ቃል ከነብዩ ﷺ ሶሒሕ ሆኖ መምጣቱን አረጋግጠዋል፡-

«مَنْ أَتَى عَرَّافًا أَوْ كَاهِنًا فَصَدَّقَهُ بِمَا يَقُولُ، فَقَدْ كَفَرَ بِمَا أُنْزِلَ عَلَى مُحَمَّدٍ ﷺ».

«ሟርተኛ ወይም ጠንቋይ ዘንድ ሄዶ የተናገረውን ያመነ፣ ወደ ሙሐመድ ﷺ በወረደው ክዷል።»

ዒምራን ቢን ሑሰይን (ረዲየሏሁ ዓንሁ) የአላህ መልዕክተኛ ﷺ እንዲህ ማለታቸውን አስተላልፈዋል፡-

«لَيْسَ مِنَّا مَنْ تَطَيَّرَ أَوْ تُطُيِّرَ لَهُ، أَوْ تَكَهَّنَ أَوْ تُكُهِّنَ لَهُ، أَوْ سَحَرَ أَوْ سُحِرَ لَهُ، وَمَنْ أَتَى كَاهِنًا فَصَدَّقَهُ بِمَا يَقُولُ، فَقَدْ كَفَرَ بِمَا أُنْزِلَ عَلَى مُحَمَّدٍ ﷺ».

«የገድ ተግባርን የፈፀመ ወይም ለሱ የተፈፀመለት፣ ወይም የጠነቆለ ወይም ያስጠነቆለ፣ ወይም የደገመ ወይም ያስደገመ ከኛ አይደለም። ጠንቋይ ዘንድ የሄደና የሚናገረውን ነገር አምኖ የተቀበለ በሙሐመድ ﷺ ላይ በወረደው ነገር በእርግጥ ክዷል።» አል-በዛር በጥሩ ሰነድ ዘግበውታል።

በእነዚህ የተከበሩ ሐዲሦች ውስጥ ወደ ጠንቋዮች፣ ሟርተኞች፣ ደጋሚዎችና መሰሎቻቸው ዘንድ መሄድ፣ እነርሱን መጠየቅና የሚናገሩትን ማመን የተከለከለ ሲሆን በዚህ ላይ ዛቻም እንዳለበት ተገልጿል።

በአንዳንድ አጋጣሚዎች ላይ ትክክል ሆነው በመገኘታቸውም ይሁን ወደነርሱ በሚመጡ አላዋቂ ሰዎች ብዛት መታለል አይገባም። ምክንያቱም የአላህ መልዕክተኛ ﷺ ወደ እነርሱ መሄድን፣ መጠየቅንና በተናገሩት ማመንን ከልክለዋልና ነው። የከለከሉትም ከሚያስከትለው ከባድ መዘዝ፣ አደገኛ ክፋት እና አስከፊ ፍፃሜ አንፃር እንዲሁም እነርሱ ክፉ ውሸታሞች በመሆናቸውም ነው።

ልክ እንደዚሁ በእነዚህ ሐዲሦች ውስጥ ጠንቋይና ድግምተኛ መሆናቸውን የሚጠቁም ማስረጃም አለ። ምክንያቱም ጠንቋይና ድግምተኛ የሩቅ ዕውቀት የሚሞግቱ በመሆናቸውና ግባቸው ላይ ሊደርሱ የሚችሉትም በጂኖች በመታገዝ በመሆኑ በጂኖች መታገዝ የሚችሉት ደግሞ እነርሱን በማስተናገድና ከአላህ ውጭ እነርሱን በማምለክ ስለሆነ ነው። ይህ ደግሞ ጥራት ይገባውና በአላህ ላይ መካድና በእርሱም ማጋራት ነው። የሚሞግቱትን የሩቅ ዓዋቂነትን አምኖ የሚቀበል የነርሱ አምሳያ ነው። እነዚህን ጉዳዮች ከሚያከናውኑ ሰዎች ጋር የተሳተፈ ደግሞ የአላህ መልዕክተኛ ﷺ ከእንዲህ ዓይነቱ የጠሩ ናቸው።

በተመሳሳይም ማንኛውም ሙስሊም በመድሀኒት ሰበብ ለሚያነበንቡት መተትም ይሁን ለሚያስተምሩት ሌላ አጉል እምነት ተገዥ ሊሆን አይፈቀድለትም። ምክንያቱም ይህ ሟርትና ሰዎችን ማምታታት በመሆኑ ይህንንም ወዶ የተቀበለ ሰው በውሸታቸውና በክህደታቸው ላይ እየተባበራቸው ነው።

