مَا لَا يَسَعُ المُسْلِمَ جَهْلُهُ
ማንም ሙስሊም ሳያውቀው ሊቀር የማይፈቀድለት ጉዳዮች (እያንዳንዱ ሙስሊም ሊያውቀው የግድ የሚለው)
اللَّجْنَةُ العِلْمِيَّةُ
بِرِئَاسَةِ الشُّؤُونِ الدِّينِيَّةِ بِالمَسْجِدِ الحَرَامِ وَالمَسْجِدِ النَّبَوِيِّ
በመስጂደል ሐረም እና በመስጂድ አን-ነበዊይ በሃይማኖት ዘርፍ የዕውቀት ነክ ጉዳዮች ርዕሰ መስተዳድር ኮሚቴ ያዘጋጀው
بِسْمِ اللَّهِ الرَّحْمَنِ الرَّحِيمِ
ማንም ሙስሊም ሳያውቀው ሊቀር የማይፈቀድለት ጉዳዮች (እያንዳንዱ ሙስሊም ሊያውቀው የግድ የሚለው)
መግቢያ
ምስጋና ሁሉ ለዓለማት ጌታ ለሆነው ለአላህ የተገባ ነው። የአላህ ሰላትና ሰላም የዓለማት እዝነት ተደርገው በተላኩት ነቢይ፣ በቤተሰቦቻቸው፣ በባልደረቦቻቸውና እስከ ዕለተ ትንሳኤ የርሳቸውን ሱንና (ፈለግ) በተከተሉ እንዲሁም በመመሪያቸው በተመሩ ላይ ሁሉ ይስፈን። ከዚህ በመቀጠል:
ይህች፤ አንድ ሙስሊም በዐቂዳው (በእምነቱ)፣ በዒባዳው (በአምልኮው) እና በመስተጋብሩ (በማህበራዊ ግንኙነቱ) ውስጥ ከሚያስፈልጉት መካከል በጣም ወሳኞቹን ያካተተች አጭር መልእክት (መጽሐፍ) ናት። ያጠናቀርነውም የሁለቱን የተከበሩ ሐረሞች (የመካና የመዲናን) ጎብኚ ለሆኑ ወንዶችና ሴቶች ሲሆን ሃይማኖታቸውን በዕውቀትና በግልፅ መረጃ ላይ ሆነው እንዲይዙ በማሰብ ነው። ቸርና ለጋስ የሆነው አላህ ጠቃሚ ሊያደርጋት፣ ለርሱ ብቻ የተሰራች በጎ ስራ ያደርግልን ዘንድ ተስፋ እናደርጋለን። እነሆ ቢለምኑት ደጉ ተስፋ ቢያደርጉበት ቸሩ እርሱ ነውና።
በመስጂደል ሐረም እና በመስጂድ አን-ነበዊይ በሃይማኖት ዘርፍ የዕውቀት ነክ ጉዳዮች ርዕሰ መስተዳድር ኮሚቴ የተዘጋጀ
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ምዕራፍ አንድ
ዐቂዳን (እምነትን) የሚመለከቱ ጉዳዮች
የመጀመሪያው ክፍል: የእስልምና ትርጉምና ማዕዘናቱ፦
እስልምና ማለት: ለአላህ ትዕዛዝ ሁለመናን ሰጥቶ እርሱን በብቸኝነት ማምለክ፤ ለትዕዛዙ ፍፁም ታዛዥ መሆን እንዲሁም ከሺርክና ከባለቤቶቹ ሙሉ ለሙሉ መጥራት ነው፡፡
የእስልምና ማዕዘናቱ አምስት ናቸው፦
የመጀመሪያው ማዕዘን፦ ከአላህ በስተቀር በእውነት የሚመለክ አምላክ እንደሌለና ሙሐመድም የአላህ መልዕክተኛ መሆናቸውን መመስከር፤
ሁለተኛው ማዕዘን፡ ሰላትን በአግባቡ መስገድ፤
ሶስተኛው ማዕዘን፡ ዘካን መስጠት፤
አራተኛው ማዕዘን፦ የረመዷንን ወር መፆም፤
አምስተኛው ማዕዘን: አቅሙ የሚችል ከሆነ ወደ ተከበረው የአላህ ቤት ሐጅ ማድረግ ነው።
የተውሒድ አስፈላጊነት:
አሸናፊና የበላይ የሆነው አላህ ፍጡራኑን የፈጠረው እርሱን በብቸኝነት ሊያመልኩትና በእርሱ ላይ ምንንም ላያጋሩ መሆኑን እወቅ! አላህ እንዲህ ብሏል፦
﴿وَمَا خَلَقۡتُ ٱلۡجِنَّ وَٱلۡإِنسَ إِلَّا لِيَعۡبُدُونِ 56﴾
{ጂኒንና ሰውንም ሊግገዙኝ እንጅ ለሌላ አልፈጠርኳቸውም፡፡} [አዝ-ዛሪያት፡ 56] ይህ አምልኮ ደግሞ ካልተማሩ በቀር ሊታወቅ አይችልም። አላህ እንዲህ ብሏል፦
﴿فَٱعۡلَمۡ أَنَّهُۥ لَآ إِلَٰهَ إِلَّا ٱللَّهُ وَٱسۡتَغۡفِرۡ لِذَنۢبِكَ وَلِلۡمُؤۡمِنِينَ وَٱلۡمُؤۡمِنَٰتِۗ وَٱللَّهُ يَعۡلَمُ مُتَقَلَّبَكُمۡ وَمَثۡوَىٰكُمۡ 19﴾
{እነሆ ከአላህ ሌላ አምላክ አለመኖሩንም ዕወቅ፡፡ ስለ ስህተትህም ለምእመናንም ምሕረትን ለምን፡፡ አላህም መዘዋወሪያችሁን፣ መርጊያችሁንም ያውቃል፡፡} [ሙሐመድ፡ 19] ከንግግሩም ከተግባሩም በፊት ማወቅን አስቀድሞ ጀመረ። አንድ ሙስሊም ከሁሉም እውቀቶች አስቀድሞ መማር ያለበት ዋናው ነገር ስለ አላህ ብቸኛ ተመላኪነት (ተውሒድ) ነው። ምክንያቱም ተውሒድ የእስልምና ስረ መሰረት ነውና። እስልምና ያለ ተውሒድ ፀንቶ አይቆምም። አንድ ሙስሊም ላይ በመጀመሪያም ይሁን በመጨረሻ ያለበት ግዴታ ተውሒድ (አላህን መነጠል) ነው። ሁሉም ሙስሊም ማወቅና መተግበር ግዴታ ከሆኑበት ከእስልምና ማዕዘናት መካከልም የመጀመሪያው ማዕዘን ተውሒድ ነው። እስልምና አምስት ማዕዘናት አሉት: በዐብደላህ ቢን ዑመር ረዲየሏሁ ዐንሁማ -አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና- ሐዲሥ ውስጥ እንደተላለፈው እንዲህ አሉ: የአላህ መልክተኛ ﷺ እንዲህ ሲሉ ሰምቻዋለሁ:
«بُنِيَ الإسْلَامُ عَلَى خَمْسٍ: شَهَادَةِ أنْ لَا إلَهَ إلَّا اللَّهُ وأنَّ مُحَمَّدًا رَسُولُ اللَّهِ، وَإقَامِ الصَّلَاةِ، وَإيتَاءِ الزَّكَاةِ، وَحَجِّ البَيْتِ، وصَوْمِ رَمَضَانَ».
«እስልምና በአምስት ነገሮች ላይ ተገንብቷል፦ ከአላህ በስተቀር በእውነት የሚመለክ አምላክ አለመኖሩን እና ሙሐመድ የአላህ መልዕክተኛ መሆናቸውን መመስከር፣ ሶላትን ደንብና ሥርዓቱን ጠብቆ መስገድ፣ ዘካ መስጠት፣ ሐጅ ማድረግ (የአላህን ቤት መጎብኘት) እና የረመዳንን ወር መጾም ናቸው።»1
ስለዚህም የተውሒድን ትርጉም ማወቅ እያንዳንዱ ሙስሊም ላይ ግዴታ ነው። ትርጉሙም: አላህን በአምልኮ መነጠል ማለት ነው። ቅርብ መላእክቶችንም ሆነ የተላኩ ነቢያትን አንድንም አካል ከርሱ ጋር በአምልኮ አያጋራ።
ከአላህ በስተቀር በእውነት የሚመለክ እንደሌለ (ላኢላሃ ኢለሏህ በማለት) የመመስከር ትርጉሙ:
አንድ ባሪያ ከአላህ በቀር በእውነት የሚመለክ እንደሌለ ቁርጥ ያለና የማያወላዳ እምነት እንደሚያምን ማረጋገጡ ነው። አላህን በብቸኝነት ያመልካል፤ በዱዓም፣ በፍራቻም፣ በተስፋም፣ በመመካትም ሆነ ከዛ ውጪ ባሉ በሁሉም የአምልኮ አይነቶች አላህን ይነጥላል።
(ሸሃዳ) የላኢላሃ ኢለሏህ ምስክርነት ሁለት ማዕዘናት እስካልተሟሉ ድረስ አትረጋገጥም:
የመጀመሪያው: ተመላኪነትንና አምልኮን ከአላህ ውጪ ካሉ ሁሉ ባላንጣዎች፣ አማልክትና ጣዖታት ውድቅ ማድረግ ነው።
ሁለተኛው: ተመላኪነትንና ትክክለኛውን አምልኮ ከአላህ ውጪ ላሉ ሳይሆን ለአላህ ብቻ እንደሚገባ ማረጋገጥ ነው። የላቀው አላህ እንዲህ ብሏል፦
﴿وَلَقَدۡ بَعَثۡنَا فِي كُلِّ أُمَّةٖ رَّسُولًا أَنِ ٱعۡبُدُواْ ٱللَّهَ وَٱجۡتَنِبُواْ ٱلطَّٰغُوتَۖ...﴾
{በየሕዝቡም ሁሉ ውስጥ «አላህን ተገዙ፤ ጣዖትንም ራቁ» በማለት መልክተኛን በእርግጥ ልከናል።} [አን-ነሕል፡ 36]
የላኢላሃ ኢለሏህ መስፈርቶች ደግሞ የሚከተሉት ናቸው:
የመጀመሪያው: አለማወቅን የሚጋፈጥ የሆነ ዕውቀት፤
ሁለተኛው: ጥርጣሬን የሚጋፈጥ የሆነ እርግጠኝነት፤
ሶስተኛው: ሺርክን የሚጋፈጥ የሆነ ኢኽላስ (ስራን ለአላህ ማጥራት)፤
አራተኛው: ሀሳዊነትን የሚጋፈጥ የሆነ እውነተኝነት፤
አምስተኛው: ጥላቻን የሚጋፈጥ የሆነ ውዴታ፤
ስድስተኛው: መተውን የሚጋፈጥ የሆነ ታዛዥነት፤
ሰባተኛው: ውድቅ ማድረግን የሚጋፈጥ የሆነ መቀበል፤
ስምንተኛው: ከአላህ ውጪ በሚመለኩ ነገሮች መካድ ነው።
እነዚህን መስፈርቶች መጠበቅ ግዴታ ነው። በእነዚህ ስንኞች ተሰብስበውም ይገኛሉ:
① ለአላህ ብቻ ② በእውነተኝነት ***
③ እውቀትም ኖሮህ ④ በእርግጠኝነት ***
⑤ ታዛዥነትን አጣምረህ ⑥ በውዴታ ***
⑦ መቀበልህም ሆነህ በደስታ
⑧ በጣኦት መካድን ስታክልበት ***
ሙሉ መስፈርቷ ሆነልህ ስምንት
የላኢላሃ ኢለሏህ ምስክርነት የሚረጋገጠውም አላህን ሳያጋሩበት አምልኮን ለርሱ ብቻ በማረጋገጥ ነው። ከአላህ በቀር ማንንም አይለምን፤ ከአላህ በቀር በማንም ላይም አይመካ፤ ከማንምም ተስፋ አያድርግ፤ ለአላህ እንጅ ለማንምም አይስገድ፤ ለማንምም አይረድ።
አንዳንድ ሰዎች የሚሰሩት በመቃብር ዙሪያ ጦዋፍ ማድረግ፣ ውስጡ የተቀበሩትን እርዳታ መጠየቃቸውና ከአላህ ውጪ እነሱን መለመናቸው በአምልኮ ላይ የሚፈፀም ሺርክ ነው። ስለሆነም ይህንን መጠንቀቅና ማስጠንቀቅ ግዴታ ነው። ይህ ጣዖት፣ ድንጋይ፣ ዛፍና ሌሎችንም ከአላህ ውጪ የሚያመልኩ አጋርያን የሚሰሩት የሺርክ አይነት ነው። መጽሐፍት የወረዱት፣ መልክተኞች የተላኩት ይህንን ሺርክ ለማስጠንቀቅና ለመከልከል ነው።
ሙሐመድ የአላህ መልዕክተኛ መሆናቸውን የመመስከር ትርጓሜ:
ያዘዙትን መታዘዝ፤ የተናገሩትን እውነት ብሎ ማመንና መቀበል፤ ከከለከሉትና ካስጠነቀቁት ነገር መራቅ፤ አላህንም እርሳቸው ባስተማሩትና በደነገጉት መልኩ ብቻ ማምለክ፤ እንዲሁም ሙሐመድ ቢን ዐብደላህ አልቁረሺይ አልሃሺሚይ ከፍጡራን ወደ ሰውና ጂን ባጠቃላይ የተላኩ የአላህ ዓዘ ወጀል መልክተኛ መሆናቸውን ማመን ነው። የላቀው አላህ እንዲህ እንዳለን:
﴿قُلۡ يَٰٓأَيُّهَا ٱلنَّاسُ إِنِّي رَسُولُ ٱللَّهِ إِلَيۡكُمۡ جَمِيعًا...﴾
{(ሙሐመድ ሆይ!)፡- «እናንተ ሰዎች ሆይ! እኔ ወደናንተ ወደ ሁላችሁም የአላህ መልክተኛ ነኝ» በላቸው።…} [አልአዕራፍ:158]
አላህ ሃይማኖቱን እንዲያደርሱና ፍጡራንን እንዲመሩ ልኳቸዋል። ልክ የላቀው አላህ እንዲህ እንዳለን፦
﴿وَمَآ أَرۡسَلۡنَٰكَ إِلَّا كَآفَّةٗ لِّلنَّاسِ بَشِيرٗا وَنَذِيرٗا وَلَٰكِنَّ أَكۡثَرَ ٱلنَّاسِ لَا يَعۡلَمُونَ 28﴾
{አንተንም ለሰዎች ሁሉ በመላ አብሳሪና አስፈራሪ አድርገን ቢሆን እንጂ አላክንህም፡፡ ግን አብዛኞቹ ሰዎች አያውቁም፡፡} [ሰበእ፡ 28] የላቀው አላህ እንዲህም እንዳለን፦
﴿وَمَآ أَرۡسَلۡنَٰكَ إِلَّا رَحۡمَةٗ لِّلۡعَٰلَمِينَ 107﴾
{(ሙሐመድ ሆይ!) ለዓለማትም እዝነት አድርገን እንጅ አልላክንህም፡፡} [አል-አንቢያእ: 107]
ሙሐመድ የአላህ መልክተኛ መሆናቸውን መመስከር ከሚያስፈርዳቸው እውነታዎች መካከል: የአላህ መልክተኛ ﷺ የጌትነትና በፍጥረተ ዓለሙ የማስተናበር ወይም የተመላኪነት መብት እንዳላቸው ከማመን መቆጠብ፣ ይልቁንም እርሳቸው ﷺ ፈፅሞ የማይመለኩ ባሪያና ሊስተባበሉ የማይገባ መልክተኛ ናቸው። ለራሳቸውም ሆነ ለሌላው አላህ ከሻላቸው በቀር አንዳችም መጥቀምና መጉዳት አይችሉም። የላቀው አላህ እንዲህ እንዳለን፦
﴿قُل لَّآ أَقُولُ لَكُمۡ عِندِي خَزَآئِنُ ٱللَّهِ وَلَآ أَعۡلَمُ ٱلۡغَيۡبَ وَلَآ أَقُولُ لَكُمۡ إِنِّي مَلَكٌۖ إِنۡ أَتَّبِعُ إِلَّا مَا يُوحَىٰٓ إِلَيَّ...﴾
{«ለእናንተ የአላህ ግምጃ ቤቶች እኔ ዘንድ ናቸው አልልም፡፡ ሩቅንም አላውቅም፡፡ ለእናንተም እኔ መልአክ ነኝ አልልም፡፡ ወደእኔ የሚወርድልኝን እንጅ ሌላን አልከተልም» በላቸው፡፡…} [አልአንዓም: 50]
ክፍል ሁለት: የኢማን ትርጓሜና ማዕዘናቱ:
ኢማን ማለት: በቀልብ ማረጋገጥ፣ በምላስ መናገር፣ በቀልብና በአካል መተግበርን የሚያጠቃልል ነው። በታዛዥነት ይጨምራል። በአመፀኝነት ይቀንሳል።
አምልኮዎች ተቀባይነት እንዲያገኙና ትክክለኛ እንዲሆኑ ኢማን አንዱ መስፈርት ነው። ልክ ሺርክና ክህደት አምልኮዎችን ባጠቃላይ የሚያበላሹ እንደሆኑት ማለት ነው። አላህ ሶላትን ያለ ዉዱእ እንደማይቀበለው ሁሉ አምልኮንም ያለ ኢማን አይቀበልም። የላቀው አላህ እንዲህ ብሏል፡
﴿وَمَن يَعۡمَلۡ مِنَ ٱلصَّٰلِحَٰتِ مِن ذَكَرٍ أَوۡ أُنثَىٰ وَهُوَ مُؤۡمِنٞ فَأُوْلَٰٓئِكَ يَدۡخُلُونَ ٱلۡجَنَّةَ وَلَا يُظۡلَمُونَ نَقِيرٗا 124﴾
{ከወንድ ወይም ከሴት እርሱ አማኝ ኾኖ ከበጎ ሥራዎች አንዳችን የሚሠራም ሰው እነዚያ ገነትን ይገባሉ፡፡ በተምር ፍሬ ላይ ያለችን ነጥብ ያክል እንኳ አይበደሉም፡፡} [አን-ኒሳእ: 124]
አላህ ሺርክ ሥራን እንደሚያበላሽ ገለፀ። ልክ አላህ እንዲህ እንዳለን፦
﴿وَلَقَدۡ أُوحِيَ إِلَيۡكَ وَإِلَى ٱلَّذِينَ مِن قَبۡلِكَ لَئِنۡ أَشۡرَكۡتَ لَيَحۡبَطَنَّ عَمَلُكَ وَلَتَكُونَنَّ مِنَ ٱلۡخَٰسِرِينَ 65﴾
{ብታጋራ ሥራህ በእርግጥ ይታበሳል፡፡ በእርግጥም ከከሓዲዎቹ ትኾናለህ ማለት ወደ አንተም ወደእነዚያም ካንተ በፊት ወደነበሩት በእርግጥ ተወርዷል፡፡} [አዝዙመር : 65]
የኢማን ማዕዘናት ስድስት ናቸው: በአላህ፣ በመላዕክቶች፣ በመጻሕፍቱ፣ በመልዕክተኞቹ፣ በመጨረሻው ቀን፣ እንዲሁም በክፉም በደጉም የአላህ ቀደር ማመን ነው።
1) በላቀው አሏህ ማመን ሶስት ነገሮችን ያካትታል:
1 - በጌትነቱ ማመን:
ይህም መፍጠር፣ ሲሳይን መለገስ፣ ህይወትን መስጠትና መግደል በመሰሉ ድርጊቶቹ አላህን መነጠል ማለት ነው። ከአላህ በቀር ፈጣሪ የለም፤ ከአላህም ውጪ ሲሳይ ሰጪ የለም፤ ከአላህ በቀር ህይወትን ሰጪም ሆነ ህይወትን የሚነፍግ የለም፤ ጥራትና ልዕልና ይገባውና ከርሱ በቀርም በፍጥረተ ዓለሙ አስተናባሪ የለም።
የሚናገረውን የማያምንበት ኩራተኛ ካልሆነ በቀር ከፍጡራን መካከል የአላህን ጌታንት ያወገዘ አይታወቅም። ፊርዓውን ለህዝቦቹ እንዲህ ያለ ጊዜ እንደተከሰተው:
﴿...أَنَا رَبُّكُمُ الْأَعْلَى﴾
{ «እኔ ታላቁ ጌታችሁ ነኝ፡፡»} [አን-ናዚዓት: 24] ነገር ግን ይህን የተናገረው አምኖበት አልነበረም። አላህ ሙሳ (ዓለይሂ ሰላም) የተናገረውን እንዲህ በማለት ተርኮልናል:
﴿قَالَ لَقَدۡ عَلِمۡتَ مَآ أَنزَلَ هَٰٓؤُلَآءِ إِلَّا رَبُّ ٱلسَّمَٰوَٰتِ وَٱلۡأَرۡضِ بَصَآئِرَ وَإِنِّي لَأَظُنُّكَ يَٰفِرۡعَوۡنُ مَثۡبُورٗا 102﴾
{(ሙሳም) «እነዚህን (ተዓምራቶች) መገሰጫዎች ሲኾኑ የሰማያትና የምድር ጌታ እንጂ ሌላ እንዳላወረዳቸው በእርግጥ ዐውቀሃል፡፡ እኔም ፈርዖን ሆይ! የምትጠፋ መኾንህን በእርግጥ እጠረጥርሃለሁ» አለው፡፡} [አልኢስራእ:102] የላቀው አላህ እንዲህ ብሏል:
﴿وَجَحَدُوا بِهَا وَاسْتَيْقَنَتْهَا أَنْفُسُهُمْ ظُلْمًا وَعُلُوًّا... ﴾
{ነፍሶቻቸው ያረጋገጧት ሲሆኑ ለበደልና ለኩራት በእርሷ ካዱ።} [አንነምል፡ 14]
ለእነዚህ ፍጡራን ፈጣሪ ሊኖራቸው የግድ ነው። ምክንያቱም ራሳቸውን በራሳቸው ወደ ሕልውና ማምጣት በፍፁም የማይሆን ነገር ነው፤ የትኛውም ነገር ራሱን መፍጠርም ሆነ በአጋጣሚ የሚሆን ነገርም የለም፤ ምክንያቱም ማንኛውም ክስተት አስከሳች ያስፈልገዋልና። ከዚህም በላይ ፍፁም ስርአቱ፣ የተቀናጀ ውህደቱ፣ ትስስሩና ጥምረቱ ይህ ፍጥረተ አለም በአጋጣሚ ወደ ሕልውና ሊመጣ እንደማይችል ግልጽ ማሳያ ነው። ስለዚህ ለነሱ ፈጣሪ ሊኖር ግድ ነው ማለት ነው፤ ያ ፈጣሪም የዓለማቱ ጌታ አላህ ነው። የላቀው አላህ እንዲህ ብሏል፡
﴿أَمۡ خُلِقُواْ مِنۡ غَيۡرِ شَيۡءٍ أَمۡ هُمُ ٱلۡخَٰلِقُونَ 35 أَمۡ خَلَقُواْ ٱلسَّمَٰوَٰتِ وَٱلۡأَرۡضَۚ بَل لَّا يُوقِنُونَ 36﴾
{ወይስ ያለ አንዳች (ፈጣሪ) ተፈጠሩን? ወይስ እነርሱ ፈጣሪዎች ናቸውን? (35)
ወይስ ሰማያትንና ምድርን ፈጠሩን? አይደለም አያረጋግጡም፡፡ (36)} [አጥ‐ጡር: 35 - 36]
ሙሽሪኮች በአምልኮ ላይ ከማጋራታቸውም ጋር በአሏህ ብቸኛ ጌትነት ያምኑ ነበር። ይህ ግን እስልምና ውስጥ አላስገባቸውም። ነቢዩ ﷺ ግን ተዋጓቸው፣ ደማቸውን እንዲሁም ገንዘቦቻቸውንም ፍቁድ አደረጉ። ይህ ሁሉ የሆነው በአምልኮ ስላጋሩ ነው። ከአላህ ጋር ጣዖታትን፣ ድንጋዮችን፣ መልአክትንና ሌሎችንም አመለኩ።
2 - በተመላኪነቱ ማመን:
በተመላኪነቱ ማመን ማለት: እውነተኛና አጋር የሌለው ብቸኛ አምላክ መሆኑን ማመን ማለት ነው። (አምላክ) ማለት በውዴታ፣ በማላቅና በመተናነስ ተመላኪ የሆነ ማለት ነው።
የላቀው አላህ እንዲህ ብሏል፡
﴿وَإِلَٰهُكُمۡ إِلَٰهٞ وَٰحِدٞۖ لَّآ إِلَٰهَ إِلَّا هُوَ ٱلرَّحۡمَٰنُ ٱلرَّحِيمُ 163﴾
{አምላካችሁም አንድ አምላክ ብቻ ነው፤ ከርሱ በቀር ሌላ አምላክ የለም፡፡ (እርሱ) እጅግ በጣም ርኅሩህ አዛኝ ነው፡፡} [አል-በቀራህ፡ 163]
በአምልኮው ከአላህ ጋር የሚጋራ ሌላ አምላክን ያደረገ ሰው ሁሉ አምልኮው ውድቅ ነው። የላቀው አላህ እንዲህ ብሏል፡
﴿ذَٰلِكَ بِأَنَّ ٱللَّهَ هُوَ ٱلۡحَقُّ وَأَنَّ مَا يَدۡعُونَ مِن دُونِهِۦ هُوَ ٱلۡبَٰطِلُ وَأَنَّ ٱللَّهَ هُوَ ٱلۡعَلِيُّ ٱلۡكَبِيرُ 62﴾
{ይህ አላህ እርሱ እውነት በመሆኑ ከእርሱም ሌላ የሚግገዙት ነገር እርሱ ፍጹም ውሸት በመሆኑ አላህም እርሱ የሁሉ በላይ ታላቅ በመኾኑ ነው፡፡} [አል'ሐጅ፡ 62]
ለዚህም ሲባል ሁሉም መልዕክተኞች ከኑሕ እስከ ሙሐመድ ﷺ የነበሩት ሁሉ ህዝቦቻቸውን ሁሉንም አማልክት ትተው አላህን በአምልኮ ወደ መነጠል ይጣሩ ነበር። የአጋርያን ከአላህ ጋር ሌላ የሚያመልኳቸውን አማልክት መያዝ፣ እነርሱንም እርዳታ መጠየቅ፣ እገዛንም ከነርሱ መጠየቅን አላህ ውድቅ አድርጎታል። ይህም በሁለት አመክኗዊ ማስረጃዎች ነው።
አንደኛ፡- እነዚያ የያዟቸው አማልክት ምንም አይነት መለኮታዊ ባህሪ የሌላቸው ናቸው፤ እነሱም የተፈጠሩ እና ምንም ነገር መፍጠር የማይችሉም ናቸው፤ ለሚያመልኳቸው ሰዎች እንኳ ምንም አይነት ጥቅም ማምጣትም ሆነ ጉዳትን ማስወገድ የማይችሉም ናቸው፤ እነሱ በሰዎች ሕይወትም ይሁን ሞት ላይ አልያም በመቀስቀስ ላይ ምንም ማድረግ የማይችሉ ናቸው። አላህ እንዲህ እንዳለን:
﴿وَٱتَّخَذُواْ مِن دُونِهِۦٓ ءَالِهَةٗ لَّا يَخۡلُقُونَ شَيۡـٔٗا وَهُمۡ يُخۡلَقُونَ وَلَا يَمۡلِكُونَ لِأَنفُسِهِمۡ ضَرّٗا وَلَا نَفۡعٗا وَلَا يَمۡلِكُونَ مَوۡتٗا وَلَا حَيَوٰةٗ وَلَا نُشُورٗا 3﴾
{(ከሓዲዎች) ከእርሱም ሌላ ምንንም የማይፈጥሩን፣ እነርሱም የሚፈጠሩን፣ ለነፍሶቻቸውም ጉዳትን ለመከላከል ጥቅምንም ለማምጣት የማይችሉን ሞትንና ሕይወትንም መቀስቀስንም የማይችሉን፣ አማልክት ያዙ፡፡} [አል-ፉርቃን: 3]
ሁለተኛ፡- እነዚያ ሙሽሪኮች አላህ ብቻውን ፈጣሪና አስተናባሪ መሆኑን ያረጋግጣሉ። ይህም በጌትነቱ ብቸኝነት እንዳመኑ ሁሉ በአምላክነቱ ብቸኝነትም ሊያምኑ ዘንድ የሚያስፈርድ ነው። አላህ እንዲህ እንዳለን:
﴿قُل لِّمَنِ ٱلۡأَرۡضُ وَمَن فِيهَآ إِن كُنتُمۡ تَعۡلَمُونَ 84 سَيَقُولُونَ لِلَّهِۚ قُلۡ أَفَلَا تَذَكَّرُونَ 85 قُلۡ مَن رَّبُّ ٱلسَّمَٰوَٰتِ ٱلسَّبۡعِ وَرَبُّ ٱلۡعَرۡشِ ٱلۡعَظِيمِ 86 سَيَقُولُونَ لِلَّهِۚ قُلۡ أَفَلَا تَتَّقُونَ 87 قُلْ مَنْ بِيَدِهِ مَلَكُوتُ كُلِّ شَيْءٍ وَهُوَ يُجِيرُ وَلَا يُجَارُ عَلَيْهِ إِنْ كُنْتُمْ تَعْلَمُونَ 88 سَيَقُولُونَ لِلَّهِ قُلْ فَأَنَّى تُسْحَرُونَ 89﴾
{«ምድርና በውስጥዋ ያለው ሁሉ የማን ነው የምታውቁ ብትኾኑ (ንገሩኝ)» በላቸው፡፡ (84)
«በእርግጥ የአላህ ነው» ይሉሃል፡፡ «ታዲያ አትገሰጹምን» በላቸው፡፡ (85)
«የሰባቱ ሰማያት ጌታና የታላቁ ዐርሽ ጌታ ማን ነው» በላቸው፡፡ (86)
«በእርግጥ አላህ ነው» ይሉሃል፡፡ «እንግዲያ አትፈሩትምን» በላቸው፡፡ (87)
«የነገሩ ሁሉ ግዛት በእጁ የኾነ እርሱ የሚጠብቅ በእርሱ ላይ የማይጠበቅ ማን ነው የምታውቁ እንደኾናችሁ (መልሱልኝ)» በላቸው፡፡ (88)
«በእርግጥ አላህ ነው» ይሉሃል፡፡ «ታዲያ እንዴት ትታለላላችሁ» በላቸው፡፡ (89)} [አል-ሙእሚኑን: 84 - 89] በአላህ ጌትነት እስካረጋገጡ ድረስ በአምልኮም አላህን ብቻ መነጠልና ከርሱም ጋር በአምልኮ አንድንም አለማጋራት ግድ ይላቸዋል።
3 - በስሞቹና በባህሪያቱ ማመን:
ማለትም: አላህ በመጽሐፉ ስለ ነፍሱ ያፀደቀውን፣ ወይም የአላህ መልክተኛ ﷺ በሐዲሣቸው ለአላህ ያፀደቁትን ስሞችና ባህሪያት ለአላህ ተገቢ በሆነ መልኩ ያለምንም ማጣመም፣ ትርጉም አልባ ሳያደርጉ፣ አኳኋኑን ሳይገልፁና ሳያመሳስሉት ማፅደቅ ማለት ነው። የላቀው አላህ እንዲህ ብሏል፡
﴿وَلِلَّهِ ٱلۡأَسۡمَآءُ ٱلۡحُسۡنَىٰ فَٱدۡعُوهُ بِهَاۖ وَذَرُواْ ٱلَّذِينَ يُلۡحِدُونَ فِيٓ أَسۡمَٰٓئِهِۦۚ سَيُجۡزَوۡنَ مَا كَانُواْ يَعۡمَلُونَ 180﴾
{ለአላህም መልካም ስሞች አሉት፡፡ (ስትጸልዩ) በእርሷም ጥሩት፡፡ እነዚያንም ስሞቹን የሚያጣምሙትን ተውዋቸው፡፡ ይሠሩት የነበሩትን ነገር በእርግጥ ይምመነዳሉ፡፡} [አልአዕራፍ: 180] የላቀው አላህ እንዲህ ብሏል:
﴿...لَيۡسَ كَمِثۡلِهِۦ شَيۡءٞۖ وَهُوَ ٱلسَّمِيعُ ٱلۡبَصِيرُ﴾
{...የሚመስለው ምንም ነገር የለም። እርሱም ሰሚው ተመልካቹ ነው።} [አሽ'ሹራ፡ 11]
በአላህ የማጋራት (የሺርክ) ሶስቱ ክፍሎች:
1 - ሺርኩ አክበር (ትልቁ ማጋራት)
2 - ሺርኩ አስገር (ትንሹ ማጋራት)
3 - ሺርኩ ኸፍይ (ድብቁ ማጋራት)
1 - ትልቁ ሺርክ
መገለጫው: አላህ በብቸኝነቱ የሚለይባቸው በሆኑ ጉዳዮች ላይ ከርሱ ውጪ ያሉን ከእርሱ ጋር እኩል ማድረግ ነው። የላቀው አላህ እንዲህ እንዳለን:
﴿إِذۡ نُسَوِّيكُم بِرَبِّ ٱلۡعَٰلَمِينَ 98﴾
{(ጣዖቶቹን) በዓለማት ጌታ ባስተካከልናችሁ ጊዜ፡፡} [አሽ-ሹዓራእ፡ 98]
ይህም የሚከተሉትን ያጠቃልላል: አምልኮን ከአላህ ውጪ ላሉ አሳልፎ መስጠት፤ ወይም እንደ ዱዓ፣ እገዛን መማፀን፣ ስለት፣ እርድ እና ከመሳሰሉት የአምልኮ አይነቶች አንዱንም ከአላህ ውጪ ላለ አካል መስጠትን ያጠቃልላል።
ወይም አላህ ሐራም ያደረገውን ሐላል ማድረግ፤ ወይም ሐላል ያደረገውን ሐራም ማድረግ፤ ወይም አላህ የወሰነውን ውድቅ ማድረግ፤ ማለትም በእስልምና ሐራምነቱ በጉልህ የሚታወቅን ሐላል ማድረግ እንደማለት ነው። ዝሙትን ወይም አስካሪ መጠጥን ወይም የወላጆችን መብት ማጓደል ወይም ወለድና የመሳሰሉትን ሐላል ማድረግ ማለት ነው።
ወይም አላህ ሐላል ያደረገውን መልካምና ጥሩ ነገሮችን ሐራም ማድረግ፤ ወይም አላህ ግዴታ ያደረገውን ነገር ውድቅ ማድረግ ነው። ሶላት ወይም ፆም ወይም ዘካ ግዴታ አይደለም ብሎ ማመንን እንደምሳሌ መጥቀስ ይቻላል።
ትልቁ ሺርክ የስራን መበላሸት፣ በዛው ላይ ከሞተም በእሳት ውስጥ መዘውተርን ያስፈርዳል። አላህ እንዲህ እንዳለን:
﴿...وَلَوۡ أَشۡرَكُواْ لَحَبِطَ عَنۡهُم مَّا كَانُواْ يَعۡمَلُونَ﴾
{ባጋሩም ኖሮ ይሰሩት የነበሩት ከነሱ በታበሰ ነበር።} [አልአንዓም፡ 88]
ሸርክን እየፈፀመ የሞተ አላህ አይምረውም፤ ጀነትም በእርሱ ላይ እርም ናት። አላህ እንዲህ እንዳለን:
﴿إِنَّ ٱللَّهَ لَا يَغۡفِرُ أَن يُشۡرَكَ بِهِۦ وَيَغۡفِرُ مَا دُونَ ذَٰلِكَ لِمَن يَشَآءُ...﴾
{አላህ በእርሱ ማጋራትን በፍጹም አይምርም። ከዚህ ሌላ ያለውንም (ኀጢአት) ለሚሻው ሰው ይምራል።} [አንኒሳእ፡ 48] የላቀው አላህ እንዲህ ብሏል:
﴿إِنَّهُۥ مَن يُشۡرِكۡ بِٱللَّهِ فَقَدۡ حَرَّمَ ٱللَّهُ عَلَيۡهِ ٱلۡجَنَّةَ وَمَأۡوَىٰهُ ٱلنَّارُ...﴾
{እነሆ! በአላህ የሚያጋራ ሰው አላህ በርሱ ላይ ገነትን በእርግጥ እርም አደረገ፡፡ መኖሪያውም እሳት ናት፡፡ …} [አልማኢዳህ:72]
2 - ትንሹ ሺርክ
ትንሹ ሺርክ የሚባለው በቁርአን ወይም በሐዲሥ ሺርክ በሚል ስያሜ ቢጠራም የትልቁ ሺርክ ደረጃ ያልደረሰ ነው። ይህም ትንሹ ሺርክ ይባላል። ለምሳሌ ከአላህ ውጪ ባለ አካል መማል፤ በከዕባ፣ በነቢያት፣ በአደራ፣ በእከሌ ህይወትና (እከሌ ይሙት) በመሳሰሉት መማል ከትንሹ ሺርክ ይመደባል። ነቢዩ ﷺ እንዲህ ብለዋል:
«مَنْ حَلَفَ بِغَيرِ اللهِ فَقَدْ كَفَرَ أَو أَشرَكَ».
{"ከአሏህ ውጭ ባለ አካል የማለ በእርግጥም ክዷል ወይም አጋርቷል።"}2
አንዳንዴ በሚምለው ሰው ቀልብ ውስጥ እንደሚኖረው ደረጃ ልክ ትልቁ ሺርክ የሚሆንበትም አጋጣሚ አለ። በነቢዩ ወይም በእከሌ ሸይኽ የሚምለው ሰው ቀልብ ውስጥ እነርሱ ማለት እንደ አላህ ናቸው የሚል እሳቤ ካለ ወይም የሚምልባቸው አካላት ከአላህ ውጪ ይለመናሉ ብሎ ካሰበ ወይም እነርሱ በፍጥረተ ዓለሙ ውስጥ ያስተናብራሉ ካለ ትልቁ ሺርክ ይሆናል። ከአላህ ውጪ የማለው ሰው ይህንን ካላሰበና ስለለመደበት በምላሱ ላይ ስለመጣለት ብቻ ከማለ ግን ትንሹ ሺርክ ይሆናል። አንዳንድ አካባቢዎች ላይ ይህ በስፋት ይስተዋላልና ተውሒድን ለመጠበቅና ለመመከት ይህንን መገንዘብና ከርሱ ማስጠንቀቅ ግድ ይላል።
3 - ድብቁ ሺርክ:
ይህም በቀልቦች ውስጥ የሚገኘው ይዩልኝ ነው። ሰዎች እንዲያዩት የሚቀራ ወይም የሚሰግድ ሰው ወይም ሰዎች እንዲያሞግሱት ተስቢሕ (ሱብሓነላህ) እያለ ዚክር የሚያደርግ ወይም ሶደቃ የሚሰጥ አይነቱ ነው። ይህም ለአላህ ብሎ አጥርቶ የሰራውን ሳይሆን ይዩልኝ የታከለበትን ስራ ያበላሻል።
ነቢዩ ﷺ እንዲህ ብለዋል፦
«الشِّرْكُ فِي هَذِهِ الْأُمَّةِ أَخْفَى مِنْ دَبِيبِ النَّمْلَةِ السَّودَاءِ عَلَى الصَّفَاةِ السَّودَاءِ فِي ظُلْمَةِ اللَّيْلِ، وَكَفَّارَتُهُ أَنْ يَقُولَ: "اللَّهُمَّ إِنِّي أَعُوذُ بِكَ أَنْ أُشْرِكَ بِكَ شَيْئًا وَأَنَا أَعْلَمُ، وَأَسْتَغْفِرُكَ مِنَ الذَّنْبِ الَّذِي لَا أَعْلَمُ».
