مِنْ أَحْكَامِ الصِّيَامِ
የፆም ህግጋት
اللَّجْنَةُ العِلْمِيَّةُ
بِرِئَاسَةِ الشُّؤُونِ الدِّينِيَّةِ بِالمَسْجِدِ الحَرَامِ وَالمَسْجِدِ النَّبَوِيِّ
በመስጂደል ሐረም እና በመስጂድ አን-ነበዊይ በሃይማኖት ዘርፍ የዕውቀት ነክ ጉዳዮች ርዕሰ መስተዳድር ኮሚቴ ያዘጋጀው
بِسْمِ اللَّهِ الرَّحْمَنِ الرَّحِيمِ
የፆም ህግጋት
የመጀመሪያው ጥናት:
የፆም ትርጓሜ እና የረመዷን ወርን መፆም ግዴታ ስለመሆኑ:
አንደኛ: የፆም ትርጓሜ
ፆም ማለት: ጎህ ከቀደደበት ጊዜ ጀምሮ ፀሐይ እስክትጠልቅ ድረስ አላህን ለማምለክ በማሰብ ፆምን ከሚያፈርሱ ነገራቶች መታቀብ ነው።
ሁለተኛ: የረመዷንን ወር መፆም ግዴታ ስለመሆኑ
የረመዷን ወርን መፆም አንድ ሙስሊም ሃይማኖቱ በነሱ ላይ ካልሆነ በቀር መቆም የማይችልባቸው ከሆኑት ከአምስቱ የእስልምና ማእዘናት መካከል አንዱ ነው። ፆም አፈፃፀሙና የጊዜው ርዝመት ቢለያይም በሁሉም ህዝብ ላይ የተደነገገ ግዴታ ነው። አላህ እንዲህ ብሏል:
﴿يَٰٓأَيُّهَا ٱلَّذِينَ ءَامَنُواْ كُتِبَ عَلَيۡكُمُ ٱلصِّيَامُ كَمَا كُتِبَ عَلَى ٱلَّذِينَ مِن قَبۡلِكُمۡ لَعَلَّكُمۡ تَتَّقُونَ 183﴾
{እናንተ ያመናችሁ ሆይ ጾም በነዚያ ከናንተ በፊት በነበሩት (ሕዝቦች) ላይ እንደ ተጻፈ በናንተም ላይ ተጻፈ (ተደነባ) ልትጠነቀቁ ዘንድ፡፡} (አል‐በቀራህ: 183) ተጻፈ (ተደነባ) ማለት ግዴታ ተደረገ ማለት ነው።
ለግዴታነቱም የቁርአንም የሐዲሥም ይሁን የኢስላም ሊቃውንት ስምምነት ማስረጃ አለ።
ቁርአናዊ ማስረጃው: እንዲህ የሚለው የአላህ ቃል ነው፦
﴿يَٰٓأَيُّهَا ٱلَّذِينَ ءَامَنُواْ كُتِبَ عَلَيۡكُمُ ٱلصِّيَامُ كَمَا كُتِبَ عَلَى ٱلَّذِينَ مِن قَبۡلِكُمۡ لَعَلَّكُمۡ تَتَّقُونَ 183 أَيَّامٗا مَّعۡدُودَٰتٖ...﴾
(እናንተ ያመናችሁ ሆይ ጾም በነዚያ ከናንተ በፊት በነበሩት (ሕዝቦች) ላይ እንደ ተጻፈ በናንተም ላይ ተጻፈ (ተደነባ) ልትጠነቀቁ ዘንድ፡፡ 183
የተቆጠሩን ቀኖች [ፁሙ]።) (አል‐በቀራህ: 183‐184)
የሐዲሥ ማስረጃውም እንዲህ የሚለው የነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በርሳቸው ላይ ይስፈንና) ንግግራቸው ነው፦
«بُنِيَ الإِسْلَامُ عَلَى خَمْسٍ: شَهَادَةِ أَنْ لَا إِلَـهَ إِلَّا اللَّهُ، وَأَنَّ مُحَمَّدًا رَسُولُ اللَّهِ، وَإِقَامِ الصَّلَاةِ، وَإِيتَاءِ الزَّكَاةِ، وَصَوْمِ رَمَضَانَ، وَحَجِّ الْبَيْتِ».
