የነቢዩ መስጂድ ትሩፋቶችና ስነ ስርዓት፤ የነቢዩን (ﷺ) ቀብርና የሁለቱ ባልደረቦቻቸውን (ረዲየሏሁ ዐንሁማ) ቀብሮች የመዘየር ህግጋት (አማርኛ)

የነቢዩ መስጂድ ትሩፋቶችና ስነ ስርዓት፤ የነቢዩን (ﷺ) ቀብርና የሁለቱ ባልደረቦቻቸውን (ረዲየሏሁ ዐንሁማ) ቀብሮች የመዘየር ህግጋት

  • earth ቋንቋ
    (አማርኛ)
  • earth ዝግጅት፦:
    اللجنة العلمية برئاسة الشؤون الدينية بالمسجد الحرام والمسجد النبوي
PHPWord

 

 

فَضَائِلُ وَآدَابُ المَسْجِدِ النَّبَوِيِّ

وَأَحْكَامُ زِيَارَةِ قَبْرِ النَّبِيِّ ﷺ

وَقَبْرَي صَاحِبَيْهِ رَضِيَ اللَّهُ عَنْهُمَا

 

የነቢዩ መስጂድ ትሩፋቶችና ስነ ስርዓት፤ የነቢዩን (ﷺ) ቀብርና የሁለቱ ባልደረቦቻቸውን (ረዲየሏሁ ዐንሁማ) ቀብሮች የመዘየር ህግጋት

 

 

اللَّجْنَةُ العِلْمِيَّةُ

بِرِئَاسَةِ الشُّؤُونِ الدِّينِيَّةِ بِالمَسْجِدِ الحَرَامِ وَالمَسْجِدِ النَّبَوِيِّ

 

በመስጂደል ሐረም እና በመስጂድ አን-ነበዊይ በሃይማኖት ዘርፍ የዕውቀት ነክ ጉዳዮች ርዕሰ መስተዳድር ኮሚቴ ያዘጋጀው

 

بِسْمِ اللهِ الرَّحمَنِ الرَّحِيمِ

የነቢዩ መስጂድ ትሩፋቶችና ስነ ስርዓት፤ የነቢዩን (ﷺ) ቀብርና የሁለቱ ባልደረቦቻቸውን (ረዲየሏሁ ዐንሁማ) ቀብሮች የመዘየር ህግጋት

በመስጂደል ሐረም እና በመስጂድ አን-ነበዊይ የሃይማኖት ጉዳዮች ርዕሰ መስተዳድር የሊቃውንት ኮሚቴ

የነቢዩ መስጂድ ትሩፋቶችና ስነ ስርዓት፤ የነቢዩን (ﷺ) ቀብርና የሁለቱ ባልደረቦቻቸውን (ረዲየሏሁ ዐንሁማ) ቀብሮች የመዘየር ህግጋት

ዝግጅት

በመስጂደል ሐረም እና በመስጂድ አን-ነበዊይ የሃይማኖት ጉዳዮች ርዕሰ መስተዳድር የሊቃውንት ኮሚቴ

1447 ዓ·ሂ

መግቢያ

ምስጋና ሁሉ ለዓለማት ጌታ ለሆነው ለአላህ የተገባ ነው። የአላህ ሰላትና ሰላም የዓለማት እዝነት ተደርገው በተላኩት ነቢይ፣ በቤተሰቦቻቸው፣ በባልደረቦቻቸውና እስከ ዕለተ ትንሳኤ የርሳቸውን ሱንና (ፈለግ) በተከተሉ እንዲሁም በመመሪያቸው በተመሩ ላይ ሁሉ ይስፈን። ከዚህ በመቀጠል:

ይህች አጠር ያለች መልዕክት የነቢዩን (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) መስጂድ ወሳኝ የሆኑ ትሩፋቶችን፣ የመዘየር ስነ ስርዓቱን፣ እንዲሁም የነቢዩን (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) እና የሁለቱን ባልደረቦቻቸውን ቀብር የመዘየር ስነ ስርዓትን አካታ የያዘች ናት። ያጠናቀርነውም የነቢዩን (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) መስጂድ ለሚዘይሩ ሰዎች ሲሆን፤ የኡማውን ነቢይ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) መስጂድ ያለውን ደረጃ፣ የመዘየር ስነ ስርዓቱንና በውስጡ የመስገድን ሁኔታ በዕውቀትና በግልፅ መረጃ ላይ ሆነው እንዲያውቁ በማሰብ ነው። ቸርና ለጋስ የሆነው አላህ ጠቃሚ ሊያደርጋት፣ ለርሱ ብቻ የተሰራች በጎ ስራ ያደርግልን ዘንድ ተስፋ እናደርጋለን። እነሆ ቢለምኑት ደጉ፤ ተስፋ ቢያደርጉበት ቸሩ እርሱ ነውና።

የሊቃውንት ኮሚቴ

የመጀመሪያው: የነቢዩ (ﷺ) መስጂድ ትሩፋት

የላቀው አላህ እንዲህ ብሏል፦

﴿وَرَبُّكَ يَخۡلُقُ مَا يَشَآءُ وَيَخۡتَارُۗ مَا كَانَ لَهُمُ ٱلۡخِيَرَةُۚ سُبۡحَٰنَ ٱللَّهِ وَتَعَٰلَىٰ عَمَّا يُشۡرِكُونَ68﴾

{ጌታህም የሚሻውን ይፈጥራል:: ይመርጣልም:: ለእነርሱ ምርጫ የላቸዉም:: አላህ ከማይገባው ሁሉ ጠራ ከሚያጋሯቸዉም ላቀ::} [አል-ቀሶስ፡ 68] በርግጥ አላህ ይህን ስፍራ ለነቢዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) መስጂድ እንዲሆን መርጦታል፤ በበርካታ ትሩፋቶችም ለይቶታል፤ ከእነዚህም ውስጥ፦

ጓዝ ተሸክፎ ጉዞ ከሚደረግባቸው ሶስቱ መስጂዶች አንዱ መሆኑ፦

ከአቡ ሁረይራ እንደተላለፈው፤ ነቢዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) እንዲህ ብለዋል:

«لَا تُشَدُّ الرِّحَالُ إِلَّا إِلَى ثَلَاثَةِ مَسَاجِدَ: مَسْجِدِي هَذَا، وَمَسْجِدِ الحَرَامِ، وَمَسْجِدِ الأَقْصَى».

«ከሶስቱ መስጊዶች በስተቀር ጓዝ ሸክፎ ጉዞ አይወጣም። እነርሱም: ይህ መስጂዴ፣ መስጂደል ሐራም እና መስጂደል አቅሷ ናቸው።»1

በርሱ ውስጥ የሚሰገድ ሶላት ከርሱ ውጪ ከሚሰገድ አንድ ሺህ ሶላት ይበልጣል። መስጂደል ሐራም ሲቀር፡

ከአቡ ሁረይራ -አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና- እንደተላለፈው ነቢዩ ﷺ እንዲህ ብለዋል፡-

«صَلَاةٌ فِي مَسْجِدِي هَذَا خَيْرٌ مِنْ أَلْفِ صَلَاةٍ فِيمَا سِوَاهُ، إِلَّا المَسْجِدَ الحَرَامَ».