«ሺርክ በዚህ ኡመት ውስጥ ጥቁር ጉንዳን በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ በጥቁር ለስላሳ ድንጋይ ላይ ስትሄድ ከሚኖራት የኮቴ ድምፅ የበለጠ ድብቅ ነው። ማስማሪያውም እንዲህ ማለቱ ነው: "አላሁመ ኢኒ አዑዙ ቢከ አን ኡሽሪከ ቢከ ሸይአን ወአነ አዕለም፤ ወአስተጝፊሩከ ሚነዝዘንቢ አለዚ ላ አዕለም።"» ትርጉሙም "አላህ ሆይ! እያወቅኩኝ ባንተ ላይ አንዳችን ከማጋራት ባንተ እጠበቃለሁ፤ ለማላውቀው ወንጀል ደግሞ ምህረትህን እጠይቅሀለሁ።"3
የክህደት ዓይነቶች:
የመጀመሪያው አይነት: ትልቁ ክህደት:
ይህም እሳት ውስጥ ለመዘውተር የሚያስፈርደው የክህደት አይነት ነው። እሱም አምስት አይነት ነው:
1 - የማስተባበል ክህደት:
ይህ መልክተኞች ውሸታም ናቸው ብሎ እንደማመን አይነቱ ነው። ይህ የክህደት አይነት ከከሃዲያን መካከል በጥቂቶቹ የሚስተዋል ነው። ምክንያቱም አላህ መልክተኞቹን በግልፅ ማስረጃዎች አግዟልና። የእነዚህ አስተባባዮች ሁኔታ አላህ እንዲህ በማለት እንደገለፃቸው ነው:
﴿وَجَحَدُوا بِهَا وَاسْتَيْقَنَتْهَا أَنْفُسُهُمْ ظُلْمًا وَعُلُوًّا...﴾
{ነፍሶቻቸው ያረጋገጧት ሲሆኑ ለበደልና ለኩራት በእርሷ ካዱ።} [አንነሕል:14]
2 - የእምቢተኝነትና የኩራት ክህደት:
የዚህም ምሳሌ የኢብሊስ ክህደት ነው። ኢብሊስ የአላህን ትእዛዝ በእምቢተኝነትና በኩራት አልታዘዝ እንጅ የአላህን ትእዛዝ አልካደምም አላወገዘምም። አላህ እንዲህ ብሏል፡
﴿وَإِذۡ قُلۡنَا لِلۡمَلَٰٓئِكَةِ ٱسۡجُدُواْ لِأٓدَمَ فَسَجَدُوٓاْ إِلَّآ إِبۡلِيسَ أَبَىٰ وَٱسۡتَكۡبَرَ وَكَانَ مِنَ ٱلۡكَٰفِرِينَ 34﴾
{ለመላእክትም «ለአደም ስገዱ» ባልን ጊዜ (አስታውስ) ፡፡ ሁሉም ወዲያውኑ ሰገዱ፤ ኢብሊስ (ዲያብሎስ) ብቻ ሲቀር እምቢ አለ፤ ኮራም ከከሓዲዎቹም ሆነ፡፡} [አልበቀራህ፡ 34]
3 - የመዞር (ጀርባ የመስጠት) ክህደት:
ይህም ማለት በጆሮውና በቀልቡ እውነትን ከመከተል ጀርባ መስጠት ነው። እውነታን ዞር ብሎም አያይም ቦታም አይሰጥም። የላቀው አላህ እንዲህ ብሏል፡
﴿وَمَنۡ أَظۡلَمُ مِمَّن ذُكِّرَ بِـَٔايَٰتِ رَبِّهِۦ ثُمَّ أَعۡرَضَ عَنۡهَآۚ إِنَّا مِنَ ٱلۡمُجۡرِمِينَ مُنتَقِمُونَ 22﴾
{በጌታውም አንቀጾች ከተገሰጸና ከዚያም ከተዋት ሰው ይበልጥ በደለኛ ማነው? (የለም)፤ እኛ ከተንኮለኞቹ ተበቃዮች ነን፡፡} [አስሰጅዳ: 22]
በተወሰነ መልኩ ችላ ማለት ግን ወንጀል እንጂ ክህደት አይሆንም። ለምሳሌ የፆም ወይም የሐጅ ወይም የመሳሰሉት የዲን ግዴታዎቹን ከመማር ችላ ያለ ሰው ወንጀል ይሆንበታል እንጂ ክህደት ውስጥ አይወድቅም።
4 - የጥርጣሬ ክህደት:
ይህም ማወላወል ማለት ነው። በሐቅ ላይ ልቡ አትቆርጥም። ይልቁንም ይጠራጠራል። አላህ እንዲህ እንዳለን:
﴿وَدَخَلَ جَنَّتَهُ وَهُوَ ظَالِمٌ لِنَفْسِهِ قَالَ مَا أَظُنُّ أَنْ تَبِيدَ هَذِهِ أَبَدًا 35 وَمَا أَظُنُّ السَّاعَةَ قَائِمَةً وَلَئِنْ رُدِدْتُ إِلَى رَبِّي لَأَجِدَنَّ خَيْرًا مِنْهَا مُنْقَلَبًا 36﴾
{እርሱም ነፍሱን በዳይ ሆኖ ወደ አትክልቱ ገባ፡፡ «ይህች ዘለዓለም ትጠፋለች ብዬ አልጠረጥርም» አለ፡፡ (35)
«ሰዓቲቱንም ቋሚ (ኋኝ) ናት ብዬ አልጠረጥርም፡፡ (እንደምትለው) ወደ ጌታዬም ብመለስ ከእርሷ የበለጠን መመለሻ በእርግጥ አገኛለሁ» (አለው)፡፡ 36} [አል‐ከህፍ: 35 - 36]
5 - የንፍቅና ክህደት:
ይህም ማለት በምላሱ ኢማንን ይፋ እያደረገ በልቡ ማስተባበልን መደበቁ ነው። የላቀው አላህ እንዲህ ብሏል፡
﴿وَمِنَ ٱلنَّاسِ مَن يَقُولُ ءَامَنَّا بِٱللَّهِ وَبِٱلۡيَوۡمِ ٱلۡأٓخِرِ وَمَا هُم بِمُؤۡمِنِينَ 8﴾
{ከሰዎችም «በአላህና በመጨረሻው ቀን አምነናል» የሚሉ አልሉ፤ እነርሱም አማኞች አይደሉም፡፡} [አልበቀራህ፡ 8]
እነዚህ ከእስልምና የሚያስወጣው የትልቁ ክህደት አይነቶች ናቸው።
ሁለተኛው አይነት: ትንሹ ክህደት
ይህ አይነቱ ክህደት በእሳት ውስጥ ዘላለም መዘውተርን አያስፈርድም፤ ይህም በቁርአንና በሐዲሥ ትልቁን ክህደት በሚያሳይ ቋንቋዊ አገባብ ሳይሆን በጥቅሉ ክህደት የሚል ስያሜ የመጣበት ወንጀል ነው። ለዚህም በርካታ ምሳሌዎች ያሉት ሲሆን ለናሙና ያህል: በአቡ ሁረይራ አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላቸውና ሐዲሥ የአላህ መልዕክተኛ ﷺ እንዲህ ብለዋል፦
«اثْنَتَانِ فِي النَّاسِ هُمَا بِهِمْ كُفْرٌ: الطَّعْنُ فِي النَّسَبِ، وَالنِّيَاحَةُ عَلَى المَيِّتِ».
«በሰዎች ውስጥ ሁለት ነገሮች አሉ፤ እነርሱም ክህደት ናቸው። በዘር መተቸትና በሞተ ላይ ሙሾ ማውረድ ናቸው።»4
2 - በመላእክት ማመን
እነርሱ የሩቅ (የማይታየው) ዓለም ላይ ያሉ፤ አላህ ከብርሃን የፈጠራቸው ናቸው። እነርሱ የአላህ ባሪያዎች ናቸው። የጌትነትም ሆነ የተመላኪነት አንዳችም መለዮ የላቸውም። አላህ ያዘዛቸውንም አያምፁም። የሚፈፅሙትም የታዘዙትን ነው። ቁጥራቸው እጅግ በርካታ ስለሆነ ከአላህ በቀር ማንም ትክክለኛ ብዛታቸውን አያውቀውም።
በመላእክት ማመን አራት ነገሮችን ያካትታል:
1 - በመኖራቸው ማመን:
2 - ከነርሱ መካከል ስሙን ባወቅነው ማመን። ለምሳሌ ጂብሪል፣ ሚካኢል፣ ኢስራፊልና ሌሎችም ይጠቀሳሉ። ስማቸውን ያላወቅናቸውን ደሞ በጥቅሉ እናምናለን።
3 - በቁርአንና በሐዲሥ በመጣው መልኩ ባወቅነው ባህሪያቸውም ማመን። ለምሳሌ የጂብሪል ባህሪ: ነቢዩ ﷺ አላህ በፈጠረው ባህሪ ላይ ሆኖ እንዳዩትና አድማሱን የሚጋርድ ስድስት መቶ ክንፍ አንዳለው ተናግረዋል።
4 - ተግባራቸውን ባወቅነው ማመን: ለአላህ አጥሪዎች መሆናቸው፣ ያለምንም ማቋረጥና መሰላቸት ቀን ከሌት አላህን የሚገዙ መሆናቸውን ማመን ማለት ነው።
ለምሳሌ: ጂብሪል: በወሕይ ጉዳይ ላይ ታማኙ አምባሳደር ነው።
ኢስራፊል: ቀንዱን የመንፋት ኃላፊነት የተሰጠው ነው።
መለከልመውት: ነፍሶች በሚሞቱ ወቅት ነፍስን የመንጠቅ ኃላፊነት የተሰጠው ነው።
ማሊክ: የእሳት ዘበኛ ነው። ሪድዋን: የጀነት ዘበኛ ነው። ሌሎቹንም እንዲሁ ባላቸው የስራ ድርሻ ማመን ግዴታ ነው።
3 - በመጽሐፍት ማመን:
መፃህፍት ስንል የሚፈለገው: አላህ ወደ መልእክተኞቹ ያወረዳቸው መለኮታዊ መጻሕፍቶችን ማለታችን ነው። ለሰው ልጆች መመሪያና እዝነት ሁኖ የሁለቱን ዓለማት ደስታ ይጎናፀፉ ዘንድ የወረደ ነው።
በመጻሕፍቱ ማመን አራት ነገሮችን ያጠቃልላል፡-
1 - በእውነት ከላቀው አላህ ዘንድ የወረዱ መሆናቸውን ማመን፤
2 - ስሞቻቸው ያወቅናቸውን መጽሐፎች በሚታወቀው ስማቸው ማመን፤ ለምሳሌ: በነቢዩ ሙሐመድ ﷺ ላይ የወረደው ቁርኣን፤ በሙሳ ዓለይሂ ሰላም ላይ የወረደው ተውራት፣ በዒሳ (ዐለይሂ-ሰላም) ላይ የወረደው ኢንጂል፣ በዳውድ ዓለይሂ ሰላም ላይ በወረደው ዘቡር ማመን ነው።
ስማቸውን ያላወቅናቸውን ደሞ እንዲሁ በጥቅሉ እናምንባቸዋለን።
3 - በውስጡ በተካተቱት መረጃዎች ማመን፤ ልክ በቁርኣን ውስጥ የተገለጸ መረጃ ማመን እና በቀደሙት ቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥም ቢሆን ያልተቀየረ ወይም ያልተዛባ መረጃ ካለ ማመን ይጠበቅብናል።
4 - ከነሱ ጀርባ ያለውን ጥበብ ተረዳንም አልተረዳን በውስጡ ያሉት ፍርዶች እስካልተሻሩ ድረስ ወዶ መቀበል እና እጅ መስጠት ይጠበቅብናል። የቀደሙት መለኮታዊ መጻሕፍት በሙሉ በላቀው ቁርኣን ተሽረዋል። በቀደሙት መጽሐፍት ውስጥ ከተቀመጡት ፍርዶች መካከል ትክክለኛ እና በቁርኣን ተቀባይነት ያላቸው ከሆኑት በስተቀር ማናቸውንም አንሰራባቸውም።
4) በመልዕክተኞች (የአላህ ሰላም ይስፈንባቸውና) ማመን:
መልዕክተኞች ማለት: አላህ ሱብሓነሁ ወተዓላ መመርያውን አውርዶላቸው ለሰዎች እንዲያደርሱ ያዘዛቸው ናቸው። የመጀመሪያው ኑሕ (ዓለይሂ ሰላም) ሲሆን የመጨረሻው ደግሞ ሙሐመድ ﷺ ናቸው። እነርሱ የሰው ዘር የሆኑ ፍጡራን ናቸው። የጌትነትም ሆነ የተመላኪነት አንዳችም መለዮ የላቸውም።
በመልዕክተኞች ማመን የሚከተሉትን ያጠቃልላል:
1 - መልእክታቸው በእውነት ከአላህ ዘንድ የመጣ መሆኑን ማመን፤ ስለሆነም በአንዱም መልእክተኛ ተልዕኮ የሚክድ ሰው በሁላቸውም መልዕክተኝነት ክዷል።
2- እንደ ሙሐመድ፣ ኢብራሂም፣ ሙሳ፣ ዒሳ እና ኑሕ ያሉት -የአላህ ሶለዋትና ሰላም ይስፈንባቸውና - መሰል ስሞቻቸውን ባወቅናቸው በስሞቻቸው ለይተን ማመን ይጠበቅብናል። ከላይ የተጠቀሱት መልክተኞች ኡሉል ዓዝም (የቆራጥነት ባለቤት) ተብለው ይጠራሉ።
ከነርሱ መካከል ስማቸውን የማናውቃቸውን ደግሞ ስለ እነርሱ በተነገረን ልክ እንዲሁ በጥቅሉ እናምናለን። የላቀው አላህ እንዲህ ብሏል፡
﴿وَلَقَدۡ أَرۡسَلۡنَا رُسُلٗا مِّن قَبۡلِكَ مِنۡهُم مَّن قَصَصۡنَا عَلَيۡكَ وَمِنۡهُم مَّن لَّمۡ نَقۡصُصۡ عَلَيۡكَ...﴾
{ካንተ በፊትም መልክተኞችን በእርግጥ ልከናል፡፡ ከእነርሱ ባንተ ላይ የተረክንልህ አልለ፡፡ ከእነርሱም ባንተ ላይ ያልተረክነው አልለ፡፡} [ጋፊር፡ 78]
3 - በትክክል ከእነርሱ (ዓለይሂም አስሰላም) እንደመጣ የተረጋገጠን መረጃ አምኖ መቀበል።
4 - ከነርሱ መካከል ወደኛ በተላከልን መመርያ መስራት፤ ከመካከላቸው ወደ እኛ የተላከልን የመጨረሻው ነብይ ሙሐመድ ﷺ ናቸው።
5 - በመጨረሻው ቀን ማመን
የመጨረሻው ቀን የሚባለው፡ ሰዎች ለሂሳብና ለምንዳ የሚቀሰቀሱበት የትንሳኤ ቀን ነው። እንደዛ ተብሎ የተሰየመውም ከዛ በኋላ ምንም ቀን ስለማይኖር ነው። የጀነት ሰዎች ዘላለማቸውን በስፍራቸው ይሰፍራሉ፤ የእሳት ጓዶችም ዘላለማቸውን እንዲሁ በጀሀነም ይሰፍራሉ።
በመጨረሻው ቀን ማመን ሶስት ነገሮችን ያጠቃልላል:
ሀ) ከሞት በመቀስቀስ ማመን:
ማለትም: ለሁለተኛ ጊዜ ጥሩንባው ሲነፋ ሙታን እንደገና ወደ ሕይወት እንደሚመለሱ በትንሣኤ ማመን ነው። ከዚያም ሰዎች ራቁታቸውን ያልተሸፈኑ ሆነው፣ ባዶ እግራቸውን ያልተጫሙ ሆነው እና ያልተገረዙ ሆነው በዓለማቱ ጌታ ፊት ይቆማሉ። የላቀው አላህ እንዲህ ብሏል፡
﴿كَمَا بَدَأْنَا أَوَّلَ خَلْقٍ نُعِيدُهُ وَعْدًا عَلَيْنَا إِنَّا كُنَّا فَاعِلِينَ 104﴾
{የመጀመሪያን ፍጥረት እንደ ጀመርን እንመልሰዋለን፡፡ (መፈጸሙ) በእኛ ላይ የሆነን ቀጠሮ ቀጠርን፡፡ እኛ (የቀጠርነውን) ሠሪዎች ነን።} [አልአንቢያእ: 104]
ለ) በሒሳብና ምንዳ ማመን:
ይህም ማለት: ሁሉም ሰው ለሰራው ስራ የሚተሳሰብ ይሆናል፤ ይመነዳበታልም። የላቀው አላህ እንዲህ ብሏል:
﴿إِنَّ إِلَيۡنَآ إِيَابَهُمۡ 25 ثُمَّ إِنَّ عَلَيۡنَا حِسَابَهُم 26﴾
{መመለሻቸው ወደእኛ ብቻ ነው፡፡ (25)
ከዚያም ምርመራቸው በእኛ ላይ ብቻ ነው፡፡} [አል-ጋሺያህ: 25-26]
መ) በጀነትና በእሳት ማመን:
እነሱም የፍጡር ዘላለማዊ መኖሪያ ናቸው። ጀነት አላህንና መልክተኛውን ﷺ ታዛዥ ለሆኑት እንዲሁም ለአማኞችና እርሱን ለፈሩት አላህ ያዘጋጃት የድሎት አገር ናት። ጀነት ውስጥ አይን ያላየውን፣ ጆሮ ያልሰማውን፣ በሰው ልብ ውስጥ ውል ብሎ የማያውቅ የሆነ ፀጋ ያለባት ነች።
እሳት ደግሞ: የቅጣት አገር ናት። አላህ በእርሱ ለካዱ ከሃዲዎች እና መልእክተኞቹንም ላመፁ ያዘጋጃት ናት። በአዕምሮ ሊታሰብ የማይችልን የቅጣት እና የስቃይ አይነትን ሁሉ ይዛለች።
6 - በቀደር ክፉውም ሆነ ደጉን ማመን፡
በቀደር ማመን ሲባል የሚፈለገው: አሏህ ቀድሞ አዋቂነቱ እና ጥበቡ በሚፈርደው መሰረት ለወደፊት የሚሆነውን አስቀድሞ የሚያስቀምጠው ውሳኔ ነው።
በቀደር ማመን አራት ነገሮችን ያጠቃልላል፡
1 - ዕውቀት: ማለትም በአላህ እውቀት ማመን ማለት ነው። አላህ የነበረውንም፣ የሚሆነውንም፣ እንዴት እንደሚሆንም በጥቅልም ይሁን በዝርዝር በፊትም ዘላለምም እንደሚያውቅ ማመን ነው። አላህ ያልተከሰተንም ነገር ቢሆን ቢከሰት ኖሮ እንዴት ይሆን እንደነበር ያውቃል። ጥራት የተገባው አላህ እንዲህ እንዳለን:
﴿وَلَوۡ رُدُّواْ لَعَادُواْ لِمَا نُهُواْ عَنۡهُ ...﴾
{(ወደ ምድር አለም) በተመለሱም ኖሮ ከእርሱ ወደ ተከለከሉት ነገር በተመለሱ ነበር።…} [አልአንዓም፡ 28]
2 - መጻፍ: ይህም አላህ የሁሉን ነገር ውሳኔዎች እስከ እለተ ትንሳኤ ድረስ ጽፎታል። የላቀው አላህ እንዲህ ብሏል፦
﴿أَلَمۡ تَعۡلَمۡ أَنَّ ٱللَّهَ يَعۡلَمُ مَا فِي ٱلسَّمَآءِ وَٱلۡأَرۡضِۚ إِنَّ ذَٰلِكَ فِي كِتَٰبٍۚ إِنَّ ذَٰلِكَ عَلَى ٱللَّهِ يَسِيرٞ 70﴾
{አላህ በሰማይና በምድር ውስጥ ያለን ሁሉ በእርግጥ የሚያውቅ መሆኑን አታውቅምን ይህ በመጽሐፍ ውስጥ (የተመዘገበ) ነው፡፡ ይህ በአላህ ላይ ገር ነው፡፡} [አልሐጅ: 70]
3 - (የአላህ) መሻት: ይህም ማለት በዚህ ፍጥረተ ዓለም ውስጥ አላህ የፈለገው ካልሆነ በቀር ምንም የማይከሰት መሆኑ ነው። የላቀው አላህ እንዲህ ብሏል፡
﴿وَرَبُّكَ يَخۡلُقُ مَا يَشَآءُ وَيَخۡتَارُ ...﴾
{ጌታህም የሚሻውን ይፈጥራል፤ ይመርጣልም።} [አል-ቀሶስ፡ 68] የሰው ልጅ የራሱ ፍላጎትና መሻት አለው። የሰው ልጅ መሻት ግን ከአላህ መሻት ክልል አይወጣም።
﴿وَمَا تَشَآءُونَ إِلَّآ أَن يَشَآءَ ٱللَّهُ رَبُّ ٱلۡعَٰلَمِينَ 29﴾
{የዓለማት ጌታ አላህ ካልሻም አትሹም።}
[አትተክዊር: 29]
4 - መፍጠር: ይህም ማለት አላህ ፍጥረታትን፣ ስራዎቻቸውን፣ ድርጊቶቻቸውን መልካሙንም መጥፎውንም ሁሉ ፈጥሯል ብሎ ማመን ነው። የላቀው አላህ እንዲህ ብሏል፡
﴿ٱللَّهُ خَٰلِقُ كُلِّ شَيۡءٖۖ وَهُوَ عَلَىٰ كُلِّ شَيۡءٖ وَكِيلٞ 62﴾
{አላህ የነገሩ ሁሉ ፈጣሪ ነው፡፡ እርሱም በነገሩ ሁሉ ላይ አስተናባሪ ነው፡፡} [አዝ-ዙመር፡ 62]
እነዚህን አራት የቀደር ደረጃዎች በዚህ ስንኝ ተሰባስበዋል:
የረዳታችን አላህ ዕውቀትና መፃፍ ብሎም መሻቱን*** መፍጠር ይሀውም ማስገኘቱና መከወኑን
ክፍል ሶስት: ኢሕሳን (በጎነት)
ኢሕሳን (በጎነት) : አንድ ማዕዘን ነው ያለው። እሱም እንደምታየው ሆነህ አላህን መገዛትህ ነው። አንተ ባታየው እንኳ እርሱ ያይሃልና።
ማለትም: ሰውዬው አላህን ሲያመልክ አላህ ፊት እንደቆመ እያሰበ መፈፀሙ ነው። ይህም ለአላህ የተሟላ ፍራቻንና መመለስን ያስፈርዳል። የመልክተኛውን ﷺ ሱና በገጠመ መልኩ አምልኮ መፈፀምንም ያስፈርዳል።
ኢሕሳን ሁለት ደረጃዎች አሉት: በጎ አድራጊዎችም ሁለት የሚበላለጡ ደረጃዎች አላቸው:
የመጀመሪያውና የላቀው ደረጃ: የእይታ ደረጃ ነው። ማለትም አንድ ባሪያ በቀልቡ ልክ አላህን እንደሚያይ እያሰበ መስራቱ ነው። ያኔ ሩቁ እንደ ቅርብ እስኪመስል ድረስ ልቡ በኢማን ይበራል።
ሁለተኛው ደረጃ: የማጥራትና የመጠባበቅ ደረጃ ነው። ይህም ማለት አንድ ባሪያ አላህ እያየውና እያወቀበት መሆኑን ልቡ ውስጥ አስቀምጦ መስራቱ ነው። ይህንን ልቡ ውስጥ ካኖረ ደሞ እርሱ ስራውን ለአላህ ያጠራ ይባላል።
ክፍል አራት: በአህሉ ሱና ወልጀመዓ መሰረቶች ዙርያ አጠር ያለ ገለፃ:
አንደኛ: በቁርአንና በሐዲሥ የመጣውን በውስጥም ሆነ በውጭ መከተል: የአንድንም ሰው ንግግር ከአላህና ከመልክተኛው ﷺ ንግግር አለማስቀደም ነው።
ሁለተኛ: ልቦቻቸውና አንደበቶቻቸው ለአላህ መልክተኛ ﷺ ባልደረቦች ንፁህ መሆን አለበት። አህለ ሱናዎች ከአላህ መልክተኛ ﷺ በኋላ ያለው ኸሊፋ (ምትክ መሪ) አቡበከር አስ-ሲዲቅ፣ ከዚያም ዑመር፣ ከዚያም ዑሥማን፣ ከዚያም ዐሊይ - አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና - መሆናቸውን ያምናሉ።
ሶስተኛ: የአላህን መልክተኛ ﷺ ቤተሰቦች መውደድና መወዳጀት አለብን። የርሳቸው ﷺ ቤተሰቦች የሚባሉት ከርሳቸው ቤተሰቦች መካከል ደጋግ (አማኝ) የሆኑትን ብቻ ናቸው።
አራተኛ: መሪዎችና ሹማምንቶች ግፍ ቢሰሩ እንኳ አምፆ አለመውጣት። ለነርሱም መልካም እንዲሆኑና ይቅር እንዲባሉ ዱዓ ይደረግላቸዋል እንጅ በነርሱ ላይ ዱዓ አይደረግባቸውም። መሪዎች በወንጀል እስካላዘዙ ድረስ እነርሱን መታዘዝ አላህን መታዘዝ እንደማለት ነው። ግዴታም ነው። በወንጀል ካዘዙ ግን እነርሱን መታዘዝ አይፈቀድም። ከዛ ውጪ ባሉ ጉዳዮች ግን ተሰሚነታቸው እንደተጠበቀ ይቀጥላል።
አምስተኛው: በወሊዮች ከራማ ማመን: የወሊዮች ከራማ ማለት: አላህ በወሊዮቹ እንዲፈፀም የሚያደርገው ከተለምዶ የወጣ ክስተት ነው።
ስድስተኛው: አህሉ ሱናዎች ወደ ቂብላ ዞሮ የሚሰግድን በትላልቅ ወንጀሎች አያከፍሩም። ከኸዋሪጆች በተቃራኒ ማለት ነው። ይልቁንም ወንጀል ከመስራታቸውም ጋር እምነታዊ ወንድማማችነታቸው እንደፀናች ትቀጥላለች። ወንጀል በሚሰራ ሰው ዙሪያ እንዲህ ይላሉ: በኢማኑ ልክ አማኝ ነው። ትልቅ ወንጀል በመፈፀሙ ደግሞ አመፀኛ ነው።
ምዕራፍ ሁለት: ከአምልኮ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች
ክፍል አንድ: ጠሃራ
ጠሃራ በቋንቋ ትርጓሜው: ውጫዊም ሆነ ውስጣዊ ከሆኑ ቆሻሻዎች መፅዳት ማለት ነው።
በሸሪዓ ትርጓሜው ደግሞ፡- ሐደሥን (ርኩሰትን) እና ቆሻሻን (ነጃሳን) ማስወገድ ነው። ጠሃራ የሶላት ቁልፍ ነው። ስለዚህም ጠሃራን መማር ሁሉም ሙስሊም መማርና ትኩረት መስጠት ግድ ከሚለው የእስልምና ዋና ዋና ጉዳዮች መካከል ነው።
የመጀመሪያ: የውሃ ክፍሎች:
1 - አፅጂ (ንፁህ) ውሃ: በርሱ መፅዳትና ዉዱእ ማድረግ ይፈቀዳል። ይህም ውሃ በተፈጥሯዊ ባህሪው ያለም ቢሆን በርሱ መፅዳዳት የሚፈቀድበት የውሃ ክፍል ነው: የዝናብ፣ የወንዝና የባህር ውሃ በምሳሌነት ይጠቀሳሉ። ወይም ከውሃው ጋር ንፁህ ነገር ቢቀላቀልና ከውሃው ካልበዛ ወይም የተቀላቀለው ነገር ውሃውን ውሃ ከሚለው ስያሜ ካላስወጣው አፅጂ ውሃ ይባላል።
2 - ነጃሳ ውሃ: መጠቀሙ አይፈቀድም። ሐደሥንም አያነሳም፤ ነጃሳንም አያስወግድም። ነጃሳ የሚባለው ውሃ: ቀለሙ ወይም ሽታው ወይም ጣዕሙ በነጃሳው የተለወጠ ውሃ ነው።
ሁለተኛ: ነጃሳ:
ነጃሳ ማለት በሸሪዓ የተለየ የቆሻሻ አይነት ነው። ነጃሳ የሆነ ነገር ሶላትን ይከለክላል። ሽንት፣ ሰገራ፣ ደምና መሰል ቆሻሻዎች በምሳሌነት የሚጠቀሱ ሲሆን ይህም አካል ላይም፣ መስገጃ ስፍራ ላይም ሆነ ልብስ ላይ አርፎ ሊነጅሰው ይችላል።
በመሰረቱ ሁሉም ነገሮች ፍቁድና ንፁህ ናቸው። ስለዚህም አንድ ነገር "ነጃሳ ነው" ብሎ የሞገተ ሰው ማስረጃ የማምጣት ግዴታ አለበት። ንፍጥ፣ የሰው ላብ፣ የአህያም ላብ ነጃሳ አይደሉም። ነገር ግን ቆሻሻ ከመሆናቸውም ጋር (በሸሪዓዊ እይታ) ንፁህ ናቸው። ሁሉም ነጃሳ ቆሻሻ ነው። ነገር ግን በተቃራኒ ሁሉም ቆሻሻ ነጃሳ አይደለም።
ነጃሳ ሶስት ደረጃዎች አሉት:
የመጀመሪያው: ከባድ ነጃሳ:
ለምሳሌ: ውሻ በለሃጩ የነካው ነጃሳ ነው። ማፅጃ መንገዱም: አንዱን በአፈር ከመቀላቀል ጋር አድርጎ ሰባት ጊዜ በውሃ ማጠብ ነው።
ሁለተኛ: ቀላል ነጃሳ ነው።
ለምሳሌ: ወተት የሚጠባ የወንድ ህፃን ልጅ ሽንት ልብስንና የመሳሰሉትን የነካ ጊዜ ነው። ማፅጃ መንገዱም: ሽንቱ የነካውን ቦታ በውሃ አዳርሶ ማርከፍከፍ በቂው ነው። መፈግፈግም ሆነ መጭመቅ አያስፈልገውም።
ሶስተኛ: መካከለኛ ነጃሳ:
ለምሳሌ: የሰው ልጅ ሽንትና ሰገራ መሰል አብዛኛው ነጃሳዎች መካከለኛው ነጃሳዎች ናቸው። እነዚህ የነጃሳ አይነቶች መሬት ላይ ወይም ልብስ ላይና የመሳሰሉት ላይ ካረፉ ይነጅሱታል። የማፅጃ መንገዱም: ነጃሳው መገለጫ ካለው የነጃሳውን መገለጫ ማስወገድና ቦታውን ከነጃሳው በውሃ ወይም በሌላ የማፅጃ መንገድ ማፅዳት ነው።
ማስረጃ በቀጥታ ከመጣባቸው ነጃሳዎች መካከል:
1: የሰው ልጅ ሽንትና ሰገራ:
2 - መዚይና ወዲይ:5
3 - ስጋው የማይበላ እንስሳ ሰገራ (ፍግ)
4 - የወር አበባና የወሊድ ደም
5 - የውሻ ለሀጭ:
6 - ስጋው በሸሪዓዊ መልኩ ሳይታረድ የሞተ ነገር (የበከተ)፤ ከሞቱ ነገሮች መካከል ግን በልዩነት የሚታዩ የማይነጅሱም አሉ:
ሀ) የሰው ልጅ የሞተ ጊዜ፤
ለ) የሞተ አሳና አንበጣ፤
መ) እንደ ዝንብ፣ ጉንዳን፣ ንብና የመሳሰሉት የሚፈስ ደም የሌላቸው እንስሳ ሲሞቱ፤
ሰ) የበክት አጥንት፣ ቀንድ፣ ጥፍር፣ ፀጉርና ላባ ናቸው።
የነጃሳ አፀዳድም:
1 - በውሃ: ውሃ ነጃሳን ለማፅዳት መሰረት ነው። ውሃ ባለበት ሌላ ነገር ለማፅጃነት አማራጭ አይሆንም።
2 - በሸሪዓ ነጃሳን ወይም የተነጀሰን ነገር ለማፅጃነት የመጡ ማፅጃ መንገዶች:
ሀ) የበክት ቆዳ በመልፋት ይፀዳል።
ለ) እቃ ውስጥ ውሻ ምላሱን ከነከረ አንዱን በአፈር በመቀላቀል ሰባት ጊዜ በማጠብ ይፀዳል።
መ) ልብስ የወር አበባ ደም የነካው ጊዜ በመጀመሪያ በመፈቅፈቅ ቀጥሎ በውሃ በማሸት ከዚያም በማጠብ (በማለቅለቅ) ይፀዳል። በዚህ መልኩ ከታጠበ በኋላ ምልክት ከቀረ ምንም አይጎዳም።
ሰ) የረዘመ የሴት ልጅ ልብስ ከተነጀሰ ቀጥላ ስትራመድ በሚነካት ንፁህ መሬት ይፀዳል።
ረ) ወተት የሚጠባ የወንድ ጨቅላ ሽንት የነካው ልብስ ውሃ በማርከፍከፍ ይፀዳል። የሴት ጨቅላ ሽንት ከሆነ ደግሞ በማጠብ ይፀዳል።
ሸ) መዚይ የነካው ልብስ የነካው ስፍራ ላይ ውሃ በማርከፍከፍ (በመርጨት) ይፀዳል።
ቀ) የጫማ ታችኛው ክፍል ንፁህ መሬት ላይ በመፈግፈግ ይፀዳል።
በ) መሬት ከነጃሳ የሚፀዳው የነካው ስፍራ ላይ በቡሃቃ ውሃን በመድፋት ወይም በፀሃይ ወይም በንፋስ እስክትደርቅ በመተው ነው። የነጃሳው ምልክት ከተወገደ ይፀዳል።
ሶስተኛ: ዉዱእ ያጠፋ ሰው መስራት የሚከለከላቸው ነገሮች:
ዉዱእ ያጠፋ ሰው ወይም የተጀነበ (የዘር ፈሳሽ የወጣው) ሰው የሚከተሉትን ነገሮች ይከለከላል:
1 - ግዴታ ወይም ሱና ሶላት መስገድ: ከኢብኑ ዑመር -አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና - እንደተላለፈው: ነብዩ ﷺ እንዲህ ብለዋል፦
«لَا يَقْبَلُ اللَّهُ صَلَاةً بِغَيْرِ طُهُورٍ».
«ያለ ዉዱእ የተሰገደ ሰላትን አላህ አይቀበለውም።)6
2 - ሙስሐፍ (የቁርአን መጽሐፍ) መንካት። መልክተኛው ﷺ ለዓምር ቢን ሐዝም በላኩት ደብዳቤ እንደመጣው እዛ ውስጥ እንዲህ የሚል ሰፍሮ ይገኛልና:
«لَا يَمَسُّ الْقُرْآنَ إِلَّا طَاهِرٌ».
«ንፁህ ከሆነ ሰው በቀር ቁርአንን አይንካ።»7
3 - በአላህ ቤት ጠዋፍ ማድረግ ነቢዩ ﷺ እንዲህ ብለዋልና:
«الطَّوَافُ بِالْبَيْتِ صَلَاةٌ، إِلَّا أَنَّ اللَّهَ أَبَاحَ فِيهِ الْكَلَامَ».
«በጠዋፍ ላለ ሰው መናገር በአላህ የተፈቀደ ከመሆኑ በቀር በቤቱ (በካዕባ) ዙሪያ ጠዋፍ ማድረግ እንደሶላት ነው።»8 ነቢዩ ﷺ ጦዋፍ ለማድረግ ዉዱእም አድርገዋል። ከነቢዩ ﷺ በሶሒሕ ሐዲሥ እንደተረጋገጠው የወር አበባ ላይ ያለች ሴት ከመፅዳቷ በፊት በአላህ ቤት ጦዋፍ ከማድረግ ከልክለዋታል።
ትልቁ ሐደሥ (ገላ የሚያስታጥብ) የተከሰተበት ሰው ብቻ የሚከተሉትን ነገሮች ይከለከላል:
1 - ቁርኣንን መቅራት: ይህም ዐሊይ -አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላቸውና- እንዲህ ስላሉ ነው «ነቢዩን ﷺ ከጀናባ ውጪ ቁርአን ከመቅራት ምንም ነገር አይከለክላቸውም ነበር።»9
2 - ያለ ዉዱእ መስጂድ መቆየት: ምክንያቱም የላቀው አላህ እንዲህ ብሏልና፦
﴿يَٰٓأَيُّهَا ٱلَّذِينَ ءَامَنُواْ لَا تَقۡرَبُواْ ٱلصَّلَوٰةَ وَأَنتُمۡ سُكَٰرَىٰ حَتَّىٰ تَعۡلَمُواْ مَا تَقُولُونَ وَلَا جُنُبًا إِلَّا عَابِرِي سَبِيلٍ حَتَّىٰ تَغۡتَسِلُواْ...﴾
{እናንተ ያመናችሁ ሆይ! እናንተ የሰከራችሁ ኾናችሁ የምትሉትን ነገር እስከምታውቁ የረከሳችሁም ስትኾኑ መንገድን አላፊዎች ካልኾናችሁ በስተቀር (አካላታችሁን) እስከምትታጠቡ ድረስ ስግደትን አትቅረቡ፡፡} [አንኒሳእ:43]
ትልቁ ሐደሥ (ገላ የሚያስታጥብ) ያጋጠመው ሰው ዉዱእ አድርጎ መስጂድ ውስጥ መቆየት ይፈቀድለታል። ልክ እንደዚሁ ትልቁ ሐደሥ ላይ የሆነ ሰው መስጂድ ውስጥ ምንም ሳይቀመጥ (ያለውዱእ) ማለፍ ብቻም ይፈቀድለታል።
አራተኛ: የመፀዳዳት ሥነ-ስርአት (አዳብ):
በመፀዳዳት ወቅት የሚከተሉት ይወደዳሉ:
1 - በመፀዳዳት ወቅት ከሰዎች መሸሸግና መራቅ:
2 - በሚገባበት ወቅት በሐዲሥ የመጣውን ዱዓ ማለት። እሱም:
«اللَّهُمَّ إِنِّي أَعُوذُ بِكَ مِنَ الْخُبْثِ وَالْخَبَائِثِ».
