PHPWord

 

 

 

رِسَالَتَانِ مُوجَزَتَانِ فِي الزَّكَاةِ وَالصِّيَامِ

 

ዘካና ፆምን የሚመለከቱ አጠር ያሉ መልዕክቶች

 

سَمَاحَةُ الشَّيْخِ

عَبْدِ الْعَزِيزِ بْنِ عَبْدِ اللَّهِ بْنِ بَازٍ

رَحِمَهُ اللَّهُ

 

የተከበሩ ሸይኽ

ዐብዱልዐዚዝ ቢን ዐብደላህ ቢን ባዝ

ሀያሉ አላህ ይዘንላቸውና

 

بِسْمِ اللهِ الرَّحمَنِ الرَّحِيمِ

ዘካና ፆምን የሚመለከቱ አጠር ያሉ መልዕክቶች

የተከበሩ ሸይኽ

ዐብዱልዐዚዝ ቢን ዐብደላህ ቢን ባዝ

ሀያሉ አላህ ይዘንላቸውና

የመጀመሪያው መልዕክት:

ዘካን የተመለከተ አንገብጋቢ ጥናት:

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው፡

ምስጋና ሁሉ ለብቸኛው አላህ የተገባ ነው። የአላህ ሶላትና ሰላም ከእሳቸው በኋላ ነብይ የሌለ በሆኑት ነብይ፣ በቤተሰቦቻቸውና በባልደረቦቻቸውም ላይ ይስፈን፤ በመቀጠል:

እነዚህን የተወሰኑ መልዕክቶች ለመጻፍ ያነሳሳኝ በርካታ ሙስሊሞች ግዴታ የሆነውን ዘካ ከማውጣት ስለተዘናጉ ለማስታወስና ስለርሱ ለመምከር ነው። በእስልምና የዘካ ጉዳይ የላቀ ከመሆኑም ጋር በርካታ ሙስሊሞች በተደነገገው መልኩ አያወጡትም። በተጨማሪም እስልምና ያለነርሱ የማይስተካከልባቸው ከሆኑት አምስቱ ማዕዘናቱ መካከል አንዱ ዘካ ስለሆነም ነው። ይህም ነቢዩ ሶለሏሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ በማለታቸው ነው:

«بُنِيَ الإِسْلَامُ عَلَى خَمْسٍ: شَهَادَةِ أَنْ لَا إِلَهَ إِلَّا اللَّهُ وَأَنَّ مُحَمَّدًا رَسُولُ اللَّهِ، وَإِقَامِ الصَّلَاةِ، وَإِيتَاءِ الزَّكَاةِ، وَصَوْمِ رَمَضَانَ، وَحَجِّ البَيْتِ».

"እስልምና በአምስት ነገሮች ላይ ተገንብቷል፦ ከአላህ በስተቀር በእውነት የሚመለክ አምላክ አለመኖሩን እና ሙሐመድ የአላህ መልዕክተኛ መሆናቸውን መመስከር፣ ሶላትን ደንብና ሥርዓቱን ጠብቆ መስገድ፣ ዘካ መስጠት፣ የረመዳንን ወር መጾም እና ሐጅ ማድረግ (የአላህን ቤት መጎብኘት) ናቸው።" ሰሒሕ ለመሆኑ ተስማምተውበታል።

ዘካ በሙስሊሞች ላይ ግዴታ መደረጉ ከእስልምና ጉልህ ውበቶች መካከል መሆኑንና እስልምና የተከታዮቹም ጉዳይ እንደሚያሳስበው የሚያሳይ ነው። ይህም (ዘካ) ጥቅመ ብዙ ስለሆነና ድሃ የሆኑ ሙስሊሞች ዘካ ማግኘት ስለሚያስፈልጋቸው ነው።

ከዘካ ጥቅሞች መካከል: ነፍስ መልካም የዋለላትን የመውደድ ባህሪ ስላላት በሀብታምና ድሃ መካከል የውዴታን ትስስር ያፀናል።

ከጥቅሞቹ መካከል: ነፍስን ያፀዳልም ያጠራልም። ነፍስን ከስስታምነትና ስቁንቁንነት ባህሪ ያርቃታል። ይህንን ሃሳብም የተከበረው ቁርአን በዚህ አንቀፅ አንፀባርቆታል:

﴿خُذۡ مِنۡ أَمۡوَٰلِهِمۡ صَدَقَةٗ تُطَهِّرُهُمۡ وَتُزَكِّيهِم بِهَا...

{ከገንዘቦቻቸው ስትሆን እርሷ የምታጠራቸውና የምታፋፋቸው የሆነችን ምፅዋት ያዝ።} [አት ተውባህ፡ 103]

ከጥቅሞቹ መካከል: ሙስሊም የሆነ ሰው ለተቸገሩ የቸርነትን፣ የደግነትና የርህራሄ ባህሪ መላበስን ያለማምዱታል።

ከጥቅሞቹ መካከል: በረከት፣ ጭማሪና ያወጣው ወጪ ከአላህ ምትክ ይዞለት ይመጣል። አላህ እንዲህ ብሏል:

﴿...وَمَا أَنفَقْتُم مِّن شَيْءٍ فَهُوَ يُخْلِفُهُ وَهُوَ خَيْرُ الرَّزِقِينَ

{ከማንኛውም ነገር የምትለግሱትን እርሱ ይተካዋል። እርሱም ከሲሳይ ሰጪዎች ሁሉ በላጭ ነው።} [ሰበእ፡ 39] ነቢዩም (የአላህ ሶላትና ሰላም በርሳቸው ላይ ይስፈንና) ሶሒሕ በሆነ ሐዲሥ አላህ እንዲህ ይላል ብለዋል:

«يَا ابْنَ آدَمَ أَنفِقْ نُنفِقْ عَلَيكَ...».

"የአደም ልጅ ሆይ! ስጥ ላንተ እንሰጥሃለን ...." ከዚህም ውጪ የሆኑ በርካታ ጥቅሞች አሉት።

ዘካ ከማውጣት የሚሰስት ወይም ሲያወጣ የሚያጓድል ሰውን በሚመለከት ከባድ ዛቻ መጥቷል። የላቀው አላህ እንዲህ ብሏል:

﴿وَٱلَّذِينَ يَكۡنِزُونَ ٱلذَّهَبَ وَٱلۡفِضَّةَ وَلَا يُنفِقُونَهَا فِي سَبِيلِ ٱللَّهِ فَبَشِّرۡهُم بِعَذَابٍ أَلِيمٖ 34 يَوۡمَ يُحۡمَىٰ عَلَيۡهَا فِي نَارِ جَهَنَّمَ فَتُكۡوَىٰ بِهَا جِبَاهُهُمۡ وَجُنُوبُهُمۡ وَظُهُورُهُمۡۖ هَٰذَا مَا كَنَزۡتُمۡ لِأَنفُسِكُمۡ فَذُوقُواْ مَا كُنتُمۡ تَكۡنِزُونَ 35

{እነዚያንም ወርቅንና ብርን የሚያደልቡትን በአላህም መንገድ ላይ የማያወጧትን በአሳማሚ ቅጣት አብስራቸው።

በርሷ ላይ በገሀነም እሳት ውስጥ በሚጋልባትና ግንባሮቻቸውም፣ ጎኖቻቸውም፣ ጀርባዎቻቸውም በርሷ በሚተኮሱ ቀን (አሳማሚ በሆነ ቅጣት አብስራቸው)፡፡ ይህ ለነፍሶቻችሁ ያደለባችሁት ነው፡፡ ታደልቡት የነበራችሁትንም ቅመሱ (ይባላሉ)፡፡} [አት ተውባህ፡ 34 - 35] ሶሒሕ ከሆነ ሐዲሥ እንደምንረዳው ዘካው ያልወጣለት ገንዘብ ባጠቃላይ የትንሳኤ ቀን ባለቤቱ የሚቀጣበት ድልብ ነው። ነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በርሳቸው ላይ ይስፈንና) እንዲህ ብለዋል:

«مَا مِنْ صَاحِبِ ذَهَبٍ وَلَا فِضَّةٍ لَا يُؤَدِّي حَقَّهَا إِلَّا إِذَا كَانَ يَوْمُ القِيَامَةِ صُفِّحَتْ لَهُ صَفَائِحُ مِنْ نَارٍ فَأُحْمِيَ عَلَيْهَا فِي نَارِ جَهَنَّمَ فَيُكْوَى بِهَا جَنْبُهُ وَجَبِينُهُ وَظَهْرُهُ، كُلَّمَا بَرَدَتْ أُعِيدَتْ لَهُ فِي يَوْمٍ كَانَ مِقْدَارُهُ خَمْسِينَ أَلْفَ سَنَةٍ حَتَّى يُقْضَى بَيْنَ العِبَادِ فَيَرَى سَبِيلَهُ: إِمَّا إِلَى الجَنَّةِ، وَإِمَّا إِلَى النَّارِ».