«በዚህ መስጂዴ የሚሰገድ ሶላት ከርሱ ውጪ ከሚሰገዱ አንድ ሺህ ሶላቶች የተሻለ ነው። የተከበረው መስጊድ (መስጂደል ሐራም) ሲቀር።»2

ከመጀመሪያ ቀን ይዞ በአላህ ፍራቻ ላይ የተመሠረተው መስጂድ ነው፡

ከአቡ ሰዒድ አልኹድሪይ (ረዲየላሁ ዐንሁ) -አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላቸውና- እንዲህ ብለዋል፡- «የአላህ መልክተኛ ﷺ ዘንድ ከባለቤቶቻቸው በአንዷ ቤት ገባሁና ‹የአላህ መልክተኛ ﷺ ሆይ! ከሁለቱ መስጂዶች በአላህ ፍራቻ ላይ የተመሰረተው የትኛው ነው?› አልኳቸው። እርሳቸውም አንድ እፍኝ ጠጠር ወስደው መሬቱን መቱበት፤ ከዚያም እንዲህ አሉ፡-

«هُوَ مَسْجِدُكُمْ هَذَا» لِمَسْجِدِ المَدِينَةِ.

«ይህ መስጂዳችሁ ነው» የመዲና መስጂድ።3

በውስጡ የዕውቀት ፈላጊ ምንዳው በአላህ መንገድ ላይ እንደታገለ ሙጃሂድ ምንዳ ነው፦

አቡ ሁረይራ ረዲየሏሁ ዐንሁ እንዲህ ብለዋል፦ "የአላህ መልዕክተኛን (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) እንዲህ ሲሉ ሰምቻቸዋለሁ፦"

«مَنْ جَاءَ مَسْجِدِي هَذَا، لَمْ يَأْتِهِ إِلَّا لِخَيْرٍ يَتَعَلَّمُهُ أَوْ يُعَلِّمُهُ، فَهُوَ بِمَنْزِلَةِ المُجَاهِدِ فِي سَبِيلِ اللهِ، وَمَنْ جَاءَ لِغَيْرِ ذَلِكَ، فَهُوَ بِمَنْزِلَةِ الرَّجُلِ يَنْظُرُ إِلَى مَتَاعِ غَيْرِهِ».

«መልካም ነገርን ሊማር ወይም ሊያስተምር እንጂ ለሌላ ነገር ወደዚህ መስጂዴ ያልመጣ ሰው እርሱ በአላህ መንገድ ላይ እንዳለ ታጋይ (ሙጃሂድ) ነው፤ ከዚህ ውጪ የመጣ ሰው ደግሞ እርሱ የሌላን ሰው እቃ እንደሚመለከት ሰው ነው»4

በውስጡ የተከበረችው ረውዷ መኖሯ፦

ከአቡ ሁረይራ -አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና- እንደተላለፈው ነቢዩ ﷺ እንዲህ ብለዋል፡

«مَا بَيْنَ بَيْتِي وَمِنْبَرِي رَوْضَةٌ مِنْ رِيَاضِ الجَنَّةِ، وَمِنْبَرِي عَلَى حَوْضِي».

«በቤቴና በሚንበሬ መካከል ከጀነት ጨፌዎች መካከል የሆነ ጨፌ አለ፤ ሚንበሬም በሐውዴ ላይ ነው።»5

ሁለተኛ፡ የነቢዩን ﷺ መስጂድ መዘየር መወደዱ

ለእነዚህና ለመሰል ትሩፋቶች የነቢዩን ﷺ መስጂድ ለሶላትና ለዒባዳ መዘየር ይወደዳል።

- ለሐጅ አድራጊም ሆነ ለሌላ ሰው ከሐጅ በፊትም ይሁን በኋላ የነቢዩን (የአላህ ሶላትና ሰላም በርሳቸው ላይ ይስፈን) መስጂድ መዘየር ሱና ነው። ይህ መዘየር የሐጅ መስፈርትም፣ ማእዘንም ሆነ ግዴታም አይደለም፤ ከሐጅም ጋር ምንም አይነት ተያያዥነት የለውም።

- የነቢዩን (የአላህ ሶላትና ሰላም በርሳቸው ላይ ይስፈንና) መስጂድ ለመዘየር የተወሰነ የሶላት ብዛት መስገድ ወይም በመዲና ውስጥ ለተወሰነ ጊዜ መቆየት መስፈርት አይደለም። ይልቁንም የግዴታም (ፈርድ) ይሁን የሱና አንዲት ሶላትን በመስገድ ብቻ ጉብኝቱ ይፈጸማል። ነገር ግን በውስጡ የሚሰገዱ የሶላቶች ብዛት በጨመረ ቁጥር ምንዳውም ይጨምራል።

የነቢዩን ﷺ መስጂድ ለዘያሪው በውስጡ ሁሉንም የግዴታ ሶላቶች እንዲሁም የሱና ሶላቶችን መስገዱ ይወደድለታል። ይህም ቀደም ሲል እንደተገለጸው በውስጡ የሚሰገድ ሶላት ከመስጂደል ሐራም ውጪ በሌሎች መስጂዶች ከሚሰገድ ሶላት በአንድ ሺህ ስለሚበልጥ ነው።

ሶስተኛ: የነቢዩን ﷺ መስጂድ የመዘየር ስነ ስርዓት

ሙስሊሙ ወደ ነቢዩ ﷺ መስጂድ ሲመጣ በአጠቃላይ መስጂዶችን፣ በተለይ ደግሞ የነቢዩን ﷺ መስጂድ የሚመለከቱ ሸሪዓዊ ስነ-ስርዓቶችን ሊላበስ ይወደድለታል። እነሱም፡

ወደ መስጂድ በእርጋታና በስክነት፣ በጦሀራ፣ በመልካም ገፅታና በመልካም መዓዛ መምጣት ይገባል፤ ከአቡ ሁረይራ -አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና- እንደተላለፈው የአላህ መልእክተኛ ﷺ እንዲህ አሉ፦

«إِذَا ثُوِّبَ لِلصَّلَاةِ فَلَا تَأْتُوهَا وَأَنْتُمْ تَسْعَوْنَ، وَأْتُوهَا وَعَلَيْكُمُ السَّكِينَةُ، فَمَا أَدْرَكْتُمْ فَصَلُّوا، وَمَا فَاتَكُمْ فَأَتِمُّوا، فَإِنَّ أَحَدَكُمْ إِذَا كَانَ يَعْمِدُ إِلَى الصَّلَاةِ فَهُوَ فِي صَلَاةٍ».