«አልላሁመ ኢንኒ አዑዙ ቢከ ሚነልኹብሢ ወልኸባኢሥ" ትርጉሙም "አላህ ሆይ! ከወንድም ሆነ ከሴት ሸይጣን ባንተ እጠበቃለሁ።" ማለት ነው።10
በመፀዳዳት ወቅት የሚከተሉት ግዴታዎች ናቸው:
1 - ከሽንት መፅዳት፣
2 - ሀፍረተ ገላን መሸፈን።
በመፀዳዳት ወቅት የሚከተሉት ክልክል ናቸው:
1 - ወደ ቂብላ አቅጣጫ ዞሮ ወይም ጀርባ ሰጥቶ መፀዳዳት፣
2 - በሰዎች መተላለፊያ መንገድና ህዝባዊ ስፍራዎች መፀዳዳት፣
3 - የተገደበ ወራጅ ያልሆነ ውሃ ውስጥ መሽናት፣
በመፀዳዳት ወቅት የሚከተሉት ይጠላሉ:
1 - በመፀዳዳት ወቅት ብልትን በቀኝ እጅ መያዝ፣
2 - በቀኝ እጅ ማደራረቅና ኢስቲንጃእ ማድረግ፣
3 - በመፀዳዳት ወቅት ማውራት ይጠላል። በተለይም አላህን ማውሳት።
አምስተኛ: የኢስቲንጃእ እና የኢስቲጅማር ህግጋት:
ኢስቲንጃእ ማለት ከሁለቱ ሀፍረተ ገላ ቀዳዳዎች የሚወጣን ቅሪት በውሃ ማስወገድ ማለት ነው።
ኢስቲጅማር ማለት ደሞ ከሁለቱ ሃፍረተ ገላ ቀዳዳዎች የሚወጣን ቅሪት ድንጋይና ሶፍት (ፎጣ) በመሰሉ ከውሃ ውጪ ባሉ ነገሮች ማስወገድ ማለት ነው።
የምናደራርቅበት ነገር ማሟላት ያለበት መስፈርቶች:
1 - የተፈቀደ መሆን አለበት፣
2 - ንፁህ መሆን አለበት፣
3 - አፅጂ መሆን አለበት፣
4 - አጥንት ወይም የከብት ሰገራ መሆን የለበትም፣
5 - የሚደራረቅበት ነገር የአላህ ስም እንደለበት አይነት ወረቀት የተከበረ መሆን የለበትም።
ሁለት መስፈርቶች ከተሟሉ በውሃ ኢስቲንጃእ ሳያደርጉ በማደራረቅ ብቻ ዉዱእ አድርጎ መስገድም ይፈቀዳል:
1 - የሚወጣው ነገር ከተለመደው ስፍራ ማለፍ የለበትም።
2 - የሚያደራርቀው በሶስትና ከዛ በላይ በሆኑ አፅጂ ድንጋዮች መሆን አለበት።
ስድስተኛ: የዉዱእ ህግጋት:
ሶስት አምልኮዎችን ለመፈፀም ዉዱእ ግዴታ ነው:
1: ሶላት: ግዴታም ሶላት ሆነ ሱና ሶላት ለመስገድ ዉዱእ ግዴታ ነው።
2: ቁርአን ለመንካት
3: ጦዋፍ ለማድረግ:
የዉዱእ መስፈርቶች:
1 - እስልምና፣
2: የአይምሮ ጤነኝነት፣
3: መለየት መቻል
4: ኒያ: የኒያ ቦታው ቀልብ ነው። ኒያውን በአፍ መናገር ግን ቢድዓ ነው። ዉዱእ ማድረግ የፈለገ ሰው ሁሉ ነይቷል ይባላል። ቀዝቀዝ እንዲለው ወይም መፅዳትን በማሰብ የዉዱእ አካላትን መታጠብ ዉዱእ አይባልም።
5: የዉዱእን ብይን ማጎዳኘት: ማለትም ዉዱእን አሟልቶ እስኪያጠናቅቅ ድረስ ዉዱኡን የማቋረጥ ኒያ ውስጥ መግባት የለበትም።
6: ዉዱእን የሚያስገድዱ ነገራት መቋረጥ አለባቸው። እዚህ መስፈርት ውስጥም ዘውትር በማይቋረጥ መልኩ ሽንቱ የሚወጣና የበሽታ ደም የሚፈሳት ሴት አይካተቱም።
7: ሽንት ወይም ሰገራ የወጣው ሰው ከዉዱእ በፊት ኢስቲንጃእ ወይም ማደራረቅ፣
8: ውሃው ንፁህና ፍቁድ መሆን አለበት።
9: ውሃውን ወደ ሰውነት ከመድረስ የሚከለክልን ነገር ማስወገድ፣
10: ሐደሡ (ዉዱእ የሚያጠፋ ነገር) ዘውትር ሳይቋረጥ የሚወጣው ሰው ዉዱእ ለማድረግ የሶላቱ ወቅት መግባት አለበት።
የዉዱእ ግዴታዎች:
1: ፊትን መታጠብ: መጉመጥመጥና አፍንጫ ውስጥ ውሃ መክተት ፊትን መታጠብ ውስጥ ይካተታል።
2: ሁለት እጆችን ከክርን ጋር መታጠብ፤
3: ጭንቅላትን ባጠቃላይ ማበስ፤ ጆሮዎችንም ማበስ እዚሁ ውስጥ የሚካተቱ ናቸው።
4: ሁለት እግሮችን ቁርጭምጭሚትንም ጨምሮ መታጠብ፤
5: በዉዱእ አካላቶች መካከል ቅደም ተከተልን መጠበቅ፤
6: አከታትሎ ማድረግ: በአካላቶች መካከል ረጅም የጊዜ ክፍተትን አለመተው ማለት ነው።
የዉዱእ አፈፃፀም:
1: ቢስሚላህ ማለት:
2: ሁለት መዳፎችን ሶስት ሶስት ጊዜ መታጠብ:
3: ፊትን ሶስት ሶስት ጊዜ መታጠብ፤ መጉመጥመጥና አፍንጫ ውስጥ ውሃ መሳብ ፊትን መታጠብ የሚለው ውስጥ ይካተታሉ።
4: ሁለት እጆችን እስከ ክርን ድረስ ሶስት ሶስት ጊዜ መታጠብ፤ ቀኝ እጅን በቅድሚያ መታጠብ ቀጥሎ ግራን መታጠብ ነው።
5: ጭንቅላትን ከጆሮ ጋር ጨምሮ ማበስ፤
6: ሁለት እግሮችን እስከ ቁርጭምጭሚት ድረስ ሶስት ሶስት ጊዜ መታጠብ፤ በቅድሚያ ቀኝ እግርን መታጠብ ቀጥሎ ግራን መታጠብ።
ዉዱእን የሚያበላሹ ነገሮች:
1: ከሁለቱ መንገዶች የወጡ ነገሮች: ለምሳሌ ሽንት፣ ፈስና ሰገራ ይጠቀሳሉ።
2: ከሰውነት የሚወጣ ቆሻሻና ነጃሳ የሆነ ነገር፤
3: በእንቅልፍ ወይም በሌላ ምክንያት የአይምሮ መወገድ፤
4: የፊለፊቱንም ሆነ የኋላውን ብልት ያለ ግርዶሽ በእጅ መንካት፤
5: የግመል ስጋ መብላት፤
6: አላህ እኛንም ሙስሊሞችንም ይጠብቀንና ከእስልምና መውጣት ናቸው።
ሰባተኛ: በኹፍ እና ካልሲዎች ላይ የማበስ ህግጋት:
1: ኹፍ: ከቆዳና ከመሳሰሉት ግብዓት ተሰርቶ እግሮች ላይ የሚለበስ ነው።
2: ጀውረብ: ከሱፍ ጨርቅ ወይም ከጥጥ ወይም ከመሳሰሉት የሚሰራ እግር ላይ የሚለበስ የእግር ሹራብ ነው።
በሁለቱ ላይ የማበስ መስፈርቶች:
1: የለበሰው ሁለቱንም የተሟላ ጦሃራ ካደረገ በኋላ መሆን፤
2: ሁለት እግሮችን ቁርጭምጭሚትንም ጨምሮ የሚሸፍኑ መሆን አለባቸው፤
3: ንፁህ (ያልተነጀሱ) መሆን አለባቸው፤
4: ማበሱ በተገደበለት የጊዜ ገደብ ውስጥ መሆን አለበት፤
5: የሚያብሰው ለዉዱእ እንጂ ለትጥበት መሆን የለበትም፤
6: ኹፉም ሆነ መሰል የተደረገው ልብስ ፍቁድ መሆን አለበት። የተቀማ ወይም ለወንድ ልጅ ከሐር የተሰራ ከሆነ እርሱ ላይ ማበስ አይፈቀድም። ለማግራራት የተፈቀደ ነገር የሚደረገው ሐራም ላይ ከሆነ መግራራቱ ይሰረዛልና።
የማበሻ ጊዜ:
ለሃገር ቤት ተቀማጭ: አንድ ቀን ከነምሽቱ ሲሆን ጉዞ ለወጣ ሰው ደግሞ ሶስት ቀን ከነምሽቱ ነው።
የማበስ አፈፃፀም:
እጅን በውሃ በማራስ የካልሲውን ወይም የኹፉን የላይኛውን ክፍል ከእግሮች ጣት በመነሳት እስከ ባቱ ድረስ አንድ ጊዜ ማበስ ነው።
ማበስን የሚያበላሹ ነገሮች:
1: የማበሻ ጊዜ መጠናቀቁ፤
2: ሁለቱንም ካልሲዎቹን ወይም አንዱን ማውለቅ፣
3: ትልቁ ሐደሥ (ገላ የሚያስታጥብ) መከሰቱ ናቸው።
በሁለቱ ኹፎች ላይ የማበስ ብይን:
የአላህ ማግራሪያ ነው። የአላህን ማግራሪያ ለመተግበር፣ ነቢዩን ﷺ ለመከተልና የቢድዓ ሰዎችን ለመቃረን ሲባል ሁለቱን ኹፎች አውልቆ እግሮችን ከመታጠብ ይልቅ ማበሱ በላጭ ነው።
3: በመጠገኛዎች፣ በፋሻዎችና ፕላስተር ላይ ማበስ:
መጠገኛ: ማለት ጀሶ ወይም እንጨቶችንና የመሳሰሉትን ለተሰበረ አጥንት መጠገኛ መጠቀም ነው።
ፋሻ: ማለት ቁስል ላይ ወይም ፍንክት ላይ ወይም የተቃጠለ ላይ የሚጠቀለልበት ጨርቅና የመሳሰሉት ነው።
ፕላስተር: ማለት ቁስል ላይ ወይም ቡግር ላይ ለህክምና የሚለጠፍ ነው።
በነዚህ ላይ የማበስ ብይን:
እስካስፈለገ ድረስ አስፈላጊ በሆነ ወቅት ሁሉ ላዩላይ ማበስ ይፈቀዳል። ነገር ግን የሚታሰረው ወይም የሚለጠፈው ቦታ ካስፈለገው ቦታ በላይ አለማለፉ መስፈርት ነው።
አስፈላጊነቱ ሲጠናቀቅ ወይም በማውለቁ ችግር ወይም ጉዳት የማይከተለው ከሆነ ላዩላይ ማበስ አይፈቀድም።
የአስተባበሱ ሁኔታ:
ዙሪያውን ያጥብና ከሁሉም ጎን ላዩላይ ያብሳል። ከዉዱእ አካል ውጭ የሆነውን አያብስም።
ስምንተኛ: የተየሙም ህግጋት:
ተየሙም ማለት ጦሃራን በማሰብ መሬትን በመምታት ፊትንና እጅን ልዩ በሆነ መልኩ ማበስ ማለት ነው።
ብይኑ:
ውሃ በጠፋ ጊዜ ወይም ውሃን መጠቀም ባልተቻለ ጊዜ በዉዱእ እና ትጥበት ምትክ ተየሙም ማድረግ ግዴታ ነው።
ተየሙም የመደንገጉ ጥበብ:
ተየሙም ከነቢዩ ሙሐመድ ﷺ ኡመት መለዮ መካከል አንዱ ነው። በቀደሙ ህዝቦች ውስጥ የሚታወቅ አልነበረም። አላህ ለዚህ ኡመት ህግጋቱን ለማስፋትና ለዚህ ኡመት መልካምን ለማድረግ የደነገገው ነው።
ተየሙም የሚደነገግባቸው ሁኔታዎች:
1: ሃገር ቤትም ሆነ ጉዞ ላይ ውሃ አጥቶ ፈልጎም ያላገኘ ጊዜ፤
2: ውሃ ቢኖረውም ለመጠጥ ወይም ለማብሰያነት ከፈለገውና በዛ ውሃ ጦሃራ ቢያደርግ ውሃውን ከተጠቀመበት ለፈለገው ጉዳይ ስለሚያንሰው ጉዳት የሚያደርስበት ከሆነ ነው፤ ይህም ማለት በራሱ ላይ ጥምን ከፈራ ወይም የሌላን የተከበረን የሰው ልጅም ሆነ የተከበረ እንስሳን ጥም ከፈራ ውሃው ቢኖርም ተየሙም ያደርጋል።
3: ውሃን መጠቀሙ ሰውነቱ ላይ ህመምን ያመጣብኛል ብሎ ከፈራ ወይም ፈውስ ይዘገይብኛል ብሎ ከፈራ፤
4: መንቀሳቀስ እንዳይችል ያደረገው ህመም ስላለበት ውሃን መጠቀም ያቃተው ጊዜና እርሱ ዘንድም ዉዱእ የሚያስደርገው ከሌለ በተጨማሪ ውዱእ የሚያስደርገው እስኪመጣ ድረስ የሶላቱ ወቅት ይወጣብኛል ብሎም ከፈራ፤
5: ውሃን በመጠቀሙ የውሃው ቅዝቃዜ ይጎዳኛል ብሎ ከፈራና ውሃውን የሚያሞቅበት ካላገኘ ተየሙም በማድረግ ይሰግዳል።
የተየሙም አደራረግ:
በእጆቹ ጣቶቹን በመከፋፈት አፈሩን መምታት ቀጥሎ ፊቱን በጣቶቹ የውስጥ ክፍል ያብሳል በመዳፎቹ የውስጥ ክፍል ደግሞ መዳፎቹን ባጠቃላይ ያብሳል። ፊቱንና መዳፎቹን አዳርሶም ያብሳል።
ተየሙምን የሚያበላሹ ነገሮች:
1: ተየሙም ያደረገው ውሃ በማጣት ምክንያት ከሆነ ውሃን ማግኘት ተየሙምን ያበላሻል፤ ወይም ተየሙም ያደረገው ውሃን መጠቀም ባለመቻሉ ከሆነ ልክ ውሃን መጠቀም ሲችል ተየሙሙ ይበላሻል።
2: ዉዱእን ከሚያበላሹት መካከል አንዱ ከተከሰተ ወይም እንደወር አበባ፣ ጀናባና የወሊድ ደም ያሉ ትጥበትን ግዴታ ከሚያደርጉ ነገሮች መካከል አንዱ ከተከሰተ ተየሙም ይበላሻል።
ውሃንም ተየሙምንም መጠቀም ያቃተው ሰው ብይን:
ውሃንና አፈርን ያጣ ወይም ባጋጠመው ነገር ምክንያት ሰውነቱ ውሃ ወይም አፈር ሊነካው እስከማይችል ደረጃ ላይ የደረሰ ሰው ባለበት ሁኔታ ላይ ሆኖ ያለ ዉዱእም ያለ ተየሙምም ይሰግዳል። አላህ ነፍስን ከችሎታዋ በላይ አያስገድዳትምና። ከዛ በኋላ ውሃና አፈር ቢያገኝ ወይም ውሃና አፈርን መጠቀም ቢችል እንኳ የታዘዘውን ሶላት ስለፈፀመ የሰገደውን ደግሞ አይደግም። ምክንያቱም የላቀው አላህ እንዲህ ብሏልና፦
﴿...فَٱتَّقُواْ ٱللَّهَ مَا ٱسۡتَطَعۡتُمۡ...﴾
{አላህንም የቻላችሁትን ያክል ፍሩት} [አት‐ተጋቡን: 16] ነቢዩም ﷺ እንዲህ ብለዋል:
«إِذَا أَمَرْتُكُمْ بِأَمْرٍ فَأْتُوا مِنْهُ مَا اسْتَطَعْتُمْ».
"በአንድ ትእዛዝ ያዘዝኳችሁ ጊዜ የቻላችሁትን ያህል ከርሱ ፈፅሙ!"11
ማስታወሻ: በጀናባ ምክንያት ተየሙም ያደረገና ከዚያም ውሃ ያገኘ ሰው ይታጠባል።
ዘጠነኛ: የወር አበባና የወሊድ ደም ብይን:
የመጀመሪያው: የወር አበባ:
የወር አበባ ማለት: በታወቁ ጊዜያት ከማህፀን ጥልቅ ክፍል የሚወጣ ተፈጥሯዊ ደም ነው። አብዛኛው ጊዜ በየሁሉም ወር ለስድስት ቀናት ወይም ለሰባት ቀናት ይወጣል። ከዚህም ሊጨምር ወይም ሊቀንስ ይችላል። አላህ እንደወሰነው ተፈጥሯዊ ሁኔታ የሴት ልጅ ወሯ (የምታይበት ጊዜ) ሊረዝምም ሊያጥርም ይችላል።
የወር አበባ ህግጋት:
1: የወር አበባ ላይ ያለች ሴት በወር አበባ ወቅት አትሰግድም አትፆምም። ብትሰግድና ብትፆምም አይቆጠርላትም።
2: የወር አበባ ላይ ያለች ሴት ከፀዳች በኋላ ፆምን ቀዷ ታወጣለች ሶላትን ግን ቀዷ አታወጣም።
3: በአላህ ቤት ጦዋፍ ማድረግ አይፈቀድላትም። ቁርአን አትቀራም፣ በመስጂድ ውስጥም አትቀመጥም። 4: የወር አበባው እስኪቋረጥና እስክትታጠብ ድረስ በባሏ ላይ እርሷን መገናኘት ይከለከላል።
5: ሚስቱ የወር አበባ ላይ ባለችበት ጊዜ ባል በብልቷ ከመገናኘት ውጪ መላፋት ይፈቀድለታል። እንደመሳሳም፣ መዳበስና የመሳሰሉት
6: ሚስቱ የወር አበባ ላይ ሆና መፍታትም ለባል አይፈቀድለትም።
ንፅህና ማለት የደም መቋረጥ ነው። ደም የተቋረጠ ጊዜ ፀድታለች የወር አበባ ጊዜዋም ተጠናቋል ይባላል። መታጠብም በርሷ ላይ ግዴታ ይሆናል። ከዚያም በወር አበባ ምክንያት ተከልክላ የነበረውን ተግባራት ትጀምራለች።
ከፀዳች በኋላ የደፈረሰ ወይም ቢጫ ቀለም ያለው ፈሳሽ ከወጣት እንደምንም መቁጠር የለባትም።
ሁለተኛ: የወሊድ ደም:
የወሊድ ደም የሚባለው በወሊድ ወቅትና ከወሊድ በኋላ ማህፀን የሚለቀው ደም ነው። የወሊድ ደም በእርግዝና ጊዜያት ታቅቦ የቀረ የደም ቅሪት ነው።
የወሊድ ደም ብይን በወር አበባ ላይ ያለች ሴት የሚፈቀድላት ነገር የወሊድ ደም ላይ ላለችውም ይፈቀዳል። ለምሳሌ በብልት ከመገናኘት ውጪ መላፋት፤
በሚከለከለውም እንደዛው: በብልት መገናኘት፣ ከፆም፣ ከሶላት፣ ከፍቺ፣ ከጦዋፍ፣ ቁርአን ከመቅራት፣ መስጂድ ውስጥ ከመቀመጥ መከልከሉን ይመስል። እንዲሁም ልክ እንደወር አበባ ደሙ በተቋረጠ ጊዜ መታጠብ ግዴታ በመሆንም ያመሳስላቸዋል።
የወሊድ ደም የሚፈሳት ሴት ልክ የወር አበባ ላይ እንዳለችዋ ሴት ፆም ቀዷ ማውጣት ግዴታዋ ነው። ሶላትን ግን ቀዷ አታወጣም።
የወሊድ ደም ቢበዛ አርባ ቀን ነው። የወሊድ ደም ከአርባ ቀን በፊት ከቆመ የወሊድ ደሙ ስለተጠናቀቀ ታጥባ ትሰግዳለች። በወሊድ ደም ምክንያት ተከልክላ የነበረቻቸውንም ትተገብራለች።
ሁለተኛው ክፍል: ሶላት
የመጀመሪያው: የአዛንና ኢቃማ ህግጋት:
አዛን የተደነገገው በሂጅራ አቆጣጠር የመጀመሪያው ዓመት ላይ ነው። የመደንገጉ ምክንያትም: የሶላትን ወቅት ማወቅ የጠናቸው ጊዜ ወቅቱን ለማሳወቅ አንድ ምልክትን ማስቀመጥ እንዳለባቸው ተወያዩ። በዚህ መሃል ዐብደላህ ቢን ዘይድ -አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና- በህልማቸው አዛንን ተመለከቱ። ወሕይም ህልሙን አፀና።
አዛን ማለት የሶላት ወቅት መግባቱን ማወጅ ነው። ኢቃማህ ማለት ደግሞ ሶላት ሊቆም መሆኑን ማወጅ ነው።
ለግዴታ ሶላቶች አዛንና ኢቃማህ ማለት በወንዶች ላይ ፈርድ ኪፋያ (ማህበራዊ ግዴታ) ነው።12 እነርሱ ግልፅ ከሆኑት እስላማዊ መገለጫዎች መካከል ስለሆኑ መተው አይፈቀድም።
የአዛን መስፈርቶች:
1: አዛን ባዩ ወንድ መሆን አለበት፤
2: አዛኑ በቅደም ተከተል መፈፀም አለበት፤
3: አዛኑ ተከታትሎ መፈፀም አለበት፤
4: አዛኑ የሶላት ወቅት ከገባ በኋላ መሆን አለበት፤ ከዚህ የሶላቱ ወቅት መግባቱን ከሚጠየቀው መስፈርትም: የመጀመሪያዎቹ የፈጅርና የጁመዓ አዛኖች ተለይተው ይወጣሉ።
የአዛን ሱናዎች:
1: ጣቶቹን በጆሮዎቹ ላይ ማኖር፤
2: አዛንን በወቅቱ መጀመርያ ላይ ማድረግ፤
3: ሐይዐለተይን (ሐይየ ዐለሶላህ እና ሐይየ ዐለል ፈላሕ) በሚል ወቅት ወደ ቀኝ እና ወደ ግራ መዞር፤
4: አዛን ባዩ ጥሩ ድምፅ ያለው ቢሆን፤
5: ፊደላትን ያላግባብ ሳያረዝምና ወሰን ያለፈን መሳብም ሳያደርግ በአዛን ወቅት የአዛንን ቃላት ያዝ እያደረገ ማለት፤
6: በእያንዳንዱ የአዛን አረፍተ ነገሮች መካከል ረገብ ማለት፤
7: በአዛን ወቅት ወደ ቂብላ መዞር፤
ቢላል -አላህ መልካም ስራውን ይውደድለትና- የአላህ መልክተኛ ﷺ ባሉበት አዛን የሚላቸው የአዛን አረፍተ ነገራት አስራ አምስት አረፍተ ነገራቶችን ያካተተ ነው።
የአዛን ቃላቶች:
(አላሁ አክበር) አራት ጊዜ፤
(አሽሃዱ አንላ ኢላሃ ኢለሏህ) ሁለት ጊዜ፤
(አሽሃዱ አንነ ሙሐመደን ረሱሉሏህ) ሁለት ጊዜ፤
(ሐይየ ዐለስሶላህ) ሁለት ጊዜ፤
(ሐይየ ዐለል ፈላሕ) ሁለት ጊዜ፤
ቀጥሎም (አላሁ አክበር) ሁለት ጊዜ፤
ከዚያም (ላኢላሃ ኢለሏህ) አንድ ጊዜ በማለት ያጠናቅቃል።
የፈጅር ሶላት ከሆነ ሐይየ ዐለል ፈላሕ ካለ በኋላ (አስሶላቱ ኸይሩን ሚነንነውም) የሚለውን ሁለት ጊዜ ማለትን ይጨምራል። ይህም ሰዎች በብዛት የሚተኙበት ወቅት ስለሆነ ነው።
ኢቃማህ አስራ አንድ አረፍተ ነገራትን ያካተተ ነው። አላማው የተገኙን ሰዎች ለማሳወቅ ስለሆነ ዝግ ለማለት የሚጋብዝ ምንም ነገር ስለሌለ ኢቃም በሚል ወቅት ያከታትለዋል ማለትም ይፈጥናል።
የቃላት ይዘቶቹም የሚከተሉት ናቸው:
(አላሁ አክበር) ሁለት ጊዜ፤
(አሽሃዱ አንላ ኢላሃ ኢለሏህ) አንድ ጊዜ፤
(አሽሃዱ አንነ ሙሐመደን ረሱሉሏህ) አንድ ጊዜ፤
(ሐይየ ዐለስሶላህ) አንድ ጊዜ፤
(ሐይየ ዐለል ፈላሕ) አንድ ጊዜ፤
(ቀድ ቃመት አስሶላህ) ሁለት ጊዜ፤
(አላሁ አክበር) ሁለት ጊዜ፤
(ላኢላሃ ኢለሏህ) አንድ ጊዜ ይላል።
አዛን የሰማ ሰው ልክ ሙአዚኑ የሚለውን አምሳያ ማለት ይወደድለታል። (ሙአዚኑ) "ሐያ ዐለ ሰላህ" እና "ሐያ ዐለል ፈላሕ" ሲል ግን “ላ ሐውለ ወላ ቁወተ ኢላ ቢላህ” ይበል። በመቀጠልም በነቢዩ ﷺ ላይ ሰለዋት ያወርዳል: ከዚህም በኋላ እንዲህ ይላል:
«اللهمَّ رَبَّ هَذِهِ الدَّعْوَةِ التَّامَّةِ، وَالصَّلَاةِ القَائِمَةِ، آتِ مُحَمَّدًا الوَسِيلَةَ وَالفَضِيلَةَ، وَابْعَثْهُ مَقَامًا مَحْمُودًا الَّذِي وَعَدْتَهُ، إِنَّكَ لَا تُخْلِفُ الْمِيعَادَ».
"አላሁምመ ረብበ ሐዚሂ አድዳዕወቲ አትታማህ፤ ወስ-ሶላቲ አል-ቃኢማህ፤ አቲ ሙሐመደን አል-ወሲለተ ወልፈዲላህ፤ ወብዐሥሁ መቃመን መሕሙደን አልለዚ ወዐድተህ። ኢንነከ ላ ቱኽሊፉል ሚዓድ"13 (ትርጉሙም፡ የዚህ የተሟላ ጥሪና የተቋቋመው ሶላት ጌታ አላህ ሆይ! (ነብዩ) ሙሐመድን "ወሲላ" እና "ፈዲላ"ን ለግሳቸው፤ ቃል በገባህላቸው ምስጉን ስፍራም ቀስቅሳቸው። እነሆ አንተ ቃልህን አታጥፍምና።)
እንዲህም ይበል:
«رَضِيتُ بِاللَّهِ رَبًّا، وَبِالْإِسْلَامِ دِينًا، وَبِمُحَمَّدٍ ﷺ نَبِيًّا».
«ረዲቱ ቢላሂ ረበን ወቢልኢስላሚ ዲነን ወቢሙሐመደን ﷺ ነቢያ"14 "በአላህ ጌትነት፣ በእስልምና ሃይማኖትነትና በሙሐመድ ነቢይነት ወደድኩ።"
አዛን ካለ በኋላ ያለበቂ ምክንያት ወይም ተመልሶ መምጣትን ሳያልሙ ከመስጂድ መውጣት ክልክል ነው ።
ሁለት ግዴታ ሶላቶችን ሰብስቦ በሚሰገድበት ወቅት በአንድ አዛንና ለሁሉም ሶላት ኢቃም በማለት ይብቃቃል።
ሁለተኛ: የሶላት ደረጃና ትሩፋት:
ሶላት ከእስልምና ማዕዘናት መካከል ከሁለቱ የምስክርነት ቃላት በኋላ እጅግ አፅንዖት የተሰጠው ማዕዘን ነው። ሶላት ልዩ ደረጃ አለው: አላህ ሶላትን ግዴታ አድርጎ በመልክተኛው ﷺ ላይ ያወረዳት ወደ ሰማይ ባረጉበት ምሽት ነው። ይህም የሶላትን ልቅና፣ ጠንካራ ግዴታ መሆኗንና አላህ ዘንድም ያላትን ደረጃ ይጠቁማል።
ስለ ሶላት ትሩፋትና በነፍስ ወከፍ ግዴታ መሆኗን የሚጠቁሙ በርካታ ሐዲሦች መጥተዋል። በእስልምና ሃይማኖት ውስጥ የሶላት ግዴታነት ሙስሊም በመሆን ብቻ የሚታወቅ ነው።
ሶላት ግዴታ መሆኗንና አፅንዖት የተሰጣት መሆኗን የሚጠቁሙ በርካታ የቁርአንና የሐዲሥ ጥቅሶች አሉ። ከነሱም መካከል:
1: ተከታዩ የአላህ ቃል ነው፦
﴿...إِنَّ ٱلصَّلَوٰةَ كَانَتۡ عَلَى ٱلۡمُؤۡمِنِينَ كِتَٰبٗا مَّوۡقُوتٗا﴾
{ሶላት በምእምናን ላይ በጊዜያት የተወሰነች ግዴታ ናትና።} [አንኒሳእ: 103] ማለትም የአላህ መልክተኛ ﷺ በገለፁት ወቅቶች ግዴታ ተደርጋለች ማለት ነው።
2: አላህ እንዲህም ብሏል:
﴿وَمَا أُمِرُوا إِلَّا لِيَعْبُدُوا اللَّهَ مُخْلِصِينَ لَهُ الدِّينَ حُنَفَاءَ وَيُقِيمُوا الصَّلَاةَ...﴾
{አላህን ሃይማኖትን ለእርሱ ብቻ አጥሪዎች፤ ቀጥተኞች ሆነው ሊግገዙት፣ ሶላትንም አስተካክለው ሊሰግዱ እንጂ ያልታዘዙ ሲሆኑ (ተለያዩ)} [አል-በይናህ፡ 5]
3: አላህ እንዲህም ብሏል:
﴿فَإِنْ تَابُوا وَأَقَامُوا الصَّلَاةَ وَآتَوُا الزَّكَاةَ فَإِخْوَانُكُمْ فِي الدِّينِ...﴾
{ቢጸጸቱም፣ ሶላትንም ቢሰግዱ፣ ዘካንም ቢሰጡ የሃይማኖት ወንድሞቻችሁ ናቸው፡፡} [አት ተውባህ፡ 11]
ከጃቢር (ረዲየሏሁ ዐንሁ) አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና እንደተላለፈው የአሏህ መልዕክተኛ ﷺ እንዲህ ብለዋል፡
«إِنَّ بَيْنَ الرَّجُلِ وَبَيْنَ الشِّرْكِ وَالْكُفْرِ تَرْكُ الصَّلَاةِ».
«በሰውየውና በሺርክ፣ በክህደት መካከል ያለው (ግርዶ) ሶላትን መተው ነው።»15
ከቡረይዳ - አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላቸውና- እንደተላለፈው የአላህ መልዕክተኛ ﷺ እንዲህ ብለዋል፦
«العَهْدُ الَّذِي بَيْنَنَا وَبَيْنَهُمُ الصَّلَاةُ، فَمَن تَرَكَهَا فَقَدْ كَفَرَ».
«በእኛና በነሱ መካከል ያለው ቃል ኪዳን ሰላት ነው። (በመሆኑም) ሰላትን የተወ ሰው በእርግጥ ክዷል።»16
ዑለማዎች ባጠቃላይ የሶላትን ግዴታነት የካደ ሰው እንደሚከፍር ተስማምተዋል። በስንፍናና በማቃለል የተወ ሰውም የተሻለው አቋም እሱም ይከፍራል የሚለው ነው። ይህም ቀደም ብሎ በተጠቀሰው ሐዲሥ መሰረትና ሶሓቦችም በዚህ ላይ ስለተስማሙ ነው።
ሶስተኛ: የሶላት ቅድመ መስፈርቶች
1: ወቅቱ መግባት አለበት:
ምክንያቱም የላቀው አላህ እንዲህ ብሏልና፦
﴿...إِنَّ ٱلصَّلَوٰةَ كَانَتۡ عَلَى ٱلۡمُؤۡمِنِينَ كِتَٰبٗا مَّوۡقُوتٗا﴾
{ሶላት በምእምናን ላይ በጊዜያት የተወሰነች ግዴታ ናትና።} [አን'ኒሳእ] ማለትም በተገደቡ ወቅቶች ግዴታ ተደርጋለች ማለት ነው።
የግዴታ ሶላቶች ወቅት እንደሚከተለው ነው:
ሀ) ፈጅር: ጎህ ከቀደደበት አንስቶ ፀሐይ እስክትወጣ ድረስ፤
ለ) ዝሁር: ፀሐይ ወደ መግቢያዋ ከተዘነበለችበት አንስቶ የሁሉም ነገር ጥላ ርዝመት አምሳያውን እስከሚሆን ድረስ፤
መ) ዐስር: የዝሁር ወቅት ከተጠናቀቀበት አንስቶ ፀሐይ ወደቢጫ ቀለም እስክትለወጥ ድረስ ሲሆን ለዓስር የተጨናነቀ ወቅት ደግሞ ፀሐይ እስክትገባ ድረስ ነው፤
ሰ) መግሪብ: ፀሐይ ከገባችበት ወቅት አንስቶ ቀዩ ወጋገን እስኪገባ ድረስ፤
ረ) ዒሻእ: የመግሪብ ወቅት ከተጠናቀቀበት ጊዜ አንስቶ እስከ ሌሊቱ አጋማሽ ድረስ ነው።
2: ሀፍረተ ገላን መሸፈን:
ሀፍረተ ገላ ማለት መሸፈን ግዴታ የሚሆነውና መገለጡ የሚቀፈው እንዲሁም ሲታይ የሚያሳፍረው የሰውነት አካል ነው። የወንድ ልጅ ሀፍረተ ገላ ከእምብርት እስከ ጉልበት ነው። ሶላት ውስጥ የሴት ሀፍረተ ገላ ደግሞ ከፊቷ በቀር ሁሉም የሰውነት አካሏ ነው። ባዳ ወንዶች ባሉበት ቦታ ከሆነ የምትሰግደው ፊቷንም ትሸፍናለች።
3: ከነጃሳ መራቅ:
ነጃሳ ማለት: ከሶላት የሚከለክል ልዩ የቆሻሻ አይነት ነው። ለምሳሌ: ሽንት፣ ሰገራ፣ ደምና ሌሎችም ይጠቀሳሉ። ሰውነትም፣ መስገጃ ስፍራም፣ ልብስም ላይ ሊሆን ይችላል።
4: ወደ ቂብላ መዞር:
ቂብላ የሚባለው የተከበረው ከዕባ ነው። ቂብላ (መቅጣጫ) የተባለበት ምክንያትም ሰዎች ወደርሱ ስለሚቅጣጩ ነው።
ወደ ቂብላ ሳይዞሩ የሚሰገድ ሶላት አይቆጠርም። ምክንያቱም የላቀው አላህ እንዲህ ብሏልና፦
﴿...وَحَيۡثُ مَا كُنتُمۡ فَوَلُّواْ وُجُوهَكُمۡ شَطۡرَهُ...﴾
{… የትም ስፍራ ብትሆኑም (ስትሰግዱ) ፊቶቻችሁን ወደርሱ አቅጣጫ አዙሩ። …} [አልበቀራህ:144]
5: ኒያህ:
ኒያ ማለት በቋንቋ ትርጓሜው ማሰብ ማለት ነው። በሸሪዓ ትርጓሜው ደግሞ ወደ አላህ መቃረብን በማሰብ አምልኮን የመፈፀም ቁርጠኝነት ማለት ነው። የኒያ ቦታው ቀልብ ነው። ኒያን በአፍ መናገር አያስፈልግም። እንደውም ኒያን በአፍ መናገር ቢድዓ ነው።
አራተኛ: የሶላት ማእዘናት:
የሶላት ማዕዘናት አስራ አራት ናቸው:
የመጀመሪያው ማዕዘን: ለቻለ ሰው መቆም:
ምክንያቱም የላቀው አላህ እንዲህ ብሏልና፦
﴿...وَقُومُواْ لِلَّهِ قَٰنِتِينَ﴾
{…ታዛዦች ኾናችሁም ለአላህ ቁሙ፡፡} [አል‐በቀራህ: 203] በዒምራን -አላህ መልካም ስራውን ይውደድለትና- ሐዲስ ከነቢዩም ﷺ እንዲህ የሚል ተዘግቧል:
«صَلِّ قَائِمًا، فَإِن لَمْ تَسْتَطِعْ فَقَاعِدًا، فَإِن لَمْ تَسْتَطِعْ فَعَلَى جَنْبٍ».
«ቁመህ ስገድ! ካልቻልክ ተቀምጠህ ስገድ! ካልቻልክ በጎንህ ተጋድመህ ስገድ።»17
በበሽታ ምክንያት መቆም ያልቻለ ሰው እንደየሁኔታው ተቀምጦ ወይም በጎኑ ተጋድሞ ይሰግዳል። እንደ ህመምተኛ ሁሉ የፈራ፣ የተራቆተ ሰው፣ ለህክምና ሲባል መቀመጥ ወይም መጋደም እንጂ መቆም የሚከለከልም ቁጭ ብሎ መስገድ አለበት። ልክ እንደዚሁ የመስጂድ መደበኛ ኢማም ቆሞ ማሰገድ ካቃተው ከሱ ኋላ የሚሰግድ ሰው ቁጭ ብሎ ቢሰግድ ይፈቀድለታል። ኢማሙ ቁጭ ብሎ ካሰገደ ከኋላው ያሉትም ኢማማቸውን ተከትለው ቁጭ ብለው ይሰግዳሉ። መቆም የቻለ ሰው ሱና ሶላትን ተቀምጦ መፈፀምም ይፈቀድለታል። ነገር ግን ቆሞ የሰገደ ሰው የሚያገኘውን ያህል ምንዳ አያገኝም።
ሁለተኛው ማዕዘን: መጀመሪያ ላይ የመክፈቻ ተክቢራ ማለት፤
ነቢዩ ﷺ እንዲህ ብለዋልና:
«ثُمَّ اسْتَقْبِلِ الْقِبْلَةَ، وَكَبِّرْ».
«ከዚያም ወደ ቂብላ ዙርና ተክቢራ በል!»18
የተክቢራ ይዘቱም (አላሁ አክበር) ማለት ነው። ከዚህ ቃል ውጪ ቢል አይቆጠርለትም።
ሶስተኛው ማዕዘን: ፋቲሓን መቅራት:
ነቢዩ ﷺ እንዲህ ብለዋልና:
«لَا صَلَاةَ لِمَنْ لَمْ يَقْرَأْ بِفَاتِحَةِ الْكِتَابِ».
«የመጽሐፉን መክፈቻ (ፋቲሓን) ያልቀራ ሰው ሰላት የለውም።»19
አራተኛው ማዕዘን: በየሁሉም ረከዓ ሩኩዕ መውረድ ነው።
ምክንያቱም የላቀው አላህ እንዲህ ብሏልና፦
﴿يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا ارْكَعُوا وَاسْجُدُوا...﴾
{እናንተ ያመናችሁ ሰዎች ሆይ! (በስግደታችሁ) አጎንብሱ፣ በግንባራችሁም ተደፉ …} [አልሐጅ: 77]
አምስተኛውና ስድስተኛው ማዕዘኖች:
ከሩኩዕ መነሳትና ከሩኩዕ በፊት እንደነበረው ሁኔታ ቀጥ ብሎ መቆም: ነቢዩ ﷺ ይህንን በመፈፀም ዘውትረዋልና ነው።
ነቢዩ ﷺ ሶላቱ ለተበላሸበት ሰው እንዲህ ብለውታል:
«ثُمَّ ارْفَعْ حَتَّى تَعْتَدِلَ قَائِمًا».
«ከዚያም ተስተካክለህ እስክትቆም ድረስ ተነሳ!»20
ሰባተኛው ማዕዘን: ሶላት ላይ በሰባት አካላት ሱጁድ ማድረግ :
እነዚህ ሰባት አካላትም: ግንባራችን አፍንጫችንን አክሎ፣ ሁለቱ መዳፎቻችን፣ ሁለቱ ጉልበቶቻችንና የሁለቱ እግር ጣቶች ናቸው። ነቢዩ ﷺ እንዲህ ብለዋልና:
«أُمِرْنَا أَنْ نَسْجُدَ عَلَى سَبْعَةِ أَعْظُمٍ: الجَبْهَةِ، وَأَشَارَ بِيدِهِ عَلَى أَنْفِهِ، وَالكَفَّيْنِ، وَالرُّكْبَتَيْنِ، وَأَطْرَافِ القَدَمَيْنِ».
