PHPWord

 

 

العَقِيدَةُ الصَّحِيْحَةُ وَمَا يُضَادُّهَا

 

 

ትክክለኛ ዐቂዳ እና ተቃራኒው

 

 

 

 

 

لِسَمَاحَةِ الشَّيْخِ العَلَّامَةِ

عَبْدِ العَزِيزِ بْنِ عَبْدِ اللهِ بْنِ بَازٍ

رَحِمَهُ اللهُ

 

ዝግጅት፦ የተከበሩ ሸይኽ

ዐብዱልዐዚዝ ቢን ዐብደላህ ቢን ባዝ

 

 

 


بِسْمِ اللهِ الرَّحمَنِ الرَّحِيمِ

የመጀመሪያው መልዕክት:

ትክክለኛ ዐቂዳ እና ተቃራኒው

ዝግጅት፦ የተከበሩ ሸይኽ

ዐብዱልዐዚዝ ቢን ዐብደላህ ቢን ባዝ

ምስጋና ሁሉ ለብቸኛው አላህ የተገባ ነው። የአላህ ሰላትና ሰላም ከእሳቸው በኋላ ነብይ የሌለ በሆኑት ነብይ፣ በቤተሰቦቻቸውና በባልደረቦቻቸውም ላይ ይስፈን።

በመቀጠል፦ ትክክለኛው ዓቂዳ (እምነት) የእስልምና መሰረት እና የሃይማኖቱም ምሰሶ በመሆኑ፣ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ መነጋገር እንዲሁም እሱን በማብራራትና ግልጽ በማድረግ ላይ መጻፍና ማዘጋጀት አስፈላጊ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።

ከቁርኣንና ሐዲሥ ሸሪዓዊ ማስረጃዎች መረዳት እንደሚቻለው፤ ተግባራትና ንግግሮች ትክክል የሚሆኑትና ተቀባይነት የሚያገኙት ከትክክለኛ ዐቂዳ (እምነት) ሲመነጩ ነው። ዐቂዳው ትክክለኛ ካልሆነ ግን የእርሷ ቅርንጫፍ የሆኑት ተግባራትና ንግግሮች ውድቅ ይሆናሉ። የበላይ የሆነው አላህ እንዲህ ብሏል፦

﴿...وَمَن يَكۡفُرۡ بِٱلۡإِيمَٰنِ فَقَدۡ حَبِطَ عَمَلُهُۥ وَهُوَ فِي ٱلۡأٓخِرَةِ مِنَ ٱلۡخَٰسِرِينَ﴾

{በአላህ ካመነ በኋላ ከእምነቱ ወደ ክህደት የሚመለስ ሁሉ በእርግጥ ስራው ተበላሸ:: በመጨረሻም ቀን ከከሳሪዎች ነው::} [አል ማኢዳህ፥5]

የላቀው አላህ እንዲህም ብሏል፡

﴿وَلَقَدۡ أُوحِيَ إِلَيۡكَ وَإِلَى ٱلَّذِينَ مِن قَبۡلِكَ لَئِنۡ أَشۡرَكۡتَ لَيَحۡبَطَنَّ عَمَلُكَ وَلَتَكُونَنَّ مِنَ ٱلۡخَٰسِرِينَ 65﴾

{(መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ብታጋራ ስራህ በእርግጥ ይታበሳል:: በእርግጥም ከከሓዲያን ትሆናለህ በማለት ወደ አንተና እነዚያ ካንተ በፊት ወደ ነበሩት በእርግጥ ተወርዷል::} [አዝ-ዙመር፡ 65]

በዚህ ዙሪያ የመጡ ቁርአናዊ ማስረጃዎች በርካት ናቸው። ግልፅ የሆነው የአላህ መፅሀፍና የታማኙ መልዕክተኛ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን )ሱና እንዳመላከቱት፤ ትክክለኛው እምነት በስድስት ነገሮች ይጠቃለላል። እነርሱም፦ በአላህ፣ በመላዕክቶቹ፣ በመጽህፍቶቹ፣ በመልዕክተኞቹ፣ በመጨረሻው ቀን፣ እና በጥሩውም ይሁን በመጥፎው የአላህ ቅድመ ውሳኔ (በቀደር) ማመን ናቸው። እነኝህ ስድስቱ ነገሮች አላህ መጽሐፍት ያወረደባቸው መልዕክተኛው ሙሐመድንም (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) የላከበት የትክክለኛው እምነት መሰረቶች ናቸው።

እነዚህን ስድስት መሰረቶች በተመለከተ በቁርኣንና ትክክለኛ በሆነው ሱንና (ሐዲሥ) ላይ በርካታ ማስረጃዎች መጥተዋል። ከነዚህም መካከል ለምሳሌ የሚከተሉት ይገኙበታል፦

አንደኛ: ቁርአናዊ ማስረጃዎች: አላህ እንዲህ ብሏል፦

﴿لَّيۡسَ ٱلۡبِرَّ أَن تُوَلُّواْ وُجُوهَكُمۡ قِبَلَ ٱلۡمَشۡرِقِ وَٱلۡمَغۡرِبِ وَلَٰكِنَّ ٱلۡبِرَّ مَنۡ ءَامَنَ بِٱللَّهِ وَٱلۡيَوۡمِ ٱلۡأٓخِرِ وَٱلۡمَلَٰٓئِكَةِ وَٱلۡكِتَٰبِ وَٱلنَّبِيِّـۧنَ...﴾

{መልካም ስራ ፊቶቻችሁን ወደ ምስራቅና ምዕራብ አቅጣጫ ማዞር አይደለም። ግን መልካም ስራ በአላህ፣ በመጨረሻው ቀን፣ በመላዕክት፣ በመጻሕፍት፣ በነብያት ያመነ፤…} [አል-በቀራህ፥177]

ጥራት የተገባውና የላቀው አላህ እንዲህም ብሏል፦

﴿ءَامَنَ ٱلرَّسُولُ بِمَآ أُنزِلَ إِلَيۡهِ مِن رَّبِّهِۦ وَٱلۡمُؤۡمِنُونَۚ كُلٌّ ءَامَنَ بِٱللَّهِ وَمَلَٰٓئِكَتِهِۦ وَكُتُبِهِۦ وَرُسُلِهِۦ لَا نُفَرِّقُ بَيۡنَ أَحَدٖ مِّن رُّسُلِهِ...﴾

{መልዕክተኛው (ሙሐመድ) ከጌታው ወደ እርሱ በተወረደለት (ቁርኣን) አመነ:: አማኞችም እንደዚሁ አመኑ:: ሁሉም በአላህ፣ በመላዕክቱ፣ በመጽሐፍቱና በመልዕክተኞቹ «ከእነርሱ በአንዱም መካከል አንለይም (አንክድም)» የሚሉ ሲሆኑ አመኑ::} [አል-በቀራህ:285]

የላቀው አላህ እንዲህም ብሏል፦

﴿يَٰٓأَيُّهَا ٱلَّذِينَ ءَامَنُوٓاْ ءَامِنُواْ بِٱللَّهِ وَرَسُولِهِۦ وَٱلۡكِتَٰبِ ٱلَّذِي نَزَّلَ عَلَىٰ رَسُولِهِۦ وَٱلۡكِتَٰبِ ٱلَّذِيٓ أَنزَلَ مِن قَبۡلُۚ وَمَن يَكۡفُرۡ بِٱللَّهِ وَمَلَٰٓئِكَتِهِۦ وَكُتُبِهِۦ وَرُسُلِهِۦ وَٱلۡيَوۡمِ ٱلۡأٓخِرِ فَقَدۡ ضَلَّ ضَلَٰلَۢا بَعِيدًا 136﴾

{እናንተ ያመናችሁ ሆይ! በአላህና በመልዕክተኛው በዚያ በመልዕክተኛው ላይ ባወረደው መጽሐፍም በዚያም ከበፊቱም ባወረደው መጽሐፍ እመኑ:: በአላህ፣ በመላዕክቱ፣ በመጽሐፍቱ፣ በመልዕክተኞቹና በመጨረሻውም ቀን የካደ ሁሉ ከእውነት የራቀን መሳሳት በእርግጥ ተሳሳተ።} [አን-ኒሳእ: 136]

የላቀው አላህ እንዲህም ብሏል፦

﴿أَلَمۡ تَعۡلَمۡ أَنَّ ٱللَّهَ يَعۡلَمُ مَا فِي ٱلسَّمَآءِ وَٱلۡأَرۡضِۚ إِنَّ ذَٰلِكَ فِي كِتَٰبٍۚ إِنَّ ذَٰلِكَ عَلَى ٱللَّهِ يَسِيرٞ 70﴾

{(መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) አላህ በሰማይና በምድር ውስጥ ያለን ሁሉ በእርግጥ የሚያውቅ መሆኑን አታውቅምን? ይህ በመጽሐፍ ውስጥ የተመዘገበ እውነት ነው:: ይህም በአላህ ላይ ገር ነው::} [አል'ሐጅ፡ 70]

ሁለተኛ፦ ሐዲሣዊ ማስረጃዎች፤ ከነዚህም መካከል ሙስሊም በሰሒሕ ኪታባቸው ላይ ከምእመናን መሪ (አሚረል ሙእሚኒን) ዑመር ኢብኑል ኸጣብ - አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላቸውና - የዘገቡትና ጂብሪል ዐለይሂ ሰላም ነቢዩን - የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና - ስለ ኢማን የጠየቀበት የታወቀው ሰሒሕ ሐዲሥ ይገኝበታል፤ በሐዲሡም ጅብሪል ነብዩን - የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና - ስለ ኢማን ሲጠይቃቸው እንዲህ ብለውታል፦

«الإِيمَانُ أَنْ تُؤْمِنَ بِاللَّهِ، وَمَلَائِكَتِهِ، وَكُتُبِهِ، وَرُسُلِهِ، وَاليَوْمِ الآخِرِ، وَتُؤْمِنَ بِالقَدَرِ خَيْرِهِ وَشَرِّهِ».

«ኢማን ማለት በአላህ፣ በመላእክቱ፣ በመጻሕፍቱ፣ በመልዕክተኞቹ እና በመጨረሻው ቀን ማመን እና በቀደር መልካምም ይሁን መጥፎው ማመን ነው።»1 ሐዲሥ ቡኻሪ እና ሙስሊም በጥቂት የቃላት ልዩነት ከአቡ ሁረይራ ረዲየላሁ ዐንሁ ዘግበውታል።

ማንኛውም ሙስሊም ስለ አላህ፣ ስለ ቂያማ ቀን ጉዳይ እና ከዚህ ውጭ ያሉም የግድ ማመን ያለበት አላህና መልእክተኛው - የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና - የተናገሯቸው ሌሎች የሩቅ ምስጢር ጉዳዮች ሁሉ ከነዚህ ስድስቱ መሰረቶች የሚውጣጣ ነው።

የእነዚህ ስድስቱ መሰረቶች ማብራሪያም እንደሚከተለው ነው፡

የመጀመሪያው መሰረት: የበላይ በሆነው አላህ ማመን

ይህም በርካታ ጉዳዮችን ይዟል፤ ከእነዚህም መካከል፦ የባሮቹ ፈጣሪ፣ በጎ የሚውልላቸው፣ ሲሳይንም የሚለግሳቸው፣ ድብቅም ሆነ ግልፅ ማንነታቸውን ጠንቅቆ የሚያውቅላቸው፤ ከመካከላቸው መልካሞቹን የሚመነዳ ክፉዎቹንም የሚቀጣ በመሆኑ እርሱ እውነተኛ እና ያለ ምንም ተጋሪ በብቸኝነት ሊመለክ የሚገባው አምላክ መሆኑን ማመን ነው።

አላህ ሁለቱን ከባባድ ፍጡሮች (ጂኒን እና ሰውን) የፈጠራቸው ለዚሁ አምልኮ ነው፤ በዚህም አዟቸዋል፤ አላህ እንዲህ ብሏል:-

﴿وَمَا خَلَقۡتُ ٱلۡجِنَّ وَٱلۡإِنسَ إِلَّا لِيَعۡبُدُونِ 56 مَآ أُرِيدُ مِنۡهُم مِّن رِّزۡقٖ وَمَآ أُرِيدُ أَن يُطۡعِمُونِ 57 إِنَّ ٱللَّهَ هُوَ ٱلرَّزَّاقُ ذُو ٱلۡقُوَّةِ ٱلۡمَتِينُ 58﴾