እንዲሁም ከሙስሊሞች መካከል የትኛውም ሰው ወደ እነርሱ ሄዶ ልጁን ወይም ሌላ ዘመዱን ለማን ማጋባት እንዳለበት፣ ወይም በትዳር አጋሮች እና በቤተሰቦቻቸው መካከል ያለባቸውን የፍቅር፣ የመተማመን፣ የጥላቻና የመለያየት ሁኔታዎችን እና የመሳሰሉትን በተመለከተ ለመጠየቅ ብሎ መሄድ በፍፁም የተከለከለ ነው። ምክንያቱም ይህ ጥራት ከተገባው አላህ በቀር ማንም የማያውቀው የሩቅ ምስጢር ውስጥ የሚካተት ነው።

በመሆኑም ባለስልጣናትና አቅምና ችሎታው ያላቸው የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ወደ ጠንቋዮች እና ሟርተኞች ዘንድ የሚሄዱ ሰዎችን ማውገዝና በእንዲህ አይነቱ ድርጊት ላይ በግብይትም ይሁን በሌላ መስክ የሚሳተፉ አካላትን እንዲሁም ወደነርሱ የሚሄዱ ሰዎችን በደንብ ሊያወግዟቸው ይገባል።

ድግምትም ተመሳሳይ ብይን ነው ያለው፤ ድግምት በክህደት ደረጃ እርም ከተደረጉ ሐራም ነገሮች መካከል የሚመደብ ነው፤ ልዕለ ኃያሉ አላህም ሁለቱን መላእክቶችን በተመለከተ እንዲህ ብሏል፦

﴿...وَمَا يُعَلِّمَانِ مِنۡ أَحَدٍ حَتَّىٰ يَقُولَآ إِنَّمَا نَحۡنُ فِتۡنَةٞ فَلَا تَكۡفُرۡۖ فَيَتَعَلَّمُونَ مِنۡهُمَا مَا يُفَرِّقُونَ بِهِۦ بَيۡنَ ٱلۡمَرۡءِ وَزَوۡجِهِۦۚ وَمَا هُم بِضَآرِّينَ بِهِۦ مِنۡ أَحَدٍ إِلَّا بِإِذۡنِ ٱللَّهِۚ وَيَتَعَلَّمُونَ مَا يَضُرُّهُمۡ وَلَا يَنفَعُهُمۡۚ وَلَقَدۡ عَلِمُواْ لَمَنِ ٱشۡتَرَىٰهُ مَا لَهُۥ فِي ٱلۡأٓخِرَةِ مِنۡ خَلَٰقٖۚ وَلَبِئۡسَ مَا شَرَوۡاْ بِهِۦٓ أَنفُسَهُمۡۚ لَوۡ كَانُواْ يَعۡلَمُونَ﴾

{... (ሀሩትና ማሩት) «እኛ መፈተኛ ነንና አትካድ» እስከሚሉ ድረስ አንድንም አያስተምሩም:: ከእነርሱም በሰውዬውና በሚስቱ መካከል በርሱ የሚለዩበትን ነገር ይማራሉ:: እነርሱም በአላህ ፈቃድ ካልሆነ አንድንም ጎጂዎች አይደሉም:: የሚጎዳቸውንና የማይጠቅማቸውን ይማራሉ:: የገዛውም ሰው ለርሱ በመጨረሻይቱ አገር ምንም ዕድል የሌለው መሆኑን በእርግጥ አወቁ:: ነፍሶቻቸውንም በርሱ የሸጡበት ዋጋ ከፋ! የሚያውቁ በሆኑ ኑሮ (ይህን ተግባር ባልሰሩት ነበር::)} [አል-በቀራህ፡ 102]

እነዚህ የተከበሩ ጥቅሶች ድግምት ክህደት መሆኑን እና ደጋሚዎች በአንድ ወንድና በሚስቱ መካከል መለያየትንም የሚፈጥሩ መሆናቸውን ያመለክታሉ። ከዚያም ባሻገር ድግምት ተፅእኖ ሊያሳድር የሚችለው በራሱ እንዳልሆነ ይልቁን ጥቅምም ሆነ ጉዳትን ሊያስከትል የሚችለው የአላህን ይሁንታዊ ፈቃድ እና ፍርድ ተከትሎ እንደሆነም ያመለክታል። ምክንያቱም ጥራት የተገባው የላቀው አላህ መልካሙንም እና ክፉውንም የፈጠረው እርሱ ነውና።

እነዚህ የተከበሩት አንቀጾች ድግምት የሚማሩ ሰዎች እየተማሩ ያሉት የማይጠቅማቸውን ብሎም የሚጎዳቸውን እንደሆነም ግልፅ አድርገዋል። አላህ ዘንድ ምንም አይነት ድርሻ እንደሌላቸው ማለትም፡ እድለኝነት እና መልካም ምንዳ የሌላቸው መሆኑንም አስረድተዋል። ይህ ደግሞ በዱኒያም በአኺራም የሚገጥማቸው ክስረት አደገኛ መሆኑን የሚጠቁም ከባድ ዛቻ ነው። ራሳቸውንም በዝቅተኛ ዋጋ የሸጡ በመሆናቸው ልዕለ ኃያሉ አላህ እንዲህ ሲል ኮንኗቸዋል፦