"የወርቅና የብር ባለቤት ሆኖ ሐቃቸውን የማይወጣ ሰው የትንሳኤ ቀን ለርሱ የእሳት ዝርግ ተዘርግቶለት በርሷ በጀሃነም እሳት ውስጥ ሳይቃጠል፤ ጎኑም፣ ግንባሩና ጀርባውም ሳይተኮስ አይቀርም።" በቀዘቀዘች ቁጥር እየተመላለሰች መጠኑ ሀምሳ ሺህ አመት የሚያህል ለሆነ ቀን ይተኮሳል። ይህም በባሮች መካከል ፍርድ ተፈርዶ መንገዱ ወደ ጀነት ወይስ ወደ እሳት ነው የሚለውን እስኪመለከት ድረስ የሚዘልቅ ነው።"

ቀጥለውም ነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በርሳቸው ላይ ይስፈንና) የግመል፣ የከብትና የፍየል ባለቤት ሆኖ ዘካውን ስለማያወጣ ሰው ጠቀሱ። እርሱም ቢሆን ዘካውን ባለማውጣቱ የትንሳኤ ቀን እንደሚቀጣ ተናገሩ።

የአላህ መልእክተኛ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) እንዲህ ማለታቸውም በሶሒሕ ሐዲሥ ተዘግቧል፡-

«مَنْ آتَاهُ اللَّهُ مَالًا فَلَمْ يُؤَدِّ زَكَاتَهُ مُثِّلَ لَهُ شُجَاعًا أَقْرَعَ لَهُ زَبِيبَتَانِ يُطَوِّقُهُ يَوْمَ القِيَامَةِ، ثُمَّ يَأْخُذُ بِلَهْزِمَتَيْهِ (يَعْنِي شِدْقَيْهِ)، ثُمَّ يَقُولُ: أَنَا مَالُكَ، أَنَا كَنْزُكَ»، ثُمَّ تَلَا النَّبِيُّ قَوْلَهُ تَعَالَى: ﴿وَلَا يَحْسَبَنَّ الَّذِينَ يَبْخَلُونَ بِمَا ءَاتَاهُمُ اللَّهُ مِن فَضْلِهِ هُوَ خَيْرًا لَّهُمْ بَلْ هُوَ شَرٌّ لَهُم سَيُطَوَّقُونَ مَا بَخِلُوا بِهِ يَوْمَ الْقِيَمَة...

"አላህ ገንዘብ ሰጥቶት ዘካውን ያላወጣ ሰው ገንዘቡ የትንሳኤ ቀን መላጣና ከአይኖቹ በላይ ጥቋቁር ነጠብጣብ ያሉበት ዘንዶ ተመስሎ ይመጣበታል። ቀጥሎ ፊቱን እየቦጨቀ "እኔ ገንዘብህ ነኝ። እኔ ድልብህ ነኝ።" ይለዋል። ቀጥለው ነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በርሳቸው ላይ ይስፈንና) ይህንን አንቀፅ አነበቡ {እነዚያም አላህ ከችሮታው በሰጣቸው ገንዘብ የሚነፍጉ እርሱ ለእነሱ ደግ አይምሰላቸው። ይልቁንም እርሱ ለእነሱ መጥፎ ነው። ያንን በርሱ የነፈጉበትን በትንሳኤ ቀን (እባብ ሆኖ) ይጠለቃሉ።} [አሉ ዒምራን: 180]

ዘካ ግዴታ የሚሆነው ከአራት የንብረት አይነቶች ነው። ከመሬት ከሚወጡ እህሎችና ፍራፍሬዎች፣ የሚሰማሩ ከሆኑት ከሶስቱ የቤት እንስሶች፣ ከወርቅና ከብር፣ ከንግድ ሸቀጥ ነው።

ለነዚህ አራት የገንዘብ አይነቶች ባጠቃላይ የተወሰነላቸው የዘካ መነሻ አላቸው። ከዛ በታች ባለ የገንዘብ መጠን የዘካ ግዴታ አይኖርም። የአዝርእትና ፍራፍሬ የዘካ መነሻ መጠን: አምስት "አውሱቅ" ነው። አንድ "ወሰቅ" በነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በርሳቸው ላይ ይስፈንና) "ሷዕ" (የቁና መለኪያ) ስልሳ "ሷዕ" ነው። ስለዚህ ተምርም፣ ዘቢብም፣ ስንዴም፣ ሩዝም፣ ገብስና የመሳሰሉትም የዘካ መነሻ መጠናቸው በነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በርሳቸው ላይ ይስፈንና) የቁና መለኪያ መሰረት 300 (5*60) ቁና ነው። አንድ "ሷዕ"ም መካከለኛ እጅ ባለው ሰው አራት ሙሉ እፍኝ ነው።

አዝርእቱና የተምር ዛፉ እየጠጡ የበሰሉት ባልተለፋበት ውሃ ማለትም በዝናብ፣ በወንዝ፣ በወራጅ ምንጭና በመሳሰሉት ከሆነ ይህ መጠን የደረሰለት ሰው የማውጣት ግዴታ ያለበት አስራት (አንድ አስረኛውን) ነው።

አዝርእቱ የበሰለው በወጪና በልፋት ከሆነ ለምሳሌ ውሃ በግመል ጭኖ እያመላለሰ፣ ውሃን ከፍ አድርገው የሚያጠጡ በሆኑ ትራክተሮችና በመሳሰሉት ከሆነ ሶሒሕ በሆነ ሐዲሥ ከአላህ መልክተኛ (የአላህ ሶላትና ሰላም በርሳቸው ላይ ይስፈንና) እንደተረጋገጠው ዘካ የማውጣት ግዴታ ያለበት የአስራት ግማሽ (የአንድ አስረኛው ግማሽ ማለትም 1/20) ነው።

የሚሰማሩ የሆኑ ግመሎች፣ ከብቶችና ፍየሎች የዘካ መነሻ መጠናቸው ከአላህ መልክተኛ (የአላህ ሶላትና ሰላም በርሳቸው ላይ ይስፈንና) ሶሒሕ በሆኑ ሐዶሦች በዝርዝር ተገልጿል። ማወቅ የፈለገ ሰው የእውቀት ባለቤቶችን ስለጉዳዩ በመጠየቅ ማወቅ ይችላል። ማሳጠርን ስላሰብን እንጂ አንባቢው የተሟላ ፋይዳ እንዲያገኝ እንጠቅሰው ነበር።

የብር (የሲልቨር) የዘካ መነሻ መጠን መቶ አርባ "ሚሥቃል" ነው። በሳዑዲ ዓረቢያ ዲርሃም ደግሞ ሃምሳ ስድስት ሪያል ነው።

ዝቅተኛው የወርቅ የዘካ መነሻ መጠን ሐያ "ሚሥቃል" ነው። በሳዑዲ የወርቅ ሳንቲም ደግሞ አስራ አንድ የወርቅ ሳንቲም ከአንድ የወርቅ ሳንቲም ሶስት ሰባተኛ ነው። በግራም ደግሞ ዘጠና ሁለት ግራም ነው። ከወርቅም ይሁን ከብር ይህንን መጠን ከደረሰና ሳይቀነስ አመት ዞሮ ከመጣ ማውጣት ግዴታ የሚሆንብን መጠን የአስራት ሩብ (1/40) ያህል ነው።