{ጂኒንና ሰዉን ሊገዙኝ እንጂ ለሌላ አልፈጠርኳቸዉም::

ከእነርሱም ምንም ሲሳይን አልፈልግም:: እንዲመግቡኝም አልፈልግም::

አላህ እርሱ ሰጪና የብርቱ ሀይል ባለቤት ነውና።} [አዝ-ዛሪያት: 56-58]

የላቀው አላህ እንዲህም ብሏል፡

﴿يَٰٓأَيُّهَا ٱلنَّاسُ ٱعۡبُدُواْ رَبَّكُمُ ٱلَّذِي خَلَقَكُمۡ وَٱلَّذِينَ مِن قَبۡلِكُمۡ لَعَلَّكُمۡ تَتَّقُونَ 21 ٱلَّذِي جَعَلَ لَكُمُ ٱلۡأَرۡضَ فِرَٰشٗا وَٱلسَّمَآءَ بِنَآءٗ وَأَنزَلَ مِنَ ٱلسَّمَآءِ مَآءٗ فَأَخۡرَجَ بِهِۦ مِنَ ٱلثَّمَرَٰتِ رِزۡقٗا لَّكُمۡۖ فَلَا تَجۡعَلُواْ لِلَّهِ أَندَادٗا وَأَنتُمۡ تَعۡلَمُونَ 22﴾

{እናንተ ሰዎች ሆይ! እናንተንና እነዚያን ከናንተ በፊት የነበሩትንም የፈጠረውን ጌታችሁን (አላህን) በብቸኝነት ተገዙት:: ቅጣትን ልትጠነቀቁ ይከጀላልና።

እርሱ (አላህ) ያ ለእናንተ ምድርን ምንጣፍ፤ ሰማይን ጣራ ያደረገ ጌታ ነው::ከሰማይም (ከዳመና) ውሃን ያወረደና በርሱም (በውሃው) ከፍሬዎች ሁሉ ለእናንተ ሲሳይን ያወጣላችሁ ነው:: እናንተም (ብቸኛ ፈጣሪነቱን) የምታውቁ ስትሆኑ ለአላህ (በአምልኮ) ባላንጣዎችን አታድርጉ፡፡} [አል-በቀራህ: 21-22]

ይህንኑ እውነታ እንዲያብራሩ፤ ወደዚህም ጥሪ እንዲያደርጉ፤ ከሚፃረረውም እንዲያስጠነቅቁ የላቀው አላህ መልእክተኞችን ልኮ መጽሐፎችን አውርዷል። ጥራት የተገባውና የላቀው አላህ እንዲህ ብሏል፡-

﴿وَلَقَدۡ بَعَثۡنَا فِي كُلِّ أُمَّةٖ رَّسُولًا أَنِ ٱعۡبُدُواْ ٱللَّهَ وَٱجۡتَنِبُواْ ٱلطَّٰغُوتَ...﴾

{በየሕዝቡም ሁሉ ውስጥ አላህን ተገዙ ጣዖትንም ራቁ በማለት (የሚያስተምሩ) መልዕክተኛን በእርግጥ ልከናል...} [አን-ነሕል፡ 36]

ጥራት የተገባው አላህ እንዲህ ብሏል፡

﴿وَمَآ أَرۡسَلۡنَا مِن قَبۡلِكَ مِن رَّسُولٍ إِلَّا نُوحِيٓ إِلَيۡهِ أَنَّهُۥ لَآ إِلَٰهَ إِلَّآ أَنَا۠ فَٱعۡبُدُونِ 25﴾

{(መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ካንተ በፊትም እነሆ ከእኔ ሌላ አምላክ የለምና ተገዙኝ በማለት ወደ እርሱ የምናወርድለት ቢሆን እንጂ ከመልዕክተኛ አንድንም አላክንም::} [አል-አንቢያእ፡ 25]

አላህ እንዲህ ብሏል፦

﴿الر كِتَابٌ أُحْكِمَتْ آيَاتُهُ ثُمَّ فُصِّلَتْ مِنْ لَدُنْ حَكِيمٍ خَبِيرٍ1 أَلَّا تَعْبُدُوا إِلَّا اللَّهَ إِنَّنِي لَكُمْ مِنْهُ نَذِيرٌ وَبَشِيرٌ2﴾

{አሊፍ፤ ላም፤ ራ፤. ይህ ቁርኣን አንቀጾቹ በጥንካሬ የተሰካኩ ከዚያም የተዘረዘሩ የሆነ መጽሀፍ ነው፤ ጥበበኛና ውስጠ አዋቂ ከሆነው (አምላክ) ዘንድ የተወረደ ነው::

(እንዲህ በላቸው): «አላህን እንጂ ሌላን አትገዙ:: እኔ ለእናንተ ከእርሱ ዘንድ የተላኩ አስፈራሪና አብሳሪ ነኝ።» [ሁድ: 1-2]

የዚህ አምልኮ እውነተኛ መገለጫ፡- በዱዓ፣ በፍራቻ፣ በተስፋ፣ በሰላት፣ በፆም፣ በእርድ፣ በስለት እና ከእነዚህ ውጭ ባሉ ሌሎች የአምልኮ ዓይነቶች ሁሉ፣ ለእርሱ በመተናነስ፣ ምንዳውን በመከጀልና ከቅጣቱ በመፍራት እንዲሁም ለእርሱ የተሟላ ውዴታንና ለልቅናው መዋረድን በተላበሰ መልኩ የበላይ የሆነውን አላህን ብቸኛ አድርጎ ማምለክ ነው።

የተከበረውን ቁርኣን ያስተነተነ ሰው አብዛኛው የቁርአን ክፍል በዚህ ታላቅ መሰረት ላይ እንደወረደ ያገኛል፤ ለምሳሌ ከእንከን የጠራውና የላቀው ጌታችን እንዲህ ብሏል፦

﴿إِنَّآ أَنزَلۡنَآ إِلَيۡكَ ٱلۡكِتَٰبَ بِٱلۡحَقِّ فَاعْبُدِ اللَّهَ مُخْلِصًا لَهُ الدِّينَ 2 أَلَا لِلَّهِ الدِّينُ الْخَالِصُ وَٱلَّذِينَ ٱتَّخَذُواْ مِن دُونِهِۦٓ أَوۡلِيَآءَ مَا نَعۡبُدُهُمۡ إِلَّا لِيُقَرِّبُونَآ إِلَى ٱللَّهِ زُلۡفَىٰٓ إِنَّ ٱللَّهَ يَحۡكُمُ بَيۡنَهُمۡ فِي مَا هُمۡ فِيهِ يَخۡتَلِفُونَۗ إِنَّ ٱللَّهَ لَا يَهۡدِي مَنۡ هُوَ كَٰذِبٞ كَفَّارٞ3﴾

{(መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) እኛ ወደ አንተ መጽሐፉን በእውነት የተሞላ ሲሆን አወረድነው:: አላህንም ሃይማኖትን ለእርሱ ብቻ ያጠራህ ሆነህ ተገዛው::

ንቁ! ፍጹም ጥሩ የሆነው ሃይማኖት የአላህ ብቻ ነው:: እነዚያ ከእርሱ ሌላ ጣዖታትን ረዳቶች አድረገው የያዙት ሁሉ «ወደ አላህ ማቃረብን እንዲያቃርቡን በማሰብ እንጂ ለሌላ አንገዛቸዉም።» ይላሉ:: አላህ በዚያ እነርሱ በሚለያዩበት ነገር በመካከላቸው ይፈርዳል:: አላህም ውሸታም ከሓዲ የሆነን ሰው አያቀናም::} [አዝ-ዙመር: 2-3]

ጥራት የተገባውና የላቀው አላህ እንዲህም ብሏል፦

﴿وَقَضَىٰ رَبُّكَ أَلَّا تَعۡبُدُوٓاْ إِلَّآ إِيَّاهُ...﴾

{ጌታህም እንዲህ ሲል አዘዘ:: እርሱን እንጂ ሌላን አትገዙ፤…} [አል-ኢስራእ፡ 23]

አላህ እንዲህም ብሏል፦

﴿فَٱدۡعُواْ ٱللَّهَ مُخۡلِصِينَ لَهُ ٱلدِّينَ وَلَوۡ كَرِهَ ٱلۡكَٰفِرُونَ14﴾

{አላህንም ከሓዲያን ቢጠሉም (እንኳ) ሃይማኖትን ለእርሱ አጥሪዎች ሆናችሁ ተገዙ::} [ጋፊር: 14]

እንደዚሁም የነብዩን ሐዲሦች ያጤነ ለዚህ ታላቅ መሠረት ትልቅ ትኩረት እንደተሰጠው ይገነዘባል። ከዚህም መካከል በሶሒሕ ቡኻሪና ሙስሊም ከሙዓዝ - አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላቸውና - በተላለፈ ሐዲሥ ነቢዩ - የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና- እንዲህ ብለዋል፦

«حَقُّ اللهِ عَلَى العِبَادِ أَن يَعْبُدُوهُ وَلَا يُشْرِكُوا بِهِ شَيْئًا».

"አላህ በባሮቹ ላይ ያለው መብት በእርሱ ላይ ምንንም ሳያጋሩ በብቸኝነት ሊያመልኩት ነው።"(2)2

እንዲሁም በአላህ ማመን ውስጥ ከሚካተቱ ነገሮች መካከል፦ አላህ በባሮቹ ላይ ግዴታ ባደረገባቸውና በደነገገላቸው እንደ አምስቱ ግልፅ የእስልምና ማእዘናት ባሉት ሁሉ ማመን አንዱ ነው።

እነሱም፦ ከአላህ በስተቀር በእውነት የሚመለክ አምላክ አለመኖሩን እና ሙሐመድ የአላህ መልዕክተኛ መሆናቸውን መመስከር፣ ሶላትን ደንብና ሥርዓቱን ጠብቆ መስገድ፣ ዘካ መስጠት፣ የረመዳንን ወር መጾም፣ አቅሙ ለቻለ ሰው የተከበረውን የአላህን ቤት ሐጅ ማድረግ እና የጠራው ሸሪዓ በደነገጋቸው ሌሎችም ግዴታዎች ማመን ነው።

ከእነዚህ ማዕዘናት ውስጥ ዋነኛውና ትልቁ፡ ከአላህ በስተቀር በእውነት አምልኮ የሚገባው ሌላ አምላክ አለመኖሩንና ሙሐመድም የአላህ መልእክተኛ መሆናቸውን መመስከር ነው። ይህቺም የምስክርነት ቃል የምታስፈርደው፡ አላህን ብቻ መገዛትን እና ሌላ ማንኛውንም ነገር ከመገዛት መቆጠብን ነው። ይህም የ«ላኢላሃ ኢለሏህ» ትርጉም ነው፤ ትርጉሙም - ዑለማዎች አላህ ይዘንላቸውና እንዳሉት፡ «ከአላህ በስተቀር በእውነት የሚመለክ አምላክ የለም» ማለት ነው። በዚህ ላይ ተመስርቶም፡ ከአላህ ውጭ የሚመለክ ነገር ሁሉ - ሰውም ይሁን መልአክ፣ ጂኒም ሆነ ሌላ - የሚመለከው በውሸት ነው። በእውነት የሚመለከውም አጋር የሌለው አላህ ብቻ ነው። ጥራት የተገባውና የላቀው (አላህ) እንዲህ ብሏል፡-

﴿ذَٰلِكَ بِأَنَّ ٱللَّهَ هُوَ ٱلۡحَقُّ وَأَنَّ مَا يَدۡعُونَ مِن دُونِهِۦ هُوَ ٱلۡبَٰطِلُ...﴾

{ይህ የሆነው አላህም ፍፁም እውነት በመሆኑ፤ ከርሱም ሌላ የሚገዙት ነገር ፍጹም ውሸት በመሆኑ...} [አል'ሐጅ፡ 62]

ጥራት የተገባው አላህ ሁለቱን ከባባድ ፍጥረታት ለዚሁ ቀዳሚ መርሕ ብሎ የፈጠረ፣ በእርሱም ያዘዛቸው፣ መልዕክተኞቹንም የላከ፣ ኪታቦቹንም ያወረደ መሆኑ ቀደም ብሎ ተብራርቷል። ስለሆነም አንድ ባሪያ ይህንን ቁም ነገር በደንብ ሊያስተውለውና ደጋግሞም ሊያስተነትነው ይገባል፤ ይሄንን ካስታዋለ ብዙሀኑ ሙስሊሞች በዚህ መሰረታዊ ነገር ላይ የወደቁበት ከባድ አላዋቂነት ፍንትው ብሎ ይታየዋል፤ ከአላህ ጋር ሌሎችን እስከማምለክና የእርሱን ብቸኛ መብት ከእርሱ ውጪ ላሉ አካላት እስከመስጠትም ደርሰዋል። አሏሁል ሙስተዓን