«ለሶላት ጥሪ ሲደረግ እየሮጣችሁ እንዳትመጡ፤ የተረጋጋችሁ ሆናችሁ ኑ። የደረሳችሁበትን ስገዱ፤ ያለፋችሁን ደግሞ አሟሉ። አንዳችሁ ወደ ሶላት ያቀና ጊዜ በሶላት ላይ ነውና።»6 ከአቡ ሰዒድ አልኹድሪይ (ረዲየሏሁ ዐንሁ) - አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላቸውና - እንደተላለፈው ነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) እንዲህ ብለዋል፦

«الغُسْلُ يَوْمَ الجُمُعَةِ وَاجِبٌ عَلَى كُلِّ مُحْتَلِمٍ، وَأَنْ يَسْتَنَّ، وَأَنْ يَمَسَّ طِيبًا إِنْ وَجَدَ».

"ለአቅመ አዳም በደረሰ ሰው ላይ ሁሉ የጁሙዓ ቀን መታጠብ፣ ጥርሱን ሊፍቅና ካገኘም ሽቶ መቀባቱ ግዴታ ነው።"7 ሴትን በተመለከተ ደግሞ ወደ መስጂድ ስትመጣ በሒጃቧ ተከናንባ መሆን ግዴታ ይሆንባታል። ሽቶ መቀባትም አይፈቀድላትም፤ ነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በርሳቸው ላይ ይስፈንና) እንዲህ ብለዋልና፦

«إِذَا شَهِدَتْ إِحْدَاكُنَّ المَسْجِدَ فَلَا تَمَسَّ طِيبًا».

«ከእናንተ (ከሴቶች) መካከል አንዳችሁ ወደ መስጂድ ከሄደች፤ ሽቶን አትንካ (አትቀባ)።»8

ወደ ነቢዩ ﷺ መስጂድ ሲገቡ ቀኝ እግርን ማስቀደም፤ መስጂድ ሲገባ የሚባለውን ዱዓም ማድረግ። ዘያሪው እንደሌሎች መስጂዶች ሁሉ ወደ ነቢዩ ﷺ መስጂድ ሲገባ ቀኝ እግሩን ማስቀደሙ ይወደድለታል፤ ይህንንም ዱዓ ይላል፦

«بِسْمِ اللَّهِ، وَالسَّلَامُ عَلَى رَسُولِ اللَّهِ، اللَّهُمَّ اغْفِرْ لِي ذُنُوبِي وَافْتَحْ لِي أَبْوَابَ رَحْمَتِكَ».

"ቢስሚላህ፣ ወስሰላሙ ዐላ ረሱሊልላህ፣ አልላሁምመ-ግፊርሊ ዙኑቢ ወፍተሕሊ አብዋበ ረሕመቲክ"9 ትርጉሙም፦ ‹‹በአላህ ስም፤ ሰላምም በአላህ መልዕክተኛ ላይ ይሁን፤ አላህ ሆይ! ወንጀሎቼን ማረኝ፤ የእዝነት ደጆችህንም ክፈትልኝ።››" እንዲህም ይላል፦

«أَعُوذُ بِاللَّهِ العَظِيمِ، وَبِوَجْهِهِ الكَرِيمِ، وَسُلْطَانِهِ القَدِيمِ، مِنَ الشَّيْطَانِ الرَّجِيمِ».

«አዑዙ ቢላሂል-ዐዚም፣ ወቢወጅሂሂል-ከሪም፣ ወሱልጧኒሂል-ቀዲም፣ ሚነሽ-ሸይጧኒ-ር-ረጂም።» ትርጉሙም፦ "በታላቁ አላህ፣ በክቡር ፊቱም እንዲሁም ከጥንት በነበረው ስልጣኑም ከተረገመው ሰይጣን እጠበቃለሁ።"10

ተሒየተል መስጂድን (መስጂድ ሲገባ የሚሰገድ ሰላትን) መስገድ፡ በመስጂደ ነበዊ ለመስገድ የገባ ሰው ከመቀመጡ በፊት የተሒየተል መስጂድ ሁለት ረከዓ መስገዱ ሱና ነው። ከአቢ ቀታዳህ አል-ሓሪሥ ኢብን ሪብዒይ አል-አንሷሪይ እንደተዘገበው ነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) እንዲህ አሉ፡-

«إِذَا دَخَلَ أَحَدُكُمُ المَسْجِدَ، فَلَا يَجْلِسْ حَتَّى يُصَلِّيَ رَكْعَتَيْنِ».

"አንዳችሁ መስጂድ የገባ ጊዜ ሁለት ረከዓ ከመስገዱ በፊት እንዳይቀመጥ።11"

በመጀመሪያዎቹ ሰልፎች ላይ ሶላት ለመስገድ መጓጓት ይገባል፤ ይህም በውስጣቸው ትልቅ ደረጃ ስላለው ነው። ይህንንም ማግኘት የሚቻለው ወደ ሶላት ቀድሞ በመሄድ ነው። ከአቡ ሁረይራ ረዲየላሁ ዐንሁ እንደተዘገበው: የአላህ መልእክተኛ ﷺ እንዲህ ብለዋል፦

«لَوْ يَعْلَمُ النَّاسُ مَا فِي النِّدَاءِ وَالصَّفِّ الأَوَّلِ، ثُمَّ لَمْ يَجِدُوا إِلَّا أَنْ يَسْتَهِمُوا عَلَيْهِ لَاسْتَهَمُوا».

«ሰዎች በአዛንና በመጀመሪያ ሰልፍ ያለውን ምንዳ ቢያውቁና እርሱንም እጣ ካልተጣጣሉ በቀር የማያገኙት ቢሆኑ ኖሮ እጣ ይጣጣሉበት ነበር።»12 ነቢዩ ﷺ ለሶሐቦቻቸው (አላህ ስራቸውን ይውደድላቸውና) እንዲህም ብለዋል:

«تَقَدَّمُوا فَأْتَمُّوا بِي، وَلْيَأْتَمَّ بِكُمْ مَنْ بَعْدَكُمْ، لَا يَزَالُ قَوْمٌ يَتَأَخَّرُونَ حَتَّى يُؤَخِّرَهُمُ اللهُ».

«ቅደሙና በእኔ ተከተሉ፤ ከእናንተ በኋላ ያሉትም በእናንተ ይከተሉ። ሰዎች ወደ ኋላ ከመቅረት አይወገዱም በመጨረሻም አላህ ወደ ኋላ የሚያስቀራቸው ቢሆን እንጂ።»13

ሴቶችን በተመለከተ ደግሞ ምርጡ በኋለኞቹ ሰልፎች መስገድና ከወንዶች መራቅ ነው፤ ይህም አቡ ሁረይራ (ረዲየሏሁ ዐንሁ) - አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላቸውና - ባስተላለፉት ሐዲሥ የተነሳ ሲሆን እርሳቸውም የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ ብለዋል፦

«خَيْرُ صُفُوفِ الرِّجَالِ أَوَّلُهَا، وَشَرُّهَا آخِرُهَا، وَخَيْرُ صُفُوفِ النِّسَاءِ آخِرُهَا، وَشَرُّهَا أَوَّلُهَا».