«እስልምና በአምስት መሰረቶች ላይ ተገነባ። እነርሱም: ከአላህ በስተቀር በእውነት የሚመለክ አምላክ አለመኖሩን እና ሙሐመድም የአላህ ባሪያና መልዕክተኛ ናቸው ብሎ የምስክርነት ቃልን መስጠት፣ ሶላትን አሟልቶ መስገድ፣ ዘካን መስጠት፣ የረመዷንን ወር መፆም እና ሐጅ ማድረግ ናቸው።»1
የኢጅማዕ (የኢስላም ሊቃውንት ሙሉ ስምምነት) ማስረጃውም: የረመዷንን ቀናት መፆም ግዴታ መሆኑንና የመፆሙን ግዴታነት የማይቀበልም ከሃዲ መሆኑን ሁሉም ሙስሊም ይስማማበታል።
ሁለተኛው ጥናት:
የረመዷን ወር ትሩፋቶች
ይህ ታላቅ ወር ከሌሎቹ ወራቶች ለየት የሚልባቸው ታላላቅ መለያዎችና ትሩፋቶች አሉት። ከነዚህ መካከልም:
1) የተከበረው ቁርአን የወረደበት ወር መሆኑ፤ የላቀው አላህ እንዲህ ብሏል:
﴿شَهۡرُ رَمَضَانَ ٱلَّذِيٓ أُنزِلَ فِيهِ ٱلۡقُرۡءَانُ...﴾
(ቁርኣን የተወረደበት የረመዳን ወር ነው፡፡) (አል‐በቀራ: 185)
2) መልካም ሥራዎች ከመብዛታቸው አኳያ በዚህ ወር የጀነት በሮች ይከፈታሉ።
3) የሚሰሩ ወንጀሎች ከማነሳቸው አኳይ የጀሀነም በሮች በዚህ ወር ይዘጋሉ።
ይህም ከተከታዩ የነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በርሳቸው ላይ ይስፈንና) ንግግር ላይ የምንረዳው ነው:
«إِذَا جَاءَ رَمَضَانُ، فُتِّحَتْ أَبْوَابُ الْجَنَّةِ، وَغُلِّقَتْ أَبْوَابُ النَّارِ، وَصُفِّدَتِ الشَّيَاطِينُ».
«የረመዷን ወር በመጣ ጊዜ የጀነት በሮች ይከፈታሉ፤ የጀሀነም በሮችም ይዘጋሉ፤ ሰይጣናትም ይታሰራሉ።»2
4) ከትሩፋቶቹ መካከልም ነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በርሳቸው ላይ ይስፈንና) እንዲህ ብለዋል:
«مَا مِنْ حَسَنَةٍ يَعْمَلُهَا ابْنُ آدَمَ إِلَّا كُتِبَ لَهُ عَشْرُ حَسَنَاتٍ إِلَى سَبْعِمِائَةِ ضِعْفٍ، قَالَ اللَّهُ: إِلَّا الصِّيَامَ، فَإِنَّهُ لِي وَأَنَا أَجْزِي بِهِ، يَدَعُ شَهْوَتَهُ وَطَعَامَهُ مِنْ أَجْلِي، الصِّيَامُ جُنَّةٌ، وَلِلصَّائِمِ فَرْحَتَانِ: فَرْحَةٌ عِنْدَ فِطْرِهِ، وَفَرْحَةٌ عِنْدَ لِقَاءِ رَبِّهِ، وَلَخُلُوفُ فَمِ الصَّائِمِ أَطْيَبُ عِنْدَ اللَّهِ مِنْ رِيحِ الْمِسْكِ» .
«የሰው ልጅ በሚሠራው መልካም ስራ ሁሉ ከአስር እስከ ሰባት መቶ እጥፍ ድረስ ይታሰብለታል። አላህ እንዲህ ብሏል: "ከፆም በቀር፤ እርሱ (በእኔና በባሪያዬ መካከል ያለ ምስጢር ስለሆነ) የእኔ ነው፤ እኔ ነኝ ምንዳውን የምለግሰው፤ ስሜቱንም ምግቡንም ለኔ ብሎ የሚተውበት ነውና።" ፆም ጋሻ ነው። ለፆመኛ ሁለት ደስታዎች አሉለት: ሲያፈጥርም ይደሰታል አላህን በሚያገኘው ጊዜም ይደሰታል። የፆመኛ አፍ ጠረን አላህ ዘንድ ከውድ ሽቶ በላይም ያውዳል።»3 የፆም ምንዳ መደራረብ በቁጥር የሚገደብ አይደለም።
5) በፆም ጊዜ የሚኖር ኢኽላስ በሌላው አምልኮ ወቅት ከሚኖር ኢኽላስ በላይ ነው። እንዲህ ብሎ ገልፆታልና:
«تَرَكَ شَهْوَتَهُ وَطَعَامَهُ وَشَرَابَهُ مِنْ أَجْلِي».