ጥራት በተገባው አላህ ከማመን መካከል: አላህ የዓለም ፈጣሪ፣ የጉዳዮቻቸው አስተናባሪ፣ በዕውቀቱም በኃይሉም እንደፍላጎቱ አድርጎ የሚያስተዳድራቸው መሆኑን፤ እንዲሁም እርሱ የዱኒያውም የአኺራውም ባለቤት መሆኑን፤ ከእርሱ ውጭ ፈጣሪ የሌለ ከእርሱም ውጭ ጌታ የሌለ ብቸኛ መሆኑንም ማመን ይገኝበታል። እንዲሁም አላህ ባሮችን ለማረምና፣ በቅርቢቱም (በዱንያ) ሆነ በመጪው ዓለም (በኣኺራ) መዳናቸውና መበጀታቸው (ደህንነታቸው/ስኬታቸው) ወዳለበት ነገር እነርሱን ለመጥራት ሲል፤ መልእክተኞችን እንደላከና መጽሐፍትንም እንዳወረደ (ያምናሉ)።»

ጥራት የተገባውና የላቀው አላህ በዚህ ሁሉ ምንም ተጋሪ የለውም። ከፍ ያለው አላህ እንዲህ ብሏል፦

﴿ٱللَّهُ خَٰلِقُ كُلِّ شَيۡءٖۖ وَهُوَ عَلَىٰ كُلِّ شَيۡءٖ وَكِيلٞ 62﴾

{አላህ የነገሩ ሁሉ ፈጣሪ ነው:: እርሱም በነገሩ ሁሉ ላይ አስተናባሪ ነው::} [አዝ-ዙመር፡ 62]

የላቀው አላህ እንዲህም ብሏል፡

﴿إِنَّ رَبَّكُمُ ٱللَّهُ ٱلَّذِي خَلَقَ ٱلسَّمَٰوَٰتِ وَٱلۡأَرۡضَ فِي سِتَّةِ أَيَّامٖ ثُمَّ ٱسۡتَوَىٰ عَلَى ٱلۡعَرۡشِۖ يُغۡشِي ٱلَّيۡلَ ٱلنَّهَارَ يَطۡلُبُهُۥ حَثِيثٗا وَٱلشَّمۡسَ وَٱلۡقَمَرَ وَٱلنُّجُومَ مُسَخَّرَٰتِۭ بِأَمۡرِهِۦٓۗ أَلَا لَهُ ٱلۡخَلۡقُ وَٱلۡأَمۡرُۗ تَبَارَكَ ٱللَّهُ رَبُّ ٱلۡعَٰلَمِينَ54﴾

{(ሰዎች ሆይ) ጌታችሁ አላህ ያ ሰማያትንና ምድርን በስድስት ቀናት ውስጥ የፈጠረና ከዚያም በዐርሹ ላይ ከፍ ያለ ነው። ቀኑንም በሌሊቱ ይሸፍነዋል:: ሁለቱም እርስ በእርስ በፍጥነት ይፈላለጋሉ:: ጸሐይ ጨረቃና ከዋክብት በትዕዛዙ የተገሩ ናቸው። አስተውሉ! መፍጠርም ማዘዝም የእርሱ (የአላህ) ነው:: የዓለማት ጌታ የሆነው አላህ ክብሩ ላቀ::} [አል'አዕራፍ፡ 54]

በላቀው አላህ ማመን ውስጥ ከሚካተት ነገር መካከል፦ በታላቁ ቁርአን ውስጥ በመጡና ከታማኙ መልዕክተኛው በተረጋገጡ የተዋቡ የአላህ ስሞች እና ታላላቅ ባህሪያት፤ ያለ ማዛባት፣ ውድቅ ሳያደርጉ፣ አኳኋኑን ሳይገልፁ እና ከማንም ጋር ሳያመሳስሉ ማመን ነው።

﴿...لَيۡسَ كَمِثۡلِهِۦ شَيۡءٞۖ وَهُوَ ٱلسَّمِيعُ ٱلۡبَصِيرُ﴾

{የሚመስለው ምንም ነገር የለም:: እርሱ ሁሉን ነገር ሰሚና ሁሉን ተመልካች ነው::} [አሽ ሹራ፡ 11]

ልክ በመጣበት መልኩ ‹እንዴት ነው?› ሳይባል (ያለ ከይፍ) እንዲያልፉ ማድረግ ግዴታ ነው። እንዲሁም በመጣበት መልኩ አኳኋኑን ሳይገልፁ መቀበል፣ በሚያመለክቷቸው ታላላቅ ፍቺዎችም -ለሀያሉና የላቀው አላህ መገለጫዎች በሆኑት- ማመን፣ እንዲሁም ማናቸውንም ባህሪያቱ ከፍጡራኑ ጋር ሳያመሳስሉት ለእርሱ በሚገባው መልኩ መግለጽ ግዴታ ነው። ልክ (ከፍ ያለው) አላህ እንደተናገረው።

አሸናፊና ኃያሉ አላህ እንዲህ ብሏል፦

﴿فَلَا تَضۡرِبُواْ لِلَّهِ ٱلۡأَمۡثَالَۚ إِنَّ ٱللَّهَ يَعۡلَمُ وَأَنتُمۡ لَا تَعۡلَمُونَ74﴾

{ለአላህ አምሳያዎችን አታድርጉ:: አላህ ያውቃል፤ እናንተ ግን አታውቁም::} [አን'ነሕል፡ 74]

ይህች እንግዲህ የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ባልደረቦች እና ቅን ተከታዮቻቸው የሆኑት አህለ ሱና ወል-ጀማዓዎች በአላህ ስሞችና ባህሪያት ላይ ያላቸው እምነት ነች። ኢማሙ አቡ አል-ሐሰን አል-አሽዓሪይ አላህ ይዘንላቸውና በ“አልመቃላት” ኪታባቸው ላይ ከአስሓቡል ሐዲሥና ከአህሉ ሱና ያስተላለፉት ሌሎችም የዒልምና የኢማን ሰዎችም ያስተላለፉት አቋም ነች።

አል-አውዛዒይ አላህ ይዘንላቸውና እንዲህ ብለዋል፡- አዝ-ዙህሪይ እና መክሑልም የአላህን ባህሪያት ስለሚገልፁ አንቀጾች ተጠይቀው እንዲህ ብለዋል፦ "እንደ አመጣጡ አሳልፉት።"3

አል-አውዛዒይ አላህ ይዘንላቸውና በድጋሚ እንዲህ ብለዋል፦ (በርካታ ታቢዒዮች በነበሩበት ወቅት ጥራት የተገባው አላህ ከዐርሹ በላይ ነው፤ በሓዲሥ በተጠቀሱት የአላህ ባህሪያትም እናምናለን እንል ነበር።)4

አል-ወሊድ ቢን ሙስሊም አላህ ይዘንላቸውና እንዲህም ብለዋል፦ ማሊክ፣ አል-አውዛዒይ፣ አል-ለይሥ ቢን ሰዕድ እና ሱፍያን አሥ-ሠውሪይ አላህ ይዘንላቸውና የአላህን ባህሪያት የሚገልፁ አንቀፆች በተመለከተ ተጠይቀው ሁሉም በጋራ እንዲህ አሉ፦ "አኳኋኑን ሳትገልፁ ልክ እንደመጣው አፅድቁት።"5

የማሊክ ሸይኽ የሆኑት ረቢዓህ ኢብኑ አቢ ዐብዱረሕማን ሁለቱንም አላህ ይዘንላቸውና ስለ ኢስቲዋእ (ከዐርሽ በላይ ስለመሆኑ) ሲጠየቁ እንዲህ አሉ፡- (አል-ኢስቲዋእ የታወቀ ነው፤ አኳኋኑ በአዕምሮ የሚደረስበት አይደለም፤ መልእክቱ ከአላህ ዘንድ የመጣ ነው፤ መልዕክተኛው የሚጠበቅበት ግልጽ አድርጎ ማድረስ ነው፤ ማመኑ የኛ ፋንታ (ግዴታ) ነው።)6፣ በዚሁ ጉዳይ ኢማሙ ማሊክ አላህ ይዘንላቸውና በተጠየቁ ጊዜም እንዲህ አሉ: (አል-ኢስቲዋእ የታወቀ ነው፤ አኳኋኑ በአዕምሮ የማይደረስበት ነው፤ ማመኑ ግዴታ ነው፤ ስለ ጉዳዩ -በዚህ መልኩ- መጠየቅ ቢድአ (ፈጠራ) ነው።) ከዚያም ጠያቂውን እንዲህ አሉት: ”መጥፎ ሰው (የቢድዓ ሰው) መስለህ ነው የታየኸኝ! “ብለው እንዲወጣላቸው አዘዙ።7 ይኸው መልዕክትም የሙእሚኖች እናት ከሆነችው ከኡሙ ሰለማ - ረዲየሏሁ ዐንሃ - ተላልፏል።8

ኢማም አቡ ዐብዱረሕማን ኢብኑል ሙባረክ (አላህ ይዘንላቸውና) እንዲህ አሉ፦ (የላቀው ጌታችን አላህ በሰማያት ላይ ከፍጡራኑ ተለይቶ ከዐርሹ በላይ መሆኑን እናውቃለን።)9

የኢስላም ኢማሞች በዚህ ረገድ የተናገሩት ንግግር በጣም ብዙ ነው። በዚህ ጥንቅር ብቻ ለማሰባሰብ አይመችም። በመሆኑም በርእሰ ጉዳዩ የተላለፉ ሃሳቦችን በተሻለ መልኩ መረዳት የሚፈልግ የሱና ሊቃውንት የፃፉትን ይመልከት። ለምሳሌ፦ በዐብደሏህ ቢን ኢማም አሕመድ የተፃፈውን "አስ-ሱና" የሚለውን ኪታብ፤ በታላቁ ኢማም ሙሐመድ ቢን ኹዛይማህ የተፃፈውን “ተውሒድ” የተሰኘውን ኪታብ፤ እንዲሁም በአቡ አል-ቃሲም አል-ላለካኢይ አጥ-ጦባሪይም የተፃፈውን "አስ-ሱና" የተሰኘውን ኪታብ፤ በአቡበክር ቢን አቢ ዓሲም የተፃፈውን “አስ-ሱና” የተሰኘውን ኪታብ እና ሸይኹል ኢስላም ኢብኑ ተይሚያህ አላህ ይዘንላቸው ለሐመዊዮች የሰጡትን መልስ ይከልስ። ሸይኹል ኢስላም በመልሱ የአህለ ሱና ዓቂዳን አብራርተው ተቃዋሚዎቻቸው ስለሚያመጡት ሙግት ስህተትነትም ሸሪዓዊ እና አመክንዮአዊ ማስረጃውን የሱና ሰዎችንም ንግግር ትክክለኛነት እና በርእሰ ጉዳዩ የተናገሩትን ብዙ ቃላቶቻቸውንም አስተላልፈዋል።

ልክ እንደዚሁ ተድሙሪያ ብለው በሰየሙት ጽሑፋቸው ላይም፤ የአህለሱና ወልጀማዓን አቋም በሸሪዓዊና አእምሯዊ ማስረጃዎቹ በስፋት አብራርተው፤ ከእውቀት ባለቤቶች መካከል በቅን ልቦናና ሐቅን ለማወቅ ፈልጎ ለተመለከተው ሁሉ እውነትን ግልፅ በሚያደርግና ሃሰትን በሚንድ መልኩ ለተቃዋሚዎችም ምላሽ ሰጥተውበታል። ማጠቃለያውም፡ አህሉስ-ሱንና ወል-ጀማዓ በአላህ ስሞችና ባህሪያት ላይ ያላቸው እምነት ጥራትና ልዕልና የተገባው አላህ በቁርአኑ ለራሱ ያፀደቀውን ወይም መልዕክተኛው ሙሐመድ (ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) በሱንናቸው ያፀደቁለትን ያለምንም ማመሳሰል ያፀድቃሉ፤ ጥራት የተገባውንም ጌታ ፍጡራኑን ከመምሰልና (ባህሪያቱን) ትርጉም አልባ ከማድረግ የጸዳ በሆነ መልኩ ያጠሩታል። በዚህም ከተቃርኖ ድነዋል። በአላህ እገዛ (ተውፊቅ) ሁሉንም ማስረጃዎችም በተግባር ላይ አዋሉ። ምክንያቱም ጥራት የተገባው አላህ መልዕክተኞቹ ይዘው የመጡትን እውነት አጥብቆ የያዘን፣ ለዚህም የሚችለውን ያህል የጣረን፣ ፍለጋውንም ለእርሱ ብቻ ያደረገን ሰው ወደ እውነት መምራትና ማስረጃውንም ግልጽ ማድረግ የርሱ ፈለግ (ሱንና) ነውና። ልክ የላቀው አላህ እንዲህ እንዳለን ፡-