«ለወንዶች ምርጡ የሶላት ሰልፍ የመጀመሪያው ሰልፍ ነው። መጥፎው ደግሞ የመጨረሻው ነው። ለሴቶች ምርጡ ሰልፍ የመጨረሻው ሰልፍ ነው። መጥፎው ደግሞ የመጀመሪያው ነው።»14 ነገር ግን ለብቻቸው ከሰገዱ፣ ወይም ልክ በመስጂደ ነበዊይ እንዳለው በነርሱና በወንዶች መካከል መከለያ ካለ፣ የነርሱ ምርጡ ሰልፍ የመጀመሪያው ነው የሚሆነው። ይህም የተከለከሉበት ምክንያት ስለሚወገድ ነው።

ከኢማሙ ኋላ መስገድ፤ እርሱን ከመቅደምም መጠንቀቅ። ይህም አቡ ሁረይራ ረዲየላሁ ዐንሁ ባስተላለፉት ሀዲስ ነቢዩ ﷺ እንዲህ ስላሉ ነው፡-

«إِنَّمَا جُعِلَ الإِمَامُ لِيُؤْتَمَّ بِهِ».

«ኢማም የተደረገው እንዲከተሉት ብቻ ነው።»15

መስጂዱ በሰጋጆች በመሙላቱ እና መስገጃ ቦታ ከኢማሙ ፊት ለፊት ብቻ በሚገኝበት አስገዳጅ ሁኔታ ካልሆነ በቀር ለሰጋጅ ከኢማሙ መቀደም አይፈቀድለትም።

በሰልፎች መካከል ያሉትን ክፍት ቦታዎች በመሙላትና በማስተካከል ላይ መጣር፤ ነገር ግን ሰዎችን ከመገፋፋትና ከማጨናነቅ፣ ጀርባቸው ላይ ከመረማመድና በሰጋጆች ፊት ከማለፍ መጠንቀቅ ይገባል፤ ይህ ለወንጀል ይዳርጋልና።

በተከበረችው ረውዷ ውስጥ ለተገራለት ሰው መስገድ ይወደዳል፤ ይህም ከአቡ ሁረይራ (አላህ መልካም ስራውን ይውደድለትና) በተላለፈው ሐዲስ ላይ ነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በርሳቸው ላይ ይስፈንና) እንዲህ ስላሉ ነው፦

«مَا بَيْنَ بَيْتِي وَمِنْبَرِي رَوْضَةٌ مِنْ رِيَاضِ الجَنَّةِ، وَمِنْبَرِي عَلَى حَوْضِي».

«በቤቴና በሚንበሬ መካከል ከጀነት ጨፌዎች መካከል የሆነ ጨፌ አለ። ሚንበሬም በሐውዴ ላይ ነው።»16

በረውዷ ውስጥ ስለሚሰገድ ሶላት የተለየ ትሩፋት አልመጣም፤ ነገር ግን ቀደም ሲል ያለፈው የአቢ ሁረይራ (አላህ ስራቸውን ይውደድላቸውና) ሐዲስ እንዳመለከተው እርሷ ከጀነት (ጨፌዎች) መናፈሻዎች አንዷ መናፈሻ መሆኗ ተረጋግጧል፤ ዒባዳዎችም በጊዜያቸውና በቦታቸው ትሩፋት ይበልጣሉ።

* ዘያሪው ረውዷ ውስጥ ለመስገድ ተስማሚ ጊዜዎችን መምረጥና መጨናነቅ የሚቀንስባቸውን ጊዜያት መፈለግ ይገባዋል። ሙስሊም ወንድሞችን ማጨናነቅ፣ በሰዎች አንገት ላይ መረማመድ፣ እንዲሁም በውስጧ ለመስገድ በሰጋጆች ፊት ለፊት ማለፍ አይፈቀድም። ረውዷ ውስጥ መስገድ የሱና ሶላት ነውና በተከለከለ መንገድ ሊደረስበት አይገባም። እንዲሁም ዘያሪው ወደ ረውዷ ለመግባት የተቀመጡትን ልዩ ስርዓቶችና ደንቦች አክብሮ ለመገዛት፣ ተስማሚ ጊዜዎችን ለመምረጥና የዘያሪዎችን አገባብ ከሚያደራጁት ጋር ለመተባበር ጥረት ማድረግ ይገባዋል።

ወደ ፈጣሪው (አላህ) በሚያቃርቡ እንደ ሶላት፣ ቁርአን መቅራት፣ ዚክር፣ ዱዓ፣ የዚክር መድረኮች ላይ መገኘት፣ የዕውቀት ትምህርቶች፣ የተከበረውን ቁርአን የማስተማሪያ ክበባት እና ሌሎችም ያሉ በጎ ስራዎችን በማብዛት ጊዜን በአግባቡ መጠቀም ይገባል።

የአላህን መጽሐፍ ማክበር፤ እንዲሁም ወረቀቶቹን በከንቱ ከመነካካት፣ በላዩ ላይ ከመፃፍ፣ ወይም ጫማን ከጎኑ በማስቀመጥ፣ መሬት ላይ በማስቀመጥና በመሳሰሉት ነገሮች ከማዋረድና ከማቃለል መጠበቅ። የላቀው አላህ እንዲህ ብሏልና፦

﴿ذَٰلِكَۖ وَمَن يُعَظِّمۡ شَعَٰٓئِرَ ٱللَّهِ فَإِنَّهَا مِن تَقۡوَى ٱلۡقُلُوبِ32﴾

{(ነገሩ) ይህ ነው። የአላህን ሃይማኖታዊ ምልክቶች የሚያከብር ሁሉ ይህ ድርጊቱ አላህን ከሚፈሩ ልቦች የሚፈጸም ጥንቃቄ ነው።} [አል-ሐጅ : 32]

አሸናፊና የላቀው አላህ ክልክል ካደረገው ነገር እይታን ዝቅ ማድረግ፡ የነቢዩን ﷺ መስጂድ በሚጎበኝ ሰው ላይ እይታውን ወደ እርሱ ማየት ከተከለከለው ነገር ዝቅ ማድረግ ግዴታ ይሆንበታል። በእነዚህ ስፍራዎች ወንጀል የመፈፀምን ከባድነትና የሚያስከትለውንም ቅጣት ሊያውቅ ይገባል። ምክንያቱም ወንጀሎች በጊዜና በቦታው ክቡርነት ምክንያት ይበልጥ ይገዝፋሉ፤ መልካም ስራዎችም እንደዚሁ ናቸው። ሙስሊሟ ሴትም ሸሪዓዊ ሒጃብን አጥብቃ ልትይዝና ወንዶችን እንዳትፈትን ጌጧን ከመግለጽ ልትቆጠብ ይገባል። የዚህ ሀጢያቱ የገዘፈ ነውና።

በስልክ ፎቶ በመቅረፅ ወይም ምስሎችንና ተንቀሳቃሽ ምስሎችን በመመልከት ከመጠመድ መጠንቀቅ ያስፈልጋል፤ እነዚህ ምስሎችና ተንቀሳቃሽ ምስሎች ክልክል ከሆኑ ደግሞ ጉዳዩ ይበልጥ አደገኛ ይሆናል።

የነቢዩን ﷺ መስጂድ ከጭቅጭቅ፣ ድምፅን ከፍ ከማድረግ፣ የጠፋን ነገር ከማስተዋወቅ፣ ከመሸጥና መሰል በእርሱም ሆነ በሌሎች መስጂዶች ውስጥ ሊፈጸሙ ከማይገባቸው ነገሮች ሁሉ መጠበቅ ይገባል። ለዚህም የአቡ ሁረይራ -ረዲየላሁ ዐንሁ- ሐዲሥ ማስረጃ ነው፤ ነቢዩ -የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና- እንዲህ ብለዋል፦

«إِذَا رَأَيْتُمْ مَنْ يَبِيعُ أَوْ يَبْتَاعُ فِي المَسْجِدِ، فَقُولُوا: لَا أَرْبَحَ اللَّهُ تِجَارَتَكَ، وَإِذَا رَأَيْتُمْ مَنْ يَنْشُدُ فِيهِ ضَالَّةً، فَقُولُوا: لَا رَدَّ الله عَلَيْكَ».