«ለኔ ብሎ ስሜቱንም ምግቡንም መጠጡንም ትቷልና።»4
6) አላህ ከጀነት በሮች መካከል አንዱን ለፆመኞች ብቻ መለየቱ፤ ይህም ረያን የተሰኘው በር ሲሆን ከፆመኞች ውጭ የሚገባበት የለም።
7) ፆመኛ ዱዓው ተቀባይነቱ ከፍ ያለ ነው: ይህም ነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በርሳቸው ላይ ይስፈንና) እንዲህ በማለታቸው ነው:
«لِلصَّائِمِ عِنْدَ فِطْرِهِ دَعْوَةٌ لَا تُرَدُّ».
«ፆመኛ በሚያፈጥር ጊዜ የሚያደርገው ዱዓ ምላሹን ያገኛል አይመለስም።»5
8) ነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በርሳቸው ላይ ይስፈንና) እንዲህ ብለዋል:
«مَنْ صَامَ رَمَضَانَ إِيمَانًا وَاحْتِسَابًا، غُفِرَ لَهُ مَا تَقَدَّمَ مِنْ ذَنْبِهِ».
«አምኖ እና አላህ ዘንድ ያለውን ምንዳ አስቦ የረመዷንን ወር የፆመ ሰው ያለፈው ወንጀሉ ይማርለታል።»6
በመሆኑም ሙስሊም ምንዳውን ሊያገኝና ወንጀሉ እንዲማርለት ዘንድ ወሩን ሲፆም አምኖ እና አላህ ዘንድ የሚያገኘውን ምንዳ አስቦ መሆን አለበት።
ሶስተኛው ጥናት:
የረመዷን ወር መግባቱ የሚረጋገጥበት መንገድ:
የረመዷን ወር መግባቱ የሚረጋገጠው ከሁለት መንገዶች በአንዱ ነው:
1) ጨረቃን በማየት፤ ነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በርሳቸው ላይ ይስፈንና) እንዲህ ብለዋል:
«إِذَا رَأَيْتُمُ الْهِلَالَ فَصُومُوا، وَإِذَا رَأَيْتُمُوهُ فَأَفْطِرُوا، فَإِنْ غُمَّ عَلَيْكُمْ فَاقْدُرُوا لَهُ».
«ጨረቃ ስታዩ ፁሙ፤ ጨረቃን ስታዩ ደግሞ ፆማችሁን ፍቱ። (ጨረቃዋ) ከተጋረደባችሁ ደሞ (ላላችሁበት ወር) ገምቱለት።»7 እንዲህም ብለዋል:
«لَا تَصُومُوا حَتَّى تَرَوُا الْهِلَالَ، وَلَا تُفْطِرُوا حَتَّى تَرَوْهُ».
«ጨረቃን ካላያችሁ እንዳትፆሙ፤ ካላያችሁትም ፆማችሁን እንዳትፈቱ።»8
2) ጨረቃ ካልታየች የሸዕባንን ወር ሰላሳ ቀን ይሞላሉ፤ ይህም ነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በርሳቸው ላይ ይስፈንና) እንዲህ ብለዋል:
«الشَّهْرُ تِسْعٌ وَعِشْرُونَ لَيْلَةً، فَلَا تَصُومُوا حَتَّى تَرَوْهُ، فَإِنْ غُمَّ عَلَيْكُمْ فَأَكْمِلُوا الْعِدَّةَ ثَلَاثِينَ».
«አንድ ወር (ቢያንስ) ሃያ ዘጠኝ ቀን ነውና (ጨረቃን) እስክታዩ ድረስ ፆማችሁን አትጀምሩ፤ ከተጋረደባችሁ ግን የወሩን ቀናት ሰላሳ ሙሉት።»9
አራተኛው ጥናት:
የፆም ኒያ
የትኛውም ሥራ ትክክል ሊሆን ዘንድ ኒያ (ልባዊ ቁርጠኛ ሃሳቡ) ቅድመ መስፈርት ነው። የረመዷንን ፆም ለመፆምም ገና ከምሽቱ አንስቶ ማሰብ ግዴታ ነው። ይህም ነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በርሳቸው ላይ ይስፈንና) እንዲህ ስላሉ ነው:
«مَنْ لَمْ يُبَيِّتِ الصِّيَامَ قَبْلَ الْفَجْرِ، فَلَا صِيَامَ لَهُ».
«ጎህ ከመቅደዱ በፊት አስቀድሞ የፆም ኒያን (ሃሳብን) ያላሳደረ ሰው ፆም የለውም።»10
ሸይኹል ኢስላም ኢብኑ ተይሚያ (አላህ ይዘንላቸውና) እንዲህ ብለዋል: "ቀጣዩ ቀን ከረመዷን መሆኑን አውቆ እንደሚፆም ያሰበ ሁሉ የኒያ ቃሉን ቢያወጣም ባያወጣም የፆም ኒያን ነይቷል። ይህም አብዛኞቹ ሙስሊሞች የሚያደርጉትና የሚነይቱበት ነው።"11
አምስተኛው ጥናት:
ፆም ግዴታ የሚሆነው በማን ላይ ነው?