በአመት መካከል የሚገኝ ትርፍ ወደ መነሻው ጋር ተደምሮ አብሮ ይቆጠራል እንጂ ትርፉ ለብቻው አዲስ አመት አይቆጠርለትም። ልክ እንደዚሁ ከእንስሶች የሚወለዱ ልጆች መሰረታቸው የዘካ መነሻ ላይ ከደረሱ በዓመት መካከል የሚወለዱ ልጆቹም ዘካ መቁጠር ከተጀመረበት አመት ይጀመራሉ እንጂ አዲስ አመት አይጀመርላቸውም።

ዛሬ ላይ ሰዎች የሚገበያዩበት የወረቀት ገንዘብ ዲርሃምም ተባለ፣ ዲናርም ተባለ፣ ዶላርም ተባለ ወይም ከዛ ውጪ ስያሜ ቢሰጠው መጠኑ የብርን (የሲልቨርን) ወይም የወርቅን የዘካ መነሻ ደርሶት ዓመት ከዞረ የወርቅና የብር ተመሳሳይ ብይን አለው። ዘካ ማውጣትም ግዴታ ይሆንበታል።

የወርቅና የብር የሴት ጌጦች በተለይ የዘካ መነሻ መጠን ከደረሱና ለአመት ያህል በባለቤትነት ከዞሩ ለመጠቀሚያነት የተዘጋጁ ወይም ለሰው ያዋስነውም ቢሆን እንኳ በትክክለኛው የዑለሞች አቋም መሰረት እንደወርቅና ብር ሳንቲሞች ዘካ ይወጣባቸዋል። ይህም ነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በርሳቸው ላይ ይስፈንና) በተናገሩት በዚህ ሐዲሥ ጥቅል ሃሳብ ውስጥ ስለሚካተት ነው:

«مَا مِنْ صَاحِبِ ذَهَبٍ أَوْ فِضَّةٍ لَا يُؤَدِّي زَكَاتَهَا إِلَّا إِذَا كَانَ يَومُ القِيَامَةُ صُفِّحَتْ لَهُ صَفَائِحَ مِنْ نَارٍ».

"የወርቅና የብር ባለቤት ሆኖ ሐቃቸውን የማይወጣ ሰው የትንሳኤ ቀን ለርሱ የእሳት ዝርግ ተዘርግቶለት በርሷ በጀሃነም እሳት ውስጥ ሳይቃጠል የሚቀር የለም።" ቀደም ብሎ እስከተጠቀሰው የመጨረሻው ሐዲሥ ድረስ ያንብቡ!

እንዲሁም ነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በርሳቸው ላይ ይስፈንና) በአንድ ሴት እጅ ላይ የወርቅ አንባር ተመልክተው እንዲህ ማለታቸው ተረጋግጧል:

«أَتُعْطِينَ زَكَاةَ هَذَا؟»، قَالَتْ: لَا، قَالَ: «أَيَسُرُّكِ أَنْ يُسَوِّرَكِ اللَّهُ بِهِمَا يَوْمَ القِيَامَةِ سِوَارَيْنِ مِنْ نَارٍ!»، فَأَلْقَتْهُمَا، وَقَالَتْ: «هُمَا لِلَّهِ وَلِرَسُولِهِ».

"የዚህን ዘካ ትሰጪያለሽን?" እርሷም "አይ" አለች። እርሳቸውም "የትንሳኤ ቀን አላህ ሁለት የእሳት አንባር እንዲያለብስሽ ትፈልጊያለሽ እንዴ?" አሏት። እርሷም አውልቃ ጣለቻቸውና "እነዚህ አንባሮችን ለአላህና ለመልክተኛው ትቻቸዋለሁ።" አለች። አቡዳውድና ነሳኢይ ሐሰን በሆነ ሰነድ ዘግበውታል።

ከኡሙ ሰለማ (አላህ መልካም ስራዋን ይውደድላትና) እንደተላለፈው: እርሷ የወርቅ ጌጥ ትለብስ ነበርና "የአላህ መልክተኛ ሆይ! እርሱ (ቁርአን ውስጥ) ድልብ ተብሎ የተጠራው ነው?" በማለት ጠየቀቻቸው። እርሳቸውም:

«مَا بَلَغَ أَنْ يُزَكَّى فَزُكِّيَ فَلَيْسَ بِكَنْزٍ».

"ለዘካ የደረሰውን ዘካ ከወጣለት ቁርአን ውስጥ የተጠቀሰው ድልብ አይሆንም።" አሏት። ሌሎችም ይህንን ሃሳብ ያዘሉ ሐዲሶች ተደማምረው የወርቅና የብር ጌጦች ዘካ እንደሚወጣባቸው እንረዳለን።

የንግድ ሸቀጥን በተመለከተ የአመቱ መጨረሻ ላይ ተገምቶ ከተመኑ የአስራት ሩብ (የአንድ አስረኛ ሩብ ማለትም 1/40) ይወጣለታል። ይህም የሸቀጡ ተመን በመጣበት ዋጋ ቢሆንም ወይም ከመጣበት በላይ ቢሆንም ወይም ቢያንስ ዘካ የሚወጣው በእለቱ ተመን ነው። የዚህም ማስረጃ የሰሙራህ ሐዲሥ ነው። ሰሙራህ እንዲህ አለ:

«كَانَ رَسُولُ اللَّهِ يَأْمُرُنَا أَنْ نُخْرِجَ الصَّدَقَةَ مِنَ الَّذِي نُعِدُّهُ لِلْبَيْعِ».

"የአላህ መልክተኛ (የአላህ ሶላትና ሰላም በርሳቸው ላይ ይስፈንና) ለንግድ ያዘጋጀነውን ሸቀጥ ዘካ እንድናወጣለት ያዙን ነበር።" አቡዳውድ ዘግበውታል።

እዚህ ውስጥም ለንግድ የተዘጋጁ መሬቶች፣ ህንፃዎች፣ መኪናዎች፣ ትራክተሮችና ከነዚህም ውጪ ያሉ ለንግድ የተዘጋጁ የሸቀጥ አይነቶች ይካተታሉ።

ለንግድ ሳይሆን ለኪራይ የተዘጋጁ ህንፃዎች ዘካ ግዴታ የሚሆንባቸው የኪራይ ገንዘባቸው ዓመት ከሞላው ከኪራይ ገንዘቡ ነው። ህንፃውን ለብቻው ከተመለከትን ግን ለንግድ የተዘጋጀ ስላልሆነ ዘካ የለበትም። ልክ እንደዚሁ የግልና ተከራይቶ የሚነዳቸው መኪኖችም ባለቤቱ የገዛቸው ለመጠቀሚያነት ስለሆነ ለንግድ እስካልቀረቡ ድረስ ዘካ የለባቸውም።

የመኪናው ባለቤት የመኪና ኪራይ ወይም በሌላ መልኩ የዘካ መነሻ የሚደርስ ገንዘብ ከተጠራቀመለትና እጁ ላይ እያለ ዓመት ከሞላው ያዘጋጀው ለቀለብም ይሁን ወይም ለጋብቻውም ይሁን ወይም መሬት ለመግዛትም አዘጋጀው ወይም እዳ ለመክፈልም አዘጋጀው ወይም ከዛ ውጪ ላለ አላማ ቢያዘጋጀው ዘካ ማውጣት ይኖርበታል። ይህም በዚህ መሰል ለተገኙ ገንዘቦች ዘካ ማውጣት ግዴታ መሆኑን የሚጠቁሙ ጥቅል ሸሪዓዊ ማስረጃዎች ስላሉ ነው።

ቀደም ብለን በዘረዘርነው ማስረጃ መሰረት ትክክለኛው የዑለሞች አቋም እዳ ከዘካ እንደማያግድ ነው።

ልክ እንደዚሁ የየቲሞችና የእብዶች ገንዘብ ለዘካ መነሻ መጠን ከደረሰና አመት ከዞረ በብዙሃኑ ዑለሞች አቋም መሰረት ዘካ ማውጣት ግዴታ ይሆንባቸዋል። አመት ሲሞላ አስተዳዳሪዎቻቸው ለነርሱ ነይተው ማውጣት ግዴታ ይሆንባቸዋል። ይህም ጥቅል የሆኑ ሐዲሦች የሚጠቁሙት ሃሳብ ውስጥ ስለሚካተቱ ነው። ለምሳሌ በሙዓዝ (አላህ መልካም ስራውን ይውደድለትና) ሐዲሥ ነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በርሳቸው ላይ ይስፈንና) ወደ የመኖች በላኩት ጊዜ እንዲህ ማለታቸው:

«إِنَّ اللَّهَ افْتَرَضَ عَلَيْهِمْ صَدَقَةً فِي أَمْوَالِهِمْ تُؤْخَذُ مِنْ أَغْنِيَائِهِمْ وَتُرَدُّ فِي فُقَرَائِهِمْ».