﴿بَلۡ نَقۡذِفُ بِٱلۡحَقِّ عَلَى ٱلۡبَٰطِلِ فَيَدۡمَغُهُۥ فَإِذَا هُوَ زَاهِقٞ...﴾

{በእርግጥ እውነትን በውሸት ላይ እንጥላለን:: አንጎሉን ያፈርሰዋልም:: ወዲያዉም እርሱ ጠፊ ነው...} [አል'አንቢያእ፡ 18]

የላቀው አላህ እንዲህም ብሏል፡

﴿وَلَا يَأۡتُونَكَ بِمَثَلٍ إِلَّا جِئۡنَٰكَ بِٱلۡحَقِّ وَأَحۡسَنَ تَفۡسِيرًا33﴾

(መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) በየትኛዉም ጥያቄ አይመጡብህም እውነተኛውን መልስና መልካም ፍቺውንም የምናመጣልህ ብንሆን እንጅ::} [አል'ፉርቃን፡ 33]

አህሉሱናን በአላህ ስምና ባህርያት ዙርያ ባላቸው አቋም የተቃረኑ በሚያፀድቁትም ሆነ በሚያወግዙት ነገር ሁሉ ግልፅ የሆነ እርስ በርስ መጋጨት ውስጥ ከመግባታቸውም ባሻገር የቁርአንና ሐዲሥንም ሆነ አእምሯዊ ማስረጃዎችን መቃረናቸው አይቀሬ ነው። አል-ሓፊዝ ኢብኑ ከሢር አላህ ይዘንላቸውና በታዋቂው የተፍሲር ኪታባቸው ይህንን የልዕለ ሃያሉን አላህ ቃል ሲያብራሩ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ምርጥ ንግግር አውስተዋል፦

﴿إِنَّ رَبَّكُمُ ٱللَّهُ ٱلَّذِي خَلَقَ ٱلسَّمَٰوَٰتِ وَٱلۡأَرۡضَ فِي سِتَّةِ أَيَّامٖ ثُمَّ ٱسۡتَوَىٰ عَلَى ٱلۡعَرۡشِ...﴾

{ጌታችሁ ያ ሰማያትንና ምድርን በስድስት ቀናት ውስጥ የፈጠረና ከዚያም በዐርሹ ላይ ከፍ ያለ ነው።…} [አል'አዕራፍ፡ 54]

ካለው ታላቅ ፋይዳ አንፃር እዚህ ላይ እናወሳዋለን፤ አላህ ይዘንላቸውና እንዲህ ብለዋል፦

"ሰዎች በዚህ ጉዳይ እጅግ በርከት ያለ አቋም አላቸው። ይህ ቦታ ታዲያ የነሱን አቋም የምናብራራበት አይደለም። ይልቁን እኛ በዚህ ቦታ የምንከተለው የደጋግ ቀደምት ሰለፎች የነ ኢማም ማሊክ፣ የነ አል-አውዛዒን፣ የነ አሥ-ሠውሪይን፣ የነአል-ለይሥ ቢን ሰዕድን፣ የነ አሽሻፊዒይን፣ የነ ኢማም አሕመድ ቢን ሐንበልን፣ የነ ኢስሓቅ ቢን ራህወይህን እንዲሁም ሌሎችም የጥንትም የዘመናችንም የህዝበ ሙስሊሙ ታላላቅ ኢማሞችን ፈለግ ነው። ይኸውም አኳኋኑን ሳንገልፅ፣ ያለ ማመሳሰልና ውድቅም ሳናደርግ እንደመጣው በማፅደቅ ነው። አላህን ከፍጡራኑ ጋር ወደሚያመሳስሉ ሰዎች አእምሮ ከሚመጣው ምስል ሁሉ አላህ የጠራ ነው። ምክንያቱም አላህ ከፍጡራኑ መካከል እርሱን የሚመስለው ምንም ነገር የለምና።

﴿...لَيۡسَ كَمِثۡلِهِۦ شَيۡءٞۖ وَهُوَ ٱلسَّمِيعُ ٱلۡبَصِيرُ﴾

{የሚመስለው ምንም ነገር የለም:: እርሱ ሁሉን ነገር ሰሚና ሁሉን ተመልካች ነው::} (አሽ'ሹራ፡ 11) ከዛም ባሻገር ጉዳዩ እንደነ የቡኻሪይ ሸይኽ ኑዐይም ኢብኑ ሐምማድ አል-ኹዘዒይ እንዳሉት ነው፡ “አላህን ከፍጡራኑ ጋር ያመሳሰለ ከፍሯል፤ አላህ ራሱን የገለፀበትን ባህሪይ ያወገዘም እንዲሁ ከፍሯል።”10 አላህ ራሱን የገለፀበት መገለጫም ይሁን መልዕክተኛው አላህን የገለፁበት መገለጫ ከፍጡራን ጋር ማመሳሰል የሚባል ነገር የለውም። በመሆኑም በግልፅ የቁርአን አንቀፅና ሶሒሕ በሆነ ሓዲሥ ለአላህ የፀኑ መገለጫዎች ለአላህ ተገቢ በሆነ መልኩ ያፀደቀ፤ አላህም ከእንከን የፀዳ መሆኑን ያመነ ቀናውን ጎዳና ተጉዟል11።" የኢብኑ ከሢር - አላህ ይዘንላቸውና - ንግግር ተጠናቀቀ።

በተጨማሪ በአላህ ማመን ውስጥ ከሚካተቱ ነገሮች መካከል: ኢማን ንግግርም ተግባርም መሆኑን፤ ኢማን አላህን በመታዘዝ የሚጨምር አላህን በማመፅም የሚቀንስ መሆኑን፤ ማንኛውም ሙስሊም እንደ ዝሙት፣ ስርቆት፣ ወለድ መብላት፣ አስካሪ መጠጥ መጠጣት፣ ወላጆችን መጨቆን እና ሌሎች ከሽርክ እና ከኩፍር ያነሱ ወንጀሎችን በመፈፀሙ ብቻ ሐላል ነው ብሎ እስካላለ ድረስ ከእስልምና ወጥቷል ማለት የማይፈቀደ መሆኑን ማመን ነው። ምክንያቱም የላቀውና ከፍ ያለው አላህ እንዲህ ስላለን፦

﴿إِنَّ ٱللَّهَ لَا يَغۡفِرُ أَن يُشۡرَكَ بِهِۦ وَيَغۡفِرُ مَا دُونَ ذَٰلِكَ لِمَن يَشَآءُ...﴾

{አላህ በእርሱ ማጋራትን ፈጽሞ አይምርም:: ከዚህ በታች (ውጭ) ያለውን ኃጢአት ግን ለሚሻው ሁሉ ይምራል...} [አን'ኒሳእ፡ 48] እንዲሁም በሙተዋቲር ሐዲሦች ከአላህ መልዕክተኛ - ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም - ከተዘገቡት መካከል እንዲህ ማለታቸው ይገኝበታል፡

«إِنَّ اللهَ يُخْرِجُ مِنَ النَّارِ مَنْ كَانَ فِي قَلْبِهِ مِثْقَالُ حَبَّةٍ مِنْ خَرْدَلٍ مِنْ إِيْمَانٍ».

«በልቡ ውስጥ የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያክል ኢማን ያለውን አላህ ከእሳት ያወጣዋል።»12

ሁለተኛው መሰረት፦ በመላእክቶች ማመን:

ይህም ሁለት ነገሮችን ያካትታል፡ አንደኛ፦ በመላእክቶች በጥቅሉ ማመን፤ ይህም አላህ ሊታዘዙት ዘንድ የፈጠራቸውና እንዲህ በማለት የገለጻቸው መላእክት እንዳሉት ማመን ነው፦

﴿وَقَالُواْ ٱتَّخَذَ ٱلرَّحۡمَٰنُ وَلَدٗاۗ سُبۡحَٰنَهُۥۚ بَلۡ عِبَادٞ مُّكۡرَمُونَ 26 لَا يَسۡبِقُونَهُۥ بِٱلۡقَوۡلِ وَهُم بِأَمۡرِهِۦ يَعۡمَلُونَ27 يَعۡلَمُ مَا بَيۡنَ أَيۡدِيهِمۡ وَمَا خَلۡفَهُمۡ وَلَا يَشۡفَعُونَ إِلَّا لِمَنِ ٱرۡتَضَىٰ وَهُم مِّنۡ خَشۡيَتِهِۦ مُشۡفِقُونَ28﴾

{«አር-ረሕማንም ከመላእክት ልጅን ያዘ።» አሉ። ጥራት ተገባው። አይደለም መላእክት የተከበሩ ባሮች ናቸው።

በንግግር አይቀድሙትም (ያላለውን አይሉም)፤ እነርሱም በትእዛዙ ይሰራሉ።

በፊታቸው ያለውንና በኋላቸው ያለውንም ሁሉ ያውቃል:: ለወደደውም እንጂ ለሌላው አያማልዱም:: እነርሱም እርሱን ከመፍራታቸው የተነሳ ተጨናቂዎች ናቸው::} [አል-አንቢያእ፡ 26-28]

መላእክቶች ብዙ አይነት ናቸው። ከመካከላቸው የዐርሽ ተሸካሚዎች አሉ፤ ከመካከላቸውም የጀነት እና የጀሀነም በር ጠባቂዎች አሉ፤ ከመካከላቸውም የፍጡራንን ስራ የመመዝገብ የስራ ድርሻ የተሰጣቸው አሉ። ሁለተኛው ጉዳይ፦ በመላእክት በዝርዝር ማመን፤ ይህም ማለት አላህና መልእክተኛው ስማቸውን በጠቀሷቸው ለምሳሌ በወሕይ በተወከለው ጂብሪል፣ በዝናብ በተወከለው ሚካኢል፣ የጀሀነም እሳት ጠባቂ በሆነው ማሊክ እና ቀንዱን በመንፋት በተወከለው ኢስራፊል ማመን ነው። እንዲሁም በሶሒሕ ሐዲሦች በተወሱ የመላእክት ባህሪ ማመን ነው፤ ከእነዚህም መካከል፦ በሶሒሕ ሐዲሥ ከዓኢሻ -አላህ መልካም ስራዋን ይውደድላትና- እንደተዘገበው ነቢዩ ﷺ እንዲህ ብለዋል፦

«خُلِقَتِ الـمَلَائِكَةُ مِن نُورٍ، وَخُلِقَ الجَانُّ مِنْ مَارِجٍ مِنْ نَارٍ، وَخُلِقَ آدَمُ مِمَّا وُصِفَ لَكُم».

