PHPWord

 

 

التَّحْذِيرُ مِنْ بِنَاءِ المَسَاجِدِ

عَلَى القُبُورِ

 

 

መቃብሮች ላይ መስጂዶችን ከመገንባት ማስጠንቀቅ

 

 

 

 

لِسَمَاحَةِ الشَّيْخِ العَلَّامَةِ

عَبْدِ العَزِيزِ بْنِ عَبْدِ اللهِ بْنِ بَازٍ

رَحِمَهُ اللهُ

 

ዝግጅት፦ የተከበሩ ሸይኽ

ዐብዱልዐዚዝ ቢን ዐብደላህ ቢን ባዝ

 

 

 


بِسْمِ اللهِ الرَّحمَنِ الرَّحِيمِ

አስረኛው መልዕክት፦

መቃብሮች ላይ መስጂዶችን ከመገንባት ማስጠንቀቅ

በአላህ ስም፤ ምስጋናም ሁሉ ለአላህ የተገባ ነው። የአላህ ሰላትና ሰላምም በአላህ መልእክተኛ ላይ ይስፈን።

ከዚህ በመቀጠል፡ በራቢጠቱል ኡሉም አል-ኢስላሚያ መጽሔት ሶስተኛ እትም ‹‹የወሩ የሙስሊሞች ዜና›› በሚለው ክፍል ውስጥ፤ በጆርዳን ሃሺማዊት ንጉሳዊ ግዛት የሚገኘው ራቢጠቱል ኡሉም አል-ኢስላሚያ፣ አር-ሩሐይብ በምትባል መንደር በቅርቡ በተገኘው ዋሻ ላይ መስጊድ ለመገንባት ማሰቡን የሚገልጽ ጽሑፍ ተመልክቻለሁ። ይህ ዋሻም በቅዱስ ቁርኣን ውስጥ የተጠቀሱት የዋሻው ሰዎች (አህለል-ከህፍ) ያንቀላፉበት ነው ተብሎ የሚነገርለት ነው፤ አበቃ።

ለአላህና ለባሮቹ ተቆርቋሪ መሆን ግዴታ መሆኑን ከግምት በማስገባት፤ በዚሁ መጽሔት ላይ በሃሺማዊቷ የጆርዳን መንግስት ለሚገኘው የኢስላማዊ ምርምር ማህበር አንድ ቃል ለማቅረብ አሰብኩ፤ ይዘቱም ማህበሩ በተጠቀሰው ዋሻ ላይ መስጂድ ለመገንባት የነበረውን ሀሳብ እንዳይተገብረው መምከር ነው፤ ይህም የሆነበት ምክንያት፣ በነቢያቶችና በሷሊሖች መቃብር እንዲሁም በቅሪቶቻቸው ላይ መስጂዶችን መገንባት ወደ ሺርክ ከሚያደርሱና በነቢያቶችና በሷሊሖች ድንበር ከማለፍ መንገዶች አንዱ ስለሆነ ፍፁም የሆነው ኢስላማዊ ሸሪዓ የከለከለው፣ ያስጠነቀቀበት እንዲሁም ፈፃሚውን የረገመበት በመሆኑ ነው። ተጨባጩ ሸሪዓው ይዞት የመጣው ነገር እውነት ለመሆኑ ምስክር ነው፣ ክብሩ የላቀ ከሆነው ከአላህ ዘንድ ለመሆኑ ማስረጃ ነው፣ እንዲሁም የአላህ መልዕክተኛ ﷺ ከአላህ ዘንድ ይዘውት በመጡትና ለህዝባቸው ባደረሱት ነገር ላይ እውነተኛ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ፍንትው ያለ ማስረጃና የማያዳግም ማረጋገጫም ነው። የሙስሊሙን ዓለም ሁኔታዎችና በውስጡም በዶሪሖች ላይ መስጂዶችን በመገንባት፣ እነርሱንም በማላቅ፣ ለነርሱ ምንጣፍ በማንጠፍና በማስዋብ እንዲሁም አገልጋዮችን በመመደብ ምክንያት የተከሰተውን ሽርክና ድንበር ማለፍ በጥሞና የተመለከተ ማንኛውም ሰው ይህ ድርጊት ወደ ሽርክ ከሚያዳርሱ መንገዶች መካከል መሆኑንና፤ የእስልምና ሸሪዓም ካሉት መልካም ገፅታዎች መካከል ይህንን እንደሚከለክልና ከመገንባቱም እንደሚያስጠነቅቅ በእርግጠኝነት ይገነዘባል።

በዚህ ዙሪያ ከተዘገቡት መካከል ቡኻሪና ሙስሊም (አላህ ይዘንላቸውና) በዘገቡት ሐዲሥ: እናታችን ዓኢሻ (ረዲየሏሁ ዐንሃ) - አላህ መልካም ሥራዋን ይውደድላትና - እንዲህ ብላለች: "የአላህ መልክተኛ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) እንዲህ ብለዋል:"

«لَعَنَ اللَّهُ الْيَهُودَ وَالنَّصَارَى، اتَّخَذُوا قُبُورَ أَنْبِيَائِهِمْ مَسَاجِدَ، قالَتْ عَائِشَةُ: يُحَذِّرُ مَا صَنَعُوا، قالَتْ: وَلَوْلَا ذَلِكَ لَأُبْرِزَ قَبْرُهُ، غَيْرَ أَنَّهُ خُشِيَ أَنْ يُتَّخَذَ مَسْجِدًا».