"አላህ በነርሱ ላይ ከገንዘቦቻቸው መካከል ከሃብታሞቻቸው ተይዞ ለድሃዎቻቸው የሚሰጥ የምፅዋት ድርሻ ወስኖባቸዋል።"

ዘካ የአላህ ሐቅ ነው። ለማይገባው ሰው መስጠት አይፈቀድም። ዘካ ሰጪው መስጠቱን ለነፍሱ ጥቅም ማምጫ ወይም ጉዳት መከላከያ ወይም መስጠቱን ገንዘቡን መጠበቂያ ወይም ወቀሳን መከላከያ ማድረግ የለበትም። ይልቁንም ሙስሊም የሆነ ሰው ዘካ የሚቀበሉትን መርጦ ዘካ ስለሚገባቸው ብቻ ብሎ ለሚገባቸው ብቻ መስጠት ይገባዋል እንጂ ለሌላ ለምንም አላማ መስጠት የለበትም። ሲሰጥም ከጫንቃው ላይ ተጠያቂነት እንዲነሳለት እና ትልቅ ምንዳና ምትክ እንዲገባው ተደስቶና መስጠቱን ለአላህ አጥርቶ መሆን ይገባዋል።

ጥራት የተገባው አላህ በተከበረው መጽሐፉ ዘካ የሚገባቸውን አካላት ገልጿቸዋል። የላቀው አላህ እንዲህ አለ:

﴿إِنَّمَا ٱلصَّدَقَٰتُ لِلۡفُقَرَآءِ وَٱلۡمَسَٰكِينِ وَٱلۡعَٰمِلِينَ عَلَيۡهَا وَٱلۡمُؤَلَّفَةِ قُلُوبُهُمۡ وَفِي ٱلرِّقَابِ وَٱلۡغَٰرِمِينَ وَفِي سَبِيلِ ٱللَّهِ وَٱبۡنِ ٱلسَّبِيلِۖ فَرِيضَةٗ مِّنَ ٱللَّهِۗ وَٱللَّهُ عَلِيمٌ حَكِيمٞ 60

{ግዴታ ምጽዋቶች (የሚከፈሉት) ለድሆች፣ ለምስኪኖችም፣ በርሷም ላይ ለሚሠሩ ሠራተኞች፣ ልቦቻቸውም (በእስልምና) ለሚለማመዱት፣ ጫንቃዎችንም (በባርነት ተገዢዎችን) ነጻ በማውጣት፣ በባለ ዕዳዎችም፣ በአላህ መንገድም በሚሠሩ፣ በመንገደኛም ብቻ ነው፡፡ ከአላህ የተደነገገች ግዴታ ናት፡፡ አላህም ዐዋቂ ጥበበኛ ነው፡፡} [አት ተውባህ፡ 60]

ይህቺ የተከበረች አንቀፅ በእነዚህ ሁለት ስሞች መጠናቀቃቸው ጥራት የተገባው አላህ ለባሮቹ እርሱ የባሮቹን ሁኔታ አዋቂ እንደሆነ፣ ከባሮቹ ማን ዘካ እንደሚገባውና እንደማይገባው ለማስገንዘብ፤ በድንጋጌዎቹና በውሳኔዎቹ እርሱ ጥበበኛ እንደሆነና አንዳንድ ሰዎች ዘንድ የጥበቡ ምስጢር ቢሰወርባቸውም ነገሮች ተገቢው በሆነ ስፍራ ካልሆነ በቀር እንደማያኖረው ለማስገንዘብ ነው። ይህም ባሮች በህግጋቱ እንዲረጋጉና ለጥበቡ ታዛዥ እንዲሆኑ ነው።

አላህ እኛንም ሆነ ሙስሊሞችን እስልምናን መገንዘብን፣ ከርሱ ጋር ያለንን መስተጋብር እውነተኛ መሆንን፣ ወደ ሚያስደስተው ነገሮች መሽቀዳደምን፣ ቁጣውን ከሚያመጡ ነገሮች መጠበቅን እንዲገጥመን እንጠይቀዋለን።

የአላህ ሰላትና ሰላም ባሪያውና መልክተኛው በሆኑት በሙሐመድ እንዲሁም በቤተሰቦቻቸውና በባልደረቦቻቸው ላይ ይስፈን።

የእውቀታዊ ምርምር ተቋም ሊቀ መንበር

የፈታዋ፣ የደዕዋና የመምሪያም (ሊቀ መንበር) የሆኑት

የተከበሩ ሸይኽ ዐብዱልዐዚዝ ቢን ዐብደላህ ቢን ባዝ

 

***

 


ሁለተኛው መልዕክት

የረመዷን ፆምና ረመዳንን በሰላት የማሳለፍ ትሩፋቶችን እንዲሁም አንዳንድ ሰዎች ዘንድ ከሚሰወሩ የተወሰኑ አንገብጋቢ ህግጋቶችን ከማብራራት ጋር አዘጋጅቼዋለሁ።

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩህሩህ በጣም አዛኝ በሆነው እጀምራለሁ:

ከዐብዱልዐዚዝ ቢን ዐብደላህ ቢን ባዝ ይህንን መልዕክት ለሚያይ ሙስሊም ባጠቃላይ የተላለፈ መልዕክት: አላህ እኔንም እነርሱንም ወደ አማኞች መንገድ ያስገባን፤ እኔንም እነርሱንም ቁርአንና ሱናን ለመገንዘብ ይግጠመን! አሚን

የአላህ ሰላም እዝነትና በረከቱ በናንተ ላይ ይስፈን

ከዚህ በመቀጠል: ይህቺ ረመዷንን የመጾም፣ በሰላት የመቆምና ለእነዚህ መልካም ስራዎች የመሽቀዳደምን ትሩፋት እንዲሁም አንዳንድ ሰዎች ላያውቋቸው የሚችሉ የተወሰኑ ወሳኝ ህግጋቶችን ከማብራራት ጋር የተያያዘች አጠር ያለች ምክር ናት።

ከአላህ መልክተኛ (የአላህ ሶላትና ሰላም በርሳቸው ላይ ይስፈንና) እንደተረጋገጠው የረመዷን ወር መግባትን አስመልክተው ባልደረቦቻቸውን ያበስሩ ነበር። እንዲሁም (የአላህ ሶላትና ሰላም በርሳቸው ላይ ይስፈንና) የእዝነት በርና የጀነት በር የሚከፈትበት፣ የጀሃነም በሮች የሚዘጉበትና ሰይጣናት የሚጠፈነጉበት ወር መሆኑንም ይነግሯቸው ነበር። እንዲህ ይሉ ነበር:

«إِذَا كَانَتْ أَوَّلُ لَيْلَةٍ مِنْ رَمَضَانَ فُتِّحَتْ أَبْوَابُ الجَنَّةِ فَلَمْ يُغْلَقْ مِنْهَا بَابٌ، وَغُلِّقَتْ أَبْوَابُ جَهَنَّمَ فَلَمْ يُفْتَحْ مِنْهَا بَابٌ، وَصُفِّدَتِ الشَّيَاطِينُ، وَيُنَادِي مُنَادٍ: يَا بَاغِيَ الخَيْرِ أَقْبِلْ، وَيَا بَاغِيَ الشَّرِّ أَقْصِرْ، وَلِلَّهِ عُتَقَاءُ مِنَ النَّارِ، وَذَلِكَ كُلَّ لَيْلَةٍ».