“መላእክት የተፈጠሩት ከብርሃን ነው፤ ጋኔኖችም ከእሳት ከሆነ ነበልባል ተፈጠሩ። አደም ደግሞ ለእናንተ ከተገለፀላችሁ ነው የተፈጠረው።”13 ሙስሊም በሶሒሓቸው ዘግበውታል።

ሦስተኛው መሠረት፦ በመጽሐፍቱ ማመን፣ እርሱም በተመሳሳይ ሁለት ነገሮችን ያጠቃልላል፦

አንደኛው ነገር፦ አላህ ለነቢያቱና ለመልዕክተኞቹ እውነታውን እንዲያብራሩ እና ወደ እርሱም ጥሪ እንዲያደርጉ መጽሐፍትን ያወረደላቸው መሆኑን በጥቅሉ ማመን ነው፤ ከፍ ያለው አላህ እንዲህ ብሏል፦

﴿لَقَدۡ أَرۡسَلۡنَا رُسُلَنَا بِٱلۡبَيِّنَٰتِ وَأَنزَلۡنَا مَعَهُمُ ٱلۡكِتَٰبَ وَٱلۡمِيزَانَ لِيَقُومَ ٱلنَّاسُ بِٱلۡقِسۡطِ...﴾

{መልዕክተኞቻችንን በግልጽ ማስረጃዎች በእርግጥ ላክን። ሰዎችም በትክክል ቀጥ እንዲሉ መጽሐፎችንና ሚዛንን ወደ እነርሱ አወረድን።…} [አል'ሐዲድ፡ 25] የላቀው አላህ እንዲህም ብሏል፡

﴿كَانَ ٱلنَّاسُ أُمَّةٗ وَٰحِدَةٗ فَبَعَثَ ٱللَّهُ ٱلنَّبِيِّـۧنَ مُبَشِّرِينَ وَمُنذِرِينَ وَأَنزَلَ مَعَهُمُ ٱلۡكِتَٰبَ بِٱلۡحَقِّ لِيَحۡكُمَ بَيۡنَ ٱلنَّاسِ فِيمَا ٱخۡتَلَفُواْ فِيهِ...﴾

{ሰዎች ሁሉ (አላህን አንድ በማድረግ) አንድ ሕዝብ ነበሩ:: (ተለያዩ) አላህም ነቢያትን አብሳሪዎችና አስፈራሪዎች አድርጎ ላከ:: ከነርሱም ጋር በሰዎች መካከል በዚያ እነርሱ በተለያዩበት ነገር ይፈርድ ዘንድ መጽሐፍትን በእውነት አወረደ::…} [አል'በቀራህ፡ 213]

ሁለተኛው ጉዳይ፦ ዝርዘር በሆነ መልኩ ማመን ነው:- ይህም እንደ ተውራት፣ ኢንጂል፣ ዘቡር እና ቁርኣን አላህ ስማቸውን በጠቀሰልን መጽሐፍት ማመን፣ ቁርአን ከመካከላቸው በላጭና የመጨረሻው እንደሆነ እና ከሌሎቹ ሁሉ የበላይ እና አረጋጋጫቸው እንደሆነም እናምናለን። ኡመቱ ባጠቃላይ ከመልዕክተኛው ሰለሏሁ ዓለይሂ ወሰለም ከመጡ ሶሒሕ ሐዲሦች ጋር አጣምረው ሊከተሉትና ሊፋረዱበትም ግዴታቸው ነው። ምክንያቱም ጥራት የተገባው አላህ መልዕክተኛው ሙሐመድን ሰለሏሁ ዓለይሂ ወሰለምን ወደ ሰዎችና ጂኖች መልዕክተኛ አድርጎ ልኳቸዋል። በመካከላቸውም እንዲፈርዱበት ይህን ቁርኣን በእርሳቸው ላይ አውርዶታል። ለልቦና ፈውስ፣ ለሁሉም ነገርም ማብራርያ፣ ለሙእሚኖችም መመርያ እና እዝነት አድርጎታል። የላቀው አላህ እንዲህ ብሏል፦

﴿وَهَٰذَا كِتَٰبٌ أَنزَلۡنَٰهُ مُبَارَكٞ فَٱتَّبِعُوهُ وَٱتَّقُواْ لَعَلَّكُمۡ تُرۡحَمُونَ155﴾

{ይህ ያወረድነው የሆነ የተባረከ መጽሐፍ ነው:: እናም ተከተሉት፤ ይታዘንላችሁም ዘንድ ከክህደት ተጠንቀቁ።} [አል'አንዓም፡ 155] የላቀው አላህ እንዲህም ብሏል፡

﴿...وَنَزَّلۡنَا عَلَيۡكَ ٱلۡكِتَٰبَ تِبۡيَٰنٗا لِّكُلِّ شَيۡءٖ وَهُدٗى وَرَحۡمَةٗ وَبُشۡرَىٰ لِلۡمُسۡلِمِينَ﴾

{መጽሐፉንም ለሁሉም ነገር አብራሪ፤ መመሪያ፣ እዝነትና ለሙስሊሞች አብሳሪ ሆኖ ባንተ ላይ አወረድነው::} [አን'ነሕል፡ 89] የበላይ የሆነው አላህ እንዲህም ብሏል፡

﴿قُلۡ يَٰٓأَيُّهَا ٱلنَّاسُ إِنِّي رَسُولُ ٱللَّهِ إِلَيۡكُمۡ جَمِيعًا ٱلَّذِي لَهُۥ مُلۡكُ ٱلسَّمَٰوَٰتِ وَٱلۡأَرۡضِۖ لَآ إِلَٰهَ إِلَّا هُوَ يُحۡيِۦ وَيُمِيتُۖ فَـَٔامِنُواْ بِٱللَّهِ وَرَسُولِهِ ٱلنَّبِيِّ ٱلۡأُمِّيِّ ٱلَّذِي يُؤۡمِنُ بِٱللَّهِ وَكَلِمَٰتِهِۦ وَٱتَّبِعُوهُ لَعَلَّكُمۡ تَهۡتَدُونَ158﴾

{(ሙሐመድ ሆይ!) «እናንተ ሰዎች ሆይ! እኔ ወደ እናንተ ወደ ሁላችሁም የአላህ መልዕክተኛ ነኝ:: እርሱም ያ የሰማያትና የምድር ንግስና ለእርሱ ብቻ የሆነ ነው:: እርሱ እንጂ ሌላ አምላክ የለም:: ህያው ያደርጋል:: ይገድላልም:: በአላህ በዚያም በአላህና በቃላቶቹ በሚያምነው የማይጽፍ የማያነብ በሆነው መልዕክተኛውም እመኑ:: ወደ ቅኑ መንገድ ትመሩ ዘንድም ተከተሉት።» በላቸው::} [አልአዕራፍ:158] በዚህ መልኩ የመጡ ቁርአናዊ ማስረጃዎች በርካታ ናቸው።

 

አራተኛው መሠረት፡ በመልዕክተኞች ማመን

ይህም በተመሳሳይ ለሁለት ይከፈላል፦ አንደኛው ጉዳይ፡ በመልዕክተኞች በጥቅሉ ማመን ነው፤ ይህም ጥራት የተገባውና የላቀው አላህ ወደ ባሮቹ ከመካከላቸው የሆኑ መልዕክተኞችን፤ አብሳሪዎች፣ አስፈራሪዎችና ወደ እውነትም ተጣሪዎች አድርጎ እንደላከ እናምናለን፤ እነርሱን አምኖ የተቀበላቸው በደስታ ስኬትን ይጎናፀፋል፤ የተቃወማቸው ደግሞ ክስረትን ይከናነባል። የመጨረሻቸውና ከመካከላቸው በላጩ ነብያችን ሙሐመድ ቢን ዐብደላህ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ናቸው። የላቀው አላህ እንዲህ ብሏል፦

﴿وَلَقَدۡ بَعَثۡنَا فِي كُلِّ أُمَّةٖ رَّسُولًا أَنِ ٱعۡبُدُواْ ٱللَّهَ وَٱجۡتَنِبُواْ ٱلطَّٰغُوتَ...﴾

{በየሕዝቡም ሁሉ ውስጥ አላህን ተገዙ ጣዖትን ራቁ በማለት መልዕክተኛን በእርግጥ ልከናል...} [አን-ነሕል፡ 36] የላቀው አላህ እንዲህ ብሏል፡

﴿رُّسُلٗا مُّبَشِّرِينَ وَمُنذِرِينَ لِئَلَّا يَكُونَ لِلنَّاسِ عَلَى ٱللَّهِ حُجَّةُۢ بَعۡدَ ٱلرُّسُلِ...﴾

{ከመልዕክተኞች በኋላ ለሰዎች በአላህ ላይ ምንም አስረጂ እንዳይኖራቸው አብሳሪዎችና አስፈራሪዎች አድርገን መልዕክተኞችን ላክን...} [አን'ኒሳእ፡ 165] የላቀው አላህ እንዲህም ብሏል፡

﴿مَّا كَانَ مُحَمَّدٌ أَبَآ أَحَدٖ مِّن رِّجَالِكُمۡ وَلَٰكِن رَّسُولَ ٱللَّهِ وَخَاتَمَ ٱلنَّبِيِّـۧنَ...﴾

{(እናንተ ያመናችሁ ሆይ!) ሙሐመድ ከወንዶቻችሁ የአንዱም ሰው አባት አይደለም:: ግን የአላህ መልዕክተኛና የነብያት መደምደሚያ ነው...} [አል'አሕዛብ፡ 40]

ሁለተኛው፡ በመልዕክተኞች በዝርዝር ማመን ነው፤ ይህም አላህ ስማቸውን በጠቀሳቸው ወይም የአላህ መልክተኛ ﷺ በተረጋገጠ ዘገባ በጠቀሷቸው መልክተኞች ለይተን በስማቸው ማመን ነው። እንደ ኑሕ፣ ሁድ፣ ሷሊሕ፣ ኢብራሂም እና ሌሎችም፤ የአላህ ሶላትና ሰላም በነሱም፣ በቤተሰቦቻቸውም እንዲሁም በተከታዮቻቸውም ላይ ይስፈን።

አምስተኛው መሰረት፡ በመጨረሻው ቀን ማመን

እርሱም የሚከተሉትን አጠቃሏል:

አላህና መልዕክተኛው -ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም- ከሞት በኋላ እንደሚከሰት በተናገሩት ነገር ሁሉ ማመን፤ ይህም የቀብር ፈተና፣ የቀብር ቅጣትና ፀጋ፣ በእለተ ትንሳኤ የሚሆኑ ከባባድ መጨናነቆችና መከራዎች፣ የሲራጥ ፈተና፣ የስራ መመዘን፣ በስራ መተሳሰብ፣ ምንዳን ማግኘት፣ የስራ መዝገብ ለእያንዳንዱ ሰው መታደል፤ ከዚያም መዝገቡን በቀኙ የሚቀበል፣ በግራ እጁ የሚቀበል፣ ወይም ከጀርባው በኩል የሚቀበል መኖሩን ነው።

በተጨማሪም ነቢያችን ሙሐመድ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) በተሰጣቸው "ሐውድ" ማመን፣ በጀነት እና በጀሀነም ማመን፣ ሙእሚኖች የላቀው አላህን የሚመለከቱና አላህም እነርሱን የሚያነጋግራቸው ስለመሆኑ እና ከዚህም ውጭ በተከበረው ቁርአንና ሶሒሕ በሆኑ ከነብዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) በተረጋገጡ ሐዲሦች የመጡ እውነታዎችን ሁሉ ማመንንም የሚያጠቃልል ነው። በመሆኑም በባሪያው ላይ ይህንን ሁሉ እውነት ነው ብሎ መቀበልና አላህና መልዕክተኛው (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ባብራሩት መልኩ ማመን ግዴታ ነው።

ስድስተኛው መሰረት፡ በቀደር ማመን

በአራት ጉዳዮች ማመንን ያጠቃልላል፡

የመጀመርያው፡ ጥራት የተገባው አላህ የሆነውንም የሚሆነውንም ጠንቅቆ የሚያውቅ እንደሆነ፤ የባሪያዎቹንም ሁኔታ፣ ሲሳያቸውን፣ የህይወት ጊዜያቸውን፣ ስራዎቻቸውን እና ከዚህም ውጭ ያሉ ጉዳዮቻቸውንም ሁሉ እንደሚያውቅ፤ ጥራት ይገባውና ከእርሱ የሚደበቅ አንዳችም ነገር የሌለ መሆኑን ማመን ነው። አላህ እንዲህ ብሏል፦

﴿...وَٱعۡلَمُوٓاْ أَنَّ ٱللَّهَ بِكُلِّ شَيۡءٍ عَلِيمٞ﴾

{አላህ በሁሉ ነገር ላይ አዋቂ መሆኑንም እወቁ::} [አል-በቀራህ፡ 231] የላቀው አላህ እንዲህ ብሏል፦

﴿...لِتَعۡلَمُوٓاْ أَنَّ ٱللَّهَ عَلَىٰ كُلِّ شَيۡءٖ قَدِيرٞ وَأَنَّ ٱللَّهَ قَدۡ أَحَاطَ بِكُلِّ شَيۡءٍ عِلۡمَۢا﴾

{አላህ በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ መሆኑን አላህም በነገሩ ሁሉ በእውቀት ያካበበ መሆኑን ታውቁ ዘንድ…} [አጥ'ጠላቅ: 12]