﴿...وَلَبِئۡسَ مَا شَرَوۡاْ بِهِۦٓ أَنفُسَهُمۡۚ لَوۡ كَانُواْ يَعۡلَمُونَ﴾

{…ነፍሶቻቸውን የሸጡበት ዋጋ ከፋ! የሚያውቁ በሆኑ ኑሮ (ይህን ተግባር ባልሰሩት ነበር::)} [አል-በቀራህ፡ 102] እዚህ አንቀጽ ውስጥ መግዛት የተባለው ራሳቸውን መሸጣቸው ለማለት ነው።

ይህንን ዕውቀት ከሙሽሪኮች በወረሱና ደካማ አዕምሮ ያላቸውንም ሰዎች ባደናገሩ በእነዚህ ቀጣፊዎች ምክንያት ከባድ ጉዳት ደርሷል፤ ንግግሩም አፅንዖት ባለው መልኩ ሆኗል። እኛም የአላህ ነን፤ ወደርሱም ተመላሾች ነን። አላህም በቂያችን ነው፤ ምንኛ ያማረ መመኪያ ነው።

ከጠንቋዮች፣ ከሟርተኞችና እና ሌሎችም አጭበርባሪዎች ክፋት አላህ ይጠብቀን ዘንድ እንማፀነዋለን። ጥራት የተገባው አላህ ሙስሊሞችን ከክፋት እንዲጠብቃቸው፣ የሙስሊም መሪዎችንም እንዲጠነቀቋቸው፣ የአላህ ባርያዎች ከክፋታቸውም ከመጥፎ ስራዎቻቸውም ሰላም ሊሆኑ ዘንድ የአላህን ፍርድ ተግባራዊ እንዲያደርጉ አላህ ይወፍቃቸው ዘንድ እንማፀነዋለን።

ጥራት የተገባው አምላካችን አላህ ድግምት ከመከሰቱ በፊት ከድግምቱ መጠንቀቅ የሚቻልበትን መንገዶች ለባሮቹ ደነግጎላቸዋል። ጥራት ይገባውና ለእነርሱ ካለው እዝነትና ከእነርሱ አንፃር ከተከሰተ በኋላ መታከም የሚቻልበትንም መንገድ ግልፅ አድርጎላቸዋል።

የድግምትን አደጋ ከመከሰቱ በፊት መጠንቀቅ የሚቻልባቸውንም ይሁን ከተከሰተ በኋላ መታከም የሚቻልባቸውን መንገዶች በሸሪዓም ከተፈቀዱት መካከል ማብራሪያቸው እንደሚከተለው ነው፡

አንደኛ፡ ድግምት ከመከሰቱ በፊት ከሚያስከትለው አደጋ መከላከያ፤ ከእነዚህም እጅግ አስፈላጊና ጠቃሚው፦ በሸሪዓዊ ዚክሮች፣ በዱዓዎች እና ከነብዩ በተገኙ የክፋት መጠበቂያ ውዳሴዎችን በመጠቀም መከላከል ነው። ከእነዚህም መካከል፦ ከእያንዳንዱ የግዴታ ሶላት በኋላ ካሰላመቱ በኋላ አየተል ኩርሲይን መቅራት ነው፤ እርሱም በቅዱስ ቁርአን ውስጥ እጅግ ታላቅ አንቀፅ ሲሆን እርሱም የሚከተለው የአላህ ንግግር ነው፦

﴿ٱللَّهُ لَآ إِلَٰهَ إِلَّا هُوَ ٱلۡحَيُّ ٱلۡقَيُّومُۚ لَا تَأۡخُذُهُۥ سِنَةٞ وَلَا نَوۡمٞۚ لَّهُۥ مَا فِي ٱلسَّمَٰوَٰتِ وَمَا فِي ٱلۡأَرۡضِۗ مَن ذَا ٱلَّذِي يَشۡفَعُ عِندَهُۥٓ إِلَّا بِإِذۡنِهِۦۚ يَعۡلَمُ مَا بَيۡنَ أَيۡدِيهِمۡ وَمَا خَلۡفَهُمۡۖ وَلَا يُحِيطُونَ بِشَيۡءٖ مِّنۡ عِلۡمِهِۦٓ إِلَّا بِمَا شَآءَۚ وَسِعَ كُرۡسِيُّهُ ٱلسَّمَٰوَٰتِ وَٱلۡأَرۡضَۖ وَلَا يَـُٔودُهُۥ حِفۡظُهُمَاۚ وَهُوَ ٱلۡعَلِيُّ ٱلۡعَظِيمُ255﴾