«በመስጂድ ውስጥ የሚሸጥ ወይም የሚገዛን ሰው ካያችሁ፣ “አላህ ንግድህን ትርፋማ አያድርገው” በሉት፤ በውስጡም የጠፋ ነገር የሚያሳውጅን ሰው ካያችሁ፣ “አላህ አይመልስልህ” በሉት።»17

በግል ንፅህና ላይ መጣር፣ እንዲሁም እንደ ነጭ ሽንኩርት፣ ቀይ ሽንኩርት፣ ጢስና ላብ የመሳሰሉ ሰጋጅ ወንድሞቹን አዛ ከሚያደርጉ መጥፎ ሽታዎች መጠንቀቅ፤ ጀቢር ኢብኑ ዐብዲላህ (ረዲየላሁ ዐንሁ) የአላህ መልእክተኛ ﷺ እንዲህ ማለታቸውን አስተላልፈዋል፦

«مَنْ أَكَلَ ثُومًا أَوْ بَصَلًا، فَلْيَعْتَزِلْنَا - أَوْ قَالَ: فَلْيَعْتَزِلْ مَسْجِدَنَا - وَلْيَقْعُدْ فِي بَيْتِهِ».

"ነጭ ሽንኩርት ወይም ቀይ ሽንኩርት የበላ ሰው ከኛ ገለል ይበል ወይም ከመስጂዳችን ገለል ይበል። ቤቱም ይቀመጥ።"18

የመስጂደ-ነበዊን ንጽህና ለመጠበቅ መጣር፤ እንደ የምግብ ትራፊና የኢፍጣር ሱፍራ ያሉ ቆሻሻዎችን -በተለይም በረመዷን ወር- መስጂድ ውስጥና በግቢዎቹ አለመጣል፤ ወይም በመተላለፊያዎችና በግቢዎች ላይ ምራቅ አለመትፋት እና የመሳሰሉት።

በመተላለፊያዎች፣ በበር መግቢያዎችና በተጨናነቁ ስፍራዎች ከመስገድ መቆጠብ ይገባል። ይህም የሚያስከትላቸው ጥፋቶች ስላሉ፣ መንገዶችን መዝጋትና ሙስሊሞችን ማስቸገር ስለሆነ ነው።

ወንዶችና ሴቶች በነብዩ ﷺ መስጂድ ውስጥም ሆነ በግቢዎቹ ውስጥ የሚሰግዱት እያንዳንዳቸው በተመደበላቸው ቦታ ነው። ወንድ ከሴት ጎን አይሰግድም፤ ሴትም ከወንድ ጎን አትሰግድም። በተቻለ መጠን ኢማሙን ከመቅደምም መጠንቀቅ ይገባል።

ከመስጂድ ሲወጣ ግራ እግርን ማስቀደም፤ ሲወጣም እንዲህ ይላል፦

«اللهُمَّ إِنِّي أَسْأَلُكَ مِنْ فَضْلِكَ».

«አልላሁምመ ኢንኒ አስአሉከ ሚን ፈድሊክ»19፣ (ትርጉሙም፡ «አላህ ሆይ! ከችሮታህ እንድትለግሰኝ እማፀንሀለሁ።») ወይም በነቢዩ ﷺ ላይ ሰለዋት ያወርድና እንዲህ ይላል፦

«رَبِّ اغْفِرْ لِي ذُنُوبِي، وَافْتَحْ لِي أَبْوَابَ فَضْلِكَ».

«ረብቢግፊርሊ ዙኑቢ፣ ወፍተሕሊ አብዋበ ፈድሊክ»20 ትርጉሙም: ‹‹ጌታዬ ወንጀሎቼን ማረኝ፤ የችሮታህንም ደጆች ክፈትልኝ፡፡››

አራተኛ: የነቢዩን ﷺ ቀብርና የሁለቱ ባልደረቦቻቸውንም (አላህ ስራቸውን ይውደድላቸውና) ቀብሮች የመዘየር ህግጋትና ስነስርዓት:

* የነቢዩን ﷺ ቀብርና የሁለቱን ባልደረቦቻቸውን የአቡበክርን እና የዑመርን - ረዲየሏሁ ዐንሁማ - ቀብሮች መዘየር ለመዲና ሰዎችና ወደርሷ ለሚመጡ እንግዶችና ጎብኚዎችም ይወደዳል። ይህም ቀብሮችን መዘየር የተደነገገ መሆኑን ከሚያመለክቱት አጠቃላይ ማስረጃዎች የሚመነጭ ነው፤ ከነዚህም መካከል የርሳቸው ﷺ ንግግር ነው፡

«نَهَيْتُكُمْ عَنْ زِيَارَةِ القُبُورِ، فَزُورُوهَا».

«መቃብሮችን ከመዘየር ከልክያችሁ ነበር፤ መቃብርን ዘይሩ።»21

ነቢዩም የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና ከሞቱ በኋላ በእርሳቸው ላይ ሰላምታን የማውረድን ትሩፋት በተመለከተ እንዲህ ብለዋል፦

«مَا مِنْ أَحَدٍ يُسَلِّمُ عَلَيَّ، إِلَّا رَدَّ اللهُ عَزَّ وَجَلَّ إِلَيَّ رُوحِي حَتَّى أَرُدَّ عَلَيْهِ السَّلَامَ».

«አንድም በኔ ላይ ሰላምታን የሚያቀርብ የለም ለርሱ ሰላምታን እስክመልስ ድረስ ኃያሉና የላቀው አላህ ወደኔ ነፍሴን የሚመልስልኝ ቢሆን እንጂ።»22

* ሴቶች የነቢዩን ﷺ ቀብርም ሆነ የሌሎች ሙስሊሞችን ቀብር መዘየር አይፈቀድላቸውም፤ ቀብርን መዘየር ለወንዶች የተደነገገ ሲሆን ሴቶች ግን ቀብርን ከመዘየር ተከልክለዋል። ከኢብኑ ዐባስ ረዲየላሁ ዐንሁማ እንደተዘገበው እንዲህ ብለዋል፦

«لَعَنَ رَسُولُ اللَّهِ ﷺ زَائِرَاتِ القُبُورِ، وَالمُتَّخِذِينَ عَلَيْهَا المَسَاجِدَ وَالسُّرُجَ».