"የረመዷን የመጀመሪያው ምሽት ሲሆን የጀነት በሮች ይከፈታሉ። ከጀነት በሮችም አንድም በር አይዘጋም። የጀሃነም በሮችም ይዘጋሉ። ከጀሃነም በሮች አንድም በር አይከፈትም። ሰይጣናትም ይታሰራሉ። አንድ ተጣሪም እንዲህ በማለት ይጣራል: አንተ መልካም ፈላጊ ሆይ! ወደ መልካም ዙር! አንተ መጥፎ ፈላጊ ሆይ! ተቆጠብ። አላህ ከእሳት ነፃ የሚያወጣቸው ባሮች አሉት። ይህም በየሁሉም ምሽት ነው።"

(የአላህ ሶላትና ሰላም በርሳቸው ላይ ይስፈንና) እንዲህም ብለዋል:

«جَاءَكُمْ شَهْرُ رَمَضَانَ شَهْرُ بَرَكَةٍ، يَغْشَاكُمُ اللَّهُ فِيهِ: فَيَنْزِلُ الرَّحْمَةَ، وَيَحُطُّ الخَطَايَا، وَيَسْتَجِيبُ الدُّعَاءَ، يَنْظُرُ اللَّهُ إِلَى تَنَافُسِكُمْ فِيهِ فَيُبَاهِي بِكُمْ مَلَائِكَتَهُ؛ فَأَرُوا اللَّهُ مِنْ أَنْفُسِكُمْ خَيْرًا؛ فَإِنَّ الشَّقِيَّ مَنْ حُرِمَ فِيهِ رَحْمَةَ اللَّهِ».

"የረመዷን ወር የበረከቱ ወር መጣላችሁ። አላህ በዚህ ወር በእዝነቱ ይሸፍናችኋል። እዝነቱን ያወርዳል። ወንጀሎችን ይምራል። ዱዓን ይቀበላል። በዚህ ወር አላህ እሽቅድድማችሁን ይመለከታል። በመላእክቶችም ፊት ያወድሳችኋል። ለአላህ የነፍሳችሁን መልካም ነገር አሳዩት። እድለቢስ ማለት የዚህን ወር የአላህ እዝነት የተነፈገ ነው።"

(የአላህ ሶላትና ሰላም በርሳቸው ላይ ይስፈንና) እንዲህም ብለዋል:

«مَنْ صَامَ رَمَضَانَ إِيمَانًا وَاحْتِسَابًا غُفِرَ لَهُ مَا تَقَدَّمَ مِنْ ذَنْبِهِ، وَمَنْ قَامَ رَمَضَانَ إِيمَانًا وَاحْتِسَابًا غُفِرَ لَهُ مَا تَقَدَّمَ مِنْ ذَنْبِهِ، وَمَنْ قَامَ لَيْلَةَ القَدْرِ إِيمَانًا وَاحْتِسَابًا غُفِرَ لَهُ مَا تَقَدَّمَ مِنْ ذَنْبِهِ».

"ረመዷንን አምኖበትና (ምንዳ እንደሚያገኝበት) አስቦ የጾመ ሰው ያለፈው ወንጀሉ ይማርለታል። ረመዷንን አምኖበትና (ምንዳ እንደሚያገኝበት) አስቦ (በሶላት) የቆመ ሰው ያለፈው ወንጀሉ ይማርለታል። ለይለቱል ቀደርን አምኖበትና (ምንዳ እንደሚያገኝበት) አስቦ (በሶላት) የቆመ ሰው ያለፈው ወንጀሉ ይማርለታል።"

(የአላህ ሶላትና ሰላም በርሳቸው ላይ ይስፈንና) እንዲህም ብለዋል:

«يَقُولُ اللَّهُ: كُلُّ عَمَلِ ابْنِ آدَمَ لَهُ الحَسَنَةُ بِعَشْرِ أَمْثَالِهَا إِلَى سَبْعِمِائَةِ ضِعْفٍ، إِلَّا الصِّيَامَ فَإِنَّهُ لِي وَأَنَا أَجْزِي بِهِ؛ تَرَكَ شَهْوَتَهُ وَطَعَامَهُ وَشَرَابَهُ مِنْ أَجْلِي، لِلصَّائِمِ فَرْحَتَانِ: فَرْحَةٌ عِنْدَ فِطْرِهِ، وَفَرْحَةٌ عِنْدَ لِقَاءِ رَبِّهِ، وَلَخُلُوفُ فَمِ الصَّائِمِ أَطْيَبُ عِنْدَ اللَّهِ مِنْ رِيحِ المِسْكِ».

"አላህ እንዲህ ብሏል: የአደም ልጅ ስራዎች ሁሉ ለርሱ ናቸው። ከጾም በቀር ባሉት መልካም እንደየስራዎቹ በአስር እስከ ሰባት መቶ እጥፍ እመነዳዋለሁ። ጾም ግን ለኔ ነው እኔው በርሱ እመነዳዋለሁ። በመጾሙ ስሜቱን፣ ምግቡንና መጠጡን ለኔ ብሎ ተወ። ለጾመኛ ሁለት ደስታዎች አሉት: (እነርሱም) ሲያፈጥር የሚደሰተውና ጌታውን ሲገናኝ የሚደሰተው ነው። የጾመኛ መጥፎ አፍ ጠረን አላህ ዘንድ ከሚስክ ሽታ የበለጠ ያውዳል።"

ረመዷን ላይ የመጾምና በሰላት የመቆምን ትሩፋት እንዲሁም በጥቅሉ መጾም የሚየስገኘውን ትሩፋት የሚጠቁሙ ሐዲሦች ብዙ ናቸው።

አንድ አማኝ የሆነ ሰው ለዚህ እድል መቻኮል ይገባዋል። እርሱም: አላህ የረመዷንን ወር እንዲያገኝ የዋለለትን ውለታን ነው። በዚህ ወር ወደ አምልኮ መቻኮል፣ ሀጢአቶችን መራቅ፣ አላህ ግዴታ ያደረገበትን ተግባራት በመፈፀም መታገል፣ በተለይ አምስቱን የግዴታ ሶላቶች በመስገድ ላይ መታገል ይገባዋል። ሶላት የእስልምና ምሰሶ ነው። ሶላት ከሁለቱ የምስክርነት ቃላቶች ቀጥሎ ትልቁ ግዴታ ነው። ሁሉም ሙስሊም ወንድም ሴትም ወቅቱን ጠብቆ፣ በመመሰጥና በመረጋጋት ሶላትን መስገድ ግዴታው ነው።

ወንዶችን በተመለከተ ካሉባቸው የሶላት ግዴታዎች መካከል አላህ በውስጧ ስሙ ከፍ እንዲልና እንዲወሳ ባዘዘው በአላህ ቤቶች ውስጥ በህብረት መስገድ አንዱ ግዴታ ነው።

﴿وَأَقِيمُواْ ٱلصَّلَوٰةَ وَءَاتُواْ ٱلزَّكَوٰةَ وَٱرۡكَعُواْ مَعَ ٱلرَّٰكِعِينَ 43

{ሶላትንም ደንቡን ጠብቃችሁ ስገዱ፡፡ ዘካንም (ግዴታ ምጽዋትን) ስጡ፡፡ (ለጌታችሁ) ከአጎንባሾች ጋርም አጎንብሱ፡፡}

[አልበቀራህ: 43]

አላህ እንዲህም ብሏል:

﴿حَٰفِظُواْ عَلَى ٱلصَّلَوَٰتِ وَٱلصَّلَوٰةِ ٱلۡوُسۡطَىٰ وَقُومُواْ لِلَّهِ قَٰنِتِينَ 238

{በሶላቶች (በተለይ) በመካከለኛይቱም ሶላት ላይ ተጠባበቁ፡፡ ታዛዦች ሆናችሁም ለአላህ ቁሙ፡፡}

[አልበቀራህ: 238]

እንዲህም ብሏል፦

﴿قَدۡ أَفۡلَحَ ٱلۡمُؤۡمِنُونَ 1 ٱلَّذِينَ هُمۡ فِي صَلَاتِهِمۡ خَٰشِعُونَ 2﴾

{ምእምናን ፍላጎታቸውን ሁሉ በእርግጥ አገኙ (ዳኑ)፡፡ 1

እነዚያ እነርሱ በስግደታቸው ውስጥ (አላህን) ፈሪዎች፡፡ 2}

[አል-ሙእሚኑን: 1 - 2]

እንዲህ እስከሚለው ድረስ

﴿وَالَّذِينَ هُمْ عَلَى صَلَوَتِهِمْ يُحَافِظُونَ 9 أَوَلَيْكَ هُمُ الْوَرِثُونَ 10 الَّذِينَ يَرِثُونَ الْفِرْدَوسَ هُمْ فِيهَا خَالِدُونَ 11

{እነዚያም እነርሱ በስግደቶቻቸው ላይ የሚጠባበቁ የሆኑት (አገኙ)። እነዚያ ወራሾቹ እነርሱ ናቸው። እነዚያ ፊርደውስን (ላእላይ ጀነትን) የሚወርሱ ናቸው። እነርሱ በእርሷ ውስጥ ዘውታሪዎች ናቸው።}

[አል-ሙእሚኑን: 9 - 11]

ነቢዩም (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) እንዲህ ብለዋል:-

«العَهْدُ الَّذِي بَيْنَنَا وَبَيْنَهُمُ الصَّلَاةُ، فَمَنْ تَرَكَهَا فَقَدْ كَفَرَ».