«በሰባት አጥንቶቼ ሱጁድ እንዳደርግ ታዝዣለሁ። በግንባሬ ብለው በእጃቸው ወደ አፍንጫቸው አመላከቱ፣ በሁለቱ እጆቼ፣ በሁለቱ ጉልበቴ፣ በሁለቱ የእግር ጣቶቼ ፤»21
ስምንተኛው ማዕዘን: ከሱጁድ መነሳትና በሁለቱ ሱጁዶች መካከል መቀመጥ ነው።
ዓኢሻ -አላህ መልካም ሥራዋን ይውደድላትና- ባስተላለፈችው ሐዲሥ፦
«كَانَ النَّبِيُّ ﷺ إِذَا رَفَعَ رَأْسَهُ مِنَ السَّجْدَةِ، لَمْ يَسْجُدْ حَتَّى يَسْتَوِيَ جَالِسًا».
«ነቢዩ ﷺ ጭንቅላታቸውን ከሱጁድ ቀና ያደረጉ ጊዜ ተስተካክለው እስኪቀመጡ ድረስ ሱጁድን አይወርዱም ነበር።»22
ዘጠነኛው ማዕዘን: በሁሉም ማዕዘናት መረጋጋት፤
ሰከን ማለት: ላነሰ ጊዜ ቢሆንም እንኳ መርጋት ማለት ነው። ነቢዩ ﷺ ሶላቱ ለተበላሸበት ሰውዬ እንዲህ ብለውታልና:
«حَتَّى تَطْمَئِنَّ».
«እስክትረጋጋ ድረስ»23
አስረኛና አስራ አንደኛ ማዕዘኖች:
የመጨረሻው ተሸሁድና ለርሱ መቀመጥ: ኢብኑ መስዑድ - አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና - ከነቢዩ ﷺ ባስተላለፉት ሐዲሥ እንዲህ ብለዋልና:
«إِذَا صَلَّى أَحَدُكُمْ فَلْيَقُلْ: التَّحِيَّاتُ لِلَّهِ وَالصَّلَوَاتُ وَالطَّيِّبَاتُ، السَّلَامُ عَلَيْكَ أَيُّهَا النَّبِيُّ وَرَحْمَةُ اللَّهِ وَبَرَكَاتُهُ، السَّلَامُ عَلَيْنَا وَعَلَى عِبَادِ اللَّهِ الصَّالِحِينَ، أَشْهَدُ أَنْ لَا إِلٰهَ إِلَّا اللَّهُ وَأَشْهَدُ أَنَّ مُحَمَّدًا عَبْدُهُ وَرَسُولُهُ».
«አንዳችሁ የሰገደ ጊዜ እንዲህ ይበል: “አት‐ተሒያቱ ሊላሂ ወስ‐ሶላዋቱ ወጥ‐ጠይ‐ዪባቱ፣ አስ‐ሰላሙ ዐለይከ አይዩሀን-ነቢይዩ ወረሕመቱልላሂ ወበረካቱሁ፤ አስሰላሙ ዐለይና ወዐላ ዒባዲላሂ አስሷሊሒነ፣ አሽሀዱ አንላኢላሀ ኢልለልላህ ወአሽሀዱ አንነ ሙሐመደን ዐብዱሁ ወረሱሉሁ።”»24 “ትርጉሙም: ክብርና ልዕልና እንዲሁም ሶላቶችና መልካም ነገሮች ሁሉ ለአላህ ናቸው። አንቱ ነቢዩ ሆይ! የአላህ ሰላም፣ እዝነቱና በረከቶች በእርሶ ላይ ይስፈን፤ ሰላም በእኛና በአላህ ደጋግ ባሮችም ላይ ይስፈን፤ ከአላህ ሌላ በእውነት የሚመለክ አምላክ እንደሌለ እመሰክራለሁ፤ ሙሐመድም የአላህ ባርያና መልዕክተኛው መሆናቸውንም እመሰክራለሁ።” ማለት ነው።
አስራ ሁለተኛ ማዕዘን: በመጨረሻው ተሸሁድ ወቅት በነቢዩ ﷺ ላይ ሶላት ማውረድ:
ሶላት ማውረድ ሲባል እንዲህ ማለቱ ነው :
«اللَّهُمَّ صَلِّ عَلَى مُحَمَّدٍ».
"አልላሁምመ ሶሊ ዐላ ሙሐመዲን"25 ከዚህ በላይ ያለው ሱና ነው።
አስራ ሶስተኛ ማዕዘን: በማዕዘናት መካከል ቅደም ተከተልን መጠበቅ:
ነቢዩ ﷺ ሶላትን በቅደም ተከተል ነበርና የሚፈፅሙት። እንዲህም ብለዋል፦
«صَلُّوا كَمَا رَأَيْتُمُونِي أُصَلِّي».
«(አሰጋገዴን) ስሰግድ እንዳያችሁት አድርጋችሁ ስገዱ።»26 ሶላቱ ለተበላሸበት ሰውዬ ሶላትን "ከዚያም" እያሉ በቅደም ተከተል ነው ያስተማሩት።
አስራ አራተኛ ማዕዘን: ማሰላመት:
ነቢዩ ﷺ እንዲህ ብለዋልና:
««وَخِتَامُهَا التَّسْلِيمُ».
«የሶላት ማገባደጃ ማሰላመት ነው።» እንዲህም ብለዋል:
«وَتَحْلِيلُهَا التَّسْلِيمُ».
«መፈቻው ማሰላመት ነው።»27
አምስተኛ: የሶላት ግዴታዎች:
ስምንት ናቸው:
1: ከተክቢረተል ኢሕራም ውጪ ያሉ ሁሉም ተክቢራዎች፤
2: በማጎንበስ ወቅት አንድ ጊዜ «ሱብሓነ ረቢየል ዓዚም» ማለት፤ እስከ ሶስት ድረስ መጨመሩ ሱና ነው። ይህም አነስተኛው ሙሉ ነው። እስከ አስር ድረስ ደግሞ የመጨረሻው ሙሉ ነው።
3: ኢማምም ሆነ ብቻውን የሚሰግድ ሰው ከሩኩዕ በሚነሳ ወቅት «ሰሚዓሏሁ ሊመን ሐሚደህ» ማለት፤
4: ከሩኩዕ ቀና በሚሉበት ወቅት «ረበና ወለከል ሐምድ» ማለት፤
5: በሱጁድ ወቅት አንድ ጊዜ «ሱብሓነ ረቢየል አዕላ» ማለት፤ እስከ ሶስት መጨመር ሱና ነው።
6: በሁለቱ ሱጁዶች መካከል አንድ ጊዜ «ረቢግፊርሊ» ማለት፤ እስከ ሶስት ድረስ መጨመር ሱና ነው።
7: የመጀመሪያውን ተሸሁድ ማለት: እሱም እንዲህ ማለቱ ነው:
«التَّحِيَّاتُ لِلَّهِ، وَالصَّلَوَاتُ وَالطَّيِّبَاتُ، السَّلَامُ عَلَيْكَ أَيُّهَا النَّبِيُّ وَرَحْمَةُ اللَّهِ وَبَرَكَاتُهُ، السَّلَامُ عَلَيْنَا وَعَلَى عِبَادِ اللَّهِ الصَّالِحِينَ، أَشْهَدُ أَنْ لَا إِلٰهَ إِلَّا اللَّهُ وَأَشْهَدُ أَنَّ مُحَمَّدًا عَبْدُهُ وَرَسُولُهُ».
“አት‐ተሒያቱ ሊላሂ ወስ‐ሶላዋቱ ወጥ‐ጠይ‐ዪባቱ፣ አስ‐ሰላሙ ዐለይከ አይዩሀን-ነቢይዩ ወረሕመቱልላሂ ወበረካቱሁ፤ አስሰላሙ ዐለይና ወዐላ ዒባዲላሂ አስሷሊሒነ፣ አሽሀዱ አንላኢላሀ ኢልለልላህ ወአሽሀዱ አንነ ሙሐመደን ዐብዱሁ ወረሱሉሁ።”28 “ትርጉሙም: ክብርና ልዕልና እንዲሁም ሶላቶችና መልካም ነገሮች ሁሉ ለአላህ ናቸው። አንቱ ነቢዩ ሆይ! የአላህ ሰላም፣ እዝነቱና በረከቶች በእርሶ ላይ ይስፈን፤ ሰላም በእኛና በአላህ ደጋግ ባሮችም ላይ ይስፈን፤ ከአላህ ሌላ በእውነት የሚመለክ አምላክ እንደሌለ እመሰክራለሁ፤ ሙሐመድም የአላህ ባርያና መልዕክተኛው መሆናቸውንም እመሰክራለሁ።” ማለት ነው።
8: ለመጀመሪያው ተሸሁድ መቀመጥ፤
ስድስተኛ: የሶላት ሱናዎች:
የሶላት ሱናዎችን በመተው ሶላት አይበላሽም። የሶላት ሱናዎች በሁለት ይከፈላሉ: ንግግራዊ ሱናዎችና ድርጊታዊ ሱናዎች ናቸው።
የመጀመሪያው: ንግግራዊ ሱናዎች:
1: የመክፈቻ ዱዓ: ይህም በርካታ ይዘቶች አሉት። ከነርሱም መካከል:
«سُبْحَانَكَ اللَّهُمَّ وَبِحَمْدِكَ، وَتَبَارَكَ اسْمُكَ، وَتَعَالى جَدُّكَ، وَلا إِلٰهَ غَيْرُكَ».
«ሱብሓነከ አልላሁምመ ወቢሐምዲከ፤ ወተባረከ ኢስሙከ፤ ወተዐላ ጀዱከ፤ ወላኢላሃ ገይሩከ»29 ((ትርጉሙም: አላህ ሆይ! ጥራት ከምስጋና ጋር ላንተ የተገባ ነው፤ ስምህ የተባረከ ነው፤ ግርማህም ከፍ ያለ ነው፤ ካንተ በቀር በእውነት አምልኮ የሚገባው የለም።))
2: ከፋቲሓ በፊት የአላህን ጥበቃ መፈለግ፤ የአላህን ጥበቃ መፈለግ ማለት «አዑዙ ቢላሂ ሚነሽሸይጧኒር-ረጂም» ማለት ነው።
3: ፋቲሓን ከመቅራት በፊት በስመላህ ማለት: ይህም ማለት: «ቢስሚልላሂ አርረሕማኒር-ረሒም» ማለት ነው።
4: በሩኩዕና ሱጁድ ወቅት ከአንድ በላይ ተስቢሕ ማለት፤
5: በሁለቱ ሱጁዶች መካከል ከአንድ ጊዜ በላይ
«رَبِّ اغْفِرْ لِي».
«ረቢግፊርሊ» ማለት በሁለቱ ሱጁዶች መካከል
6: ይህን ማለት:
«مَلْءَ السَّمَاوَاتِ، وَمَلْءَ الْأَرْضِ، وَمَلْءَ مَا بَيْنَهُمَا، وَمَلْءَ مَا شِئْتَ مِنْ شَيْءٍ بَعْدُ».
«ሚልአስሰማዋቲ ወሚልአል አርዲ ወሚልአ ማበይነሁማ ወሚልአ ማሺእተ ሚን ሸይኢን በዕዱ» ትርጉሙም: «ምስጋና በሰማያት ሙሉ በምድር ሙሉ በመካከላቸው ባለው ሙሉ ላንተ ይሁን፤ ከዚያም በኋላ የሻኸውን ሙሉም ምስጋና ላንተ ይሁን።» ማለት ነው። ይህንንም የሚለው እንዲህ ካለ በኋላ ነው:
«رَبَّنَا ولَكَ الحَمْدُ».
"ረበና ወለከል ሐምድ"
ትርጉሙም: «ጌታችን ሆይ! ምስጋና የተገባህ ነህ።»30
7: ከፋቲሓ በኋላ መቅራት፤
8: እንዲህ ማለት:
«اللَّهُمَّ إِنِّي أَعُوذُ بِكَ مِنْ عَذَابِ جَهَنَّمَ، وَمِنْ عَذَابِ الْقَبْرِ، وَمِنْ فِتْنَةِ الْمَحْيَا وَالْمَمَاتِ، وَمِنْ فِتْنَةِ الْمَسِيحِ الدَّجَّالِ».
"አልላሁምመ ኢንኒ አዑዙ ቢከ ሚን ዐዛቢ ጀሀነም፣ ወሚን ዐዛቢል ቀብር፣ ወሚን ፊትነቲል መሕያ ወልመማት፣ ወሚን ፊትነቲል መሲሒ ደጃል"31 ትርጉሙም: (አሏህ ሆይ! እኔ ከጀሀነም ቅጣት፤ ከቀብር ቅጣትም፤ ከህይወትም ከሞትም ፈተና እንዲሁም ከመጥፎው የመሲሑ ደጃል ፈተናም ባንተው እጠበቃለሁ።) ማለት ነው። ከመጨረሻው ተሸሁድ በኋላ ከዚህ በላይ ዱዓ መጨመርም ሱና ነው።
ሁለተኛ: ድርጊታዊ ሱናዎች:
1: በአራት ስፍራዎች ሁለት እጆችን በትከሻ ትይዩ ወይም በሁለቱ ጆሮዎች ትይዩ ማንሳት ነው:
ሀ) ተክቢረተል ኢሕራም በሚልበት ወቅት፤
ለ) በሩኩዕ ወቅት፤
መ) ከሩኩዕ ቀና በሚልበት ወቅት፤
ሰ) ለሶስተኛ ረከዓ በሚቆም ወቅት፤
2: ከሩኩዕ በፊትም ሆነ በኋላ በሚቆም ወቅት ቀኝ እጅን ግራ እጅ ላይ በማኖር ደረት ላይ ማስቀመጥ፤
3: ወደ ሱጁድ ስፍራ መመልከት፤
4: በሱጁድ ወቅት ጡንቻዎችን ከጎንና ጎን ማራቅ፤
5: በሁለቱ ሱጁዶች ውስጥ ሆድን ከታፋዎች ማራራቅ፤
6: ሶላት ውስጥ በሚቀመጥባቸው ሁሉ ስፍራዎች የባለ ሶስት ረከዓና የባለአራት ረከዓ ሶላት ላይ የመጨረሻው ተሸሁድ እስካልሆነ ድረስ ግራ እግርን በማንጠፍ ቀኝ እግርን በመትከል መቀመጥ፤
7: ባለ ሶስትና ባለ አራት ረከዓ ላይ በመጨረሻው ተሸሁድ መቀመጥ ወቅት ግራ እግርን በቀኝ ባት ስር በማሳለፍ የቀኝ እግርን ተረከዝ ደግሞ በመትከል መሬት ላይ መቀመጥ።
ሰባተኛ: የሶላት አሰጋገድ:
1: የአላህ መልክተኛ ﷺ ለሶላት በቆሙ ወቅት ወደ ቂብላ ይዞሩና እጃቸውን በማንሳት የመዳፋቸውን የውስጥ ጣቶች ወደ ቂብላ በማዞር እንዲህ ይላሉ:
«اللهُ أَكْبَرُ».
«አላሁ አክበር»
2: ቀጥለው ግራቸውን በቀኝ በመያዝ ደረታቸው ላይ ያኖሩታል።
3: ቀጥለውም የመክፈቻ ዱዓ ይላሉ። በአንድ የመክፈቻ ዱዓ ብቻ አይገደቡም ነበር። ከርሳቸው በመጡ ሁሉ የመክፈቻ ዱዓዎች መጠቀም ይፈቀዳል። ከርሳቸው ከመጡ የመክፈቻ ዱዓዎች መካከልም:
«سُبْحَانَكَ اللَّهُمَّ وَبِحَمْدِكَ، وَتَبَارَكَ اسْمُكَ، وَتَعَالى جَدُّكَ، وَلَا إِلٰهَ غَيْرُكَ».
«ሱብሓነከ አልላሁመ ወቢሐምዲከ፤ ወተባረከ ኢስሙከ፤ ወተዓላ ጀዱከ፤ ወላኢላሃ ገይሩከ» ትርጉሙም "ትርጉሙም አሏህ ሆይ! ክብርና ምስጋና ላንተ ይሁን፤ ስምህ የተባረከ ነው፤ ልዕልናህም የተከበረ ነው፤ ካንተ በቀር በእውነት አምልኮ የሚገባው የለም።"
4: ቀጥሎ እንዲህ ይላል:
«أَعُوذُ بِاللَّهِ مِنَ الشَّيْطَانِ الرَّجِيمِ، بِسْمِ اللَّهِ الرَّحْمَٰنِ الرَّحِيمِ».
"አዑዙ ቢላሂ ሚነ ሸይጧኒ-ር-ረጂም ቢስሚላሂር-ራሕማኒር-ረሒም" ትርጉሙም፦ "ከተረገመው ሰይጣን በአላህ እጠበቃለሁ። በአላህ ስም እጅግ በጣም አዛኝና ሩሕሩሕ በሆነው እጀምራለሁ።"
5: ቀጥሎ ፋቲሓን ይቀራል። ፋቲሓን ሲያጠናቅቅ «አሚን» ይላል።
6: ከዚያም የገራለትን ከቁርአን ይቀራል። በፈጅር እና በመግሪብና ዒሻእ የመጀመሪያዎቹ ሁለት ረከዓ ድምፁን ከፍ ያደርጋል። ከዛ ውጪ ባሉት ድምፁን ዝግ አድርጎ ይቀራል። በየሁሉም ሶላት የመጀመሪያውን ረከዓ ከሁለተኛው ረከዓ ያረዝማል።
7: ቀጥሎ ሶላቱን ሲጀምር እንዳደረገው ሁለቱን እጆቹን ከፍ ያደርጋል። ከዚያም «አላሁ አክበር» ይላል። ወደ ሩኩዕም ይወርዳል። እጆቹንም ጣቶቹን ከፋፍቶ በጉልበቶቹ ላይ አመቻችቶ ያኖራል። ጀርባውንም ይዘረጋል። ጭንቅላቱንም ትይዩ ያደርገዋል። አያንጋጥጥምም አያቀረቅርምም። አንድ ጊዜ እንዲህ ይላል:
«سُبْحَانَ رَبِّيَ الْعَظِيمِ» مرةً.
«ሱብሓነ ረቢየል ዓዚም» ትርጉሙም፡ ታላቁ አላህ ጥራት ይገባው። ቀደም ብሎ እንደተጠቀሰው በትንሹ ሙሉ የሚባለው ሶስት ጊዜ ማለት ነው።
8: ቀጥሎ እንዲህ እያለ ጭንቅላቱን ቀና ያደርጋል:
«سَمِعَ اللَّهُ لِمَنْ حَمِدَهُ».
«ሰሚዐሏሁ ሊመን ሐሚደህ» ትርጉሙም (አላህ ያመሰገነውን ሰሚ ነው።) ማለት ነው። እጆቹን ልክ በሩኩዕ ወቅት ከፍ እንዳደረገው አሁንም ያደርጋል።
9: ተስተካክሎ እንደቆመ እንዲህ ይላል:
«اللَّهُمَّ رَبَّنَا وَلَكَ الْحَمْدُ، حَمْدًا كَثِيرًا طَيِّبًا مُبَارَكًا فِيهِ، مَلْءَ السَّمَاءِ، وَمَلْءَ الْأَرْضِ، وَمَلْءَ مَا بَيْنَهُمَا، وَمَلْءَ مَا شِئْتَ مِنْ شَيْءٍ بَعْدُ، أَهْلَ الثَّنَاءِ وَالْمَجْدِ، أَحَقُّ مَا قَالَ الْعَبْدُ، وَكُلُّنَا لَكَ عَبْدٌ، لَا مَانِعَ لِمَا أَعْطَيْتَ، وَلَا مُعْطِيَ لِمَا مَنَعْتَ، وَلَا يَنْفَعُ ذَا الْجَدِّ مِنْكَ الْجَدُّ».
(አልላሁመ ረብበና ወለከል ሐምዱ ሐምደን ከሢረን ጠዪበን ሙባረከን ፊህ፤ ሚልአ'ስሰማዋቲ ወሚልአል አርዲ ወሚልአ ማበይነሁማ ወሚልአ ማሺእተ ሚን ሸይኢን በዕዱ አህለሥ-ሠናኢ ወልመጅዲ፣ አሐቁ ማቃለል ዐብዱ ወኩሉና ለከ ዐብዱን፤ ላ ማኒዐ ሊማ አዕጠይተ፣ ወላ ሙዕጢየ ሊማ መነዕተ፣ ወላ የንፈዑ ዘልጀዲ ሚንከል ጀድ)32 ትርጉሙም (ጌታችን ሆይ! ምስጋና ላንተ የተገባ ነው። ላንተ የበዛ፣ ምርጥ የሆነ፣ የተባረከ፣ ሰማያትን የሞላ ምድርንም የሞላና በመካከላቸው ያለውንም የሞላ ከዚህም ሁሉ ኃላ ከነገሮች ሁሉ አንተ የፈለግከውን የሞላ ምስጋና የተገባህ ነህ። የውደሳና የልቅና ባለቤት ነህ። ሁላችንም ላንተ ባሪያዎች ከመሆናችንም ጋር ባሪያው ከተናገራቸው እጅግ ተገቢው ንግግር "አላህ ሆይ! አንተ ለሰጠኸው ከልካይ የለውም። አንተ ለከለከልከውም ሰጪ የለውም። የልቅና ባለቤትም ልቅናው አይጠቅመውም፤ ልቅናም ካንተው ነው።) ማለት ነው። ይህንንም መቆም ያረዝሙት ነበር።
10: ከዚያም ተክቢራ በማለት ወደ ሱጁድ ይወርዳል። እጁንም አያነሳም። በግንባሩ፣ በአፍንጫው፣ በእጆቹ፣ በጉልበቶቹና በእግሮቹ ጣቶች ሱጁድ ይወርዳል። በእጆቹና በእግሮቹ ጣቶችም ወደ ቂብላ ይዞራል። በሱጁድም ወቅት ቀጥ ይላል። ግንባሩንና አፍንጫውንም መሬት ላይ ያመቻቻል። በመዳፎቹ ላይም ይደገፍና ክንዱን ከፍ ያደርጋል። ጡንቻዎቹንም ከጎንና ጎኖቹ ያራርቃል። ሆዱንም ከታፋዎቹ ከፍ ያደርጋል። ታፋዎቹንም ከባቱ ያራርቃል። በሱጁድ ወቅትም እንዲህ ይላል:
«سُبْحَانَ رَبِّيَ الأَعْلَى».
«ሱብሓነ ረቢየል አዕላ» ትርጉሙም፡ ልዑሉ ጌታዬ ጥራት ይገባው። አንድ ጊዜ ቀደም ብሎ እንደተጠቀሰው በትንሹ ሙሉ የሚባለው ሶስት ጊዜ ማለት ነው። በሐዲሥ ውስጥና ቁርአን ውስጥ በመጡ ዱዓዎችም ያደርጋል።
11: ከዚያም «አላሁ አክበር» በማለት ጭንቅላቱን ያነሳል። ከዚያም ግራ እግሩን በማንጠፍ ይቀመጥባታል። ቀኙን ደግሞ ይተክላታል። እጆቹን ታፋዎቹ ላይ በማኖር ቀጥሎ እንዲህ ይላል:
«اللَّهُمَّ اغْفِرْ لِي، وَارْحَمْنِي، وَاجْبُرْنِي، وَاهْدِنِي، وَارْزُقْنِي».
"አልላሁምመ-ግፊርሊ ወርሐምኒ ወጅቡርኒ ወህዲኒ ወርዙቅኒ"33 ትርጉሙም: ‹‹አላህ ሆይ! ኃጢአቴን ማረኝ፤ እዘንልኝም፤ ድክመቴንም ጠግነኝ፤ ምራኝም፤ ሲሳይም ለግሰኝ፡፡››
12: ቀጥሎ ተክቢራ በማለት ሱጁድ ይወርዳል። በሁለተኛውም ሱጁድ በመጀመሪያው ሱጁድ ወቅት ያደረገውን አምሳያ ይፈፅማል።
13: ቀጥሎ ተክቢራ በማለት ራሱን ቀና ያደርጋል። ጉልበቱንና ታፋውን ደገፍ ብሎ ከእግሮቹ መጀመሪያ ይነሳል።
14: ተስተካክሎ ከቆመ በኋላ መቅራት ይጀምራል። ልክ እንደ መጀመሪያው ረከዓ አድርጎ ሁለተኛውንም ረከዓ ይሰግዳል።
15: ቀጥሎ በሁለቱ ሱጁዶች መካከል በተቀመጠው መልኩ ለመጀመሪያው ተሸሁድ እግሩን አንጥፎ ይቀመጣል። ቀኝ እጁን ቀኝ ታፋው ላይ ያኖራል። ግራ እጁንም ግራ ታፋው ላይ ያኖራል። የቀኝ እጁን አውራ ጣት በቀኝ እጁ መሃል ጣት ላይ በማኖር ክብ ይሰራል። መጠቆሚያ ጣቱንም በመዘርጋት ወደርሷ ይመለከታል። እንዲህም ይላል:
«التَّحِيَّاتُ لِلَّهِ وَالصَّلَوَاتُ وَالطَّيِّبَاتُ، السَّلَامُ عَلَيْكَ أَيُّهَا النَّبِيُّ وَرَحْمَةُ اللَّهِ وَبَرَكَاتُهُ، السَّلَامُ عَلَيْنَا وَعَلَى عِبَادِ اللَّهِ الصَّالِحِينَ، أَشْهَدُ أَنْ لَا إِلٰهَ إِلَّا اللَّهُ وَحْدَهُ لَا شَرِيكَ لَهُ، وَأَشْهَدُ أَنَّ مُحَمَّدًا عَبْدُهُ وَرَسُولُهُ».
“አት‐ተሒያቱ ሊላሂ ወስ‐ሶላዋቱ ወጥ‐ጠይ‐ዪባቱ፣ አስ‐ሰላሙ ዐለይከ አይዩሀን-ነቢይዩ ወረሕመቱልላሂ ወበረካቱሁ፤ አስሰላሙ ዐለይና ወዐላ ዒባዲላሂ አስሷሊሒነ፣ አሽሀዱ አንላኢላሀ ኢልለልላህ ወሕደሁ ላሸሪከ ለህ ወአሽሀዱ አንነ ሙሐመደን ዐብዱሁ ወረሱሉሁ።” “ትርጉሙም: ክብርና ልዕልና እንዲሁም ሶላቶችና መልካም ነገሮች ሁሉ ለአላህ ናቸው። አንቱ ነቢዩ ሆይ! የአላህ ሰላም፣ እዝነቱና በረከቶች በእርሶ ላይ ይስፈን፤ ሰላም በእኛና በአላህ ደጋግ ባሮችም ላይ ይስፈን፤ ከአላህ ሌላ በእውነት የሚመለክ አምላክ እንደሌለና ብቸኛና አጋር እንደሌለው እመሰክራለሁ፤ ሙሐመድም የአላህ ባርያና መልዕክተኛው መሆናቸውንም እመሰክራለሁ።” ማለት ነው። ይህንን መቀመጥ ቀለል ያደርጉት ነበር።
16: ከዚያም ተክቢራ በማለት ይነሳል። ሶስተኛና አራተኛ ረከዓም ይሰግዳል። ከመጀመሪያዎቹ ሁለት ረከዓ ቀለል ያደርጋቸዋል። በነዚህም ረከዓዎች ፋቲሓን ብቻ ይቀራል።
17: ቀጥሎ ለመጨረሻው ተሸሁድ እንደተቀመጠው (የተወሩክ አቀማመጥ) በመቀመጫው ይቀመጣል። ተወሩክ የሚባለው አቀማመጥ ግራ እግሩን በማንጠፍ በቀኝ ጎን በኩል ያወጣታል። የቀኙን ተረከዝም ይተክላታል። መቀመጫውንም መሬት ላይ ያሳርፋል።
18: ቀጥሎ የመጨረሻውን ተሸሁድ ይላል። እርሱም እንደ መጀመሪያው ተሸሁድ ነው። በተጨማሪም:
«اللَّهُمَّ صَلِّ عَلَى مُحَمَّدٍ وَعَلَى آلِ مُحَمَّدٍ، كَمَا صَلَّيْتَ عَلَى آلِ إِبْرَاهِيمَ، إِنَّكَ حَمِيدٌ مَجِيدٌ، وَبَارِكْ عَلَى مُحَمَّدٍ وَعَلَى آلِ مُحَمَّدٍ، كَمَا بَارَكْتَ عَلَى آلِ إِبْرَاهِيمَ، إِنَّكَ حَمِيدٌ مَجِيدٌ».
“አልላሁመ ሰሊ ዐላ ሙሐመድ ወዐላ ኣሊ ሙሐመድ ከማ ሰለይተ ዐላ ኢብራሂም ወዐላ ኣሊ ኢብራሂም ኢንነከ ሐሚዱን መጂድ ወባሪክ ዐላ ሙሐመድ ወዐላ ኣሊ ሙሐመድ ከማ ባረክተ ዐላ ኢብራሂም ወዐላ ኣሊ ኢብራሂም ኢንነከ ሐሚዱን መጂድ።” ይላል። (ትርጉሙም፡ አላህ ሆይ! በኢብራሂምና በቤተሰቦቻቸው ላይ ውዳሴህን እንዳወረድክ ሁሉ በሙሐመድና በቤተሰቦቻቸው ላይም ውዳሴህን አውርድ፤ አንተ ምስጉንና የላቅክ አምላክ ነህና። አላህ ሆይ! በኢብራሂምና በቤተሰቦቻቸው ላይ በረከትህን እንዳሰፈንክ ሁሉ በሙሐመድና በቤተሰቦቻቸው ላይም በረከትህን አዉርድ። አንተ ምስጉንና የላቅክ አምላክ ነህና።) ማለት ነው።
19: አላህንም ከጀሃነም ቅጣት፣ ከቀብር ቅጣት፣ ከህይወትና ሞት ፈተና፣ ከመሲሕ ደጃል ፈተና እንዲጠብቀው ይማፀናል። ቁርአንና ሐዲሥ ውስጥ የመጡ ሌሎች ዱዓዎችንም ያደርጋል።
20: ከዚያም ወደ ቀኝ ዞሮ እንዲህ በማለት ያሰላምታል:
«السَّلاَمُ عَلَيْكُمْ وَرَحْمَةُ اللَّهِ».
"አስሰላሙ ዐለይኩም ወረሕመቱላህ" ትርጉሙም: የአላህ ሰላም እና እዝነት በእናንተ ላይ ይሁን! ወደ ግራውም በመዞር ተመሳሳዩን ይላል። ማሰላመቱን ወደ ቂብላ ዞሮ ይጀምርና እየዞረ ይጨርሰዋል።
ስምንተኛ: ሶላት ውስጥ የሚጠሉ ነገሮች:
1: አላስፈላጊ መዞር
2: ዓይንን ወደ ሰማይ ማንጋጠጥ
3: ሳያስፈልግ ዓይኖችን መጨፈን
4: በሱጁድ ወቅት ክንዶችን ማንጠፍ
5: ሳያስፈልግ አፍና አፍንጫን መሸፈን
6: ሽንት ወይም ሰገራ እያጨናነቁት ወይም ሊበላው የሚፈልገው ምግብ ቀርቦ መስገድ
7: ሱጁድ ሲያደርግ ግንባርና አፍንጫው ላይ ተያይዞ የተነሳውን ከግንባሩና አፍንጫው መጥረግ። ሶላት ካጠናቀቀ በኋላ መጥረጉ ችግር የለውም።
8: አስፈላጊ ሆኖ ካልተገኘ በቀር በሚቆም ወቅት ግድግዳና መሰል ነገር መደገፉ ነው።
ዘጠነኛ: ሶላትን የሚያበላሹ ነገሮች:
1: መብላትና መጠጣት፤
2: የሶላቱ አካል ያልሆነን ንግግር መናገር፤
3: መሳቅና ከትከት ብሎ መሳቅ፤
4: የሶላትን አንዱን ማዕዘን ወይም ግዴታ ሆነብሎ መተው፤
5: አንድ ማዕዘን ወይም ረክዓ ሆነብሎ መጨመር፤
6: ከኢማም በፊት ሆነብሎ ማሰላመት፤
7: ከሶላቱ ውጪ የሆነን ብዙ እንቅስቃሴ ምንም ሳያስፈልገው አከታትሎ መንቀሳቀስ፤
8: ከሶላት መስፈርቶች መካከል አንዱን የሚፃረር ነገር መፈፀም፤ ለምሳሌ ያህል: ዉዱእ ማፍረስ፣ ሆነብሎ ሀፍረተ ገላን መግለጥ፣ ያለምንም አስገዳጅ ምክንያት የበዛን መዞር በሰውነቱ ከቂብላ መዞር፣ ኒያን ማቋረጥ ይጠቀሳሉ።
አስረኛ: የመርሳት ሱጁድ:
ነቢዩ ﷺ ሶላት ውስጥ የረሱበት አጋጣሚ አለ። መርሳት ሰው በመሆናችን የሚከሰት ተፈጥሯዊ ባህሪ ነው። የርሳቸው መርሳት አላህ በኡመቱ ላይ ከዋላቸው የተሟላ ፀጋና ለዚህ ኡመት ሃይማኖታቸውን ከመሙላቱ የሚመደብ ነው። ይህም የሆነው ሰዎች ሶላት ውስጥ በሚረሱ ወቅት አላህ የደነገገላቸውን ነገር በነቢዩ ﷺ እንዲከተሉ ማሳያ በመሆኑ ነው።
ሱጁድ አስሰህው የሚደነገግባቸው ምክንያቶች:
1: የመጀመሪያው ሁኔታ:
ሶላት ውስጥ መጨመር፤ ይህም ማለት ወይ ድርጊቶችን መጨመር ነው ወይም ንግግሮችን መጨመር ነው።
ሀ) ድርጊቶችን መጨመር: ጭማሪዋ የሶላቱ አካል ከሆነች ለምሳሌ ያህል: መቀመጥ ባለበት ቦታ ከቆመ፣ መቆም ባለበት ቦታ ከተቀመጠ፣ ሩኩዕ ወይም ሱጁድ ከጨመረ ይህንን ረስቶ የፈፀመ ሰው የመርሳት ሱጁድ ይወርዳል።
ለ) ንግግርን መጨመር: ሩኩዕ ውስጥና ሱጁድ ውስጥ ቁርአን መቅራትን ይመስል።
ይህንን የፈፀመ ጊዜ የመርሳት ሱጁድ መውረዱ ተወዳጅ ነው።
2: ሁለተኛው ሁኔታ:
በመርሳት ከሶላት ማጉደል። ይህም ከሁለት በአንዱ በኩል ይሆናል:
ሀ) አንድን ማዕዘን መተው: ይህ ማዕዘን የመክፈቻ ተክቢራ ከሆነ ከመነሻው ሶላቱ አልተጀመረም። ስለዚህ የመርሳት ሱጁድ መውረድ አይጠግነውም። የተወው ሩኩዕና ሱጁድን የመሰለ ከመክፈቻ ተክቢራ ውጪ የሆነ ማዕዘን ከሆነና የቀጣዩን ረከዓ ወደመቅራት ከመግባቱ በፊት መተውን ካስታወሰ ወደተወው ማዕዘን የግዴታ መመለስ አለበት። ከዛም የተወውንና ቀጥሎ መስራት ያለበትን ይፈፅማል።
የቀጣዩን ረከዓ መቅራት ከጀመረ በኋላ ካለፈው ረከዓ መተዉን ካስታወሰ ማዕዘኑን የተወበት ረከዓ ይበላሻል። አሁን ያለበት ረከዓ ደግሞ የተበላሸውን ረከዓ ቦታ ይይዛል።
ለ: ግዴታን መተው: ለምሳሌ:- የመጀመሪያውን ተሸሁድ መርሳት ወይም ሩኩዕ ላይ ተስቢሕ ማለትን መርሳት ነው። በዚህ ሁኔታ የመርሳት ሱጁድ መውረድ አለበት።
3: ሶስተኛው ሁኔታ: መጠራጠር፤
ለምሳሌ: ዝሁር ሶላት እየሰገደ ያለሁት ሶስተኛ ላይ ነው ወይስ አራተኛ ረከዓ የሚለውን ከተጠራጠረ በዚህ ወቅት:
ሀ- ከጥርጣሬዎቹ አንዱ እርሱ ዘንድ ሚዛን ከደፋ በዛ ይሰራና የመርሳት ሱጁድ ይወርዳል።
ለ - አንዱም ጥርጣሬው እርሱ ዘንድ ሚዛን ካልደፋ እርግጠኛ በሆነበት ነገር ላይ ተመስርቶ ይሰራና የመርሳት ሱጁድ ይወርዳል።
ጥርጣሬ የተፈጠረበት ከሶላት በኋላ ከሆነ ወይም በጣም ጥርጣሬ የሚበዛበት ሰው ከሆነ ጥርጣሬውን ዞርም ብሎ ማየት የለበትም።
ጠቃሚ ሃሳብ: የመርሳት ሱጁድ የሚያደርግበት ምክንያት በማጉደሉ ወይም በመጠራጠሩ ከሆነና እርሱ ዘንድ አንዱም ካላመዘነ የመርሳት ሱጁዱን የሚያደርገው ከማሰላመት በፊት ነው። የመርሳት ሱጁዱን የሚያደርግበት ምክንያት በጭማሪ ወይም ከመጠራጠሩም ጋር እርሱ ዘንድ ሚዛን በደፋው ተመስርቶ በሰራው የጥርጣሬ አይነት ከሆነ የመርሳት ሱጁድ የሚያደርገው ከማሰላመት በኋላ ይሆናል። በዚህ ዙሪያ በፈለገው አማራጭ ቢሰራም ጉዳዩ በአላህ ፍቃድ ሰፊ ነው።
አስራ አንድ: ሶላት መስገድ የሚከለከልባቸው ወቅቶች:
በመሰረቱ በሁሉም ወቅቶች ሶላት መስገድ ይፈቀዳል: ነገር ግን ሸሪዓ በተወሰኑ ወቅቶች ሶላት መስገድን ከልክሏል። እነርሱም የሚከተሉት ናቸው:
1 - ከፈጅር ሶላት በኋላ ፀሐይ እስክትወጣ ድረስና በአይን ግምት ከመሬት የጦር ያህል ከፍ እስክትል ድረስ፤
2 - ሰማዩ መሃል ላይ ስትሆን ወደ መግቢያዋ እስክትዘነበል ድረስ፤
3 - ከዐስር ሶላት በኋላ ፀሐይ እስክትገባ ድረስ፤ ይህ ከተከለከሉት ወቅቶች ሁሉ ረጅሙ ነው።
በተከለከሉት ወቅቶች መፈፀም የሚፈቀዱ ሶላቶች:
1 - ያመለጠ ግዴታ ሶላትን ቀዷእ ማውጣት፤
2 - ምክንያት ጋር የተቆራኙ ሶላቶች፤ ለምሳሌ ያህል:- ተሒየተል መስጂድ (መስጂድ ሲገባ የሚሰገድ)፣ የጦዋፍ ሁለት ረከዓ፣ የግርዶች ሶላት፣ የጀናዛ ሶላት ይጠቀሳሉ።
3 - ከፈጅር ሶላት በኋላ የፈጅር ሱናን ቀዷእ ማውጣት ነው።
አስራ ሁለተኛ: የጀመዓ (የህብረት) ሶላት:
ይህ ከእስልምና መገለጫዎች መካከል አንዱ መገለጫ ነው። እርሱም የጀማዓን ሶላት በመስጂዶች ውስጥ መፈፀም ነው። ሙስሊሞች ባጠቃላይ አምስት ወቅት ሶላቶችን በመስጂድ ውስጥ መፈፀም ጠንካራ ከሚባሉ አምልኮዎችና ትላልቅ ከሆኑ መቃረቢያዎች መካከል አንዱ እንደሆነ ተስማምተዋል። ከዛም በላይ ትልቁ የእስልምና መገለጫም ነው።
1: የጀማዓ ሶላት ብይን:
አቅም ባላቸው ወንዶች ላይ አምስቱን ሶላቶች መስጂድ ውስጥ በጀማዓ (በህብረት) መስገድ ግዴታ ነው። ሃገር ቤትም ሆኑ ጉዞም ላይ ሆኑ፣ በደህንነት ወቅትም ሆነ በአስፈሪ ወቅት በነፍስ ወከፍ ደረጃ ግዴታ ነው።
የጀማዓ (የህብረት) ሶላት ቁርአን፣ ሐዲሥና ከክፍለ ዘመን ክፍለ ዘመን የመጡት ቀደምቶችም ሆኑ ተተኪ ትውልድም ጭምር የመላ ሙስሊሞች ግዴታ መሆኑን በተግባር ያሳዩት ነው።
ከቁርአን: የሚከተለው የአላህ ንግግር ነው:
﴿وَإِذَا كُنتَ فِيهِمۡ فَأَقَمۡتَ لَهُمُ ٱلصَّلَوٰةَ فَلۡتَقُمۡ طَآئِفَةٞ مِّنۡهُم مَّعَكَ...﴾
{በውስጣቸውም በሆንክና ሶላትን ለነርሱ ባሰገድካቸው ጊዜ ከእነሱ አንዲት ጭፍራ ካንተ ጋር ትቁም። …} [አንኒሳእ: 102] ይህም አንቀፅ የጀማዓ ሶላት ግዴታነት አፅንዖት የተሰጠው መሆኑን ይጠቁማል። ይህም የሆነው በአስፈሪ ወቅትም እንኳን ቢሆን የጀማዓ ሶላትን እንዲተዉዋት ለሙስሊሞች አለመግራራቱ ነው። ግዴታ ባትሆን ኖሮ የጀማዓ ሶላትን ለማስቀረት እጅግ አሳሳቢው ምክንያት የስጋት ምክንያት ነበር። የጀማዓ ሶላትን መተውና ከጀማዓ ሶላት መቅረት ግልፅ የሆነ የሙናፊቅነት ምልክት ነው።
የሐዲሥ ማስረጃዎቹ ደግሞ እጅግ ብዙ ናቸው: ከነርሱም መካከል:
በሶሒሕ ሙስሊም እንደተዘገበው:
أَنَّ رَجُلًا أَعْمَى قَالَ: يَا رَسُولَ اللَّهِ، لَيْسَ لِي قَائِدٌ يَقُودُنِي إِلَى الْمَسْجِدِ، فَسَأَلَهُ أَنْ يُرَخِّصَ لَهُ أَنْ يُصَلِّيَ فِي بَيْتِهِ، فَرَخَّصَ لَهُ، فَلَمَّا وَلَّى دَعَاهُ فَقَالَ: «هَلْ تَسْمَعُ النِّدَاءَ؟» قَالَ: نَعَمْ، قَالَ: «فَأَجِبْ».