«የአላህ መልዕክተኛ ﷺ ቀብርን አዘውትረው የሚጎበኙ ሴቶችንና በመቃብር ላይ መስገጃዎችንና መብራቶችን የሚይዙትን ረግመዋል።»23 ከአቡ ሁረይራ -አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና- እንደተዘገበው እንዲህ አሉ:

«أَنَّ رَسُولَ اللَّهِ ﷺ لَعَنَ زَوَّارَاتِ القُبُورِ».

"የአላህ መልክተኛ ﷺ ቀብርን አዘውትረው የሚጎበኙ ሴቶችን ረግመዋል"24

* የነቢዩን (የአላህ ሶላትና ሰላም በርሳቸው ላይ ይስፈንና) ቀብር ብቻ ለመዘየር አስቦ ጓዝን ሸክፎ መውጣት አይፈቀድም። ይልቁንም በጉዞው ሊያስብ የሚገባው መስጂዱን ለመዘየርና በውስጡ ለመስገድ ነው። መዲና ከደረሰ በኋላ ግን ለመዲና ነዋሪዎች እንደተደነገገው ሁሉ ቀብሩን መዘየር ይደነገግለታል። ነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በርሳቸው ላይ ይስፈንና) እንዲህ ብለዋል፡

«لَا تُشَدُّ الرِّحَالُ إِلَّا إِلَى ثَلَاثَةِ مَسَاجِدَ: مَسْجِدِي هَذَا، وَمَسْجِدِ الحَرَامِ، وَمَسْجِدِ الأَقْصَى».

«ከሶስቱ መስጊዶች በስተቀር ጓዝ ሸክፎ ጉዞ አይወጣም። እነርሱም: ይህ መስጂዴ፣ መስጂደል ሐራም እና መስጂደል አቅሷ ናቸው።»25

የነቢዩን ﷺ ቀብርና የሁለቱን ባልደረቦቻቸውን - ረዲየሏሁ ዐንሁማ - ቀብሮች ሲዘየር የተደነገጉ ስርዓቶች

ጎብኝው በነቢዩ ﷺ ቀብር ፊት ለፊት ይቆማል። ከዚያም በስርዓትና ድምፁን ዝቅ በማድረግ በነቢዩ ﷺ ላይ ሰላምታን ያቀርባል። እንዲህም ይላል፡ (አስሰላሙ ዐለይከ ያ ረሱለላህ ወረሕመቱላሂ ወበረካቱህ)። በዚህ ላይም ጨምሮ (አሽሃዱ አንነከ ቀድ በለግተር-ሪሳላህ፣ ወአደይተል-አማናህ፣ ወነሰሕተል-ኡመተ፣ ወጃሃድተ ፊላሂ ሐቀል-ጂሃድ) ቢልም ችግር የለውም፤ ምክንያቱም ይህ ሁሉ እውነት ነውና።

ቀጥሎ ወደ ቀኝ በኩል አንድ እርምጃ በመራመድ የአቡበከር አስሲዲቅ (አላህ መልካም ስራውን ይውደድለትና) ቀብር ፊት ለፊት ይቁምና እንዲህ ይበል: «አስሰላሙ ዐለይከ ያ አባ በክሪን ሲዲቅ፣ አስሰላሙ ዐለይከ ያ ኸሊፈተ ረሱሊላሂ ﷺ ረዲየሏሁ ዐንከ ወአርዷክ፣ ወጀዛከ ዐን ኡመቲ ሙሐመዲን ﷺ ኸይራ» (ትርጉሙም "አንተ አቡበከር አስሲዲቅ ሆይ ሰላም ባንተ ላይ ይስፈን፣ አንተ የአላህ መልክተኛ ﷺ ምትክ ሆይ ሰላም ባንተ ላይ ይስፈን፣ አላህ ከአንተ ስራህን ይውደድ አንተንም ያስደስትህ፣ ለሙሐመድ ኡመት ﷺ ለዋልከው ውለታም በመልካም ይመንዳህ።" ማለት ነው።)

ቀጥሎ የዑመር ኢብኑል ኸጧብን (አላህ መልካም ስራውን ይውደድለትና) ቀብር ፊት ለፊት ለመሆን አንድ እርምጃ ወደ ቀኙ ይራመድና እንዲህም ይበል፡ "(አስሰላሙ ዓለይከ ያ ዑመር አልፋሩቅ ረዲየሏሁ ዓንከ ወአርዷክ፣ ወጀዛከ ዓን ኡመቲ ሙሐመዲን ﷺ ኸይራ)።" (ትርጉሙም፡ "አንተ አል ፋሩቅ የሆንከው ዑመር ሆይ! ሰላም ባንተ ላይ ይስፈን፣ አላህ ከአንተ ስራህን ይውደድ አንተንም ይውደድህ፣ ለሙሐመድ ﷺ ኡመት ለዋልከው ውለታ በመልካም ይመንዳህ።" ማለት ነው።)

ኢብኑ ዑመር - አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና - ከጉዞ ሲመለስ ወደ ነብዩ ﷺ ቀብር ይመጣና እንዲህ ይል ነበር፦ “አስ-ሰላሙ ዐለይከ ያ ረሱለልላህ፣ አስ-ሰላሙ ዐለይከ ያ አባ በክር፣ አስ-ሰላሙ ዐለይከ ያ አበታህ።”26 ትርጉሙም “የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! የአላህ ሰላም በእርሶ ላይ ይስፈን፤ አቡበክር ሆይ! የአላህ ሰላም በእርሶ ላይ ይስፈን፤ አባቴ ሆይ! የአላህ ሰላም በእርሶ ላይ ይስፈን።” ካለ በኋላ ይመለሳል ማለት ነው።

የመቃብሩን ግድግዳዎችና አጥር አይነካም፤ አይስማቸውምም፡

ኢማሙ ማሊክ አላህ ይዘንላቸውና እንዲህ ብለዋል፡ በነቢዩ ﷺ ላይ ሰላምታ ሲያቀርብ ፊቱን ወደ ቂብላ ሳይሆን ወደ ቀብሩ አዙሮ ይቁም፤ ይጠጋና ሰላምታ ያቅርብ፤ ቀብሩንም በእጁ አይንካ።27

አኢማዎች የነቢዩን ﷺ ቀብር በእጅ መንካትም ሆነ መሳም እንደማይፈቀድ ተስማምተዋል።

መቃብር ዘንድ ቆይታውን አያራዝምም፤ ይልቁንም ሰላምታ ያቀርባል ከዚያም ይሄዳል።

ኢማም ማሊክ አላህ ይዘንላቸውና እንዲህ ብለዋል: “በነቢዩ ﷺ ቀብር ዘንድ ቆሞ ዱዓ ማድረግን አልቀበልም፤ ይልቁንስ ሰላምታ ያቅርብና ይሂድ።”28

