PHPWord

 

 

دَفْنُ المَوتَى فِي المَسَاجِدِ

 

 

ሙታንን በመስጂዶች ውስጥ መቅበር

 

 

 

 

 

لِسَمَاحَةِ الشَّيْخِ العَلَّامَةِ

عَبْدِ العَزِيزِ بْنِ عَبْدِ اللهِ بْنِ بَازٍ

رَحِمَهُ اللهُ

 

ዝግጅት፦ የተከበሩ ሸይኽ

ዐብዱልዐዚዝ ቢን ዐብደላህ ቢን ባዝ

 

 

 


بِسْمِ اللهِ الرَّحمَنِ الرَّحِيمِ

አስራ አንደኛ መልዕክት:

ሙታንን በመስጂዶች ውስጥ መቅበር

በአላህ ስም፤ ምስጋና ሁሉ ለአላህ የተገባ ነው። የአላህ ሰላትና ሰላም በአላህ መልእክተኛ፣ በቤተሰቦቻቸውና እንዲሁም የእርሳቸውን ቅን ጎዳና በተከተለም ላይ ሁሉ ይስፈን። በመቀጠል፦

በ 17/4/1415 ዓ.ሂ የወጣችውን «አል-ኸርጡም» ጋዜጣ ተመልክቼ ነበር፤ በውስጧም አስ-ሰይድ ሙሐመድ አል-ሐሰን አል-ኢድሪሲ በኡምዱርማን ከተማ በሚገኘው መስጊዳቸው ከአባታቸው ጎን ስለመቀበራቸው …… የወጣ መግለጫ ታትሞ አግኝቻለሁ።

አላህ ለሙስሊሞች መካሪ መሆንን፣ መጥፎን ነገር መከልከልን እና ግልፅ ማድረግን ግዴታ ስላደረገ፤ በመስጂዶች ውስጥ መቅበር የማይፈቀድ ነገርና ይልቁንም ወደ ሺርክ ከሚያዳርሱ ነገሮች መካከል መሆኑን ለማስታወስ ወደድኩ። እንዲሁም አላህ በእርሱ የወቀሳቸውና የአላህ መልዕክተኛም ﷺ የረገሟቸው ከሆኑት ከአይሁዶችና ከክርስቲያኖች ተግባራትም ነው። በቡኻሪና ሙስሊም ከእናታችን ዓኢሻ (አላህ ስራዋን ይውደድላትና) እንደተዘገበው ነቢዩ ﷺ እንዲህ ብለዋል፦

«لَعَنَ اللَّهُ الْيَهُودَ وَالنَّصَارَى، اتَّخَذُوا قُبُورَ أَنْبِيَائِهِمْ مَسَاجِدَ».

"አላህ አይሁድና ክርስቲያኖችን ረገመ። የነቢያቶቻቸውን መቃብር መስጂድ አድርገው ያዙ።" በሶሒሕ ሙስሊምም ጁንዱብ ቢን ዐብዲላህ እንዳስተላለፉት ነብዩ - የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን - እንዲህ ብለዋል:

«أَلَا وَإِنَّ مَنْ كَانَ قَبْلَكُمْ كَانُوا يَتَّخِذُونَ قُبُورَ أَنْبِيَائِهِمْ وَصَالِحِيهِمْ مَسَاجِدَ، أَلَا فَلَا تَتَّخِذُوا الْقُبُورَ مَسَاجِدَ؛ فَإِنِّي أَنْهَاكُمْ عَنْ ذَلِكَ».

"ንቁ! ከእናንተ በፊት የነበሩት የነቢያቶቻቸውንና የደጋጎቻቸውን መቃብር መስገጃ አድርገው ይይዙ ነበር፤ ንቁ! መቃብሮችን መስገጃ አድርጋችሁ አትያዙ፤ እኔ ከዚህ ነገር እከለክላችኋለሁና።" ይህንን መልዕክት ይዘው የመጡ ሐዲሦች እጅግ በጣም ብዙ ናቸው።

በመሆኑም በየትኛውም ቦታ በሚገኙ ሙስሊሞች ላይ - መንግስታትም ሆኑ ህዝቦች - አላህን መፍራት፣ እርሱ ከከለከለው ነገር መጠንቀቅና ነቢዩ ﷺ እና ባልደረቦቻቸው (አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላቸውና) እና እነርሱን በመልካም የተከተሉት ሟቾችን ከመስጂዶች ውጭ ይቀብሩ እንደነበረው ሁሉ ሟቾቻቸውን ከመስጂዶች ውጭ መቅበር ግዴታ ነው።

የነብዩ ﷺ እና የሁለቱ ባልደረቦቻቸው የአቡበክርና የዑመር (አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላቸውና) ቀብር በእርሳቸው መስጂድ ውስጥ መገኘቱ ሙታንን በመስጂዶች ውስጥ ለመቅበር ማስረጃ አይሆንም። ምክንያቱም እርሳቸው ﷺ የተቀበሩት በቤታቸው - በአዒሻ (አላህ መልካም ሥራዋን ይውደድላትና) ቤት ውስጥ - ነውና። ከዚያም ሁለቱ ባልደረቦቻቸው ከእርሳቸው ጋር ተቀበሩ። ወሊድ ኢብን ዐብዱልመሊክ ከሂጅራ በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን መባቻ ላይ መስጂዱን ሲያሰፋ ክፍሉን ከመስጂዱ ጋር አካተተው። የእውቀት ሰዎችም ይህን ድርጊቱ አውግዘውበት ነበር። ነገር ግን እርሱ ይህ መስጂዱን ከማስፋፋት እንደማይከለክልና ጉዳዩም ግልፅና የማያሻማ እንደሆነ አስቧል።

በዚህም ለእያንዳንዱ ሙስሊም ግልፅ የሚሆነው፤ እርሳቸው ﷺ እና ሁለቱ ባልደረቦቻቸው (አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና) መስጂድ ውስጥ አለመቀበራቸው ነው። በመስጂዱ የማስፋፊያ ስራ ምክንያት ወደ መስጂዱ ግዛት ውስጥ መካተታቸው በመስጂዶች ውስጥ መቅበር እንደሚፈቀድ ማስረጃ ሊሆን አይችልም። ምክንያቱም እነርሱ የተቀበሩት መስጂድ ውስጥ ሳይሆን በሳቸው ﷺ ቤት ውስጥ ነውና። እንዲሁም የወሊድ ስራ በዚህ ጉዳይ ላይ ለማንም ሰው ማስረጃ ሊሆን አይችልም። ይልቁንም ማስረጃው ቁርአን እና ሐዲሥ እንዲሁም የኡማው ቀደምት ሰለፎች ስምምነት (ኢጅማዕ) ነው። አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና እኛንም በበጎ መልኩ ከተከታዮቻቸው ያድርገን።

ምክርን ለመለገስና ኃላፊነትን ለመወጣት ሲባል በ14/5/1415 ሂ. ተጻፈ (ተዘጋጀ)።

ለመልካም የመገጠም ባለቤቱ አላህ ነው። የአላህ ሶላትና ሰላም በነቢያችን ሙሐመድ፣ በቤተሰቦቻቸውና ባልደረቦቻቸው እንዲሁም በመልካም በተከተሏቸው ላይ ሁሉ ይስፈን።

 

 

***

 

 

am397v4.0 - 21/04/2026