ሙስሊም ሆኖ፣ ለአቅመ አዳም የደረሰ (ለአቅመ ሄዋን የደረሰች) ሆኖ ጤናማ አዕምሮ ባለው ሰው ላይ ሁሉ ፆም ግዴታ ነው።
ጤናማ ሁኖ በሃገሩ ላይ ያለ ሰው በዕለቱ መፆሙ ግዴታው ሲሆን፤ ህመምተኛ ከሆነ ግን ግዴታው በተመቸው ቀን መፆም ነው።
ጤናማ ከመሆኑም ጋር መንገደኛ ከሆነ በማፍጠርና በመጾም መካከል ያማርጣል። በላጩ ግን ማፍጠሩ ነው።
ካፊር የመፆም ግዴታ የለበትም፤ ቢፆምም ፆሙ የተበላሸ ነው። በረመዷን ወር ውስጥ ሁኖ ከሰለመ ቀሪዎቹን ቀናት መፆም የሚጠበቅበት ሲሆን በክህደት ጊዜው ላለፉት ቀናት የመፆም ግዴታ የለበትም።
ህፃን ልጅ ላይ ፆም ግዴታ አይደለም፤ ልጅ ከመሆኑም ጋር ነገራቶችን መለየት የሚችልበት አዕምሯዊ አቅም ካለው ግን ፆሙ ትክክል ነው። ይህ ፆም ከልጅነቱ አንፃር እንደተጨማሪ መልካም ስራ ይታሰብለታል።
የአዕምሮ ህመምተኛ የመፆም ግዴታ የለበትም። ከእብደቱ ጋር ቢፆምም ፆሙ ትክክለኛ ኒያ [ሃሳብ] ስለሚጎለው ትክክል አይሆንም።
ስድስተኛው ጥናት:
ፆምን ለመተው ትክክለኛ ዑዝር (በቂ ምክንያት) የሚሆንለት ለማን ነው?
የረመዷን ወር ፆምን ለመተው ትክክለኛ ዑዝር (በሸሪዓ ተቀባይነት ያለው ምክንያት) የሚሆነው:
1) ፆም የሚከብደው ህመምተኛ ማፍጠሩ ይወደድለታል።
2) ጉዞ ላይ ባለበት ሁኔታ የረመዷን ወር የገጠመው ወይም በወሩ ውስጥ ሰማንያ (80) ኪ.ሜ እና ከዛም በላይ ርቀት ያለውን ጉዞ የወጣ ሰው (ለማፍጠር በቂ ምክንያት አለው)።
3) በወር አበባ ወይም በወሊድ ደም ላይ ያለች ሴት ደም መፍሰሱ ሳይቆም መፆም ትከለከላለች። ይህም እናታችን ዓኢሻ (አላህ መልካም ስራዋን ይውደድላትና) እንዲህ ስላለች ነው: «(የደም መፍሰሱ) ይገጥመንና ፆማችንን ቀዷ እንድናወጣ የምንታዘዝ ሲሆን ሰላትን ግን ቀዷ እንድናወጣ አንታዘዝም ነበር።»12
4) ህመሙ እያለ መፆምን አዳጋች በሚያደርግ የማይለቅ በሽታ የተጠቃ ሰው ያፈጥራል፤ ለየቀኑም ከስንዴ ወይም ከሌላ እህል ግማሽ "ሷዕ" ያህል እያሰበ ለሚስኪን ያበላል እንጂ (ሌላ ጊዜ) መፆም አለብህ አይባልም።
5) መፆም የተሳነው ደካማ ሽማግሌ ያፈጥራል፤ ለየቀኑም ሚስኪንን ያበላል እንጂ ቀዷ ማውጣት አለብህ አይባልም።
6) ነፍሰ ጡር እና የምታጠባ በፆሟ ምክንያት ራሷ ላይም ይሁን ልጇ ላይ የሚያሰጋቸው ነገር ካለ አፍጥረው ቀዷ ማውጣት ይጠበቅባቸዋል። ስጋቱ የመጣው ለልጇ ሲባል ከሆነ ግን ቀዷ ከማውጣት በተጨማሪ ለእያንዳንዱ ቀን ሚስኪንን ማብላት ይጠበቅባታል።
ሰባተኛ ጥናት:
ፆምን የሚያበላሹ ነገሮች
1‐ ፆታዊ ግንኙነት መፈፀም
በረመዷን የቀኑ ክፍለ ጊዜ ግንኙነት ከፈፀመ ፆሙ ይበላሻል፤ ይሁን እንጂ ቀሪውን የቀኑን ክፍለ ጊዜ (ከሚያስፈጥሩ ነገራቶች) ከመታቀብ በተጨማሪ ሊፀፀትና የአላህን መሃርታ መጠየቅ አለበት። እንዲሁም ያፈጠረበትን ቀን ማካካሻ ከመፆም በተጨማሪ ማሰረዣውንም ማውጣት ይጠበቅበታል። ይህም ባርያን ነፃ ማውጣት ነው፤ ይህንን ማድረግ ካልቻለ ሁለት ወር አከታትሎ መፆም ነው፤ ሁለት ወር አከታትሎ መፆም ካልቻለም ለእያንዳንዱ ሚስኪን ከስንዴም ይሁን ከሌላ የአካባቢው ቀለብ ግማሽ "ሷዕ" እያደረገ ስልሳ ሚስኪኖችን ማብላት ይጠበቅበታል።