"አንድ ማየት የተሳነው ሰውዬ ነቢዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ዘንድ በመምጣት እንዲህ አለ: 'የአላህ መልክተኛ ሆይ! እኔ ወደ መስጂድ የሚመራኝ መሪ የለኝም።' በማለት የአላህ መልክተኛ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) በቤቱ መስገድን እንዲያገሩለት ጠየቀ። ለርሱም አግራሩለት። ለመሄድ የዞረ ጊዜ ጠሩትና 'የሶላትን ጥሪ ትሰማለህን?' አሉት። እርሱም 'አዎን' አላቸው። እሳቸውም 'እንግዲያውስ ለጥሪው መልስ ስጥ!' አሉት።"34
ዓይነ ስውር ከመሆኑ ጋርና በዚህም ምክንያት ሊያጋጥመው ከሚችለው መከራ ጋር ነቢዩ ﷺ ለጀመዓ ሶላት መስጂድ እንዲገኝና ለሶላት ጥሪ መልስ እንዲሰጥ አዘዙት። ይህም የጀመዓ ሶላት ግዴታ እንደሆነ ይጠቁማል።
2 - የጀመዓ ሶላት ላይ የሚደረሰው መቼ ነው?
የጀመዓ ሶላት ላይ የሚደረሰው ከኢማሙ ጋር (ቢያንስ) አንድ ረከዓ አብሮ መስገድ ከተቻለ ነው። ነቢዩ ﷺ እንዲህ ብለዋልና:
«مَنْ أَدْرَكَ رَكْعَةً مِنَ الصَّلَاةِ فَقَدْ أَدْرَكَ الصَّلَاةَ».
"የሰላትን አንድ ረከዓ ያገኘ ሰው ሰላቱን አግኝቷል።"35
3: ከኢማሙ ጋር አንድ ረከዓ አግኝቷል የሚባለውስ መቼ ነው?
ኢማሙ ጋር ሩኩዕ ላይ መሆን ከቻለ ከኢማሙ ጋር አንድ ረከዓ አግኝቷል። አንድ ኢማሙ ቀድሞት የጀመረ ሰው ኢማሙን ሩኩዕ ላይ ከደረሰበት በቅድሚያ በቆመበት የመክፈቻ ተክቢራ ማለት ግዴታው ነው። ከዚያም ለሩኩዕ ሌላ ተክቢራ በማለት ወደ ሩኩዕ ይወርዳል። በቆመበት የመክፈቻን ተክቢራ በማለት ላይ ብቻ ቢቆጠብም የሩኩዕ ተክቢራ ከማለት ያብቃቃዋል።
4 - አንድ ሰው የጀመዓን ሶላት ለማሳለፍ ፍቃድ የሚያሰጡት ምክንያቶች:
1 - ለጁመዓና ለጀማዓ ሶላት መገኘት እንዲከብደው የዳረገው ህመም፤
2 - ሽንት ወይም ሰገራ ካጨናነቀው፤ ምክንያቱም ውጥረት ላይ ከሆነ ሶላት ውስጥ ተመስጦውንም እንዲወገድ ይዳርጉታል፤ አካላዊ ጉዳትም ያስከትሉበታልና።
3 - ተርቦ ወይም ነፍሱ ምግቡን እየከጀለች ምግብ ከቀረበ፤ ነገር ግን ይህ መጥፎ ልማድ አድርጎ ካልያዘው ወይም ሆን ብሎ ከጀማዓ ሶላት ለመቅረት ዘዴ አድርጎ ካልያዘው ነው።
4 - ነፍሱ ላይ ወይም ገንዘቡ ላይ ወይም ከዚህም ውጪ ባሉ ነገሮቹ ላይ የተጋረጠ የተረጋገጠ ስጋት ካለ ነው።
አስራ ሶስተኛ: የስጋት ሶላት:
ከሃዲያንን፣ ወሰን አላፊዎችን፣ ወራሪዎችን በመሰሉ በሁሉም ፍቁድ ውጊያዎች ወቅት የፍርሃተረ ሶላትን መስገድ ይፈቀዳል። አላህ እንዲህ ብሏልና:
﴿...إِنۡ خِفۡتُمۡ أَن يَفۡتِنَكُمُ ٱلَّذِينَ كَفَرُوٓاْ...﴾
{…እነዚያ የካዱት ያውኩናል ብላችሁ ብትፈሩ ከሶላት (ባለ አራት ረከዓት የኾኑትን) ብታሳጥሩ በናንተ ላይ ኀጢአት የለም፡፡…} [አንኒሳእ:101] የተቀሩትን መዋጋት የተፈቀዱ ወገኖችን በዚህ ላይ ይቀየሳሉ።
ሁለት መስፈርቶች ከተሟሉ የፍርሃት ሶላት ይፈቀዳል:
1) ጠላቶቹ ከነርሱ ጋር መዋጋት የተፈቀዱ መሆን አለባቸው:
2) ሙስሊሞች በሶላት ላይ ሳሉ ጠላቶች በሙስሊሞች ላይ ጥቃት ይሰነዝራሉ ተብሎ በሚሰጋበት ልክ መሆን አለበት።
የፍርሃት ሶላት አሰጋገድ፤
የፍርሃት ሶላት የተለያየ አይነት አሰጋገድ ቢኖረውም የታወቀው አሰጋገድ በሰህል - አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና - የተዘገበው አሰጋገድ ነው:
أَنَّ طَائِفَةً صَفَّتْ مَعَ النَّبِي ﷺ، وَطَائِفَةً وِجَاهَ العَدُوِّ، فَصَلَّى بِالَّتِي مَعَهُ رَكْعَةً، ثُمَّ ثَبَتَ قَائِمًا، وَأَتَمُّوا لِأَنْفُسِهِمْ، ثُمَّ انْصَرَفُوا، وَصَفُّوا وِجَاهَ العَدُوِّ، وَجَاءَتِ الطَّائِفَةُ الأُخْرَى، فَصَلَّى بِهِمُ الرَّكْعَةَ الَّتِي بَقِيَتْ مِنْ صَلَاتِهِ، ثُمَّ ثَبَتَ جَالِسًا، وَأَتَمُّوا لِأَنْفُسِهِمْ، ثُمَّ سَلَّمَ بِهِمْ.
«አንዱ ጭፍራ ከነቢዩ ﷺ ጋር ሰልፍ ሰሩ። ሌላኛው ጭፍራ ደግሞ በጠላት አቅጣጫ ተሰለፉ። ነቢዩም ﷺ ከርሳቸው ጋር ካሉት ጋር አንድ ረከዓ ሰገዱና ከዚያም (ሁለተኛው ረከዓ) ላይ ባሉበት ቆሙ። (ከኋላቸው ያሉትም) በራሳቸው ሶላታቸውን ሞሉና ከዚያም በመሄድ በጠላት አቅጣጫ ሰልፍ ሰሩ። (በመጀመሪያው ረከዓ ወደ ጠላት ዙረው ሲጠብቁ የነበሩት) ሌላኛው ጭፍራ መጡ። ነቢዩ ﷺ የቀራቸውን አንድ ረከዓም ከነርሱ ጋር ሰገዱና ቁጭ ባሉበት ቆዩ። (ከኋላቸው ያሉትም) የራሳቸውን ሶላት ሞልተው ተሸሁድ ላይ ደረሱ። ነቢዩም ﷺ ከነርሱ ጋር አሰላመቱ።»36
ከፍርሃት ሶላት የምንጠቀማቸው ነገሮች:
1 - ሶላት በእስልምና ውስጥ ያለውን አንገብጋቢነት፣ በዚህ አስጨናቂ ሁኔታ ሳይቀር አለመቅረቷ የጀማዓ ሶላት ያለውን አንገብጋቢነት ያስረዳናል።
2 - እዚህ ኡመት ላይ ችግር መነሳቱ፣ የሸሪዓን ገርነትና ለሁሉም ዘመንና ስፍራ የሚበጅ መሆኑንም እንረዳለን።
3 - የእስልምና ሸሪዓ ምሉዕ መሆኑን እንረዳለን። እስላማዊ ሸሪዓ የተደነገገው ለሁሉም ሁኔታ የሚስማማ ሁኖ ነው።
አስራ አራተኛ: የጁመዓ ሶላት:
አንደኛ: ብይኑ:
የጁመዓ ሶላት በሁሉም ሙስሊም፣ ወንድ፣ አቅመ አዳም በደረሰ፣ አይምሮ ጤነኛ በሆነና የሚቀርበት በቂ ምክንያት በሌለው ሃገር ቤት ነዋሪ በሆነ ላይ ሁሉ የነፍስ ወከፍ ግዴታ ነው።
ምክንያቱም የላቀው አላህ እንዲህ ብሏልና፦
﴿يَٰٓأَيُّهَا ٱلَّذِينَ ءَامَنُوٓاْ إِذَا نُودِيَ لِلصَّلَوٰةِ مِن يَوۡمِ ٱلۡجُمُعَةِ فَٱسۡعَوۡاْ إِلَىٰ ذِكۡرِ ٱللَّهِ وَذَرُواْ ٱلۡبَيۡعَۚ ذَٰلِكُمۡ خَيۡرٞ لَّكُمۡ إِن كُنتُمۡ تَعۡلَمُونَ 9﴾
{እናንተ ያመናችሁ ሆይ! በዐርብ ቀን ለስግደት ጥሪ በተደረገ ጊዜ ወደ አላህ ማውሳት ኺዱ። መሸጥንም ተዉ። ይህ የምታውቁ ብትኾኑ ለእናንተ በጣም የተሻለ ነወ። 9} [አልጁምዓህ: 9]
ነቢዩም ﷺ እንዲህ ብለዋል:
«لَيَنْتَهِيَنَّ أَقْوَامٌ عَنْ وَدْعِهِمُ الْجُمُعَاتِ، أَوْ لَيَخْتِمَنَّ اللَّهُ عَلَى قُلُوبِهِمْ، ثُمَّ لَيَكُونُنَّ مِنَ الْغَافِلِينَ».
«ሰዎች ጁሙዓዎችን ከመተው ይከልከሉ! አለበለዚያ ግን አላህ በልቦቻቸው ላይ ያሽጋል። ከዚያም ከዝንጉዎች ይሆናሉ።»37
ሁለተኛ: የጁሙዓ ሶላት ትክክለኛ እንዲሆን መሟላት ያለባቸው መስፈርቶች:
ሀ) ወቅት: ወቅቱ የዝሁር ሶላት ወቅት ነው። ከወቅቱ በፊትም ሆነ ወቅቱ ከወጣ በኋላ ቢሰገድ አይቆጠርም።
2) በጀማዓ (በህብረት) መፈፀም አለበት: ትንሹ የጀማዓ መጠን በትክክለኛው አቋም መሰረት ሶስት ሰው መገኘቱ ነው። ጁሙዓን ብቻውን ወይም ለሁለት ቢሰግድ አይቆጠርለትም።
3) ሰጋጆቹ በተለምዶ በሚገነባው የቤት አገነባብ መሰረት አካባቢው ላይ ገንብተው የሚኖሩ መሆን አለበት። ይህም በሲሚንቶ ወይም በድንጋይ ወይም በጭቃና ከዛ ውጪም ባለ ሊሆን ይችላል። በዚህም መሰረት፤ ቋሚ በሆነ ቦታ ላይ ከማይኖሩ፣ ይልቁንም ለከብቶቻቸው ሳር (ግጦሽ) ፍለጋ ከቦታ ቦታ ከሚንቀሳቀሱ፣ የድንኳንና የፀጉር ቤት ባለቤቶች ከሆኑ ዘላኖች ሰዎች (ሶላቷ/ጁሙዓዋ) ተቀባይነት የላትም።
4) ሁለት ኹጥባዎች በቅድሚያ መደረግ አለበት። ይህም ነቢዩ ﷺ በዚህ ተግባር ላይ ስለዘወተሩ ነው።
ሶስተኛ: የሁለቱ የጁመዓ ኹጥባዎች ማዕዘናት:
1 - ምስጋና ለአላህ ማቅረብ (አልሐምዱ ሊላህ ማለት) እና ሁለቱን የምስክር ቃላቶች ማለት፤
2 - በነቢዩ ﷺ ላይ ሶላት ማውረድ፤
3 - አላህን በመፍራት ማዘዝ፤
4 - ከቁርአን የተወሰነ መቅራት፤
5 - ምክር መስጠት፤
አራተኛ: ሁለቱ የጁመዓ ኹጥባዎች ወቅት የሚወደዱ ነገሮች:
1 - ኹጥባውን ሚንበር ላይ ሁኖ ማድረግ፤
2 - በሁለቱ ኹጥባዎች መካከል ጥቂት በመቀመጥ መለየት፤ 3 - በሁለቱ ኹጥባዎች ለሙስሊሞችና ለመሪያቸው ዱዓ ማድረግ፤
4 - ሁለቱን ኹጥባዎች ማሳጠር፤
5 - ኹጥባ አድራጊው ሚንበር ላይ በሚወጣበት ወቅት ለሰዎች ሰላምታ መስጠቱ፤
አምስተኛው: በጁመዓ ቀን የሚወደዱ ነገሮች:
1 - ሲዋክ መፋቅ፤
2 - ከተገኘ ሽቶ መቀባት፤
3 - ወደ ጁመዓ ሶላት ሲወጣ ማልዶ መውጣት፤
4 - ወደ መስጂድ በመጓጓዣ ሳይሆን በእግር መጓዝ፤
5 - ወደ ኢማሙ መቅረብ፤
6 - ዱዓ ማድረግ፤
7 - ሱረቱል ከህፍን መቅራት፤
8 - በነቢዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ላይ ሰላዋት ማውረድ።
ስድስተኛ: ጁመዓ የተገኘ ሰው የሚከለከላቸው ነገሮች:
1 - የጁመዓ ቀን ኢማሙ ኹጥባ እያደረገ ማውራት ይከለከላል: ነቢዩ ﷺ እንዲህ ብለዋልና:
«إِذَا قُلْتَ لِصَاحِبِكَ يَوْمَ الْجُمُعَةِ: أَنصِتْ، وَالْإِمَامُ يَخْطُبُ، فَقَدْ لَغُوتَ».
«የጁሙዓ ቀን ኢማሙ ኹጥባ እያደረገ ለባልደረባህ ዝም በል! ካልከው በርግጥም ውድቅ ንግግር ተናግረሃል።»38 ማለትም: ውድቅ ንግግር ተናግረሃል ማለት ወንጀልን ይሆንብሃል ማለታቸው ነው።
2 - ኢማም እስካልሆነ ድረስ ወይም በጀርባቸው (ጫንቃ) ካልተረማመደ በቀር የሚቀመጥበት ክፍት ቦታ እስካላጣ ድረስ የሰዎች ጀርባ ላይ መረማመድ ይጠላል።
ጁሙዓ ላይ ደረሰ የሚባለው መቼ ነው?
የጁሙዓ ሶላት የሁለተኛው ረከዓ ላይ ከኢማሙ ጋር ሩኩዕ ላይ የደረሰ ሰው ጁሙዓን አግኝቷል። የሚሰግደው የረከዓ ቁጥርም ሁለት ረከዓ ነው። የሁለተኛዋን ረከዓ ሩኩዕ ኢማሙ ጋር ካላገኘ ጁሙዓ አምልጣዋለች። ስለዚህ ዙህር አድርጎ አራት ረከዓ ይሰግዳታል። ልክ እንደዚሁ በእንቅልፍ ወይም በሌላ ምክንያት ጁሙዓ ያመለጠው ሰውም የሚሰግደው ዙህርን ነው።
አስራ አምስተኛ: እክል ያለባቸው ሰዎች የሚሰግዱት ሶላት:
አንደኛ: የበሽተኛ ሶላት:
በመጀመሪያ: በሽተኛ የሆነ ሰው በቻለው ልክ ሶላትን መፈፀም ግዴታው ነው። አይምሮው ጤነኛ እስከሆነ ድረስ ከወቅቱ ማዘግየት አይፈቀድለትም።
ሁለተኛ: በሽተኛ የሚሰግደው እንዴት ነው?
1 - በሽተኛ የሆነ ሰው ያለምንም ችግር ወይም ያለምንም ጉዳት መቆም ከቻለ ቆሞ መስገድ፣ ሩኩዕ ማድረግና ሱጁድ መውረድ ግዴታው ነው።
2 - መቆም ቢችልም ሩኩዕ በማድረግ ወይም ሱጁድ በመውረድ የሚጎዳ ከሆነ ሩኩዕ ሲያደርግ በቆመበት ከአንገቱ ያቀረቅራል። ሱጁድ ሲያደርግ ደግሞ ተቀምጦ ያቀረቅራል።
3 - ሶላትን ቆሞ መስገድ ካልቻለ ተቀምጦ ይሰግዳል። በመቆም ፈንታ ተቀምጦ ሲሰግድ እግሮቹን አጠላልፎ በመቀመጥ መስገዱ ሱና ነው። ሩኩዕ ሲያደርግ ያቀረቅራል። ከቻለ መሬት ላይ ሱጁድ ያደርጋል። ካልቻለ ደግሞ ሱጁዱን ከአንገቱ በማቀርቀር ይሰግዳል። ነገር ግን የሱጁዱ ማቀርቀር ከሩኩዑ ዝቅ ያለ መሆን አለበት።
4 - ሶላትን ተቀምጦ መስገድ ካልቻለ ፊቱን ወደ ቂብላ በማዞር በጎኑ ተጋድሞ ይሰግዳል። ከተቻለ በቀኝ ጎን መጋደም በላጭ ነው። ሩኩዕና ሱጁድ ሲያደርግም ያቀረቅራል።
5 - በጎኑ መጋደምም ካልቻለ በጀርባው ተንጋሎ መስገድ ይችላል። እግሮቹም ወደ ቂብላ ይዙር። ሩኩዕና ሱጁድ ሲወርድም እያቀረቀረ ያድርግ።
6 - በአካሉ ለሩኩዕና ሱጁድ ማቀርቀር ካልገራለት በጭንቅላቱ ብቻ ያቀረቅራል። ይህም ከከበደው ማቀርቀር ከርሱ ላይ ይነሳለታል። የሶላቱን ተግባራት በልቡ ላይ ያስኬዳል። ባለበት ሁኔታ ላይ እንዳለ ሩኩዕ፣ ሱጁድ፣ መቀመጥና ሌሎችንም የሶላት ድርጊቶች እየፈፀመ መሆኑን በእሳቤው አሳድሮ ውዳሴዎቹን በየቦታቸው ይላል።
7 - በሽተኛ የሆነ ሰው ከሶላት መስፈርቶች የቻለውን ያህል ይፈፅማል። ለምሳሌ: ወደ ቂብላ መዞር፣ በውሃ ዉዱእ ማድረግ፣ ካቃተው ተየሙም መጠቀም፣ ከነጃሳ መፅዳት፣ ከነዚህ መካከልም አንዱ ካቃተው ግዴታነቱ ይነሳለታል። ባለበት ሁኔታ ላይ ሆኖ ይሰግዳል እንጂ ሶላትን ከወቅቱ አያዘገይም።
8 - በሽተኛ የሆነ ሰው ተቀምጦ ሲሰግድ በመቆምና ሩኩዕ ወቅት እግሮቹን አጠላልፎ መቀመጡ ከዛ ውጪ ባሉ የሶላት ድርጊቶች ደግሞ ግራ እግሩን አንጥፎ መቀመጡ ሱና ነው።
ሁለተኛ: የሙሳፊር ሶላት:
1 - ሶላት ለመስገድ ከሚቸገሩት ሰዎች መካከል ጉዞ የሚወጡ ሰው ይጠቀሳል። እርሱም ባለ አራት ረከዓ ሶላቶችን ከአራት ወደ ሁለት ረከዓ አሳጥሮ መስገድ ይፈቀድለታል። ምክንያቱም የላቀው አላህ እንዲህ ብሏልና፦
﴿وَإِذَا ضَرَبۡتُمۡ فِي ٱلۡأَرۡضِ فَلَيۡسَ عَلَيۡكُمۡ جُنَاحٌ أَن تَقۡصُرُواْ مِنَ ٱلصَّلَوٰةِ...﴾
{በምድርም ላይ በተጓዛችሁ ጊዜ ከሶላት (ባለ አራት ረከዓት የኾኑትን) ብታሳጥሩ በናንተ ላይ ኀጢአት የለም፡፡ …} [አንኒሳእ:101]
ከአነስ ቢን ማሊክ ረዲየሏሁ ዐንሁ -አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላቸውና- እንደተላለፈው እንዲህ አሉ፦
«خَرَجْنَا مَعَ النَّبِيِّ ﷺ مِنَ الْمَدِينَةِ إِلَى مَكَّةَ، فَكَانَ يُصَلِّي رَكْعَتَيْنِ رَكْعَتَيْنِ، حَتَّى رَجَعْنَا إِلَى الْمَدِينَةِ».
"ከነቢዩ ﷺ ጋር ከመዲና ወደ መካ ወጣን። (ማለትም: በመሰናበቻ ሐጅ ወቅት) ወደ መዲና እስክንመለስ ድረስም (ባለ አራት ረከዓ ሶላቶችን) ሁለት ሁለት ረከዓ አድርገው ይሰግዱ ነበር።"39
ጉዞ የሚወጣ ሰው ከሃገሩ መኖሪያ ቤቶች አልፎ በወጣበት ማሳጠር ይጀምራል። ምክንያቱም አላህ ማሳጠርን የፈቀደው በምድር ላይ ለሚጓዙ ሰዎች ነውና። ከሃገሩ ከመውጣቱ በፊት በምድር ላይ ተጓዥ አይባልም። ነቢዩም ﷺ አሳጥረው ይሰግዱ የነበሩት ጉዞ በወጡ ወቅት ነበር።
2 - ጉዞ መውጣት የፈለገ ሰው ሶላትን አሳጥሮ መስገድ የሚፈቀድለት የጉዞ ርቀት ሰማኒያ ኪሎ ሜትር አቅራቢያ የሚጓዝ ከሆነ ነው።
3 - ጉዞ የወጣ ሰው ሲመለስ ወደ ወጣበት ሃገሩ እስኪገባ ድረስ አሳጥሮ መስገድ ይፈቀድለታል።
4 - ጉዞ የወጣ ሰው ወደ አንድ ሃገር የገባ ጊዜ እዛ መቆየት ከፈለገ ሶስት ሁኔታዎች ይኖሩታል:
ሀ) ከአራት ቀን በላይ መቆየትን ካሰበ: ካረፈበት የመጀመሪያ ቀን ጀምሮ ሶላቱን አሟልቶ መስገድ ግዴታው ነው። የጉዞ ማግራሪያዎችም አይፈቀዱለትም።
ለ) አራት ቀንና ከዛ በታች መቆየት ካሰበ: በሚቆይባቸው ቀናት ማሳጠርና የጉዞ ማግራሪያዎችን ተግባራዊ ማድረግ ይፈቀድለታል።
መ) በቀናት የተገደበን ጊዜያት ለመቆየት ካላሰበ በተቃራኒ አንድ ቀንም ይሁን አስር ቀናት እንደየ ሁኔታው ሊቆይ እንደሚችል ካሰበ ወይም የህክምና ወይም የክትትል ጉዳይ ኑሮት ጉዳዩ ባለቀለት ጊዜ ወደ ሃገሩ የሚመለስ ከሆነ ይህ አይነቱ ሰው የቆይታው ጊዜ ከአራት ቀን በላይ ቢጨምር ራሱ ማሳጠርም ሆነ እስኪመለስ ድረስ የጉዞ ማግራሪያዎችን መጠቀም ይፈቀድለታል።
5 - ጉዞ የወጣ ሰው የሃገሪቷ ነዋሪ የሆነን ኢማም ኋላ ተከትሎ ከሰገደ ሶላቱን መሙላት ግዴታው ነው። ከርሱ ጋር አብሮ የሰገደው የመጨረሻውን ተሸሁድ ብቻ እንኳ ቢሆን መሙላት ግዴታው ነው።
6 - የሃገሪቱ ነዋሪ የሆነ ሰው አሳጥሮ ከሚሰግድ ጉዞ ከወጣ ሰው ኋላ ተከትሎ ከሰገደ የሃገሪቱ ነዋሪ የሆነው ሰውዬ ኢማሙ ካሰላመተ በኋላ ሶላቱን መሙላት ግዴታው ነው።
አስራ ስድስተኛ: የሁለቱ ዒዶች ሶላት:
የሙስሊሞች ዓመት በዓል መለኮታዊ ዓመት በዓል ነው። በራሳቸው በኩል ሳይሆን አላህ የደነገገላቸው በዓል ነው። ከሁለቱ ዓመት በዓሎች ውጪ ምንም በዓልም የላቸውም። እነርሱም: ዒደል ፊጥርና ዒደል አድሓ ናቸው። አላህ ያልደነገጋቸውና ያላዘዘባቸው የከሃዲያንና የተፈበረኩ ቢድዓ በዓላት ግን በራሳቸው ፍላጎት የደነገጓቸው በዓላት ናቸው።
የሁለቱ ዒዶች ሶላት ብይን:
የወል ግዴታ ናቸው። ነቢዩ ﷺ ዘውትረውባቸዋል። አራቱ ቅን ምትኮችም -አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና - ዘውትረውባቸዋል። እነርሱ ከእስልምና ምልክቶችና ጉልህ መገለጫዎች መካከል ናቸው።
የሁለቱ ዒዶች ሶላት ወቅት: የዒድ ሶላት ወቅት ፀሐይ የጦር ያህል ከፍ ካለችበት ይጀምርና (ፀሐይ ከወጣች 15 ደቂቃ አካባቢ በኋላ) ፀሐይ ወደ መግቢያዋ ስትዘነበል የመስገጃ ወቅቷ ይጠናቀቃል።
የዒድ ሶላት አሰጋገድ:
1 - በመጀመሪያው ረከዓ የመክፈቻን ተክቢራ ይላል፤ ከዚያም የመክፈቻ ዱዓ ይላል፤ ከዚያም ስድስት ተክቢራዎችን ይላል፤ ከየሁሉም ተክቢራ ጋርም እጆቹን ያነሳል አላህን ያመሰግናልም ያወድሳልም። በየሁሉም ተክቢራዎች መካከል በነቢዩ ﷺ ላይ ሶላት ያወርዳል፤ ከዚያም አዑዙ ቢላሂ ሚነሽሸይጧኒርረጂም ቢስሚላሂር-ራሕማኒር-ረሒም ይልና ፋቲሓን መቅራት ይጀምራል።
2 - በሁለተኛውም ረከዓ ለሁለተኛው ረከዓ ሲነሳ የሚባለውን ተክቢራ ካለ በኋላ አምስት ተክቢራዎችን ይላል፤ ከዚያም አዑዙ ቢላሂ ሚነሽሸይጧኒርረጂም ቢስሚላሂር-ራሕማኒር-ረሒም ይልና ፋቲሓን መቅራት ይጀምራል። በመጀመሪያው ረከዓ ከፋቲሓ በኋላ ሱረቱል አዕላን መቅራት በሁለተኛው ደግሞ ሱረቱል ጋሺያን መቅራት ይወደዳል።
3 - ኢማሙ ሶላቱን እንዳጠናቀቀ ወደ ሚንበር ይወጣል። ሁለት ኹጥባዎችንም ያደርጋል። ልክ የጁመዓ ኹጥባ ላይ እንደሚደረገው በሁለቱ ኹጥባዎች መካከል ትንሽ ይቀመጣል።
የዒድ ሱናዎች:
ሀ) መታጠብ፤
ለ) መፅዳትና ሽቶ መቀባት፤
መ) በዒደል ፊጥር ወቅት ከመውጣቱ በፊት መብላት፣ በዒደል አድሓ ደግሞ ከሶላት በኋላ ኡድሒያ የሚያርድ ከሆነ ካረደው የኡድሒያው ስጋ መብላት፤
ሰ) በእግር መሄድ፤
ረ) ከሄዱበት ውጭ በሌላ መንገድ መመለስ፤
ሸ) ኢማሙ ሳይሆን ተከታይ ለሆነ ሰው ወደ መስገጃ ስፍራ ማልዶ መሄዱ፤
ተክቢራ:
የዒድ ምሽቶችን፣ አስሩን የዙልሒጃ ቀናት፣ አያመ ተሽሪቆችን ተክቢራ እያሉ ማሳለፍ ሱና ነው። አፋፃፀሙም በሁለት አይነት መንገድ ነው:
የመጀመሪያው አይነት: ልቅ በሆነ መንገድ ተክቢራ ማለት: ይህም ማለት በወቅት ያልተገደበ ተክቢራ ነው።
1: በዒደል ፊጥር ጊዜ: የዒዱ ዋዜማ ፀሐይ ከጠለቀችበት ምሽት አንስቶ የዒድ ሶላት እስኪጀምር ድረስ፤
2: በዒደል አድሓ ጊዜ: ከዙልሒጃ የመጀመሪያ ቀን ፀሐይ ከጠለቀችበት ምሽት ጀምሮ የአያመ ተሽሪቅ የመጨረሻው ቀን ፀሐይ እስክትገባ ድረስ ነው።
ሁለተኛው አይነት: በወቅት የተገደበ ተክቢራ:- ይህም ከግዴታ ሶላቶች በኋላ ብቻ የሚባል ተክቢራ ነው።
1 - ኢሕራም ላይ ያልሆነ ሰው: ከዓረፋ ቀን ፈጅር ሶላት ጀምሮ የአያመ ተሽሪቅ የመጨረሻው ዓስር ድረስ፤
2 - ኢሕራም ላይ የሆነ ሰው: ከዒድ ቀን ዝሁር ሶላት ጀምሮ የአያመ ተሽሪቅ የመጨረሻ ዓስር ሶላት ድረስ ነው።
አስራ ሰባተኛ: የግርዶሽ ሶላት:
የኹሱፍና የኩሱፍ ትርጓሜ:
ኹሱፍ ማለት: የጨረቃ ብርሃን ሙሉ ለሙሉ ወይም በከፊል በምሽት ወቅት መጋረዱ ነው።
ኩሱፍ ማለት: የፀሐይ ብርሃን ሙሉ ለሙሉ ወይም በከፊሉ በቀኑ ክፍለ ጊዜ መጋረዱ ነው።
የግርዶሽ ሶላት ብይን:
አፅንዖት የተሰጠው ጠንካራ ሱና ነው። ይህንንም የሚጠቁመው ፀሐይ በነቢዩ ﷺ ዘመን የተጋረደ ጊዜ መልክተኛው ﷺ መፈፀማቸው ነው። ልክ እንደዚሁ እንዲሰገድ ያዘዙትም ሶላት ነው። ዑለማዎች ባጠቃላይ የግርዶሽ ሶላት የተደነገገ መሆኑን ተስማምተዋል።
ወቅቱ:
ግርዶሹ ከጀመረበት አንስቶ እስኪገለጥ ድረስ ነው።
አሰጋገዱ:
የረከዓው ቁጥርም ሁለት ረከዓ ነው። በሁለቱ ረከዓም ሲቀራ ድምፁን ከፍ አድርጎ ነው። አሰጋገዱም እንደሚከተለው ነው:
ሀ) የመክፈቻ ተክቢራ ይላል፤ የመክፈቻ ዱዓ ይላል፤ አዑዙ ቢላሂ ሚነሽሸይጧኒርረጂም ቢስሚላሂር-ራሕማኒር-ረሒም ይልና ፋቲሓን ይቀራል፤ ከዚያም ረጅም ምዕራፍ ይቀራል።
ለ) ከዚያም ለረጅም ወቅት ሩኩዕ ላይ ይቆያል፤
ሐ) ከዚያም ከሩኩዕ ይነሳና (ሰሚዐሏሁ ሊመን ሐሚደህ) ይላል። ከዚያም ድጋሚ ፋቲሓን ይቀራል፤ ከዚያም ከመጀመሪያው ያነሰ ረጅም ምዕራፍ ይቀራል፤
መ) ከዚያም ከመጀመሪያው ሩኩዕ ያነሰ ለረጅም ወቅት ሩኩዕ ላይ ይቆያል፤
ሠ) ከዚያም ከሩኩዕ በመነሳት (ሰሚዓሏሁ ሊመን ሐሚደህ) ይላል።
ረ) ከዚያም ሁለት ረጃጅም ሱጁዶችን ያደርጋል፤
ሰ) ከዚያም ወደ ሁለተኛው ረከዓ ይነሳል። የሁለተኛውንም ረከዓ ልክ እንደመጀመሪያው አድርጎ ይሰግዳል። ነገር ግን ከመጀመሪያው ረከዓ ትንሽ አጠር ያለ ነው።
የግርዶሽ ሶላት ሱናዎች:
ሀ) (አስሶላቱል ጃሚዓ) የሚል ጥሪ ማድረግ። ትርጉሙም (የህብረት ሶላት) ማለት ነው።
ለ) በጀማዓ መሰገድ፤
ሐ) ሶላት ውስጥ መቆሙን፣ ሩኩዑንና ሱጁዱን ማርዘም፤
መ) ሁለተኛውን ረከዓ ከመጀመሪያው ረከዓ ያጠረ ማድረግ፤
ሠ) ከሶላቱ በኋላ መምከር፣ መልካም ተግባራትን በመስራትና ውግዝ ተግባራትን በመተው ላይ ማነሳሳት፤
ረ) ዱዓን፣ መዋደቅን፣ ኢስቲግፋርንና ሶደቃን ማብዛት ተጠቃሽ ናቸው።
አስራ ስምንተኛ: ዝናብን የመፈለግ ሶላት:-
1) ዝናብን መፈለግ ማለት:- ድርቅ በተከሰተ ወቅት አላህ ዝናብን እንዲያዘንብልን መፈለግ ማለት ነው።
ዝናብን የመፈለግ ሶላት የሚሰገድበት ወቅት:
መሬቱ የደረቀ፣ ዝናቡ የተቋረጠ፣ ዝናቡ በመቋረጡም ጉዳት የተከሰተ ጊዜ፣ ወደ ጌታቸው በተለያዩ መዋደቂያ አይነቶች ካልተዋደቁ፣ ዝናብን ካልጠየቁ፣ እርዳታን ካልተማፀኑ በቀር ሌላ ምንም መሸሻ እንደሌላቸው ያረጋገጡ ጊዜ ዝናብን የመፈለግ ሶላት መስገድ የተደነገገ ነው።
ሀ) ዝናብን መፈለግ አንዳንዴ በጀማዓም ሆነ ለየብቻ በመስገድ ይከወናል።
ለ) አንዳንዴ በጁመዓ ኹጥባ ወቅት ዱዓ በማድረግ ይከወናል። ይኸውም ኹጥባ አድራጊው ዱዓ ሲያደርግ ሙስሊሞች ደግሞ በዱዓው ላይ አሚን ይላሉ።
መ) አንዳንዴ በማንኛውም ወቅት ያለ ሶላትም ያለ ኹጥባም ዱዓ በማድረግ ሊከወን ይችላል።
ዝናብን የመፈለግ ሶላት ብይን:
ነቢዩ ﷺ ስለ ሰገዱ መስገድ የሚያስፈልግበት ምክንያት በተከሰተ ወቅት መስገዱ ጠንካራ ሱና ነው። በዐብደላህ ቢን ዘይድ - አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላቸውና - ሐዲሥ እንደተላለፈው: እንዲህ አሉ:
«خَرَجَ النَّبِيُّ ﷺ إِلَى الْمُصَلَّى، فَاسْتَسْقَى، وَاسْتَقْبَلَ الْقِبْلَةَ، وَقَلَبَ رِدَاءَهُ، وَصَلَّى رَكْعَتَيْنِ».