"«አላህ አይሁድና ክርስቲያኖችን ረገመ፤ የነቢያቶቻቸውን መቃብር መስጂድ አድርገው ያዙ።» ዓኢሻም እንዲህ አለች: "ከሰሩት ሥራ እያስጠነቀቁ ነው። ይህ ባልነበረ ኖሮ ቀብራቸው ይፋ ይሆን ነበር። ነገር ግን መስጂድ ተደርጎ እንዳይያዝ ተፈራ።" እንዲሁም በቡኻሪ እና ሙስሊም እንደተዘገበው «ኡሙ ሰላማ እና ኡሙ ሀቢባ (ረዲየሏሁ ዐንሁማ) - አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላቸውና - በሀበሻ ምድር ስላዩት ቤተ ክርስቲያን እና በውስጡ ስለነበሩት ምስሎች ለአላህ መልዕክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ነገሯቸው። የአላህ መልዕክተኛም (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፦»

«أُولَئِكَ إِذَا مَاتَ فِيهِمُ الرَّجُلُ الصَّالِحُ؛ بَنَوْا عَلَى قَبْرِهِ مَسْجِدًا، وَصَوَّرُوا فِيهِ تِلْكَ الصُّوَرَ، أُولَئِكَ شِرَارُ الْخَلْقِ عِنْدَ اللَّهِ».

«እነዚህ በመካከላቸው ደግ ሰው ሲሞት፤ በቀብሩ ላይ መስጂድ ይገነቡና በውስጡም እነዚያን ስእሎች ይስላሉ፤ እነዚህ አላህ ዘንድ እጅግ ክፉ ፍጡራን ናቸው።»

በሶሒሕ ሙስሊምም ከጁንዱብ ቢን ዐብዲላህ -አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላቸውና- እንደተዘገበው እንዲህ ብሏል: «የአላህ መልዕክተኛን ﷺ ከመሞታቸው አምስት ቀናት በፊት እንዲህ ሲሉ ሰምቻቸዋለሁ፦»

«إِنِّي أَبْرَأُ إِلَى اللَّهِ أَنْ يَكُونَ لِي مِنْكُمْ خَلِيلٌ، فَإِنَّ اللَّهَ قَدِ اتَّخَذَنِي خَلِيلًا، كَمَا اتَّخَذَ إِبْرَاهِيمَ خَلِيلًا، وَلَوْ كُنْتُ مُتَّخِذًا مِنْ أُمَّتِي خَلِيلًا، لَاتَّخَذْتُ أَبَا بَكْرٍ خَلِيلًا، أَلَا وَإِنَّ مَنْ كَانَ قَبْلَكُمْ كَانُوا يَتَّخِذُونَ قُبُورَ أَنْبِيَائِهِمْ وَصَالِحِيهِمْ مَسَاجِدَ، أَلَا فَلَا تَتَّخِذُوا الْقُبُورَ مَسَاجِدَ، فَإِنِّي أَنْهَاكُمْ عَنْ ذَلِكَ».

«እኔ ከናንተ መካከል ፍፁም ወዳጅ ከመያዝ ወደ አላህ እጥራራለሁ። ምክንያቱም አሏህ ኢብራሂምን ፍፁም ወዳጅ አድርጎ እንደያዘው ሁሉ እኔንም ፍፁም ወዳጅ አድርጎ ይዞኛልና። ከኡመቴ መካከል ፍፁም ወዳጅ (ኸሊል) አድርጌ የምይዝ ብሆን ኖሮ አቡበከርን ነበር ፍፁም ወዳጅ አድርጌ የምይዘው። አዋጅ! እነዚያ ከናንተ በፊት የነበሩት የነብያቶቻቸውንና የፃድቃኖቻቸውን መቃብር መስገጃ ስፍራ አድርገው ይይዙ ነበር። አዋጅ! መቃብርን መስገጃ ስፍራ አድርጋችሁ አትያዙ! እኔ እየከለከልኳችሁ ነው።» በዚህ ዙሪያ የመጡ ሐዲሦች በርካታ ናቸው።

በእርግጥም ከአራቱ መዝሀቦችና ከሌሎችም የሆኑ የሙስሊም ሊቃውንት እና ኢማሞች፤ የመልዕክተኛውን ﷺ ሱና በመከተል፣ ለህዝበ ሙስሊሙ በመቆርቆርና ኡመቱ ከእነርሱ በፊት የነበሩት የአይሁዶችና የክርስቲያኖች ድንበር አላፊዎች እንዲሁም ከዚህ ኡመት የጠመሙ አምሳያዎቻቸው በወደቁበት ላይ እንዳይወድቁ ለማስጠንቀቅ፤ በመቃብር ላይ መስጊዶችን መገንባት ክልክል መሆኑን በግልፅ አስቀምጠዋል፤ ከዚህም አስጠንቅቀዋል።