2‐ አብዝቶ በማየትም ይሁን በመሳሳም ወይም በመነካካት አልያም ራስን በማርካት የዘር ፈሳሽ ማውጣቱ:
ፆመኛ ከተጠቀሱት በየትኛውም ምክንያት የዘር ፈሳሽ ከወጣው ፆሙ ተበላሽቷል፤ ቀሪውን የቀኑን ክፍለጊ ዜ ከሚያስፈጥሩ ነገራቶች መታቀብ ያለበት ሲሆን ላፈጠረው ቀንም ማካካሸውን መፆም አለበት። ከፋራ ማውጣት ባይጠበቅበትም ወደ አላህ መመለስ፣ መፀፀት፣ መሀርታን መጠየቅና ስሜትን የሚያነቃቁ ከሆኑት ከነዚህ ነገራቶች መራቅ አለበት። ምክንያቱም ያለበት ሁኔታ በትልቅ ዒባዳ ላይ ነውና።
3‐ ሆን ብሎ መብላትና መጠጣት
4‐ በዋግምትም ይሁን በማፍሰስ አልያም ደም ለመለገስ የሚወጣ ደም።
ለዚህም መነሻችን ነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በርሳቸው ላይ ይስፈንና) ዋግምትን አስመልክተው እንዲህ ማለታቸው ነው:
«أَفْطَرَ الْحَاجِمُ وَالْمَحْجُومُ».
«ዋግምት ያደረገውም የተደረገለትም አፍጥረዋል።»13
ሸይኹል ኢስላም ኢብኑ ተይሚያ አላህ ይዘንላቸውና እንዲህ ብለዋል: «ዋግምት የሚያስፈጥር መሆኑ የነ ኢማም አሕመድ፣ ኢስሓቅ ኢብኑ ራሀወይህ፣ ኢብኑ ኹዘይማ፣ ኢብኑል ሙንዚር እና የሌሎችም የአብዛኞቹ የሐዲሥ ልሒቃን አቋም ነው።»14
እንደ ነስር፣ የቁስል ደም፣ በጥርስ መነቀል እና በመሳሰሉት ምክንያት ፆመኛ ያለፍላጎቱ የሚወጣውን ደም በተመለከተ ፆሙ ላይ የሚፈጥረው ተፅዕኖ የለም።
5‐ ሆን ብሎ ማስታወክ።
ሆድ ውስጥ ያለን ምግብ ወይም መጠጥ ሆን ብሎ በአፍ በኩል ማውጣት ነው። ሳይፈልግ ትውከቱ አሸንፎት የወጣ ከሆነ ግን ፆሙ ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ የለም። ምክንያቱም ነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በርሳቸው ላይ ይስፈንና) እንዲህ ስላሉ ነው:
«مَنْ ذَرَعَهُ الْقَيْءُ فَلَيْسَ عَلَيْهِ قَضَاءٌ، وَمَنْ اسْتَقَاءَ فَلْيَقْضِ».
«ትውከቱ አሸንፎት ያስታወከ ሰው ቀዷ ማውጣት አይጠበቅበትም፤ ሆን ብሎ ያስታወከ ግን ቀዷእ ማውጣት አለበት።»15 ትውከቱ አሸንፎት ሲባል መቆጣጠር አቅጦት ሲያስታውክ ማለት ነው።
ስምንተኛ ጥናት፡
በፆም ወቅት የሚወደዱ ነገሮች
1) ሰሑር መብላት: ይህም አነስ ኢብኑ ማሊክ (አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና) ባስተላለፉት ሐዲሥ ነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በርሳቸው ላይ ይስፈንና) እንዲህ ስላሉ ነው:
«تَسَحَّرُوا، فَإِنَّ فِي السُّحُورِ بَرَكَةً».