«ነቢዩ ﷺ ወደ መስገጃ ስፍራ ወጡና ወደ ቂብላ በመዞር ኩታቸውን ገልብጠው፣ ሁለት ረከዓ ሰግደው ዝናብን ከአላህ ፈለጉ።»40
ዝናብን የመፈለግ ሶላት አሰጋገድ:
ዝናብን የመፈለግ ሶላት አሰጋገድ እንደ ዒድ ሶላት ነው። ልክ እንደ ዒድ ሶላት መስገጃ ሜዳ ላይ መስገድ ይወደዳል። በረከዓ ቁጥሮቹ፣ ጮክ ብሎ በመቅራት፣ ከኹጥባ በፊት በመሰገድ፣ በመጀመሪያውና ሁለተኛው ረከዓ ፋቲሓን ከመቅራት በፊት በሚባሉት ጭማሪ ተክቢራዎች በኩል ዝናብን የመፈለግ ህግጋት ልክ እንደ ዒድ ሶላት ነው። ቀደም ብሎ የዒድ ሶላት አሰጋገድ ላይ በተብራራበት መልኩ ማለት ነው። ዝናብን የመፈለግ ኹጥባ የሚደረገው አንድ ጊዜ ነው።
አስራ ዘጠነኛ: የጀናኢዝ ህግጋት (ከአስክሬን ጋር የተያያዙ ህግጋት):
የመጀመሪያው: ጣዕረ ሞት ላይ ያለ ሰው ዘንድ የተገኘ ሰው:
1: ጣዕረ ሞት ላይ ያለ ሰው ዘንድ የተገኘ ሰው የሚጣጣረውን ሰው «ላኢላሃ ኢለሏህ» ማስባል ሱና ነው።
2: (ከሞተ በኃላ) ወደ ቂብላ አቅጣጫ ማዞር ሱና ነው።
3: ዓይኖቹን መጨፈን ይወደዳል።
4: ሟችን ከሞተ በኋላ በልብስ መሸፈን ሱና ነው።
5: ሟችን በፍጥነት ማሰናዳት ይገባል።
6: ዕዳውን ለመክፈል መቻኮል ግዴታ ነው።
7: ሟች ይታጠባልም ይከፈናልም። እነዚህ ሁለቱ የወል ግዴታ ናቸው።
ሁለተኛ: በሟች ላይ የመስገድ ህግጋት:
ብይኑ: ፈርዱ ኪፋያ (የወል ግዴታ) ነው።
መስፈርቶቹ:
1) ወደ ቂብላ መዞር፤
2) ሀፍረተ ገላን መሸፈን፤
3) ነጃሳን መራቅ፤
4) ሰጋጁም የሚሰገድበትም አስከሬን ጦሃራ ያላቸው መሆን አለበት፤
5) ሰጋጁም የሚሰገድበትም አስከሬን ሙስሊም መሆን አለባቸው፤
6) አስከሬኑ ሃገሪቱ ውስጥ ያለ ከሆነ የሚሰገድበት ቦታ መገኘት አለበት፤
7) ሰጋጁ ለአቅመ ተጠያቂነት የደረሰ መሆን አለበት።
የጀናዛ ሶላት ማዕዘናቶቹ:
1) ለሶላቱ መቆም፤
2) አራት ተክቢራዎችን ማሟላት፤
3) ፋቲሓን መቅራት፤
4) በነቢዩ ﷺ ላይ ሶላት ማውረድ፤
5) ለሟቹ ዱዓ ማድረግ፤
6) ቅደም ተከተሉን መጠበቅ፤
7) ማሰላመት ናቸው።
የጀናዛ ሶላት ሱናዎች:
1- ከየሁሉም ተክቢራ ጋር እጆችን ወደ ላይ ማንሳት፤
2) አዑዙቢላህ ሚነሽሸይጧኒርረጂም ማለት።
3) ለራስም ለሙስሊሞችም ዱዓ ማድረግ፤
4) በዝግታ መቅራት፤
5) ከአራተኛው ተክቢራ በኋላና ከማሰላመቱ በፊት ትንሽ ቆም ማለት፤
6) ቀኝ እጅን ግራ እጅ ላይ በማድረግ ደረት ላይ ማኖር፤
7) ሲያሰላምት ወደ ቀኝ መዞር፤
አሰጋገዱ:
ኢማሙ ወይም ብቻውን የሚሰግድ፤ ሟቹ ወንድ ከሆነ በደረቱ ትይዩ ሴት ከሆነች ደግሞ በወገቧ ትይዩ ይቆማል። የመክፈቻን ተክቢራም ይልና አዑዙ ቢላህ ሚነሽሸይጧኒርረጂም ይላል። የመክፈቻ ዱዓ ሳያደርግ ቢስሚላሂር-ረሕማኒር-ረሒም ይልና ፋቲሓን ይቀራል።
ቀጥሎ ተክቢራ ይልና በነቢዩ ﷺ ላይ ሶላት ያወርዳል። ቀጥሎ ተክቢራ ይልና በሐዲሥ በመጣው ዱዓ ለሟቹ ዱዓ ያደርጋል። ለምሳሌ የነቢዩን ﷺ ይህ ዱዓ:
«اللَّهُمَّ اغْفِرْ لِحَيِّنَا وَمَيِّتِنَا، وَصَغِيرِنَا وَكَبِيرِنَا، وَذَكَرِنَا وَأُنثَانَا، وَشَاهِدِنَا وَغَائِبِنَا، اللَّهُمَّ مَنْ أَحْيَيْتَهُ مِنَّا فَأَحْيِهِ عَلَى الإِيمَانِ، وَمَنْ تَوَفَّيْتَهُ مِنَّا فَتَوَفَّهُ عَلَى الإِسْلَامِ، اللَّهُمَّ لَا تَحْرِمْنَا أَجْرَهُ، وَلَا تُضِلَّنَا بَعْدَهُ».
("አልላሁምመ‐ጝፊር ሊሐዪና ወመዪቲና ወሶጚሪና ወከቢሪና ወዘከሪና ወኡንሣና ወሻሂዲና ወጛኢቢና፤ አልላሁምመ መን አሕየይተሁ ሚንና ፈአሕዪሂ ዐለል ኢማን ወመን ተወፈይተሁ ሚንና ፈተወፈሁ ዐለል ኢስላም፤ አልላሁምመ ላተሕሪምና አጅረሁ ወላቱዲለና በዕደሁ።")41 (ትርጉሙም “አላህ ሆይ! በህይወት ያለነውንም፣ የሞቱብንም፣ ትልልቆቻችንንም፣ ትንንሾቻችንንም፣ በቅርብ ያለነውንም ሩቅ ያሉትንም፣ ወንዶቻችንንም፣ ሴቶቻችንንም ማርልን። አላህ ሆይ! ከመካከላችን የምታኖረውንም ኑሮውን በኢማን አድርግለት፤ የምትገለውንም በእስልምና ላይ እንዲሞት አድርገው። አላህ ሆይ! ምንዳውን አትንፈገን ከእርሱም በኋላ እጣችንን ጥመት አታድርግብን።")
ተከታዩም ከርሳቸው ተዘግቦ ይገኛል:
«اللَّهُمَّ اغْفِرْ لَهُ وَارْحَمْهُ، وَعَافِهِ وَاعْفُ عَنْهُ، وَأَكْرِمْ نُزُلَهُ، وَوَسِّعْ مَدْخَلَهُ، وَاغْسِلْهُ بِالْمَاءِ وَالثلْجِ وَالْبَرَدِ، وَنَقِّهِ مِنَ الْخَطَايَا كَمَا نَقَّيْتَ الثَّوْبَ الْأَبْيَضَ مِنَ الدَّنَسِ، وَأَبْدِلْهُ دَارًا خَيْرًا مِنْ دَارِهِ، وَأَهْلًا خَيْرًا مِنْ أَهْلِهِ، وَزَوْجًا خَيْرًا مِنْ زَوْجِهِ، وَأَدْخِلْهُ الْجَنَّةَ، وَأَعِذْهُ مِنْ عَذَابِ الْقَبْرِ، وَمِنْ عَذَابِ النَّارِ».
("አልላሁምመ‐ጝፊር ለሁ ወርሓምሁ ወዓፊሂ ወዕፉ ዓንሁ ወአክሪም ኑዙለሁ ወወሲዕ ሙድኸለሁ ወጝሲልሁ ቢልማኢ ወሠልጂ ወልበረዲ፤ ወነቂሂ ሚነልኸጣያ ከማ ነቀይተ አሥ-ሠውበል አብየዸ ሚነ‐ድደነሲ፤ ወአብዲልሁ ዳረን ኸይረን ሚን ዳሪህ ወአህለን ኸይረን ሚን አህሊህ ወአድኺሉሁል‐ጀነተ ወአዒዝሁ ሚን ዐዛቢል ቀብሪ ወሚን ዐዛቢ ናር") (ትርጉሙም “አላህ ሆይ! (ለሟቹ) ምህረት አድርግለት፤ እዘንለትም፤ (ከእሳት) ጠብቀው፤ ይቅርም በለውም፤ መስተንግዶውንም አሳምርለት፤ መግቢያውንም አስፋለት፤ ሀጢአቱንም በውሃ፤ በበረዶና በቀዝቃዛ ውሃ እጠብለት፤ ነጭ ልብስ ከቆሻሻ እንደምታፀዳው የእርሱንም ወንጀል አፅዳለት፤ ከቤቱ የተሻለ ቤት ከቤተሰቡ የተሻለ ቤተሰብን ተካለት። ወደ ጀነት አስገባው፣ ከቀብር ቅጣትና ከእሳት ቅጣትም ጠብቀው፤ ቀብሩንም አስፋለት።")42 ከዚያም ተክቢራ በማለት ትንሽ ይቆማል ከዚያም ወደ ቀኙ አንዴ ብቻ ያሰላምታል።
ሶስተኛው ክፍል: ዘካ:
1 - የዘካ ትርጓሜና ዘካ ያላት ደረጃ:
ዘካ በቋንቋ ትርጓሜው: መፋፋት መጨመር ማለት ነው።
ዘካ በሸሪዓ ትርጓሜው: በሸሪዓ በተወሰኑ የገንዘብ አይነቶች ላይ ግዴታ የተደረገ ለተወሰኑ አይነት ሰዎች የሚሰጥ ነው።
ዘካ ከእስልምና ማዕዘናት አምስተኛው ማዕዘን ነው። በቁርአን ውስጥም በሰማኒያ ሁለት ስፍራ ከሶላት ጋር ተቆራኝታ መምጣቷ የዘካን ታላቅነት ይጠቁማል።
አላህ እንዲህ ብሏል፡
﴿وَأَقِيمُواْ ٱلصَّلَوٰةَ وَءَاتُواْ ٱلزَّكَوٰةَ...﴾
{ሶላትንም ደንቡን ጠብቃችሁ ስገዱ፡፡ ዘካንም (ግዴታ ምጽዋትን) ስጡ፡፡ …} [አል‐በቀራህ:43]
ነቢዩም ﷺ እንዲህ ብለዋል፡
«بُنِيَ الإِسْلَامُ عَلَى خَمْسٍ: شَهَادَةِ أَنْ لَا إِلٰهَ إِلَّا اللَّـهُ، وَأَنَّ مُحَمَّدًا رَسُولُ اللَّـهِ، وَإِقَامِ الصَّلَاةِ، وَإِيتَاءِ الزَّكَاةِ، وَحَجِّ الْبَيْتِ، وَصَوْمِ رَمَضَانَ».
«እስልምና በአምስት ነገሮች ላይ ተገንብቷል፦ ከአላህ በስተቀር በእውነት የሚመለክ አምላክ አለመኖሩን እና ሙሐመድ የአላህ መልዕክተኛ መሆናቸውን መመስከር፣ ሶላትን ደንብና ሥርዓቱን ጠብቆ መስገድ፣ ዘካ መስጠት፣ ሐጅ ማድረግ (የአላህን ቤት መጎብኘት) እና የረመዳንን ወር መጾም ናቸው።»43
ሙስሊሞች ባጠቃላይ ዘካ ግዴታ በመሆኗ ላይ ተስማምተዋል። ግዴታነቷን የካደም ሰው ከሃዲ እንደሚሆን ተስማምተዋል። ዘካን አልሰጥም ያሉን መዋጋት እንደሚገባም ተስማምተዋል።
2 - ዘካ ግዴታ የሚሆንበት መስፈርቶች:
ሀ) ከባርነት ነፃ መሆን: ባሪያ ገንዘብ ስለሌለውና በእጁ ገንዘብ ቢኖር ራሱ የአለቃው ንብረት ስለሚሆን ባሪያ ላይ ዘካ የለበትም። ዘካ የሚኖርበት አሳዳሪው ነው።
ለ) እስልምና: ዘካ ቁርባንና አምልኮ ስለሆነ ከሃዲ ላይ ዘካ ግዴታ አትሆንም። ካፊር የቁርባንና አምልኮ ባለቤት አይደለምና።
ሐ) ለዘካ መጠን የደረሰ ገንዘብ ባለቤት መሆን: ከዘካ መጠን በታች በሆነ ገንዘብ ዘካ ግዴታ አይሆንም።
መ) የተሟላ ባለቤትነት: ግለሰቡ የገንዘቡ የተሟላ ባለቤት መሆን አለበት። እንደተፃፃፉት እዳ አይነቱ ባለቤትነቱ ባልተረጋገጠ ገንዘብ ላይ ዘካ አይወጣበትም።
ሠ) ገንዘቡ ዓመት መዞር አለበት። እናታችን ዓኢሻ -አላህ መልካም ሥራዋን ይውደድላትና- ከነቢዩ ﷺ ባስተላለፈችው ሐዲሥ፦
«لَا زَكَاةَ فِي مَالٍ حَتَّى يَحُولَ عَلَيْهِ الْحَوْلُ».
«ገንዘብ ዓመት እስኪሞላው ድረስ ዘካ የለበትም።»44
3 - ዘካ ግዴታ የሚሆንባቸው ገንዘቦች:
የመጀመሪያው: ሶስቱ የቤት እንስሶች ናቸው:
እነርሱም: ግመል፣ ከብት እና በግና ፍየል ናቸው። እነዚህ እንሰሶች ያሉት ሰው ሁለት መስፈርቶች ከተሟሉ ዘካ ግዴታ ይሆንበታል።
1: ከብቶቹን የሚገለገልባቸው ለስራ ሳይሆን ለወተትና ለእርባታ መሆን አለበት:
2 - ከብቶቹ ግጦ ገብ መሆን አለባቸው። ለከብቶች ቀለብ ሳር እየገዛ ወይም ሳር አጭዶ እያመላለሰ ወይም በመሳሰሉት መንገድ ከሆነ የሚያሳድራቸው የነርሱን ዘካ ማውጣት ግዴታ አይሆንበትም። የዓመቱን የተወሰነ ክፍል ብቻ ግጦ ገብ ከሆኑም ዘካ አይወጣባቸውም። ዓመቱን ሙሉ ወይም አብዛኛውን የዓመቱን ክፍል ግጦ ገብ ከሆኑ ግን ዘካ ይወጣባቸዋል።
4 - የቤት እንስሶች የዘካ መጠን:
1 - የግመል ዘካ:-
ከላይ የተጠቀሱት መስፈርቶች ከተሟሉ በኃላ: ከአምስት ግመል አንድ በግ ወይም ፍየል፣ ከአስር ግመል ሁለት በግ ወይም ፍየል፣ ከአስራ አምስት ግመል ሶስት በግ ወይም ፍየል፣ ከሃያ ግመል አራት በግ ወይም ፍየል ዘካ ማውጣት ግዴታ ነው። በዚህም ዙሪያ የሐዲሥና የዑለማዎች ስምምነት ማስረጃዎች አሉ። ሃያ አምስት ግመል ሲደርሱ አንድ አመት ሞልቷት ወደ ሁለተኛ አመት የገባችን ሴት ግመል ለዘካ ይሰጣል። እርሷ ከሌለችው ሁለት አመት ሞልቶት ወደ ሶስተኛ አመት የገባን ወንድ ግመል ለዘካ ይሰጣል።
ሰላሳ ስድስት ግመል የደረሱለት ጊዜ ሁለት አመት የሞላትን ሴት ግመል ለዘካ መስጠት ግዴታው ነው።
አርባ ስድስት ግመል የደረሱለት ጊዜ ሶስት ዓመት የሞላትን ሴት ግመል መስጠት ግዴታው ነው።
ስልሳ አንድ ግመል የደረሱለት ጊዜ (የሸረፈች) አራት አመት የሞላትን ግመል ለዘካ መስጠት ግዴታው ነው።
አጠቃላይ ግመሎቹ ሰባ ስድስት ሲደርሱ ሁለት ዓመት የሞላቸውን ሁለት ሴት ግመሎችን ለዘካ መስጠት ግዴታው ነው።
ዘጠና አንድ ግመል ሲደርሱ ሁለት ሶስት ዓመት የሞላቸውን ሴት ግመሎችን መስጠት ግዴታው ነው።
አጠቃላይ ግመሎቹ ከመቶ ሃያ በላይ አንድ እንኳ ሲጨምሩ ሁለት አመት የሞላቸውን ሶስት ሴት ግመሎችን ለዘካ መስጠት ግዴታው ነው። ከዚያም በየሁሉም አርባ ግመሎች ሁለት አመት የሞላትን ሴት ግመል በየሁሉም ሃምሳ ግመሎች ሶስት አመት የሞላትን ሴት ግመል ይሰጣል።
2 - የከብት (የበሬና ላም) ዘካ:
ከብቶች ከላይ የተጠቀሰው መስፈርቶች የተሟሉ ጊዜ ሰላሳ ሲደርሱ አንድ አመት ሞልቷት ወደ ሁለት የገባን ወንድ ወይም ሴት ጥጃ ለዘካ ይሰጣል።
ከሰላሳ በታች ምንም መስጠት አይጠበቅበትም።
አርባ ከብቶች ሲደርሱለት ሁለት አመት የሞላትን ሴት ጊደር ለዘካ መስጠት ግዴታው ነው።
አጠቃላይ የከብቶቹ መጠን ከአርባ ካለፉ በየሁሉም ሰላሳ ወንድ ወይም ሴት ጥጃ በየሁሉም አርባ ደግሞ ሴት ጊደር ለዘካ መስጠት ግዴታው ነው።
3 - የበግና ፍየል ዘካ:
አጠቃላይ በጎቹ ወይም ፍየሎቹ አርባ ሲደርሱ አንድ በግ ወይም ፍየል ለዘካ ይሰጣል። የሚሰጠውም አንድ አመት የሞላቸው የሸረፈን በግ ወይም የሸረፈች ፍየል ነው።
ቁጥራቸው ከአርባ በታች በሆኑ በጎች ወይም ፍየሎች ላይ ምንም አይነት ዘካ የለበትም። አጠቃላይ በጎቹ ወይም ፍየሎቹ መቶ ሃያ አንድ ሲደርሱ ሁለት በጎች ወይም ፍየሎችን ለዘካ መስጠት ግዴታው ነው። ሁለት መቶ አንድ ሲደርሱለት ሶስት በጎች ወይም ፍየሎችን ለዘካ መስጠት ግዴታው ነው።
ከዚህ መጠን በኋላ የሚሰጠው የዘካ ግዴታው ባለበት ይፀናል። በየመቶ ፍየልም አንድ በግ ወይም ፍየል ለዘካ መስጠት ግዴታው ነው። አራት መቶ በጎች ወይም ፍየሎች ሲሞሉለት አራት በጎች ወይም ፍየሎች… በዚሁ መልክ ይቀጥላል።
ሁለተኛ: ከመሬት የሚወጣ የቡቃያና አዝርእት ዘካ:
ከመሬት የሚወጡ ነገሮች ሁለት አይነት ናቸው:
1) የእህል ዘሮችና ከዛፍ የሚለቀሙ ፍሬዎች:
2) ማዕድን
የመጀመሪያው አይነት: የእህል ዘሮችና ከዛፍ የሚለቀሙ ፍሬዎች:
እንደ ስንዴ፣ ገብስና ሩዝ ለመሰሉ የእህል ዘሮች ዘካ ማውጣት ግዴታ ነው። ከፍሬዎችም: ተምርና ዘቢብን ለመሰሉ ዘካ ማውጣት ግዴታ ነው። ከነዚህ ውጪ ላሉ ቡቃያዎችና አረንጓዴ ቅጠሎች ዘካ ማውጣት ግዴታ አይደለም።
ለእህል ዘሮችና ፍሬዎች ዘካ ግዴታ የሚሆንበት መስፈርቶች:
1) የሚከማች (ለረጅም ጊዜ የሚቀመጥ) መሆን አለበት:- ስለዚህ እንደ ፍራፍሬዎችና አትክልቶች ባሉ የማይከማቹ ነገሮች ላይ ዘካ ማውጣት የለም።
2) በስፈር የሚለካ (የሚሰፈር) መሆን አለበት፤ እንደ ሀብሀብ፣ ሽንኩርት፣ ሮማን እና የመሳሰሉት በቁጥር ወይም በክብደት (በሚዛን) በሚሸጡት ላይ ዘካ የለም።
3) መጠኑ ኒሳብ (የግዴታ የዘካ መጠን) የደረሰ መሆን አለበት፤ ይህም አምስት «አውሱቅ» ነው፤ ከዚህ በታች በሆነው ላይ ዘካ የለም።
4) የዘካ መጠን የደረሰው እህል ዘካ ግዴታ በሆነበት ወቅት ያህል በዘካ ሰጪው ቁጥጥር ስር መሆን አለበት።
የእህሉ ዘካን ማውጣት ግዴታ ከሆነበት ወቅት በኋላ በመግዛት ወይም ከታጨደ በኋላ በስጦታ መልክ ተሰጥቶት የእህሉ ባለቤት ቢሆን በርሱ ላይ ዘካ ግዴታ አይሆንበትም።
የአዝርዕት ዘካ ግዴታ የሚሆንበት ወቅት:
የእህል ዘሮችና ፍሬዎች የበሰሉና የደረሱ ጊዜ ዘካቸውን ማውጣት ግዴታ ይሆናል። የመብሰላቸውና የመድረሳቸው ምልክትም እንደሚከተለው ነው:
ሀ) በእህል ዘሮች ላይ: ዘለላው የጠነከረና ቀጥ ብሎ የቆመ ጊዜ ነው።
ለ) በተምር ፍሬ:- ወደ ቀይነት ወይም ቢጫነት የተለወጠ ጊዜ ነው።
ሐ) በወይን ፍሬ:- ለስላሳና ጣፋጭ በሆነ ጊዜ ነው።
የዘካ መጠናቸው:
የእህል ዘሮችና የፍሬዎች የዘካ መጠን: አምስት ወሰቅ መድረሱ ነው። አንድ ወሰቅ ስልሳ ቁና ነው። የዘካ መጠን የሆነው አምስቱ ወሰቅ ሶስት መቶ ነቢያዊ ቁና ያህል ነው። የዘካ መጠን ወደ ኪሎ ግራም ሲለወጥ 900 ኪግ አካባቢ ይደርሳል።
ይህን ያህል መጠን ያጨደ ወይም የለቀመ ሰው ግዴታ የሚሆንበት የዘካ መጠን:
ዘሩንና ዛፉን ያለምንም ልፋትና ወጪ እንደ ዝናብና ምንጭ በመሰሉ ያጠጣ ሰው አንድ አስረኛ (10%) ያህል ዘካ የማውጣት ግዴታ አለበት።
በእንስሳና ዘመናዊ መሳሪያዎች ከወንዝና ጉድጓድ እያመላለሰ በልፋትና ወጪ ውሃ ያጠጣ ደግሞ የአንድ አስረኛ (10%) ግማሽ ያህል (5%) ዘካ የማውጣት ግዴታ አለበት።
ሁለተኛው አይነት: ማዕድን:
ከመሬት ከሚወጡ ነገሮች መካከል አንዱ ማዕድን ነው። ማዕድን ማለት: እንደ ወርቅ፣ ብር፣ ብረትና ጌጣጌጦችን የመሰሉ የመሬት ክፍል ያልሆኑ ነገር ግን ከመሬት የሚወጡ ንጥረ ነገሮች ናቸው።
የማዕድን ዘካ ግዴታ የሚሆንበት ወቅት:
በእጁ ያስገባና የተቆጣጠረው ጊዜ በቀጥታ ዓመት መሙላቱን ሳይጠብቅ ዘካውን ያወጣል። የዘካ መጠኑም የወርቅና ብር የዘካ መጠን ያህል የደረሰ ጊዜ ነው። ከርሱም የአንድ አስረኛ (10%) ሩብ (2.5%) ያህሉን ዋጋ ለዘካ ያወጣል።
ሶስተኛ: (የመገበያያ ገንዘብ) የወርቅና ብር ዘካ:
የመገበያያ ገንዘብ የሚባሉት: ወርቅ፣ ብርና የወረቀት ገንዘቦች ናቸው። የነርሱን ዘካ ማውጣት ግዴታ ነው። ማስረጃውም: የሚከተለው የአላህ ንግግር ነው:
﴿...وَالَّذِينَ يَكْنِزُونَ الذَّهَبَ وَالْفِضَّةَ وَلَا يُنْفِقُونَهَا فِي سَبِيلِ اللَّهِ فَبَشِّرْهُمْ بِعَذَابٍ أَلِيمٍ 34﴾
{እነዚያንም ወርቅንና ብርን የሚያደልቡትን በአላህም መንገድ ላይ የማያወጧትን በአሳማሚ ቅጣት አብስራቸው። 34} [አት ተውባህ፡ 34]
በሐዲሥ እንደተላለፈው:
«مَا مِنْ صَاحِبِ ذَهَبٍ وَلَا فِضَّةٍ لَا يُؤَدِّي فِيهَا حَقَّهَا؛ إِلَّا إِذَا كَانَ يَوْمَ الْقِيَامَةِ صُفِّحَتْ لَهُ صَفَائِحُ مِنْ نَارٍ».
"የወርቅና የብር ባለቤት ሆኖ ሐቃቸውን የማይወጣ ሰው የትንሳኤ ቀን ለርሱ የእሳት ዝርግ ተዘርግቶለት በርሷ በጀሃነም እሳት ውስጥ ሳይቃጠል የሚቀር የለም።"45
ዑለማዎች ባጠቃላይ ለወርቅና ብር ዘካ ማውጣት ግዴታ እንደሆነ ተስማምተዋል። የወረቀት ገንዘብ በመገበያያነት ረገድ የወርቅንና የብርን ቦታ ስለተካ ብይኑም ከወርቅና ብር ብይን ጋር ተመሳሳይ ነው።
የመገበያያ ገንዘቦች የዘካ መነሻ መጠንና ለዘካ ግዴታ የሚሆንብን መጠን:-
ወርቅና ብር የመገበያያ ገንዘብ መሰረት ስለሆኑ የመገበያያ ገንዘብ የዘካ መነሻ መጠን ሲባል የወርቅ ወይም የብር የዘካ መነሻ መጠን ማለት ነው። የአንዳቸው የዘካ መነሻ መጠን የደረሰ ጊዜ ዘካውን ማውጣት ግዴታ ነው። በብዛት ዛሬ ላይ የምንገበያይበት የወረቀት ገንዘብን የዘካ መጠን በብር የዘካ መነሻ መጠን መሰረት ይተገበራል። ምክንያቱም ብር ከወርቅ ይልቅ ርካሽ ስለሆነ የወረቀት ገንዘባችንም የወርቅ የዘካ መነሻ መጠን ከመድረሱ በፊት የብርን የዘካ መጠን ቀድሞ ስለሚደርስ ነው። አንድ ሙስሊም (595) ግራም ብር የሚገዛ ገንዘብ ካለውና ገንዘቡ በቁጥጥሩ እያለ ዓመት ከዞረ ዘካ ማውጣት ግዴታው ይሆናል። የአንድ ግራም ብር ዋጋ እንደየ ወቅቱ ከፍና ዝቅ ይላል። እርሱ ዘንድ የተወሰነ የወረቀት ገንዘብ ኖሮት ለዘካ መጠን ደርሷል ወይስ አልደረሰም? የሚለውን ያላወቀ የብር ነጋዴዎችን የአንድ ግራም ዋጋ ስንት እንደገባ በመጠየቅ ከዚያም በ(595) ግራም በማባዛት በውጤቱ ወቅታዊው የዘካ መጠን ስንት እንደሆነ ማወቅ ይችላል።
ማስታወሻ: የገንዘቡን ዘካ ማውጣት ከፈለገ ለዘካ መጠን የደረሰውን ገንዘቡን ለአርባ አካፍሎ ሊያወጣው ግዴታ የሆነበትን የዘካ መጠን ማግኘት ይችላል።
አራተኛ: የንግድ ሸቀጥ ዘካ:
የንግድ ሸቀጥ ዘካ የሚባለው: ማትረፍ ታስቦበት ለመሸጥና ለመግዛት የተዘጋጀ ንብረት ማለት ነው። የንግድ ሸቀጥ ሲባል ከመገበያያ ገንዘብ ውጪ ያሉ ሁሉንም ነገሮች ያጠቃልላል። መኪና፣ ልብስ፣ ብትን ጨርቅ፣ ብረት፣ እንጨትና ሌሎችንም ለንግድ የተዘጋጁን ነገሮች ሁሉ ያካትታል።
የንግድ ሸቀጥ ዘካ ግዴታ የሚሆንበት መስፈርቶች:
1 - በራሱ እንቅስቃሴ የሸቀጡ ባለቤት መሆን:- ለምሳሌ: በመሸጥ፣ በመከራየትና ከዚህም ውጪ ባሉ የስራ መስኮች ያገኘው ሸቀጥ መሆን አለበት።
2 - ሸቀጡን የግሉ ሲያደርግ በንግድ ኒያ (አላማ) መሆን አለበት:- በሸቀጡ መስራትን ማሰብ አለበት። በሸሪዓ ስራዎች ግምት ውስጥ የሚገቡት በኒያ (እንደታለመላቸው አላማ) ነው። ንግድ ስራ ስለሆነ እንደሌሎች ስራዎች ከኒያ ጋር ተቆራኝቶ መፈፀሙ ግዴታ ነው።
3 - የሸቀጡ ዋጋ በወርቅ ወይም በብር ለዘካ መነሻ መጠን የደረሰ መሆን አለበት።
4 - አንድ ዓመት መዞር አለበት። ማለትም አንድ ዓመት ማለፍ አለበት።
የንግድ ሸቀጥ ዘካ አወጣጥ ሁኔታ:
የንግዱ ሸቀጥ ዓመት በሚሞላ ወቅት በወርቅ ወይም በብር ልኬት ይገመታል። ከተገመተ በኋላ በወርቅ ወይም በብር በአንዱ ልኬት የዘካ መነሻ መጠን ያህል ከደረሰ የአስራቱ ሩብ (2.5%) ያህል ከንብረቱ ለዘካ ይወጣለታል።
አምስተኛ: ዘካተል ፊጥር:
ዘካተል ፊጥር ማለት: የረመዷን ወር መጠናቀቂያ ወቅት ማውጣቱ ግዴታ የሆነ የምፅዋት አይነት ነው። ግዴታ የተደረገውም በሂጅራ ሁለተኛ ዓመት ወቅት ነው።
ብይኑ:
ዘካተል ፊጥር ለዒድ ቀንና ምሽት ለራሱና ለቤተሰቡ ከሚበቃው በላይ ምግብ የተረፈው ሙስሊም ላይ ሁሉ ግዴታ ነው። በሁሉም ወንድ ወይም ሴት፣ ህፃን ወይም ትልቅ፣ ነፃ ወይም ባሪያ ሙስሊም ላይ ሁሉ ግዴታ ነው። ይህም ለዚህ ሐዲሥ ሲባል ነው:
«فَرَضَ رَسُولُ اللَّهِ ﷺ زَكَاةَ الْفِطْرِ عَلَى الْعَبْدِ وَالْحُرِّ، وَالذَّكَرِ وَالْأُنثَى، وَالصَّغِيرِ وَالْكَبِيرِ، مِنَ الْمُسْلِمِينَ».
"የአላህ መልእክተኛ ﷺ በባሪያም ሆነ ጨዋ፤ በወንድም ሆነ በሴት፤ በልጅም ሆነ አዋቂ በሙስሊሞች ላይ ሁሉ ዘካተል ፊጥርን ግዴታ አድርገዋል።"46 ግዴታ አደረጉ ማለት የማይቀርና ግዳጅ አደረጉት ማለት ነው።
የመደንገጉ (ምስጢር) ጥበብ:
ኢብኑ ዐባስ (አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላቸውና) እንዲህ ብለዋል፡-
«فَرَضَ رَسُولُ اللَّهِ ﷺ زَكَاةَ الْفِطْرِ؛ طُهْرَةً لِلصَّائِمِ مِنَ اللَّغْوِ وَالرَّفَثِ، وَطُعْمَةً لِلْمَسَاكِينِ».
"የአላህ መልእክተኛ ﷺ ዘካተል ፊጥር ማውጣትን ፆመኛን ከከንቱ እና ፀያፍ ንግግር ለማንፃት እንዲሁም ለድሆች ደግሞ ምግብ እንዲሆን በግዴታነት ደነገጉ።"47
ግዴታ የሚሆንበትና የሚሰጥበት ወቅት:
ዘካተል ፊጥር የዒድ ዋዜማ እለት ፀሐይ ስትገባ ግዴታ ይሆናል። ለዒድ ሶላት ከመሄዱ በፊት የዒዱ ዕለት መስጠቱም ይወደዳል። ከዒድ ሶላት ማዘግየት አይፈቀድም። ከዒድ ሶላት ካዘገያት ቀዷእ አድርጎ ማውጣቱ ግዴታው ነው። ከተገደበለት ወቅት በማዘግየቱም ወንጀለኛ ይሆናል።
ከዒድ ቀን አንድ ወይም ሁለት ቀን ቀደም አድርጎ መስጠትም ይፈቀድለታል።
የሚወጣው የዘካ መጠን:
በሃገሩ ከተለመደው የእህል ዘር 1 ቁና ያህል ነው። ለምሳሌ ሩዝ፣ ተምር፣ ስንዴ ወይም ከሌሎችም መስጠት ይችላል። አንድ ቁና በኪግ ሲመዘን 3 ኪሎ ግራም አካባቢ ይሆናል። እህሉን በብር ተምኖ በእህል ፈንታ ብር መስጠት የመልክተኛውን ﷺ ትእዛዝ መቃረን ስለሆነ አይፈቀድም።
የዘካ አወጣጥ ስርዓትና ዘካ የሚሰጣቸው አካላት:
ዘካ የሚወጣበት ወቅት:
ዘካ ማውጣት ግዴታ በሆነበት ወቅት በፍጥነት ዘካውን ለሚገባው መስጠት ግዴታ ነው። ማዘግየቱ የግድ ካልሆነ በቀር ዘካን ማዘግየት አይፈቀድም። ለምሳሌ ገንዘቡ ያለው ሩቅ ሃገር ሆኖ በውክልና የሚያመጣለት ካልተገኘ ገንዘቡን በእጁ እስኪያስገባ ዘካውን ከማውጣት ማዘግየት ይፈቀድለታል።
ዘካ የሚወጣበት ስፍራ:
ገንዘቡ ያለበት ሃገር ለሚገኙ ዘካ ተቀባዮች ዘካን መስጠት በላጭ ነው። የሚከተሉት ሁኔታዎች ከተከሰቱ የዘካን ገንዘብ ከአንድ ሃገር ወደ ሌላ ሃገር ማዘዋወር ይፈቀዳል:-
ሀ) ዘካው በሚወጣበት ሃገር ውስጥ ዘካን ፈላጊ ከሌለ፤
ለ) የቅርብ ዘመድ የሆነ ዘካን ፈላጊ ሌላ ሃገር የሚገኝ ከሆነ፤
ሐ) ወደ ሌላ ሃገር እንዲዘዋወር የሚገፋፋ ሸሪዓዊ ጥቅም የሚገኝ ከሆነ፤ ለምሳሌ ያህል በረሃብና ጎርፍ የተጎዱ ሙስሊሞች ወደሚኖሩበት አካባቢዎች ማዘዋወር ይጠቀሳል።
የህፃንና የእብድ ገንዘብም በዘካ ጉዳይ የመጡ ማስረጃዎች ስለሚያጠቃልሏቸው ዘካ ይወጣበታል። ዘካቸውን የማውጣት ሃላፊነትንም ሞግዚታቸው ይወጣዋል። ዘካን ነይቶ (አስቦ) ካልሆነ በቀር ማውጣት አይፈቀድም። ነቢዩ ﷺ እንዲህ ብለዋልና:
«إِنَّمَا الْأَعْمَالُ بِالنِّيَّاتِ».
"ሥራ የሚለካው በኒያ ብቻ ነው።"48
ዘካ ተቀባዮች:
ዘካ የሚሰጣቸው አካላት ስምንት አይነት ሰዎች ናቸው:
የመጀመሪያው: ድሃዎች:-
ድሃዎች የሚባሉት: እንደ መጠለያ ቤት፣ ምግብና ልብስ የመሰሉ በመሰረታዊነት የሚያስፈልጋቸውን ነገሮች በበቂ መልኩ ያላገኙ ናቸው። ከዘካ የሚሰጣቸውም ለራሳቸውና በስራቸው ለሚያስተዳድሯቸው ለዓንድ አመት የሚበቃቸውን ያህል (ድረስ) ነው።
ሁለተኛው: ሚስኪኖች:-
ሚስኪኖች የሚባሉት: የሚያስፈልጋቸውን አብዛኛው መጠን የሚያገኙ ቢሆንም ነገር ግን በመሰረታዊነት ከሚያስፈልጋቸው መጠን የተወሰነ የጎደለባቸው ናቸው። ለምሳሌ ያህል ደሞዝተኛ ሆኖ ነገር ግን ደሞዙ ለአመት ያህል የማያደርሰው የሆነ ሰው ነው።
ለነዚህ የሚሰጣቸውም የዘካ መጠን: ለራሳቸውና ለሚያስተዳድሯቸው ለዓመት ከመሰረታዊ ፍላጎታቸው የጎደላቸውን ማሟያ ያህል ነው።
ሶስተኛው: ዘካ በመሰብሰብ ላይ የሚሰሩ:
ዘካ በመሰብሰብ ላይ የሚሰሩ የሚባሉት: አስተዳደሩ ዘካን እንዲሰበስቡ ሃላፊነት የሰጣቸው ወይም የተሰበሰበውን ዘካ የመጠበቅ ሃላፊነት የተሰጣቸው ወይም ዘካ ለሚገባቸው ሰዎች የማድረስን ሃላፊነት የተሰጣቸው ናቸው።
የሚሰጣቸው የዘካ መጠንም: በሃገሪቱ የተመደበላቸው የደሞዝ ወይም የቅጥር ክፍያ ከሌላቸው በስራቸው የክፍያ መጠን ያህል ነው።
አራተኛው: ልባቸውን ለማላመድ:-
እነርሱም: የዘካ ገንዘብ ከተሰጠው ይሰልማል ወይም ኢማኑ ይጠነክራል ወይም ሙስሊሞች ላይ ከሚያደርሰው ክፋት ይቆጠባል ተብሎ ተስፋ የሚጣልበት ነው።
የሚሰጣቸው የዘካ መጠንም: ቢሰጣቸው የልባቸው መላመድ ይገኝበታል የሚባልበት ያህል ነው።
አምስተኛው: ጫንቃን ከባርነት ነፃ ለማውጣት:-
በዚህ የሚፈለገውም: ባሪያንና የተፃፃፈን ባሪያ ማለት ነው።
የተፃፃፈ ባሪያ ማለት: ከአሳዳሪው ጋር ከባርነት ነፃ ለመውጣት በክፍያ መጠን ተስማምቶ ከፍሎ ራሱን ገዝቶ ነፃ ለማውጣት የተስማማ ማለት ነው። በጦርነት የተማረኩን ሙስሊም እስረኞች ከፍሎ ነፃ ማውጣትም እዚህ ውስጥ ይካተታል።
ስድስተኛው: ባለዕዳዎች ናቸው። እነርሱም ሁለት አይነት ናቸው:-
የመጀመሪያው: ለራሱ ጉዳይ የተበደረው እዳ ያለበትና እዳውን መክፈያ ገንዘብ ያላገኘ ነው። ለዚህም እዳውን የሚከፍልበት ያህል ይሰጠዋል።
ሁለተኛው: በሁለት ሰዎች መካከል ለማስታረቅ ሲል ራሱ ላይ እዳን የጫነ ሰው ነው። ይህ ሃብታም እንኳ ቢሆን እዳውን የሚከፍልበትን ያህል ይሰጠዋል።
ሰባተኛው: በአላህ መንገድ:-
እነዚህም በአላህ መንገድ የሚታገሉ ሰዎች ናቸው።
የሚሰጣቸው የዘካ መጠንም በአላህ መንገድ ለመታገል የሚበቃቸውን መጓጓዣ፣ መሳሪያ፣ ስንቅና ከዚህም ውጪ ለውጊያ የሚያስፈልጋቸውን ያህል ነው።
ስምንተኛው: መንገደኛ:-
መንገደኛ ማለት: ቀለቡ አልቆበት ወይም ተሰርቆ ወደ ሃገሩ የሚያደርሰው ገንዘብ ያልተረፈው ነው።
የሚሰጣቸው የዘካ መጠንም: በሃገሩ ሃብታም እንኳ ቢሆን ወደ ሃገሩ የሚያደርሰውን ያህል መጠን ነው።
ክፍል አራት: ፆም
ፆም ማለት:
ፆም ማለት: ጎህ ከቀደደበት ጊዜ ጀምሮ ፀሐይ እስክትጠልቅ ድረስ አላህን ለማምለክ በማሰብ ፆምን ከሚያፈርሱ ነገራቶች መታቀብ ነው።
የረመዳንን ወር መፆም ከእስልምና መሰረቶች መካከል አንዱ ነው። አላህ ግዴታ ካደረጋቸው ግዴታዎች መካከል አንዱ ነው። በእስልምና ሃይማኖት ውስጥ የፆም ግዴታነት ሙስሊም በመሆን ብቻ የሚታወቅ ነው። ለግዴታነቱም የቁርአንም የሐዲሥም ይሁን የኢስላም ሊቃውንት ስምምነት ማስረጃ አለ።
አላህ እንዲህ ብሏል፡
﴿شَهۡرُ رَمَضَانَ ٱلَّذِيٓ أُنزِلَ فِيهِ ٱلۡقُرۡءَانُ هُدٗى لِّلنَّاسِ وَبَيِّنَٰتٖ مِّنَ ٱلۡهُدَىٰ وَٱلۡفُرۡقَانِۚ فَمَن شَهِدَ مِنكُمُ ٱلشَّهۡرَ فَلۡيَصُمۡهُ...﴾
{(እንድትጾሙ የተጻፈባችሁ) ያ በርሱ ውስጥ ለሰዎች መሪ ከቅን መንገድና (እውነትን ከውሸት) ከሚለዩም ገላጮች (አንቀጾች) ሲሆን ቁርኣን የተወረደበት የረመዳን ወር ነው። …} [አልበቀራህ: 185]
የረመዷን ወር ፆም ግዴታ የሚሆንበት መስፈርቶች:
1- ሙስሊም መሆን፤ ካፊር ቢፆም ተቀባይነት የለውም።
2 - አቅመ አዳም መድረስ:- ህፃን ልጅ የመፆም ግዴታ የለበትም። ጥሩን ከመጥፎው የለየ ህፃን ልጅ ቢፆም ፆሙ ለርሱ እንደሱና ጾም ይቆጠርለታል።
3 - የአይምሮ ጤነኝነት:- የአዕምሮ ህመምተኛ የመፆም ግዴታ የለበትም። ከእብደቱ ጋር ቢፆምም ፆሙ ትክክለኛ ኒያ [ሃሳብ] ስለሚጎለው ትክክል አይሆንም።
4 - መፆም መቻል: መፆም የተሳነው በሽተኛ የመፆም ግዴታ የለበትም። ጉዞ በወጣ ላይም የመፆም ግዴታ የለበትም። እንዳይፆሙ የከለከላቸው ህመሙ ወይም ጉዞው በሚወገድላቸው ወቅት ቀዷ ያወጡታል። ሴት ልጅ ፆሟ ትክክለኛ እንዲሆን የወር አበባና የወሊድ ደሟ መቋረጡ መስፈርት ነው።
የረመዷን ወር መግባቱ የሚረጋገጠው ከሁለት መንገዶች በአንዱ ነው። እነርሱም:
ሀ) የረመዷንን ወር ጨረቃ መመልከት፣ ነቢዩ ﷺ እንዲህ ብለዋልና:
«صُومُوا لِرُؤْيَتِهِ، وَأفْطِرُوا لِرُؤْيَتِهِ».