ሁለተኛው ጉዳይ፦ አላህ አስቀድሞ የወሰነውንና የፈረደውን ሁሉ እንደጻፈው ማመን ነው። ጥራት የተገባው አላህ እንዲህ ብሏል፦

﴿قَدۡ عَلِمۡنَا مَا تَنقُصُ ٱلۡأَرۡضُ مِنۡهُمۡۖ وَعِندَنَا كِتَٰبٌ حَفِيظُۢ 4﴾

{ከእነርሱ አካል ምድር የምታጎድለውን በእርግጥ አውቀናል:: እኛም ዘንድ ጠባቂ መጽሐፍ አለ::} [ቃፍ፡ 4] የላቀው አላህ እንዲህ ብሏል፦

﴿...وَكُلَّ شَيۡءٍ أَحۡصَيۡنَٰهُ فِيٓ إِمَامٖ مُّبِينٖ﴾

{ሁሉን ነገርም ገላጭና መሪ በሆነ መጽሐፍ ውስጥ አጠቃለልነው::} [ሱረቱ ያሲን፡ 12] የላቀው አላህ እንዲህ ብሏል፦

﴿أَلَمۡ تَعۡلَمۡ أَنَّ ٱللَّهَ يَعۡلَمُ مَا فِي ٱلسَّمَآءِ وَٱلۡأَرۡضِۚ إِنَّ ذَٰلِكَ فِي كِتَٰبٍۚ إِنَّ ذَٰلِكَ عَلَى ٱللَّهِ يَسِيرٞ70﴾

{(መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) አላህ በሰማይና በምድር ውስጥ ያለን ሁሉ በእርግጥ የሚያውቅ መሆኑን አታውቅምን? ይህ በመጽሐፍ ውስጥ የተመዘገበ እውነት ነው:: ይህም በአላህ ላይ ገር ነው::} [አል'ሐጅ፡ 70]

ሦስተኛው ጉዳይ፦ ተፈፃሚ በሆነው የላቀው የአላህ ፈቃድ ማመን ነው፤ በመሆኑም እርሱ የሻው ነገር ይሆናል፤ እርሱ ያልሻው አንዳችም ነገር አይሆንም። ከፍ ያለውና ጥራት የተገባው አላህ እንዲህ ብሏል፦

﴿...إِنَّ ٱللَّهَ يَفۡعَلُ مَا يَشَآءُ﴾

{…አላህ የሻውን ይሰራልና} [አል'ሐጅ፡ 18] አሸናፊና ኋያሉ አላህ እንዲህ ብሏል፦

﴿إِنَّمَآ أَمۡرُهُۥٓ إِذَآ أَرَادَ شَيۡـًٔا أَن يَقُولَ لَهُۥ كُن فَيَكُونُ82﴾

{ነገሩ አንዳችን በሻ ጊዜ ሁን ማለት ብቻ ነው:: ወዲያው ይሆናልም::} [ሱረቱ ያሲን፡ 82] ጥራት የተገባው አላህ እንዲህም ብሏል፡

﴿وَمَا تَشَآءُونَ إِلَّآ أَن يَشَآءَ ٱللَّهُ رَبُّ ٱلۡعَٰلَمِينَ29﴾

{(ሰዎች ሆይ!) የዓለማት ጌታ የሆነው አላህ ካልሻ በስተቀር እናንተ አንድም ነገር አትሹም።} [አት'ተክዊር: 29]

አራተኛው ጉዳይ፡- ሁሉንም ግኝቶች የፈጠረው የላቀው አላህ መሆኑን ማመን ነው። ከእርሱ ውጭ ፈጣሪም የለም፤ ከእርሱ ውጭ ጌታም የለም። ጥራት የተገባው አላህ እንዲህ ብሏል፡

﴿ٱللَّهُ خَٰلِقُ كُلِّ شَيۡءٖۖ وَهُوَ عَلَىٰ كُلِّ شَيۡءٖ وَكِيلٞ62﴾

{አላህ የነገሩ ሁሉ ፈጣሪ ነው:: እርሱም በነገሩ ሁሉ ላይ አስተናባሪ ነው::} [አዝ-ዙመር፡ 62] ጥራት የተገባው አላህ እንዲህም ብሏል፡

﴿يَٰٓأَيُّهَا ٱلنَّاسُ ٱذۡكُرُواْ نِعۡمَتَ ٱللَّهِ عَلَيۡكُمۡۚ هَلۡ مِنۡ خَٰلِقٍ غَيۡرُ ٱللَّهِ يَرۡزُقُكُم مِّنَ ٱلسَّمَآءِ وَٱلۡأَرۡضِۚ لَآ إِلَٰهَ إِلَّا هُوَۖ فَأَنَّىٰ تُؤۡفَكُونَ3﴾

{እናንተ ሰዎች ሆይ! በእናንተ ላይ (ያለውን) የአላህን ጸጋ አስታውሱ፡፡ ከአላህ ሌላ ፈጣሪ አለን? ከሰማይና ከምድርም ሲሳይን የሚሰጣችሁ አለን? ከእርሱ በስተቀር አምላክ (ሰጪም) የለም፡፡ ታዲያ ወዴት ትዞራላችሁ፡፡} [ፋጢር፡ 3]

ከእነዚህ ከፊሎቹን ካስተባበሉ የቢድዓ ሰዎች በተቃራኒ አህለሱና ወልጀመዓዎች ዘንድ በቀደር ማመን በእነዚህ አራቱም ጉዳዮች ማመንን ያጠቃልላል።

በአህሉ ሱንና ትክክለኛ እምነት ውስጥ ከሚካተቱ አስፈላጊ ጉዳዮች መካከል ለአላህ ብሎ መውደድ፣ ለአላህ ብሎ መጥላት፣ ወዳጅነትንም ጠላትነትንም ለአላህ ብሎ መመስረት ነው። ይህ የ«ወላእና በራእ» ዐቂዳ (እምነት) ሲሆን፤ እርሱም በአላህ ማመን ውስጥ የሚካተት ነው።

ሙእሚን ምእመናንን ይወዳል ይወዳጃቸዋል፤ ከሓዲዎችንም ይጠላል ጠላት አድርጎም ይይዛቸዋል። አህሉ ሱናህ ወልጀማዓዎች ዘንድ እንደፀናውም እዚህ ኡመት ውስጥ የምእመናን ግንባር ቀደም የአላህ መልእክተኛ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ሶሓቦች ናቸው። እነርሱን ይወዷቸዋል ይወዳጇቸዋል፤ ከነብያት በኋላ ከሰዎች ሁሉ በላጭ እንደሆኑም ያምናሉ። ምክንያቱም ነብዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) እንዲህ ስላሉ፦

«خَيْرُ القُرُونِ قَرْنِي ثُمَّ الَّذِينَ يَلُونَهُمْ ثُمَّ الَّذِينَ يَلُونَهُم».

«ከትውልዶች ሁሉ ምርጡ እኔ ያለሁበት ትውልድ ነው። ከዚያም ከነርሱ በኋላ ቀጥለው የሚመጡት፤ ከዚያም ከነርሱ ቀጥለው የሚመጡት ናቸው።»14 በሰሒሕነቱ ላይ ተስማምተውበታል።

አህለ ሱናዎች ከሶሓቦች በላጩ አቡበከር አስ-ሲዲቅ፣ ከዚያም ዑመር አል-ፋሩቅ፣ ከዚያም ዑሥማን ዙን-ኑረይን፣ ከዚያም ዐሊይ አል-ሙርተዷ - አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና - መሆናቸውን፤ ከዛ በኋላ ደግሞ ጀነት ከተመሰከረላቸው ከአስሩ የተቀሩት፤ ከዚያም የተቀሩት ሰሐቦች -አላህ ሁሉንም መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና - መሆናቸውን ያምናሉ። በሶሓቦች መካከል በተከሰተው አለመግባባት ዙርያ ከማውራት ይታቀባሉ። ሶሓቦቹ በጉዳዩ ሙጅተሂዶች መኾናቸውንና እውነታውን ላገኘ ድርብ ምንዳዎች ከመካከላቸው ስህተት ላይ የነበረውም አንድ አጅር እንዳለው ያምናሉ።

በረሱል ﷺ ያመኑትን የርሳቸውን ቤተሰቦች (አህሉል በይት) ይወዳሉ፤ ወዳጅ አድርገውም ይይዛሉ። እንዲሁም ‹የምዕመናን እናቶች› የሆኑትን የረሱል ﷺ ሚስቶችንም ባለቤቶች ወዳጅ ያደርጋሉ፤ ለሁሉም አላህ መልካም ሥራቸውን እንዲወድላቸውም ዱዓእ ያደርጋሉ። የአላህ መልእክተኛን ﷺ ባልደረቦች የሚጠሉ፣ የሚዘልፉ፣ በነብዩ ቤተሰቦች ድንበር የሚያልፉና አላህ ከሰጣቸው ደረጃም ከፍ አድርገው ሌላ ደረጃ ላይ የሚያደርጓቸው ከሆኑት የራፊዷዎች አካሄድ ራሳቸውን ያጠራሉ። በተመሳሳይ የነብዩን ቤተሰቦች በንግግርም ሆነ በተግባር ከሚያውኩ ከነዋሲቦችም አካሄድ ራሳቸውን ያጠራሉ።

ይህ የጠቀስነው ሁሉ አላህ መልእክተኛው ሙሐመድን (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) የላከበት በሆነው ትክክለኛ እምነት ውስጥ የሚካተት ነው። እርሱም ልናምንበት፣ አጥብቀን ልንይዘው፣ በታማኝነት ልንፀናበት እና ከሚፃረረውም ነገር ልንጠነቀቅ የሚገባን ሲሆን፤ የፊርቀቱ ናጂያ አህሉ ሱና ወል-ጀማዓህ ዐቂዳም ነው፤ ነቢዩም (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) እርሷን አስመልክተው እንዲህ ብለዋል፦

«لَا تَـزَالُ طَائِفَةٌ مِنْ أُمَّتِي ‌ظَاهِرِينَ ‌عَلَى ‌الحَقِّ، لَا يَضُرُّهُمْ مَنْ خَذَلَهُمْ، حَتَّى يَأْتِيَ أَمْرُ اللهِ وَهُمْ كَذَلِكَ».

«ከኡመቴ መካከል በእውነት ላይ የበላይ የሆኑና ያዋረዳቸው የማይጎዳቸው ጭፍሮች ከመኖር አይወገዱም። የአላህ ትእዛዝ እስኪመጣ ድረስም በዚያው ሁኔታቸው ላይ ይቆያሉ።»15

በሌላ ዘገባ:

«لَا تَزَالُ طَائِفَةٌ مِنْ أُمَّتِي عَلَى الحَقِّ مَنْصُورَةٌ».

«በእውነት ላይ የበላይ የሆነች (ድል የተጎናጸፈች) አንዲት ጭፍራ ከኡመቴ አትወገድም።»16

እንዲህም ብለዋል፦

«افْتَرَقَتِ اليَهُودُ عَلَى إِحْدَى وَسَبْعِينَ فِرْقَةً، وَافْتَرَقَتِ النَّصَارَى عَلَى اثْنَتَيْنِ وَسَبْعِينَ فِرْقَةً، وَسَتَفْتَرِقُ هَذِهِ الأُمَّةُ عَلَى ثَلَاثِ وَسَبْعِينَ فِرْقَةً كُلُّهَا فِي النَّارِ إِلَّا وَاحِدَةً فَقَالَ الصَّحَابَةُ: مَنْ هِيَ يَا رَسُولَ اللهِ؟ قَالَ: مَنْ كَانَ عَلَى مِثْلِ مَا أَنَا عَلَيْهِ وَأَصْحَابِي».