«ሰሑር ላይ በረካ ስላለ ሰሑር ብሉ።»16
2) ጎህ እንዳይቀድ እስካልተሰጋ ድረስ ሰሑር የሚበሉበትን ጊዜ ማዘግየት።
3) ፀሐይ መጥለቋ ከተረጋገጠ ፈጥኖ ማፍጠር፤ የአላህ መልዕክተኛ (የአላህ ሶላትና ሰላም በርሳቸው ላይ ይስፈንና) እንዲህ ብለዋል:
«لَا تَـزَالُ أُمَّتِي بِخَيْرٍ، مَا أَخَّرُوا السُّحُورَ، وَعَجَّلُوا الْفِطْرَ».
«ሰሑርን እስካዘገዩና ማፍጠሪያን እስካፈጠኑ ድረስ ህዝቤ መልካም ነገር ላይ ከመሆን አይወገድም።»17
4) ከተቻለ በእሸት ቴምር ካልሆነ በተገኘው ቴምር እሱም ካልተገኘ በውሃ ማፍጠሩ የተወደደ ነው። ይህም አነስ ረዲየሏሁ ዓንሁ አንዲህ ስላሉ ነው:
«كَانَ رَسُولُ اللَّهِ ﷺ يُفْطِرُ عَلَى رُطَبَاتٍ قَبْلَ أَنْ يُصَلِّيَ، فَإِنْ لَمْ تَكُنْ رُطَبَاتٌ، فَعَلَى تَمَرَاتٍ، فَإِنْ لَمْ تَكُنْ، حَسَا حَسَوَاتٍ مِنْ مَاءٍ».
«የአላህ መልዕክተኛ (የአላህ ሶላትና ሰላም በርሳቸው ላይ ይስፈንና) ከመስገዳቸው በፊት በእሸት ቴምር ያንን ካላገኙ በተገኘው ቴምር ያንንም ካላገኙ ደግሞ ትንሽም ብትሆን ውሃ ጎንጨት ብለው ያፈጥሩ ነበር፤»18
5) ፆመኛ ሰው በሚያፈጥርበት ጊዜ ያሻውን ዱዓ ቢያደርግ የሚበረታታ ነው። ነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በርሳቸው ላይ ይስፈንና) እንዲህ ብለዋል:
«إِنَّ لِلصَّائِمِ عِنْدَ فِطْرِهِ دَعْوَةً لَا تُرَدُّ».
«ፆመኛ በሚያፈጥርበት ጊዜ የሚያደርገው ዱዓ ተቀባይነት ያገኛል አይመለስም።»19
6) መልካም ስራዎች ክፋትን ስለሚያስወግዱ አምልኮን በየአይነቱ ማብዛት: ቁርአን መቅራት፣ አላህን ማስታወስ፣ ሌሊት ተነስቶ መስገድ፣ የተራዊሕ ሶላት መስገድ፣ ከግዴታ ሶላት በፊትና በኋላ ያሉ ሱናዎችን መስገድ፣ ሶደቃ መስጠት፣ በኸይር ነገር ላይ መለገስ ይገባል።
ዘጠነኛ ጥናት:
ማሳሰቢያዎች
ፆመኛ የሆነ ሰው ውሸትን፣ ሃሜትንና ዘለፋን ይበልጥ መራቅ አለበት። ሰው ደርሶ ቢሰዳደበውና ቢዘልፈው እንኳ "እኔ ፆመኛ ነኝ" ይበለው።
ነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በርሳቸው ላይ ይስፈንና) እንዲህ ብለዋል:
«الصِّيَامُ جُنَّةٌ، فَلَا يَرْفُثْ وَلَا يَجْهَلْ، وَإِنِ امْرُؤٌ قَاتَلَهُ أَوْ شَاتَمَهُ، فَلْيَقُلْ: إِنِّي صَائِمٌ، إِنِّي صَائِمٌ».
«ፆም ጋሻ ነውና አይባልግ ፀያፍ ተግባርን አይስራ፤ ሰው ለነገር ቢፈልገውና ቢጋደለው ወይም ቢዘልፈው እንኳ ሁለት ጊዜ "እኔ ፆመኛ ነኝ" ይበል።»20
ፆመኛ ከሚከለከላቸው ነገሮች መካከልም: በውዱእ ጊዜ በአፉ ሲጉመጠመጥም ሆነ ውሃን ወደ አፍንጫው ሲያስገባ (ሲሰረነቅ) በጣም አለመሳብ ነው፤ ምክንያቱም ውሃው አምልጦት ወደ ሆዱ ሊደርስ ይችላልና።
ነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በርሳቸው ላይ ይስፈንና) እንዲህ ብለዋል፡
«وَبَالِغْ فِي الِاسْتِنْشَاقِ إِلَّا أَنْ تَكُونَ صَائِمًا».