{አላህ ከእርሱ በስተቀር ሌላ ትክክለኛ አምላክ የለም:: አላህ ሕያው፤ በራሱ የተብቃቃ ነው:: ማንገላጀትም ሆነ እንቅልፍ አትይዘዉም:: በሰማያት ውስጥና በምድር ውስጥ ያለው ሁሉ የእርሱ ብቻ ነው:: ያ እርሱ ዘንድ በፍቃዱ ቢሆን እንጂ የሚያማልድ ማን ነው? (ከፍጡራን) ሁሉ በፊታቸው ያለውንና ከኋላቸው ያለውን ሁሉ ያውቃል:: በሻውም ነገር እንጂ ከእውቀቱ (ፍጡራን) በምንም ነገር አያካብቡም:: መንበሩ ሰማያትንና ምድርን ሰፋ:: ጥበቃቸዉም አያቅተዉም:: እርሱ የሁሉ በላይ ታላቅ ነው::} [አል-በቀራህ፡ 255] ልክ እንደዚሁ በእንቅልፍ ወቅትም ይቀራል፤ የአላህ መልዕክተኛ ﷺ እንዲህ ማለታቸው በሶሒሕ ሐዲሥ ተረጋግጧል፦

«مَنْ قَرَأَ آيَةَ الْكُرْسِيِّ فِي لَيْلَةٍ، لَمْ يَزَلْ عَلَيْهِ مِنَ اللَّهِ حَافِظٌ، وَلَا يَقْرَبُهُ شَيْطَانٌ حَتَّى يُصْبِحَ».

«በምሽቱ ክፍለጊዜ አየተል ኩርሲይን የቀራ ሰው እስኪነጋ ድረስ የአላህ ከለላ አይለየውም፤ ሸይጧንም አይቀርበውም።»

ከነዚህም መካከል የሚከተለውን ማንበብ ይገኝበታል፦

﴿قُلۡ هُوَ ٱللَّهُ أَحَدٌ1﴾

{ በል፡ -እርሱ አላህ አንድ ብቻ ነው::}

﴿قُلۡ أَعُوذُ بِرَبِّ ٱلۡفَلَقِ1﴾

{በል፡ -በተፈልቃቂው ጎህ (በአል-ፈለቅ) ጌታ እጠበቃለሁ፤}

﴿قُلۡ أَعُوذُ بِرَبِّ ٱلنَّاسِ1﴾

{በል፡ -የሰዎች ሁሉ ፈጣሪ በሆነው ጌታ እጠበቃለሁ፤} [አን-ናስ: 1] እስከመጨረሻው። ከእያንዳንዱ ግዴታ ሶላት በኋላ እነኝህን ሶስት ሱራዎች በቀኑ መጀመሪያ ከፈጅር ሶላት በኋላ እና በሌሊቱ መጀመሪያ ከመግሪብ ሶላት በኋላ ሶስት ሶስት ጊዜ መቅራት።

ከእነዚህም መካከል፦ የሱረቱል በቀራህ የመጨረሻዎቹን ሁለት አንቀፆች በመጀመርያው የሌሊቱ ክፍል መቅራት። እነሱም የሚከተሉት ናቸው፦

﴿ءَامَنَ ٱلرَّسُولُ بِمَآ أُنزِلَ إِلَيۡهِ مِن رَّبِّهِۦ وَٱلۡمُؤۡمِنُونَۚ كُلٌّ ءَامَنَ بِٱللَّهِ وَمَلَٰٓئِكَتِهِۦ وَكُتُبِهِۦ وَرُسُلِهِۦ لَا نُفَرِّقُ بَيۡنَ أَحَدٖ مِّن رُّسُلِهِۦۚ وَقَالُواْ سَمِعۡنَا وَأَطَعۡنَاۖ غُفۡرَانَكَ رَبَّنَا وَإِلَيۡكَ ٱلۡمَصِيرُ285﴾

{መልክተኛው ከጌታው ወደርሱ በተወረደው አመነ:: አማኞችም እንደዚሁ አመኑ:: ሁሉም በአላህ፣ በመላእክቱም፣ በመጻህፍቱም፣ በመልክተኞቹም ከመልክተኞቹ «በአንዱም መካከል አንለይም (አንክድም)» የሚሉ ሲሆኑ አመኑ:: «ሰማን ታዘዝንም። ጌታችን ሆይ! ምህረትህን እንሻለን :: መመለሻም ወዳንተ ብቻ ነው።» አሉም::} እስከ ምዕራፉ መጨረሻ ድረስ አንብብ!