"በእኛና በነሱ መካከል ያለው ቃል ኪዳን ሰላት ነው። (በመሆኑም) ሰላትን የተወ ሰው በእርግጥ ክዷል።"

ከሶላት በመቀጠል ትልቁ ግዴታ ዘካን ማውጣት ነው። አላህ እንዲህ ብሏል:

﴿وَمَآ أُمِرُوٓاْ إِلَّا لِيَعۡبُدُواْ ٱللَّهَ مُخۡلِصِينَ لَهُ ٱلدِّينَ حُنَفَآءَ وَيُقِيمُواْ ٱلصَّلَوٰةَ وَيُؤۡتُواْ ٱلزَّكَوٰةَۚ وَذَٰلِكَ دِينُ ٱلۡقَيِّمَةِ 5

{አላህን ሃይማኖትን ለእርሱ ብቻ አጥሪዎች፣ ቀጥተኞች ኾነው ሊግገዙት፣ ሶላትንም አስተካክለው ሊሰግዱ ዘካንም ሊሰጡ እንጅ ያልታዘዙ ሲኾኑ (ተለያዩ)፡፡ ይህም የቀጥተኛይቱ (ሃይማኖት) ድንጋጌ ነው፡፡}

[አል-በይናህ፡ 5]

አላህ እንዲህ ብሏል:

﴿وَأَقِيمُوا الصَّلَوٰةَ وَءاتُوا الزَّكَوةَ وَأَطِيعُوا الرَّسُولَ لَعَلَّكُمْ تُرْحَمُونَ 56

{ሶላትንም አስተካክላችሁ ስገዱ። ዘካንም ስጡ። መልክተኛውንም ታዘዙ። ለእናንተ ይታዘንላችሁ ዘንድ።}

(አን ኑር 56)

ታላቁ የአላህ መጽሐፍና የተከበሩት መልክተኛ ሱና እንደሚጠቁሙት የገንዘቡን ዘካ ያላወጣ ሰው የትንሳኤ ቀን በርሱ ይቀጣል።

ከሶላትና ከዘካ ቀጥሎ ትልቁ ነገር ረመዷንን መጾም ነው። የረመዷን ወር ጾም በተከታዩ የነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ንግግር የተጠቀሰ ከአምስቱ የእስልምና መሰረቶች መካከል አንዱ ነው።

«بُنِيَ الإِسْلَامُ عَلَى خَمْسٍ: شَهَادَةِ أَنْ لَا إِلَهَ إِلَّا اللَّهُ وَأَنَّ مُحَمَّدًا رَسُولُ اللَّهِ، وَإِقَامِ الصَّلَاةِ، وَإِيتَاءِ الزَّكَاةِ، وَصَوْمِ رَمَضَانَ، وَحَجِّ البَيْتِ».

"እስልምና በአምስት ነገሮች ላይ ተገንብቷል፦ ከአላህ በስተቀር በእውነት የሚመለክ አምላክ አለመኖሩን እና ሙሐመድ የአላህ መልዕክተኛ መሆናቸውን መመስከር፣ ሶላትን ደንብና ሥርዓቱን ጠብቆ መስገድ፣ ዘካ መስጠት፣ የረመዳንን ወር መጾም እና ሐጅ ማድረግ (የአላህን ቤት መጎብኘት)።"

አንድ ሙስሊም የሆነ ሰው ጾሙንና ሶላቱን አላህ ክልክል ካደረጋቸው ቃላትም ይሁን ተግባራት መጠበቅ ግዴታው ነው። የመጾም ዋናው ግብ አላህን መታዘዝ፣ ክልከላውን አልቆ ማየት፣ ነፍስ አምላኳን ታዛ ስሜቷን እንድትፃረር በማድረግ ላይ መታገል፣ አላህ የከለከለውን ከመፈፀም በመታቀብ ላይ ነፍስ እንድትታገስ ማለማመድ ነው። የጾም አላማ ምግብ፣ መጠጥና ሌሎችን የሚያስፈጥሩ ነገሮችን መተው ብቻ አይደለም። ስለዚህም ሶሒሕ በሆነ ሐዲሥ ከአላህ መልክተኛ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) እንደተላለፈው እንዲህ ብለዋል:

«الصِّيَامُ جُنَّةٌ، فَإِذَا كَانَ يَوْمُ صَوْمِ أَحَدِكُمْ فَلَا يَرْفُثْ وَلَا يَصْخَبْ، فَإِنْ سَابَّهُ أَحَدٌ أَوْ قَاتَلَهُ فَلْيَقُلْ إِنِّي صَائِمٌ».

"ጾም ጋሻ ነው። አንዳችሁ የሚጾምበት ቀን የሆነ ጊዜ ውዳቂ ተግባርና ንግግር አይናገር። አይጩህም። ሰው ከተሰዳደበውም ወይም ከተጋደለው እኔ ጾመኛ ነኝ ይበል።"

(የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) እንዲህ ማለታቸውም በሶሒሕ ሐዲሥ ተላልፏል፦

«مَنْ لَمْ يَدَعْ قَوْلَ الزُّورِ وَالعَمَلَ بِهِ وَالجَهْلَ فَلَيْسَ لِلَّهِ حَاجَةٌ فِي أَنْ يَدَعَ طَعَامَهُ وَشَرَابَهُ».

"ውሸትን መናገርና በውሸትና በመሃይምነት መተግበርን ያልተወ ሰው ምግቡንና መጠጡን መተዉን አላህ ፈላጊ አይደለም።"

ከነዚህና ከሌሎችም ጥቅሶች የምንረዳው ጾመኛ የሆነ ሰው አላህ በርሱ ላይ እርም ያደረገበትን ነገሮች ሁሉ መራቅና አላህ በርሱ ላይ ግዴታ ያደረገበትን ነገሮች ሁሉ ተጠባብቆ መፈፀም ግዴታው እንደሆነ ነው። ይህንንም በማሟላቱ ምህረት ማግኘቱ፣ ከእሳት ነፃ መሆኑና ጾሙና ሶላቱ ተቀባይነት ማግኘቱ ተስፋ ይኖረዋል።

እዚህ ጋር ግን የተወሰኑ ሰዎች የማያስተውሏቸው አንዳንድ ነገሮችን መጥቀስ ይኖርብናል።

ከነርሱም መካከል: አንድ ሙስሊም ለይዩልኝ፣ ለይስሙልኝ፣ ሰዎችን ተከትሎ ወይም ቤተሰቡንና የሃገሪቱን ሰዎች ተከትሎ ሳይሆን መጾም ያለበት የግዴታ በአላህ አምኖና ምንዳውን ፈልጎ ነው መጾም ያለበት። ይልቅ የግዴታ እርሱን ለጾም ያነሳሳውም አላህ በርሱ ላይ ጾምን ግዴታ ማድረጉን ማመኑና በዛ ጾሙ ጌታው ዘንድ ምንዳን ማሰቡ መሆን አለበት። ልክ እንደዚሁ የረመዷንን ምሽት በሶላት ማሳለፍ አንድ ሙስሊም አምኖበትና ምንዳውን ፈልጎ እንጂ በሌላ ምክንያት መሆን የለበትም። ስለዚህም ነው የአላህ መልክተኛ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) እንዲህ ያሉት:

«مَنْ صَامَ رَمَضَانَ إِيمَانًا وَاحْتِسَابًا غُفِرَ لَهُ مَا تَقَدَّمَ مِنْ ذَنْبِهِ، وَمَنْ قَامَ رَمَضَانَ إِيمَانًا وَاحْتِسَابًا غُفِرَ لَهُ مَا تَقَدَّمَ مِنْ ذَنْبِهِ، وَمَنْ قَامَ لَيْلَةَ القَدْرِ إِيمَانًا وَاحْتِسَابًا غُفِرَ لَهُ مَا تَقَدَّمَ مِنْ ذَنْبِهِ».