«ፆመኛ ካልሆንክ በቀር ውሃን በጣም ወደ አፍንጫህ ሳብ።»21
ሲዋክ በፆም ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ የለም፤ ይልቁንም በትክክለኛው የዑለሞች አቋም መሰረት ጧትም ይሁን ማታ ለፆመኛም ይሁን ለሌላው ሰው የሚወደድና የሚበረታታ የሆነ ጉዳይ ነው።
አስረኛው ጥናት:
በረመዷን ሳንፆም ያመለጠንን ቀን ማካካስ
በሸሪዓ እይታ እንደሚያስፈጥሩ ከተገለፁት ነገሮች መካከል በፍቁድ ምክንያቶች ወይም ፆታዊ ግንኙነትና መሰል በሆኑ በሐራም ምክንያቶች ያፈጠረ ሰው ያፈጠረበትን ቀን ማካካሻ መፆም አለበት። የላቀው አላህ እንዲህ ብሏልና:
﴿...فَعِدَّةٞ مِّنۡ أَيَّامٍ أُخَرَ...﴾
(ከሌሎች ቀኖች ቁጥሮችን መፆም አለበት።) (አል‐በቀራህ: 184) ያለፈበትን ቀን ማካካሻውን ሲፆምም ኃላፊነቱን ለመወጣት መፍጠን አለበት። ማካካሻው ዋናውን የሚተካ ስለሆነ የማካካሻ ፆሙን ሲፆም ማከታተሉ ተመራጭ ነው። ካስፈለገ ጊዜው ሰፊ ሰለሆነ ማዘግየትም ይችላል።
እንዲሁም ቀናቱን ለያይቶ ቀዷ ማውጣትም ይቻላል። ይሁን እንጂ ከሸዕባን ወር (የቀጣዩ ረመዷን ሊገባ) የቀሩት ቀናት ካለበት የረመዷን ቀናት ቀዳ ጋር እኩል ከሆነ ከጊዜው እጥረት አንፃር ያለ ምንም ልዩነት አከታትሎ መፆም ግዴታው ነው። በቂ ምክንያት ሳይኖር እስከቀጣዩ ረመዷን ድረስ ማዘግየት አይፈቀድም።
ያመለጠውን የረመዷን ቀናት ሳያካክስ ቀጣዩ ረመዷን የደረሰበት ሰው ሁለት ሁኔታዎች ይኖሩታል:
ያዘገየው በቂ በሆነ ሸሪዓዊ ምክንያት ከሆነ ለምሳሌ: ህመሙ እስከቀጣዩ ረመዷን ድረስ ቆይቶ ከሆነ ይህ ቀዷእ ማውጣት ብቻ ነው የሚጠበቅበት።
ያለ በቂ ሸሪዓዊ ምክንያት ያዘገየው ከሆነ ለፆሙ ማካካሻውን ከመፆሙ በተጨማሪ ለየቀኑ የሀገሪቱ ህዝብ ለቀለብነት ከሚገለገለው እህል ግማሽ ሷዕ እያደረገ ሚስኪንን የማብላት ግዴታ አለበት።
ቀዷእ (የሚያካክሰው) ፆም እያለበት መፆም: ከረመዷን ቀናት ማካካስ የሚጠበቅበት ቀን ያለበት ሰው ተጨማሪውን የሱና ፆም ከመፆሙ በፊት አስቀድሞ የግዴታ ፆሙን ቢፆም የተሻለ ነው። ይሁን እንጂ ፆሙ እንደ የዓሹራና የዓረፋ አይነቱ ጊዜው ሊያመልጥ የሚችል አይነቱ ፆም ከሆነ ግን ቀዷ ከሚያወጣው ፆም በፊትም ቢሆን ይፁመው። ምክንያቱም ቀዷ የሚያወጣው ፆም ሰፊ ጊዜ ያለው ሲሆን የዓሹራ እና የዐረፋ አይነቱ ግን ወቅቱ ሊያመልጥ የሚችል አይነት ፆም ነው። ይህ ግን ስድስቱ የሸዋል ቀናትን አይመለከትም፤ ቀዷእ የሆነውን ፆም ሳይፆም መፆም የሌለባቸው ናቸውና።
አላህ ያገራልን እዚህ ድረስ ነው። የአላህ ሰለዋትና ሰላም በርከት ብሎ በነቢዩ ሙሐመድ፣ በተከታዮቻቸውና በባልደረቦቻቸውም ላይ ሁሉ ይስፈን።
***
ማውጫ
የመጀመሪያው ጥናት: 2
የፆም ትርጓሜ እና የረመዷን ወርን መፆም ግዴታ ስለመሆኑ: 2