ናፊዕም አላህ ይዘንላቸውና እንዲህ ብለዋል፦ "ኢብኑ ዑመር በቀብሩ ላይ ሰላምታ ያቀርብ ነበር... መቶ ጊዜና ከዚያም በላይ አይቼዋለሁ፤ ወደ ቀብሩ መጥቶ እንዲህ ይል ነበር፦ ‹‹አስ-ሰላሙ ዐላ አን-ነቢይ ﷺ። አስ-ሰላሙ ዐላ አቢ በክር፣ አስ-ሰላሙ ዐላ አቢ።›› ከዚያም ይመለስ ነበር።"29

አንዳንድ ዘያሪዎች የሚፈፅሙት የነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በርሳቸው ላይ ይስፈንና) ቀብር ዘንድ ድምፅን ከፍ ማድረግና ረጅም ሰአት እዛ መቆም ይህ የተደነገገውን መቃረን ነው።

ረሱልን (የአላህ ሶላትና ሰላም በርሳቸው ላይ ይስፈንና) ሆነ ከፍጡራን ሌላን አካል ጥቅም እንዲያመጡ ወይም ጉዳትን እንዲከላከሉ፣ ወይም ጉዳይን እንዲፈፅሙ ወይም ከጭንቀት እንዲገላግሉ ወይም የታመመን እንዲፈውሱ ወይም ምልጃን እንዲያማልዱ ወይም ከቅጣት እንዲያድኑና የመሳሰሉትን ዱዓኦች መማፀን አይፈቀድም። ምክንያቱም ከአላህ ውጭ ያለን አካል አላህ ብቻ በሚችለው ነገር ላይ መማፀን ክልክልና ታላቅ ሽርክ ነውና። የላቀው አላህ እንዲህ ብሏል፦

﴿وَقَالَ رَبُّكُمُ ٱدۡعُونِيٓ أَسۡتَجِبۡ لَكُمۡۚ إِنَّ ٱلَّذِينَ يَسۡتَكۡبِرُونَ عَنۡ عِبَادَتِي سَيَدۡخُلُونَ جَهَنَّمَ دَاخِرِينَ60﴾

{ጌታችሁም አለ: «ለምኑኝ እቀበላችኋለሁና። እነዚያ እኔን ከመገዛት የሚኮሩት ተዋራጆች ሆነው ገሀነም በእርግጥ ይገባሉ።»} [ጋፊር፡ 60] ጥራት የተገባው አላህ እንዲህም ብሏል፡

﴿إِنَّ ٱلَّذِينَ تَدۡعُونَ مِن دُونِ ٱللَّهِ عِبَادٌ أَمۡثَالُكُمۡۖ فَٱدۡعُوهُمۡ فَلۡيَسۡتَجِيبُواْ لَكُمۡ إِن كُنتُمۡ صَٰدِقِينَ194﴾

{እነዚያ ከአላህ ሌላ የምትገዟቸው ጣኦቶች ብጤዎቻችሁ የአላህ ባሮች ናቸው:: እውነተኞች ከሆናችሁ እስቲ ጥሯቸውና ለእናንተ ይመልሱላችሁ:: (መመለስ አይችሉም።)} [አል-አዕራፍ፡ 194] የላቀው አላህ እንዲህ ብሏል፦

﴿وَأَنَّ ٱلۡمَسَٰجِدَ لِلَّهِ فَلَا تَدۡعُواْ مَعَ ٱللَّهِ أَحَدٗا18﴾

{እነሆ መስጂዶችም የአላህ ብቻ ናቸው:: በውስጣቸው ከአላህ ጋር አንድንም አትገዙ ማለትን ተወረደልኝ::} [አል_ጂን፡ 18]

ቀብር ዘንድ አሏህ አይለምንም። ዱዓ ማድረግ ከፈለገ ከቀብሩ ያልፍና ወደ ቂብላ በመዞር ዱዓ ያደርጋል። ወደ ቀብሩ በመዞርም ዱዓ አያደርግም።

ኢማሙ ማሊክ አላህ ይዘንላቸውና እንዲህ ብለዋል: "የነቢዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ቀብር ዘንድ ቆሞ ዱዓ ማድረግን አልፈቅድም።"

መስጂድ ሲገቡም ሆነ ሲወጡ ወደ ቀብሩ መመላለስን ማብዛት ለመዲና ነዋሪዎችም ሆነ ከውጪ ለሚመጡ ጎብኚዎች አይፈቀድም። ይህም ቀብሩን ዒድ አድርጎ ከመያዝ እንዳይሆን ስለሚሰጋ ነው።

የአላህ መልዕክተኛ የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን ይህን ከልክለዋል፤ እንዲህም ብለዋል፦

«لَا تَتَّخِذُوا قَبْرِي عِيدًا، وَلَا تَجْعَلُوا بُيُوتَكُمْ قُبُورًا، وَحَيْثُمَا كُنْتُمْ فَصَلُّوا عَلَيَّ، فَإِنَّ صَلَاتَكُمْ تَبْلُغُنِي».

«ቀብሬን የሚጎበኝ የበአል ስፍራ አታድርጉት፤ ቤቶቻችሁንም መቃብር አታድርጉ። የትም ብትሆኑ በኔ ላይ ሶለዋት አውርዱ፤ ሶለዋታችሁ ትደርሰኛለችና።»30

«ቀብሬን ዒድ አታድርጉት» የሚለው ትርጉሙም፦ በተወሰነ ወቅት ወይም ሁኔታ ለይቶ ወደርሱ መመላለስ ነው፤ ለምሳሌ በየቀኑ፣ በየሳምንቱ ወይም በየወሩ እንዲጎበኝ አድርጎ መወሰን፤ ወይም ደግሞ አንድ የተወሰነ ሁኔታ ሲከሰት እንዲጎበኝ ማድረግ ነው። እንዲህም ተብሏል፦ የምትሰባሰቡበት የመሰባሰቢያ ወቅት አታድርጉት።31

ኢማሙ ማሊክ አላህ ይዘንላቸውና እንዲህ ብለዋል፡ "መስጂድ ገብቶ የሚወጣ የመዲና ነዋሪ በቀብሩ ዘንድ መቆም ግዴታ አይሆንበትም፤ ይልቁንም ይህ ለእንግዶች ነው።"32.