"ረመዷንን አምኖበትና (ምንዳ እንደሚያገኝበት) አስቦ የጾመ ሰው ያለፈው ወንጀሉ ይማርለታል። ረመዷንን አምኖበትና (ምንዳ እንደሚያገኝበት) አስቦ (በሶላት) የቆመ ሰው ያለፈው ወንጀሉ ይማርለታል። ለይለቱል ቀደርን አምኖበትና (ምንዳ እንደሚያገኝበት) አስቦ (በሶላት) የቆመ ሰው ያለፈው ወንጀሉ ይማርለታል።"

አንዳንድ ሰዎች ዘንድ ብያኔያቸው ከሚሰወሩ ነገሮች መካከል: ጾመኛ ሆኖ ያለምርጫው ቁስለት ወይም ነስር ቢያጋጥመው ወይም ትውከት ቢያመልጠው ወይም ውሃ ወደ ጉሮሮው ሾልኮ ቢገባ ወይም የቤንዚን ሽታ ጉሮሮው ጋር ቢሰማው እነዚህ ሁሉ ነገሮች ጾሙን አያበላሹም። ነገር ግን ሆን ብሎ ቢያስታውክ ነቢዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) እንዲህ ስላሉ ጾሙ ይበላሻል:

«مَنْ ذَرَعَهُ القَيْءُ فَلَا قَضَاءَ عَلَيْهِ، وَمَنِ اسْتَقَاءَ فَعَلَيْهِ القَضَاءُ».

"ትውከት ያሸነፈው ሰው ቀዷ የለበትም። ሆን ብሎ ያስታወከ ቀዷ አለበት።"

ሌላው አንዳንድ ሰዎች ላይ ከሚሰወሩ ብይኖች መካከል: ጾመኛው የጀናባን ትጥበት ፀሃይ እስክትወጣ ድረስ ማዘግየቱ፣ አንዳንድ ሴቶችም ከወር አበባ ከፈጅር በፊት ይፀዱና የወር አበባ ወይም የወሊድ ደም ትጥበታቸውን ግን ፀሃይ እስኪወጣ ድረስ ማዘግየታቸው ነው። ትጥበታቸውን ፈጅር እስኪወጣ ድረስ ማዘግየታቸው ከመጾም አይከለክልም። ስለዚህ መጾም ግዴታቸው ነው። ነገር ግን ትጥበቷን ፀሃይ እስክትወጣ ድረስ ማዘግየት አይፈቀድላትም። ይልቁንም ፀሃይ ከመውጣቷ በፊት ታጥባ ፈጅር የመስገድ ግዴታ አለባት።

ልክ እንደዚሁ ጀናባ ላይ የሆነውም ትጥበቱን ፀሃይ ከወጣ በኋላ ለመፈፀም ማዘግየት የለበትም። ይልቁንም ፀሃይ ከመውጣቱ በፊት ታጥቦ ፈጅር የመስገድ ግዴታ አለበት። በተለይ ወንድ ልጅ የፈጅር ሶላትን በጀመዓ ለመድረስ በፍጥነት የመታጠብ ግዴታ አለበት።

ጾምን ከማያበላሹ ነገሮች መካከል: የደም ምርመራ ማድረግና ለግሉኮስነት የማያገለግሉ መርፌዎችን መወጋት ነው። ነገር ግን ከተቻለ በላጩና ለጥንቃቄ ያህል ተመራጩ ይህንን እስከ ምሽት ድረስ ማዘግየት ነው። ይህም ነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) እንዲህ ስላሉ ነው:

«دَعْ مَا يَرِيبُكَ إِلَى مَا لَا يَرِيبُكَ».

"የሚያጠራጥርህን ትተህ ወደማያጠራጥርህ አድርግ።"

(የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) እንዲህ ማለታቸውም:

«مَنِ اتَّقَى الشُّبُهَاتِ فَقَدِ اسْتَبْرَأَ لِدِينِهِ وَعِرْضِهِ».

"አሻሚ የሆኑ (የሚያምታቱ) ነገሮችን የተጠነቀቀ ሰው በርግጥም ሃይማኖቱንና ክብሩን ጠብቋል።"

አንዳንድ ሰዎች ዘንድ ብያኔያቸው ከሚሰወሩ ነገሮች መካከል: ሶላቱ ግዴታም ሆነ ሱና ሶላት ውስጥ አለመረጋጋት ነው። ከአላህ መልክተኛ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) የተዘገቡ ሶሒሕ ሐዲሦች ሶላት ውስጥ መረጋጋት ከሶላት ማዕዘናቶች መካከል አንዱ እንደሆነና ባለመረጋጋት የተሰገደ ሶላትም ሶላት እንደማይባል ይጠቁማሉ። መረጋጋት ማለት ሶላት ውስጥ መርጋት፣ ሶላት ውስጥ መመሰጥና ሁሉም መገጣጠሚያ አጥንት ወደቦታው እስኪመለስ ድረስ አለመቸኮል ማለት ነው። ብዙ ሰዎች በረመዷን ወር የተራዊሕን ሶላት ሳያገናዝቧትና ሳይረጋጉ ይልቁንም ጠቅ ጠቅ እያደረጉ በፍጥነት ይሰግዷታል። ይህ አሰጋገድ የተበላሸ በሆነ መንገድ የተሰገደ ነው። ሰጋጁም እንኳን ሊመነዳበት ወንጀለኛ ያደርገዋል።

አንዳንድ ሰዎች ዘንድ ብያኔያቸው ከሚሰወሩ ነገሮች መካከል: አንዳንድ ሰዎች የተራዊሕን ሶላት ከሀያ ረከዓ ማሳነስ አይፈቀድም ብለው ማሰባቸው፤ አንዳንዶች ደግሞ ከአስራ አንድ ወይም ከአስራ ሶስት ረከዓ መጨመር አይፈቀድም ብለው ማሰባቸው ነው። ይህ ሁሉ እሳቤ ያለአግባብ የመጣ እሳቤ ነው። እንደውም ማስረጃዎችን የሚፃረር ስህተት የሆነ እሳቤ ነው።

ከአላህ መልክተኛ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) የተዘገቡ ሶሒሕ ሐዲሦች የምሽት ሶላት ሰፊ አማራጭ ያለው መሆኑንና መፃረር በማይቻል መልኩ የተገደበ ገደብ እንደሌለው ይጠቁማሉ። እንደውም ከነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) እንደተረጋገጠው በረመዷንም ሆነ በሌላ ጊዜ የምሽት ሶላትን አስራ አንድ ረከዓ አንዳንዴ አስራ ሶስት ረከዓ አንዳንዴ ከዛ በታችም ይሰግዱ ነበር። ስለምሽት ሶላት በተጠየቁ ጊዜም መልሳቸው አንዲህ ነበር:

«مَثْنَى مَثْنَى، فَإِذَا خَشِيَ أَحَدُكُمُ الصُّبْحَ صَلَّى رَكْعَةً وَاحِدَةً تُوتِرُ لَهُ مَا قَدْ صَلَّى».