ነቢዩ ﷺ እንዲህ ማለታቸው በሶሒሕ ሐዲሥ ተዘግቧል፦

«مَنْ قَرَأَ الآيَتَيْنِ مِنْ آخِرِ سُورَةِ البَقَرَةِ فِي لَيْلَةٍ كَفَتَاهُ».

"በምሽት ውስጥ የመጨረሻዎቹን የበቀራህ ምእራፍ ሁለት አንቀፆች የቀራ ሰው ይበቁታል።" ትርጉሙ፡- ከክፋት ነገር ሁሉ ይጠብቁታል ማለት ነው። ሌላው የአላህን ጥበቃ እናገኝባቸው ዘንድ በሸሪዓው የተደነገጉ (ፍፁም የሆኑ ከፍጡራኑ ክፋት የምንጠበቅባቸው) ውዳሴዎችን ሌትም ቀንም፣ በቤት ውስጥም ይሁን በበረሃ በአየርም ይሁን በባህር የአላህን ጥበቃ የሚያስገኙልን የተደነገጉ አዝካሮችን ማብዛት ነው። ምክንያቱም ነብዩ ﷺ እንዲህ በማለታቸው ነው፡-

«مَن نَزَلَ مَنْزِلًا فَقالَ: أَعُوذُ بِكَلِمَاتِ اللهِ التَّامَّاتِ مِن شَرِّ ما خَلَقَ، لَمْ يَضُرَّهُ شَيءٌ حتَّى يَرْتَحِلَ مِن مَنْزِلِهِ ذَلِكَ».

"በአንድ ስፍራ ላይ አርፎ ከዚያም ‹አዑዙ ቢከሊማቲላሂ አትታማቲ ሚን ሸሪ ማ ኸለቀ (ምሉዕ በሆኑ የአላህ ቃላት ከፈጠራቸው ጎጂ ነገሮች እጠበቃለሁ)› ያለ ሰው ከዛ ስፍራ እስኪንቀሳቀስ ድረስ አንዳችም አይጎዳውም።"

እንዲሁም አንድ ሙስሊም በቀኑ መጀመሪያ እና በሌሊቱ መጀመሪያ ላይ ሶስት ጊዜ ተከታዩን ማለት፦

«بِسْمِ اللهِ الَّذِي لَا يَضُرُّ مَعَ اسْمِهِ شَيءٌ فِي الأَرْضِ وَلَا فِي السَّمَاءِ، وَهُوَ السَّمِيعُ العَلِيمُ».

«ቢስሚላሂ ለዚ ላ የዹሩ መዐ_ስሚሂ ሸይኡን ፊል አርዺ ወላ ፊ ስሰማኢ ወሁወ አስ'ሰሚዑል ዐሊም።» (በዚያ ከስሙ ጋር በምድርም ይሁን በሰማይ ምንም ነገር የማይጎዳ በሆነው እንዲሁም ሰሚና ዐዋቂ በሆነው አላህ ስም።)

ይህንን የሚያበረታቱ ሶሒሕ ሐዲሦች ከነብዩ ﷺ በመዘገባቸው እነዚህ አዝካሮች ከክፋት ሁሉ ለመጠበቅ ሰበብ ናቸው።

ሁለተኛ፡ ድግምት ከተከሰተ በኋላ የሚታከምባቸው መንገዶች፤ ይህም በበርካታ መንገዶች ነው:-

የመጀመሪያው: ወደ አላህ መዋደቅን ማብዛት፣ እንዲሁም ጉዳትን እንዲያነሳና መከራንም እንዲያስወግድ እርሱን መጠየቅ ነው።

ሁለተኛው: ድግምትን ለማከም ከሚረዱ ፋይዳቸው ከጎሉ ዘዴዎች መካከል አንዱ ድግምቱ የተቀበረበትን ቦታ በመሬት ላይም ይሁን በተራራ አልያም በሌላ ቦታ ለይቶ ለማወቅ መጣጣር ነው። ምክንያቱም ድግምቱ ያለበት ቦታ ከታወቀ አውጥተው ቢበታትኑት ድግምቱ ይከሽፋልና ነው።

ሶስተኛው፦ በሸሪዓዊ ዚክሮች እና አውራዶች ሩቃ ማድረግ፤ እነርሱም ብዙ ሲሆኑ ከእነዚህ መካከል፦

በአላህ መልዕክተኛ ﷺ ንግግር እንደተረጋገጠው፦

«اللَّهُمَّ رَبَّ النَّاسِ، أَذْهِبِ الْبَأْسَ، وَاشْفِ أَنْتَ الشَّافِي، لَا شِفَاءَ إِلَّا شِفَاؤُكَ، شِفَاءً لَا يُغَادِرُ سَقَمًا».