«አይሁዶች ወደ ሰባ አንድ ጭፍሮች ተከፋፍለዋል፤ ክርስቲያኖችም ወደ ሰባ ሁለት ጭፍሮች ተከፋፍለዋል፤ ይህ ሙስሊሙ ኡመት ደግሞ ወደ ሰባ ሦስት ጭፍሮች ይከፋፈላሉ። ሁሉም የእሳት ይሆኑና አንዷ ብቻ ትድናለች። ሱሓቦችም 'የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! ይህች (የምትድነዋ) ማን ናት?' ብለው ጠየቁ እርሳቸውም (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) 'እኔና ባልደረቦቼ ባለንበት ሁኔታ የሆኑት ናቸው።' በማለት መለሱ።»17

ትክክለኛውን ዐቂዳ የሚፃረሩ የሆኑ እምነቶች

ከዚህ ዐቂዳ (እምነት) አፈንግጠው በተቃራኒው ጎዳና ላይ የሚጓዙት ብዙ ጭፍሮች ናቸው፤ ከነሱ መካከልም፦ ጣዖታትን፣ ግኡዝ አካላትን፣ መላእክትን፣ ቅዱሳንን፣ አጋንንትን፣ ዛፎችን፣ ድንጋዮችንና ሌሎችንም የሚያመልኩ ይገኙበታል። እነዚህ ቁረይሾችና ሌሎች የዐረብ ጭፍሮች ከነብያችን ሙሐመድ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ጋር እንደነበራቸው መስተጋብር በተመሳሳይ ለረሱል (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ዳዕዋ ምላሽ ያልሰጡ እና የተቃረኑ ሰዎች ናቸው። ቁረይሾች አማልክቶቻቸውን ጉዳዮችን እንዲፈፅሙላቸው፣ ህሙማንን እንዲፈውሱላቸው እና በጠላቶች ላይ ድል እንዲያጎናጽፏቸው ይማጸኑ ነበር፤ እርድም ያርዱላቸው፣ ስለትም ይሳሉላቸው ነበር። ረሱል (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ይህንን ድርጊታቸውን ባወገዙባቸውና አምልኮንም ለአላህ ብቻ ጥርት እንዲያደርጉ ባዘዟቸው ጊዜ፣ እንግዳ አድርገው በመደነቅ አስተባበሉ፤ እንዲህም አሉ፦

﴿أَجَعَلَ ٱلۡأٓلِهَةَ إِلَٰهٗا وَٰحِدًاۖ إِنَّ هَٰذَا لَشَيۡءٌ عُجَابٞ5﴾

«አማልክቶችን አንድ አምላክ አደረጋቸውን? ይህ አስደናቂ ነገር ነው።» [ሷድ፡ 5]

ነቢዩ ﷺ የሚያምነው እስኪያምንላቸውም ድረስ ወደ አላህ ከመጣራትና ከሽርክ ከማስጠንቀቅ፤ የጥሪያቸውን እውነታ ከማብራራትም አልተወገዱም። ከዚያም ሰዎች በቡድን በቡድን እየሆኑ ወደ አላህ ዲን መትመማቸውን ቀጠሉ፤ የአላህ መልክተኛ ﷺ ከዚያም የሶሓቦች -ረዲየሏሁ ዓንሁም- እና እነርሱን በቅንነት የተከተሏቸው ተከታዮቻቸው ያለማቋረጥ ዳዕዋ ካደረጉ በኋላ እና ያላለሰለሰ ትግል ካደረጉ በኋላ የአላህ ዲን በሌሎች ሃይማኖቶች ላይ የበላይነቱን ተቆናጠጠ። ከዚያም ሁኔታዎች ተቀያየሩ፤ በብዙ ሰዎች ዘንድም ጅህልና አመዘነ፤ እናም ብዙዎቹ በነብያቶችና በወልዮች ላይ ድንበር በማለፍ፣ እነርሱን በመማፀንና ድረሱልኝ በማለት እንዲሁም ሌሎች የሽርክ አይነቶችን በመፈፀም ወደ ጃሂሊያው እምነት ተመለሱ። የላ ኢላሃ ኢለሏህንም ትርጉም የዐረብ ሙሽሪኮቹ በተረዱት ያህል እንኳ አልተረዱትም ነበር። አላህ ይርዳንና።

ይኸው ሽርክ አላዋቂነት በማመዘኑ እና ከነብያቶች ዘመን የራቅን በመሆናችን ምክንያት አሁን እስካለንበት ዘመን ድረስ በሰዎች መካከል እየተስፋፋ ያለ ነገር ነው።

የዘመናችን አጋርያን የሚያመጡት ማምታቻ የቀድሞዎቹ አጋርያን ማምታቻን ነው። እርሱም የሚከተለው ነው፦

﴿...هَٰٓؤُلَآءِ شُفَعَٰٓؤُنَا عِندَ ٱللَّهِ...﴾

{…እነዚህ አላህ ዘንድ አማላጆቻችን ናቸው።…} [ዩኑስ፡ 18] እንዲህም ብለዋል:

﴿...مَا نَعۡبُدُهُمۡ إِلَّا لِيُقَرِّبُونَآ إِلَى ٱللَّهِ زُلۡفَىٰٓ...﴾

{…ወደ አላህ ማቃረብን እንዲያቃርቡን በማሰብ እንጂ ለሌላ አንገዛቸዉም።…} [አዝ'ዙመር፡ 3] አላህም ይህን ማምታቻ ውድቅ አድርጓል፤ ከእርሱ ሌላን ያመለከ ሰው ማንም ይሁን ማን ሽርክንና ክህደትን እንደፈፀመም ግልፅ አድርጓል። የላቀው አላህ እንዲህም ብሏል፦

﴿وَيَعۡبُدُونَ مِن دُونِ ٱللَّهِ مَا لَا يَضُرُّهُمۡ وَلَا يَنفَعُهُمۡ وَيَقُولُونَ هَٰٓؤُلَآءِ شُفَعَٰٓؤُنَا عِندَ ٱللَّهِ...﴾

{አጋሪዎች ከአላህ ሌላ የማይጎዳቸውንና የማይጠቅማቸውን ይገዛሉ:: «እነዚህ አላህ ዘንድ አማላጆቻችን ናቸው።» ይላሉ…} [ዩኑስ፡ 18] ጥራት የተገባው አላህ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦

﴿قُلۡ أَتُنَبِّـُٔونَ ٱللَّهَ بِمَا لَا يَعۡلَمُ فِي ٱلسَّمَٰوَٰتِ وَلَا فِي ٱلۡأَرۡضِۚ سُبۡحَٰنَهُۥ وَتَعَٰلَىٰ عَمَّا يُشۡرِكُونَ18﴾

{አላህ በሰማያትና በምድር ውስጥ የማያውቀው ነገር ኖሮ እናንተ ትነግሩታላችሁን?» በላቸው:: አላህ ከሚያጋሩት ሁሉ ጠራ:: ላቀም::} [ዩኑስ፡ 18]

የላቀው አላህ በዚህ አንቀፅ ከእርሱ ውጭ ነቢይንም ይሁን ወልይን ወይም ሌሎችንም ቢሆን ማምለክ ድርጊቱን የሚፈፅመው ያሻውን ስም ቢሰጠውም ከታላቁ ሽርክ የሚመደብ ወንጀል መሆኑን ግልፅ አደረገ። የላቀው አላህ እንዲህ ብሏል፦

﴿...وَٱلَّذِينَ ٱتَّخَذُواْ مِن دُونِهِۦٓ أَوۡلِيَآءَ مَا نَعۡبُدُهُمۡ إِلَّا لِيُقَرِّبُونَآ إِلَى ٱللَّهِ زُلۡفَىٰٓ...﴾

{…እነዚያ ከእርሱ ሌላ ጣዖታትን ረዳቶች አድረገው የያዙት «ወደ አላህ ማቃረብን እንዲያቃርቡን በማሰብ እንጂ ለሌላ አንገዛቸዉም።» (ይላሉ)…} [አዝ'ዙመር፡ 3] ከዚያም ከፍ ያለው አላህ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦

﴿...إِنَّ ٱللَّهَ يَحۡكُمُ بَيۡنَهُمۡ فِي مَا هُمۡ فِيهِ يَخۡتَلِفُونَۗ إِنَّ ٱللَّهَ لَا يَهۡدِي مَنۡ هُوَ كَٰذِبٞ كَفَّارٞ﴾

{…አላህ በዚያ እነርሱ በሚለያዩበት ነገር በመካከላቸው ይፈርዳል:: አላህም ውሸታምንና ከሓዲ የሆነን ሰው አያቀናም::} [አዝ'ዙመር፡ 3]

በዚህም ጥራት የተገባው አላህ ሌሎችን መለመን፣ እነርሱን መፍራት፣ ከነርሱ ተስፋ ማድረግና የመሳሰሉት የአምልኮ መገለጫዎችን ለነርሱ መስጠት በእርሱ መካድ መሆኑን ግልፅ አደረገ። ወደ አላህ መቃረብን ያቃርቡናል የሚለው ሙግታቸውንም ውሸትነቱን አጋለጠባቸው።

እንዲሁም መልዕክተኞች (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ይዘውት የመጡትን ትክክለኛ ዐቂዳ (እምነት) የሚቃረኑና የክህደት እምነቶች ከሆኑት መካከል የዘመናችን እምነተ ቢሶች የሚከተሉት የማርክሲዝምና ሌኒኒዝም እምነት ተከታዮች እና ሌሎች የእምነተ ቢስነትና የክህደት ሰባኪዎች ጥሪ ሁሉ ክህደት ነው። ይህንኑ አቋማቸውን ሲፈልጉ ሶሻሊዝም ይበሉት አልያም ኮሚዩኒዝም ከፈለጉም አብዮታዊ ይበሉት ካሻቸውም ሌላ ስም ይስጡት የአቋማቸው ስር መሰረቱ "አምላክ የሚባል ነገር የለም ህይወት የሚባለው ቁሳዊው አለም ብቻ ነው" እስካሉ ድረስ አቋማቸው የክህደት አቋም ነው።

ከአቋማቸው መሰረቶች መካከል ከሞት በኋላ ትንሳኤ መኖሩን መካድ፣ ጀነት እና ጀሀነምን መካድ፣ በሁሉም ሀይማኖቶችም መካድ፣ መጽሐፋቸውን በጥልቅ የመረመረና ያሉበትን ተጨባጭ በሚገባ ያስተዋለ ሰው አቋማቸው ይህ መሆኑን ያረጋግጣል። ይህ እምነት ደግሞ ሃይማኖቶችን በሙሉ የሚቃረን ለመሆኑ እና ሰዎችንም በዱኒያም በአኺራም ለከፋ ፍፃሜ የሚዳርግ ለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም።

እውነተኛ ዐቂዳን (እምነት) ከሚቃረኑ እምነቶች መካከል አንዳንድ ሱፊዮች ወሊይ የሚሏቸውን ሰዎች በማስተናበሩም ይሁን በአለሙ ክንውን ከአላህ ጋር ተጋሪነት እንዳላቸው የሚያምኑት ነገር ይገኝበታል። እነርሱንም "ቁጥብ"፣ "ዊትድ"፣ "ገውስ" እና ሌሎች ስያሜዎችንም እያፈለቁ አማልክቶቻቸውን የሚጠሩት ነገርም አለ። ይህ በአላህ ጌትነት የሚደረግ ሽርክ ሲሆን፤ በአላህ ከሚደረጉ የሽርክ አይነቶችም እጅግ የከፋው ነው።

የቀድሞዎቹን የጃሂሊያ ሰዎች ሽርክ እና በዘመናችን ሰዎች ዘንድ የተንሰራፋውን ሽርክ አስተውሎ ያነጻጸረ ሰው የዘመናችን ሰዎች ሽርክ ይበልጥ የገዘፈና የከፋ መሆኑን ይገነዘባል። የዚህም ማብራሪያ እንደሚከተለው ነው፡ በድንቁርና ዘመን የነበሩ የዐረብ ከሃዲያን በሁለት ነገሮች ተለይተው ነበር: የመጀመሪያው ጉዳይ፦ በጌትነት ላይ አያጋሩም ነበር፤ ሽርካቸው የነበረው በአምልኮ ላይ ነበር፤ ጌትነት የሀያሉና የላቀው አላህ ብቻ መሆኑን ያምኑ ነበርና፤ ጥራት የተገባው ጌታ እንዲህ ብሏል፦

﴿وَلَئِن سَأَلۡتَهُم مَّنۡ خَلَقَهُمۡ لَيَقُولُنَّ ٱللَّهُ...﴾

{(መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ማን እንደ ፈጠራቸው ብትጠይቃቸው በእርግጥ አላህ ነው ይላሉ...} [አዝ'ዙኽሩፍ፡ 87] የላቀው አሏህ እንዲህም ብሏል፡