አላህ ይዘንላቸውና «ይህ ለእንግዶች ብቻ ነው» ሲሉ፤ ማለት አጠቃላይ ዚያራን እንጂ፣ ሲገቡና ሲወጡ ዚያራን መደገምን አይደለም።

በመቃብሩ ፊት ልክ ሶላት እንደሚሰግድ ሰው አንዱን እጅ በሌላኛው ላይ አድርጎ ከደረቱ ላይ ወይም ከደረቱ ስር በማድረግ መቆም አይገባውም፤ ይህ ለሶላት ብቻ የተለየ የሆነ የመዋደቅና የመተናነስ ሁኔታ ስለሆነ ከአላህ (ሱብሓነሁ ወተዓላ) ውጪ ለማንም አይሆንም።

አንዳንድ ሰዎች እንደሚያደርጉት በነቢዩ (ﷺ) ላይ ሰላምታን ለማቅረብ ከሩቅ ወደ ቀብሩ መዞር አይገባም። ምክንያቱም ይህን ሶሓቦች (ረዲየሏሁ ዓንሁም) እንዲሁም ከአራቱ ኢማሞችና ከሌሎችም የሆኑት የቀደምት ደጋግ አበዎች አይፈፅሙትም ነበርና።

ወደተከበረው ቀብር ከየትኛውም አቅጣጫ በመዞር ዱዓ ማድረግም ሆነ ቁርአን መቅራትና መሰል ነገሮችን መፈፀም፤ ይህ ከዚህ በፊት ከተጠቀሱት ጋር ተመሳሳይ የሆነ አዲስ መጤ ነው። ለሙስሊም በዲኑ ውስጥ አላህ ያልፈቀደውን አዲስ ነገር ሊፈጥር አይፈቀድለትም። ኢማሙ ማሊክ (አላህ ይዘንላቸውና) የዚህን መሰል ስራዎችን አውግዘዋል፤ እንዲህም ብለዋል፦ "የዚህች ኡማ መጨረሻዋን አያቃናም፤ የመጀመሪያዋን ያቃናው ነገር ቢሆን እንጂ።"33.

በነብዩ ﷺ ላይ ሰላምታ ሲያቀርቡ (ቪዲዮ/ፎቶ) በመቅረፅና በቀጥታ ስርጭት አለመጠመድ።

የአላህ ሰላትና ሰላም በነቢያችን ሙሐመድ ላይ እንዲሁም በቤተሰቦቻቸውና በባልደረቦቻቸው ላይ ሁሉ ይስፈን።

 

***

ማውጫ

 

የመጀመሪያው: የነቢዩ () መስጂድ ትሩፋት 3

ሁለተኛ፡ የነቢዩን መስጂድ መዘየር መወደዱ 6

ሶስተኛ: የነቢዩን መስጂድ የመዘየር ስነ ስርዓት 7

አራተኛ: የነቢዩን ቀብርና የሁለቱ ባልደረቦቻቸውንም (አላህ ስራቸውን ይውደድላቸውና) ቀብሮች የመዘየር ህግጋትና ስነስርዓት: 18

***

 

 

am492v1.0 - 24/06/2026


ቡኻሪይ (1190)፤ ሙስሊም (1395)፤ ቃሉ የቡኻሪይ ዘገባ ላይ ያለው ነው።

ሙስሊም በቁጥር (1398) ዘግበውታል።

ኢብኑ ማጃህ በቁጥር (227) ላይ በሶሒሕ ሰነድ ዘግበውታል።

ቡኻሪና ሙስሊም ተስማምተውበታል። ቡኻሪ በቁጥር 1195 ላይ እና ሙስሊም በቁጥር 1390 ላይ ዘግበውታል።

ቡኻሪይ በቁጥር (636) እና ሙስሊም በቁጥር (602) ዘግበውታል።

ቡኻሪና ሙስሊም ተስማምተውበታል። ቡኻሪ ቁጥር፡ (846) ላይ እና ሙስሊም ቁጥር፡ (858) ላይ ዘግበውታል። ሙሕተሊም ማለት ለአቅመ አዳም የደረሰ ማለት ነው።

ሙስሊም በቁጥር (443) ዘግበውታል።

ኢብኑ ማጃህ በቁጥር (771) ላይ ዘግበውታል። ሰነዱም ሶሒሕ ነው።

አቡዳውድ በቁጥር (466) በሶሒሕ ሰነድ ዘግበውታል።

ቡኻሪና ሙስሊም ተስማምተው ዘግበውታል። ቡኻሪ ቁጥር (1171) ላይ እና ሙስሊም ቁጥር (714) ላይ ዘግበውታል።

ቡኻሪና ሙስሊም ተስማምተውበታል። ቡኻሪ በቁጥር (615) እና ሙስሊም በቁጥር (437) ዘግበውታል።

ሙስሊም በቁጥር (438) ዘግበውታል።

ሙስሊም በቁጥር (440) ዘግበውታል።

ቡኻሪይ በቁጥር (722) እና ሙስሊም በቁጥር (417) ዘግበውታል።

ቡኻሪና ሙስሊም ተስማምተውበታል። ቡኻሪ ቁጥር (1195) ላይ እና ሙስሊም ቁጥር (1390) ላይ ዘግበውታል።

ቲርሚዚይ በቁጥር (1321) እና ኢብኑ ኹዘይማ በቁጥር (1305) በሶሒሕ ሰነድ ዘግበውታል።

ቡኻሪይ በቁጥር (7359) እና ሙስሊም በቁጥር (564) ዘግበውታል።

ሙስሊም በቁጥር (713) ዘግበውታል።

ቲርሚዚይ በቁጥር (314) በሶሒሕ ሰነድ ዘግበውታል።

ሙስሊም በቁጥር (977) ዘግበውታል።

ኢማሙ አሕመድ በሙስነዳቸው በቁጥር (10815) ዘግበውታል። ሰነዱም ሐሰን ነው።

አቡ ዳውድ በቁጥር (3236) ላይ ቲርሚዚይም በቁጥር (320) ላይ ነሳኢይም በቁጥር (2043) ዘግበውታል።

ቲርሚዚይ በቁጥር (1056) እና ኢብኑ ማጀህ በቁጥር (1576) የዘገቡት ሲሆን ሰነዱ ሐሰን ነው።

ቡኻሪይ በቁጥር (1189)፤ ሙስሊም በቁጥር (1397)፤ ቃሉ በሙስሊም ዘገባ ላይ ያለው ነው።

አል'በይሃቂይ በ«አስ-ሱነኑ አል-ኩብራ» በቁጥር (10271) ዘግበውታል፤ ሰነዱም ሶሒሕ ነው።

አሽ-ሺፋ ሊል-ቃዲ ዒያድ (2/199)።

አሽ-ሺፋ ሊል-ቃዲ ዒያድ (2/199)

አል-ኣጁሪይ በ«አሽ-ሸሪዐህ» ኪታባቸው (5/2374) ላይ በቁጥር (1853) ዘግበውታል።

ኢማሙ አሕመድ በሙስነዳቸው በቁጥር: (8804) ዘግበውታል፤ ሰነዱም ሐሰን ነው።

የአር‐ራጊብ አል‐አስፈሃኒን “አል‐ሙፍረዳት” (ገፅ: 594) እና የሸውካኒን “ሸርሕ አስ‐ሱዱር ቢተሕሪሚ ረፍዒል ቁቡር” (ገፅ:16) ይመልከቱ።

የአል-ቃዲ ዒያድ አሽ-ሺፋ (2/204)፤ የኢብኑል ሓጅ አል-መድኸል (1/262)

የኢብኑ ባዝን መጅሙዕ ፈታዋ (16/110)።

ቡኻሪይ በቁጥር: (1189) እና ሙስሊም በቁጥር: (1397) ዘግበውታል፤ ቃሉ የሙስሊም ዘገባ ላይ ያለው ነው።