("አሏሁምመ ረበ‐ን‐ናስ፣ አዝሂቢል በእሰ፣ ወሽፊ አንተ‐ሽ‐ሻፊ፣ ላ ሺፋአ ኢላ ሺፋኡክ፣ ሺፋአን ላ ዩጋዲሩ ሰቀማ" ትርጉሙም፦ የሰዎች ጌታ የሆንከው አላህ ሆይ! በሽታውን አስወግድ፤ ፈዋሹም አንተ ነህና ፈውስ፤ ምንም አይነት በሽታ የማያስቀር ከሆነው ከአንተ ፈውስ በቀር ሌላ ፈውስ የለም።") ይህንንም ሶስት ጊዜ ይለዋል:

ከእነዚህም መካከል ጂብሪል ዓለይሂ ሰላም ነቢዩን ﷺ ሩቃ ያደረገበት ዚክር ይገኝበታል፤ ይኸውም፦

«بِسْمِ اللَّهِ أَرْقِيكَ، مِنْ كُلِّ شَيْءٍ يُؤْذِيكَ، وَمِنْ شَرِّ كُلِّ نَفْسٍ أَوْ عَيْنِ حَاسِدٍ، اللَّهُ يَشْفِيكَ، بِسْمِ اللَّهِ أَرْقِيكَ».

(“በስሚላሂ አርቂከ ሚን ኩሊ ሸይኢን ዩእዚከ ወሚን ሸሪ ኩሊ ነፍሲን አው ዓይኒን ሐሢድ፥ አሏሁ የሽፊከ ቢስሚላሂ አርቂከ” ትርጉሙ፦ «በአላህ ስም ሩቅያ አደርግልሃለሁ (አክምሀለሁ)፤ ከሚጎዳህ ነገር ሁሉ፣ ከነፍስ ሁሉ (ክፋት) እና ከምቀኛ ዓይን (ክፋት)፤ አላህ ይፈውስህ፤ በአላህ ስም ሩቅያ አደርግልሃለሁ።» ይህንንም ሦስት ጊዜ ደጋግሞ ይበለው!

ከነዚህም መካከል -በተለይ ከባለቤቱ ጋር ግንኙነት ለመፈፀም ለተቸገረ ሰው ጠቃሚ ፈውስ ነው-፡ ሰባት አረንጓዴ የቁርቁራ ቅጠል ወስዶ በድንጋይ ወይም በመሳሰሉት ፈጭቶ፣ በአንዳች እቃ አድርጎ ለትጥበት የሚበቃውን ያህል በውሀ በመዘፍዘፍ ላዩ ላይ ይቀራበታል፡

አያቱል ኩርሲይን እና

﴿قُلۡ يَٰٓأَيُّهَا ٱلۡكَٰفِرُونَ1﴾

{(ለካሓዲያን እንዲህ) በላቸው፡- እናንተ ከሓዲያን ሆይ!} [አል-ካፊሩን፡ 1] እስከመጨረሻው። እንዲሁም

﴿قُلۡ هُوَ ٱللَّهُ أَحَدٌ1﴾

{ በል፡ -እርሱ አላህ አንድ ብቻ ነው::} "[አል-ኢኽላስ፡ 1] እስከመጨረሻው። እንዲሁም

﴿قُلۡ أَعُوذُ بِرَبِّ ٱلۡفَلَقِ1﴾

{ በል፡ -በተፈልቃቂው ጎህ (በአል-ፈለቅ) ጌታ እጠበቃለሁ፤} [አል-ፈለቅ: 1] እስከመጨረሻው። እንዲሁም

﴿قُلۡ أَعُوذُ بِرَبِّ ٱلنَّاسِ1﴾

{በል፡ -የሰዎች ሁሉ ፈጣሪ በሆነው ጌታ እጠበቃለሁ፤} [አን-ናስ: 1] እስከመጨረሻው።

በሱረቱል አዕራፍ ውስጥ ያሉ ለድግምት የሚቀሩ አንቀጾች ማለትም ተከታዮቹ አንቀጾች፦

﴿وَأَوۡحَيۡنَآ إِلَىٰ مُوسَىٰٓ أَنۡ أَلۡقِ عَصَاكَۖ فَإِذَا هِيَ تَلۡقَفُ مَا يَأۡفِكُونَ117 فَوَقَعَ ٱلۡحَقُّ وَبَطَلَ مَا كَانُواْ يَعۡمَلُونَ118 فَغُلِبُواْ هُنَالِكَ وَٱنقَلَبُواْ صَٰغِرِينَ119﴾

{ ወደ ሙሳም «ዘንግህን ጣል» ስንል ላክንበት (ጣላትም) ወዲውኑም የሚቀጣጥፉትን ማታለያ መዋጥ ጀመረች::