﴿قُلۡ مَن يَرۡزُقُكُم مِّنَ ٱلسَّمَآءِ وَٱلۡأَرۡضِ أَمَّن يَمۡلِكُ ٱلسَّمۡعَ وَٱلۡأَبۡصَٰرَ وَمَن يُخۡرِجُ ٱلۡحَيَّ مِنَ ٱلۡمَيِّتِ وَيُخۡرِجُ ٱلۡمَيِّتَ مِنَ ٱلۡحَيِّ وَمَن يُدَبِّرُ ٱلۡأَمۡرَۚ فَسَيَقُولُونَ ٱللَّهُۚ فَقُلۡ أَفَلَا تَتَّقُونَ31﴾

{(መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «ከሰማይና ከምድር ሲሳይን የሚሰጣችሁ ማን ነው? መስሚያዎችንና ማያዎችንስ የፈጠረላችሁ ማን ነው? ከሙትም ህያውን የሚያወጣ፤ ከህያዉም ሙትን የሚያወጣስ ማን ነው? ነገሩን ሁሉ የሚያስተናብርስ ማን ነው?» በላቸው:: «በእርግጥ አላህ ነው።» ይሉሃል:: «ታዲያ ለምን ታጋራላችሁ? ታዲያ አትፈሩትምን?» በላቸው።} [ዩኑስ፡ 31] ይህን መሰል መልዕክት ያዘሉ የቁርኣን አንቀጾች በጣም ብዙ ናቸው።

ሁለተኛ፡- በአምልኮ ውስጥ የሚፈፅሙት ሽርካቸው ዘውታሪ ሳይሆን በተድላ ጊዜ ነበር። በችግር ጊዜ ግን አምልኳቸውን ለአላህ ጥርት ያደርጉ ነበር፤ ታላቁ አላህም እንዲህ ብሏል፦

﴿فَإِذَا رَكِبُواْ فِي ٱلۡفُلۡكِ دَعَوُاْ ٱللَّهَ مُخۡلِصِينَ لَهُ ٱلدِّينَ فَلَمَّا نَجَّىٰهُمۡ إِلَى ٱلۡبَرِّ إِذَا هُمۡ يُشۡرِكُونَ65﴾

{በመርከቦች ውስጥ በተሳፈሩ ጊዜም አላህን መገዛትን ለእርሱ ብቻ ያጠሩ ሆነው ይጠሩታል:: ወደ የብስ በማውጣት ባዳናቸው ጊዜ ግን ወዲያውኑ እነርሱ ጣዖትን ያጋራሉ::} [አል'ዐንከቡት፡ 65]

የዘመናችን ሙሽሪኮች ከቀድሞዎቹ በሁለት መንገድ የባሰባቸው ናቸው፡ አንደኛ፡ አንዳንዶቹ በጌትነት ማጋራታቸው፤ ሁለተኛው ደግሞ፡ በምቾትም በችግርም ጊዜ ሽርክ የሚፈጽሙ መሆናቸው ነው። ይህንንም ከእነርሱ ጋር ተቀላቅሎ ሁኔታቸውን ያጤነና፤ በግብፅ የሑሰይን እና የበደዊይ እና በሌሎችም ቀብር ላይ፣ በኤደን የዓይደሩስ ቀብር ላይ፣ በየመን የሃዲይ ቀብር ላይ፣ በሻም የኢብኑ ዓረቢይ ቀብር ላይ፣ በዒራቅ የሸይኽ ዐብዱልቀድር ጀይላኒይ ቀብር ላይ፣ እንዲሁም ከነዚህም ውጭ በብዙሃኑ ድንበር ያለፉባቸውና በርካታ የላቀውን አላህ ሐቅ አሳልፈው የሰጡባቸውን ታዋቂ ቀብሮች ዘንድ የሚያደርጉትን የተመለከተ ሰው ሁሉ ያውቀዋል። በዛ ላይ ድርጊታቸውን እያወገዘ አላህ ነብዩ ሙሐመድን ﷺ ከእርሳቸው በፊት የነበሩት መልዕክተኞችም -የአላህ ሰላትና ሰላም በሁሉም ላይ ይስፈን- የላከበትን ተውሒድ የሚያብራራላቸው ጥቂቱ ብቻ ነው። ኢና ሊላሂ ወኢና ኢለይሂ ራጂዑን።

ትክክለኛውን ዐቂዳ ከሚቃረኑ እምነቶች መካከል የአላህ ስምና ባህሪያትን በተመለከተ ቢድዓ ያመጡ እንደ ጀህሚዮች፣ ሙዕተዚላዎች እና የአላህን ባህሪያት በመካድ፣ ጥራት ለተገባው አላህ የተጠቀሱትን የምሉእነት ባህርያት ውድቅ በማድረግ፣ ጥራት የተገባውን አላህ የባዶነት፣ የግኡዛንና ኢ-አእምሯዊ መገለጫ በሆኑ ባህርያት በመግለፅ ፈለጋቸውን የተከተሉ ሰዎች እምነት ይገኝበታል። እነዚህ ሰዎች ከሚሉት ሁሉ ጥራት የተገባው አምላካችን አላህ ላቀ።

እዚህም ውስጥ ከፊል ባህርያቱን እየካዱ ከፊሉንም የሚያፀድቁት የአሽዓሪያዎች እምነት ይካተትበታል። እነዚህም ባፀደቁት ባህርያት የተነሳ የሸሿቸውንም ሆነ የካዷቸውን፣ ትርጉማቸውንም አጣመው የተረጎሟቸውን ባህርያት እንዲያፀድቁ ይገደዳሉ። በዚህ ድርጊታቸውም መለኮታዊውንም አእምሯዊውንም ማስረጃዎች ተቃርነዋል፤ ግልፅ በሆነ መልኩም እርስበርስ ተጋጭተዋል።

አህል ሱና ወል-ጀማዓዎች ግን አላህ ለራሱ ያፀደቀውን እና መልዕክተኛው ሙሐመድ ﷺ ለአላህ ያፀደቁለትን ስምና ባህሪ በተሟላ መልኩ መገለጫው መሆኑን ያፀድቃሉ፤ ፍጡራኑን ከመምሰልም ሆነ ራሱን የገለፀበትን ባህርይ ውድቅ ከማድረግ በመራቅ ከማይገባው ሁሉ እጅግ ጥርት ባለ መልኩ የጠራ መሆኑን ያምናሉ። በዚህም የተባሉትን ሳያዛቡም ውድቅ ሳያደርጉም አምነው፤ ሌሎቹ ካረፉበት እርስ በርስ መጣረስም ድነው የመጡትን ማስረጃዎች ሁሉ ተግባራዊ ማድረግ ቻሉ። ይህንንም ከላይ አብራርተናል።

የመዳኛው መንገድ፣ የዱኒያም የአኺራም ስኬታማነት፣ የዚህች ኡመት ቀደምት መሪዎችና ኢማሞች የተጓዙበት ቀጥተኛው መንገድ ይኸው ነው። የኋለኞቹ የሚስተካከሉበትም የመጀመሪያቸው በተስተካከሉበት ብቻ ነው። ማለትም ቁርኣንና ሱናን በመከተል ቁርአንና ሐዲሥን የሚቃረነውንም በመተው ነው። ጥራትና ልዕልና የተገባው አላህ ኡማውን ወደ ቀናው ጎዳና እንዲመልሰው፣ ቅን ዳዒዎችን እንዲያበዛ፣ መሪዎቹንና ኡለማዎቹንም ሽርክን እንዲታገሉት፣ እንዲያጠፉትና ከመንገዶቹም እንዲያስጠነቅቁ አላህ እንዲረዳቸው እርሱን እንጠይቀዋለን። እርሱ ሰሚው ቅርብ ነውና። ለመልካም የመገጠም ባለቤቱ አላህ ነው፤ እርሱም በቂያችንና መልካም መመኪያ ነው፤ በእርሱም ቢሆን እንጂ ኃይልም ብልሀትም የለም። የአላህ ሰላትና ሰላም በባሪያውና መልዕክተኛው በነብያችን ሙሐመድ፣ በቤተሰቦቻቸውና በባልደረቦቻቸው ላይ ይስፈን።

 

***

 

am397v4.0 - 21/04/2026


ቡኻሪ በቁጥር (2856) እና ሙስሊም በቁጥር (30) ዘግበውታል።

አል-ላለካኢይ በሸርሕ ኡሱል አል-ኢዕቲቃድ (735) ዘግበውታል፤ ኢብኑ ዐብዱልበርም በጃሚዕ አል-ዒልም ወፈድሊሂ (1801) ዘግበውታል፤ የኢብኑ ዐብዱልበር ዘገባ ግን “አያት አስ-ሲፋት” ከሚለው ይልቅ “አል-አሓዲሥ” በሚል ቃል ነው፤ ቃሉም፡ "እነዚህን ሓዲሦች እንደመጡት ዘግቧቸው፤ በእነርሱም ላይ አትከራከሩባቸው።"

አል-በይሀቂይ በአል-አስማእ ወስ-ሲፋት (865) ዘግበውታል፤ ኢብኑ ተይሚያህ በአል-ሐመዊያህ (269) ሰነዱን ሶሒሕ ብለውታል፤ ዘሀቢም በአል-ዐርድ (2/223) “ዘጋቢዎቹ ታማኝ ኢማሞች ናቸው።” ብለዋል።

አል-ላለካኢ በ "ሸርህ ኡሱል አል-ኢዕቲቃድ" (930)፣ በይሀቂይም በ "አል-አስማእ ወስ-ሲፋት" (955) ዘግበውታል።

አል-ላለካኢይ በ “ሸርሕ ኡሱል አል-ኢዕቲቃድ” (665) ዘግበውታል፤ አል-በይሀቂም በ “አል-አስማእ ወስ-ሲፋት” (868) ዘግበውታል።

አል-ላለካኢ በ"ሸርሕ ኡሱል አል-ኢዕቲቃድ" (664) ላይ ዘግበውታል፤ አቡ ኑዐይም በ"ሒልየቱል አውሊያእ" (325/6) ላይ ዘግበውታል፤ አል-በይሀቂም በ"አል-አስማእ ወስ-ሲፋት" (867) ላይ ዘግበውታል።

አል-ሙዘኪይ በአል-ሙዘኪያት (29)፣ ኢብኑ በጦህ በአል-ኢባናህ (120) እና አል-ላለካኢይ በሸርሕ ኡሱል አል-ኢዕቲቃድ (663) ላይ ዘግበውታል።

ዳሪሚይ በአር-ረድ ዐለል ጀህሚየህ (67) እንዲሁም በይሀቂይ በአል-አስማእ ወስ-ሲፋት (903) ዘግበውታል።

ዘሀቢ በ "አል-ዑሉው" (464) የዘገቡት ሲሆን አልባኒም በ "ሙኽተሶር አል-ዑሉው" (ገጽ: 184) ላይ “ይህ ሰነድ ሶሒሕ ነው፤ ዘጋቢዎቹ ታማኝና የሚታወቁ ናቸው።” ብለዋል።

ተፍሲር ኢብኑ ከሢር (3/426 እና 427)

ቡኻሪይ በቁጥር (22) ከአቢ ሰዒድ አል-ኹድሪይ ረዲየላሁ ዐንሁ ዘግበውታል።

ሙስሊም(2996) ከዓኢሻ አላህ መልካም ስራዋን ይውደድላትና ዘግቦታል።

ቡኻሪይ በቁጥር (3651) እና ሙስሊም በቁጥር (2533) ከዐብደላህ ኢብኑ መስዑድ ረዲየላሁ ዐንሁ ዘግበውታል።

ሙስሊም (1920) ከሠውባን (ረዲየላሁ ዐንሁ) ሐዲስ ዘግበውታል።

ኢብኑ ማጃህ (3952) ከሠውባን ረዲየላሁ ዐንሁ ሐዲስ ዘግበውታል፤ ኢብኑ ሒባንም (6714) ሐኪምም (8653) ሶሒሕ ብለውታል።

ቲርሚዚይ (2641) ከዐብደላህ ኢብኑ ዐምር ረዲየላሁ ዐንሁ ዘግበውታል። ሙናዊይም በ “ፈይዱል ቀዲር” (5/347) ላይ “በሰነዱ ውስጥ ዐብዱራሕማን ኢብኑ ዚያድ አል-ኢፍሪቂ አለ፤ ዘሀቢይ ‘ዶዒፍ ብለውታል’ ብሏል” ብለዋል። አልባኒይም በ “ሶሒሑል ጃሚዕ” (5343) ሶሒሕ ብለውታል።

ሙስሊም በቁጥር (8) ዘግበውታል።