«(የረመዷንን) ጨረቃ ስታዩ ፆም ያዙ፣ (የሸዋልን) ጨረቃ ስታዩ ፆም ፍቱ።»49
ለ) የረመዷንን ጨረቃ ካልተመለከተ ወይም እንዳይመለከት ደመና ወይም አቧራ ወይም የመሳሰሉት ከጋረዱት የሸዕባንን ወር ሰላሳ አድርጎ በመሙላት። ነቢዩ ﷺ እንዲህ ብለዋልና:
«فَإِنْ غُمَّ عَلَيْكُمْ؛ فَأَكْمِلُوا عِدَّةَ شَعْبَانَ ثَلَاثِينَ يَوْمًا».
«ከተጋረደባችሁ ግን የሸዕባንን ቀናት ሰላሳ ሙሉት።»50
ለመፆም መነየት:-
ፆም እንደሌሎቹ አምልኮዎች ሁሉ ያለኒያ ትክክል አይሆንም። ለመፆም መነየት ግዴታ የሚሆንበት ወቅት ግዴታ ፆምና ሌላ ፆም ሲሆን ይለያያል። የዚህም ማብራሪያ እንደሚከተለው ነው:
የመጀመሪያው: ግዴታ ፆም: እንደ ረመዷን፣ ቀዷና የስለት ፆም ሲሆን ኒያው ጎህ ከመቅደዱ በፊት ምሽት ላይ መሆኑ ግዴታ ነው። ነቢዩ ﷺ እንዲህ ብለዋልና:
«مَن لَمْ يُبَيِّتْ الصِّيَامَ مِنَ اللَّيْلِ فَلَا صِيَامَ لَهُ».
«ጎህ ከመቅደዱ በፊት አስቀድሞ በምሽት የፆም ኒያን (ሃሳብን) ያላሳደረ ሰው ፆም የለውም።»51
ሁለተኛው: የሱና ፆም: አንድ ሰው ቀን ላይ ቢነይተው ፆሙ ትክክለኛ ነው። ነገር ግን ጎህ ከቀደደ በኋላ ፆምን የሚያስፈቱ ነገሮችን አለመውሰዱ መስፈርት ነው።
ፆምን የሚያበላሹ ነገሮች:
የመጀመሪያው: ግብረስጋ ግንኙነት: ግንኙነት የፈፀመ ሰው ፆሙ ይበላሻል። በግንኙነት የተበላሸበትን ቀንም ቀዷ ማውጣት ግዴታው ይሆናል። ከቀዷ በተጨማሪ የወንጀሉን ማካካሻ (ከፋራ) የማውጣት ግዴታም አለበት። የሚያወጣው ከፋራም: ባሪያን ነፃ ማውጣት ነው፤ ነፃ የሚያወጣው ባሪያ ከሌለ ሁለት ወር አከታትሎ መፆም ግዴታው ይሆናል። በሸሪዓ ተቀባይነት ላለው ምክንያት ሁለት ወር በተከታታይ መፆም ያልቻለ ሰው ስልሳ ሚስኪን ማብላት አለበት። ለእያንዳንዱ ሚስኪንም በሃገሪቱ የሚበላን ግማሽ ግማሽ ቁና እህል ይሰጣል።
ሁለተኛው: የዘር ፈሳሽ ማፍሰስ: በመሳም ወይም በመዳበስ ወይም በእጅ ነካክቶ በማፍሰስ ወይም ደጋግሞ በመመልከት ምክንያት የዘር ፈሳሹን ያፈሰሰ ከፋራ ባይኖርበትም ቀዷ ማውጣት ግዴታ ይሆንበታል። ከፋራ ማውጣት ግዴታ የሚሆነው በግንኙነት ምክንያት ፆሙን ባፈረሰ ላይ ብቻ ነው። የተኛ ሰው በእንቅልፍ ውስጥ የዘር ፈሳሽ ቢፈሰው ያለምርጫው ስለፈሰሰው ለጀናባው ይታጠባል እንጂ ምንም አይጠበቅበትም።
ሶስተኛው: ሆንብሎ መብላትና መጠጣት ነው። ምክንያቱም የላቀው አላህ እንዲህ ብሏልና፦
﴿...وَكُلُواْ وَٱشۡرَبُواْ حَتَّىٰ يَتَبَيَّنَ لَكُمُ ٱلۡخَيۡطُ ٱلۡأَبۡيَضُ مِنَ ٱلۡخَيۡطِ ٱلۡأَسۡوَدِ مِنَ ٱلۡفَجۡرِۖ ثُمَّ أَتِمُّواْ ٱلصِّيَامَ إِلَى ٱلَّيۡلِ...﴾
{ከጎህ የሆነው ነጩ ክርም ከጥቁሩ ክር (ከሌሊት ጨለማ) ለእናንተ እስከሚገልጽላችሁ ድረስ ብሉ፤ ጠጡም፡፡ ከዚያም ፆምን እስከ ሌሊቱ ድረስ ሙሉ።…} [አልበቀራህ: 187]
ረስቶ የበላ ወይም የጠጣ ሰው ግን ምንም አይኖርበትም። ይህም ለተከታዩ ሐዲሥ ሲባል ነው:
«مَن نَسِيَ وَهُوَ صَائِمٌ، فَأَكَلَ أَوْ شَرِبَ، فَلْيُتِمَّ صَوْمَهُ، فَإِنَّمَا أَطْعَمَهُ اللَّهُ وَسَقَاهُ».
«ፆመኛ መሆኑን ረስቶ የበላ ወይም የጠጣ ሰው ጾሙን ይሙላ። ያበላውና ያጠጣው አላህ ነውና።"»52
አራተኛ- ሆንብሎ ማስመለስ፡ ያለ ፍላጎቱ ትውከቱ አሸንፎት የወጣ ከሆነ ግን ፆሙ ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ የለም። ነቢዩ ﷺ እንዲህ ብለዋልና:
«مَنْ ذَرَعَهُ الْقَيءُ فَلَيْسَ عَلَيْهِ قَضَاءٌ، وَمَن اسْتَقَاءَ عَمْدًا فَلْيَقْضِ».
«ትውከቱ አሸንፎት ያስመለሰ ሰው ቀዷ ማውጣት አይጠበቅበትም፤ ሆን ብሎ ያስታወከ ግን ቀዷእ ማውጣት አለበት።»53
አምስተኛ: ደም ማውጣት: በዋግምትም ይሁን በመበጣት ወይም በሽተኛን ለመርዳት በሚል ደም ለመለገስ የሚወጣ ደም ሁሉ ፆምን ያስፈታል። ለምርመራ ተብሎ የሚወሰደው ጥቂት ደም ፆሙ ላይ የሚፈጥረው ተፅዕኖ የለም። እንደ ነስር፣ የቁስል ደም፣ በጥርስ መነቀልና መሰል ምክንያት ፆመኛ ያለፍላጎቱ የሚወጣው ደም ፆሙ ላይ የሚፈጥረው ተፅዕኖ የለም።
በረመዷን አለመፆም የሚፈቀድላቸው ሰዎች:
የመጀመሪያው ክፍል: አለመጾም ቢፈቀድላቸውም ያልፆሙትን ቀን ግን ቀዷ ማውጣት ግዴታ የሚሆንባቸው። እነርሱም:
የመጀመሪያው: የመዳን ተስፋ ያለው በሽታን የታመመ በሽተኛ ከመሆኑም ጋር ቢፆም የሚጎዳ ወይም የሚከብደው ከሆነ፣
ሁለተኛው: ጉዞ የወጣ ሰው: በጉዞው ምክንያት ችግር አጋጠመውም አላገጠመውም አለመፆም ይችላል።
የሁለቱ ማስረጃው የሚከተለው የአላህ ንግግር ነው:
﴿...وَمَن كَانَ مَرِيضًا أَوۡ عَلَىٰ سَفَرٖ فَعِدَّةٞ مِّنۡ أَيَّامٍ أُخَرَ...﴾
{…በሽተኛ ወይም በጉዞ ላይ የሆነም ሰው ከሌሎች ቀኖች ቁጥሮችን (በልኩ) መፆም አለበት።…} [አልበቀራህ: 185]
ሶስተኛው: እርጉዝ ወይም አጥቢ ሆና መፆም የሚከብዳት ወይም የሚጎዳት ወይም ልጇን የሚጎዳ ከሆነ የበሽተኛ ብይን ነው የሚኖራት። ስለዚህም አለመፆም ይፈቀድላታል። ነገር ግን በሌላ ወቅት ያልፆመችውን ቀን ቀዷ ማውጣት ግዴታዋ ነው።
አራተኛው: የወር አበባ ላይና የወሊድ ደም ላይ ያለች ሴት ናት:- በነርሱ ላይ አለመፆም ግዴታ ነው። ቢፆሙም ፆማቸው ትክክለኛ አይሆንም። ከፀዱ በኋላ በሌላ ጊዜ ቀዷእ ማውጣት ግዴታቸው ነው።
ሁለተኛው ክፍል: አለመፆም የሚፈቀድላቸው። ባለመፆማቸውም ቀዷእ ሳይሆን ከፋራ (ያለመፆማቸው ማካካሻ) የማውጣት ግዴታ ያለባቸው። እነርሱም:
የመጀመሪያው: የመዳን ተስፋ የሌለውን በሽታ የታመመ ሰው፤
ሁለተኛው: መፆም የማይችሉ በእድሜ የገፉ አዛውንቶች ናቸው።
እነዚህ ባጠቃላይ አይፆሙም በረመዷን ወር ለማይፆሙት እያንዳንዱ ቀን አንድ ሚስኪን ያበላሉ። ሽማግሌው በእርጅናው ምክንያት አይምሮው ከጃጀ ከርሱ ላይ ተጠያቂነት ስለሚነሳ አይፆምም። ቀዷእና ከፋራም አይኖርበትም ምንም ማድረግም አይጠበቅበትም።
የቀዷእ ወቅትና የማዘግየት ብይን:
የረመዷንን ቀዷእ ባልፆመበት ረመዷንና በቀጣዩ ረመዷን መካከል መፆም ግዴታ ነው። በላጩም ቀዷእን ለማውጣት መቻኮሉ ነው። ቀዷእን ቀጣዩ ረመዷን እስኪገባ ማዘግየት አይፈቀድም። ዓኢሻ -አላህ መልካም ሥራዋን ይውደድላትና - ባስተላለፈችው ሐዲሥ እንዲህ ብላለች፡-
«كَانَ يَكُونُ عَلَيَّ الصَّوْمُ مِنْ رَمَضَانَ، فَمَا أَسْتَطِيعُ أَنْ أَقْضِيَ إِلَّا فِي شَعْبَانَ لِمَكَانِ رَسُولِ اللهِ ﷺ».
«ከረመዳን ቀዳ ማውጣት የሚጠበቅብኝ (መፆም ያለብኝ) ቀን ይኖርብኛና ነገር ግን በአላህ መልዕክተኛ (የአላህ ሶላትና ሰላም በርሳቸው ላይ ይስፈንና) ተጠምጄ ስለምቆይ ከሸዕባን ወር በስተቀር እነሱን ማካካስ አልችልም ነበር።»54
ያመለጠውን የረመዷን ቀናት ሳያካክስ ቀጣዩ ረመዷን የደረሰበት ሰው ሁለት ሁኔታዎች ይኖሩታል:
1 - ያዘገየው በቂ በሆነ ሸሪዓዊ ምክንያት ከሆነ ለምሳሌ: ህመሙ እስከ ቀጣዩ ረመዷን ድረስ ቆይቶበት ከሆነ የሚጠበቅበት ቀዷእ ማውጣት ብቻ ነው።
2 - ያለ በቂ ሸሪዓዊ ምክንያት ያዘገየው ከሆነ በማዘግየቱ ምክንያት ወንጀል ውስጥ ወድቋል። በርሱም ላይ ተውበት ማድረግ፣ ቀዷእና በተጨማሪ ለየቀኑ ሚስኪንን የማብላት ግዴታ አለበት።
ቀዷእ ያለበት ሰው ሱና ፆም መፆሙ:
የረመዷን ቀዷእ ላለበት ሰው በላጩ ሱና ፆም ከመፆሙ በፊት ቀዷእን ለማውጣት መቻኮል ነው። ነገር ግን የሚፆመው ሱና ፆም እንደ ዓረፋና ዓሹራእ ካልተፆመ ወቅቱ የሚያልፍ ከሆነ ከቀዷእ በፊትም ቢሆን ይፆማቸዋል። ምክንያቱም የቀዷእ ወቅቱ ሰፊ ሲሆን የዓሹራና የዓረፋ ቀናት ግን በእለቱ ካልተፆመ የሚያመልጥ ነውና። ነገር ግን የሸዋልን የስድስት ቀን ፆም ከቀዷእ በኋላ ካልሆነ አይፆማቸውም።
መፆም የተከለከለባቸው ቀናት:
1 - የዒደል ፊጥርና የዒደል አድሓን ቀን መፆም ስለተከለከለ መፆም አይቻልም።
2 - የዙልሒጃን ወር አይያመ ተሽሪቅ ቀናቶችን መፆም። ሐጅ ላይ ተመቱዕ ወይም ቂራን ኢሕራም አድርጎ የሚያርደው ሀድይ ያላገኘ ሰው ካልሆነ በቀር ለሌላው መፆም አይፈቀድም። አይያመ ተሽሪቅ የሚባሉት ቀናቶች: የዙልሒጃ አስራ አንደኛ፣ አስራ ሁለተኛና አስራ ሶስተኛ ቀኖች ናቸው።
3 - የጥርጣሬ ቀንን ስለተጠራጠረ ብሎ መፆም አይፈቀድም። የጥርጣሬ ቀን የሚባለው የሸዕባን ሰላሳኛ ቀን ነው። ምሽቱ ደመናማ ወይም በአቧራ የተሸፈነ ሆኖ ጨረቃን ከመመልከት የሚጋርደው ከሆነ ቀጣዩ ቀን የጥርጣሬ ቀን ይባላል።
ፆም የሚጠላባቸው ቀኖች:
ሀ - የረጀብን ወር ለይቶ መጾም፤ ለ- የጁመዓን ቀን ለይቶ መፆም ይህም ክልከላ መጥቶበታልና፤ ከጁመዓ አንድ ቀን በፊት ወይም በኋላ ከፆመ ጁሙዓ ቀንን ለይቶ መፆም ስለማይሆን አይጠላም።
ሱና ፆሞች:
ሀ) ከሸዋል ወር ስድስት ቀን መፆም፤ ለ) የዙልሒጃን ዘጠኝ ቀናት መፆም። የሐጅ ተግባር ላይ ላልሆነ ሰው በላጩ ቀን ዘጠነኛውን ቀን መፆም ነው። ሐጅ ላይ የሆነ ሰው የዙልሒጃን ዘጠነኛ ቀን መጾሙ ሱና አይሆንለትም። ለሌላው ግን የዘጠነኛን ቀን መፆም የሁለት ዓመት ወንጀል ያስምራል። ሐ) በየወሩ ሶስት ቀን መፆም። በላጩ ጨረቃ ሙሉ የሚሆኑበትን ቀናት መፆም ነው፤ እነሱም በሂጅራ አቆጣጠር የወሩ 13ኛ፣ 14ኛና 15ኛን ቀን መፆም ነው። መ) በየሳምንቱ ሰኞና ሀሙስን መፆም፤ የባሮች ስራ ሰኞና ሀሙስ አላህ ዘንድ ስለሚቀርቡ ነቢዩ ﷺ ይፆሙት ነበርና።
ትርፍ ፆሞች:
ሀ) የዳውድ (ዐለይሂ ሰላም) ፆም፤ ዳውድ (ዐለይሂ ሰላም) አንድ ቀን እየፆመ አንድ ቀን ያፈጥር ነበር።
ለ) የአላህ ወር ሙሐረም ላይ መፆም፤ የሙሐረም ወር መፆሙ የሚወደድ በላጩ ወር ነው። ከሙሐረም ወርም እጅግ ተወዳጁ ቀን: የዐሹራን ቀን መፆም ነው። የዐሹራ ቀን የሙሐረም አስረኛው ቀን ነው። ከአስረኛው ቀን በተጨማሪ ዘጠነኛውንም አብሮ መፆሙ ይበረታታል። ይህም ነቢዩ ﷺ እንዲህ ስላሉ ነው:
«لَئِنْ بَقِيتُ إِلَى قَابِلٍ لَأَصُومَنَّ التَّاسِعَ».
«ለቀጣይ ዓመት በህይወት ከኖርኩ ዘጠነኛውንም ቀን እፆማለሁ።»55 የዓሹራን ቀን መፆም ያለፈውን አንድ ዓመት ወንጀል ያስምራል።
ክፍል አምስት: ሐጅና ዑምራ
ሐጅ በቋንቋ ትርጓሜው ማሰብ ማለት ነው። በሸሪዓ ትርጓሜው ደግሞ በተገደቡ ወቅቶች ልዩ የሆኑ አምልኮዎችን ለመፈፀም የተከበረውን የአላህን ቤትና መሻዒሮችን (የሐጅ መገለጫዎችን) ማሰብ ማለት ነው።
ዑምራ ማለት በቋንቋ ትርጓሜው ጉብኝት (ዚያራ) ማለት ነው።
በሸሪዓ ትርጓሜው ደግሞ: በማንኛውም ወቅት ልዩ የሆኑ አምልኮዎችን ለመፈፀም የተከበረውን የአላህን ቤት መጎብኘት ማለት ነው።
ሐጅ ከእስልምና ማዕዘናት መካከል አንዱና ትልቁ መሰረት ነው። ግዴታ የተደረገውም በሂጅራ ዘጠነኛ አመት ወቅት ነው። ነቢዩ ﷺ ሐጅ ያደረጉት አንድ ጊዜ ብቻ ነው። እሱም (ሐጀቱል ወዳዕን) የመሰናበቻው ሐጅን ነው።
ሐጅ አቅሙ ላለው ሰው ግዴታ የሚሆነው በህይወት ዘመን አንድ ጊዜ ብቻ ነው። ከዛ ከጨመረ ትርፍ (ሱና) ነው የሚሆንለት። ዑምራም በበርካታ ዑለማዎች አቋም መሰረት ግዴታ ነው። ማስረጃውም ነቢዩ ﷺ «ሴቶች ጂሃድ የማድረግ ግዴታ አለባቸውን?» ተብለው ሲጠየቁ። እንዲህ ማለታቸው ነው:
«نَعَمْ، عَلَيْهِنَّ جِهَادٌ لَا قِتَالَ فِيهِ: الْحَجُّ وَالْعُمْرَةُ».
«አዎ ውጊያ የሌለው ጂሃድ የማድረግ ግዴታ አለባቸው። እነሱም ሐጅና ዑምራ ናቸው።»56
ሐጅና ዑምራ ግዴታ የሚሆኑበት መስፈርቶች:
1 - እስልምና፣
2 - የአይምሮ ጤነኝነት፣
3- ለአቅመ አዳም መድረስ፣
4- ከባርነት ነፃ መሆን፣
5 - መቻል ናቸው።
ሴት ከሆነች ስድስተኛ መስፈርት ትጨምራለች። እርሱም: ከርሷ ጋር አምልኮውን ለመፈፀም አብሯት የሚጓዝ መሕረም (ቅርብ ዘመድ) መኖር አለበት። ምክንያቱም ሴት ልጅ ያለ መሕረም (ቅርብ ዘመድ) ለሐጅም ሆነ ለሌላ አላማ መጓዝ አይፈቀድላትምና። ነቢዩ ﷺ እንዲህም ብለዋል:
«لَا تُسَافِرُ الْمَرْأَةُ إِلَّا مَعَ ذِي مَحْرَمٍ، وَلَا يَدْخُلُ عَلَيْهَا رَجُلٌ إِلَّا وَمَعَهَا مَحْرَمٌ».
«ሴት ልጅ ከመሕረም (ከቅርብ ዘመድ) ጋር ካልሆነ በቀር ጉዞ አትውጣ። ከርሷ ጋር መሕረም (ቅርብ ዘመድ) ካልኖረ በቀር ወደርሷ ወንድ አይግባ።»57
የሴት ልጅ መሕረም (ቅርብ ዘመድ) የሚባሉት: ባሏ ወይም እርሷን እስከመቼውም ማግባት የተከለከሉ ናቸው። በዘር: እንደ ወንድሟ፣ አባቷ፣ አጎቷና የወንድሟ ልጆች የመሰሉ ናቸው። ወይም በተፈቀደ ምክንያት ከጋብቻ የተከለከሉ አሉ: ለምሳሌ የጥቢ ወንድሟ፣ ወይም በአማችነት ምክንያት የተከለከሉ አሉ: የእናቷ ባል፣ የባሏ ልጅና የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ።
መቻል ማለት: ቁሳዊና አካላዊ ችሎታ መኖር ማለት ነው። ማለትም መጋለብ (መንዳት) የሚመቸው፣ መጓዝ የሚችልና ለደርሶ መልስ የሚበቃውን ገንዘብ የሚያገኝ መሆን አለበት። በተጨማሪ እስኪመለስ ድረስ ለልጆቹና መቀለብ ግዴታ ለሆነበት አካላቶች የሚበቃቸውን ያህል ቀለብ ሊተውላቸው ይገባል።
የሐጁ መንገድም ለነፍሱና ለገንዘቡ ደህንነቱ የተጠበቀ መሆን አለበት።
አካላዊ አቅም ባይኖረውም የገንዘብ አቅም ያለው ሰው ለምሳሌ እጅግ ያረጀ ሽማግሌ ወይም የመዳን ተስፋ የሌለው የአልጋ ቁራኛ በሽተኛ ሐጅና ዑምራ የሚያደርግለትን ሰው መመደብ ግዴታው ነው።
በሌላ ሰው ምትክ ለሐጅና ዑምራ የሚሄድ ሰው ትክክለኛ ሐጅ ወይም ዑምራ እንዲሆንለት ሁለት መስፈርቶች መሟላት አለባቸው:
1 - ግዴታ የሆነውን ሐጅ መፈፀም የሚፈቀድለት መሆን አለበት። እሱም ሙስሊም፣ ለአቅመ አዳም መድረስና የአይምሮ ጤነኛ መሆን አለበት።
2 - ለራሱ የሐጅ ግዴታውን የተወጣ መሆን አለበት።
የኢሕራም (ሚቃቶች) የኢሕራም ማድረጊያ ስፍራዎችና ወቅቶች:
መዋቂት ማለት: ሚቃት የሚለው የዐረብኛ ነጠላ ቃል ብዙ ቁጥር ነው። በቋንቋ ትርጓሜው: ገደብ ማለት ሲሆን በሸሪዓ ትርጓሜው ደግሞ: የአምልኮ ስፍራ ወይም ጊዜ ማለት ነው።
ለሐጅ ኢሕራም ማድረጊያ ስፍራና የጊዜ ዘመን አለው።
ሀ) የጊዜ ሚቃት (ለሐጅ ኢሕራም ማድረጊያ ጊዜያት): አላህ እንዲህ ሲል አውስቷቸዋል:
﴿ٱلۡحَجُّ أَشۡهُرٞ مَّعۡلُومَٰتٞۚ فَمَن فَرَضَ فِيهِنَّ ٱلۡحَجَّ...﴾
{ሐጅ (ጊዜያቱ) የታወቁ ወሮች ናቸው፡፡ በእነርሱም ውስጥ ሐጅን (እንዲሠራ) ነፍሱን ያስገደደ ሰው …} [አልበቀራህ: 197]
እነዚህ ወራቶችም: ሸዋል፣ ዙልቀዕዳና አስሩ የዙልሒጃ ቀናት ናቸው።
ለ) የስፍራ ሚቃት: ማለትም አንድ ሐጅ አድራጊ ያለ ኢሕራም ወደ መካ አልፎት መሄድ የማይፈቀድለት ድንበር ነው። ይህም እንደሚከተለው ነው:
1- ዙል-ሑለይፋ የመዲና ሰዎች ሚቃት ነው፣
2- አል-ጁሕፋህ: የሻም፣ ግብፅ እና ሞሮኮ ህዝቦች ሚቃት ነው፣
3 - ቀርነል መናዚል: ዛሬ ላይ ሰይል በመባል ይታወቃል። ይህም የነጅድ ሰዎች ሚቃት ነው፣
4- ዛቱ‐ዒርቅ: የዒራቅ ሰዎች ሚቃት ነው፣
5- የለምለም የየመን ሰዎች ሚቃት ነው።
ከነዚህ ኢሕራም ማድረጊያ ስፍራዎች ውጪ ወደ መካ ቅርብ የሆነ ሰው ለሐጅና ዑምራ ኢሕራም የሚያደርገው ከቤቱ ነው። የመካ ነዋሪዎች ከመካ ኢሕራም ያደርጋሉ። ኢሕራም ለማድረግም ወደ ኢሕራም ማድረጊያ ስፍራ (ሚቃት) መውጣት አይጠበቅባቸውም። (የመካ ሰዎች) ለዑምራ ኢሕራም ማድረግ ከፈለጉ ግን ከሐረም ክልል ውጪ ወደሆነ ቅርብ ስፍራ በመውጣት ነው ኢሕራም የሚያደርጉት። ሐጅ ወይም ዑምራ ማድረግ የፈለገ ሰው የአላህ መልክተኛ ﷺ ከወሰኑት ስፍራዎች ኢሕራም ማድረጉ የግድ ነው። እነርሱም ቀደም ብሎ የተጠቀሱት ኢሕራም ማድረጊያ ስፍራዎች (ሚቃቶች) ናቸው: ሐጅ ወይም ዑምራ ማድረግ የፈለገ ሰው ኢሕራም ማድረጊያ ስፍራዎችን ኢሕራም ሳያደርግ ማለፍ አይፈቀድለትም።
በነዚህ በተጠቀሱት ኢሕራም ማድረጊያ ስፍራዎች (በሚቃቶች) ነዋሪ ሳይሆን በነሱ በኩል የሚያልፍም በሚያልፍበት ሚቃት ነው ኢሕራም የሚያደርገው።
መንገዱ ወደ መካ ቢሆንም በየብስ ወይም በባሕር ወይም በአየር ሲጓዝ በተጠቀሱት ኢሕራም ማድረጊያ ስፍራዎች በኩል የማያልፍ ከሆነ ለርሱ ቅርብ ከሆነው ኢሕራም ማድረጊያ ስፍራ ጋር ትይዩ ሲሆን ኢሕራም ያደርጋል። ዑመር ቢን አል'ኸጧብ -አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላችውና- እንዲህ ብለዋል: «በመንገዳችሁ የሚቃትን ትይዩ አስተውሉ።»58
የሐጅን ወይም ዑምራን አምልኮ ለመፈፀም በአየር የሚጓዝ ከሆነ ፕሌኑ ከኢሕራም ማድረጊያ ስፍራው ጋር ትይዩ ሲሆን ኢሕራም ማድረጉ ግዴታ ነው። ፕሌኑ በአየር ማረፊያ እስኪያርፍ ድረስ መጠበቅ ኢሕራምን ማድረግ አይፈቀድለትም።
ኢሕራም:
ኢሕራም ማለት: ወደ ዑምራ ወይም ሐጅ ተግባር መግቢያ ኒያ ነው። የሐጅ ኢሕራም: የሐጅ ሥርዓቶችን ለመጀመር ኒያ (ቁርጠኛ ልባዊ ውሳኔ) ማድረግ ነው። የዑምራ ኢሕራም: የዑምራን ስርዓቶች ለመጀመር ኒያ (ቁርጠኛ ልባዊ ውሳኔ) ማድረግ ነው። ወደ ተግባራቱ ለመግባት እስካልነየተ ድረስ ኢሕራም አላደረገም። ያለኒያ የኢሕራምን ልብስ ስለለበሰ ብቻ ኢሕራም ያደረገ ሰው አይባልም።
በኢሕራም ወቅት የሚወደዱ:
1 - ኢሕራም ከማድረጉ በፊት አጠቃላይ ሰውነቱን መታጠብ፤
2 - ወንድ ከሆነ ከልብሶቹ ውጪ ሰውነቱን ብቻ ሽቶ መቀባባት፤
3 - ነጫጭ ሽርጥና ኩታ እንዲሁም ሸበጥ ለብሶ ኢሕራም ማድረጉ፤
4 - በሚጓዝ ወቅት ኢሕራም ካደረገ ወደ ቂብላ አቅጣጫ ዞሮ ኢሕራም ማድረጉ ይወደዳል።
የሐጅ አፈፃፀም አይነቶች:
ኢሕራም የሚያደርግ ሰው ከሶስቱ የሐጅ አፈፃፀሞች የፈለገውን ይመርጣል። እነርሱም:
1 - ተመቱዕ: ይህም በሐጅ ወራት ዑምራን ኢሕራም ማድረግና ዑምራን ሰርቶ ማጠናቀቅ ከዚያም በዛው አመት ሐጅን ኢሕራም ማድረግ ማለት ነው።
2 - ኢፍራድ: ይህም ኢሕራም ከማድረጊያ ስፍራው ሐጅን ብቻ ኢሕራም ማድረግና የሐጅ ተግባራትን ሰርቶ እስኪያጠናቅቅ ድረስም በኢሕራሙ ላይ መቆየት ማለት ነው።
3 - ቂራን ማለት: ሐጅና ዑምራን አቆራኝቶ ኢሕራም ማድረግ ወይም ዑምራን ብቻ ኢሕራም ያደርግና ከዚያም የዑምራን ጦዋፍ ማድረግ ከመጀመሩ በፊት የሐጅንም ኢሕራም ማካተት ማለት ነው። ኢሕራም ከማድረጊያ ስፍራ ወይም የዑምራን ጦዋፍ ከመጀመሩ በፊት ዑምራንና ሐጅን አቆራኝቶ እንደሚፈፅም መነየት አለበት። ለሁለቱም አንድ ጦዋፍና ሰዕይ (በሶፋና መርዋ መሮጥ) ያደርጋል።
የተመቱዕና ቂራን አፈፃፀም የሚያደርግ ሰው የተከበረው መስጂድ ነዋሪ እስካልሆነ ድረስ ፊዳ (ማካካሻ) ይጠበቅበታል።
ከሶስቱ የሐጅ አፈፃፀሞች በላጩ: ተመቱዕ ነው። ነቢዩ ﷺ ባልደረቦቻቸውን ያዘዙት ተመቱዕ እንዲያደርጉ ነው።59 ቀጥሎ ቂራን ነው። ይህም ሐጅንም ዑምራንም ስለሚያካትት ነው። ቀጥሎ ኢፍራድ ነው።
ሐ) ከነዚህ የሐጅ አፈፃፀሞች መካከል በአንዱ ኢሕራም እንዳደረገ ከኢሕራሙ ቀጥሎ በዚህ መልኩ ተልቢያ ይላል:
«لَبَّيْكَ اللَّهُمَّ لَبَّيْكَ، لَبَّيْكَ لَا شَرِيكَ لَكَ لَبَّيْكَ، إِنَّ الْحَمْدَ وَالنِّعْمَةَ لَكَ وَالْمُلْكَ لَا شَرِيكَ لَكَ».