እውነቱም ተገለጸ:: ይሠሩት የነበሩት ድግምትም ተበላሸ::

እዚያ ላይ ተሸነፉና ወራዶች ሆነው ተመለሱ።} [አል-አዕራፍ 117-119]

በሱረቱ ዩኑስ ውስጥ ያሉ አንቀጾች ማለትም ተከታዮቹ አንቀጾች፦

﴿وَقَالَ فِرۡعَوۡنُ ٱئۡتُونِي بِكُلِّ سَٰحِرٍ عَلِيمٖ79 فَلَمَّا جَآءَ ٱلسَّحَرَةُ قَالَ لَهُم مُّوسَىٰٓ أَلۡقُواْ مَآ أَنتُم مُّلۡقُونَ80 فَلَمَّآ أَلۡقَوۡاْ قَالَ مُوسَىٰ مَا جِئۡتُم بِهِ ٱلسِّحۡرُۖ إِنَّ ٱللَّهَ سَيُبۡطِلُهُۥٓ إِنَّ ٱللَّهَ لَا يُصۡلِحُ عَمَلَ ٱلۡمُفۡسِدِينَ81 وَيُحِقُّ ٱللَّهُ ٱلۡحَقَّ بِكَلِمَٰتِهِۦ وَلَوۡ كَرِهَ ٱلۡمُجۡرِمُونَ82﴾

{ ፈርዖን፡- «አዋቂ ድግምተኛን ሁሉ አምጡልኝ።» አለ::

ድግምተኞቹ በመጡ ጊዜም ሙሳ ለእነርሱ፡- «እናንተ የምትጥሉትን ነገር ጣሉ።» አላቸው::

በጣሉም ጊዜ ሙሳ፡- «ያ በእርሱ የመጣችሁበት ነገር ድግምት ነው:: አላህ በእርግጥ ያፈርሰዋል:: አላህ የአጥፊዎችን ሥራ ፈጽሞ አያበጅምና።» አለ::

አላህም ከሓዲያን ቢጠሉም እውነትን በቃላቱ ያረጋግጣል።} [ዩኑስ: 79-82]

በሱረቱ ጣሃ ውስጥም ያሉት አንቀጾች፡-

﴿قَالُواْ يَٰمُوسَىٰٓ إِمَّآ أَن تُلۡقِيَ وَإِمَّآ أَن نَّكُونَ أَوَّلَ مَنۡ أَلۡقَىٰ65 قَالَ بَلۡ أَلۡقُواْۖ فَإِذَا حِبَالُهُمۡ وَعِصِيُّهُمۡ يُخَيَّلُ إِلَيۡهِ مِن سِحۡرِهِمۡ أَنَّهَا تَسۡعَىٰ66 فَأَوۡجَسَ فِي نَفۡسِهِۦ خِيفَةٗ مُّوسَىٰ67 قُلۡنَا لَا تَخَفۡ إِنَّكَ أَنتَ ٱلۡأَعۡلَىٰ68 وَأَلۡقِ مَا فِي يَمِينِكَ تَلۡقَفۡ مَا صَنَعُوٓاْۖ إِنَّمَا صَنَعُواْ كَيۡدُ سَٰحِرٖۖ وَلَا يُفۡلِحُ ٱلسَّاحِرُ حَيۡثُ أَتَىٰ69﴾

{ «ሙሳ ሆይ! በመጀመሪያ ትጥላለህ ወይስ እኛ እንጣል? (ምረጥ)» አሉ።

ሙሳም «እናንተ መጀመሪያ ጣሉ።» አላቸው። ጣሉም:: ወዲያዉም ገመዶቻቸውና ዘንጎቻቸው ከድግምታቸው የተነሳ የሚሮጡ እባቦች ሆነው (መስለው) ወደ እርሱ ተመሰሉበት።

ሙሳም በውስጡ ፍርሃት አደረበት::

አልነውም: «አትፍራ። የበላዩ አንተ ነህና።»

«በቀኝ እጅህ ያለችውን ብትር ጣል:: ያንን የሰሩትን ትውጣለችና። የሰሩት የድግምተኛ ተንኮል ብቻ ነውና:: ድግምተኛም በመጣበት ስፍራ ሁሉ አይቀናዉም::»} [ጧሀ: 65-69]

ከላይ የተጠቀሱትን በውሃ ላይ ከቀራበት በኋላ ሶስት እፍኝ ይጠጣበትና በቀሪው ይታጠብ። በዚህም የአላህ ፈቃድ ታክሎበት በሽታው ይወገዳል። ሁለቴ እና ከዛ በላይ መደጋገሙ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ደግሞ በሽታው እስኪወገድ ድረስ ቢደጋገምም ችግር የለውም።