ሁለተኛው ጥናት: 4
የረመዷን ወር ትሩፋቶች 4
ሶስተኛው ጥናት: 7
የረመዷን ወር መግባቱ የሚረጋገጥበት መንገድ: 7
አራተኛው ጥናት: 8
የፆም ኒያ 8
አምስተኛው ጥናት: 9
ፆም ግዴታ የሚሆነው በማን ላይ ነው? 9
ስድስተኛው ጥናት: 10
ፆምን ለመተው ትክክለኛ ዑዝር (በቂ ምክንያት) የሚሆንለት ለማን ነው? 10
ሰባተኛ ጥናት: 11
ፆምን የሚያበላሹ ነገሮች 11
ስምንተኛ ጥናት፡ 14
በፆም ወቅት የሚወደዱ ነገሮች 14
ዘጠነኛ ጥናት: 16
ማሳሰቢያዎች 16
አስረኛው ጥናት: 17
በረመዷን ሳንፆም ያመለጠንን ቀን ማካካስ 17
***
am419v1.0 - 22/02/2026
ቡኻሪይና ሙስሊም ዘግበውታል፤ ቡኻሪይ ቁጥር 1898 (3/25) ላይ ሙስሊም ደግሞ ቁጥር 1079 (2/758) ላይ ዘግበውታል።
ነሳኢይ በ "አል‐ኩብራ" ቁጥር 2536 (3/131) ላይ ዘግበውታል።
ያለፈውን ምንጭ ይመልከቱ
ኢብኑ ማጃህ ቁጥር 1753 (1/775) ላይ ዘግበውታል።
ቡኻሪይና ሙስሊም ዘግበውታል፤ ቡኻሪይ ቁጥር 38 (1/16) ላይ ሙስሊም ደግሞ ቁጥር 760 (1/523) ላይ ዘግበውታል።
ኢማሙ አሕመድ በሙስነዳቸው ቁጥር 6323 (10/402) ላይ፤ ነሳኢይ በ "አል‐ኩብራ" ቁጥር 2446 (3/102) ላይ ዘግበውታል።
ቡኻሪይና ሙስሊም ዘግበውታል፤ ቡኻሪይ ቁጥር 1906 (3/27) ላይ ሙስሊም ደግሞ ቁጥር 1080 (2/759) ላይ ዘግበውታል።
ቡኻሪይና ሙስሊም ዘግበውታል፤ ቡኻሪይ ቁጥር 1907 (3/27) ላይ ሙስሊም ደግሞ ቁጥር 1081 (2/762) ላይ ዘግበውታል።
ነሳኢይ "አል‐ኩብራ" ላይ በቁጥር 2652 (3/170) ዘግበውታል።
"አል‐ፈታዋ አል‐ኩብራ" (2/469)
ኢማም ሙስሊም በሶሒሕ ኪታባቸው ቁጥር 335 (1/265) ላይ ዘግበውታል።
ቡኻሪይ ቁጥር 1937 (3/33) ላይ፤ አሕመድ በሙስነዳቸው ቁጥር 26217 (43/278) ላይ ዘግበውታል።
መጅሙዑል ፈታዋ (25/252)
ኢማም አሕመድ በሙስነዳቸው ቁጥር 10463 (16/283) ላይ፤ ቲርሚዚይ በ "አል‐ጃሚዑል ከቢር" ቁጥር 720 (2/91) ላይ ዘግበውታል።
ቡኻሪይና ሙስሊም ዘግበውታል፤ ቡኻሪይ ቁጥር 1923 (3/29) ላይ ሙስሊም ደግሞ ቁጥር 1095 (2/770) ላይ ዘግበውታል።
ኢማሙ አሕመድ በሙስነዳቸው ቁጥር 12507 (35/399) ላይ ዘግበውታል።
አቡ ዳውድ ቁጥር 2356 (2/306) ላይ ዘግበውታል።
ኢብኑ ማጃህ ቁጥር 1753 (1/775) ላይ ዘግበውታል።
ቡኻሪይ ቁጥር 1894 (3/24) ላይ ዘግበውታል።
አቡ ዳውድ ቁጥር 2366 (2/308) ላይ ቲርሚዚይም በ "አል‐ጃሚዑል ከቢር" ቁጥር 788 (2/147) ላይ ዘግበውታል።
ቡኻሪይና ሙስሊም ዘግበውታል፤ ቡኻሪይ ቁጥር 8 (1/11) ላይ ሙስሊም ደግሞ ቁጥር 16 (1/34) ላይ ዘግበውታል።