"ሁለት ሁለት እያደረጋችሁ ስገዱ። አንዳችሁ ንጋት (ሱብሒ) ይወጣብኛል ብሎ ከሰጋ አንድ ረከዓ ይስገድ። ከዛ በፊት የሰገደውን ዊትር ታደርግለታለች።"

ሶሒሕ በመሆኑ ላይ ተስማምተውበታል።

በረመዷንም ሆነ ከዛ ውጪ በቁጥር የተገደቡ ረከዓዎችን አላስቀመጡም። ለዛም ሶሓቦች በዑመር (አላህ መልካም ስራውን ይውደድለትና) ዘመን የሆነ ጊዜ ላይ ሀያ ሶስት ረከዓ ሰግደዋል። የሆነ ጊዜ ላይ ደሞ ሀያ አንድ ረከዓ ሰግደዋል። ይህ ሁሉ ከዑመር (አላህ መልካም ስራውን ይውደድለትና) እና በርሱ ዘመን ከነበሩ ሶሓቦች ተረጋግጦ እናገኘዋለን።

አንዳንድ ሰለፎችም በረመዷን ሰላሳ ስድስት ረከዓ ይሰግዱ እና በሶስት ረከዓ ዊትር ይጨርሱ ነበር። አንዳንዶቹ ደግሞ አርባ አንድ ረከዓ ይሰግዱ ነበር። ይህን ሁሉ ሸይኹል ኢስላም ኢብኑ ተይሚያ እና ሌሎችም ምሁራኖች አላህ ይዘንላቸውና ጠቅሰውታል። ይህ የተራዊሕ ረከዓ ቁጥር ጉዳይ ሰፊ አማራጭ ያለው እንደሆነም ጠቅሰዋል። በተጨማሪም ቂርአቱን፣ ሩኩዑንና ሱጁዱን የሚያረዝም ሰው የረከዓውን ቁጥር ማሳነሱ በላጭ እንደሆነና ቂረአቱን፣ ሩኩዑንና ሱጁዱን ያሳነሰ ሰው ደግሞ የረከዓውን ቁጥር መጨመሩ በላጭ እንደሆነ ጠቅሰዋል። የሸይኹል ኢስላም አላህ ይዘንላቸውና የንግግራቸው ጭብጥ ይህ ነው።

የነቢዩን (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ሱና ያስተነተነ ሰው በረመዷንም ሆነ ከረመዷን ውጪ ከነዚህ ሁሉ የረከዓ መጠን ለመስገድ በላጩ አስራ አንድ ረከዓ ወይም አስራ ሶስት ረከዓ መስገድ እንደሆነ ይረዳል። ይህም ነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) በአብዛኛው የህይወታቸው ዘመን ከሰገዱት የረከዓ ቁጥር ጋር ስለሚገጥም፤ ሰጋጆችን ታሳቢ ያደረገ ለመመሰጥና ለመረጋጋትም የቀረበ ስለሆነ ነው። ጨምሮ የሰገደ ሰው ግን ምንም የሚጠላም ሆነ ችግር ያለው ነገር አልፈፀመም።

በረመዷን ወር ከኢማሙ ጋር የሰገደ ሰው ከኢማሙ ጋር አብሮ ካልሆነ በቀር ባያጠናቅቅ የተሻለ ነው። ይህም ነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) እንዲህ ስላሉ ነው:

«إِنَّ الرَّجُلَ إِذَا قَامَ مَعَ الإِمَامِ حَتَّى يَنْصَرِفَ كُتِبَ لَهُ قِيَامُ لَيْلَةٍ».

"ሰውዬው ኢማሙ እስኪያጠናቅቅ ድረስ ከኢማሙ ጋር አብሮ ለምሽት ሶላት ከቆመ አላህ ለርሱ ምሽቱን ሙሉ እንደቆመ ይፅፍለታል።"

ሙስሊሞች ባጠቃላይ በዚህ በተከበረ ወር የተለያዩ አምልኮዎች ላይ ትግል ማድረጋቸው የተደነገገ ተግባር ነው። በሱና ሶላቶች፣ ቁርአንን በማስተንተንና በመገንዘብ በመቅራት፣ ተስቢሕ፣ ተህሊል፣ ተሕሚድ፣ ተክቢር፣ እስቲግፋርና ሸሪዓዊ የሆኑ ዱዓዎችን በማብዛት፣ በመልካም በማዘዝ፣ ከመጥፎ በመከልከል፣ ወደ አላህ በመጣራት፣ ሚስኪኖችንና ድሃዎችን በመርዳት፣ ወላጆችን በመንከባከብ፣ ዝምድናን በመቀጠል፣ ጎረቤትን በማክበር፣ በሽተኛን በመጠየቅና በሌሎችም የመልካም ተግባር አይነቶች በመታገል ማሳለፍ ይገባዋል። ይህም ነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ቀደም ብለን በጠቀስነው ሐዲሥ እንዲህ ስላሉ ነው:

«يَنْظُرُ اللَّهُ إِلَى تَنَافُسِكُمْ فِيهِ فَيُبَاهِي بِكُمْ مَلَائِكَتَهُ؛ فَأَرُوا اللَّهُ مِنْ أَنْفُسِكُمْ خَيْرًا؛ فَإِنَّ الشَّقِيَّ مَنْ حُرِمَ فِيهِ رَحْمَةَ اللَّهِ».

"በዚህ ወር አላህ ወደ እሽቅድድማችሁ ይመለከታል። እናንተንም መላእክቶች ፊት ያወድሳችኋል። ለአላህ የነፍሳችሁን መልካምነት (በይፋ) አሳዩት። እድለቢስ ማለት የዚህን ወር የአላህ እዝነት የተነፈገ ነው።"

እንዲሁም ከነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) እንዲህ ማለታቸውም ተዘግቧል:

«مَنْ تَقَرَّبَ فِيهِ بِخَصْلَةٍ مِنْ خِصَالِ الْخَيْرِ كَانَ كَمَنْ أَدَّى فَرِيضَةً فِيمَا سِوَاهُ، وَمَنْ أَدَّى فِيهِ فَرِيضَةً كَانَ كَمَنْ أَدَّى سَبْعِينَ فَرِيضَةً فِيمَا سِوَاهُ».

"በዚህ ወር በአንዳች መልካም ነገር ወደ አላህ የተቃረበ ሰው ከዚህ ወር ውጪ ግዴታ እንደፈፀመ (አይነት ምንዳ) ይመነዳል። በዚህ ወር አንድ ግዴታን የፈፀመ ሰው ከዚህ ወር ውጪ ሰባ ግዴታዎችን እንደፈፀመ (አይነት ምንዳ) ይመነዳል።"

እንዲሁም ሶሒሕ በሆነ ሐዲሥ ነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) እንዲህ ብለዋል:

«عُمْرَةٌ فِي رَمَضَانَ تَعْدِلُ حَجَّةً، أَوْ قَالَ: حَجَّةً مَعِي».

"በረመዷን ወር የምትደረግ ዑምራ ከሐጅ ጋር ትስተካከላለች። ወይም ከኔ ጋር አብሮ ሐጅ ከማድረግ ጋር ትስተካከላለች።"

በዚህ በተከበረ ወር በመልካም ስራ አይነቶች መሽቀዳደምና መወዳደር የተደነገገ መሆኑን የሚጠቁሙ ሐዲሦችና የሶሓቦች ንግግር በርካታ ናቸው።

አላህን እኛንም ሆነ መላ ሙስሊሞችን ውዴታው ለሚገኝበት ነገር እንዲገጥመን፣ ጾማችንንና ሶላታችንን እንዲቀበለን፣ ሁኔታችንን እንዲያስተካክልልን፣ ሁላችንንም ከአጥማሚ ፈተናዎች እንዲጠብቀን እንጠይቀዋለን። ልክ እንደዚሁ ጥራት የተገባውን አላህ የሙስሊሞችን መሪዎች እንዲያስተካክል፣ ቃላቸውን በእውነት ላይ የተሰባሰበ እንዲያደርግልን እንጠይቀዋለን። እርሱ ለዚህ ባለቤትም ቻይም ነውና።

ወስሰላሙ ዐለይኩም ወረሕመቱሏሂ ወበረካቱህ (የአላህ ሰላም፣ እዝነትና በረከት በናንተ ላይ ይሁን)

 

***

ማውጫ

 

የመጀመሪያው መልዕክት: 2

ዘካን የተመለከተ አንገብጋቢ ጥናት: 2

ሁለተኛው መልዕክት 15

የረመዷን ፆምና ረመዳንን በሰላት የማሳለፍ ትሩፋቶችን እንዲሁም አንዳንድ ሰዎች ዘንድ ከሚሰወሩ የተወሰኑ አንገብጋቢ ህግጋቶችን ከማብራራት ጋር አዘጋጅቼዋለሁ። 15

 

 

***