እነዚህ ውዳሴዎች፣ መጠበቂያ ዚክሮች እና መንገዶች በቅንነት፣ በእምነት፣ በአላህ ላይ በመተማመንና በእርሱም ላይ በመደገፍ ለሚሰጡት መልዕክትም በአፅንኦት ልቡን ከፍቶ ለሚከታተላቸው የድግምትም የሌላውንም ክፋት ለመመከት ከታላላቅ ሰበቦች ከመሆናቸውም ባሻገር ድግምቱ ከተከሰተ በኋላ ለማስወገድም ታላቅ መሳሪያ ናቸው።

ድግምትን መጠንቀቅና ማከም የሚቻልባቸው ዘዴዎችን በተመለከተ አላህ ያገራልን ይህን ይመስላል። አላህ ተውፊቁን ይግጠመን።

እዚህ ላይ አንድ ወሳኝ ጉዳይ ይነሳል። ይህም ድግምትን በድግምተኞች ስራ ማከሙ ማለትም በመስዋእት ወይም በሌላ አምልኮ ወደ አጋንንት መቃረቡ በፍፁም አይፈቀድም፤ ምክንያቱም ከሰይጣን ስራ እና ከዛም አልፎ ከባዱ ሽርክ ነውና። ልክ እንደዚሁ ጠንቋዮችን፣ ሟርተኞችንና አጭበርባሪዎችን እየጠየቁ መተካከሙና የሚሉትንም ተግባራዊ ማድረጉም አይፈቀድም። ምክንያቱም እምነተቢሶችና ቀጣፊ ሟርተኛ ጋጠወጦች በመሆናቸው ነው። የአላህ መልዕክተኛ ﷺ እነኝህ ሰዎች ዘንድ ከመሄድ፣ እነርሱን ከመጠየቅና የሚሉትን አምኖ ከመቀበል አስጠንቅቀዋል። ይህም ቀደም ብለን በዚህ ጽሑፍ መጀመሪያ ላይ ገልፀነዋል። ከዚህ ነገር መጠንቀቅ ግዴታ ሲሆን የአላህ መልዕክተኛም ﷺ ድግምትን በድግምት ስለማክሸፍ ተጠይቀው እንዲህ ማለታቸው በሶሒሕ ሐዲሥ ተረጋግጧል፡-

«هِيَ مِنْ عَمَلِ الشَّيْطَانِ».

«እርሱ የሸይጧን ስራ ነው።» ኢማሙ አሕመድ እና አቡ ዳውድ በጥሩ ሰነድ ዘግበውታል።

“ኑሽራ” ማለት ድግምትን በድግምት ማክሸፍ ማለት ሲሆን እሳቸው እንዲህ ሲሉ የፈለጉበት: “የጃሂሊያ ሰዎች ይጠቀሙበት የነበረውን የማክሸፊያ አይነት ማለትም ድግምትን ደጋሚ እንዲያከሽፈው አልያም ድግምቱን በአምሳያው ድግምት ማክሸፍን ማውገዛቸው ነው።

ሩቃ በማድረግ፣ በሸሪዓው የተደነገጉ በሆኑ ዱዓዎች እና በተፈቀዱ ፈውሶች ድግምትን ማክሸፉ ግን ቀደም ብለንም እንዳሳለፍነው ምንም ችግር የለውም። ይህም ታላቁ ሊቅ ኢብኑል ቀይም እና ሸይኽ ዐብዱረሕማን ኢብኑ ሐሰን ፈትሑል መጂድ በተሰኘው ኪታባቸው አላህ ይዘንላቸውና እንዲሁም ሌሎችም ሊቃውንት ያብራሩት ጉዳይ ነው።

አላህ ሙስሊሞችን በሙሉ ከመጥፎ ነገር ሁሉ እንዲታደጋቸው፣ ሃይማኖታቸውንም ለእነርሱ እንዲጠብቅላቸው፣ መገንዘቡንም እንዲለግሳቸው፣ የእርሳቸውን ድንጋጌ ከመጣስም እንዲያድናቸው አላህን እንማፀነዋለን።

የአላህ ሰላትና ሰላም ባሪያውና መልክተኛው በሆኑት በሙሐመድ፣ እንዲሁም በቤተሰቦቻቸውና በባልደረቦቻቸው ላይ ይስፈን።

 

 

***

 

 

am397v4.0 - 21/04/2026


ይህች መልዕክት (ወሲያ) በ1402 ዓ.ሂ ከዕውቀታዊ ምርምር፣ ፈትዋ፣ ዳዕዋና ኢርሻድ ጠቅላይ መምሪያ አማካኝነት በቁጥር 17 ኩራሳ (ቡክሌት) ታትማ ወጥታለች።