«ለበይከል-ሏሁምመ ለበይክ፤ ለበይከ ላ ሸሪከ ለከ ለበይክ፣ ኢንነል-ሐምደ ወን-ኒዕመተ ለከ ወል-ሙልክ፤ ላ ሸሪከ ለክ»
(ትርጉሙ፦ "አላህ ሆይ! ጥሪህን ተቀብያለሁ፤ አሁንም! ጥሪህን ተቀብያለሁ፤ ላንተ አጋር የለህም፤ ምስጋና ሁሉ፤ ጸጋም ሁሉ፤ ንግስናም ላንተ ብቻ ነው፤ አጋር የለህም።")60
ተልቢያ ማለት ሱና ነው። አብዝቶ ማለቱም ይወደዳል። ወንድ ልጅ ድምፁን ከፍ አድርጎ ይላል። ሴት ከሆነች ደግሞ ድምጿን ዝግ ታደርጋለች።
ወቅቱ: የተልቢያ ወቅት ከኢሕራም በኋላ ይጀምራል። የሚጠናቀቅበት ወቅትም እንደሚከተለው ነው:
የመጀመሪያው: ዑምራ የሚያደርግ ሰው ጦዋፍ ከመጀመሩ በፊት ተልቢያውን ያቋርጣል።
ሁለተኛው: የሐጅ ተግባራት የሚሰራ ሰው የዒድ ቀን ጀምረተል ዓቀባ ዘንድ ጠጠር መወርወር ሲጀምር ተልቢያ ማለቱን ያቋርጣል።
በኢሕራም ወቅት የተከለከሉ ነገሮች
አንደኛ: ሰውነቱ ላይ የሚገኝን ማንኛውንም ፀጉር መላጨት ወይም ማሳጠር ወይም መንጨት፤
ሁለተኛ: ያለምንም በቂ ምክንያት የእጅንም ይሁን የእግር ጥፍርን መቁረጥ ወይም ማሳጠር፤ ጥፍሩ በራሱ ተሰብሮበት ቢያስወግደው ምንም ፊድያ (ማካካሻ) አይኖርበትም።
ሶስተኛ: ወንድ ከሆነ እንደ ኮፍያና ጥምጣም በመሰሉ ጭንቅላቱን በሚነካ ነገር ራሱን መሸፈኑ፤
አራተኛ: ወንድ ከሆነ እንደ ጀለቢያ ወይም ጥምጣም ወይም ሱሪ የመሰሉ ሙሉም ይሁን የተወሰነ የሰውነት ክፍሉ ላይ የተሰፋ ልብስ መልበስ፤ የተሰፋ ልብስ ማለት: በሰውነት ልክ ተመጥኖ የተሰፋ ማለት ነው። ለምሳሌ ያህል: ኹፎች፣ ጓንቶችና ካልሲዎች ይጠቀሳሉ። ሴት ልጅ ግን በኢሕራም ወቅት መሰተር ስላለባት የፈለገችውን ልብስ በመልበስ ትሸፈናለች። ነገር ግን ኒቃብ መልበስ አትችልም። በአጠገቧ ባዳ ወንዶች ሲያልፉም ፊቷን ከኒቃብ ውጪ ባሉ በሻርፗና ጅልባቧ መሸፈን ይጠበቅባታል። ልክ እንደዚሁ ጓንቶችንም ለመዳፏ አትለብስም።
አምስተኛ: ኢሕራም ላይ ያለ ሰው ከአለማዊ መቀማጠል፣ መጋጌጥና ምቾት ርቆ ራሱን ወደ አኺራ ማዞር ስለሚጠበቅበት ሽቶ መቀባት የለበትም።
ስድስተኛ: የየብስ ታዳኝን መግደል ወይም ማደን፤ ኢሕራም ላይ ያለ ሰው የየብስ ታዳኞችን አያድንም፣ ለአደንም ተባባሪ አይሆንም፣ አያርድምም።
ኢሕራም ላይ ያለ ሰው ያደነውን ወይም ለአደን የተባበረበትን ወይም ለርሱ ተብሎ የታደነለትን መብላት ይከለከላል። ይህም ታዳኝ ለርሱ እንደበክት የሚቆጠር በመሆኑ ነው።
ኢሕራም ላይ ያለ ሰው የባሕር ታዳኝን ማደኑ አይከለከልም። እንደ ዶሮ፣ ግመል፣ በሬ፣ በግና ፍየል የመሰሉ የቤት እንስሳዎችን ማረድም አደን ስላልሆነ አይከለከልም።
ሰባተኛ: ለራሱም ይሁን ለሌላ ሰው ጋብቻን ማሰር ወይም በጋብቻው ወቅት ምስክር መሆን፤
ስምንተኛ: ግብረ ስጋ ግንኙነት መፈፀም: ከመጀመሪያው የኢሕራም መፈታት በፊት ግንኙነት የፈፀመ ሰው የሐጁ ወይም የዑምራው ተግባር ይበላሻል። ስለዚህም አምልኮውን ቀጥሎ መሙላት፣ በቀጣይ አመት ቀዷ ማውጣትና ግመል ማረድ ግዴታው ነው። ከመጀመሪያው መፈታት በኋላ ከሆነ ግን አምልኮው ባይበላሽም ማረድ ይጠበቅበታል።
ሴት ልጅ ለግብረ ስጋ ግንኙነቱ ፍቃደኝነት ከነበራት በወንዱ ላይ ያለበት ሁሉ በርሷም ላይ አለባት።
ዘጠነኛ: ከብልት ውጪ ባለ አካል ስሜት ቀስቃሽ ንክኪን መተሻሸት፤ ኢሕራም ያደረገ ሰው ወደተከለከለው ግንኙነት ስለሚያደርሰው ሴት ጋር መተሻሸት አይፈቀድለትም። መተሻሸት በማለት የተፈለገው ሴትን በስሜት መነካካት ማለት ነው።
ዑምራ:
ሀ) የዑምራ ማዕዘናት:
1 - ኢሕራም
2: ጦዋፍ ማድረግ:
3: ሰዕይ (በሰፋና መርዋ መካከል መሮጥ) :
ለ) የዑምራ ግዴታዎች
1. (ከሚቃት) ከኢሕራም ማድረጊያ ስፍራ ኢሕራም ማድረግ፤
2: የራስ ፀጉሩን መላጨት ወይም ማሳጠር፤
ሐ) የዑምራ አደራረግ
ዑምራ የሚያደርግ ሰው በቅድሚያ ሰባት ዙር ጦዋፍ በማድረግ ነው የሚጀምረው፤ ጦዋፉንም ከሐጀረል አስወድ በመጀመር ሐጀረል አስወድ ጋር ያጠናቅቃል። ጦዋፍ ሲያደርግም ዉዱእ ኖሮትና ሀፍረተ ገላውን (ቢያንስ) ከእምብርት እስከ ጉልበቱ ሸፍኖ መሆን አለበት። በጦዋፎቹ ላይ ሁሉ የኢድጢባዕ አለባበስ መልበሱ ሱና ነው። እሱም: ቀኝ ትከሻውን በመግለጥ ኩታውን ከስሩ ማድረግና የኩታውን ጫፍና ጫፍ በግራ ትከሻው ላይ ማድረጉ ነው። ሰባተኛውን ዙር እንደጨረሰ የኢድጢባዕ አለባበስን በመተው በኩታው ትከሻዎቹን ይሸፍናል።
ወደ ሐጀረል አስወድ በመዞር ለመሳም ከተመቸው ይስመዋል ካልሆነ በቀኝ እጁ በመዳበስ እጁን ይስማል። ሐጀረል አስወድን በእጁ መዳበስ ካልቻለ ቀኝ እጁን ወደርሱ ከፍ አድርጎ በመጠቆም አንድ ጊዜ "አላሁ አክበር" ይላል። እጆቹን መሳምም ሆነ መቆም አይጠበቅበትም። ከዚያም ከዕባን ከግራው አድርጎ ጦዋፉን ይቀጥላል። በመጀመሪያዎቹ ሶስቱ ዙሮች (በረምል) በፈጣን እርምጃ መዞሩ ሱና ነው። ረምል ማለት: እርምጃዎቹን አቀራርቦ ፈጣን እርምጃ መራመድ ማለት ነው።
በሩክነል የማኒ -የከዕባ አራተኛው ማዕዘን ነው - በኩል ሲያልፍ ከቻለ ያለምንም ተክቢራና መሳም በቀኝ እጁ ይዳብሰዋል፤ ካልቻለ ግን እጁን ወደርሱ ሳይጠቁምና ተክቢራ ሳይል ዝም ብሎ ያልፋል። በሩክነል የማኒና በሐጀረል አስወድ መካከል ሲደርስ የሚከተለውን ይላል:
﴿...رَبَّنَآ ءَاتِنَا فِي ٱلدُّنۡيَا حَسَنَةٗ وَفِي ٱلۡأٓخِرَةِ حَسَنَةٗ وَقِنَا عَذَابَ ٱلنَّارِ﴾
"ረብበና አቲና ፊ ዱንያ ሐሰነተን ወፊል አኺረቲ ሐሰነተን ወቂና ዓዛበን-ናር" ትርጉሙም: "ጌታችን ሆይ! በዱንያ መልካሙን ስጠን፤ በመጨረሻው አለምም መልካሙን ስጠን። ከእሳት ቅጣትም ጠብቀን።" ማለት ነው። [አል-በቀራህ፡ 201]
ጦዋፉን ሲያጠናቅቅም ከቻለ ከመቃም ኢብራሂም ዐለይሂ ሰላም ኋላ ሁለት ረከዓ ይሰግዳል። ያለበለዚያ መስጂደል ሐራም ውስጥ በሚገኝ ማንኛውም ስፍራ ይሰግዳል። በመጀመሪያው ረከዓ ከፋቲሓ በኋላ ሱረቱል (ካፊሩንን) መቅራቱ፣ በሁለተኛው ረከዓ ደግሞ ከፋቲሓ በኋላ ሱረቱል (ኢኽላስን) መቅራቱ ሱና ነው። ቀጥሎ ወደ መሮጫ ስፍራ ያቀናል። በሶፋና መርዋ መካከልም ሰባት ዙር ይሮጣል። ከሶፋ ተነስቶ መርዋ መሄዱ አንድ ዙር ሲሆን መመለሱ ሁለተኛ ዙር ነው።
መሮጡን የሚጀምረው ከሶፋ ነው። አናቱ ላይ ይወጣል ወይም እርሱ ዘንድ ይቆማል። ከቻለ ሰፋ ላይ መውጣቱ በላጭ ነው። በዚህ ወቅትም የሚከተለውን የአላህ ቃል ይቀራል:
﴿إِنَّ ٱلصَّفَا وَٱلۡمَرۡوَةَ مِن شَعَآئِرِ ٱللَّهِ...﴾
(ኢንነስ-ሰፋ ወልመርወተ ሚን ሸዓኢሪልሏህ… ) ትርጉሙም (ሰፋና መርዋ ከአላህ (ትእዛዝ መፈፀሚያ) ምልክቶች ናቸው።) ማለት ነው። [አልበቀራህ፡ 158]
ወደ ቂብላ በመዞር አላህን ማመስገንና ተክቢራ ማለቱ ይወደዳል። እንዲህም ይላል:
«لَا إِلٰهَ إِلَّا اللَّهُ، وَاللَّهُ أَكْبَرُ، لَا إِلٰهَ إِلَّا اللَّهُ وَحْدَهُ لَا شَرِيكَ لَهُ، لَهُ الْمُلْكُ وَلَهُ الْحَمْدُ، يُحْيِي وَيُمِيتُ، وَهُوَ عَلَى كُلِّ شَيْءٍ قَدِيرٌ، لَا إِلٰهَ إِلَّا اللَّهُ وَحْدَهُ، أَنْجَزَ وَعْدَهُ، وَنَصَرَ عَبْدَهُ، وَهَزَمَ الْأَحْزَابَ وَحْدَهُ».
" ላ ኢላሃ ኢለሏህ፣ ወሏሁ አክበር፤ ላ ኢላሃ ኢለሏሁ ወሕደሁ ላ ሸሪከ ለህ፤ ለሁል ሙልኩ ወለሁል ሐምዱ ዩሕዪ ወዩሚት፣ ወሁወ ዐላ ኩሊ ሸይኢን ቀዲር። ላ ኢላሃ ኢለሏሁ ወሕደህ፤ አንጀዘ ወዕደህ፤ ወነሰረ ዐብደህ፤ ወሀዘመል-አሕዛበ ወሕደህ።"61 ትርጉሙም: (ከአላህ በስተቀር በእውነት የሚመለክ አምላክ የለም። አላህ ታላቅ ነው፤ ከአላህ በስተቀር በእውነት የሚመለክ አምላክ የለም፤ እርሱ አንድ ነው፤ ለእርሱ አጋር የለውም። ንግስናና ምስጋና ለእርሱ ብቻ ነው፤ ህያው ያደርጋልም ይገላልም፤ እርሱም በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ ነው። ከአላህ በስተቀር በእውነት የሚመለክ አምላክ የለም፤ እርሱ አንድ ነው። የገባውን ቃል ፈጽሟል፤ ባሪያውንም ረድቷል፤ የተሰባሰቡትንም (የጠላት) ኃይሎች ብቻውን ድል ነስቷል።) ማለት ነው። ቀጥሎ እጆቹን ከፍ በማድረግ የገራለትን ያህል ዱዓ ያደርጋል። ይህንን ዚክርና ዱዓም ሶስት ጊዜ ይደጋግማቸዋል። ከዚያም ወርዶ ወደ መርዋ ይሄዳል። የመጀመሪያው ምልክት ዘንድ እስኪደርስም በእርምጃ ይሄዳል። ወንድ ከሆነ ከመጀመሪያው ምልክት እስከ ሁለተኛው ምልክት ድረስ በፈጣን እርምጃ ይሄዳል። ሴት ከሆነች መላ ነገሯ ዐውራ (መሰተር ያለበት) ስለሆነ ለርሷ በሁለቱ ምልክቶች መካከል መፍጠን አልተደነገገላትም። ይልቁንም ለርሷ የተደነገገው በሁሉም መሮጫ ስፍራ መራመድ ነው። ከዚያም እየተራመደ ወደ መርዋ ኮረብታ ይወጣል ወይም ስፍራው ላይ ይቆማል፤ ከተቻለ (ኮረብታው ላይ) መውጣቱ በላጭ ነው፤ ሰፋ ላይ ያለውን እና የፈፀመውን ሁሉ መርዋ ላይም ይደግማል። ይህን የቁርአን አንቀፅ ግን አይደግምም።
﴿إِنَّ ٱلصَّفَا وَٱلۡمَرۡوَةَ مِن شَعَآئِرِ ٱللَّهِ...﴾
(ኢንነስ-ሰፋ ወልመርወተ ሚን ሸዓኢሪልሏህ… ) ትርጉሙም (ሰፋና መርዋ ከአላህ (ትእዛዝ መፈፀሚያ) ምልክቶች ናቸው።) ማለት ነው። ይህን አንቀፅ መቅራት የተደነገገው በመጀመሪያው ዙር ብቻ ወደ ሰፋ በሚወጣ ወቅት ነው። ቀጥሎ በመውረድ ሶፋ እስኪደርስ ድረስ በመራመጃ ቦታዎች ይራመዳል በመፍጠኛ ቦታዎች ደግሞ ይፈጥናል። ይህንንም ሰባት ጊዜ ይፈፅማል። ከሶፋ ተነስቶ መርዋ መሄዱ አንድ ዙር ሲሆን መመለሱ ሁለተኛ ዙር ነው። በሰዕይ (በሶፋና መርዋ መካከል በሚያደርገው ስርዓት) ወቅት የቻለውን ያህል ዚክርና ዱዓ ማብዛቱ ይወደዳል። እንዲሁም ምንም እንኳን ያለ ዉዱእ ማድረጉ የሚበቃለት ቢሆንም ከትላልቅ (የገላ ትጥበትን ግዴታ ከሚያደርጉ) እና ከትናንሽ (ዉዱእ ማድረግን ግዴታ ከሚያደርጉ) ሐደሦች ሁሉ ንፁህ መሆኑ ይመረጣል። ልክ እንደዚሁ ሴት ልጅ ከጦዋፍ በኋላ የወር አበባ ወይም የወሊድ ደም ቢፈሳት በሶፋና መርዋ መካከል ትመላለሳለች። ይህም ይበቃላታል (ትክክል ይሆንላታል)። (ጦሃራ) ዉዱእ ያለው መሆን በሶፋና መርዋ መካከል የመመላለስ መስፈርት ሳይሆን ከሚወደዱ ተግባራት መካከል ነውና።
በሶፋና መርዋ መካከል መመላለስን ያሟላ ጊዜ ጭንቅላቱን ይላጫል ወይም ያሳጥራል። ለወንድ ልጅ በላጩ መላጨቱ ነው።
ልክ በዚህ መልኩ የተሟላ የዑምራ አምልኮ ይፈፀማል።
ሐጅ:
ሀ - የሐጅ ማዕዘናት
1 - ኢሕራም
2- በዐረፋ ላይ መቆም፤
3- ጠዋፍ አል-ኢፋዷ፤
4 - ሰዕይ (በሰፋና መርዋ መካከል መመላለስ) :
ለ - የሐጅ ግዴታዎች:
1 - (ከሚቃት) ከኢሕራም ማድረጊያ ስፍራ ኢሕራም ማድረግ፤
2 - የዙልሒጃ ዘጠነኛ ቀን ዓረፋ ላይ ቀትር ላይ የቆመ ሰው ፀሐይ እስክትገባ ድረስ መቆሙ፤
3 - የዙልሒጃን አስረኛው ምሽት እስከ ምሽቱ አጋማሽ ድረስ በሙዝደሊፋ ማደር፤
4 - የአያመ ተሽሪቅ ምሽቶችን በሚና ማደር፤
5 - ጠጠሮች መወርወር፤
6 - መላጨት ወይም ማሳጠር፤
7 - ጦዋፈል ወዳዕ (የመሰናበቻ ጦዋፍ)፤
ሐ - የሐጅ አፈጻጸም
አንድ ሙስሊም ወቅቱ ተጣቦበት የኢፍራድን አፈፃፀም ሐጅ ሊያደርግ ኢሕራም ማድረጊያ ስፍራ ጋር ሲደርስ ተልቢያ ይላል። መካ የገባ ጊዜም ጦዋፍና ሰዕይ (በሶፋና መርዋ መካከል ይመላለሳል)። በዘጠነኛው ቀን የዓረፋ ቀን ወደ ዓረፋ እስኪያቀና ድረስ በኢሕራሙ ላይ ይቀራል። ወደ ዓረፋም በመሄድ ፀሐይ እስክትገባ ድረስ እዛው ያሳልፋል።
ቀጥሎ ተልቢያ እያደረገ ወደ ሙዝደሊፋ ይጓዛል። ፈጅርን እስኪሰግድ ድረስም እዛው ያሳልፋል። ፈጅርን እንደሰገደም ንጋቱ በጣም ወገግ እስኪል ድረስ አላህን በማውሳት፣ ተልቢያ በማለትና ዱዓ በማድረግ ያሳልፋል።
ንጋቱ ወገግ ያለ ጊዜ ፀሐይ ከመውጣቷ በፊት ወደ ሚና ይጓዛል። በሰባት ጠጠሮች ጀምረተል ዓቀባ ዘንድ ይወረውራል። ከዚያም ፀጉሩን ይላጫል ወይም ያሳጥራል። በላጩም መላጨቱ ነው።
ከዚያም ጦዋፈል ኢፋዷን ያደርጋል። በሶፋና መርዋ ግን መጀመሪያ ስለፈፀመ ድጋሚ አይመላለስም። በዚህም ሐጁ ይጠናቀቃል። ሙሉ ለሙሉም ከሐጁ ይፈታል።
ወደ ሃገሩ ለመመለስ የቸኮለ ከሆነ የአስራ አንደኛና አስራ ሁለተኛ ቀን ጠጠር መወርወር ይቀርበታል። በሶስቱ የጠጠር መወርወሪያ ስፍራዎችም እያንዳንዱ ውስጥ ሰባት ሰባት ጠጠር ይወረውራል። እያንዳንዱን ጠጠር ሲወረውርም ተክቢራ ይላል። ከኸይፍ መስጂድ ቀጥላ ባለችው ከትንሿ መወርወሪያ ይጀምራል ከዚያም መካከለኛው ውስጥ ይወረውራል ከዚያም የመጨረሻውን ጀምረተል ዓቀባ ውስጥ ይወረውራል። ወደ እያንዳንዱ መወርወሪያ የሚወረውረው የጠጠር ብዛትም ሰባት ሰባት ጠጠር ነው። ከአስራ ሁለተኛ ቀን በኋላ መቆየት ከፈለገ በአስራ ሶስተኛም ቀን በአስራ አንደኛና አስራ ሁለተኛ ቀን በወረወረው መልኩ ይወረውራል።
የመወርወሪያ ወቅትም: በሶስቱም ቀናት ከዝሁር ወቅት በኋላ ነው።
በአስራ ሁለተኛው ቀን ፀሐይ ከመግባቷ በፊት ለቆ ከወጣ ችግር የለውም። በላጩ ግን የአስራ ሶስተኛ ቀንን የጠጠር ውርወራ ከዝሁር በኋላ እስኪወረውር መቆየቱ ነው። አላህ እንዲህ ብሏልና:
﴿...فَمَن تَعَجَّلَ فِي يَوۡمَيۡنِ فَلَآ إِثۡمَ عَلَيۡهِ وَمَن تَأَخَّرَ فَلَآ إِثۡمَ عَلَيۡهِۖ لِمَنِ ٱتَّقَىٰ...﴾
{… በሁለት ቀኖችም ውስጥ (በመኼድ) የተቻኮለ ሰው በርሱ ላይ ኃጢኣት የለበትም፡፡ የቆየም ሰው በርሱ ላይ ኃጢኣት የለበትም፡፡ (ይህም) አላህን ለፈራ ሰው ነው፡፡…}
[አልበቀራህ፡ 203]
ወደ ሃገሩ መጓዝ የፈለገ ጊዜ የመሰናበቻን ጦዋፍ (ጦዋፈል ወዳዕ) ሰባት ዙር ይዙር እንጅ ሰዕይ (በሶፋና መርዋ መመላለስ) የለበትም።
ከርሱ ጋር አብሮ ሀድይ (እርድ) ይዞ ላልመጣ ሰው በላጩ የሐጅ አፈፃፀም የተመቱዕ አፈፃፀም ኢሕራም ማድረጉ ነው። ከዚያም ስምንተኛው ቀን ላይ ሐጅን ኢሕራም በማድረግ ቀደም ብሎ የተጠቀሰውን የሐጅ ድርጊቶች ይፈፅማል። ሐጅና ዑምራን አንድ ላይ ኢሕራም ካደረገም ችግር የለውም። ይህም ቂራን በመባል ይጠራል። ይህም የሐጅና ዑምራን ተግባር በጋራ ሊፈፅም ኢሕራም ማድረጉ ነው። አንድ ጦዋፍና ሰዕይ ለሁለቱም ያደርጋል።
ምዕራፍ ሶስት:
መስተጋብሮችን የሚመለከቱ ጉዳዮች:
ዑለማዎች አላህ ይዘንላቸውና በነፍስ ወከፍ የግድ መማር የሚገባን እውቀት ገለፁ። እያንዳንዱ ሙስሊም በነፍስ ወከፍ መማር ባለበት መጠን ጉዳይም ተናገሩ። ከጠቀሷቸው መካከልም አንዱ: ንግድ ለሚነግድ ሰው የንግድን ህግጋት መማሩ አንዱ ነው። ይህም ባለማወቅ የሐራም ግብይት ወይም ወለድ ውስጥ እንዳይወድቅ ነው። ከተወሰኑ ሶሓቦችም -አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና- ይህንን የሚያጠናክሩ ዘገባዎች መጥተዋል።
ከዑመር ቢን አልኸጧብ -አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላቸውና - እንደተላለፈው እንዲህ አሉ፦ «ሃይማኖቱን የተገነዘበ ሰው ካልሆነ በቀር በንግድ ሱቆቻችን ውስጥ እንዳይነግድ!»62
ዐሊይ ቢን አቢ'ጧሊብ -አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላችውና- እንዲህ ብለዋል: «ዲኑን ሳይገነዘብ በፊት የነገደ ሰው ወለድ ውስጥ ይወድቃል፣ ድጋሚም ይወድቃል፣ አሁንም በድጋሚ ይወድቃል።»63
ኢብኑ ዓቢዲን ከዓላሚይ እንዳስተላለፉት እንዲህ ብለዋል: «ሁሉም አይምሯቸው ጤነኛ የሆኑና የደረሱ ወንዶችና ሴቶች ስለ ሃይማኖታቸውና ስለቀናው ጎዳና ከተማሩ በኋላ ስለ ዉዱእ፣ ትጥበት፣ ሶላት፣ ጾም፣ የዘካ መጠን የደረሰ ገንዘብ ያለው ስለ ዘካ፣ ሐጅ ግዴታ የሆነበት ሰው ስለ ሐጅ፣ ነጋዴ ለሆነ ሰው ስለ ንግድ መማር ግዴታ ነው። ይህም በሁሉም መስተጋብሮች ላይ ከሚያምታቱና ከሚጠሉ መስተጋብሮች ለመራቅ ስለሚያግዛቸው ነው። ልክ እንደዚሁ ባለሙያዎችና በተወሰነ የስራ ዘርፍ ላይ የተሰማሩም በዘርፉ የሚተገበሩ መመርያዎችን ለማወቅ እንዲረዳቸው ስለርሱና ስለብይኑ ማወቅ ግዴታቸው ነው።»64
ኢማሙ ነወዊይ አላህ ይዘንላቸውና እንዲህ ብለዋል: «በመሰረቱ ግዴታ ያልሆኑ እንደ ንግድ፣ ጋብቻና የመሳሰሉት ነገሮችም መስፈርቶቹን ሳያውቁ በፊት ወደነርሱ መግባት ክልክል ነው።»65
ከዚህ በታች የሚጠቀሱት ገንዘባዊ ውሎችን የተመለከቱ በእስላማዊ ሸሪዓ ውስጥ የመጡ አንዳንድ መርሆዎች ናቸው:
1 - ሙሉ ለሙሉ ወይም አመዛኝ ጥቅም ያላቸው ውሎች ባጠቃላይ ይፈቀዳሉ። ለምሳሌ ያህል: ፍቁድ ነገሮችን መሸጥ፣ መግዛት፣ ማከራየትና (ሹፍዓ) ጠቅልሎ መግዛት ይጠቀሳል።66
2 - የሰዎችን ሐቅ ለመጠበቅ ዋስትና የሚሆንና የሚጠብቅ ውል ባጠቃላይ የተደነገገ ነው። ለምሳሌ ያህል: መያዣና ማስመስከር ይጠቀሳል።
3 - የሁለቱ ተዋዋዮችን ጥቅም የሚያስጠብቅ ውል ባጠቃላይ የተደነገገ ነው። ለምሳሌ ያህል: በስምምነት የተሸጠ እቃ መመለስ፣ የንግድ ውል ምርጫ፣ ንግድ ላይ መስፈርቶችን ማስቀመጥ ይጠቀሳል።
4 - ሰዎችን መበደልንና ገንዘባቸውን ያላግባብ መውሰድን ያካተተ ውል ባጠቃላይ ተከልክሏል። ለምሳሌ ያህል: ወለድ፣ መቀማት፣ ሸቀጥን ለገበያ ሳያቀርቡ ማከማቸት ይጠቀሳሉ።
5 - በመልካም ነገር ላይ መተጋገዝ ያለበት ውል ባጠቃላይ የተደነገገ ነው። ለምሳሌ ያህል: ብድር፣ ማዋስ፣ አደራ ማስቀመጥ ይጠቀሳሉ።
6 - ሳይሰሩ፣ ጥቅም ሳይሰጡና ሳይደክሙ ገንዘብን መብላት ያለበት ውል ባጠቃላይ ተከልክሏል። ለምሳሌ ያህል: ቁማርና ወለድ ይጠቀሳሉ።
7 - ግልፅነት የጎደለውና ማታለል የሚበዛበት ውል ባጠቃላይ ተከልክሏል። ለምሳሌ ያህል: በእጁ ያላስገባውን ሸቀጥ መሸጥና ምንነቱ በግልፅ የማይታወቅን መሸጥ ይጠቀሳሉ።
8 - ወደ ሐራም መዳረሻ ዘዴ የሆነ ውል ባጠቃላይ ተከልክሏል። የ(ዒና) ንግድ ለአብነት ይጠቀሳል።67
9 - አላህን ከመገዛት የሚያዘናጋ ውል ባጠቃላይ ተከልክሏል። ከሁለተኛው የጁመዓ አዛን በኋላ መሸጥ ለአብነት ይጠቀሳል።
10 - ጉዳት ያለው ወይም በሙስሊሞች መካከል ጠላትነትን የሚፈጥር ውል ባጠቃላይ ተከልክሏል። ለምሳሌ ያህል: ክልክል ነገሮችን መሸጥ፣ በወንድሙ ንግድ ላይ ጣልቃ ገብቶ መሸጥ ይጠቀሳሉ።
አንድ ሙስሊም የአንድ ጉዳይ ብይን ግራ ሲያጋባው ስለጉዳዩ ዑለማዎችን መጠየቅ አለበት። በጉዳዩ ላይ ያለውን ሸሪዓዊ ብይን ሳያውቅ ወደ ጉዳዩ አይግባ። አላህ እንዲህ ብሏል:
﴿...فَاسْأَلُوا أَهْلَ الذِّكْرِ إِنْ كُنْتُمْ لَا تَعْلَمُونَ﴾
{…የማታውቁ እንደ ኾናችሁ የእውቀት ባለቤቶችን ጠይቁ።} [አንነሕል: 43]
በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ለማካተት የተሞከረው ይሀው ነው። የሚጠቅመንን ዕውቀትና ለመልካም ሥራ መገጠምን እንዲለግሰን የምንማፀነው አላህን ብቻ ነው። እነሆ እርሱ ቸርና ለጋስ ነውና። የአላህ ሰላትና ሰላም በነቢያችን ሙሐመድ በቤተሰባቸው እና በባልደረቦቹም ላይ ሁሉ ይስፈን።
***
ማውጫ
መግቢያ 2
ምዕራፍ አንድ 3
ዐቂዳን (እምነትን) የሚመለከቱ ጉዳዮች 3
የመጀመሪያው ክፍል: የእስልምና ትርጉምና ማዕዘናቱ፦ 3
የተውሒድ አስፈላጊነት: 4
ከአላህ በስተቀር በእውነት የሚመለክ እንደሌለ (ላኢላሃ ኢለሏህ በማለት) የመመስከር ትርጉሙ: 5
የላኢላሃ ኢለሏህ መስፈርቶች ደግሞ የሚከተሉት ናቸው: 6
ሙሐመድ የአላህ መልዕክተኛ መሆናቸውን የመመስከር ትርጓሜ: 8
ክፍል ሁለት: የኢማን ትርጓሜና ማዕዘናቱ: 10
1) በላቀው አሏህ ማመን ሶስት ነገሮችን ያካትታል: 11
1 - በጌትነቱ ማመን: 11
2 - በተመላኪነቱ ማመን: 13
3 - በስሞቹና በባህሪያቱ ማመን: 16
2 - በመላእክት ማመን 24
3 - በመጽሐፍት ማመን: 25
4) በመልዕክተኞች (የአላህ ሰላም ይስፈንባቸውና) ማመን: 27
5 - በመጨረሻው ቀን ማመን 28
ሀ) ከሞት በመቀስቀስ ማመን: 28
ለ) በሒሳብና ምንዳ ማመን: 29
መ) በጀነትና በእሳት ማመን: 29
6 - በቀደር ክፉውም ሆነ ደጉን ማመን፡ 30
ክፍል ሶስት: ኢሕሳን (በጎነት) 32
ክፍል አራት: በአህሉ ሱና ወልጀመዓ መሰረቶች ዙርያ አጠር ያለ ገለፃ: 32
ምዕራፍ ሁለት: ከአምልኮ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች 34
ክፍል አንድ: ጠሃራ 34
የመጀመሪያ: የውሃ ክፍሎች: 34
ሁለተኛ: ነጃሳ: 35
ሶስተኛ: ዉዱእ ያጠፋ ሰው መስራት የሚከለከላቸው ነገሮች: 38
አራተኛ: የመፀዳዳት ሥነ-ስርአት (አዳብ): 40
አምስተኛ: የኢስቲንጃእ እና የኢስቲጅማር ህግጋት: 42
ስድስተኛ: የዉዱእ ህግጋት: 43
ሰባተኛ: በኹፍ እና ካልሲዎች ላይ የማበስ ህግጋት: 46
ስምንተኛ: የተየሙም ህግጋት: 48
ዘጠነኛ: የወር አበባና የወሊድ ደም ብይን: 51
ሁለተኛው ክፍል: ሶላት 53
የመጀመሪያው: የአዛንና ኢቃማ ህግጋት: 53
ሁለተኛ: የሶላት ደረጃና ትሩፋት: 57
ሶስተኛ: የሶላት ቅድመ መስፈርቶች 59
አራተኛ: የሶላት ማእዘናት: 62
አምስተኛ: የሶላት ግዴታዎች: 67
ስድስተኛ: የሶላት ሱናዎች: 69
ሰባተኛ: የሶላት አሰጋገድ: 72
ስምንተኛ: ሶላት ውስጥ የሚጠሉ ነገሮች: 79
ዘጠነኛ: ሶላትን የሚያበላሹ ነገሮች: 80
አስረኛ: የመርሳት ሱጁድ: 81
አስራ አንድ: ሶላት መስገድ የሚከለከልባቸው ወቅቶች: 83
አስራ ሁለተኛ: የጀመዓ (የህብረት) ሶላት: 84
አስራ ሶስተኛ: የስጋት ሶላት: 87
የፍርሃት ሶላት አሰጋገድ፤ 88
አስራ አራተኛ: የጁመዓ ሶላት: 89
አምስተኛው: በጁመዓ ቀን የሚወደዱ ነገሮች: 92
ጁሙዓ ላይ ደረሰ የሚባለው መቼ ነው? 93
አስራ አምስተኛ: እክል ያለባቸው ሰዎች የሚሰግዱት ሶላት: 93
አስራ ስድስተኛ: የሁለቱ ዒዶች ሶላት: 98
አስራ ሰባተኛ: የግርዶሽ ሶላት: 100
አስራ ስምንተኛ: ዝናብን የመፈለግ ሶላት:- 103
አስራ ዘጠነኛ: የጀናኢዝ ህግጋት (ከአስክሬን ጋር የተያያዙ ህግጋት): 104
ሶስተኛው ክፍል: ዘካ: 109
1 - የዘካ ትርጓሜና ዘካ ያላት ደረጃ: 109
2 - ዘካ ግዴታ የሚሆንበት መስፈርቶች: 110
3 - ዘካ ግዴታ የሚሆንባቸው ገንዘቦች: 111
ክፍል አራት: ፆም 126
የረመዷን ወር ፆም ግዴታ የሚሆንበት መስፈርቶች: 126
ክፍል አምስት: ሐጅና ዑምራ 136
ሐጅና ዑምራ ግዴታ የሚሆኑበት መስፈርቶች: 137
የኢሕራም (ሚቃቶች) የኢሕራም ማድረጊያ ስፍራዎችና ወቅቶች: 139
ኢሕራም: 141
ዑምራ: 146
ሐጅ: 151
ምዕራፍ ሶስት: 154
መስተጋብሮችን የሚመለከቱ ጉዳዮች: 154
***
am227v3.0 - 28/02/2026
ኢማሙ አሕመድ በሙስነዳቸው በቁጥር (6072)፣ ቲርሚዚይ ደግሞ በቁጥር (1535) ላይ ዘግበውታል። ሐዲሡንም ሐሰን ነው ብለውታል።
ቡኻሪይ በአደቡል ሙፍረድ በቁጥር (716)፣ አሕመድ በሙስነድ ውስጥ በቁጥር (19606)፣ ዲያእ አልመቅደሲይ በአል‐አሓዲሥ አልሙኽታራ ውስጥ በቁጥር (1/150) ዘግበውታል። አልባኒይ በሶሒሕ አልጃሚዑ አስሶጚር በቁጥር (3731) ሶሒሕ ብለውታል።
ሙስሊም በቁጥር (121) ላይ፤ አሕመድ በሙስነዳቸው በቁጥር (10434) ላይ ዘግበውታል።
"አልመዝይ": በመተሻሸት ወቅት ወይም ስለግንኙነት ሲያስቡ ወይም ግንኙነት ሲፈልጉ ወይም ሲመለከቱ ወይም ከዛ ውጪ ባሉ ሁኔታዎች የሚወጣ የለተየ ቀለም የሌለው ቀጭን ፈሳሽ ነው። በመፍሰስ መልክ ስለሚወጣ ምናልባት መውጣቱ ላይታወቅ ይችላል። "ወድይ" ማለት: ሽንትን ተከትሎ ወይም ከባድ ነገር በሚሸከሙበት ወቅት የሚወጣ ወፍራም ነጭ ፈሳሽ ነው።
ሙስሊም በቁጥር (224) ዘግበውታል።
ኢማሙ ማሊክ በሙወጦእ በቁጥር (680 ና 219)፣ ዳሪሚይ በቁጥር (312)፣ ዐብዱረዛቅ በሙሶነፋቸው በቁጥር (1328) ዘግበውት አልባኒይ በኢርዋኡል ገሊል ውስጥ በቁጥር (122) ሶሒሕ ብለውታል።
ነሳኢይ በቁጥር (12808)፣ አሕመድ በቁጥር (15423) ዘግበውት አልባኒይ በኢርዋኡል ገሊል ውስጥ በቁጥር (121) ሶሒሕ ብለውታል።
ኢብኑ ማጀህ በቁጥር (594)፣ ኢብኑ ሒባን በቁጥር (799) ዘግበውታል። አልባኒይ በዶዒፍ ሱነን አትቲርሚዚይ በቁጥር (146) ዶዒፍ ነው ብለውታል።
ቡኻሪይ በቁጥር (142)፣ ሙስሊም በቁጥር (122) ዘግበውታል።
ቡኻሪ በቁጥር (7288) እና ሙስሊም በቁጥር (6066) ዘግበውታል።
ፈርድ ኪፋያ (ማህበራዊ ግዴታ)፡ ማለት የተወሰኑ ሰዎች ከተወጡት ከሌሎች ላይ ግዴታው ይወድቃል (ማንም አይጠየቅም)፤ ማንም ካላደረገው ግን ሁሉም ወንጀለኛ የሚሆኑበት የጋራ ግዴታ ነው።
ታላቁ ሸይኽ ዐብዱል ዓዚዝ ቢን ባዝ ረሒመሁሏህ በመጅሙዕ ፈታዋቸው ውስጥ (29/141) እንዲህ አሉ: («አልለዚ ወዓድተሁ» ከሚለው በኋላ «ኢንነከ ላቱኽሊፉል ሚዓድ» የሚለውን በይሀቂይ በጥሩ ሰነድ ከጃቢር ጨምረው ዘግበዋል።)
ቲርሚዚይ በቁጥር (2635) ዘግበውታል።
ሙስሊም በቁጥር (82) ዘግበውታል።
ቲርሚዚ በቁጥር (265) የዘገቡት ሲሆን የሐዲሡንም ደረጃ ሐሰኑን ሶሒሑን ገሪብ ብለውታል። አልባኒ በ "ሶሒሕ አትተርጊብ ወትተርሂብ" ላይ ሶሒሕ ብለውታል።
ቡኻሪይ በቁጥር (1117) ዘግበውታል።
ቡኻሪ በቁጥር (6251) እና ሙስሊም በቁጥር (884) ዘግበውታል።
ቡኻሪይ በቁጥር (756) እና ሙስሊም በቁጥር (872) ዘግበውታል።
ቡኻሪይ በቁጥር (793) እና ሙስሊም በቁጥር (398) ዘግበውታል።
ቡኻሪይ በቁጥር (812) እና ሙስሊም በቁጥር (490) ዘግበውታል።
ሙስሊም በቁጥር (498) ዘግበውታል።
ቡኻሪይ በቁጥር (724) እና ሙስሊም በቁጥር (398) ዘግበውታል።
ቡኻሪ በቁጥር (797) እና ሙስሊም በቁጥር (402) ዘግበውታል።
ቲርሚዚይ በቁጥር (839) ዘግበውታል።
ቡኻሪይ በቁጥር (6008) ዘግበውታል።
ቡኻሪይ በቁጥር (1110) ዘግበውታል።
ቡኻሪ በቁጥር (835) ዘግበውታል።
ቡኻሪይ በቁጥር (743) እና ሙስሊም በቁጥር (399) ዘግበውታል።
ቲርሚዚይ በቁጥር (266) ዘግበውታል።
ሙስሊም በቁጥር (588) ዘግበውታል።
አቡዳውድ በቁጥር (5168) ዘግበውታል።
ቲርሚዚይ በቁጥር (284) ዘግበውታል።
ሙስሊም በቁጥር (1484) ዘግበውታል።
ቡኻሪይ በቁጥር (609) እና ሙስሊም በቁጥር (602) ዘግበውታል።
ቡኻሪይ በቁጥር (4130) እና ሙስሊም በቁጥር (842) ዘግበውታል።
ሙስሊም በቁጥር (865) ዘግበውታል።
ቡኻሪይ በቁጥር (934) እና ሙስሊም በቁጥር (851) ዘግበውታል።
ቡኻሪይ በቁጥር (1081) እና ሙስሊም በቁጥር (693) ዘግበውታል።
ቡኻሪ በቁጥር (1012) እና ሙስሊም በቁጥር (894) ዘግበውታል።
አቡዳውድ በቁጥር (3201) እና ቲርሚዚይ በቁጥር (1024) ዘግበውታል። ሐዲሡንም ሐሰኑን ሶሒሕ ብለውታል።
ሙስሊም በቁጥር (962) ዘግበውታል።
ቡኻሪይ በቁጥር (8) እና ሙስሊም በቁጥር (111) ዘግበውታል።
ኢብኑ ማጀህ በቁጥር (1792) እና ቲርሚዚይ በቁጥር (63)ና (631) ዘግበውታል።
ቡኻሪይ በቁጥር (1402) እና ሙስሊም በቁጥር (2287) ዘግበውታል።
ቡኻሪይ በቁጥር (1432) እና ሙስሊም በቁጥር (984) ዘግበውታል።
አቡዳውድ በቁጥር (1609)፣ ኢብኑ ማጀህ በቁጥር (1827) የዘገቡት ሲሆን አልባኒ በ "ሶሒሕ አቡዳውድ" ውስጥ በቁጥር (1609) ላይ ሶሒሕ ብለውታል።
ቡኻሪይ በቁጥር (1) እና ሙስሊም በቁጥር (1907) ዘግበውታል።
ቡኻሪይ በቁጥር (1810) እና ሙስሊም በቁጥር (1086) ዘግበውታል።
ቡኻሪይ በቁጥር (1909) ላይ ዘግበውታል።
አሕመድ በቁጥር (26457)፣ አቡዳውድ በቁጥር (2454) እና ነሳኢይ በቁጥር (2331) ዘግበውታል። ይህ ከላይ የሰፈረውም የነሳኢይ ዘገባ ነው።
ቡኻሪይ በቁጥር (6669) እና ሙስሊም በቁጥር (2709) ዘግበውታል።
አቡ ዳውድ በቁጥር (2380) ቲርሚዚይም በቁጥር (719) ኢብኑ ማጀህም በቁጥር (676) ዘግበውታል።
ቡኻሪይ በቁጥር (1849) እና ሙስሊም በቁጥር (1846) ዘግበውታል።
ሙስሊም በቁጥር (1134) ዘግበውታል።
አሕመድ በቁጥር (25198)፣ ነሳኢይ በቁጥር (2627)፣ ኢብኑ ማጀህ በቁጥር (2901) ዘግበውታል።
ቡኻሪይ በቁጥር (1862) እና ሙስሊም በቁጥር (1341) ዘግበውታል።
ቡኻሪይ በቁጥር (1531) ላይ ዘግበውታል።
ሙስሊም በቁጥር (1211) ላይ ዘግበውታል።
ቡኻሪይ በቁጥር (1549) ዘግበውታል።
ሙስሊም በቁጥር (1218) ላይ ዘግበውታል።
ቲርሚዚ በቁጥር (487) የዘገቡት ሲሆን የሐዲሡንም ደረጃ ሐሰኑን ገሪብ ብለውታል። አልባኒ ሐሰን ብለውታል።
ሙግኒል ሙሕታጅን (2/22) ይመልከቱ።
ሓሺየቱ ኢብኑ ዓቢዲን (1/42)
መጅሙዕ (1/50) ይመልከቱ።
ሹፍዓ ማለት: ሽርካው ድርሻውን መሸጥ በፈለገ ጊዜ የሽርካውን ድርሻ መግዛት ቅድሚያ የሚሰጠው አብሮት ያለው ሸሪካ ነው። በዚህም በገንዘብ ልውጫ የሸሪካውን ድርሻ መጠቅለል (ሹፍዓ) ይባላል።
የዒና ንግድ ማለት: አንድ ሰው ለሌላ ሰው ከጊዜ በኋላ በሚከፈል ዋጋ አንድን ሸቀጥ ይሸጥለታል፣ እቃውንም ያስረክበዋል። ከዚያም ከራሱ መጀመሪያ የሸጠበትን ሂሳብ ሳይቀበል መጀመሪያ በዱቤ ከሸጠለት ዋጋ ዝቅ አድርጎ በካሽ መግዛቱ ነው።
ቡኻሪይ በሐዲሥ ቁጥር (8) ዘግበውታል።