በዮርዳኖስ በሚገኘው የእስልምና እውቀት ማህበር እና በሌሎችም ሙስሊሞች ላይ ግዴታው፤ ሱናን መያዝ፣ የኢማሞችን ፈለግ መከተል እንዲሁም አላህና መልዕክተኛው ካስጠነቀቁት ነገር መጠንቀቅ ነው። በዚህ ውስጥ የባሪያዎች መስተካከል፣ ደስታቸውና በዱንያም ሆነ በአኺራ መዳናቸው ይገኛልና። በዚህ ጉዳይ ላይም አንዳንድ ሰዎች፤ የዋሻው ባለቤቶችን ታሪክ አስመልክቶ አላህ የተናገረውን እንደማስረጃ ተጠቅመዋል ፡

﴿...قَالَ ٱلَّذِينَ غَلَبُواْ عَلَىٰٓ أَمۡرِهِمۡ لَنَتَّخِذَنَّ عَلَيۡهِم مَّسۡجِدٗا﴾

{እነዚያ በነገራቸው ላይ ያሸነፉት ግን «በእነርሱ ላይ በእርግጥ መስጊድን እንሰራለን።» አሉ።} [አልከህፍ:21]

ለዚህም ምላሹ፦ አላህ በዚያ ዘመን የነበሩትን መሪዎችና የሥልጣን ባለቤቶች ይህንን ንግግር ማለታቸውን የጠቀሰው እነርሱን በመውደድና በማጽደቅ ሳይሆን፤ ይልቁንም እነርሱን ለመኮነን፣ ለማነወርና ከድርጊታቸው ለማሸሽ ነው። ለዚህም ማሳያው ይህ አንቀጽ የወረደላቸውና ፍቺውንም ከሰዎች ሁሉ በላይ የሚያውቁት የአላህ መልዕክተኛ ﷺ ህዝባቸውን መቃብርን መስገጃ አድርገው ከመያዝ መከልከላቸው፣ ከዚህም ድርጊት ማስጠንቀቃቸው፣ እንዲሁም ይህን የፈጸመን ሰው መርገማቸውና ማውገዛቸው ነው።

ይህ ነገር የተፈቀደ ቢሆን ኖሮ የአላህ መልእክተኛ ﷺ እንዲህ በብርቱ አያጠብቁም፣ ከዚህም አልፈው ፈጻሚውን አይረግሙም፣ ከፍ ያለውና የተከበረው አላህ ዘንድም ከፍጡራን ሁሉ ክፉ መሆኑን አይናገሩም ነበር። ይህም ለሀቅ ፈላጊ በቂና አሳማኝ ነው። በቀብር ላይ መስጊድ መገንባት ከእኛ በፊት ለነበሩት ህዝቦች የተፈቀደ ነበር ብለን ብንገምት እንኳን፤ በዚህ ተግባር እነርሱን መከተል ለኛ አይፈቀድልንም፤ ምክንያቱም የእኛ ሸሪዓ ከእኛ በፊት የነበሩ ሸሪዓዎችን የሚሽር ነውና። መልክተኛችንም ﷺ የመጨረሻው መልክተኛ ሲሆኑ ሸሪዓቸውም ሙሉና ሁሉን አቀፍ ነው። እርሳቸውም በቀብር ላይ መስጊድ ከመገንባት ከልክለውናል፤ ስለሆነም ትእዛዛቸውን መቃረን አይፈቀድልንም። በኛ ላይ ግዴታ የሚሆነው እርሳቸውን መከተል፣ ይዘውት የመጡትን አጥብቆ መያዝና ይህን የሚቃረኑ የቆዩ ሸሪዓዎችንና በሰሪዎቻቸው ዘንድ ተወዳጅ የነበሩ ልማዶችን መተው ነው። ምክንያቱም ከአላህ ሸሪዓ የበለጠ ሙሉ ሸሪዓ የለምና፤ ከአላህ መልክተኛም (ﷺ) መመሪያ የተሻለ መመሪያ የለም።

አላህ እኛንም ሆነ መላ ሙስሊሞችን በሃይማኖቱ ላይ ፅናትንና የመልዕክተኛውን የሙሐመድን ﷺ ሸሪዓ አጥብቀን መያዝን፤ በንግግራችንም ሆነ በተግባራችን፣ በግልጽም ሆነ በስውር እንዲሁም በሌሎች ጉዳዮቻችን ላይ ሁሉ፣ የላቀውን አላህ እስክንገናኝ ድረስ እንዲገጥመን እንለምነዋለን። እርሱ ሰሚና ቅርብ ነውና።

የአላህ ሰላትና ሰላም ባሪያውና መልክተኛው በሆኑት በሙሐመድ፣ በቤተሰቦቻቸው፣ በባልደረቦቻቸው እና እስከ ቂያማ ቀን ድረስ በቅን መንገዱ በተመሩት ላይ ሁሉ ይስፈን።

 

***

 

am397v4.0 - 21/04/2026